ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

Monday, May 16, 2016

=>+*"+<+>+ግንቦት 9+<+>+"*+

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
አሜን
#ግንቦት 9
#የታላቁ_ጻድቅ_ንጉሥ_የቆ ስጠንጢኖስ_እናት
#የከበረች_ንግሥት_እሌኒ_ ዐረፈች፡፡ ጌታችን የተሰቀለበት
መስቀል ሙት እያስነሳ ድውይ እየፈወሰ አጋንንት እያወጣ
የተለያዩ ገቢረ ተአምራት ሲሰራ ክፉዎች አይሁዶች አይተው
ሕዝቡ ክርስቲያን እንዳይሆኑ በመፍራት በ34 ዓ.ም
ከኢየሩሳሌም ወጣ ብሎ በሚገኝ ቦታ ቆፍረው ቀበሩት፡፡
ከዚያም የከተማውን ቆሻሻ ሁሉ ከዚያ መስቀሉ በተቀበረበት
ቦታ ላይ እየደፉ ከዘመን ብዛት ቦታው በቆሻሻ ክምር የተነሣ
ተራራ ሆነ፡፡ እስራኤልን ከሮም ቅኝ አገዛዝ ነጻ ለማውጣት
ከ66-70 ዓ.ም ባደረጉት እንቅስቃሴ ጥጦስ የተባለው የሮም
ንጉሠ ነገሥት ዘምቶ ኢየሩሳሌምን በ70 ዓ.ም ደመሰሳት፡፡
ትልቁን የአይሁድ ቤተመቅደስንም አቃጠለው፡፡
እስራኤላውያንም በመላው ዓለም ተበተኑ፡፡ ከዘመነ ሐዋርያት
ጀምሮ በተከታታይ በሮም የነገሡ ነገሥታት /ቄሳሮች/
በክርስቲያኖች ላይ የማያባራ መከራ አድርሰዋል፡፡ ክርስቲያኖች
የተቀበረውን መስቀል አስፈልገው ለማውጣት ቀርቶ
ሃይማኖታቸውን የማመን ነጻነት ስላልነበራቸው ቅዱስ
መስቀል ለ300 ዓመታት ያህል ተቀብሮ የጉድፍ መጣያ ሆኖ
ቆየ፡፡ የመስቀሉ የመገኘት ታሪክ የቤተክርስቲያን የመከራ
ዘመን አልፎ የዕረፍትና የሰላም ዘመን ሲመጣ ለብዙ ዘመን
ተቀብሮ የተረሳውን መስቀል ባለቤቱ መድኃኔዓለም
አልረሳምና እርሱ የፈቀዳት ዕለት ስትደርስ በዕሌኒ ንግሥት
አማካኝነት ከተቀበረበት እንዲወጣ አደረገ፡፡
ዕሌኒና ተርቢኖስ የሚባሉ ሁለት ደጋግ ክርስቲያኖች ተጋብተው
ይኖሩ ነበር፡፡ ተርቢኖስና ዕሌኒ ኑሮአቸው ፍቅርና ሰላም
የሰፈነበት በመሆኑ ለብዙ ሰዎች እንደ ምሳሌ ሆነው ይኖሩ
ነበር፡፡ ተርቢኖስ ነጋዴ ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ራቅ ወዳለ
ሀገር በመርከብ ለንግድ ሄደ፡፡ ዕሌኒም ባለቤቷ ተርቢኖስ
ለንግድ ወጥቶ እስኪመለስ ስለባሏ ከመጸለይና ከማሰብ በቀር
ከግቢዋ አትወጣም ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ተርቢኖስ ለንግድ ሄዶ
ብዙ ዓመታትን ቆይቶ ከጓደኞቹ ጋር ወደሀገሩ ሲመለስ
ከነጋዴዎች አንዱ "በእግዚአብሔር ፈቃድ ከሽፍታና ከማዕበል
ከልዩ ልዩ አደጋ ተርፈን በሰላም ተመልሰን ሚስቶቻችን ሌላ
ሳይወዱ ሳይለምዱ እናገኛቸው ይሆን?" ብሎ ጠየቀ፡፡ ተርቢኖስ
ግን "እንኳን በሰላም አደረሰን እንጂ ሚስቴን በዚህ
አልጠረጥራትም" ብሎ ሲመልስ ሌላው ጓደኛው "ያንተ ሚስት
ከማን ትበልጣለችና ነው አሁን ሄጄ ከሚስትህ ጋር ለምዳኝ
ወዳኝ ወድጃት ብመጣስ ምን ትቀጣለህ?" አለው፡፡
ተርቢኖስም በሚስቱ ዕሌኒ ተማምኖ "ይህንን ብታደርግ ይህን
ያህል ዓመት የለፋሁበት ሀብት ከነትርፉ ውሰድ አንተም
ብታደርግ እንዲሁ ሀብትህ ከነትርፉ ለእኔ ይሁን" ተባብለው
ተወራረዱ፡፡
ከዚያም መርከቡ ወደብ ከመድረሱ በፊት ነጋዴው ወደ ዕሌኒ
ቤት ደረሰና በሩን አንኳኩቶ ሠራተኛይቱን "ዕሌኒን ማነጋገር
እፈልጋለሁና ንገሪልኝ" ብሎ ጠየቃት፡፡ እርሷም እያፈረች
የተላከችውን ለዕሌኒ ነገረቻት፡፡ ዕሌኒም ተቆጥታ "ከመች
ወዲህ ነው እንግዳ የማነጋግረው?" ብላ አሳፈረቻት፡፡
ሠራተኛይቱም ለነጋዴው መልሱን ስትነግረው ነጋዴው
እንደማይሆንለት ከተረዳ በኋላ ሌላ ተንኮል አቀደና
ለሠራተኛይቱ "ባልና ሚስቱ ብቻ የሚያውቁትን አንድ ነገር ብቻ
ብትሰጪኝ ብዙ ገንዘብና ወርቅ እሰጥሻለሁ" ብሎ ወርቅ
ሰጣት፡፡ ሠራተኛይቱም "ሁለቱ ብቻ የሚያውቁት የእመቤቴ
ሀብል አለ ያንን እመጣልሀለሁ መጀመርያ አንተ በከተማው
ውስጥ እየዞርህ ነጋዴዎችን መጡ የብስ ረገጡ እያልክ አስወራ
ከዚያም ተመልሰህ እንድትመጣ" ብላ ሰደደችው፡፡ ነጋዴውም
እንደተመከረው የነጋዴዎቹን መምጣት በከተማይቱ እንዳወራ
የነጋዴዎቹ ቤተሰቦች ነጋዴዎችን ለመቀበል ዝግጅት ማድረግ
ጀመሩ፡፡ የዕሌኒም ሠራተኛ "እመቤቴ ነጋዴዎች መጡ ተብሎ
ይወራልና፡፡ ባለቤትዎ በሰላም ስለመጡ ይዘገጃጁ ገላዎን
ይታጠቡ" ብላ መከረቻት፡፡ ዕሌኒም ገላዋን ስትታጠብ ያንገቷን
ሐብል ቁጭ ካደረገችበት ቦታ ሠራተኛይቱ አንስታ ለነጋዴው
በተቃጠሩበት ዕለት ሰጠችው፡፡ ነጋዴውም ለሠራተኛይቱ
የውለታዋን ብዙ ገንዘብና ወርቅ ሰጥቶአት ደስ እያለው ወደ
ጓደኞቹ ሄደ፡፡ ለተርቢኖስ "ሚስትህን ለምጃት ወድጃት
መጣሁ" አለው፡፡ ተርቢኖስም "ውሸት ነው ለዚህ ምን ምልክት
አለህ?" ብሎ ጠየቀው፡፡ ተንኮለኛውም ነጋዴ ያንን ሐብል
አውጥቶ "ይህ ሀብል የሚስትህ አይደለምን?" ብሎ ሰጠው፡፡
ተርቢኖስም ደነገጠ የሚናገረውን አጣ፡፡ በውርርዱም መሠረት
ሀብቱን ሁሉ አስረከበና ባዶ እጁን ወደቤቱ እያዘነ እየተቆጨ
ሔደ፡፡
ባለቤቷን በናፍቆትና በታማኝነት ስትጠብቅ የከረመችው ዕሌኒ
በተርቢኖስ ያልተለመደ ሀዘንና ብስጭት ግራ ተጋብታ
"ወንድሜ ምን ሆነሀል? ለወትሮው እንኳን ይህን ያህል ዘመን
ተለያይተን ቀርቶ ለጥቂት ቀናት ተለያይተን እንኳ ለጥቂት
ቀናት ተለያይተን ስንገናኝ እንነፋፈቃለን፡፡ አሁን ግን
ከመጣህበት ጊዜ ጀምሮ አዝነህ አይሃለሁ" ብላ ጠየቀችው፡፡
ተርቢኖስም "ብዙ የደከምኩበትና የለፋሁበት ሀብት ንብረቴ
እንዳለ ማዕበል አጠፋብኝ እኔ ያላዘንኩ ማን ይዘን?" አላት፡፡
ዕሌኒም የተማረች ናትና "እግዚአብሔር ሰጠ እግዚአብሔር ነሣ
የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን እንዳለ ኢዮብን
አስበው፡፡ አንተ እንኳን በሰላም መጣህ እንጂ ሀብቱ ውሎ
አድሮ ይመጣል..." እያለች አጽናናችው፡፡ ተርቢኖስም "እንግዲህ
በተከበርኩበት ሀገር ተዋርጄ፣ በሰጠሁበት ሀገር ለምኜ ለመኖር
አልችልምና ወደሌላ ወደማያውቁኝ ሀገር እሔዳለሁ አንቺ ግን
ሁሉ ይወድሻል ያከብርሻል ከወደድሸው ጋር ኑሪ" አላት፡፡
ዕሌኒም "በደስታ ጊዜ አብሬህ እንደሆንኩ በችግርም ጊዜ
ልለይህም የእኔንና ያንተን አንድነት ችግር አይፈታውም ከአንተ
ተለይቼ ወዴት እቀራለሁ ወደምትሄድበት አብሬህ እሄዳለሁ"
ብላ ተነሳች፡፡ ሁለቱም ቤታቸውን ጥለው ሲሄዱ በመንገድ ላይ
ተርቢኖስ በልቡናው ይዞት የነበረውን ምሥጢር አወጣው
"ዕሌኒ ስወድሽ የጠላሽኝ ሳምንሽ የከዳሽኝ ምን አድርጌሽ
ነው?" ብሎ ጠየቃት፡፡ ዕሌኒም "እኔ አንተን አልጠላሁም
አልከዳሁምም ይህንን ሐሳብ እንዴት አሰብህ?" ብትለው ከኪሱ
አውጥቶ ሀብሉን አሳያትና የሆነውን ሁሉ ነገራት፡፡ ዕሌኒም
ያልጠበቀችው ነገር ስለተፈጸመ አዝና የሆነውን እውነተኛ ታሪክ
በሙሉ ነገረችው፡፡ ተርቢኖስ ግን አላመናትም፡፡ ከባህር ዳር
በደረሱ ጊዜ በቁመቷ ልክ ሣጥን አሠርቶ ዕሌኒን በውስጡ
አስገባትና "ብታደርጊውም ባታደርጊውም እንደሥራሽ ሥራሽ
ያውጣሽ" ብሎ ወደ ባሕሩ ወረወራት፡፡
ዕሌኒ ያለችበት ሣጥን በፈቃደ እግዚአብሔር እየተንሳፈፈ
ከወደብ ደረሰ፡፡ በዚያ ወደብ አካባቢ ምዕራብ ሮምን ያስተዳደር
የነበረው ኮስታንዲዮስ (ቁንስጣ) የተባለው ንጉሥ ነበርና
ሣጥኑን አይቶ አውጥቶ እንዲከፍቱት ወታደሮችን አዘዘ፡፡
ሣጥኑን አውጥተውም ሲከፍቱት እጅግ የተዋበች ሴት ሆና
አገኟት፡፡ ንጉሡም ዕሌኒን ወስዶ ሚስቱ አደረጋት፡፡
ኮስታንዲዮስ (ቁንስጣ) የመክስምያኖስ ቄሳር ሆኖ ምዕራብ
ሮምን ያስተዳደር ነበር፡፡ ንግስት ዕሌኒም በ272 ዓ.ም ታላቁ
ቆስጠንጢኖስን ወለደችለት ቆስጠንጢኖስም ገና በወጣትነቱ
የአባቱ እንደራሴ ሆኖ እንደሠራ አባቱ ሞተ፡፡ የአባቱ
ባለሟሎችና ሕዝቡ ተስማምተው የ18 ዓመቱን
ቆስጠንጢኖስን በአባቱ ቦታ ሐምሌ 25 ቀን 316 ዓ.ም
በሮም ምዕራብ ክፍል በገላትያ አነገሡት፡፡ በጦር ሜዳዎች
ብዙ የጀግንነት ሥራዎች ስለሠራ በሠራዊቱ ዘንድ ይወደድ
ነበር፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴን ወላጅ እናቱ በፈርዖን ቤት
ሃይማኖቱን ባሕሉን ታሪኩን በሚገባ እያስተማረች
እንዳሳደገችው ሁሉ ንግሥት ዕሌኒም ልጇን ቆስጠንጢኖስን
ከልጅነቱ ጀምሮ ስለክርስትና ሃይማኖትና ስለክርስቲያኖች
መከራ ታስተምረው ስለነበር በክርስቲያኖች ላይ የነበረው
አመለካከት በሮም ከነገሡት ቄሣሮች ሁሉ የተሻለ ነበር፡፡
በተለይም በ312 ዓ.ም ከጠላቱ ከመክስምያኖስ ጋር ለመዋጋት
"ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት" ብሎ ለዘመቻ እንደተሰለፈ
በራእይ በሰማይ ላይ "በዚህ መስቀል (ምልክት) ጠላትህን ድል
ታደርጋለህ" የሚል የመስቀል ቅርጽና የተጻፈ ጽሑፍ ስላየ
ለሠራዊቱ የመስቀል ምልክት በመሳሪያቸውና በሰንደቅ
ዓላማው ላይ እንዲያደርጉ አዘዘ፡፡ ወደያው ጦርነት ቢገጥም
ጠላቱን ድል ነሥቶ በጠቅላላው የሮም መንግሥት ግዛቶች ሁሉ
ገዥ ሆነ፡፡
ታላቁ ቆስጠንጢኖስ የሮም ንጉሠ ነገሥት ከሆነ በኋላ በ300
ዓመታት ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ ለክርስቲያኖች የነጻነት ዐዋጅ
ዐወጀ፡፡ ክርስትናም ብሔራዊ ሃይማኖት ተባለች፡፡ ንግሥት
እሌኒም በተፈጠረላት አመች ሁኔታ በመጠቀም የጌታችን
መስቀል ከተቀበረበት ለማውጣት በ327 ዓ.ም
ወደኢየሩሳሌም ሔደች፡፡ ዕሌኒ ልጅዋ ቆስጠንጢኖስ
ክርስቲያን ከሆነላት ወደ ኢየሩሳሌም ሔዳ መስቀሉን
ለመፈለግ እንዲሁም በኢየሩሳሌም ያሉ ቅዱሳት መካናትንና
አብያተ ክርስቲያናትን ለማሳነጽ ለእግዚአብሔር ተሳለች፡፡ ከዚህ
በኋላ ቆስጠንጢኖስ አምኖ በ337 ዓ.ም ተጠመቀ፡፡ ቅድስት
ዕሌኒም ወደ ኢየሩሳሌም ሔደች፡፡ ከእርሷም ጋር ብዙ
ሠራዊት ነበር፡፡ እንደደረሰችም ስለ ቅዱስ መስቀል
መረመረች፡፡ ነገር ግን ቦታውን የሚያስረዳት አላገኘችም፡፡
የአይሁድ ወገን እንቢ ቢሉም በኋላ ግን ባደረገችው ጥረት
አረጋዊው ኪራኮስ የጎልጎታን ኮረብታ አመለከታትና አስቆፍሪው
ብሎ ነገራት ኪራኮስም ዘመኑ ከመርዘሙ ጋር ተያይዞ
እውነተኛው ተራራ ይህ ነው ብሎ ማሳየት ባለመቻሉ "ከሦስቱ
ተራሮች አንዱ ነው" ስላላት አይሁድ ተራሮቹን ይቆፍሩ ዘንድ
አዘዘቻቸው፡፡ የጌታችን ቅዱስ መስቀል በሚያደርጋቸው
አስደናቂ ተአምራት የተነሣ ሕዝቡ እያመነ በተቸገሩ ግዜ
ክፉዎች አይሁዶች ማንም እንዳያገኘው የኢየሩሳሌም ነዋሪ
ሁሉ የእቤቱን ቆሻሻ የከበረ መስቀል ባለበት ቦታ እንዲጥል
አዘው ስለነበር ከሁለት መቶ ሃምሳ ዓመት በላይ ጥራጊ
ስለጣሉበት ታላቅ ተራራ ሆነ፡፡
ዕሌኒ ተራሮቹን ለማስቆፈር ከሦስቱ ተራሮች የቱ እንደሆነ
ለመለየት ደመራ አስደምራ ብዙ ዕጣን በመጨመርና
በማቃጠል ከአኢየሩሳሌም ወጣ ብለው ያሉትን ኮረብቶች
አሳያት፡፡ የዕጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ በመውጣት በቀጥታ ተመልሶ
መስቀሉ ባለበት ተራራ ላይ በማረፍና በመስገድ መስቀሉ
ያለበትን ትክክለኛ ሥፍራ አመለከታት፡፡ ቅዱስ ያሬድም "ሰገደ
ጢስ" ጢሱ ሰገደ ብሎታል፡፡ ከዚያም መስከረም 16 ቀን
ቁፋሮው እንዲጀመር አዘዘች፡፡ ሰባት ወር ያህል ከተቆፈረ በኋላ
መጋቢት 10 ቀን ሦስት መስቀሎች በአንድነት ተገኙ፡፡ ንግሥት
ዕሌኒም የክብር ባለቤት ጌታችን የተሰቀለበት የትኛው እንደሆነ
ለማወቅ በወደደች ጊዜ "ከራሱ በላይ ይህ የናዝሬቱ ኢየሱስ
የአይሁድ ንጉሥ ነው" የሚል የተቀረጸበት ጽሑፍ ያለው
እንደሆነ የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ ቅዱስ መቃርስ ነገራት፡፡
ከእርሱም ምልለክት ታይ ዘንድ ወደደች፡፡ የሞተ ሰው አምጥታ
በሁለቱ መስቀሎች ላይ በተራ ቢታስቀምጠው አልተነሣም፡፡
በመጨረሻ ጽሕፈት ባለው በአንዱ መስቀል ላይ
ቢታስቀምጠው ያንጊዜ የሞተው ሰው ተነሣ፡፡ በዚህም
የጌታችንን መስቀል ለየችው፡፡ ዕሌኒም ለጌታችን መስቀል
ሰገደችለት፡፡ ክርስቲያኖች ሁሉ ሰገዱለት፡፡ በየሀገሩ ያሉ
ክርስትያኖች ሁሉ የመስቀሉን መገኘት በሰሙ ግዜ መብራት
አብርተው ደስታቸውን በመግለጥ ለዓለም እንዲታወቅ
አደረጉ፡፡ በዚህም ምክንያት ይህ ታላቅ የድኅነት ምልክት
የሆነው መስቀል የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ደመራ በመደመር
በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ታከብረዋለች፡፡
ንግሥት ዕሌኒ መስከረም 16 ቀን 320 ዓ.ም በዕጣን ጢስ
ምልክት ቁፋሮ አስጀምራ መጋቢት 10 ቀን አግኝታ
በማውጣት ታላቅ ቤተ መቅደስ ጎልጎታ ላይ ሠርታ በክብር
አስቀመጠችው፡፡ ጌታችን ስለ ቅዱስ መስቀሉ ለቅድስት
ንግስት ዕሌኒ ቃልኪዳን ሲገባላት እንዲህ አላት፡- ‹‹በደሜ
የከበረ የመስቀሌን ስም የሚጠራውን እርሱን እምረዋለሁ፡፡
በዕፀ መስቀሌ ቤ/ክ ውስጥ የለመነውን የጸለየውን ሰው
መላእክት እንኳን ተድላ ደስታውን ወደማያውቁት ወደ
መንግሥተ ሰማያት አዳራሽ ያለወቀሳ ይገባል፡፡ ለከበረ
መስቀሌ ከቅርብም ከሩቅም ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ተጉዞ
የመጣውን ወደ መቃብሬ ኢየሩሳሌም እንደጓዘ እኔ
አደርግለታለሁ፡፡ ይህንንም መጽሐፍ የጻፈ ያጻፈ ወይም
ያነበበውን የተረጎመውን ቃሉን በዕዝነ ልቡና የሰማውን
የመጽሐፉንም ገበታዎቹን የሳመውን በተጸለየበት ውኃም
የተጠመቀውን እኔ በሕይወት መጽሐፍ በዓምደ ወርቅ ላይ
በወርቅ ቀለም ስሙን እጽፈዋለሁ፡፡›› (ድርሳነ መስቀል)
የጌታችንን ቅዱስ መስቀል ንግሥት ዕሌኒ መጋቢት 10 ቀን
አግኝታ በማውጣት ታላቅ ቤተ መቅደስ ጎልጎታ ላይ ሠርታ
በክብር ካስቀመጠችው በኋላ ከዚያ ዕለት ጀምሮ እንደ ፀሐይ
እያበራ ድውይ እየፈወሰ አጋንንት እያባረረ ልዩ ልዩ ገቢረ
ተአምራት እየሠራ ሙት እያነሣ ዕውር እያበራ ተአምራቱን
ቀጠለ፡፡ ይህንንም የሰማው ከኃያላን ነገሥታት መካከል የፋርስ
ንጉሥ መስቀሉን ማርኮ ፋርስ ወስዶ አስቀመጠው፡፡ ነገር ግን
ንጉሡ ሕርቃል የጌታችንን ቅዱስ መስቀል አስመልሶታል፡፡
በዚህ ጊዜ የኢየሩሳሌም ምእመናን የድሉን ዜና ሰምተው
ስለነበር የአንድ ቀን መንገድ ያህል ሄደው በመቀበል ካህናቱ
በዝማሬና በእልልታ ችቦ አብርተው ተቀብለዋቸዋል፡፡
የቤተክርስቲያን አባቶች እንደሚሉት ንጉሡ ሕርቃል ይህንን
ታላቅ ድል ለማግኘትና የጌታን ቅዱስ መስቀል ከአሕዛብ
(ከፋርሶች) እጅ ለማስመለስ የቻለው በዚያን ጊዜ አብያተ
ክርስቲያንናት ሁሉ ለአንድ ሳምንት (አንድ ሱባዔ) ባደረጉት ጾም
ጸሎት ነው፡፡ ይህንንም ለማስታወስና ጌታን ለማመስገን
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንና የግብጽ ኮፕቲክ
ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ የዐቢይ ጾም ከመጀመሩ አስቀድሞ
"ጾመ ሕርቃል" ብለው አንድ ሳምንት ይጾማሉ፡፡ የጌታ
መስቀል ለብዙ ጊዜያት ኢየሩሳሌም ከቆየ በኋላ ነገሥታት
‹‹ይህን መስቀል እኔ ልውሰድ፣ እኔ ልውሰድ›› በማለት ጠብ
ፈጠሩ፡፡ በዚህ ጊዜ የአንጾኪያ፣ የኤፌሶን፣ የአርማንያ፣ የግሪክ፣
የእስክንድርያ፣ የመሳሰሉት የሃይማኖት መሪዎች ጠቡን
አበረዱት፡፡ ከዚያም አያይዘው በኢየሩሳሌም የሚገኘውን
የክርስቶስን መስቀል ከአራት ከፍለው በዕጣ አድርገው
በስምምነት ተካፍለው ከሌሎች ታሪካዊ ንዋያተ ቅዱሳት ጋር
በየሀገራቸው ወስደው በክብር አስቀመጡት፡፡ የቀኝ ክንፉ
የደረሰው ለአፍሪቃ ስለነበር ከታሪካዊ ንዋየ ቅዱሳት ጋር
በግብጽ የሚገኘው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ተረክቦ ወስዶ
በክብር አስቀመጠው፡፡ ግማደ መስቀሉ ለብዙ ዘመን
በእስክንድርያ ሲኖር በግብጽ ያሉ እስላሞች እየበዙ ኃይላቸው
እየጠነከረ ሲሔድ በእስክንድርያ የሚኖሩ ክርስትያኖች ላይ
ሥቃይ ያጸኑባቸው ጀመር፡፡ ክርስቲያኖቹም አንድ ሆነው
መክረው ለኢትዮጵያዊው ዓጼ ዳዊት እንዲህ የሚል መልእክት
ላኩ "ንጉሥ ሆይ! በዚህ በግብጽ ያሉ እስላሞች መከራ
አጽንተውብናልና ኃይልህን አንሥተህ አስታግስልን" ብለው
ጠየቁት ዳግማዊ ዐጼ ዳዊትም ለመንፈሳዊ ሃይማኖት
ቀንተው የክርስቶስ ፍቅር አስገድዷቸው 20,000 ሠራዊት
አስከትለው ወደ ግብጽ ዘመቱ በዚህ ጊዜ በግብጽ ያሉ ኃያላን
ፈሩ ተሸበሩ፡፡ ንጉሡ ዳግማዊ ዳዊትም እንዲህ የሚል
መልዕክት ለእስላሞቹ ላከ፡- "በተፈጥሮ ወንድሞቻችሁ ከሆኑት
ክርስቲያኖች ካልታረቃችሁ ሀገራችሁን መጥቼ አጠፋለሁ"
የሚል ማስጠንቀቂያ ላከ፡፡
የንጉሡ መልዕክትም ለእስላሞቹ እንደደረሳቸው ፈርተው እንደ
ጥንቱ በየሃይማታቸው ጸንተው በሰላም እንዲኖሩ ከክርስቲያን
ወንድሞቻቸው ጋር ታረቁ፡፡ መታረቃቸውን ዓጼ ዳዊት ሰሙ
በዚህም ጉዳይ ንጉሡ ደስ አላቸው፡፡ እግዚአብሔርንም
አመሰገኑ በግብጽ የሚኖሩ ክርስቲያኖችም ከ12,000 ወቄት
ወርቅ ጋር ደስታቸውን ለኢትዮጵያዊው ንጉሥ ለዳግማዊ
ዳዊት በደብዳቤ አድርገው ላኩላቸው፡፡ ንጉሡም የደስታውን
ደብዳቤ ተመልክተው ደስ አላቸው ወርቁን ግን መልሰው
በመላክ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጻፉ፡- "በግብጽ የምትኖሩ
የክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ የላካችሁልኝ
12,000 ወቄት ወርቅ መልሼ ልኬላችኋለሁ፡፡ የእኔ ዓላማ
ወርቅ ፍለጋ አይደለም የክርስቶስ ፍቅር አስገድዶኝ በተቻለኝ
ችግራችሁን ሁሉ አስወገድኩላችሁ፤አሁንም የምለምናችሁ
በሀገሬ ኢትዮጵያ ረሀብና ቸነፈር ድርቅ ስለወረደብኝ
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀልና
የቅዱሳን አጽም ከሌሎች ክቡራን ዕቃዎች ጋር እንድትልኩልኝ
ነው" የሚል ነበር፡፡
እስክንድርያ ያሉ ምዕመናንም የዐፄ ዳዊት "በሀገሬ ኢትዮጵያ
ረሀብና ቸነፈር ድርቅ ስለወረደብኝ መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀልና የቅዱሳን አጽም
ከሌሎች ክቡራን ዕቃዎች ጋር እንድትልኩልኝ" የሚለው
መልዕክት እንደደረሳቸው ከሊቃነ ጳጳሳትና ከኤጲስ ቆጶሳቱ ጋር
ውይይት በማድረግ "ይህ ንጉሥ ታላቅ ክርስቲያን ነው፡፡ ስለዚህ
ልቡን ደስ እንዲለው የፈለገውን የጌታችንን ግማደ መስቀል
ከቅዱሳን ዐፅምና ንዋየ ቅዱሳት ጋር አሁን በመለሰው ወቄት
ወርቅ የብርና የነሐስ የመዳብና የወርቅ ሣጥን አዘጋጅተን
እንላክለት" ብለው ተስማምተው በክብር በሥነ ሥርዓት
በሠረገላና በግመል አስጭነው ስናር ድረስ አምጥተው
ለኢትዮጵያውያን ባስረከቧቸው ጊዜ በእጃቸው እያጨበጨቡ
በእግራቸው እያሸበሸቡ በግንባራቸው እየሰገዱ በክብር በደስታ
ተቀበሏቸው፡፡
ግማደ መስቀሉ ወደ መካከለኛው ኢትዮጵያ ሳይደርስ በድንገት
ዐፄ ዳዊት ስናር በሚባል በረሃ ላይ አረፉ፡፡ ግማደ መስቀሉም
የግድ በዚያው በስናር መቆየት አስፈለገው፡፡ ከዚህ በኋላ የሟቹ
የዳግማዊ ዳዊት ልጅ ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ እንደነገሡ ወደ ስናር
ሔደው ግማደ መስቀሉን ከሌሎቹ ንዋያተ ቅዱሳት ጋር
አምጥተው በመናገሻ ከተማቸው በደብረ ብርሃን ላይ
ቤተመቅደስ ሠርተው ለማስቀመጥ ሲደክሙ በሕልማችው
አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል "ወዳጄ ዘርዐ ያዕቆብ ሆይ
መስቀሌን በመስቀለኛ ቦታ ላይ አስቀምጥ" የሚል ራእይ
አዩ፡፡
ከእስክንድርያ ሀገር ከመስቀሉ ጋር በልዩ ልዩ ሣጥን ተቆልፈው
የመጡትም ዝርዝር ስማቸው ጌታችን በዕለተ ዓርብ ለብሶት
የነበረው ቀይ ልብስ፣ ከሮም የመጣው ከለሜዳው፣ ሐሙት
የጠጣበት ሰፍነግ /ጽዋ/፣ ዮሐንስ የሳለው ኩርዓተ ርዕሱ ስዕል
እንዲሁም የተለያዩ የቅዱሳን አጽም፣ ከግብጽ ታላላቅ ገዳማት
የተቆነጠረ አፈር፣ የዮርዳኖስ ውሃ ይገኛል፡፡ ንጉሡም
መስቀለኛ ቦታ እየፈለጉ በኢትዮጵያ አውራጃዎች ሁሉ
በመፈለግ ከብዙ ቦታ አስቀምጠውት ነበር፡፡ ለምሳሌ በሸዋ
በደብር ቅዱስ ደብረ ጽጌ ማርያም ገዳም፣ በማናገሻ ማርያም፣
በወጨጫ መስቀሉን አሳርፈውት ነበር፡፡ ነገር ግን
የመጨረሻውን ቦታ ባለማግኘታቸው በራዕይ እየደጋገመ
አንብር መስቅልየ በዲበ መስቅል መስቀሌን በመስቀለኛ
ሥፍራ አስቀምጥ እያለ ይነግራቸው ነበር፡፡ ዓጼ ዘርዓ
ያዕቆብም ለሰባት ቀን ሱባዔ ገቡ፡፡ በዚያም የተገለጸላቸው
"መስቀለኛውን ቦታ የሚመራህ ዓምደብርሃን ይመጣል"
አላቸው፡፡ እርሳቸውም ከዚያ እንደወጡ መስቀለኛውን ቦታ
የሚመራ የብርሃን ዓምድ ከፊታቸው መጥቶ ቆመ፡፡ በዚያ
መሪነት ወደ ወሎ ክፍለ ሀገር አምባሰል አውራጃ ውስጥ ግሸን
ከምትባል አምባ መርቶ መስከረም 21 ቀን 1440 ዓ.ም
አደረሳቸው፡፡ በእውነትም ይህች ግሸን የተባለችው አምባ
ጥበበኛ ሰው እንደቀረጻት የተዋበች መስቀለኛ ቦታ ሆና
ስላገኟት የልባቸው ስለደረሰ ደስ አላቸው፡፡ እግዚአብሔር ገና
ዓለምን ሲፈጥር የግሸንን ዓምባ ለዚህ ክብር የተዘጋጀች አድርጎ
ፈጥሯታልና፡፡ በዚያም አምባ ታላቅ ቤተ መቅደስ ሠርተው
ቅዱስ መስቀሉንና ሌሎች ንዋየ ቅዱሳቱን በየመዓረጋቸው
የክብር ቦታ መድበው አስቀመጡዋቸው፡፡ ዘመኑም በ14ኛው
ክፍለ ዘመን ነው፡፡ የንግሥት ዕሌኒ ረድኤት በረከቷ ይደርብን
በጸሎቷ ይማረን፡፡ የመስቀሉ ፍቅር ይደረብን!

Sunday, May 15, 2016

=>+*"+<+>+ግንቦት 8+<+>+"*+

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
አሜን
ግንቦት 8
+ አርባ ዓመት በአስቄጥስ ገዳም ሲኖር ከቅጠል በቀር
ተመግቦ የማያውቀው የገዳመ አስቄጥሱ ገድለኛው አባት አቡነ
ዳንኤል የዕረፍቱ ዓመታዊ መታሰቢያ በዓሉ ነው፡፡
+ ሰማዕቱ አቡነ ዮሐንስ ከ224 ማኅበርተኞቹ ጋር
ምስክርነቱን በድል ፈጸመ፡፡
ሰማዕቱ አቡነ ዮሐንስ፡- ይህንንም ቅዱስ ግብፅ ስንሑት
በምትባል ሀገር በ14 ዓመቱ የአባቱን በጎች ሲጠብቅ
የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦለት እየመራው ወስዶ ከገዳም
አስገባው፡፡ ሃይማኖትን ጠንቅቆ ከተማረ በኋላ በ21 ዓመቱ
መንኩሶ ተጋድሎውን ጀመረ፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ በገዳም በተጋድሎ ሲኖር መልአኩ ድጋሚ
ተገልጦለት የብርሃን አክሊል አሳይቶ ወደ አትሪብ ከተማ ሄዶ
በክርስቶስ ስም ሰማዕት እንዲሆን ነገረው፡፡ በጥሪውም
መሥረት እናትና አባቱን ተሰናብቶ ወደ አትሪብ ሄዶ በከሃዲው
መኰንን ፊት የክርስቶስን አምላክነት መመስከር ጀመረ፡፡
ብዙዎቹ የመኰንኑ ወታደሮች በእርሱ እምነት አመኑ፡፡ ነገር
ግን መኰንኑና ክፉዎች ተባብረው በልዩ ልዩ ዓይነት መንገድ ጽኑ
መከራን አደረሱበት፡፡ መልአኩም እየተገለጠ እያጽናናው
ቁስሎቹን ይፈውስለት ጀመር፡፡ መኰንኑም ወደ እንዴና ሀገር
ላከውና በዚያም እጅግ አሠቃዩት፡፡ በተአምራትም ብዙዎችን
አሳመነ፡፡ የእንዴናውም መኰንን ማሠቃየት በሰለቸው ጊዜ
ግንቦት 8 ቀን አንገቱን በሰይፍ አስቆረጠውና ሰማዕትነቱን
በድል ፈጽሞ የክብር አክሊልን ተቀዳጀ፡፡ ማኅበርተኞቹ የሆኑ
224 ሰዎችም ከእርሱ ጋር ተሰይፈው ዐረፉ፡፡ በቅዱስ
ዮሐንስም በመቃብሩም ላይ 12 ቀን ሙሉ ቀስተ ደመና
ተተክሎና መቃብሩን ሸፍኖት ታይቷል፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ
ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን፡፡
+ + + + + + + + + + + + + + +
የገዳመ አስቄጥሱ አባ ዳንኤል፡- በመቃርስ ገዳም በደብረ
ሲሐት ይኖር የነበረ ሲሆን እርሱም እጅግ ገድለኛ አባት ነው፡፡
40 ዓመት በአስቄጥስ ገዳም ሲኖር ከቅጠል በቀር ተመግቦ
አያውቅም፡፡ በአስቄጥስ ገዳም ዜናው ሁሉ በዓለም በተሰማ
ጊዜ የነገሥታት ልጆችም ወደ እርሱ እየመጡ እየተባረኩ ይሄዱ
ነበር፣ ግማሾቹም በዚያው ይመነኩሱ ነበር፡፡ ይህም አባ
ዳንኤል ስሟን እንጣልዮስ አስብላ የነበረች ንግሥት
የነበረችውን ቅድስት በጥሪቃን የገነዛት ነው፡፡ እርሷም ወንድ
የነበረች ሲሆን ይህም የታወቀው ከሞተች በኋላ ነው፡፡
አውሎጊስ የሚባለውን የወፍጮ ድንጋይ እየወቀረ በመሸጥ
ለድኆች የሚመጸውትን ጻድቅ ሰው ዋስ እሆነዋለሁ በማለት
ከእግዚአብሔር ዘንድ ለምኖ ሥልጣንና ብዙ ወርቅ እንዲያገኝ
ያደረገው ይህ አባ ዳንኤል ነው፡፡ በኋላም አውሎጊስ ሀብቱና
ንብረቱ ከእግዚአብሔር የሚያርቀው ቢሆን አባ ዳንኤል
በጸሎቱ መልሶ ሀብቱን እንዲያጣ አድርጎታል፡፡
አውሎጊስ የሚባል ጻድቅ የወፍጮ ድንጋይ እየወቀረ
(እየጠረበ) በመሸት የሚየገኘውን ለድኆችና ጦም አዳሪዎች
ይመጸውት ነበር፡፡ አባ ዳንኤልም የአውሎጊስን መልካም ሥራ
ተመልክቶ እጅግ ደስ ብሎት ለአውሎጊስ የሀብቱን መጠን
እንዲጨምርለትና ይበልጥ እንዲመጸውት በማሰብ ወደ
እግዚአብሔር በጸሎት አሳሰበ፡፡ ለአውሎጊስም ዋስ ሆነውና
ሀብቱ ተጨመረለት፡፡ አንድ ቀን የሚወቅረውን ድንጋይ
ሲፈቅል በሸክላ ዕቃ የተደፈነ ሙሉ ወርቅ አገኘ፡፡ ወደ
ቁስጥንጥንያም ከተማ ሄዶ ለንጉሡ አስረከበና የንጉሡ
የሠራዊት አለቃ ሆኖ ተሾመ፡፡ ከተሾመም በኋላ የቀድሞውን
የጽድቅ ሥራውን ተወ፡፡ አባ ዳንኤልም ስለ እርሱ ሰምቶ
ሊያየው ቢሄድ በፈረስ ላይ ተቀምጦ በሠራዊት ታጅቦ በትዕቢት
ተመልቶ አገኘው፡፡ ክፉ የትዕቢት መንፈስ አድሮበት ነበር፡፡ አባ
ዳንኤልም አውሎጊስ ሀብት እንዲያገኝ በመለመኑ አዘነ፡፡
በሌሊትም የአውሎጊስ ነፍስ በእርሱ ምክንያት እንደጠፋች ራሱ
አባ ዳንኤልም ሲሰቀልና እመቤታችን ስለ እርሱ ስትማልድ
ራእይ አየ፡፡ ከእንቅልፉም በቃ ጊዜ የአውሎጊስ ሀብት
እንዲጠፋና ወደ ቀደመ ግብሩ እንዲመለስ በጾም ጸሎት ሱባኤ
ያዘ፡፡ መልአክም ተገልጦለት በእግዚአብሐር የፍርድ ሂደት
ውስጥ ጣልቃ በመግባቱ ከገሠጸው በኋላ አውሎጊስም
ምሕረት እንደሚያገኝ ነገረው፡፡ አውሎጊስን የሾሸመው
ንጉሥም ሞተና ሌላ ንጉሥ ነገሠ፡፡ አውለጊስንም ንብረቱን
ሁሉ ቀምቶ ነፍሱንም ለመግደል አሳደደው፡፡ አውሎጊስም
ነፍሱን ለማዳን ሽሽቶ ወደ ሀገሩ በመግባት የቀድሞ ሥራውን
መሥራት ጀመረ፡፡ ነዳያንንም እንደዱሮም መመገብ ጀመረ፡፡
አባ ዳንኤል ከታለቁ ጻድቅ ንጉሥ ከቅዱስ አኖሬዎስ ጋር
የተገናኘ ታሪክ አለው፡፡ ይኸውም አባ ዳንኤል 40 ዓመት ሙሉ
በአስቄጥስ ገዳም ሲኖር ከቅጠል በቀር ተመግቦ አያውቅም
ነበርና ከጽድቁና ከብቃቱ የተነሣ ከብዙ ዘመን በኋላ የመመካት
ክፉ ሀሳብ መጣበት፡፡ ‹‹በገዳም ውስጥ እንደእኔ ትርሕምትን
ገንዘብ ያደረገ ይኖር ይሆን?›› ብሎም አሰበ፡፡ ሰውን ወዳድ
የሆነ ጌታችንም ይህን ክፉ ሀሳቡን ሊያርቅለት ሽቶ ብርሃናዊ
መልአኩን ላከለት፡፡ መልአኩም አባ ዳንኤልን ስለ ትምክህቱ
ቢቆጣውም አባ ዳንኤል መልአኩን መልሶ ‹‹ጌታዬ ከእኔ
የሚሻል ካለ ንገረኝ፣ ወደ እርሱ ሄጄ አየው ዘንድ እወዳለሁ፣
በመመካቴም ወደ ፈጣሪዬ በልመና እመለስ ዘንድ›› አለው፡፡
መልአኩም ‹‹እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው የሮሜና
የቁስጥንጥንያ ንጉሥ አኖሬዎስ በመንግሥተ ሰማያት
ባልንጀራህ ነው›› አለው፡፡
‹‹ንጉሥ አኖሬዎስም የመነኮሳትን ሥራዎች ሁሉ ስለሚሠራ
ከልብሰ መንግሥቱ ሥር በሥጋው ላይ ማቅ ይለብስ ነበር››
ተብሎ በስንክሳሩ ላይ የተጻፈለት ጻድቅ ንጉሥ ሲሆን
ሰማያውያን የሆኑ ቅዱሳን መላእክትም ቅድስናውን
የመሰከሩለት በንግሥና ያለ ታላቅ የእግዚአብሔር አገልጋይ
ነው፡፡ አባ ዳንኤልም ይህ በሰማ ጊዜ መሬት ላይ ወድቆ
በራሱም ላይ አመድ ነስንሶ የዚህን የሮም ንጉሥ አኖሬዎስን
ግብር ያሳየው ዘንድ ጌታችንን ለመነ፡፡ ደመናም መጥታ ነጥቃ
ወሰደችውና ንጉሥ አኖሬዎስ ደጅ አደረሰቸውና ንጉሡን በዙፋኑ
ላይ ሆኖ ባየው ጊዜ ከግርማው የተነሣ አይቶት በታላቅ ፍርሃት
ውስጥ ሆኖ ከእግሩም በታች ሰገደለትና አኗኗሩንም ይነግረው
ዘንድ በጌታችን ስም አማፀነው፡፡ ንጉሥ አኖሬዎስም ሰሌን
በመታታት በእጅ ሥራው ደክሞ ከሚያገኘው በቀር ምንም
ሳይበላና ሳይለብስ 40 ዓመት እንደሆነው፣ ሰሌን ታቶ ሸጦ
ካገኘውም ውስጥ ከዕለት ምግቡ መግዣ የሚተርፈውን
ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች እንደሚመጸውት፣ ምግቡም
እንጀራና ጨው፣ ቅጠል መጻጻም እንደሆነ፣ የማንንም ንብረት
ፈጽሞ እንዳልንካ፣ ድንግልናውንም ጠብቆ እንደሚኖር
ነገረው፡፡ አባ ዳንኤልም ድጋሚ ከእግሩ ሥር ወድቆ ሰግዶለት
ስለ ትምክህቱም ፈጽሞ እያዘኑ ወደ በዓታቱ ተመልሷል፡፡
አባ ዳንኤል አንድ ቀን ከረድኡ ጋር ወደ እስክንድርያ ሲጓዝ
ስሙ ምህርካ የሚባል እብድ አገኘ፡፡ ብዙ እብዶችም ይከተሉት
ነበር፡፡ እርሱም ለአገሩ ሰዎች ሁሉ በእውነት ያበደ ይመስላቸው
ነበር፡፡ አባ ዳንኤልም እጁን ይዞ ወደ ሊቀ ጳጳሳቱ ወስዶ
ትሩፋቱን ተጋድሎውን ነገረው፡፡ ከሊቀ ጳጳሳቱም ጋር ሆነው
እብዱን ስለራሱ እንዲነግራቸው በእግዚአብሔር ስም ባማሉት
ጊዜ ከዝሙት ጦር በመሸሽ ራሱን እብድ እንዳስመሰለ
ነገራቸው፡፡
አንድ ቀን አባ ዳንኤል በሌሊት በበረሃ ውስጥ በጨረቃ ብርሃን
ሲጓዝ በተራራ ላይ ቀምጣ ጠጉሯ መላ ሰውነቷን የሸፈናት
በዚያም በረሃ ስትኖር በተሰነጠቀ ዓለት ውስጥ 38 ዓመት
ብቻዋን ማንም ሳያያት የኖረች ጻድቅ እናት አግኝቶ ምሥጢሯን
ሁሉ ነግራዋለች፡፡ እርሷም ቅድስት አመተ ክርስቶስ ናት፡፡ አባ
ዳንኤልም 38 ዓመት ሙሉ በዚህ በረሃ ምንም ሰው ሳታይ
የኖረችበትን ተገድሎዋን በዝርዝር ነግራቸዋለች፡፡ እርሳቸውም
ወደ ገዳማቸው ተመልሰው ለአበ ምኔቱና ለመነኮሳቱ ታሪኳን
በመንገር ልብስ ይዘውላት ቢመጡ ዐርፋ አግኝተዋታል፡፡
አባ ዳንኤል የልዮንን የክህደት ደብዳቤ ወታደሮቹ አምጥተው
በመነኮሳቱ ፊት ሲያነቡ ደብዳቤውን ተቀብሎ በሕዝቡ ፊት
ቀዶታል፡፡ ወታደሮቹም አባ ዳንኤልንደብደበው ከገዳሙም
አሳደውታል፡፡ ብዙ ሥቃይም አድርሰውበታል፡፡
አባ ዳንኤል በአንዲት ዕለት ከደናል ገዳም ደርሶ ደጁን አንኳኳ፡፡
እነርሱም አባ ዳንኤል መሆኑን ዐውቀው ከፈቱለት፡፡ አንዲት
ሴትም ራሷን ዕብድ አስመስላ በደጅ የምትተኛ ሴት ነበረች፡፡
እርሱም ዕብድ መስላ በደጅ ስለተቀበጠችው ሴት አበምነቷን
ሲጠይቃት እብድ መሆኗን ነገረችው፡፡ አባ ዳንኤል ግን ዕብድ
የመሰለቻቸው ሴት እብድ ሳትሆን በድብቅ በታላቅ ተጋድሎ
የምትኖር ቅድስት ሴት መሆኗን ነገራት፡፡ ዕብድ የተባለችውም
ሴትም አባ ዳንኤል ምሥጢሯን እንደገለጠባት በስውር ዐውቃ
ወዲያው ደብዳቤ ጽፋ ይኸውም ‹‹የተከበራችሁ እኅቶቼ
ስላስቀየምኳችሁና ስላሳዘንኳችሁ ይቅር በሉኝ›› ብላ ጽፋ
ደብዳቤውን አስቀምጣ ጥላቸው ጠፋች፡፡ እነርሱም ከዚያ በኋላ
ዳግመኛ አላዩአትም፡፡
ደናግል ወደሚኖሩበት ገዳም አንድ የወንበዴዎች አለቃ ሰይጣን
አነሳስቶት ወደ ገዳሙ በአባ ዳንኤል ተመስሎ ቆቡን ደፍቶ
በሩን አንኳኳ፡፡ ደናግላኑም ሊዘርፋቸው መምጣቱን ምንም
ባለማወቅ ይልቁንም አባ ዳንኤል መጣ ብለው በሩን
ከፈቱለትና አስገቡት፡፡ እግሩንም አጥበው ለበረከት ብለው
የእግሮቹን ዕጣቢ በፊታቸው ላይ ረጩት፡፡ ከመካከላቸውም
አንዷ ዐይነ ሥውር ነበረችና ዐይኗ ወዲያው በራላት፡፡ በዚህም
ደናግሉ እጅግ ተደስተው ‹‹አባ ዳንኤል አንተ ንዑድ ክቡድ ነህ››
ብለው ሰገዱለት፡፡ ይህን ጊዜ የሽፍቶቹ አለቃ በጣም ደንግጦ
በመጸጸት ወደ አባ ዳንኤል ዘንድ ሄዶ ያደረገውን ሁሉ በመናገር
ንስሓ ገባ፡፡ መንኩሶም በታላቅ ተጋድሎ መኖር ጀመረ፡፡
እርሱም ተአምራት እስከማድረግ ደርሶ በሰላም ዐረፈ፡፡ የአባ
ዳንኤልም ተጋድሎና ተአምር ምን ቢጽፉት የሚያልቅ
አይደለም፡፡ ዕረፍቱም በደረሰ ጊዜ ጌታችን ታላቅ ቃልኪዳን
ሰጥቶት ቅድስት ነፍሱን ወደ እርሱ ወስዷታል፡፡ የአባ ዳንኤል
ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን፡፡

=>+*"+<+>+ኢየሱስ ክርስቶስ ተማላጅ እንጂ አማላጅ አይደለም+<+>+"*+

“ያመኑትም ሕዝብ አንድ ልብ አንዲትም ነፍስ ነበሩአቸው”።
የሐ.ሥራ ፬፡፴፪
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተማላጅ
እንጂ አማላጅ አይደለም::
የተሐድሶ መናፍቃኑ አንደበት “ክርስቶስ አማላጅ ነው” በማለት
በዛሬው ዕለት የእምነት አቋሙን የገለጹበት ጽሑፍ
አውጥቶዋል::
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
#ጌታችን_መድኃኒታችን_ኢየ ሱስ_ክርስቶስን
#አምላክ_ወልደ_አምላክ_ብ ላ_ታምናለች፤
ታስተምራለችም:: ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ተማላጅ እንጂ አማላጅ እንዳልሆነ ቅዱሳን መጻሕፍ
ይናገራሉ:: በዚህ በተሐድሶ ለወጣው የምንፍቅና ትምህርት
ምላሽ ይሆን ዘንድ የሚከተለውን የቤተ ክርስቲያናችን
አስተምህሮ የሚገልጽ ጽሑፍ አቅርበንላችኋል::
+++
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእርሱን
ማንነት ገልጦ ያስተማረበት ትምህርት ነው። በዚህም
ትምህርቱ፥ እርሱ የበጎች እረኛ እንደሆነ፥ የበረቱም በር እርሱ
መሆኑን ተናግሯል። እውነት የባህርይ ገንዘቡ ስለሆነም፥
ትምህርቱን «እውነት እውነት እላችኋለሁ፤» በማለት
ጀምሯል። በዚህም አማናዊ በሆነ ትምህርቱ «ወደ በጎች በረት
በበሩ የማይገባ፥ በሌላም በኲል የሚገባ ሌባ፣ ወንበዴም
ነው፤» ብሏል። ይኽንንም ስለ ሦስት ነገር ተናግሮታል።
፩ኛ፦ #ጌታችን_አምላካችን_መድኃ ኒታችን #ኢየሱስ_ክርስቶስ
፥ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ዕውር ሆኖ የተወለደውን ብላቴና
በምራቁ ጭቃ አድርጐ፥ በሰሊሆም ጠበልም እንዲጠመቅ
በማድረግ ፈጽሞ ስለፈወሰው፥ አይሁድ ብላቴናውንም
ወላጆቹንም አስቸግረዋቸው ነበር። ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ፦
«ይህ ሰው (ኢየሱስ) ከእግዚአብሔር አይደለም፥ ሰንበትንም
አይከብርምና፤» እያሉ ብላቴናውን ተከራክረውታል። እርሱ
ግን፦ «ኃጢአተኛ ሰው እንዲህ ያለ ተአምራት ማድረግ (በደረቅ
ግንባር ላይ ዓይን መፍጠር) እንዴት ይችላል? . . . እርሱ ነቢይ
ነው፤» አላቸው። ይኸውም፦ የነቢያት አለቃ ሙሴ፥
ከእግዚአብሔር አግኝቶ፥ «እግዚአብሔር ከወንድሞቻችሁ
መካከል (ከእናንተ ወገን) እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣላችኋልና
እርሱን ስሙት፤» በማለት ለእስራኤል ዘሥጋ የነገራቸው ቃለ
ትንቢት ነው። የሐዋ ፯፥፴፯። ምክንያቱም በብዙ መንገድ
ሙሴ ለኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነውና። የነቢያት አምላካቸው
ኢየሱስ ክርስቶስ «ነቢይ» መባሉም ነቢያት በአንድም ሆነ
በሌላ ምሳሌዎቹ በመሆናቸው ነው።
የብላቴናው ወላጆች ደግሞ አይሁድ ወጥረው በጠየቋቸው ጊዜ፥
«ይህ ልጃችን እንደሆነ፥ እውር ሆኖም እንደተወለደ
እናውቃለን። አሁን ግን እንዴት እንደሚያይ፥ ዓይኖቹንም ማን
እንደ አበራለት እናውቅም፥ እርሱን ጠይቁት፥ አዋቂ ነውና፥
ስለራሱም መናገር ይችላልና፤» አሉ። እንዲህም ማለታቸው
«እርሱ ክርስቶስ ነው፥ ብሎ በእርሱ የሚያምን ቢኖር
ከምኲራብ ይውጣ፤» የሚለውን የአይሁድን ዓዋጅ ፈርተው
ነው። ብላቴናው ግን ደጋግመው በጠየቁት ጊዜ «አትሰሙኝም
እንጂ ነገርኋችሁ፥ እንግዲህ ምን ልትሰሙ ትሻላችሁ? እናንተም
ደቀመዛሙርቱ ልትሆኑ ትሻላችሁን?» ብሎ ሳይፈራ
ተከራከራቸው። በዚህን ጊዜ «ራስህ በኃጢአት የተወለድህ አንተ
እኛን ታስተምራለህን?» ብለው ከምኲራብ አወጡት። በዚህም
ንግግራቸው በጌታ ቃል፦ «የእግዚአብሔር ሥራ ሊገለጥበት
ነው እንጂ እርሱ አልበደለም፥ ወላጆቹም አልበደሉም፤»
የተባለውን ሰው በልበ ደንዳናነት ኰነኑት። ከቤተ መቅደስም
አስወጡት። ዮሐ ፱፥፫። ጌታችንም አግኝቶት «አንተ
በእግዚአብሔር ልጅ ታምናለህን?» አለው። ብላቴናውም፦
«አቤቱ፥ አምንበት ዘንድ እርሱ ማነው?» ብሎ መለሰለት።
ጌታችን ኢየሱስም «የምታየው፥ ከአንተ ጋርም የሚነጋገረው
እርሱ ነው፤» አለው። ይኸውም «ነቢይ ነው፤» እንዳለ
በምሳሌው እንዳይቀር «አምላክ ወልደ አምላክ» ብሎ
እንዲያምን ነው። እርሱም «አቤቱ ፥ አምናለሁ፤» ብሎ
ሰገደለት። ከዚህ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «እኔ
የማያዩት እንዲያዩ (አላዋቆች ነን የሚሉ ሐዋርያት አዋቆች
ይሆኑ ዘንድ) የሚያዩትም እንዲታወሩ (አዋቆች ነን የሚሉ
ፈሪሳውያን አለዋቆች ይሆኑ ዘንድ) ለፍርድ መጥቻለሁ።
(ላመነብኝ ልፈርድለት ላላመነብኝ ልፈርድበት፥ ለሰው
መፈራረጃ ለመሆን ከሰማይ ወርጃለሁ)። አለው። በዚህን ጊዜ
ይኽንን የሰሙ ፈሪሳውያን፦ «እኛ ደግሞ ዕውሮች ነን?»
አሉት። ጌታችን ኢየሱስም ዕውሮችስ ብትሆኑ ኃጢአት
ባልሆነባችሁ ነበር፤ (ነውረ ሥጋ ከመንግሥተ ሰማይ
አያወጣምና)፤ አሁን ግን እናያለን (እናውቃለን) ትላላችሁ፥
አታዩምም፤ (አታውቁምም)፤ ስለዚህም ኃጢአታችሁ ጸንቶ
ይኖራል፤ (ንስሐ ስለማትገቡ ኃጢአታችሁ አይሰረይላችሁም)፤
አላቸው። ዮሐ ፱፥፩፥፵፩። እንግዲህ በዚህ ምክንያት «ለሰው
መፈራረጃ እሆን ዘንድ መጥቻለሁ።» በማለቱ፥ ለምሕረትም
እንደመጣ ለማጠየቅ በዮሐንስ ወንጌል በምዕራፍ አሥር
ያለውን አስተምሯል።
፪ኛ፦# ይህ_ዕውር_ሆኖ_ተወልዶ_ ጌታ #የፈወሰው_ብላቴና፥
ፈሪሳውያን፦ እንዴት እንዳየ ደጋግመው በጠየቁት ጊዜ፥ ደጋግሞ
እውነቱን ነግሯቸዋል። በተጨማሪም፦ «እናንተም ደቀ
መዛሙርቱ ልትሆኑ ትሻላችሁን?» ብሎም ጠይቋቸዋል።
እነርሱ ግን፥ «አንተ የእርሱ ደቀመዝሙር ሁን፥ እኛስ የሙሴ
ደቀመዛሙርት ነን። እግዚአብሔር ሙሴን እንደተነጋገረው
እናውቃለን፥ ይህን ግን ከወዴት እንደሆነ አናውቅም፤» አሉት።
በዚህን ጊዜ «. . . ከወዴት እንደሆነ፥ አታውቁምና እጅግ ድንቅ
ነው፤ ነገር ግን ዓይኖቼን አበራልኝ። ይህ ሰው ከእግዚአብሔር
ባይሆን ኖሮ ምንም ማድረግ ባለቻለም ነበር፤» ብሎአቸዋል።
እንግዲህ፦ «ከወዴት እንደሆነ አናውቅም፤» ብለውት ስለነበረ
ከወዴት እንደሆነ ለማጠየቅ አንቀጸ አባግዕን አስተምሯል።
፫ኛ፦ «ቸር እረኛ አይደለህም፤» ብለውት ስለነበር፥ ቸር እረኛ
መሆኑን ለማጠየቅ ነው። ይኽንንም፦ «ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ፥
ቸር ጠባቂ ስለ በጎቹ ነፍሱን ይሰጣል። ጠባቂ ያይደለ፥ በጎቹም
ገንዘቡ ያይደሉ ምንደኛ ግን፥ ተኲላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ
ይሻላል፤ ተኲላም መጥቶ በጎቹን ይነጥቃቸዋል፥
ይበትናቸዋልም። ምንደኛስ ይሸሻል፥ ስለ በጎቹም አያዝንም፥
ምንደኛ ነውና።» በማለት ነግሯቸዋል።
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ በጎች
ያላቸው ምእመናንን ነው። የዕለተ ምጽአት ፍርድ እንዴት
እንደሆነ ለደቀመዛሙርቱ በነገራቸውም ጊዜ፥ ጻድቃንን በበጎች
መስሎ፥ «በጎቹን በቀኝ ያቆማቸዋል፤» ብሏል። ማቴ
፳፭፥፴፫። ቅዱስ ጴጥሮስንም፦ «በጎቼን ጠብቅ፤» ብሎታል።
ዮሐ ፳፩፥፲፭። ተኲላ ያለው ደግሞ ሰይጣንን እና መልክተኞቹን
ነው። ቅዱስ ዳዊት፦ በልዑል ረድኤት የሚያድር፥ በሰማይ
አምላክ ጥላ ውስጥ የሚቀመጥ፥ እግዚአብሔርን፦ «አንተ
መጠጊያዬና አምባዬ፥ አምላኬና ረዳቴ ነህ፥ በአንተ
እታመንብሃለሁ፤» የሚል ሰው፥ የሚያገኘውን ጸጋ ሲናገር፥
«ክፉ ነገር ወደ አንተ አይቀርብም፥ መቅሠፍትም ወደ ቤትህ
አይገባም። በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ
አንተ ያዝዛቸዋልና፥ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል
በእጆቻቸው ያነሡሃል። በተኲላና በእባብ ላይ ትጫናለህ፥
አንበሳውንና ዘንዶውን ትረግጣለህ፤» ብሏል። መዝ ፺፥፩-፲፫።
ካልተጠነቀቁ በስተቀር ተኲላት (መናፍቃን) አደገኞች ናቸው።
ይኽንንም ጌታችን «የበግ ለምድ ለብሰው ወደ እናንተ
ከሚመጡ ከሐሰተኞች ነቢያት (ከመናፍቃን) ተጠንቀቁ፥
በውስጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኲላዎች ናቸው።» በማለት
ነግሮናል። ማቴ ፯፥፲፭። ከዚህም ሌላ «እነሆ እኔ እንደ በጎች
በተኲላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ . . . ከክፉዎች ሰዎች
ተጠበቁ፤» ብሎናል።
ተኲላ ተንኰለኛ አውሬ ነው፥ ተመሳስሎ ከበጎች ጋር መደባለቅ
ያውቅበታል፥ ሥጋ በል ሲሆን ሣር እንደሚነጭ እንስሳ
አንገቱን ቀብሮ ይውላል፥ ቢርበውም ምቹ ጊዜ እስኪያገኝ
ይታገሣል። በጎች በራሳቸው አቅም ይኽንን መከላከል
አይችሉም፥ ምክንያቱም የዋሃን ናቸውና። በመሆኑም ተግቶ
የሚጠብቅ እረኛ ያስፈልጋቸዋል። እረኛ ከሌላቸው ግን
ይጠፋሉ። ይኽንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ
ከምእመናን ሕይወት ጋር በማገናዘብ፦ «እንደ በጎች ትቅበዘበዙ
ነበርና፥ አሁንም ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመለሱ፤»
ብሏል። ፩ኛ ጴጥ ፪፥፳፭። በጎች የምእመናን ብቻ ሳይሆን
የክርስቶስም ምሳሌዎች ናቸው። መጥምቀ መለኰት ቅዱስ
ዮሐንስ፦ «እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ
የእግዚአብሔር በግ፤» ያለው ለዚህ ነው። ዮሐ ፩፥፳፱። ነቢዩ
ኢሳይያስም፦ «እርሱ ግን በመከራው ጊዜ አፉን አልከፈተም፥
እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፥ የበግ ጠቦትም በሸላቾቹ ፊት
ዝም እንደሚል እንዲሁ አፉን አልከፈተም።» በማለት
አስቀድሞ ተናግሯል። ኢሳ ፶፫፥፯።
፩፥፩፦ #በበሩ_የሚገባና_የማይገባ ፤
#በበሩ_የሚገባ_ማለት፦ ትንቢት ተነግሮለት፥ እግዚአብሔር
አብ መስክሮለት፥ ምእመናን ወደ አሉበት ወደ ኢየሩሳሌም
በመምሕርነት የሚመጣ ማለት ነው። ጌታችን አምላካችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣው
ትንቢት ተነግሮለት፥ ሱባዔ ተቆጥሮለት ነው። ኢሳ ፯፥፲፬፤ ፱፥፪-
፮፤ ፲፩፥፩። የባህርይ አባቱም በዮርዳኖስ፦ «በእርሱ ደስ
የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤» በማለት መስክሮለታል።
ማቴ ፫፥፲፯። ከዚያም በፊት የልደቱን ብሥራት ለእመቤታችን
ለቅድስት ድንግል ማርያም የነገረ፥ ቅዱስ ገብርኤል፥
«ማርያም ሆይ፥ በእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን
አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆ ትፀንሻለሽ፥ ወንድ ልጅንም
ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ። እርሱም ታላቅ
ነው፥ የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል፤» ብሏል። ሉቃ
፩፥፴-፴፪። በተወለደ ጊዜም ቅዱሳን መላእክት፥ ለእረኞች
ተገልጠው፥ «እነሆ፥ ለእናንተና ለሕዝቡ ሁሉ ደስታ የሚሆን
ታላቅ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ እነሆ፥ ዛሬ በዳዊት
ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋል፥ ይኸውም ቡሩክ ጌታ ክርስቶስ
ነው።» በማለት መስክረውላቸዋል። ሉቃ ፪፥፲፥፲፩።
መጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስም፦ «ጫማውን እሸከም
ዘንድ ከማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ
ይበረታል፥እርሱ በእሳትም በመንፈስ ቅዱስም ያጠምቃችኋል፤
መንሹም በእጁ ነው፥ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፥
ስንዴውን በጎተራ ይከታል፥ ገለባውን በማይጠፋ እሳት
ያቃጥለዋል።» ማቴ ፫፥፲፩። «ተጐንብሼ የጫማውን ጠፍር
መፍታት ከማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ በኋላዬ ይመጣል።» ማር
፩፥፯፣ ሉቃ ፫፥፲፭። «ዳሩ ግን እናንተ
የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል፤ እኔ የጫማውን ጠፍር
ልፈታ የማይገባኝ፥ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ ይልቅ
የሚከብር ይህ ነው። . . . አንድ ሰው ከእኔ ይልቅ የከበረ
ሆኖአል ብዬ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነው። እኔም አላውቀውም
ነበር፥ ነገር ግን ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ ስለዚህ በውኃ
እያጠመቅሁ መጣሁ።» ዮሐ ፩፥፳፮። «ከሰማይ ካልተሰጠው
ሰው አንዳች ሊቀበል አይቻለውም። እናንተ እኔ ክርስቶስ
አይደለሁም፥ ነገር ግን ከእርሱ በፊት ተልኬአለሁ እንዳልሁ
ራሳችሁ ትመሰክሩልኛላችሁ። ሙሽራይቱ ያለችው እርሱ
ሙሽራ ነው፥ ቆሞ የሚሰማው ሚዜው ግን በሙሽራው ድምፅ
እጅግ ደስ ይለዋል። እንግዲህ ይህ ደስታዬ ተፈጸመ። እርሱ
ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ይገባል።» ብሏል። ዮሐ ፫፥፳፯።
ከእግዚአብሔር አብ፥ ከነቢያት ትንቢት፥ ከቅዱሳን መላእክት
ብሥራትና የምሥራች፥ እንዲሁም ከመጥምቀ መለኰት ቅዱስ
ዮሐንስ ምስክርነት እንደተማርነው፦ ጌታችን አምላካችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ በበሩ የገባ ቸር እረኛ ነው።
በመሆኑም «ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፥ በጎቹም ቃሉን
ይሰሙታል፥ እርሱም በጎቹን በየስማቸው ይጠራቸዋል፥
አውጥቶም ያሰማራቸዋል።» ብሎአል። በረኛ የተባለ መንፈስ
ቅዱስ ነው፤ ሕዋሳቱን በሰበሰበ፥ ዐሠርቱ ቃላትን በያዘ፥ በሰቂለ
ኅሊና፥ በነቂሐ ልቡና በሚኖር ሰው የሚያድር እርሱ ስለሆነ
የሰውን አእምሮ ለበጎ ይከፍተዋል። አንድም በረኛ የተባለ ራሱ
ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ምክንያቱም፥ ለጊዜው አምስት ሺ
አምስት መቶ ዘመን የተዘጋች ገነትን በቤዛነቱ የሚከፍት፥
ለፍጻሜውም በዕለተ ምጽአት መንግሥተ ሰማያትን የሚከፍት
እርሱ ነውና። «በጎቹ ቃሉን ይሰሙታል፥» እንዳለ፥ አሥራ ሁለቱ
ሐዋርያት፥ ሰባ ሁለቱ አርድእት፥ ሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት
ትምህርቱን ተቀብለውታል። በየስማቸውም ዮሐንስ፥ ያዕቆብ፥
ስምዖን፥ ታዴዎስ፥ ዲዲሞስ፥ ቶማስ እያለ ጠርቶአቸዋል።
«አውጥቶም ያሰማራቸዋል፤» የተባለው ደግሞ፦ «በጠባቢቱ
በር ግቡ፤ . . . እኔን ሊከተል የሚወድ ራሱን ይካድ፥ ጨክኖም
የሞቱን መስቀል ተሸክሞ ይከተለኝ፤» እያለ ያስተምራቸዋል
ማለት ነው። መሰማሪያ የተባለው ትምህርተ ወንጌል ነው፥
አንድም መከራ ነው፥ አንድም በመጨረሻ የሚወርሱት ክብረ
መንግሥተ ሰማያት ነው።
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስት
ዓመት ከሦስት ወር ካስተማራቸው በኋላ ይሰቀልላቸዋል
(ነፍሱን አሳልፎ ይሰጥላቸዋል)። «በጎቹም ይከተሉታል»፤
እርሱን አብነት አድርገው ወንጌልን ያስተምራሉ፥ መከራን
ይቀበላሉ፥ በመከራ ይመስሉታል። «ቃሉን ያውቃሉና።»
ትምህርቱን ተቀብለውታልና። «ሌላውን ግን ይሸሹታል እንጂ
አይከተሉትም፥ የሌላውን ቃሉን አያውቁምና።» ትንቢት
ሳይነገርለት፥ መጻሕፍት ሳይመሰክሩለት የመጣውን ግን ሌባ
ወንበዴም በመሆኑ አብነት አያደርጉትም፥ አይመስሉትም፤
ይነቅፉታል፥ ያወግዙታል እንጂ ትምህርቱን አይቀበሉም።
ጌታችን ይኽንን ምሳሌ ቢነግራቸውም እረኛ የተባለ እርሱ፥
አባግዕ የተባሉ ደግሞ እነርሱ እንደሆኑ አልገባቸውም።
ዳግመኛም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ፥ «እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የበጎች በር እኔ ነኝ።
ከእኔ በፊት የመጡ ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፥ ነገር ግን
በጎች አልሰሙአቸውም። እውነተኛው የበጎች በር እኔ ነኝ፥ በእኔ
በኲልም የሚገባ ይድናል፤» (ወደ ሃይማኖት ወደ ወንጌል
ይገባል)፤ «ይወጣልም፤» (ከፈቃደ ሥጋ ይወጣል፤ አንድም በጎ
ሥራ ለመሥራት ለማስተማር ይወጣል)፤ መሰማሪያም
ያገኛል። (መከራን ማለትም እስራቱን፣ ግርፋቱን፣ እሳቱን፣
ስለቱን፣ ያገኛል)። አንድም በጉባኤ ምእመናንን ያገኛል፤
አንድም ክብረ ሥጋን ክብረ ነፍስን ያገኛል)። ሌባ ግን ሊሰርቅና
ሊያርድ፥ ሊያጠፋም ካልሆነ በቀር አይመጣም። (ሌባው
ወንበዴው ግን በነፍስም በሥጋም ሊጐዳ ሊያጠፋ ነው እንጂ
ሊያለማ ሊጠቅም አይመጣም)። እኔ ግን የዘለዓለም ሕይወትን
እንዲያገኙ፥ እጅግም እንዲበዛላቸው መጣሁ።» አላቸው።
በበሩ የማይገባ ማለት ደግሞ፦ ትንቢት ሳይነገርለት፥ ሱባዔ
ሳይቆጠርለት፥ እግዚአብሔር አብ ሳይመሰክርለት፥ ቅዱሳን
መላእክትም ብሥራቱንም የምሥራቹንም ሳይናገሩለት የመጣ
ማለት ነው። ይኸውም እንደ ይሁዳ ዘገሊላ አንድም እንደ
ቴዎዳስ ዘግብፅ ነው። የአይሁድ ሸንጎ በቅዱሳን ሐዋርያት
ተቆጥተው ሊገድሉአቸው በወደዱ ጊዜ፥ በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ
የከበረ ስሙ ገማልያል የሚባል የኦሪት መምህር ነበረ።
እርሱም ቅዱሳን ሐዋርያትን ፈቀቅ እንዲያደርጉአቸው ካዘዘ
በኋላ፥ «እናንተ የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ በእነዚህ ሰዎች
በምታደርጉት ነገር ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ቀድሞም ከዚህ
ዘመን በፊት ቴዎዳስ ተነሥቶ ራሱን ከፍ ከፍ አደረገ፤ (እኔ
አምላክ ነኝ አለ)፤ አራት መቶ ሰዎችም ተከተሉት፥ ነገር ግን
እርሱም ጠፋ፥ የተከተሉትም ሁሉ ተበታተኑ፥ እንደ ኢምንትም
ሆኑ። ከእርሱም በኋላ ሰዎች ለግብር በተቈጠሩበት ወራት
ገሊላዊ ይሁዳ ተነሣ፥ ብዙ ሕዝብም ተከተሉት፥ እርሱም ሞተ፥
የተከተሉትም ሁሉ ተበታተኑ። አሁንም እላችኋለሁ፥ ከእነዚህ
ሰዎች (ከቅዱሳን ሐዋርያት) ራቁ፥ ተዉአቸውም፥ ይህ
ምክራቸው ይህም ሥራቸው ከሰው የተገኘ ከሆነ ያልፋል፥
ይጠፋልም። ከእግዚአብሔር የመጣ ከሆነ ግን ልታፈርሱት
አትችሉም፥ ከእግዚአብሔርም ጋር እንደሚጣላ አትሁኑ።»
ብሎአል። የሐዋ ፭፥፴፬፥፴፱።
፩፥፪፦ #ቸር_ጠባቂ_እኔ_ነኝ፤
ቅዱስ ዳዊት እግዚአብሔር እረኛ ጠባቂ መሆኑን ሲናገር፦
«እግዚአብሔር ይጠብቀኛል፥ የሚያሳጣኝም የለም።
በለመለመ መስክ ያሳድረኛል፥ በዕረፍት ውኃ ዘንድ አሳደገኝ፤»
ብሎአል። መዝ ፳፪፥፩። ቸር እረኛ የጠፋውን በግ እስኪያገኘው
ድረስ ይፈልገዋል። ይኽንንም፦ «የሰው ልጅ (ወልደ ዕጓለ
እመሕያው ክርስቶስ) የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን
መጥቶአልና። ምን ትላላችሁ? መቶ በጎች ያለው ሰው ቢኖር፥
ከመካከላቸውም አንዱ ቢጠፋው፥ ዘጠና ዘጠኙን በተራራ ላይ
ትቶ የጠፋውን ሊፈልግ ይሄድ የለምን? እውነት እላችኋለሁ፥
ባገኘው ጊዜ ካልጠፉት ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ ጠፍቶ ስለተገኘው
ፈጽሞ ደስ ይለዋል፤» በማለት ነግሮናል። ማቴ ፲፰፥፲፩-፲፫።
እግዚአብሔር ቅዱሳን መላእክትን የፈጠራቸው በነገድ መቶ
አድርጎ ነበር። አንደኛው ነገድ (የሳጥናኤል ነገድ) በክህደት
በመጉደሉ ምክንያት አዳም መቶኛ ሆኖ ተቈጥሯል።
በመሆኑም የጠፋው በግ የተባለው አዳም ነው። ነቢዩ
ኢሳይያስም፦ «እነሆ እግዚአብሔር በኃይሉ ይመጣል፥
በክንዱም (በሥልጣኑ፥ በባህርይ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ)
ይገዛል፥ እነሆ ዋጋው ከእርሱ ጋር ሥራውም በፊቱ ነው።
መንጋውን እንደ እረኛ ይመራል፥ ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ
በብብቱ ይሸከማል፥ የሚያጠቡትንም በቀስታ ይመራል።»
በማለት እርሱ አምላካችን የሕይወታችን እረኛ እንደሆነ
ተናግሯል። ኢሳ ፵፥፲፩። ነቢዩ ሕዝቅኤል ደግሞ፦ «ጌታ
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ እኔ ራሴ በጎቼን እሻለሁ፥
እጎበኛቸዋለሁ። ከአሕዛብም ዘንድ አወጣቸዋለሁ፥ ከሀገሮችም
ሁሉ እሰበስባቸዋለሁ፥ ወደ ገዛ ሀገራቸውም አመጣቸዋለሁ፥
በእስራኤልም ተራሮች ላይ፥ በፈሳሾችም አጠገብ፥ በምድርም
ላይ ሰዎች በሚኖሩባት ስፍራ ሁሉ አሰማራቸዋለሁ።
በመልካም ማሰማርያ አሰማራቸዋለሁ፥ ጉሮኖአቸውም
በረዥሞቹ በእስራኤል ተራሮች ላይ ይሆናል፥ በዚያ በመልካም
ጉረኖ ውስት ይመሰጋሉ፥ በእስራኤልም ተራሮች ላይ በለመለመ
መሰማሪያ ይሰማራሉ። እኔ ራሴ በጎቼን አሰማራለሁ፥
አስመስጋቸውማለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደሆንሁ
ያውቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የጠፋውንም እፈልጋለሁ፥
የባዘነውንም እመልሳለሁ፥ የተሰበረውንም እጠግናለሁ፥
የደከመውንም አጸናለሁ፥ የወፈረውንና የበረታውንም
እጠብቃለሁ፥ በፍርድም እጠብቃቸዋለሁ።» ብሏል። ሕዝ
፴፬፥፲፩-፲፮።
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጎቹን
ፍለጋ የመጣ ቸር እረኛ በመሆኑ፥ «ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ፥ ቸር
ጠባቂ ስለ በጎቹ ነፍሱን ይሰጣል። ጠባቂ ያይደለ፥ በጎቹም
ገንዘቡ ያይደሉ ምንደኛ ግን ተኲላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ
ይሸሻል፥ ተኲላም መጥቶ በጎቹን ይነጥቃቸዋል፥
ይበትናቸዋልም። ምንደኛስ ይሸሻል፥ ስለ በጎቹም አያዝንም፥
(የምእመናን ጥፋት አያሳዝነውም)፥ ምንደኛ ነውና። (ሥጋዊ፥
ዓለማዊ በመሆኑ መናፍቅ ጳጳስ፥ አላዊ ንጉሥ በተነሣ ጊዜ
ይክዳል፤ ምዕመናንን አሳልፎ ይሰጣቸዋል፥ ሐሰተኛ ነውና)።
ቸር ጠባቂ (እውነተኛ መምህር) እኔ ነኝ፥ የእኔ የሆኑትን
መንጋዎቼን (ወልድ ዋሕድ ብለው ያመኑብኝን) አውቃለሁ፥
የእኔ የሆኑትም ያውቁኛል፤ (በእኔ ያመኑብኝ እኔን አብነት
አድርገው መከራን ይቀበላሉ)፤ ብሏል።
፩፥፫፦ #አብ_እኔን_እንደሚያውቀኝ _እኔም_አብን
#አውቀዋለሁ፤
አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ህልዋን ናቸው። አብ በወልድ
በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነው፥ ወልድም በአብ በመንፈስ ቅዱስ
ህልው ነው፥ መንፈስ ቅዱስም በአብ በወልድ ህልው ነው።
«እኔ በአብ እንዳለሁ፥ አብም በእኔ እንዳለ እመኑ፤» ብሏል።
ዮሐ ፲፩፥፲፩። በስም በአካል በግብር ሦስት የሆኑ ሥላሴ
በህልውና አንድ እንደሆኑ ሁሉ በመለኰት፥ በሥልጣን፥
በባህርይ፥ በፈቃድ አንድ ናቸው። «እኔና አብ አንድ ነን፤» ያለው
ለዚህ ነው። ዮሐ ፲፥፴። እንግዲህ፥ አይሁድ በክፋታቸው «ይህ
ከወዴት እንደመጣ፥ ማን እንደሆነ አናውቅም፤» ብለውት
ስለነበረ፥ እናንተ ባታውቁኝ የባህርይ አባቴ አብ ያውቀኛል፥
እንደማለት፥ «አብ እኔን እንደሚያውቀኝ እኔም አብን
አውቀዋለሁ፤» ብሎባቸዋል። ይኸውም፦ «እኔ ልሰቀል ልሞት
መምጣቴን አብ እንደሚያውቅ ሁሉ እኔም የመጣሁበትን
ዓላማ አውቃለሁ፤» ሲል ነው። ለዚህ ነው ከዚያው አያይዞ፥
«ለበጎችም ቤዛ አድርጌ ሰውነቴን አሳልፌ እሰጣለሁ፤»ያለው።
በማቴዎስ ወንጌልም፦ «ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቀው
የለም፤ (ያለ አብ ወልድን በባሕርዩ የሚያውቀው የለም፥
በባሕርይ አንድ ናቸውና)፤ አብንም ከወልድ በቀር፥ ወልድም
ሊገልጥለት ከሚፈቅደው በቀር የሚያውቅ ማንም የለም።
(ያለ ወልድ አብን በባሕርዩ የሚያውቀው የለም)፤» የሚል
አለ። ማቴ ፲፩፥፳፯።
ትንቢት ተነግሮለት፥ ሱባዔ ተቆጥሮለት፥ ወደዚህ ዓለም የመጣ
ቸር እረኛ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ «ከዚህ ቦታ ያይደሉ ሌሎች
በጎችም አሉኝ፤ (በኢየሩሳሌም የሌሉ በአራቱ ማዕዘን ያሉ
ሌሎች አሉኝ)፤ ቃሌንም ይሰሙኛል፤ (ትምህርቴን
ይቀበሉኛል)፤ ለአንድ እረኛ አንድ መንጋም ይሆናሉ። (ለአንድ
ለክርስቶስ አካሉ ይሆናሉ፤ አንድም ለአንድ ሊቀ ጳጳስ አንድ
ማኅበር፥ አንድ ቤተሰብእ ይሆናሉ)፤ ብሎአል። ይህም ወደዚህ
ዓለም መምጣቱ ለቤተ አይሁድ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም
መሆኑን ያስተምረናል።
፩፥፬፦ #ሥልጣን_አለኝ፤
ነፍስንም ሥጋንም ከእመቤታችን ነስቶ (ወስዶ) በተዋሕዶ ሰው
የሆነ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ዓለምን ለማዳን መከራ
የተቀበለው፥ የሞተውም በፈቃዱ ነው። ይህም ይታወቅ ዘንድ፦
«ስለዚህም አብ ይወድደኛል፤» ካለ በኋላ «እንደ ገና አስነሣት
ዘንድ እኔ ነፍሴን እአጣለሁና። ከእኔ ማንም አይወስዳትም፤
ነገር ግን እኔ በፈቃዴ እሰጣታለሁ፥ እኔ ላኖራት ሥልጣን አለኝ፤
(ነፍሴን በገነት፥ ሥጋዬን በመቃብር ላኖራቸው ሥልጣን አለኝ)፤
መልሼ እወስዳት ዘንድ ሥልጣን አለኝ። (ነፍሴን ከሥጋዬ
አዋሕጄ በማስነሣት፥ በዕርገት፥ በየማነ አብ፥ በዘባነ ኪሩብ
አስቀምጣት ዘንድ ሥልጣን አለኝ)፤ ብሏል። መከራውን፥
ትንሣኤውን እና ዕርገቱን በተመለከተም ነቢያት አስቀድመው
ተናግረውታል።
- «እርሱ ስለ ኃጢአታችን ቈሰለ፥ ስለበደላችንም ታመመ፤
የሰላማችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቊስል እኛ
ተፈወስን። . . . እግዚአብሔርም ስለ ኃጢአታችን ለሞት
አሳልፎ ሰጠው።» ኢሳ ፶፫፥፭-፮።
- «እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ፤» መዝ
፸፯፥፷፭።
- «እግዚአብሔር በእልልታ፥ ጌታችንም በመለከት ድምፅ
አረገ።» መዝ ፵፮፥፭።
በመጨረሻ የምንመለከተው፥ ጌታችን አምላካችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «እውነተኛ የበጎች በር እኔ
ነኝ፤»ያለበትን ዋና ምክንያት ነው። ይኸውም በር የተከፈተለት
እንደሚገባ፥ የተዘጋበት ደግሞ በአፍአ እንደሚቀር ሁሉ፥
በጌታችን ያመነ የመንግሥተ ሰማያት በር ይከፈትለታል፥
ያላመነበት ደግሞ በሩ ተዘግቶበት በአፍአ እንደሚቀር ነው።
በመሆኑም በር የተባለው በእርሱ ላይ ያለን እምነት እንደሆነ
ከትርጓሜው እንረዳለን። የበሩንንም ቊልፍ ለቅዱሳን
አስረክቧል። ይኸውም ይታወቅ ዘንድ ቅዱስ ጴጥሮስን «አንተ
ብፁዕ ነህ፥ በሰማይ ያለው አባቴ ነው እንጂ ሥጋና ደም ይህን
አልገለጠልህምና። እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ዐለት ነህ፥ በዚያች
ዐለት ላይም ቤተክርስቲያኔን እሠራታለሁ፥ የሲኦል በሮችም
(ደጅ ጠባቂ አጋንንት) አይበረቱባትም። የመንግሥተ ሰማያትም
መክፈቻ እሰጥሃለሁ፥ በምድር የምታስረው በሰማይ የታሰረ
ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው በሰማይ የተፈታ ይሆናል።»
ብሎታል። ማቴ ፲፮፥፲፯-፲፱። ሌሎችን ግን፦ «መንግሥተ
ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ ወዮላችሁ! እናንተም
አትገቡም፥ የሚገቡትንም ከመግባት ትከለክላላችሁ።»
ብሏቸዋል። ማቴ ፳፫፥፲፬። ስለዚህ በር በተባለ በኢየሱስ
ክርስቶስ ፈጽመን ልናምን ይገባል። እናምናለን ማለት ብቻም
ሳይሆን የምናምነውስ ማን እና ምን ብለን ነው ማለትም
ያስፈልጋል። ምክንያቱም ስሙን እየጠሩ፥ እንምንበታለን
እያሉ፥ ስለ እርሱ የሚያስተምሩት ትምህርት ፈጽሞ መስመር
የለቀቀባቸው ብዙዎች ናቸውና። የእኛ ግን መስመሩን
የጠበቀው ፍጹም እምነታችን እንደሚከተለው ነው።
፩ኛ፦ #ፈጣሪ_ነው፥ ብለን እናምንበታለን። «ሁሉም በእርሱ
ሆነ፥ (በእርሱ ተፈጠረ)፥ ከሆነውም (ከተፈጠረውም) ሁሉ ያለ
እርሱ ምንም የሆነ የለም። ዮሐ ፩፥፫።
፪ኛ፦ #የፈጠረውን_ፍጥረት_የሚገ ዛ_የባሕርይ አምላክ ነው።
«የእግዚአብሔር ልጅ እንደመጣ፤ እውነተኛም የሆነውን
እግዚአብሔርን እናውቅ አንድ ልቡናን እንደሰጠን እናውቃለን፤
እውነተኛውም በሆነው በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ
በማመን እንኖራለን፤ እርሱም እውነተኛ አምላክና የዘለዓለም
ሕይወት ነው።» ፩ኛ ዮሐ ፭፥፳።
፫ኛ፦# ፈጣሪ፥ የባሕርይ አምላክ በመሆኑም እግዚአብሔር
ነው። «በመጀመሪያ ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ
(በፈጣሪነት ከአብ ተካክሎ) ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ።
ይህም በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ (በፈጣሪነት
ከመንፈስ ቅዱስም ተካከልሎ) ነበረ። . . . ያም ቃል ሥጋ ሆነ፥
በእኛም አደረ፤ (ነፍስንና ሥጋን ነስቶ በተዋሕዶ ሰው ሆነ)።»
ዮሐ ፩፥፩፣ ፩። «አሁንም በገዛ ደሙ የዋጃትን
የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ትጠብቁ አንድ መንፈስ ቅዱስ
እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ
ተጠንቀቁ፤» የሐዋ ፳፥፳፰።
፬ኛ፦ #ወልድ_በተለየ_አካሉ_ከሰ ማይ_ወርዶ፥ በተዋሕዶ ሰው
ሆኖ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በመወለዱ
በሥልጣን ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ አላነሰም። «እኔና አብ አንድ
ነን፤» ዮሐ ፲፥፴። በሕልውናም አንድ ነው። «እኔ በአብ
እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑ፤» ዮሐ ፩፥፲፩። «እኔን
የሚጠላ አቤን ይጠላል። . . . አሁን ግን እኔንም አባቴንም
አይተዋል፥ ጠልተውማል።» ዮሐ ፲፭፥፳፫።
፭ኛ፦ #ከእመቤታችን_ከቅድስት_ድ ንግል
#ማርያም_ከሥጋዋ_ሥጋ_ከነ ፍሷም_ነፍስ_ነስቶ የተወለደ
እርሱ የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ ነው። «እነሆም፥ በእርሱ
ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው።» ማቴ ፫፥፩።
፮ኛ፦ #ሰው_የሆነው_በተዋሕዶ_ነ ው፥ በመሆኑም ከተዋሕዶ
በኋላ ሁለትነት የለም፥ ይህ የሥጋ ነው፥ ይህ ደግሞ የመለኰት
ነው ተብሎ መከፈል የለበትም። አብ «ልጄ ነው፤» ያለው
በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ የሆነውን ኢየሱስ
ክርስቶስን ነው። ወደ ሠርግ ቤት የተጠራውም ውኃውን ወደ
ወይን ጠጅ የለወጠውም ከተዋሕዶ በኋላ ሁለትነት የሌለበት
አንድ እርሱ ነው። ዮሐ ፪፥፩-፲። ሥጋን እንደተዋሐደ
ለማጠየቅ «አልዓዛርን የት ቀበራችሁት?» ያለም ከሞት
ያስነሣም አንድ እርሱ ነው። ዮሐ ፲፩፥፴፬፣፵፫። ከዚህም ሌላ
መቃብሩ ሳይከፈት ከመቃብር የወጣው (ሞትን ድል አድርጐ
የተነሣው) አንዱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ማቴ
፳፯፥፷፮፣፳፰፥፩። በተዘጋ ቤትም በሩ ሳይከፈት ከአንዴም ሁለት
ጊዜ የገባው አንዱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ዮሐ ፳፥፲፱፣፳፮።
፯፦ #ኢየሱስ_ክርስቶስ_ፈራጅ_ ዳኛ ነው። «አሁንም
በእግዚአብሔር ፊትና በመንግሥቱ በሚመጣበት ጊዜ፥
በሕያዋንና በሙታን ይፈርድ ዘንድ ባለው በጌታችን በኢየሱስ
ክርስቶስ እመክርሃለሁ። . . . እንግዲህስ የጽድቅ አክሊል
ይቆየኛል፥ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው እግዚአብሔር በዚያ
ቀን ለእኔ ያስረክባል።» ፪ኛ ጢሞ ፬፥፩፣፰።
፰፦ #እኛ_የምንለምነውን_በቅዱ ሳንም_ጸሎት
የምናስለምነውን ሁሉ እርሱ ያደርገዋል። «እኔ ወደ አብ
እሄዳለሁና፤ አብ በወልድ ይከብር (ይገለጥ) ዘንድ በስሜ
የምትለምኑትን ሁሉ አደርግላችኋለሁ። በስሜ የምትለምኑት
ነገር ቢኖር ያን አደርግላችኋለሁ።» ዮሐ ፲፬፥፲፪-፲፫።
እንግዲህ ሥጋን መዋሐዱን ለማጠየቅ የተናገረውን ቃል፥
አብነት ለመሆንም የሠራውን የትህትና ሥራ ሁሉ በትርጓሜ
እያስታረቅን በትክክለኛው እምነት ጸንተን ልንቆም ይገባናል።
በአምልኮታችን ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስን፥ እንደ ቅዱስ
እስጢፋኖስ፥ ከአብ ተካክሎ ልናየው ይገባል እንጂ ዝቅ
ልናደርገው አይገባም። «እነሆ ሰማይ ተከፍቶ፥ የሰው ልጅም
በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ፤» ይላል። ጸሎታችንም፦
ጌታዬ ኢየሱስ ሆይ፥ ነፍሴን ተቀበል፤ . . . አቤቱ ይህን ኃጢአት
አትቊጠርባቸው፤» የሚል መሆን አለበት። የእግዚአብሔር
ቸርነት፥ የድንግል ማርያም አማለጅነት አይለየን። አሜን።

=>+*"+<+>+ ሰርግ በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትምህርት +<+>+"*+

ሰርግ በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትምህርት
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ቅዱስ ጳውሎስ ለቈላስይስ ሰዎች
በላከው መልእክት ም.፬፥፲፪ ላይ ያለውን ኃይለ ቃል
በተረጎመበት ፲፪ኛው ድርሳኑ በዘመኑ የሚፈጸመውን የሰርግ
ሥርዐት መሠረት በማድረግ ሰርግን አስመልክቶ ሰፋ ያለ
ትምህርትን ሰጥቶአል ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በሰርግ
ምክንያት የሚወጡትን ወጪዎችና ግርግርና ሁካታ አጥብቆ
የሚቃወም አባት ነው ፡፡ በዚህም ጽሑፍ ይህን ወደማስተዋል
ልንመጣም እንችላልን ፡፡ መልካም ንባብ
ስለዚህ እንዲህ ብሎ ያስተምራል ፡- ትዳር ምንድን ነው?
ትዕይንት(ትያትር) ነውን ? አይደለም፡፡ ምንም እንኳ እናንተ
ለትዳርና ለምሳሌው አክብሮት ባይኖራችሁ ትዳር ግሩም
ምሥጢርና የታላቅ መንፈሳዊ ምሥጢር ምሳሌ ነው ፡፡ ቅዱስ
ጳውሎስ ስለዚህ ሲያስተምር “ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው”
ይልና ጨምሮ “እኔ ግን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን
እላለሁ” ይላል ፡፡(ኤፌ.፭፥፴፪) ጋብቻ የቤተ ክርስቲያንና
የክርስቶስ ምሳሌ ነው ፤ እንዲህ በከበረ ምሥጢር ላይ
ዳንኪረኞችን በመጋበዝ ዝሙትን ታስተዋውቁበታላችሁን ?
ነገር ግን ከእናንተ መካከል አንዱ እኔን፡- እንዲህ ስትል ደናግል
ወይም ያገቡት አይጨፍሩ እያልክ ነው ፤ እንግዲያ እነርሱ በዚህ
ሰርግ ላይ ካልጨፈሩ ማን ሊጨፍር ነው ? ብሎ ሊጠይቅ
ይችላል ፡፡ ማንም አይጨፍር ነው መልሴ ፡፡
በአሕዛብ ዘንድ ይህን በመሰሉ ሥርዐቶቻቸው ዳንኪረኞች
ዳንኪራቸውን ያቀርባሉ፡፡ በእኛ ግን ማንኛውም ምሥጢራት
ሲከናወኑ በጸጥታ፣ በትሕትናና በጥሩ ሥነምግባር እንዲሁም
በመልካም ሥርዐት ነው፡፡ ይህ የጋብቻ ሥርዐት አመንዝሮች
ከተጠሩበት እግዚብሔርን የማይፈሩ ከተጋበዙበት እንዴት ብለን
ነው መንፈሳዊ ጋብቻ ብለን ልንጠራው የምንችለው ? እንዲህ
ከሆነ እንዴት ተብሎ ነው ሁለቱ አካላት አንድ ሆነዋል ልንል
የምንችለው ?
ክርስቶስ በተገኘበት ጋብቻ ግን ዳንኪራ የለም የእምቢልታም
ድምፅ አይሰማበትም፡፡ ነገር ግን ግሩም የሆነ ጸጥታ
የሰፈነበት፣ በታላቅ መንፈሳዊ ሥርዐት የሚከናወን ነው፡፡ በዚህ
ሥርዐት አንድ አካል ወደመሆን ሲመጡ አንድነታቸው ሕይወት
አልባ ፍጥረታት እንደሚኖራቸው አንድነት ወይም በዚህ ምድር
የሚታየውን ዓይነት አንድነት አይደለም፡፡ ነገር ግን
የእግዚአብሔር አርዓያና አምሳል ሆነው አንድ ይሆናሉ፡፡ ይህ
ታላቅ የሆነ ምሥጢር በሚከናወንበት ሥፍራ እንደ አራዊት
ታላቅ ሁካታና ረብሻ እንዲሁም ነፍስን የሚያሳድፉ ታላቅ የሆነ
በደል ይፈጸማልን ?
ሁለቱ አንድ አካል በመሆናቸው በዚህ ያለውን የፍቅርን
ምሥጢር አስተውል ፡፡ እነዚህ ሁለት አካላት ሁለትነታቸውን
ይዘው የሚቀጥሉ ከሆነ ብዙ ሊሆኑ አይችሉም ፡፡ ነገር ግን
አንድ ወደመሆን ሲመጡ ብዙዎች ይሆናሉ ፡፡ ከዚህ ምን
እንማራለን ? የትዳርን ታላቅነት አይደለምን ? ሥላሴ ሁለት
የሆነው አካል አንድ አድርጎ ፈጠረው ስሙንም ሰው አለው፡፡
ይህን አንድ የሆነው አካልንም ሁለት በማድረግ ገለጠው ፡፡
ምንም እንኳ እነዚህ አካላት ሁለት ቢሆኑ የእግዚአብሔር ፈቃድ
ግን አንድ ይሆኑ ዘንድ ነበር ፡፡
በዚህም ምክንያት አንዱ አምሳሉን ለመውለድ ብቻውን ብቁ
እንዲሆን አላደረገውም ፡፡ ስለዚህ ከተቃራኒው አካል ጋር
አንድነትን ላልመሠረተ ሰው አንድ አካል የሚባለው ስያሜው
አይሰጠውም ነገር ግን የሌላኛው ግማሽ አካል ይባላል ፡፡
ለዚህም ምስክሩ ልጅን መውለድ አለመቻሉ ነው ፡፡ ይህ
እግዚአብሔር አስቀድሞ የሠራው ሥርዐት ነው፡፡ የጋብቻን
ምሥጢር አስተዋላችሁን ? አስቀድሞ አንድ አድርጎ ፈጠራቸው
በኋላም ነጣጠላቸው ፤ እንደገና ሁለት የነበሩትን እነዚህን
ወገኖች ወደ አንድነት አመጣቸው ፡፡ እንዲህም አድርጎ
ስለሠራው ሰው በትዳር አንድ ከሆኑ ወገኖች እንዲፈጠር ሆነ ፡፡
ባልና ሚስት ሁለት አካላት አይደሉም ነገር ግን አንድ አካል
ናቸው ፡፡…. ይህን “ሰውን በአርዓያችንና በአምሳላችን እንፍጠር
…ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” (ዘፍ.1፡27) በሚለው ቃል
ማረጋገጥ ይቻላል ፡፡ ባል ራስ ነው ፤ ሚስት ደግሞ ቀሪው
አካል ናት ፡፡ ስለዚህ አንዱ የደቀመዝሙርነት ማዕረግ ሲኖረው
አንዱ የመምህርነት ቦታ ይይዛል አንዱ መሪ ሲሆን ሌላው
ደግሞ ታዛዥ አደረገው ፡፡ ሔዋን ከአዳም ጎን ትገኝ እንጂ ወደ
ኋላ መለስ ብለን የእርሱዋን ልደት ስንመረምረው አንድ አካል
እንደነበሩ ማስተዋል እንችላለን ፡፡በዚህ ምክንያት አንድ አካል
እንደሆኑ ለማስረዳት ሲል እግዚአብሔር አምላክ ሴቲቱን ረዳት
አላት፡፡ (ዘፍ.2፡18) በአንድነት ከመኖራቸውና አባትና እናት
ከመሆን ባለፈ አንድ አካል በማድረግ አከበራቸው፡፡ (ዘፍ.2፡
24)
በሌላ መልኩ ደግሞ አባት ወንድ ልጁ ወይም ሴት ልጁ
የራሳቸውን አካል አግኝተው በመጣመራቸው እጅግ ደስ
ይሰኛል፡፡ አባት ምንም ሀብት የተረፈው ባለጠጋ ቢሆን ወንድ
ልጁ ወይም ሴት ልጁ ያላገቡ ከሆኑ ውስጡ ምንም ዓይነት
መረጋጋት አይኖረውም፡፡ ይህን ታግሶ መኖርም አይቻለውም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ምንም ልጅ ከእናቱ አካል ተከፍሎ
የተወለደ ቢሆን በዚህ ምድር ዘሩ እንዲቀጥል ብቻውን በቂ
አይደለም፡፡ ስለዚህም በራሱ ሙሉ አይደለም ማለት ነው፡፡
ስለዚህም ነቢዩ ሚልክያስ “እግዚአብሔር የሕይወትን መንፈስ
አንድ አድርጎ ጠብቆልን የለምን? እርሱም የሚፈልገው
ምንድን ነው? ዘር አይደለምን? (ሚል.፪፥፲፭) ይለናል፡፡
እንዴት ነው ታዲያ አንድ ሥጋ ወደ መሆን የሚመጡት ? እጅግ
ንጹሕ የሆነን ወርቅን ማግኘት ከፈለግህ ወርቅህን ከሌላ
ወርቅ ጋር ትቀይጠዋለህ፤ ከእነዚህም አንድነት ልዩ የሆነ
ወርቅ ይገኛል፡፡ በዚሁ መልክ እናት በደስታ ዘርን ተቀብላ
ከራሱዋ ጋር በማዋሐድ፣ ፅንሱን በመመገብና እንክብካቤ
በማድረግ ሰው ሆኖ ወደዚህ ዓለም እንዲመጣ የራሱዋን ድርሻ
ትወጣለች፡፡ልጅ እንደ ድልድይ ነው ፡፡ በእርሱም ምክንያት
ሦስቱ አንድ ሥጋ ይባላሉ ፡፡ ልጅ ሁለቱ አካላት ፍጹም አንድ
እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ፡፡ በመካከላቸው ባለው ታላቅ ወንዝ
ምክንያት የተለያዩ ከተሞች በወንዙ ላይ በሚሠራው ድልድይ
ምክንያት ሁለት መሆናቸው ቀርቶ አንድ እንዲሆኑ እንዲሁም
ልጅም እንዲህ ነው ፡፡
ልጅ በፊት በባልና በሚስት መካከል የተፈጠረውን አንድነት
ይበልጥ ያጠናክረዋል ፡፡ ለባልና ሚስት ድልድይ የሆነው ልጅ
የሁለቱ ተዋሕዶ ውጤት ነውና ፡፡ ራስና ቀሪው አካል በአንገት
አንድ እንዲሆን ፣ እንዲሁ ልጅም በባልና በሚስት መካከል ሆኖ
በእነርሱ መካከል ያለውን አንድነት ይበልጥ ያጠብቀዋል ፡፡
ከልዩነታቸው ይልቅ አንድነታቸውን በልጅ ምክንያት ይበልጥ
እየጠበቀ ይመጣል ፡፡
እንዲሁም ዘማርያን በአንድነት ሲዘምሩ ዝማሬው አንድ ሆኖ
ይወጣል ፡፡ ወይም ሁለት ወገኖች እጃቸውን እርስ በእርሳቸው
ቢያቆላልፉ ከእንግዲህ አንድ እንጂ ሁለት አይደለንም
ማለታቸው እንደሆነ እንዲሁ ባልና ሚስትም በአንድነታቸው
በሚፈጠሩት በልጅ በኩል ፍጹም የሆነ አንድነትን ይመሠርታሉ
፡፡ ስለዚህ ጌታችን ግሩም በሆነ ቃሉ “ሁለቱም አንድ ሥጋ
ይሆናሉ አለ” በተለይ በልጆቻቸው ፡፡ እንዲህ ሲባል ባልና
ሚስት ልጅ ካልወለዱ ሁለት እንደሆኑ አይቀጥሉም ማለት
ነውን ? በፍጹም አይደለም ፤ ሁለቱ በሥጋ ሲተባበሩ አንድ አካል
ወደ መሆን ይመጣሉ ፡፡ የሽቶ ዘይትን ከሌላ የሽቶ ዘይት ጋር
ሲደባልቁት አንድ እንዲሆኑ ከተቀየጡም በኋላ አንድ የሽቶ
ዘይት እንዲሆኑ እንዲሁ በዚህም እንዲሁ ነው ፡፡
እኔ አሁን እንዲህ በግልጽ ስለዚህ ጉዳይ በመናገሬ አንዳንዶች
ነውር ነው በማለት ትምህርቴን እንደሚጠየፉት እረዳለሁ ፡፡
ለዚህ ምክንያቱ ምንድነው ? ይህን አሁን የምናገረውን እንደ
ብልግና ንግግር ስለሚቆጥሩት ነው ፡፡እነዚህ ወገኖች በትዳር
ውስጥ የሚፈጠረውን እንደዚህ ላለው አንድነት ልዩ የነቀፋ ስም
ይሰጡታል (ብልግና ይሉታል) ፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ጳውሎስ
“መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ
ይሁን”(ዕብ.፲፫፥፬) ብሎ አስተምሮናል ፡፡
ስለምን እናንተ ክቡር የሆነውን እንደ ነውር ፣ ንጹሕ የሆነውን
እንደ ርኩስ ትቆጥሩታላችሁ ? ይህ ጋብቻን እንደ ርኩሰት
የሚቆጥሩትና በራሳቸው አካል ላይ ዝሙትን የሚፈጽሙ
የከሃድያን አመለካከት ነው፡፡ ስለዚህም ነው ይህን ክፉ
አስተሳሰብ ለማጥራትና ወደ ቀድሞው ክብሩ ለመመለስ ስል
በዚህ መልክ ያስተማርኩት፡፡ በዚህም እስተምህሮ የከሃድያን
አፍ ይዘጋል፡፡
እነርሱ የእግዚአብሔርን ድንቅ ስጦታንና የልደታችን መሠረት
የሆነውን ተራክቦን ሲነቅፉት ይሰማሉ፡፡
ይህን የመገኛችን ምንጭ የሆነውን ተራክቦ እንደ ቆሻሻና
እንደማይጠቅም ረብ የለሽ ከንቱ ነገር አድርገው ይቆጥሩታል፡፡
ስለዚህ እኛ ይህን አስተምህሮ ከዚህ ዓይነት አመለካከት ንጹሕ
ልናደርገው ይገባናል፡፡ተወዳጆች ሆይ ይህ ጉዳይ ሲነሣ
እንደሚጠየፉት ከሃዲያን እንድንሆን አልሻም፤ ይልቁንስ
ከእነርሱ አጸያፊ ሥራ ትሸሹ ዘንድ እመክራችኋለሁ፡፡ ነገር ግን
በዚህ እነርሱን የምትመስሉዋቸው ከሆነ በቀጥታ
እግዚአብሔርን እየተሳደባችሁ ነው፡፡
ትዳር ለቤተ ክርስቲያን የተፈጸመላት ምሥጢር ምሳሌ
እንደሆነ ላስረዳችሁን? ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
ቤተ ክርስቲያንን የራሱ ሲያደርጋትና በመንፈሳዊ ተዋሕዶ
ከእርሱዋ ጋር አንድ ሲሆን ቅዱስ ጳውሎስ “እንደ ንጽሕት
ድንግል” ይልና “እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ
አጭቻችኋለውና” ይለናል፡፡ (፪ቆሮ.፲፪፥፪) ታዲያ እኛ ምን
ሆንን ? የእርሱ የአካል ሕዋሳቶችና “ሥጋው” ሆንን፡፡ ይህን
ሁሉ በማስተዋል ታላቅ ምሥጢር የሆነውን ትዳርን ከማቃለል
እንቆጠብ፡፡ ሰርግ ማለት የክርስቶስ በሰዎች መካከል
ሰለመገኘቱ የሚመሰልበት ታላቅ ምሥጢር ነው፡፡ ታላቅ
የሆነው ይህ ምሥጢር በሚፈጸምበት ቦታ ስካር የሚገባ
ነውን? ንገረኝ የንጉሥ ምስል በቆመበት ስፍራ ሆነህ እርሱን
ማዋረድ ትጀምራለህን? ይህን ፈጽሞ አታደርገውም፡፡
አሁን ግን ሰርግ ሲሲረግ ሰርጉ ለተመሰለበት ምሳሌ ተገቢውን
አክብሮት ከመስጠት ይልቅ ቦታውን የኃጢአት መፍለቂያ
ምንጭ አድርገነዋል፡፡ ሥርዐቱ ሙሉ ለሙሉ ተለውጦ
ሕገወጥ ሥራዎች የሚፈጸሙት ሥርዐት ሆኗል፡፡ ቅዱስ
ጳውሎስ “የሚያሳፍር ነገርም የስንፍና ንግግርም ወይም ዋዛ
የማይገቡ ናቸው” አላለንምን? እንዲሁም “ለሚሰሙት ጸጋን
ይሰጥ ዘንድ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም
በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ
አይውጣ፡፡” (ኤፌ.፭፥፬፤፬፥፳፱) ብሎ አላስተማረንምን? አሁን
ግን በዚህ ታላቅ በሆነ ምሥጢር ላይ የስንፍና ንግግር፣ ዋዛ
ፈዛዛ ነገሮች፣ ፌዝና ቀልዶች ሞልተውበታል፡፡
እነዚህ ከንቱ ነገሮች በቀላሉ የሚቀርቡም አይደሉም እኮ
እነዚህ ከንቱ ነገሮች እንደ ጥበብ ተቆጥረው በአቅራቢዎቻቸው
ተቀናብረው በሰርጉ ለታደሙት ይቀርባሉ፡፡ ይህንንም
ለሚያቀርቡ ሰዎችም ታላቅ ክብርና ምስጋና ይሰጣቸዋል፡፡
ይገርማል ኃጢአት እንደ ጥበብ ተቆጠረ፡፡ ከዚህም በላይ
ኃጢአትን ለእኛ የሚያስተዋውቁንን ወገኖች ትዕይንት
የምንከታተለው ትኩረት ሰጥተንና በጸጥታ ነው፤ ከአንደበታቸው
የሚያወጡትንም ቃል በአጽንዖት በመስማት ጭምር እንጂ
እንዲያው በከንቱ አናዳምጣቸውም፡፡ ስለዚህ ዲያብሎስ በዚህ
የሰርግ ቤት ለእርሱ ወታደሮች ይሆኑ ዘንድ ሠራዊቶችን
ይመለምላል፡፡ ስካር ባለበት ቦታ ዝሙት አለ፡፡ ከንቱ ንግግር
ባለበት ቦታ ሰይጣን የራሱን አስተዋጽኦ ለማድረግ ይመቸዋል፡፡
እስቲ ንገረኝ እንዲህ በሆነ ቦታ ሰይጣን እንዲገኝ እየጋበዝህ
ክርስቶስ የሚገኝበትን ምሥጢር እየፈጸምኩ ነው ትላለህን?
አንተ እኔን ለዚህ ነገር ጠንካራ ተቃዋሚ እንደሆንኩ አድርገህ
ትቆጥረኛለህ ፡፡ ከዚህ ጥመትህ ትድን ዘንድ አንተን በጽኑ
የሚገሥጽህንም ሰው እንዲህ እንድትመለከተው አውቃለሁ ፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ አንተን “የምትበሉም የምትጠጡም ብትሆኑ
ወይም ማናቸውም ተግባር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር
ክብር አድርጉት”(፩ቆሮ.፲፥፴፩ ) አላለህምን ? አንተ ግን
ሥራዎችህን ሁሉን ራስህን ለማዋረድና የሰውን ልጅ ለሚጎዱ
ነገሮች ታውላዋለህ ፡፡ ነቢዩስ “ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ
በረዓድም ደስ ይበላችሁ”(መዝ.፪፥፲፩) አላለህምን ? አንተ
ግን ሥርዐት አልባ ሆነህ ትመላለሳለህ ፡፡
በአንድ ጊዜ ደስታውንና ጥንቃቄውንም ማስኬድ
ትፈልጋላችሁን? አጥንትን የሚያለመልም መዝሙርን
መስማትስ ትሻላችሁን? በእርግጥ ከመዝሙሮች ሁሉ የሚልቅ
መዝሙርን ልትሰሙ ትችላላችሁ፡፡ እናንተ ግን አትፈቅዱም፤
ብትፈቅዱ ግን ሰይጣናዊ ዘፈኖች ከመስማት ይልቅ መንፈሳዊ
ዝማሬን ለመስማት ትበቃላችሁ፡፡ የመዘምራንን ግሩም የሆነ
መጓደድ መመልከት ትሻላችሁ? እነሆ የመላእክት ዝማሬና
መጓደድ፡፡ እንዴት ሆኖ ነው የእነርሱን ዝማሬን መስማት
በልዑል ፊት መጓደዳቸው መመልከት የሚቻለው ብሎ
የሚጠይቀኝ ካለ “እነዚህን ግሳንግሶችን ከነአካቴው ከተውክና
በሰርግህ ክርስቶስ እንዲገኝ ከፈቀድክ ይህ ይሆናል፡፡ ክርስቶስ
በሰርግህ የታደመ ከሆነ መላእክትም ከእርሱ ጋር በሰርግህ
ይገኙልሃል፡፡
ከአንተ ዘንድ ፈቃዱ ካለ እርሱ በአንተ ሰርግ መገኘት ብቻ
አይደለም ውኃውን ወደ ወይን ጠጅነት በመቀየርም ሰርግህን
ያደምቅልሃል፡፡ እንደ ውኃ ቀዝቃዛና ወራጅ የሆነውን የዚህን
ዓለም ደስታና ፈንጠዝያ አጥፍቶ መንፈሳዊ ደስታን
ከሚያጎናጽፈው ከዚህ ተአምር በላይ ምን ድንቅ ተአምር አለ!!
ይህ ነው ውኃውን ወደ ወይንነት የመቀየሩ ትርጉም፡፡ እንቢልታ
ነፊዎች ባሉበት ክርስቶስ ፈጽሞ አይገኝም፡፡ እርሱ በዚህ ሰርግ
ቢገኝ እንኳ መጀመሪያ ይህንን አስወግዶ ነው፡፡ ከዚያም የራሱን
ተአምርን ይፈጽማል፡፡ ከዚህ የሰይጣን መሳሪያ ከሆነ እቢልታ
በላይ ምን የሚጠላ ነገር አለ? ሁሉ በሥርዐት ካልሆነ ምንም
ነገር ያለጥቅም ይሆናል፡፡ ድካማችን ሁሉ ያለፍሬ ይቀራል
እኛንም ወደ ውርደት ይጥለናል፡፡
ከመልካም ሥነምግባር የበለጠ አስደሳች ነገር የለም፣ ሥርዐት
ወዳድ ከመሆን የበለጠ ጣፋጭ የሆነ ነገር የለም፣ ጽድቅ
ለመፈጸም ቆራጥ ከመሆን የበለጠ ተወዳጅ ነገር የለም፡፡
ሁሉም ሥርዐቶቻችን ልክ እኔ ስለጋብቻ ሥነ ሥርዐት
ባስተማርኩት መልክ ይሁኑ፡፡ እንዲህ ከሆነ ደስተኛ ልንሆን
እንችላለን፡፡
ነገር ግን ጋብቻን ሊያደርግ የሚሻ ሰው ከማን ጋር ጋብቻውን
መፈጸም እንዳለበት ይጠንቀቅ፡፡ ሴት ልጅ ያለችው ሰው
አስቀድሞ እውነተኛና እርሱዋን ሊንከባከባት የሚችል ባልን
ሊፈልግላት ይገባል፡፡ እንዲህ ዓይነት ወንድ ለአካል ራስ
እንዲሆን ሊመረጥ ይገባዋል፡፡ ለእርሱ ስትሰጥም እንደ ባሪያ
አድርጎ ሊይዛት ሳይሆን እንደ ልጁ ሊያያት ሊሆን ይገባል፡፡
ሀብት ስላለው ወይም ከከበረ ቤተሰብ በመሆኑ ወይም ሰፊ
ግዛት ስላለው እርሱን ለልጃችሁ ባል ይሆን ዘንድ አትምረጡ፡፡
ነገር ግን በነፍሱ ትሑት፣ አስተዋይ፣ ቅንነት ያለውና
እግዚአብሔርን የሚፈራ የሆነን ሰው ለልጃችሁ ባል ይሆን
ዘንድ ምረጡ፡፡ እንዲህ ከሆነ የምታፈቅሩዋት ልጃችሁ በደስታ
ልትኖር ትችላለች፡፡ ባለጠጋ ሆኖ በምግባሩ ግን ብልሹ የሆነን
ሰው ለልጃችሁ ባል ይሆን ዘንድ ያጫችሁት ከሆነ እርሱዋን
አለመጥቀማችሁ ብቻ ሳይሆን እርሱዋን ነጻ ሰው ከማድረግ
ይልቅ የእርሱ ባሪያ በማድረግ ትጎዱአታላችሁ፡፡ ልጃችሁ
የእርሱ ሚስት በመሆኑዋ ምክንያት በምታገኛቸው ሀብት ደስ
ከመሰኘት ይልቅ እርሱዋን እንደ ባሪያ ቆጥሮ በእርሱዋ ላይ
የሚያደርስባት በደል የከፋ ይሆናል፡፡
እንዲህ ዓይነት ድርጊትን ከመፈጸም ትቆጠቡ ዘንድ
እለምናችኋለሁ ፡፡ ነገር ግን ከእርሱዋ ጋር ተቀራራቢ ኑሮ
ያለውን ለልጃችሁ ባል ይሆን ዘንድ ታጩ ዘንድ እመክራችኋለሁ
፡፡ ይህ ባይሆን ምንም ሀብት ለሌለው ነገር ግን በጎ ሕሊና
ላለው ሰው ትድሩዋት ዘንድ አሳስባችኋለሁ ፡፡ እንዲህ
በማድረጋችሁ ልጃችሁን ሌላው ቢቀር ለአንድ ጌታ ልጃችሁን
እንደባሪያ ከመሸጥ ተቆጥባችሁ በትክክለኛው ትርጉም እንደ
ባል ሊሆናት ለሚችል ሰው መስጠት ይቻላችኋል ፡፡
ለልጅህ ባል የሚሆናትን ጥሩ ሥነ ምግባር የተላበሰውን ሰው
በጥንቃቄ መርምረህ በማግኘት ልትድራት ስትዘጋጅ ክርስቶስ
ኢየሱስ በጋብቻው ሥነ ሥርዐት ላይ እንዲገኝልህ ጥራው፡፡
በዚህ የደስታ ቀንህ እርሱን በእንግድነት እንዲገኝ ስለጋበዝከው
ቅር አይሰኝም፡፡ ምክንያቱም እርሱ የሚገኝበት ምሥጢር
ነውና፡፡ አዎን ከዚሀ ይልቅ ግን አስቀድመህ ለልጅህ ባል
አድርገህ ያጨኸውን ሰው እርሱ እግዚአብሔር ተወዳጅ ባል
ያደርገው ዘንድ ለምነው፡፡
የአብርሃም ባሪያ እንኳ ያላደረገውን አስከፊ ድርጊት ከማድረግ
ግን ራስህን ጠብቅ፡፡ እርሱ በጌታው በአብርሃም በተላከ ጊዜ
እግዚአብሔርን መንገዱን ያቀናለት ዘንድ ለምኖት ነበር፡፡
እንዲህ በማድረጉም ሁሉን ነገር ሰመረለት፡፡ እንዲሁ አንተም
ለልጅህ ባልን በመፈለግ አእምሮ ቢባክን ወደ እግዚአብሔር
“ጌታ ሆይ አንተ የፈቀድከውን አድርግ” ብለህ ጸልይ፡፡ ለእርሱን
እንዲህ በማለት ፈቃድህን አሳልፈህ ስጠው፡፡ በዚህ መልክ
ለእርሱ ክብርን ስጥ፤ እርሱም በምላሹ ፈቃድህን በመፈጸም
ያከብርሃል፡፡ በእርግጥ አንተን ሁለት ሥራዎች ይጠብቁሃል፡፡
እነርሱም ፈቃድህን ለእርሱ ሙሉ ለሙሉ መስጠትና፣ እርሱ
የመሰከረለትን በጥሩ ሥነ ምግባር የታነጸውን ሰው መሻት
ናቸው፡፡
የልጅህን ሰርግ ለመሰረግ በምትዘጋጅበትም ጊዜ እቃዎችንና
ልብሶችን ለመዋስ ስትል ቤት ለቤት አትዙር፡፡ ምክንያቱም
ሰርጉ የሚፈጸመው ትዕይንትን ልታቀርብ ወይም የልጅህን
ቁንጅና ልታሳይበት አይደለምና፡፡ በመሆኑም ሰርግህን
ልትፈጽም በምትዘጋጅበት ጊዜ ባለህ ነገር ብቻ ቤትህ
ለማስዋብ ሞክር፡፡ በመቀጠል ጎረቤቶችህን ወዳጆችህንና
የቅርብ ዘመዶችህን ጥራ፡፡ እንዲሁም ጥሩ ባሕርይ አላቸው
የምትላቸውን ሰዎች በሰርጉ እንዲታደሙልህ ጋብዝ፡፡
ሙዚቀኞችን ግን ፈጽመህ አትጥራ ለእነርሱ የምታወጣው
ወጪ በራሱ ከፍተኛና ሊሆን የማይገባ ነው፡፡
ከእነዚህ ሁሉ አስቀድሞ ግን ክርስቶስን በሰርግህ እንዲገኝ
ጋብዘው፡፡ እርሱን እንዴት አድርገህ እንደምትጋብዘው
ታውቃለህን ? “ንጉሡም መልሶ፡- እውነት እላችኋለሁ ከሁሉ
ከሚያንሱት ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት
ለእኔ አደረጋችሁት ይላቸዋል”(ማቴ.፳፭፥፵) እንዲል ድሆችን
በሰርግ እንዲገኙ በማድረግ ክርስቶስን በሰርግህ እንዲገኝ
ማደረግ ይቻልሃል፡፡ ስለክርስቶስ ብለህ ድሆች በሰርግህ
እንዲገኙ ስላደረግህ ሰርግህ የተበላሸ አድርገህ አትቁጠር፤ ነገር
ግን ሴሰኞችን በሰርግህ ብትጋብዝ ሰርግህ በእርግጥ የረከሰ
ይሆናል፡፡ ድሆችን ወደ ሰርግህ መጥራትህ ሀብት ወደ ቤትህ
እንዲገባ መጥራትህ ነው፡፡ ቅምጥሎችን ከሰርጉ እንዲታደሙ
የጠራህ እንደሆነ ግን ውርደትን እየጠራህ ነው፡፡
ሙሽሪትን በወርቅ ጌጣ ጌጦች አታስጊጣት ነገር ግን በጥሩ ሥነ
ምግባርና በጭምትነት አስጊጣት እነዚያን ነገሮች ፈጽመህ
አትፈልጋቸው፡፡ ግርግርና ሁካት በሰርግህ ፈጽሞ አይኑር፡፡
ሙሽራውን ጥራና ሚስቱን ይዞ ወደ ቤቱ ይግባ፡፡ በምሳና በራት
ግብዣህ ላይ አስካሪ መጠጦች አይገኙ፡፡ ነገር ግን ሰርግህ
በደስታ የሞላበት ይሁን፡፡
እንዲህ አድርገህ ሰርግህን በመከወንህ ምን ያህል ተጠቃሚ
እንደሆንክ ለማስተዋል እንድትችል በዘመኑ ሰርግ ተብለው
ከሚቆጠሩት ጋር ያንተን የሰርግ ሥነ ሥርዐት አስተያይ፡፡ ሌላው
ይቅርና ያንተን ሰርግ የተመለከተ ሰው ሁሉ የቁንጅና ውድድር
ሳይሆን በእውነተኛ ትርጉም ሰርግን እንዳየ ምስክርነትን
ይሰጥሃል፡፡ በዘመኑ ሰርግ ተብለው ከሚጠሩት ውስጥ ግን
እጅግ የበዙ ክፋቶች ታጭቀው ይገኙበታል፡፡ በአዳራሽ
የሚፈጸመው ሰርግ በጥንቃቄና እግዚአብሔርን በመፍራት
ከሚደረገው ጋር ሲነጻጸሩ በቶሎ የሚጠናቀቁ ሰርጎች
አይደሉም ፡፡ ከዚህም ባለፈ በውሰት የመጡት እቃዎች
ሊጠፉም ስለሚችሉ ፍጻሜው ከደስታ ይልቅ ሊቋቋሙ
ከማይችሉት ከባድ ሃዘን ውስጥ ሊጥል ይችላል ፡፡ ይህ የከበደ
ሃዘን በአማች ላይ የሚታይ ነው ፡፡ ነገር ግን ሙሽሪትም ከዚህ
ሃዘን ነጻ ልትሆን አትችልም ፡፡ በሰርጉም ፍጻሜም የቤቱ
ውበቱ ጠፍቶ በሃዘን ታወሮ ይታያል ፡፡
በጥንቃቄና እግዚአብሔርን በመፍራት በሚከናወነው ሰርግና
በአሕዛብ ልማድ በሚፈጸመው ሰርግ መካከል ሰፊ የሆነ ልዩነት
አለ፡፡ በዚህ ክርስቶስ ሲገኝ በዚያ ግን ሰይጣን ነግሦ ይታይበታል
፡፡ በዚህ ፍጽም የሆነ ፍስሐ ሲታይ በዚያ ደግሞ ጥቅ ያጣ
አለባበስ ይተዋወቅበታል ፡፡ በዚህ ፍጹም ደስታ ሲኖር በዚያ
ግን ሕማምና ሰቆቃ ይተርፈዋል ፡፡ በዚያ የወጣው ወጪ
ታላቅ ሲሆን በዚህ ግን እዚህ ግባ የማይባል ወጪ ብቻ
ያስተናግዳል ፡፡ በዚያ ግርግርና ሁካታ ሲታይ በዚህ ግን ግብረ
ገብነት ጎልቶ ይንጸባረቅበታል፡፡ በዚያ ኃጢአት ሠልጥና ስትታይ
በዚህ ግን ኃጢአት ፈጽማ አትኖርም ፡፡ በዚያ ስካሮች ሲኖሩባት
በዚህ ግን ሰላም ወዳዶች ይታዩባታል ፡፡ በዚያ ሁካታና ጠብ
ሲኖር በዚህ ግን እርጋትና ሰላም ሰፍነው ይታዩበታል ፡፡
እነዚህን ሁሉ ልብ በሉ ፡፡ እግዚአብሔርን ደስ በማሰኘት
እርሱን ለሚያፈቅሩት ካዘጋጀው ከመንግሥቱ ተካፋዮች
እንድንሆን ከዚህ ቀን ጀምረን ይህን ክፉ ልማድ ከራሳችን
አርቀነው እናስወግደው ፡፡ የሰውን ልጅ ከመውደዱ የተነሣ ሰው
በሆነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር አብ
ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጋር ክብር ምስጋና ዛሬም
ዘወትርም እስከዘለዓለሙ ይሁን አሜን !!

=>+*"+<+>+#ቅድስት_ሥላሴ +<+>+"*+

#ቅድስት_ሥላሴ
#ሥላሴ_የሚለው_ቃል ሠለሰ፤ ሦስት አደረገ ከሚለው የግእዝ
ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙ ሦስት ማለት ነው፡፡ ይህን
ሦስትነት ለጌታ ስንቀጽለው ልዩ የሆነ ሦስትነት የሚለውን ፍቺ
ያመላክታል፡፡
#የእነርሱን /የቅድስት ሥላሴን/ ሦስትነት ልዩ የሚያደርገው
በሦስትነት ውስጥ አንድነት፣ በአንድነት ውስጥ ሦስትነት ያላቸው
በመሆኑ ነው፡፡ ይህን በሚመለከት የሚሰጠው ትምህርተ
ሃይማኖት ምሥጢረ ሥላሴ ይባላል፡፡ ይህ ትምህርት ምሥጢር
መባሉ በዐይነ ሥጋ የማናየው፣ በዕደ ሥጋ የማንዳስሰው፣
በሥጋዊ ምርምር ፈጽሞ የማይደረስበት በመሆኑ ነው፡፡
ሆኖም ምሥጢረ ሥላሴ የሰላም ወንጌልና የእምነታችን
መሠረት ነው፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ትምህርተ ሰላምነ
ነአምን አበ ፈናዌ ወነአምን ወልደ ተፈናዌ ወነአምን መንፈሰ
ቅዱስ ማኅየዌ አሐደ ህላዌ፤ በሰላማችን ትምህርት ላኪ አብን
እናምናለን፤ ተላኪ ወልድንም እናምናለን፤ አዳኝ መንፈስ
ቅዱስንም በአንድ ባሕርይ እናምናለን እንዲል፡፡
#ቅድስት_ሥላሴ የእግዚአብሔር ልዩ መጠሪያው ነው፡፡
እግዚአብሔር ስንልም ስለ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ
መናገራችን ነው፡፡ ሊቁ አንሰ ሶበ እቤ እግዚአብሔር በእንተ
አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ እንዲል፡፡ ቢሆንም ግን
የእርሱን ነገር ልንመረምረው አንችልም፡፡ አንዳንድ ጊዜ
ሰዎች እግዚአብሔር ቅዱስ ተብሎ በወንድ አንቀጽ፣ ቅድስት
ተብሎ ደግሞ በሴት አንቀጽ /ቅድስት ሥላሴ/ ተብሎ ሲጠራ
እውነትም ከምርምር በላይ ነው ይላሉ፡፡ ይሁን እንጂ
የሚመራመር አእምሮን ስለሰጠን በተወሰነ መልኩ ቅዱስ እና
ቅድስት፣ ልዩ ሦስትነት የሚባልበትን ሃይማኖታዊ ምሥጢር
በጥቂቱ እንመለከታለን፡፡
1. #ቅዱስና_ቅድስት_መባል
ቅዱሳት መጻሕፍት ጾታ የሌላቸውን አካላት በወንድና በሴት
አንቀጽ መጥራት ልማዳቸው ነው፡፡ ለምሳሌ ቅዱሳን
መላእክትን በወንድ አንቀጽ ሲጠራቸው ወይሴብሕዎ ኩሎሙ
መላእክቲሁ፤ መላእክቱ ሁሉ ያመሰግኑታል ሲል በሴት አንቀጽ
ሲጠራቸው ደግሞ ሰማያት ይነግራ ስብሐተ እግዚአብሔር፤
ሰማያት (መላእክት) የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ ይላል
(መዝ. 148:1-2)፡፡ ነፍስንም በወንድ አንቀጽ ሲጠራ መንፈስ
እምከመ ወጽአ ኢይገብእ፤ ነፍስ ከተለየ በኋላ አይመለስም ሲል
በሴት አንቀጽ ደግሞ ትባርኮ ነፍስየ ለእግዚአብሔር፤ ነፍሴ
እግዚአብሔርን ታመሰግነዋለች ይላል /መዝ. 77:39፣ መዝ.
102:1/፡፡ እንዲሁም ፀሐይን በወንድ አንቀጽ ሲጠራ ፀሐይኒ
አእመረ ምዕራቢሁ፤ ፀሐይ መግቢያውን ዐወቀ ሲል በሴት
አንቀጽ ደግሞ ወድቀት እሳት ወኢርኢክዋ ለፀሐይ፤ እሳት
ወደቀች ፀሐይን አላየኋትም ይላል /መዝ. 103:19፣ መዝ.
57:8/፡፡ ስለዚህ ልማደ መጻሕፍት መሆኑን በዚህ ይረዷል፡፡
ሌላው ምክንያት ደግሞ የቅድስና ሕይወት ለወንዱም ሆነ
ለሴቷ የተሰጠ መሆኑን ያመላክታል፡፡ እዚህ ላይ የሚጠቀሰው
የሰው ልጅ የእኩልነት ሚዛን ደግሞ ቅድስና ነው፡፡
በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን ወንዶች
እንዳሉ ሁሉ ቅዱሳት ሴቶች መኖራቸው ለዚህ ማሳያ ነው፡፡
ይልቁንም የእመቤታችን የቅድስተ ቅዱሳን የድንግል
ማርያምን ቅድስና ስናስብ እንዲያውም በወንድ ምን ቅድስና
አለና! ያሰኛል፡፡ በእግዚአብሔር መንግሥት /በቤተ ክርስቲያን/
ፍትሕ፣ ርትዕ እንጂ ዓመፅና አድልዎ የለም፡፡ ዘአኮ ይዔምፅ
እግዚአብሔር ከመ ይርሳዕ ምግባሪክሙ ወተፈቅሮተክሙ
ዘአርአይክሙ በስሙ ወተልእክምዎሙ ለቅዱሳን
ወትትለአኩሂ፤ እግዚአበሔር ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ
አሁንም ስለምታገለግሉአቸው ያደረጋችሁትንም ሥራ
ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለምና፡፡እንዲል /
ዕብ. 6:10፡፡ እኛም ሃይማኖታችን የእኩልነት፣ የነጻነት፣
የሰላምና የአንድነት ሥርዓት እንጂ የሴቶች መጨቆኛ መሣሪያ
አይደለም የምንለውም ለዚህ ነው፡፡ አሁንም ቤተ ክርስቲያንን
የሚቃወሙ ወገኖች ይህን የጠራ አስተምህሮዋን በእምነት
መነፅር መረዳት አለባቸው፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ቅዱስ እና ቅድስት የመባሉን ነገር ሊቁ
አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በምሳሌዊ አገላለጽ ኀበ ርኅራኄክሙ
በዝኀ ወኀበ አልቦቱ መሥፈርት እለ ትሠመዩ በስመ ብእሲት
ሥላሴ ዕደወ ምሕረት ግናይ ለክሙ፤ ቸርነታችሁ ከበዛና
መሥፈሪያም ከሌለው ዘንድ ቅድስት ተብላችሁ በሴት ስም
የምትጠሩ የይቅርታ ወንዶች ሥላሴ ሆይ ለእናንተ መገዛት
ይገባል በማለት ምሥጢሩን እንደ ወርቅ አንከብልሎ እንደ
ሸማ ጠቅልሎ አስተምሯል፡፡
የሥላሴ በወንድና በሴት አንቀጽ መጠራት ምሳሌነት አለው
ማለት ነው፡፡ ወንድ ኃያል ነውና ቢመታ ያደቅቃል፤ ቢወረውር
ያርቃል፤ ቢያሥር ያጠብቃል፡፡ ሥላሴም ከቸርነታቸው በቀር
ፍጥረቱን ሁሉ እናጥፋው ቢሉ ይቻላቸዋል፡፡ አንድም ወንድ
ወጥቶ ወርዶ ነግዶ ሚስቱን ይመግባል፤ ልጆቹን ያሳድጋል፡፡
ሥላሴም በፈጢር ወላድያነ ዓለም ናቸውና የፈጠሩትን ፍጥረት
በዝናብ አብቅለው፣ በፀሐይ አብስለው ይመግቡታልና በወንድ
አንቀጽ ቅዱስ ይባላሉ፡፡
#ቅድስት_ተብለው በሴት አንቀጽ መጠራታቸው ደግሞ ሴት /
እናት/ በልጁዋ ወለደችው /አልወለደችው/ ተብላ
እንደማትጠረጠረው ሁሉ ሥላሴም ይህን ዓለም ፈጠሩት
አልፈጠሩት ተብለው አይጠረጠሩም፡፡ ሁሉም ከእነርሱ፣
ለእነርሱ፣ በእነርሱ ሆኗልና፡፡ ሴት /እናት/ ልጅዋ ቢታመምባት
ወይም ቢሞትባት አትወድም፤ ሥላሴም ከፍጥረታቸው አንዱ
እንኳ በዲያብሎስ እጅ ቢገዛባቸው አይወዱም፡፡ አንድም ሴት /
እናት/ ፈጭታ ጋግራ ቤተሰቦቿን ትመግባለች፤ ሥላሴም
በዝናም አብቅለው በፀሐይ አብስለው ፍጥረቱን ሁሉ
ይመግባሉና በሴት አንቀጽ ቅድስት ሥላሴ እያልን
እንጠራቸዋለን፡፡
2. #ልዩ_ሦስትነት
ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ልዩ ሦስትነት የሚለው
የምሥጢረ ሥላሴ ሃይማኖታዊ ትምህርት በቅድምና፣
በፈጣሪነት፣ በሥልጣን፣ በማሰገድ፣ በመመስገን፣ በክብር፣
በፈቃድ አንድ /እግዚአብሔር/ ሲሆኑ በስም፣ በአካል፣ በግብር
ሦስት (ሥላሴ) የሚለውን ይገልጻል፡፡
2.1. #በስም
የስም ሦስነታቸው አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ መባል ነው፡፡
ይኸንንም ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል /ወልድ/ እንግዲህ ሒዱና
አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ
እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርቴ አድርጓቸው ሲል
አስተምሯል /ማቴ. 28:19/ ታዲያ አብ በራሱ ስም አብ ቢባል
እንጂ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አይባልም፡፡ ወልድም ወልድ ቢባል
እንጂ አብ መንፈስ ቅዱስ አይባልም፡፡ መንፈስ ቅዱስም
መንፈስ ቅዱስ ቢባል እንጂ አብ ወልድ አይባልም፡፡ ስማቸው
ፈጽሞ የማይፋለስ (የማይተባበር) ነውና፡፡
አንዳንድ የእምነት ድርጅቶች ይህን ትምህርት በአግባቡ
ካለመረዳታቸው የተነሣ # ኢየሱስ ብቻ /Only Jesus/
በማለት የአብንና የመንፈስ ቅዱስን ስም ለኢየሱስ (ለወልድ)
ብቻ በመስጠት ስመ ተፋልሶ እያመጡ ኑፋቄን ይዘራሉ፡፡ እኛ
ግን በቅድስት ሥላሴ ዘንድ ስመ ተፋልሶ እንደሌለ እናምናለን፡፡
በአንጾኪያ ከቅዱስ ጴጥሮስ ቀጥሎ በሦስተኛነት ተሹሞ
የነበረው ቅዱስ አግናጥዮስ አብሂ አብ ውእቱ ወኢኮነ ወልደ
ወመንፈሰ ቅዱሰ፣ ወልድሂ ወልድ ውእቱ ወኢኮነ አበ
ወኢመንፈሰ ቅዱሰ፣ መንፈስ ቅዱስሂ መንፈስ ቅዱስ ውእቱ
ወኢኮነ አበ ወኢወልደ፣ ኢይፈልስ ስመ አብ ለከዊነ ስመ ወልድ
ወመንፈስ ቅዱስ፣ ወኢይፈልስ ለከዊነ ስመ አብ ወወልድ፤ አብ
አብ ነው ወልድን መንፈስ ቅዱስን አይደለም፣ ወልድም ወልድ
ነው አብን መንፈስ ቅዱስንም አይደለም፡፡ መንፈስ ቅዱስ
መንፈስ ቅዱስ ነው፤ አብን ወልድን አይደለም፤ አብ ወልድንና
መንፈስ ቅዱስን ለመሆን አይለወጥም፣ ወልድም አብንና
መንፈስ ቅዱስን ለመሆን አይለወጥም፣ መንፈስ ቅዱስም
አብንና ወልድን ለመሆን አይለወጥም ሲል፣ ዮሐንስ
ዘአንጾኪያም አስማትሰ ኢየኀብሩ፤ ስሞች ግን አይተባበሩም
ብሏል/ ሃይ አበው ዘቅዱስ አግናጥዮስ ምዕ. 11 ገጽ. 18፣ ሃይ
አበው ዘዮሐንስ/፡፡
ይህ የቅድስት ሥላሴ ስም እንደ ሰው ስም አካል ቀድሞት ኋላ
የተገኘ አይደለም፡፡ የሰው ስሙ አካሉ ቀድሞት ኋላ ይገኛል፡፡
ወንዱን በ40 ቀኑ እገሌ ሲሉት ሴቲቱን በ80 ቀኗ እገሊት
ይሏታል፡፡ የተወለደ ዕለትም እናት አባቱ ዓለማዊ የመጠሪያ
ስም ያወጡለታል፡፡ ሰው ሲባል ስሙ ከአካሉ አካሉ ከስሙ
ሳይቀድም እንደተገኘ ሁሉ የሥላሴም ስማቸው ከአካላቸው፣
አካላቸው ከስማቸው ሳይቀድም ቅድመ ዓለም የነበረ ስም ነው
እንጂ ድኅረ ዘመን የተገኘ አይደለም፡፡ ቅድምናቸው ዘመኑን
ቢወስነው እንጂ ዘመኑ ቅድምናቸውን አይወስነውምና፡፡
(መንገደ ሰማይ-በብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ገጽ. 32/፡፡
ሊቁ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ገባሬ መንክራት ወናሁ ንቤ ካዕበ አብ
ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ወአኮ እሉ አስማት ዘቦኡ ላዕሌሆሙ
ድኅረ አላ እሙንቱ እስመ አካላት ወብሂለ ሰብእሂ አኮ ውእቱ
ስም ዳዕሙ ፍጥረት ውእቱወአካሎሙኒ ለሥሉስ ቅዱስ
ወአስማቲሆሙ አልቦ ውስቴቶሙ ዘይዴኀር አላ እሉ እሙንቱ
ብሉያነ መዋዕል እምቀዲሙ ዘእንበለ ጥንት ወዘመን፤ አሁን
ደግሞ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ እንላለን ግን አካላት
ተቀድመው ተገኝተው እሊህ ስሞች ኋላ የተጠሩባቸው
አይደለም፤ ሰው ማለት ኋላ የወጣ ስም ሳይሆን ባሕርዩ ነው
የሥላሴ አካላቸውም ቀድሞ ስማቸው ከአካላቸው በኋላ የተገኘ
አይደለም፡፡ ጥንት ሳይኖራቸው ዘመን ሳይቀድማቸው የነበሩ
ናቸው እንጂ እንዲል /ሃይ-አበው ዘቅዱስ ጎርጎርዮስ ገባሬ
መንክራት 13-4-8/፡፡
2.2. #በአካል
የቅድስት ሥላሴን የአካል ሦስትነት ስናይ ደግሞ አብ በተለየ
አካሉ ፍጹም አካል፣ ፍጹም ገጽ፣ ፍጹም መልክእ አለው፡፡
ወልድም በተለየ አካሉ ፍጹም አካል፣ ፍጹም ገጽ፣ ፍጹም
መልክእ አለው፡፡ መንፈስ ቅዱስም በተለየ አካሉ ፍጹም አካል፣
ፍጹም ገጽ፣ ፍጹም መልክእ አለው፡፡ ይህን እውነት ሊቁ
አቡሊደስ ነአምን በአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ከመ ሠለስቱ
ገጻት ፍጹማነ መልክእ ወአካል እሙንቱ እንዘ አሐዱ
መለኮቶሙ፤ ባሕርያቸው በእውነት አንድ ሲሆን በመልክ፣
በአካል ፍጹማን የሚሆኑ ሦስት ገጻት እንደሆኑ በአብ በወልድ
በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን ብሏል /ሃይ አበው ዘአቡሊደስ
ምዕ. 39-3/፡፡
ይህ አካላቸው ምሉዕ በኩለሄ፣ ስፉሕ፣ ረቂቅ ሲሆን ዳር
ድንበር፣ ወሰን የለውምና ከጽርሐ አርያም በላይ ቁመቱ፣
ከበርባሮስ በታች መሠረቱ፣ ከአድማስ እስከ ናጌብ ስፋቱ ተብሎ
አይመረመርም፤ ቢመረመርም አይደረስበትም፡፡ ሁሉን ሥላሴ
ይወስኑታል እንጂ የሚወስናቸው የለምና፡፡«ንሕነ ናገምሮ
ለኩሉ ወአልቦ ዘያገምረነ አልቦ ወኢምንትኒ እምታሕቴነ እስመ
ለኩሉ የዐውድ ዕበየ ኃይልነ አልብነ ውሳጤ ወአፍአ አልቦ
ሰማይ ዘያገምረነ ወኢምድር ዘይጸውረነ፤ ሁሉን እኛ
እንሸከመዋለን እንጂ እኛን የሚሸከመን የለም፤ ከእኛ በላይ
ከእኛም በታች ቦታ የለም፣ ባሕርያችን ሁሉን ይወስናል እንጂ
የሚወስነው የለም» እንዲል /መጽ. ቀሌምንጦስ/፡፡
2.3. #በግብር
በግብር ሦስትነታቸው ደግሞ የአብ ግብሩ መውለድ ማሥረጽ
ነው፤ ወልድን ወልዷል፣ መንፈስ ቅዱስንም አሥርጿልና፡፡
የወልድ ግብሩ መወለድ ነው፤ ከአብ ተወልዷልና፡፡ የመንፈስ
ቅዱስ ግብሩ መሥረጽ ነው፤ ከአብ ሠርዷልና፡፡ እግዚአብሔር
አለኝ አንተ ልጄ ነህ ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ
ጊዜ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል እንዲል /መዝ. 2:7፣ ዮሐ.
3:16/፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተረዳነው /ከሊቃውንተ
ቤተ ክርስቲያን እንደተማርነው) አብ ወልድን ቢወልድ፣ መንፈስ
ቅዱስንም ቢያሠርፅ እንጂ አይወለድም፣ አይሠርጽም፡፡ ወልድ
ቢወለድ እንጂ አይወልድም፤ አይሠርጽም፤ አያሠርጽም፡፡
በመሆኑም ቅድስት ሥላሴ በዚህ ግብራቸው አብ ወላዲ፣ ወልድ
ተወላዲ፣ መንፈስ ቅዱስ ሠራጺ ተብለው ይጠራሉ፡፡
የወልድ ከአብ መወለዱና የመንፈስ ቅዱስ ከአብ መሥረጹ
እንደምንድን ነው? ቢሉ ቃልና እስትንፋስ ልብ ሳይቀድማቸው
አካላቸው ከልብ ሳይለይ ቃል እንደሚወለድና እስትንፋስ
እንደሚወጣ ሁሉ ወልድና መንፈስ ቅዱስም ቅድመ ዓለም አብ
ሳይቀድማቸው እንበለ ተድኅሮ አካል ዘእም አካል ባሕርይ
ዘእምባሕርይ ወልድ ከአብ ተወለደ፤ መንፈስ ቅዱስም ከአብ
ሠረጸ፡፡ ከመ ልደተ ቃል ወጸአተ እስትንፋስ እምልብ ከማሁ
ልደቱ ለወልድ ወጸአቱ ለመንፈስ ቅዱስ እም አብ፤ ወልድ ከአብ
የሚወለድበት ልደትና መንፈስ ቅዱስ ከአብ የሚወጣበት
አወጣጥ ከልብ እንደሚሆን እንደ ቃል መወለድና ከልብ
እንደሚሆን እንደ እስትንፋስ አወጣጥ ነው እንዲል /ርቱዐ
ሃይማኖት/፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ድንቅ ምሥጢር አሁንም
ቢሆን በዕፁብ ይወሰናል እንጂ በምርምር አይደረስበትም፡፡
ሆኖም ኦርቶዶክሳውያን አበው የመጽሐፍ ቅዱስን የቀና
አስተምህሮ መሠረት በማድረግ መንፈስ ቅዱስ ከአብ ብቻ እንደ
ሠረጸ አስተምረዋል፡፡ ዳግመኛም በቁስጥንጥንያ በተካሔደው
ዓለም አቀፍ ጉባኤም ላይ መቅዶንዮስን ተከራክረው የረቱ
መቶ ሃምሳው ቅዱሳን ሊቃውንት ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ
እግዚእ ማኅየዊ ዘሠረጸ እም አብ ንስግድ ሎቱ ወንሰብሖ
ምስለ አብ ወወልድ፤ ሕይወትን በሚሰጥ ጌታ ከአብ በሠረጸ
ከአብና ከወልድ ጋር በሚሰገድለት በነቢያት አድሮ በተናገረ
መንፈስ ቅዱስ እናምናለን በማለት ከቅዱስ ወንጌል እውነታ
በመነሣት ትክክለኛውን እምነት ገልጸዋል /ጸሎተ
ሃይማኖት/፡፡
በአንጻሩ ግን ይህን ትምህርተ ሃይማኖት ወደ ኋላ በመተው
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከጊዜ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ዘሠረጸ
እም አብ ወወልድ፤ ከአብ ከወልድም የሠረጸ የሚል ሥርዋጽ
አስገብተዋል፡፡ ይህ የስሕተት አስተምህሮ በላቲን ፊሊዮኬ
(Filio tve)ሲባል ትርጉሙ እንዲሁም ከወልድ ማለት ነው፡፡
ይህ አመለካከት ኑፋቄ በመሆኑ በእኛ ቤተ ክርስቲያን መቼም
ቢሆን ተቀባይነት የሌለው ትምህርት ሲሆን በላቲኖች ዘንድ ግን
ተቀባይነትን ያገኘ አስተምህሮ ነበር፡፡
ለእነርሱ የስሕተት ትምህርት መሠረት የሆናቸው አውግስጢኖስ
የተባለው ሰው (dusia is the Sours of trinity)፣ አብ
ፍቅር ነውና ልጁን ወዳጅ ነው (The father is the one
who loves or/over)፣ ወልድ ደግሞ በአብ ዘንድ ተወዳጅ
ነው /The son is the one who is Loved or
Beloved፣ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በሁለቱ ፍቅር መካከል ያለ
አያያዥ ነው /The Sprit is Love bond)በማለት
አስቀድሞ ያስተማረውን ችግር ያለበት ትምህርት
በመቀበላቸውና መመሪያ በማድረጋቸው ሲሆን ይህን ተከትለው
በ589 ዓ.ም በስፔን ቶሌዶ ካካሔዱት ጉባኤ ጀምሮ በ1014
ዓ.ም ተቀብለውት በቅዳሴያቸው አስገብተውታል፡፡ /The
Doctrine of God P. 172/.
በእርግጥ ምሥጢረ ሥላሴን በሚገባ መረዳት ለማንም ቢሆን
አይቻለውም፡፡ እርሱ ባወቀ ግን ምሥጢረ ሥላሴ በምሥጢረ
ጥምቀት ተገልጧል፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በመጽሐፈ
ሰላምታው ላይ ለምህሮ ትሥልስት ሥላሴ በሌሊተ ጥምቀት
ሐዲስ ዘአስተርአይክሙ በዮርዳኖስ በአምሳል ዘይሤለስ ግናይ
ለክሙ፣ በዐዲሲቱ ጥምቀት ሌሊት ሦስትነታችሁን ለማስተማር
በሦስት አካላት በዮርዳኖስ የተገለጣችሁ ሥላሴ መገዛት
ለእናንተ ይገባል እንዲል፡፡
እንግዲህ እምነታችንን በቅድስት ሥላሴ ላይ በማድረግ
በርትዕት ሃይማኖት ልንጸና ይገባል፡፡ወአኮ ዘንብል አሐዱ ከመ
አዳም ቀዳሜ ኩሉ ፍጥረት አላ ሠለስቱ እንዘ አሐዱ ህላዌ ናሁ
ንሰምዖሙ ለአይሁድ እኩያን ወለእስማኤላውያን ጊጉያን እለ
ይብሉ አሐዱ ገጽ እግዚአብሔር ወአሐዱ አካል በኢለብዎቶሙ
ዕውራነ ልብ እሙንቱ፤ የሰው ሁሉ መጀመሪያ እንደሆነ እንደ
አዳም አንድ ነው አንልም፤ ነገር ግን በባሕርይ አንድ ሲሆን
በአካሉ ሦስት ነው እንላለን እንጂ፡፡ ክፉዎች አይሁድን በደለኞች
እስማኤላውያንን እነሆ እናያቸዋለንና እግዚአብሔርን አንድ
አካል አንድ ገጽ ሲሉ ባለማወቃቸው በልቡናቸው የታወሩ
ናቸውና በሚል ተግሣጽ አዘል ምክር ተችሮናልና /ቅ.ማርያም
ቁ. 70/፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

=>+*"+<+>+ ግንቦት 7 +<+>+"*+

<<< በስመ አብ: ወወልድ: ወመንፈስ ቅዱስ: አሐዱ አምላክ . . . አሜን:: >>>
+<+>+ ግንቦት 7 +<+>+
+*" ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ "*+
=>በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከሐዋርያት ቀጥሎ የቅዱስ
አትናቴዎስን ያሕል ስለ ሃይማኖት የተዋጋ ቅዱስ ፈልጐ
ማግኘት አይቻልም::
=>ቅዱስ አትናቴዎስ ማን ነው?
=>ቅዱስ አትናቴዎስ በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት
በዘመነ ሰማዕታት መጠናቀቂያ በ300 (296) አካባቢ
እስክንድርያ (ግብፅ) ውስጥ ነው የተወለደው:: ወላጆቹ
አረማውያን በመሆናቸው ክርስትናን አልተማረም ነበር::
+ሕጻን እያለ ለጭዋታ ከቤቱ ሲወጣ የክርስቲያን ልጆች
ሃይማኖታዊ ጨዋታ ሲጫወቱ ተመለከተ:: ሊቀላቀላቸው
ቢፈልግም ክርስቲያን ባለመሆኑ ከለከሉት:: አትናቴዎስም
"ክርስቲያን ልሁንና አጫውቱኝ" ብሏቸው "እሺ" ስላሉት
ሕጻናቱ ዕጣ ተጣጣሉ::
+ላንዱ ቄስ : ላንዱም ዲያቆን መሆን ሲደርሳቸው ለአትናቴዎስ
ፓትርያርክ መሆን ስለ ደረሰው ሌሎቹ ሕጻናት ይሰግዱለት
ጀመር:: በአጋጣሚ ሕጻናቱ ይሕንን ሁሉ ሲያደርጉ የወቅቱ
ፓትርያርክ ቅዱስ እለ እስክንድሮስ በመገረም ያያቸው ነበርና
ለሕጻኑ አትናቴዎስ ትንቢት ተናገረለት::
+ከዚያም የአትናቴዎስ አባቱ ሲሞት ሊቀ ዻዻሳቱ ከእናቱ ወስዶ
አጥምቆ : የሚገባውን መንፈሳዊ ትምሕርት ሁሉ በልቡናው
ላይ ቀረጸበት:: ከዚሕ በሁዋላ ዲቁናን ሹሞ አስተምር አለው::
ምንም ሕጻን ቢሆንም ከሊቅነቱ : ከአመላለሱና ከአንደበቱ
ጣፋጭነት የተነሳ የሰማው ሁሉ ይደነቅ ነበር:: ጸጋ
እግዚአብሔር በእርሱ ላይ አድራለችና::
+ቅዱስ አትናቴዎስ ሊቀ ዲቁና በተሾመ ወራት አርዮስ ቤተ
ክርስቲያንን በመረበሹ ኒቅያ ላይ 318ቱ ሊቃውንት ሲሰበሰቡ
ጸሐፊ አድርገው ሾሙት::
+በጊዜውም በዕድሜ የስንት ጊዜ ትልቁ የሚሆነውን አርዮስን
ተከራክሮ ምላሽ አሳጣው:: ቅዱስ አትናቴዎስ ከሊቃውንቱ ጋር
ሆኖ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ : እግዚአብሔር
መሆኑን በአደባባይ መሠከረ:: ጸሎተ ሃይማኖትንም ያረቀቀው
እርሱ ነው::
+ከዚሕ በሁዋላ የእስክንድርያ (የግብፅ) 20ኛ ፓትርያርክ ሆኖ
ተሾመ:: ቤተ ክርስቲያንን በመልካም እረኝነት ለ48 ዓመታት
ሲመግብ ብዙ መከራዎችን ተቀበለ:: ለ5 ጊዜ ከመንበሩ
አፈናቅለው ወደ በርሃ ሲያግዙት : በስደት ከ15 ዓመታት በላይ
አሳልፏል::
+በተሰደደባቸው ቦታዎች መከራን እየተቀበለ ያላመኑትን
አሳምኗል:: በጎቹ እንዳይባዝኑበት ደግሞ በጦማር (በደብዳቤ)
ይጠብቃቸው ነበር:: ዛሬ በሃይማኖተ አበው የምናገኘው ቃለ
ሃይማኖት በዚሕ ዘመን የተጻፈ ነው::
+በወቅቱ የነበረው ንጉሥ (ትንሹ ቆስጠንጢኖስ) የአባቱን
(ታላቁ ቆስጠንጢኖስን) ዕረፍት ተከትሎ ነገሠ::
+ወዲያውም አርዮሳዊ (መናፍቅ) ሆነ:: ሃይማኖታቸው የቀና
አባቶችንም ያሳድድ ገባ:: ከአበው ቅዱሳን መካከል ግን የዚህ
መከራ ቀዳሚው ገፈት ቀማሽ ታላቁ ሊቅ ቅዱስ አንትናቴዎስ
ነበር::
+በተለይ አንድ ጊዜ ንጉሡ ቅዱሱን ወደ በርሃ አግዞ : መናፍቅ
ዻዻስ በግብጽ ሹሞ : ብዙ ክርስቲያኖችን በግፍ ሲያስገድል:
ቅዱሱን ለ6 ዓመታት አሰቃየው:: የወገኖቹ (የልጆቹን) ስቃይ
የሰማው ቅዱስ አትናቴዎስ ግን በድፍረት ወደ ቤተ መንግስት
ገብቶ ተናገረው::
+2 አማራጭን አቅርቦ "ወይ ግደለኝና እንደ አባቶቼ ሰማዕት
ልሁን: ካልሆነ ግን ወደ መንጐቼ (ምዕመናን) መልሰኝ"
አለው:: መናፍቁ ንጉሥም ቢገድለው ብጥብጥ እንደሚነሳ
ስለሚያውቅ በስልት ሊያጠፋው ወሰነ::
+ቀዛፊ: መቅዘፊያ: ምግብና ውሃ በሌላት ጀልባ ውስጥ ከቶ
ሜዲትራኒያን ባሕር ውስጥ ጣለው:: ድንገት ግን ከሰማይ
ጌታችን መላእክቱን አስከትሎ ወረደ::
+ሚካኤልና ገብርኤል ባሕሩን እየቀዘፍ : ሌሎች መላእክት
እየመገቡት እስክንድርያ (ግብጽ) አድርሰውት ተሠውረዋል::
ሕዝቡም በታላቅ ሐሴት እየዘመሩ አባታቸውን
ተቀብለውታል::
+ሐዋርያዊው ቅዱስ ስለ ኦርቶዶክስ ተዋግቶ : ብዙ ስቃይንም
ተቀብሎ በ373 ዓ/ም አካባቢ አርፏል:: ቤተ ክስርቲያን "ሊቀ
ሊቃውንት : ርዕሰ ሊቃውንት : የቤተ ክርስቲያን (የምዕመናን)
ሐኪም (Doctor of the Church) : ሐዋርያዊ . . ." ብላ
ታከብረዋለች::
=>አምላከ አበው ምሥጢራቸውን አይሰውርብን::
ከበረከታቸውም ያድለን::
=>ግንቦት 7 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
2.የባሕታውያን አለቃ ታላቁ አባ ሲኖዳ (ጽንሰቱ)
3.ቅዱስ ዮሐንስ ጻድቅ (ሃብቱን : ንብረቱን : ልብሱን ሳይቀር
መጽውቶ ራቁቱን የተገኘ ደግ ሰው ነው)
4.አባ ሐርስዮስ ገዳማዊ
=>+"+ ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብጹዐን ናቸው:: መንግስተ
ሰማያት የእነርሱ ናትና:: ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም
ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብጹዓን ናችሁ::
ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ:: ሐሴትም
አድርጉ:: ከእናንተ በፊት የነበሩ ነቢያትን እንዲሁ
አሳደዋቸዋልና:: +"+ (ማቴ. 5:10)
<ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Friday, May 13, 2016

=>+*"ሥርዓተ ቤተክርስቲያን"*+

**ሥርዓተ ቤተክርስቲያን***=======Share
1. ጫማ አድርጐ ወደ ቤተመቅደስ መግባት ክልክል
ነው፡፡ ዘጸ 3፡5 የሐዋ 7፡39 2ኛ ዜና7፡14
2. ለሃጩን የማዝረክረክ ነውር /ልጋግ/ ያለበት ሰው
ቤተክርስቲያን አይገባም
3. በቤተክርስቲያን አጸድ ግብዣ ማድረግ አይገባም፡፡ ፍት.ነገ.
አንቀጽ 1 ክርስቶስ ሥጋና ደም
ከሚሰዋበት ምዕመናን ሥጋወደሙን ከሚቀበሉበት
ከቤተክርስቲያን ራቅ ብሎ በደጀ ሰላም አቅራቢያ
በቤተ ምርፋቅ ካልሆነ በቀር በቤተመቅደስ ውስጥና
በዓውደ ምሕረት ላይ ሥጋዊ መብል መጠጥ
ማቅረብ መብላት መጠጣት አይገባም፡፡ 4. የቤተክርስቲያን
መገልገያ ንዋያተ ቅዱሳትን ለግል
አገልግሎት ማዋል አይገባም፡፡ ዳን 5፡35-31 ፍት.
ነገ. አን.1 ረስጣ 28
5. በቅጽረ ቤተክርስቲያን ገበያ መገበያየት አይገባም
ዮሐ2፡14-17 ፍት.ነገ. አን. 1
6. በቤተመቅደስ በማኅበር ጸሎት ወቅት የግል ጸሎት
ማድረግ
ክልክል ነው፡፡
7. በቤተመቅደስ በቅዳሴ ሰዓት አቋርጦ መውጣት
ክልክል ነው፡፡ ማቴ 26፡26 ዕንባ2፡2ዐ
8. ሴት ልጅ በወር አበባ ወቅት ወደ ቤተመቅደስ
መግባት አይፈቀድላትም፡፡ ዘሌዋ 15፡18-30 ፍት.
ነገ. 14፡583 9. ወንድ ልጅ ሕልመ ሌሊት /ዝንየት/
ከመታው
በዕለቱ ወደ ቤተመቅደስ አይገባም፡፡ ዘሌዋ 15፡
2-18
10. የሌሊት ልብስ /የአረማውያን ልብስ/ ለብሶ ወደ
ቤተመቅደስ መግባት ክልክል ነው፡፡ 1ኛ ቆሮ 11፡
5-14 11. ባልና ሚስት ከተራክቦ በኋላ ዕለቱን ወደ
ቤተመቅደስ ለመግባት አይፈቀድላቸውም፡፡
«ጋብቻ ቅዱስ መኝታውም ንጹሕ ቢሆንም
በቤተክርስቲያን ሥርዓት መሠረት ከተራክብ በኋላ
ዕለቱኑ ወደ መቅደስ መግባት አይቻልም፡፡ ቅዱስ
ጳውሎስ «ለጸሎት በመፈቃቀድ ካልሆነ በስተቀር ባልና ሚስት
አይከላከሉ» እንዳለው ባልና ሚስት
ከተራክቦ የሚርቁት በበዓላት፣ በአጽዋማት፣
ለጸሎትና ለቅዳሴ በሚዘጋጁበት ዕለታት በሰንበት
ነው፡፡ ስለዚህ ጠዋት ለቅዳሴ በሚዘጋጁበት ጊዜ
ራሳቸውን ሊጠብቁ ይገባል፡፡ 1ኛ ቆሮ 7፡5 ኩፋሌ
34፡12 ዘጸ19፡15 12. በቤተ መቅደስ ውስጥ መሳቅ፣
መሳለቅ፣
ዋዛፈዛዛ
ነገር መነጋገር ክልክል ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
«በምድራዊ ንጉሥ ፊት በቆምክ ጊዜ በምንም
ምክንያት ቢሆን ለመሳቅ አትደፋፈርም ታዲያ
በሰማያዊ ንጉሠ ነገሥት ፊት ትስቃለህን? ብሏል፡፡
ተግሣጽ ዘዮሐንስ አፈወርቅ አንቀጽ 6 «በቅዳሴ ሰዓት /ጊዜ/
የሚስቅ ዓለማዊ ቢሆን ወደ ውጭ
ያውጡት ከቅዱስ ምሥጢር /ከቁርባኑ/ አያቀብሉት
ተብሏል፡፡ ቀኖና ባስሌዎስ አንቀጽ 79
13. አብዝቶ ጠጥቶና ሰክሮ መግባት ክልክል ነው፡፡
«እንዳትሞቱ ወደ መገናኛው ድንኳን ስትገቡ አንተና
ልጆችህ የወይን ጠጅና የሚያሰክር ነገር ሁሉ አትጠጡ» ዘሌዋ
1ዐ፡8-10 ሉቃስ 21፡34 ምሳሌ
23፡29-35 ይሁንና ይህን ወይን አትጠጣ ቀምሰህ
ፈጣሪህን ለማመስገን ያህል ብቻ ይሁን እንጂ እንደ
ጢሞቴዎስ ብትታመም ከገድል ጽናት የተነሳ በድኑ
ደዌ ብትያዝ ግን ከወይን ጥቂት ጠጣ እርሱ ለሥጋ
ሕይወት ይሆንልሃልና፡፡ 1ኛ ጢሞ 5፡23 ሃይማኖተ አበው
ዘሠልስቱ ምዕት 21፡17-18
14. በቂም በቀል ሰውን አስቀይሞ የሰውን ገንዘብ
በማጭበርበር ወስዶ ወደ ቤተክርስቲያን መጥቶ
መጸለይ ክልክል ነው፡፡ ማቴ 5፡23-24 ማር 11፡25
ሉቃስ 18፡9-14
15. «ወደ እግዚአብሔር ቤት በገባህ ጊዜ እግርህን ጠብቅ . . .
» (ከተቀደሰ ስፍራ እንደቆምክ
አስተውል፡፡) መክ 5፡1 ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Wednesday, May 11, 2016

=>+*"ግንቦት 3"*+

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
አሜን
ግንቦት 3
+ ጌታችን ከመረጣቸው ከሰባ ሁለቱ አርድእት ውስጥ አንዱ
የሆነውና ቅዱስ ጳውሎስ በጠርሴስ አገር ላይ ኤጲስቆጶስነት
የሾመው ሐዋርያው ቅዱስ ያሶን ዕረፍቱ ነው፡፡
+ ሰማዕቱ አባ ብሶይ ሰማዕትነቱን በድል ፈጸመ፡፡
+ ‹‹የንጉሥ ወግና ሰገድ እናቱ የሆነች የተባረከች ንግሥት ወለተ
ማርያም›› ዕረፍቷ መሆኑን ስንክሳሩ በስም ይጠቅሳታል፡፡
እርሷም በምግባር፣ በሃይማኖትና በመንፈሳዊ ተጋድሎ
የከበረችና የተመሰገነች ናት፡፡
+ + + + + + + + + + + + + + +
ሰማዕቱ አባ ብሶይ፡- ይኽንንም ቅዱስ ክፉዎችና ጣኦት
አምላኪዎች ይዘውት ሰውነቱን በማጣመምና በመቆልመም
ብዙ አሠቃዩት፡፡ የእግዚአብሔርም መልአክ በእጁ አክሊል ይዞ
‹‹አትፍራ ጽና፣ እነሆ በእጄ ውስጥ አክሊል አለ›› አለው፡፡
ደግሞም ብዙ ካሠቃዩት በኋላ ወደ እሳት ውስጥ ጨመሩት፡፡
ጌታችንንም በማመን እስከመጨረሻው ጸንቶ ተጋድሎውንም
በዚኹ ፈጸመ፡፡ መልአኩም አስቀድሞ አሳይቶ ተስፋ
እንደሰጠው የሰማዕትነት አክሊልን አቀዳጀው፡፡ የሰማዕቱ
የቅዱስ ብሶይ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡
+ + + + + + + + + + + + + + +
ሐዋርያው ቅዱስ ያሶን፡- ይኽም ቅዱስ ሐዋርያ ከከበሩ
ሐዋርያት ጋራ ወንጌልን በሰበከ ጊዜ ብዙ አሠቃቂ መከራዎችን
በጌታችን ስም ተቀበለ፡፡ በ50ኛው ቀን ከሐዋርያት ጋራ አጽናኝ
መንፈስ ቅዱስን ተቀብሏልና ድንቅ ድንቅ የሆኑ ብዙ
ተአምራትን አደረገ፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ያሶን ትውልዱ ከጠርሴስ አገር ነው፡፡
ጠርሴስም ሰዎች አስቀድሞ በወንጌል ያመነው እርሱ ነው፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከተጠራና ካመነ በኋላ ወንጌልን ዞሮ
ሲሰብክ ቅዱስ ያሶን ተከትሎት በብዙ አገሮች በወንጌል
ትምህርት አገልግሎታል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ያሶን
በተሰሎንቄ ከተማ ወንጌልን ሲሰብኩ ክፉዎች ይዘዋቸው
እየጎተቱ ወስደው ከተሰሎንቄ አገር ገዥ ፊት አቅርበዋቸዋል፡፡
ከዚህም በኋላ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ቅዱስ ያሶንን
በጠርሴስ አገር ላይ ኤጲስቆጶስነት ሾመው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ
ያሶንም ቤተ ክርስቲያንን በመልካም አጠባበቅ ጠበቃት፡፡
ምእመናንን በቀናች ሃይማኖት ካጸናቸውና በበጎ ምግባር
ካነጻቸው በኋላ ወደ ምዕራብ አገር ሄዶ በዚያ ወንጌልን ሰበከ፡፡
ስሟ ኮራኮራስ ወደምትባል ደሴትም ገብቶ በውስጧ ወንጌልን
ሰብኮ ነዋሪዎቿን እግዚአብሔርን ወደማመን መለሳቸው፡፡
በደሴቷም ውስጥ በዲያቆናት አለቃ በሰማዕቱ በቅዱስ
እስጢፋኖስ ስም ቤተ ክርስቲያን ሠራላቸው፡፡ የአገሪቱ ገዥም
ይኽንን ባወቀ ጊዜ ቅዱስ ያሶንን ይዞ ከእሥር ቤት ጣለው፡፡
ሐዋርያው ግን በእሥር ቤት ያገኛቸውን ሰባት ኃይለኛ
ወንበዴዎችን አስተምሯቸው ካሳመናቸው በኋላ አጠመቃቸው፡፡
እነርሱም በከሃዲው መኮንን ፊት በጌታችን ታመኑ፡፡ ‹‹በቅዱስ
ያሶን አምላክ እናምናለን›› ብለውም በጮኹ ጊዜ መኮንኑ
ዝፍጥና ድን በተመላ ምጣድ ውስጥ አግብቶ አቃጠላቸው፡፡
የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበሉ፡፡ ረድኤት በረከታቸው
ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን፡፡
ከዚኽም በኋላ መኮንኑ ቅዱስ ያሶንን ከእሥር ቤት አውጥቶ ብዙ
አሠቃየው ነገር ግን ጌታችን መከራውን ያስታግስለት ነበርና
ምንም እንዳልነካው ሆነ፡፡ በተአምራቱም ብዙዎችን
አሳመናቸው፡፡ የንጉሡም ሴት ልጅ ከቤቷ መስኮት ሆና አይታ
በክብር ባለቤት በጌታችን አመነች፡፡ ልብሶቿንና ጌጦቿንም ሁሉ
አውጥታ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች ሰጠችና በሐዋርያው
በቅዱስ ያሶን አምላክ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ
ክርስቶስ ስም ታመነች፡፡ ንጉሡ አባቷም ይኽንን በሰማ ጊዜ
ይዞ አሠራት፡፡ ጌታችንንም በማመን ስለጸናች አባቷ ብዙ
ሥቃጦችን አደረሰባት፡፡ በጢስ አፍኖ አሠቃያት፣ ልብሷን
አውልቆ ካራቆታት በኋላ ሰውነቷን በፍለጻ ነደፋት እርሷም
በዚሁ ሰማዕትነቷን ፈጽማ ነፍሷን ለእግዚአብሔር ሰጠች፡፡
ረድኤት በረከቷ ይደርብን፣ በጸሎቷ ይማረን፡፡
ከዚኽም በኋላ ሐዋርያው ቅዱስ ያሶንን አሠቃይተው ይገድሉት
ዘንድ ከአንድ መኮንንና ከሠራዊቱ ጋራ ወደ ደሴት ሰደደው፡፡
መኮንኑም በመርከብ ወደዚያ በሄደ ጊዜ እግዚአብሔር
መኮንኑን ከነሠራዊቱ አሰጠመው፡፡ ቅዱስ ያሶንም ወንጌልን
ተዘዋውሮ እየሰበከ ብዙ ዘመናት ኖረ፡፡ ሁለተኛም ሌላ መኮንን
በተሾመ ጊዜ ቅዱስ ያሶንን ይዞ በምጣድ ውስጥ ድኝና ዝፍጥ
ሰም መልቶ ነበልባሉ ወደላይ እስኪወጣ ድረስ ከሥሩ አነደደና
ሐዋርያውን በውስጡ ጨመረው፡፡ ነገር ግን የክብር ባለቤት
ጌታችን አገልጋዩን ያለምንም ጉዳት አዳነው፡፡ መኮንኑም
ይኽንን ድንቅ ሥራ ባየጊዜ በክብር ባለቤት በጌታችን በኢየሱስ
ክርስቶስ ስም አመነ፡፡ ቤተሰቦቹና የአገሪቱ ሰዎችም ሁሉ
አብረው አመኑ፡፡ ቅዱስ ያሶንም አጠመቃቸው፡፡ ቤተ
ክርስቲያንም ከሠራላቸው በኋላ የከበረች የወንጌልን ሕግና
ትእዛዝ ሠራላቸው፡፡ እነርሱም በምግባር በሃይማኖት ጸኑ፡፡
ሐዋርያውም ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን አደረገላቸው፡፡
መልካም የሆነውን አገልግለቱንም ፈጽሞ በበጎ ሽምግልና ሆኖ
በዚኽች ዕለት ዐረፈ፡፡ የሐዋርያው የቅዱስ ያሶን ረድኤት በረከቱ
ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡

=>+++ግንቦት 4+++

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
አሜን
ግንቦት 4
በደጃቸው የተቀበረውን ሰው ዐፈር የማያስበሉት ኢትዮጵያዊው
ጻድቅ አቡነ መልከጼዴቅ ዕረፍታቸው ነው፡፡
የብሩክ ፊቅጦር አገልጋዮች የሆኑ ሶሲማ እና ኖዳ በሰማዕትነት
እንዳረፉ ስንክሳሩ በስም ይጠቅሳቸዋል፡፡
ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ መልከጼዴቅ፡- አቡነ መልከጼዴቅ
በ13ኘው መ/ክ/ዘ መጨረሻ በንጉሥ ዐፄ በእደ ማርያም
ዘመነ መንግሥት የነበሩ እደጃቸው የተቀበረውን ሰው አፈር
የማያስበሉ እጅግ ድንቅ ቃል ኪዳን ያላቸው ታላቅ አባት
ናቸው፡፡ የአምላካቸውን የክርስቶስን መከራ ለማሰብ ገዳመ
ቆሮንቶስን የመሰለ ዋሻ ቆፍረውና በዚያ ገብተው ቀንና ሌሊት
ዘግተው በረደኝ ፀሐይ ልሙቅ፣ ጨለመኝ ብርሃን ልይ ሳይሉ
በጸሎት ብቻ ዘግተው በመኖር ራሳቸውን በችንካር እያቆሰሉና
ጭንቅላታቸውን እያተሉ ትሉን ለሰማይ አእዋፍ ይመግቡ
ነበር፡፡ እግዚአብሔር ወልድ የተገረፈውን ግርፋት እያሰቡ
በየቀኑ እስከ 3ሺህ ድረስ ይሰግዱ ሰውነታቸውንም እንዲሁ
ይገርፉ እንደነበር መጽሐፈ ገድላቸው ይናገራል፡፡ የክርስቶስን
መቸንከር እያሰቡ እጅና እግራቸውን፣ ወገብና ደረታቸውን
በብረት ቸንክረው መከራውን ያስቡ ነበር፡፡ ጎኑ በጦር መወጋቱን
አስበው አጥንታቸው እስኪሰበር ድረስ ጎናቸውን ወጉ፡፡ ሐሞትና
ከርቤ መጠጣቱን አስበው እርሳቸውም መራራ ይጠጡና
አንክርዳድን ይመገቡ ነበር፡፡ ሞቱን አስበው ደም እንባን ያነቡ
ነበር፡፡ በእንደዚህ ዓይነቱ ተጋድሎ የክርስቶስን መከራ እያሰቡ
ነቢያን፣ ሐዋርያትን፣ ሰማዕታትን፣ ደናግል መነኮሳትን መስለው
ሁሉን እያከናወኑ እያለ የወዳጆቹን መከራ የማይዘነጋ፣ የሰውን
የድካሙን ዋጋ ፈጽሞ የማያስቀር አምላክ ሠራዊተ መላእክትን
አስከትሎ መጥቶ ‹‹መገረፍህ፣ ስለ እኔ መገረፍ ይሁንልህ፣
የደምህ መፍሰስ ስለ እኔ ደም መፍሰስ ይሁንልህ፣
መቸንከርህም ስለ እኔ መቸንከር ይሁንልህ፣ ሞትህም ስለ እኔ
ሞት ይሁንልህ›› ብሎ የሚከተለውን ቃልኪዳን ሰጥቷቸዋል፡-
‹‹ከዚህ ቦታ መጥቶ የተሳለመውን እምርልሃለሁ፤ ነፍሱ በአንተ
ቃልኪዳን የማይማር በአንተ ቦታ ለመሳለምም፣ ንስሓ
ለመግባትም ሆነ ለመቀበር አላቀርብብህም፤ መጥቶም
የተቀበረውን ሥጋውን አፈር አይበላውም›› የሚል እጅግ ድንቅ
ቃል ኪዳን ነው መድኃኔዓለም የሰጣቸው፡፡ ቃል ኪዳኑንም
የሰጣቸው ቅዱሳን መልእክትን፣ ነቢያትን፣ ሐዋርያትን፣
ጻድቃንን፣ ሰማዕታትን፣ ቀሳውስትን፣ ዲያቆናትን፣ ደናግል
መነኮሳትን ሁሉ ምስክር አቁሞ እንደሆነ ቅዱስ ገድላቸው
ይናገራል፡፡ ይህም ድንቅ ቃልኪዳን ዛሬም በገሀድ እየታየ ነው፡፡
እስከ ዕለተ ምጽዓትም ሲታይ ይኖራል፡፡ በደጃቸው የተቀበረ
ሰው አይበሰብስም፡፡ ይህም የሥጋው አለመበስበስ ለሞተው
ሰው ለሥጋው አንዳች ረብ ጥቅም ኖሮት ሳይሆን የጻዲቁ
ቃልኪዳናቸው እስከ ዕለተ ምፅዓት ድረስ ተፈጻሚ መሆኑንና
ምልክትን ለሚሻ ለዚህ ክፉ ዘመን ትውልድ ምልክት ይሆን
ዘንድ ነው፡፡
ከአ.አ 225 ኪ.ሜ ርቀት ለመራኛ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው
የሚዳ አቡነ መልከጼዴቅ ገዳም ተፈጥሮአዊ አቀማመጡ
እጅግ አስገራሚ በሆነው ዋሻ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሁሉም
ነገር በግልጽ ይታያል፡፡ ይህም እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ሁሉ
በተለይም እኛ ኢትዮጵያውን በኃጢአት ሳንጠፋበት የመዳኛ
መንገድ አድርጎ የሰጠን ድንቅ የቃል ኪዳን አባታችን
መሆናቸውን ተረድቶና አውቆ በቃል ኪዳናቸው መጠቀም
መቻል በራሱ ዕድለኛነት ነው፡፡ አቡነ መልከጼዴቅ ጌታችን
ዕድሜአቸው ረጅም መሆኑን በምሳሌ እያሳየ ሲነግራቸው
‹‹በዚህ ዓለም መኖር ጥቅሙ ምንድር ነው? ወደ እረፍትህ
ውሰደኝ እንጂ›› ብለው ሞታቸውን የለመኑ ቅዱስና ጻዲቅ አባት
ናቸው፡፡ ከመጽሐፈ ገድላቸው ውስጥ አንዳንድ ነጥቦች እንይ፡-
1.ትልቅ የቅድስና ደረጃ ላይ ቢደረስም እንኳ ራስን ለካህን
ማሳየት እንደሚገባ፡- ‹‹አባታችን መልከጼዴቅ ወደ ዋልድባ
ገዳም ሄደ፡፡ ወደ እምፍራንዝ ደብር ሄዶ ቤተክርስቲያንን እጅ
ነሳ፣ ተሳለመ፣ በውስጧም ጸለየ፡፡ ጸሎቱንም በፈጸመ ጊዜ
መድኃኔዓለም ‹አትፍራ፣ በምትሄድበት መንገድ ሁሉ እኔ ከአንተ
ጋር እሆናለሁና› አለው፡፡ ሰላምታንም ሰጥቶት ከእርሱ
ተሰወረ፡፡ ከቤክርስቲያንም ወጥቶ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር እጅ
ተነሳሳ፤ ‹አባ አባ ገረምኸን ከየት መጣህ?› አሉት፡፡ ‹እኔ
ኃጢአተኛና በደለኛ ስሆን ከምዕራብ አገር ቅዱሳንን ለመጎብኘት
መጣሁ› አላቸው፡፡ ይህንንም እየተናገረ እያለ እግዚአብሔርን
የምትፈራ አንዲት መነኩሲት ሴት ወደ እርሱ መጣችና እጅ
ነሳችው፡፡ እግሩንም ሳመችው፡፡ ዐይነ ስውር ነበረችና
‹የእግዚአብሔር ሰው ወደ እኛ መምጣትህ መልካም ነው፤
ሰላም ለአንተ ይሁን› አለችው፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ
አስቀድሞ ነገረኝ ‹የእግዚአብሔር ካህን መልከጼዴቅ
ይመጣል፣ እርሱም ይናዘዝሻል አለኝ› አለች፡፡ ይህንን ስትናገር
አባታችን መልከጼዴቅ ይህችን ዐይነ ስውርና ጻዲቅ ሴት ከራስ
ጠጉሯ እስከ እግር ጣቶቿ በወርቅ ልብስ ተሸልማ በመስቀል
ምልክት የተሠራ የብርሃን አክሊል በራስዋ ላይ ደፍታ ቅዱስ
ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል በቀኟና በግራዋ እየጠበቋት አያት፡፡
አባታችን መልከጼዴቅም ይህን ባየ ጊዜ አደነቀ፡፡ ‹እኔን
እንደጻድቅ ሰው አታስመስይኝ፣ ለሴቶች ንስሓ መስጠት
ቢቻላቸውስ ኖሮ እኔን በናዘዝሽኝ ነበር› አላት፡፡
ባስጨነቀችውም ጊዜ ንስሓ ሰጣት፡፡ ጻዲቋ ሴት በእርሱ ዘንድ
የተናዘዘች ኃጢአት ስለሠራች አይምሰላችሁ ‹በቃልህ
የተናዘዘውን ምሬልሃለሁ› ብሎ ለአባታችን ለመልከጼዴቅ
እግዚአብሔር በሰጠው በምህረቱ ቃልኪዳን ትጨመርና
በረከቱን ትቀበል ዘንድ ነው እንጂ፡፡ ወንድሞቸ ሆይ በደላችሁን
ለካህን ማሳየትን አታስታጉሉ፡፡ ጻዲቅ ሰውም እንኳ ቢሆን
ራሱን ለካህን ማሳየትን አያስታጉል፡፡ መጽሐፍ ‹እሳት ወርቅን
ከሚያጠራው በስተቀር ምን ያደርገዋል?› ይላልና፡፡ ይህችም
ጻዲቅ ሴት የዳነች የጠራች ስትሆን እንደ ኃጢአተኛ
ተናዘዘችለት፣ በኋላም በማዘን በቅዱስ መልከጼዴቅ ላይ
የሚመጣውን ሁሉ ትንቢት ነገረችው›› እንዲሁም በብሔረ
ሕያዋን ያለ አንድ የእግዚአብሔር ሰው ወደ ቅዱስ አባታችን
ዘንድ መጥቶ ኑዛዜን እንደተቀበለ አቡነ መልከጼዴቅ
ለተማሪዎቻቸው ነግረዋቸዋል፡፡ ታሪኩ እንዲህ ይነበባል፡-
‹‹አባታችን መልከጼዴቅ አደሴዋ በምትባል ደብር ሳለ እንዲህ
አለ፡- እንደ ነጭ የአውራ በግ ፀጉር ሁለንተናውን የከደነውና
ረጅም የሆነ የአካሉ ፀጉር እንደ ግምጃ የነጣ የራሱም ጫፍ
ከደመና የሚደርስና ቁመቱ ረጅም የሆነ አንድ ሰው ወደ እኔ
መጣ፡፡ ባየሁትም ጊዜ ደነገጥኩና አጋንንትን በማሳድድበት
በሥላሴ ስም በመስቀል ምልክት ፊቴን አማተብሁ፤
ከአጠገቤም ጥቂት ፈቀቅ አላለም፡፡ እኔም አንተ ማነህ?
ከወዴትስ መጣህ?› አልሁት፡፡ እርሱም ‹እኔ ኃጢአተኛ ሰው
ከቀደሙ አባቶች ዘመድ የሆንሁና ከኖኅ ልጆች ወገን ነኝ፣
ስሜም የእግዚአብሔር ሰው ነው፣ በነቢዩ በዳዊት ዘመንም
እግዚአብሔር ከሞት በፊት ሰወረኝ፣ በሕያዋን አገርም
ከሔኖክ፣ ከኤልያስ፣ ከዕዝራና ከጌታ ወዳጅ ከዮሐንስ ጋር
እኖራለሁ፣ ከእርሱም ጋር በሐሰተኛው መሢህ እጅ እሞታለሁ፣
ትናዝዘኝ ዘንድ ወደ አንተ እስከመጣሁበትና እግዚአብሔር ኑር
እስካለኝ ጊዜ ድረስ እኖራለሁ› አለኝ፡፡ ለእግዚአብሔርም
ያለውን አምልኮትና የሃይማኖቱን ደግነት በሰማሁና እንደ ዕንቈ
የሚያበራ የሥጋውን ንጽሕና ባየሁ ጊዜ ምንም እኔ ከጉልበቱ
የማልደርስ ብሆንም ዝቅ ብዬ ከእግሮቹ ስር እጅ ነሳሁ፡፡
እርሱም ከእኔ ፈቀቅ ብሎ ራሱን ወደ እኔ አዘነበለ፡፡ በመስቀል
ምልክት አማተብሁና ባረክሁት፣ ኑዛዜም ሰጠሁት፡፡ እርሱም
እጅ ነሳኝና ከእኔ ተሰወረ፡፡ በዳሞትም፣ በአደሴዋም እንዲሁ
ዘወትር ሲጎበኘኝ ነበረ አላቸው፡፡ አባታችን መልከጼዴቅ
ለተማሪዎቹ ይህን ነገራቸው፡፡ ጸሎቱና በረከቱ የዚህም
የእግዚአብሔር ሰው በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን ዛሬም
ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን፡፡››
2.ኢትዮጵያውያን ሁሉ የቅድስት ድንግል ማርያም የአስራት
ልጆች እንደሆንን ጌታችን የተናገረው፡- ‹‹የእግዚአብሔርም
ቃል በመልከጼዴቅ ላይ መጣና ‹ወንድምህ አቤል በንጉሡ
አዳራሽ ሞተ› አለው፡፡ ያንጊዜም ወደ ገዳም መጥቶ ወደ
እግዚአብሔር ጸለየ፡፡ ‹አቤል ወንድሜን ነፍሱን ያኖርህበትን
አሳየኝ› አለ፡፡ ጌታችንም መጣና ‹ባስቀመጥሁት በሲኦል
ውስጥ ንስሓውን ይፈጽም ዘንድ ተወኝ› አለው፡፡ ጌታችንም
ይህን ብሎ ከእርሱ ተሰወረ፡፡ ንስሓስ ከሞት በኋላ ኖሮ
አይደለም መልከጼዴቅ እንዲፈጽምለት ነገረው እንጂ፡፡ ከዚህ
በኋላ አባታችን መልከጼዴቅ ወደ እግዚአብሔር ይለምንለት
ጀመር፡፡ ደሙም በምድር ላይ እንደ ውሃ እስከሚፈስ ድረስ
ቁጥር በሌለው ብዙ ግርፋት ተገረፈ፡፡ ደም የተቀላቀለው ዕንባ
እያነባ መራራ ልቅሶን አለቀሰ፣ ዐይኑም ታመመ፡፡ ራሱንም
በሰንሰለት ቸንክሮ ሰውነቱን በእጅጉ አደከመ፡፡ ከዚህም በኋላ
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እርሱ መጣና ‹ስለ
ድካምህ ምሬልሃልሁ፡፡ ግርፋትህ በጲላጦስ እጅ እንደተገረፍሁት
ግርፋቴ ይሁን፣ ችንካርህም በዕፀ መስቀል ላይ አይሁድ
እንደቸነከሩኝ ችንካሬ ይሁን፣ መታሰርህም የደምህም መፍሰስ
ስለ ፈሰሰው ደሜ ይሁንልህ፣ ነፍስህን መስጠትህም ስለ ነፍሴ
መውጣት ይሁን፡፡ ዛሬም ና የወንድምህን የአቤል ነፍስ
ያለችበትን ላሳይህ› አለው፡፡ ያን ጊዜም የመንፈስ ቅዱስ ክንፍ
ተሰጠው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እየመራው
ሄደና ከሲኦል በር አደረሰው፡፡ ‹እኔ ወደ ሲኦል ወርጄ የጻድቃንን
ነፍሳት እንዳወጣሁ አንተም ወደ ሲኦል ውረድና ወንድምህ
አቤልን አውጣው› አለው፡፡ አባታችን መልከጼዴቅም ‹እኔ
መሬታዊ ሰው ስሆን ወደ ሲኦል መውረድ እንዴት እችላለሁ?
አንተስ የኃይል ባለቤት ሁሉ የሚቻልህ ስለሆንህ ከውስጧ
ወርደህ የብረት በሮቿን ቀጥቅጠህ ሰባበርህ› አለው፡፡ ጌታችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ‹በእኔ የሚያምን እኔ
የምሠራውን ይሠራልና እምቢ አትበለኝ ሂድ ውረድ› አለው፡፡
አባታችን መልከጼዴቅም ያንጊዜ መርከብ ወደ ጥልቅ ወንዝ
እንደሚወርድ ወደ ሲኦል ወረደ፤ ሲኦልም ደነገጠችና
‹የተሰጡኝን ነፍሳት ይቀማኝ ዘንድ ፈጣሪዬ ዳግመኛ ወረደን?›
አለች፡፡ አባታችንም ወንድሙን አቤልን ያዘውና ከውስጧ
አወጣው፡፡ ከእርሱ ጋርም ብዙዎች የኃጥአን ነፍሳትን አወጣ፡፡
በእርሱ ላይም የነካው የእሳት ሽታ ምንም አልነበረም፡፡
ወንድሙ አቤልን ከእሳት እንዳወጡት የእንጨት ግንድ ከሰል
መስሎ አየው፡፡ ከእርሱ ጋር የወጡት ነፍሳትም እንደ እርሱ
ጠቁረው ነበር፡፡ አባታችን መልከጼዴቅም ጌታችንን
‹ወንድሜን እንዲህ ጠቁሮ አየሁት ታዲያ ምኑን ማርህልኝ?
እነዚህም ነፍሳት እንዲሁ› አለው፡፡ ጌታችንም መላእክቱን
አዘዛቸውና መርተው ወስደው የገነትን ውኃ አሳዩት፡፡ ወንድሙ
አቤልንም በዚህ ውስጥ አጠመቀው፡፡ ከእርሱ ጋር
የወጡትንም ነፍሳት ሁሉ አጠመቃቸው፡፡ ያንጊዜም ፊቱ
ከጸሐይ ሰባት እጅ አበራ፡፡ አምላክን የወለደች እመቤታችን
ማርያምም መጣችና አባታችን መልከጼዴቅን ‹ወንድምህ
አቤልን ስጠኝ ወደ ርስቴ ልውሰደው፣ እርሱ ዕድል ፈንታዬ የእኔ
ድርሻ ነውና› አለችው፡፡ አባታችን መልከጼዴቅም ‹የእኔ ድርሻ
ነው፣ ልጅሽም የደምህ ዋጋ ይሁንህ ብሎኛል› አላት፡፡ እሷም
‹ና ወደ ልጄ እንሂድ› አለችውና ሁለቱም ሄደው ከጌታችን
ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ደረሱ፡፡ እመቤታችንም ‹ይህ
ኢትዮጵያዊ ሰው የሰጠኸኝ የእኔ ድርሻ ነው› አለችው፡፡
አባታችን መልከጼዴቅም ‹ለእኔም የደምህ ዋጋ ይሁንህ
ብለኸኛል› አለ፡፡ ጌታችንም ‹አንተም ኢትዮጵያዊ፣ እርሱም
ኢትዮጵያዊ፣ የኢትዮጵያዊን ሰዎች ሁሉ የእርሷ ድርሻ ይሆኑ
ዘንድ ሰጥቻለሁ› አለው፡፡ ወይቤ እግዚእነ አንተኒ ኢትዮጵያዊ
ወውእቱኒ ኢትዮጵያዊ እስመ ወሃብክዋ ኰሎሙ ሰብአ
ኢትዮጵያ ከመ ይኩኑ መክፈልታ እንዲል መጽሐፍ፡፡ ያንጊዜም
በፊቱ ሰግዳ አቤልን ወሰደችውና የብርሃን ልብስ አልብሳ ወደ
ገነት ደስታ አገባችው፡፡ ከእርሱ ጋር የወጡትን ነፍሳትም
ከጸሐይ ሰባት እጅ አብርተው አባታችን መልከጼዴቅ
ወሰዳቸውና ወደ ዘለዓለም ርስቱ አገባቸው፡፡ ለአባታችን
መልከጼዴቅ ታላቅ ምህረትን ላደረገለት ለእግዚአብሔር
ምስጋና ይሁን! ርስቱንም ይክፈለን! እኛንም ዕድል ፈንታው
ያድርገን! ለዘለዓለሙ አሜን!››
3.መድኃኔዓለም ክርስቶስ ለአቡነ መልከጼዴቅ የተገለጠበት
ልዩ ሁኔታ፡-
3.1.ጌታችን በምድር ላይ ተገልጦ ከአቡነ መልከጼዴቅ ጋር
እየተነጋገረ ሳለ በክብር ዙፋኖ ሆኖ አንድነቱን ሦስትነቱን
እንዳሳያቸው፡- ‹‹የእግዚአብሔር መልአክ አባታችን
መልከጼዴቅን ‹በግራርያ አገር ወደምትገኝ የቅዱስ
ተክለሃይማኖት ደብር ወደሆነች ወደ ደብረ ሊባኖስ ሂድ›
አለው፡፡ አባታችን መልከጼዴቅም በመልአኩ ትእዛዝ ሄዶ
ደብረ ሊባኖስ ደረሰና በዚያ ያሉ ቅዱሳንን እጅ ነሳቸው፡፡ ከንቡረ
ዕድ እንድርያስም ጋር ተቀመጠ፡፡ ትንሽ ዋሻ በዓትን ሰጠውና
‹ትእዛዛቱን በመጠበቅ እግዚአብሔር ያጽናህ፣ የገደልህንም
ፍጻሜ ይስጥህ› አለው፡፡ መልከጼዴቅም ወደዋሻው ገብቶ
ምስጋና፣ ጸሎትና ስግደትን ተግቶ ያዘ፡፡ እንደመጀመሪያውም
ታስሮ እያለ በየለቱ እስከ ሦስት ሺህ ስግደት ይሰግድ ነበር፡፡
ደሙም በምድር ላይ እስከሚፈስ ድረስ መንታ በሆነ የገመድ
ጅራፍ ሰውነቱን ይገርፍ ነበር፡፡ እንባውም እንደክረምት
ነጠብጠብ ይፈስ ነበር፣ የዓይኑ ብሌን እስኪገለበጥ ድረስ ያነባ
ነበር… እንዲህ ሆኖ መከራ ሲቀበልም እግዚአብሔር ዝም
አይልም፣ ሥራውንም ፈጽሞ ያደንቅ ነበር፡፡ ‹ጌታ ሆይ!
የተኛሁትን አንቃኝ፣ የደከምሁትን አበርታኝ፣ የጨለምሁትን
እኔን አብራኝ› ይል ነበር፡፡ ይህንንም የሚለው ለራሱ ብቻ
አይደለም ስለ ዓለሙ ሁሉ ነበር እንጂ፡፡ እርሱስ በኢየሩሳሌም
ከሐዋርያት ጋርና በአርያም ካሉ ከሱራፌል ጋር በክህነት
የሚያገለግል ፍጹም ንጹሕና ጻዲቅ ሰው ነው፡፡ ከዚህም በኋላ
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አባታችን ወደ መልከጼዴቅ
መጣና ‹ወዳጄ ሆይ! ሰላም ለአንተ ይሁን› አለው፡፡
መልከጼዴቅም ‹አንተ ማን ነህ?› አለው፡፡ ጌታችንም ‹እኔ
የድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነኝ› አለው፡፡
ያንጊዜም ከእግሩ በታች ወደቀ፡፡ ጌታም እጁን ይዞ አነሣውና
‹ጽና አትፍራ› አለው፡፡ ያንጊዜም እናቱ ድንግል ማርያም
ከቅዱስ ሚካኤልና ከቅዱስ ገብርኤል ጋር፣ ከሱራፌልና
ከኪሩቤል ጋር፣ ከነቢያትና ከሐዋርያት ጋር፣ ከጻድቃንና
ከሰማዕታት ጋር መጣች፡፡ መድኃኔዓለምም አባታችን
መልከጼዴቅን ‹ከእናትህ ማኅፀን ጀምሮ በምስክር ሁሉ ፊት
መረጥሁህ፣ ካህንም አደረግሁህ፣ ዛሬም የብዙዎች አባት
አድርግሃለሁ፡፡ ኃጢአተኞችንም የምትመልስ ትሆናለህ፡፡ ብሩህ
አክሊልና በሰው እጅ ያልተሠሩ የብርሃን ልብሶችን እሰጥሃለሁ፡፡
ርስትህ ከአጥማቂዬ ከዮሐንስ ጋር ይሁን፤ ሹመትህም ከሃያ
አራቱ ካህናተ ሰማይና ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት ጋር ይሁን›
አለው፡፡ ‹ስምህም የእኔ ምሳሌ በሆነው መልከጼዴቅ ይሁን›
አለው፡፡ የመጀመሪያው በጥምቀት የተሰጠው ስሙ ኅሩየ
ወልድ (በወልድ የተመረጠ) የሚል ነበርና፡፡ ያንጊዜም
ቁመታቸው እስከሰማይ የሚደርስ፣ ብርሃናቸው እንደ ፀሐይ
የሚያበራ ሦስት የወርቅ መስቀሎችን ሰጠው፡፡ ጌታችንም
‹በላያቸው ላይ ውጣ አለኝ፣ እኔም በእያንዳንዳቸው ላይ ሦስት
ጊዜ ወጣሁ፣ እስከ አርያምም አገቡኝ፡፡ በዚያም
የእግዚአብሔርን መንበር አየሁ፡፡ በአንድነት በሦስትነት
የሚኖር የዘመናት ጌታም በላይ ተቀምጧል፡፡› ይህም ነገር
እጅግ ድንቅ ነው ወልድ በምድር ላይ ከእርሱ ጋር እየተነጋገረ
ሳለ በአርያም ደግሞ በሦስትነቱ ተቀምጦ አየው፡፡ ጌታም
‹ሥርዓትህ እንዲሁ እንዳየኸው ይሁን፣ እስከ ዕለተ ዕረፍትህም
ድረስ ስለ ገድልህ ጽናት የሚሆን ሰጥቼሃለሁ› አለው፡፡ በጸሎቱ
የተማጸነውን እንደሚምርለትና ሌላም ብዙ ቃልኪዳን
ሰጠው፡፡ ‹እኔም ከአንተ አልለይም፣ መላእክቶቼም
ይጠብቁሃል› አለው፡፡ መልከጼዴቅም ይህንን በሰማ ጊዜ በፊቱ
ሰገደ፡፡ ‹አቤቱ ለእኔ ለኃጢአተኛው አገልጋይህ ይህን ሁሉ ክብር
የሰጠኸኝ ጌታ ሆይ መንግሥትህ ይባረክ› አለው፡፡ ጌታችንም
ባርኮት በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ዐረገ፡፡››
3.2.ጌታችን ሠራዒ ካህን ሆኖ ከአቡነ መልከጼዴቅ ጋር
እንደቀደሰ፡- ‹‹አባታችን መልከጼዴቅ ወደ እግዚአብሔር ቤተ
መቅደስ ገብቶ በመሠዊያው ፊት ቆመ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠለትና ‹እኔ ሠራዒ ካህን እሆናለሁ፣
አንተም ንፍቅ ሁነኝ› አለው፡፡ አባታችን መልከጼዴቅም ‹ሸክላ
(ጭቃ) ሠሪውን አትሥራኝ ማለት ይችላልን? የአንተ ፈቃድ
ይሁን› አለው፡፡ እነሆ የወርቅ ማዕድና የወርቅ ጽዋ፣
የወርቅም ዕርፈ መስቀል ከሰማይ ወረደና በመሠዊያው ላይ
ተቀመጠ፡፡ ጌታችንም በሰው እጅ ያልተሠራ የቅድስና ልብስ
ለበሰ፡፡ ያንጊዜም የሰማይ ኅብስትና የወይን ጽዋ ወረደ፡፡
ኅብስቱን በማዕድ ላይ፣ ወይኑንም በጽዋው ውስጥ ጨመረና
የራሱን ቅዳሴ ቅዳሴ እግዚእን ይቀድስ ጀመር፡፡ ‹ቅዱስ›
ከሚለው ቃል በደረሰ ጊዜም መላእክት በአንድ ቃል ‹ቅዱስ
ቅዱስ ቅዱስ የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር ፈጽሞ
በሰማይና በምድር ያለ፣ ወደፊትም የሚኖር፣ ሕያው› እያሉ
ጮሁ፡፡ አባታችን መልከጼዴቅም በቅዱሳን ጸሎት እንደ
ሱራፌል በወርቅ ማዕጠንት ዕጣን እያጠነ እንደ እነርሱ
‹ቅዱስ› አለ፡፡ የማዕጠንቱም ፍህም ከሰማይ የወረደ እሳት
ነው፡፡ የጻድቃን ጸሎትም በሚጤስ ጊዜ ቤቱን ይሞላል፡፡
ይህም ከሟች ሰው ልቡና የተሠወረ እፁብ ድንቅ ነገር ነው፡፡
ጌታም ይህን ኅብስት ለመቁረስ በያዘው ጊዜ ሕፃን ሆነ፣
ከዚያም ተመልሶ በግ ሆነ፣ ከዚያም ተመልሶ ኅብስት ሆነ፡፡ ይህ
ኅብስትም ፍህም ሆነ፡፡ አባታችን መልከጼዴቅም ይህን ባየ
ጊዜ ፈጽሞ ደነገጠ፣ ተንቀጠቀጠ፣ ይሸሽም ዘንድ ወደደ፡፡
መድኃኔዓለምም ‹ጽና አይዞህ አትፍራ፣ ከእኔ በኋላ አንተ
በክህነት በምታገለግልበት ጊዜ በእጅህ እንደዚህ
እንደሚደረግልህ አሳይሃለሁና› አለው፡፡ ይህም ነገር ፈጽሞ
የሚያስደንቅ ነው፡፡ እርሱ መሥዋዕት አቅራቢ፣ እርሱም ሕፃን
ይሆናል፡፡ እርሱም አራጅ፣ እርሱም በግ ይሆናል፡፡ እርሱ ፈታች
(ቆራሽ)፣ እርሱም የእሳት ፍህም የተከመረበት ኅብስት
ይሆናል፡፡ ከሰው ወገን በሁለት ወይም በሦስት መንገድ
መገለጥ የሚችል ማነው? እርሱ ግን ሁሉን ቻይ ነውና
ከመንበሩ ሳይነዋወጥ፣ ከሦስትነቱም ሳይለይ በምድር ላይ
በብዙ መንገድ ይገለጣል፡፡
መዓዛ ባለው እንጨት ለኄኖክ የታየበት ጊዜ አለ፤ በቀስተ
ደመና ለኖኅ የታየበት ጊዜ አለ፤ ከሁለት ሰዎች ጋር በሰው
አምሳል ወደ አብርሃም ሄዷል፤ ለይስሃቅ በበግ አምሳል
ታይቷል፣ ለመልከጼዴቅ በኅብስትና በወይን አምሳል ታይቷል፤
ለያዕቆብ በመሰላል ላይ በእሳት ነበልባል ተገልጧል፤ ለኤልያስ
በቀጭን ፉጨት ተገልጧል፤ ለኢሳይያስ በመንግሥቱ ዙፋን
በተቀመጠ ሰው ተገልጧል፤ ለዳንኤል በሽበታም ሰውና
በድንጋይ አምሳል ተገልጧል፤ ለሕዝቅኤል ሕብር ያለው በፍታ
በለበሰ አምሳል ተገልጧል፤ ለኤርምያስ በለውዝ በትር አምሳያ
ታይቷል፤ ለዕዝራ በአንበሳ አምሳል ታይቷል፤ ለአሞፅ
በሽበታም ሰው አምሳል ታይቷል፤ ለእመቤታችን ድንግል
ማርያም በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል አምሳል እንደጠልም
በማኅፀኗ አድሮ ከእርሷ ተወለደና በዚህም ሰው ሆነ፡፡ በአርያም
መላእክት በፈለጉት ጊዜም ከአባቱና ከመንፈስ ቅዱስ፣
ከቅዱሳንም ጋር እንደጥንቱ አገኙት፡፡ ለእንድርያስ በመርከብ
መሪ (ዋናተኛ) አምሳል በባሕር ላይ፣ ለኤዎስጣቴዎስ በበረቱ
ክንዶችና በሕፃን አምሳል በመስቀል ላይ፣ ለእስክንድርያ ሊቀ
ጳጳስ ለተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ ልብሱ በተቀደደ
በሕፃን አምሳል ተገልጧል፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ክብርና
ልዕልናዎቹን ስንቱን እናገራለሁ? እስከዛሬ ድረስ በሁሉም
አምሳል ይመሰላልና፡፡ ወደቀደመው ነገር እንመለስ፡፡ ጌታችን
ይህንን ኅብስት ሲፈትተው መንፈስ ቅዱስ እንደ እሳት እየነደደ
በእርሱ ላይ ወረደ፡፡ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለማክበር
ለመለወጥ መውረዱ እንደማይቋረጥ ተረዳ፣ ታወቀ፡፡
ኅብስቱንም ፈትቶ በጨረሰ ጊዜ ‹ይህ የሕይወት እንጀራ
ከሰማይ የወረደ ሥጋዬ ነው› ብሎ ለአባታችን መልከጼዴቅ
ሰጠው፡፡ ዳግመኛም በሕይወተ ሥጋና ነፍስ ላሉ ሰጣቸው፡፡
ጌታችንም ‹እንደ ነቢዩ ኢሳይያስ ከንፈርህን አስነካሁህ፤
ከኃጢአትህም አነጻሁህ፡፡ ዛሬ እንዳየኸኝ ነገም አንተ እንዲህ
በክህነት አገልግል› አለው፡፡
አባታችን መልከጼዴቅም በአገልግሎት ጊዜ በፈጣሪያችን እጅ
የተሠራ ልብሰ ተክህኖ ለበሰ፡፡ እንደ ትናንቱም ማዕድና ጽዋ፣
የወርቅም ዕርፈ መስቀል፣ የሰማይም ኅብስትና ወይን ወረደ፡፡
በማዕዱ ላይ ኅብስቱን አኖረ፤ በጽዋውም ላይ ወይኑን
ጨመረ፡፡ የጌታችንንም ቅዳሴ ቀደሰ፡፡ ‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ
የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር ዘወትር በሰማይና በምድር
የሚኖር ነው› ባለጊዜ በዚያ የነበሩና በሰማይም ያሉ መላእክት
‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር› ሲሉ ምድር
እስክትነዋወጥ ድረስ የምስጋናቸውን ቃል ሰማ፡፡ የእውነት
መንፈስ ቅዱስ ጰራቅሊጦስን ላከው› ባለጊዜም ሰማይ ተከፍተ፣
የኢየሩሳሌምም የቤቷ ጠፈር ተቀደደ፣ መንፈስ ቅዱስም በዚህ
ኅብስት ላይ ወረደ፡፡ እርሱም ሕፃን ሆነ፣ መድኃኔዓለምም
‹ይህን ሕፃን ሰዋው፣ ለዓለምም ሁሉ መድኃኒት ይሆን ዘንድ›
አለው፡፡ ይህን ሕፃን ሊይዘው በወደደ ጊዜም በግ ሆነ፡፡
እግዚአብሔርም ‹ይህን በግ እረደው› አለው፡፡ ይህንንም በግ
ሊይዘው በወደደ ጊዜ ከእሳት ጋር የተዋሐደ ኅብስት ሆነ፡፡
ይህም እጅግ ድንቅ ነገር ነው፡፡ ጌታ ከአገልጋይ ይናገር ዘንድ፣
ጌታ ንፍቅ ቄስ ሆኖ ከመልከጼዴቅ ጋር እየተነጋገረ ቆሞ ሳለ
በመሠዊያው ላይ ሕፃን ሆነ፤ ሁለተኛም በግ ሆነ፣ ሦስተኛም
ኅብስት ሆነ፡፡ ይህንም ኅብስት በሚፈትተው ጊዜ እንደ እሳት
ይነድ ነበር፡፡ አባታችንም ቅዳሴውን በፈጸመ ጊዜ ከዚህ
ኅብስት ራሱ ተቀበለ፣ በዚያም ለነበሩ ቅዱሳን ሁሉ
አቀበላቸው፡፡ ይህን ታላቅ ክብር ለሰጠው ‹ለአብ ለወልድ
ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁን› በማለት አመሰገነ፡፡›› ከዚሁ
ጋር በተያያዘ ለጻዲቁ ጌታችን የገባላቸውን ልዩ ቃልኪዳንም
አብረን ማየት እንችላለን፡-
‹‹በማግስቱም ቅዱስ ጴጥሮስ ከሰማይ በወረደ ኅብስት ካህን
በሆነ ጊዜ መልከጼዴቅ ንፍቅ ሆነ፤ እንዲሁ ከሁሉም ሐዋርያት
ጋር አሥራ ሁለት ቀን ንፍቅ ሆነ፡፡ ዳግመኛም እርሱ ካህን ሆነ፣
ሐዋርያትም እያንዳንዳቸው አሥራ ሁለት ቀን ንፍቅ ሆኑት፡፡
ለሃያ ስድስት ቀናትም ያህል ሁሉም በኢየሩሳሌም ሆኑ፡፡
ይህንም ተልእኮ በፈጸመ ጊዜ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ‹እኔ ከእናትህ ማኅፀን መረጥሁህ፣ ከአፌ በወጣ
ቃሌም እንደማልዋሽህ ቃልኪዳን ሰጠሁህ› አለው፡፡ ያንጊዜም
እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ከቅዱሳን መላእክቶች ጋር
መጣች፡፡ መላእክትንና ቀደምት አባቶችን፣ ነቢያትንና
ሐዋርያትን፣ ጻደቃን ሰማዕታትን፣ ቀሳውስትና ዲያቆናትን፣
ደናግልና መነኮሳትን፣ ወንዶችንና ሴቶችን ሕፃናትንም
ምስክሮች አድርጎ አቆመ፡፡ ሄሮድስ ያስገደላቸው 144,000
ሕፃናት ከአለቃቸው ከቅዱስ ቂርቆስ ጋር መጡ፡፡ ‹በእኔና
በአንተ መካከል እነዚህ ሁሉ ምስክሮች ይሁኑ፤ ስምህን የጠራ፣
መታሰቢያህን ያደረገ፣ በእጅህ የተጠመቀ፣ በቃልህ የተናዘዘና
በእጅህ የተሳለመ ምሬልሃለሁ፤ የገድልህን መጽሐፍ የጻፈውና
ያጻፈውን ምሬልሃለሁ ከአንተም ጋር ርስት እሰጠዋለሁ፤ የቤትህ
ልጆች መንግሥተ ሰማያትን ከአንተ ጋር ይውረሱ› አለው፡፡
ዳግመኛም ‹ለምህረት ያልጠራኋትን ነፍስ ለመሳለምም ሆነ
ለመባረክ ወይም ለመናዘዝ ወደ አንተ አላቀርብም፤
ከኃጥአንም ወገን አንተ ስለ እነርሱ ከለመንኸኝ እምርልሃለሁ፤
ሥጋቸውንም መሬት አይበላውም› አለው፡፡ ጌታችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ሁሉ ቃልኪዳን
በኢየሩሳሌም ከሰጠው በኋላ አባታችን በመንፈስ ክንፎች
ተመሰጠ፤ ተነጥቆም አዴሴዋ ከምትባል ከትግራይ ምድር
ተመለሰ፡፡ የዚህች አገር ሰዎችም ‹ለምን እስከዛሬ ድረስ
ተደበቅኸን?› አሉት፡፡ ‹እኔስ በቤቴ ውስጥ ታምሜ ነበርሁ›
አላቸው፡፡ ከእርሱ ጋር ከተነጠቁት በቀርም መንፈስ ቅዱስ
ኢየሩሳሌም እንደወሰደው አላወቁም፡፡››
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን! የጻድቁ አባታችን የአቡነ
መልከጼዴቅ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው
ይማረን፡፡
(ምንጭ፡- ገድለ አቡነ መልከጼዴቅ-ሊቀ ጠበብት ዘላለም
መንግሥቱ ከግእዝ ወደ አማርኛ የተረጎሙትና የገዳሙ እድሳት
ኮሚቴ ያሳተመው-2004 ዓ.ም፣ ስንክሳር ዘወርሃ ግንቦት)

=>*++በዓታ_ለማርያም++*

#በዓታ_ለማርያም
ይህ ዕለት የልዑል እግዚአብሔር እውነተኛ መቅደስ የምትሆን
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተ መቅደስ
የገባችበትን ዕለት የምናስብበት ነው፡፡ የአምላክ እናት ከእናት
ከአባቷ ቤት ተለይታ እግዚአብሔር ወደመረጠላት ሥፍራ ወደ
ቤተ መቅደስ ገባች፡፡ ዕድሜዋ ሦስት ዓመት ነበር፡፡
አባታችን ኢዮብ እንደተናገረው “ሁሉን ማድረግ እንደሚቻለው፤
በባሕርይው የሚሣነው እንደሌለ አሳቡንም ይከለከል ዘንድ ከቶ
እንደማይቻል” 《 ኢዮ 42፡2 》አውቀን ለተጠራንበት ዓላማ
መልስ መስጠት ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡
እግዚአብሔር ሲጠራ፣ ልዑል ሲናገር የዕድሜ ጉዳይ የጾታ
ጉዳይ የዜግነት ጉዳይ የአቅም ጉዳይ የጊዜ ጉዳይ የስልጣን
ጉዳይ የእውቀት ጉዳይ ሥፍራ አይገኝላቸውም፡፡ ጥያቄ
ውስጥም የሚገቡ አይደሉም፡፡ እኛ ግን እንኳንስ ራሳችንን
ለሕይወት ዘመን አገልግሎት ልንሰጥ ይቅርና በተወሰነ ሰዓት
ለሚሆነው መውጣት መግባት እየተቸገርን ነው፡፡ አገልግሎት
ለእግዚአብሔር ያለንን ፍጹም ፍቅር የምንገልጽበት
በሕይወታችንም ተጠቃሚ የምንሆንበት ምሥጢር ነው፡፡
ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ
ጥንተ ነገር አባቷ ቅዱስ ኢያቄም እናቷ ቅድስት ሐና እንደ
መጽሐፍ ቃል፥ እንደ አባቶች ሥርዓት፥ እንደኦሪቱ ሕግ
በእግዚአብሔር ትእዛዛትና ሕግጋት ሁሉ እየሄዱ በእግዚአብሔር
ፊት ፍጹም ጻድቅ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ልጅ አልነበራቸውም፡፡
ስዕለት ተሳሉ፤ እግዚአብሔር ልጅ ብቻ ሳይሆን ፈጣሪዋን
የምትወልድ ከመልኳ ደም ግባት ይልቅ የልቡናዋ ደም ግባት
ደስ የሚያሰኝ፤ አሸናፊ የሚሆን የእግዚአብሔር አብን የባሕርይ
ልጅ በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ በድንጋሌ ኅሊና ጸንሳ
የወለደች የብርሃን እናትን ወለዱ፡፡
ሊቃውንቱ “ማኅጸነ ሐና ሕያው ሰማያተ ገብረ”፤ ሕያው የሆነ
የሐና ማኅጸን ሰማይ የተባለች ቅድስት ድንግል ማርያምን
አስገኘ በማለት ዘመሩ፡፡ እግዚአብሔር ስጦታው ድንቅ ነው
የለመኑትን ሳይሆን ሰዎች ፈጽሞ ሊያስቡት ቀርቶ ሊገምቱት
የማይቻለውን ስጦታ ይሰጣል፡፡
የአባታቸውን የነቢዩን ዳዊት ቃል ቃላቸው አድርገው
በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ደጅ ይጠኑ የነበሩ ቅዱስ
ኢያቄምና ቅድስት ሐና “እኔ ግን በምሕረትህ ብዛት ወደ ቤትህ
እገባለሁ አንተን በመፍራት ወደ ቅድስናህ መቅደስ
እሰግዳለሁ” 《 መዝ 5፡7 》 በማለታቸው የጸሎታቸው ውጤት
ብቻ ሳትሆን የእግዚአብሔር ስጦታ የምትሆን፣ ፍጥረት ሁሉ
ተሰብስቦ ቢመዘን የአንዲቱን የጸጉሯን ዘለላ የማያክል ቅድስት
ድንግልን ወለዱ፡፡ ከእግዚአብሔር የተቀበሉአትን ቅድስት
ለእግዚአብሔር ሊሰጡአት ስዕለት ተስለው ነበር፡፡
አስቀድሞ በቤተ እስራኤል ዘንድ ደናግል በቤተ መቅደስ
ውስጥ የሚቀመጡበት ሥርዓት አልነበረም፡፡ በርግጥ በኦሪቱ
ነቢይት በአፍአ እንደነበረች ተገልጧል፤ ነገር ግን የእመቤታችን
ወደቤተ መቅደስ መግባትና የነቢይት ወደ ቤተ መቅደስ
መግባት የተለየ ነው፡፡ በዓይነትም በመጠንም የሚነጻጸር
አይደለም፡፡
ቅድስት ድንግል ማርያም ከሦስት ዓመቷ እስከ አሥራ አምስት
ዓመቷ ለአሥራ ሁለት ዓመታት በቤተ መቅደስ ቆየች፡፡ ሕያው
መቅደስ፥ እመቤትና የአምላክ እናት የምትሆን ቅድስት ድንግል
በእነዚህ ዓመታት መላእክት ምግቧንና መጠጧን እያመጡ
ከዜማው ጣዕም የተነሣ አጥንትን የሚያለመልም
የመላእክትን ዝማሬ እያዳመጠች በቤተ መቅደስ ኖረች፤
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን “ንጽሕተ ንጹሐን ከወይና ከመ ታቦተ
ዶር ዘሲና ውስተ ቤተ መቅደስ ነበረት በድንግልና ሲሳያ ኅብስተ
መና ወስቴሃኒ ስቴ ጽሞና” እያሉ አዲስ ቅኔን ተቀኙላት፡፡
የበዓሉ ትርጉም በዘመኑ ለምንገኝ ክርስቲያኖች
እግዚአብሔር በማንኛውም የዕድሜ ጣራ ሥር የሚገኝ
ክርስቲያንን እንደሚፈልግ የተመለከትንበት ዕለት ነው፡፡
በአቅማችን እንድንነጋገር ስለሚያስፈልግ እንጂ የበዓሉ
ትርጉም ከዚህም በላይ ላይ ነው፡፡ በልዑል እግዚአብሔር ቤተ
መቅደስ ስንኖር ልንከተለው የሚገባ ቅድስና በእግረ ሥጋ
ለምንመላለስ ወገኖች ያለው አስተማሪነት የጎላ ነው፡፡
በሕይወት ዘመን በእግዚአብሔር ቤት ለመኖር እንፈልግ ዘንድ
፣ ሕይወታችንን በፍጹም ቅድስና እንመራ ዘንድ መቅደስ
የተባለ ለእግዚአብሔር ማደሪያነት የተመረጠ ሰውነታችን
ከኃጢአት ሁሉ እንጠብቅ ዘንድ የተማርነበት በዓል ነው፡፡
ይልቁንም በመከራ ጊዜ ከንፈሮቻችን የተናገሩትን ስዕለት
ለእግዚአብሔር መፈጸም እንደሚገባን እግዚአብሔርን
የሚያስደስተው ፍጹም ስጦታ ራሳችንን አሳልፈን ከመስጠት
የበለጠ እንደሌለ ልንረዳ የሚገባን መሆኑን በዓሉ
ያስተምራል፡፡ ልመናዋ ክብሯ የልጇ ቸርነት በሁላችን ላይ
ይደርብን፡፡

ተዋሕዶ ማለት ምን ማለት ነው?

<<<ተዋሕዶ ማለት ምን ማለት ነው? መልስ >>>>>> በስመዓብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ዓሐዱ
አምላክ አመ
****
ብዙ ኦርቶዶክሶች እንዲሁም እራሳቸው ተቃዋሚዎች እኛ
ኦርቶዶክሳውያን ከመናፍቃን ጋር ያለን ልዩነት በቅድስት
ድንግል ማርያም እና በቅዱሳን እንዲሁም በሚስጥራተ
ቤተ ክርስትያን ላይ ብቻ ይመስላቸዋል፡፡
ዋናው እና መሰረታዊ የመናፍቃኑ ልዩነት ከኦርቶዶክሳውያን
ጋር በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለን ልዩነት ነው!
ተቃዋሚዎች ስለ ኢየሱስ:-
አንድ አካል ሁለት ባህሪ ብለው ያምናሉ :: ስጋ እና
መለኮት አልተዋሃዱም ,ያልተዋሀዱ የመለኮትና የትስብዕት
ባህሪ አሉ ብለው ያምናሉ፡፡ ልክ ዘይት ውሃ ላይ ጠልሎ
እንደሚታየው መለኮትና ስጋም ፍጹም አልተዋሃዱም
የሚሉ ናቸው፡፡መናፍቃኑ ባለፈው እንዳየነውና ወደፊት
እንደምንመለከተው እንዲሁ ጥራዝ ነጠቅ ጥቅስ ይዘው
ክርስቶስን አማላጅ ነው ይላሉና መለኮትና ትስብዕት
ፍፁም ስላልተዋሃዱ ትስብዕቱ መለኮቱን ይለምነዋል፤
ሰውነቱ አምላክነቱን ይማልደዋል ብለው በማስተማር
የክርስቶስን ፍጹም ሰው፣ፍጹም አምላክነት ይቃወማሉ!
ተዋሕዶ ስንል ምን ማለታችን ነው?
ተዋሕዶ ማለት የቃል በቃል ትርጉሙ ተዋሀደ አንድ ሆነ
ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን ተዋሕዶ ሲል አንድ
መሆን ማለት ነው።
ምስጢራዊ ፍቹ ግን ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት
ባሕርይ አንድ ባሕርይ የመሆን ምስጢር ነው።
- ሁለት አካላት የተባሉተ አካል መለኮትና አካለ ሥጋ
ናቸው።
- ሁለቱ ባህርይ የተባሉትም ባሕርየ መለኮትና ባሕርየ ሥጋ
ናቸው።
እንደሚታወቀው ሁለቱ አካላትም ሆነ ሁለቱ ባሕርያት
ፈጽመው የማይገናኙ የማይመሳሰሉ ናቸው። ይኸውም
አንደኛው ፈጣሪ ሌላው ፍጡር ከመሆናቸውም ባሻገር
የመለኮት አካል የማይጨበጥ፣ የማይዳደስ፣ ረቂቅ ሲሆን
የሥጋ አካል ደግሞ የሚጨበጥ፣ የሚዳሰስ ግዙፍ ነው።
እንግዲያውስ ከሁለቱ አካል አንድ አካል ሆነ ሲባል ረቂቁ
መለኮት ርቀቱን ሳይለቅ፤ ግዙፉ ሥጋም ግዙፍነቱን
ሳይለቅ: ይህ ማለት ረቂቅ መለኮት ግዙፉን ሥጋ
ሳያረቅቀው፣ ግዙፉ ሥጋም ረቂቁን መለኮት ሳያገዝፈው
በተዓቅቦ አንድ ሆኑ ማለት ነው።
የመለኮት ባሕርይ:
************
የማይሞት፥ የማይታተም፥ የማይደክም፥ የማይለወጥ
ሲሆን
የሥጋ ባሕርይ
*********
ደግሞ መዋቲ ታማሚ፣ የሚደክምና የሚለወጥ ነው።
ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ሆነ ማለት እንግዲህ
መለኮት የራሱ ባሕርይ ያልሆነው የሥጋ ባሕርይ ሕማም
ሞት ድካም ገንዘብ አድርጎ፣ ሥጋም የራሱ ባሕርይ
ያልሆነው የመለኮትን ባሕርይ ገንዘቡ አድርጎ ሁለቱም
ተዋሃዱ አንድ ሆኑ ማለት ነው። ተዋሕዶ መንታነትን
አጥፍቷልና ከእንግዲህ አንድ እንጂ ሁለት ብሎ ነገር
የለም። /ዮሐ 20፥26/
በተዋሕዶ የመለኮት ገንዘብ ለትስብእት፣ የትስእትም
ገንዘብ ለመለኮት ሆኗል።
ይህም ቀደም ሲል እንደተገለጠው መለኮት ትስብእትን /
ሥጋን/ በመዋሀዱ ምሉእ ውሱን፣ ሰጪው ተቀባይ፣
የማያንቀላፋው የሚተኛ፣ ኃያሉ ደካማ፣ ሕያው መዋቲ
ሆኗል።
በግርግም አስተኛችው (ሉቃ 2፥7)
እርሱም ትራስ ተንተርሶ ተኝቶ ነበር (ማር 4፥38)
ይችን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበለሁ (ዮሐ 10፥18)
ውኃ አጠጩኝ (ዮሐ 4፦........)
ሀብታም ሲሆን እናንተ በእርሱ ድህነት ባለወጎች ትሁኑ
ዘንድ ስለእናንተ ድሀ ሆነ:: (2ቆሮ 8፥9)
ኢየሱስም መንገድ ከመሔድ ደክሞ....... (ዮሐ 4፥6-8)
ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ መቼም ነበርሁ
እነሆም ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ ሕያው ነኝ
---- /ራእ 1፥17/
ትስብእትም መለኮትን በመወሃዱ ውሱን ምሉእ፣ ተቀባዩ
ሰጪ፣ ደካማው ኃያል፣ መዋቲው ሕያው ተባለ
ተሰወራቸው ከመቅደስም ወጥቶ በመካከላቸውም አልፎ
ሔደ:: /ዮሐ 8፥59/
ሰላሜን እስጣችኃለሁ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም
እንደሚሰጥ አይደለም:: /ዮሐ 14፥27/
በስሜ የምትለምኑትም ሁሉ አደርገዋለሁ ማናቸውንም
ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አድርገዋለሁ:: /ዮሐ
14፥13፣14/
በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ:: /ጴጥ 3፥18/
ይህ ሁሉ የተመለከትነው በኢየሱስ ክርስቶስ የተነገረና ስለ
እርሱ የተነገረውን ነው:: ታዲያ ከጥቅሶቹ የምንመለከተው
አንድነትን እንጂ ሁለትነትን አይደለም። በመለኮት የሥጋን
ገንዘብ ገንዘቡ አደረገ ሲባል ባሕርዩ ተለውጦ ትስብእቱ /u
ሰው/ የሆነ፤ ትስብእትም የመለኮትን ገንዘብ ገንዘቡ
አደረገ ሲባል ባሕርዩን ለቅቆ መለኮት የሆነ አይደለም።
ተዋሕደው በተዓቅቦ /በመጠባበቅ/ የሆነ ነው እንጂ
በተዋሕዶ ሁለትነትም ሆነ መለወጥ የለም። ምክንያቱም
ውላጤ /መለወጥ/ በእግዚአብሔር አይስማማምና ነው።
እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም:: (ሚል 3፥6)
ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትናና ዛሬ፣ እስከ ዘለዓለምም ያው
ነው:: (ዕብ 13፥18) እንዲል።
ክርስቶስን ከሁለት መክፈል እንደማይቻልና በተሕዶ ውስጥ
ምንታዊ /መንታነት/ እንደሌለ ቅ/ጳውሎስ
''ክርስቶስ ተከፍሏልን?" (1ኛ ቆሮ 1፥13)
''አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው ጌታም አንድ ነው::" (1ኛ
ቆሮ 12፥5) በማለት ያስረዳል። አሁንም ቢሆን
የሚከተሉትን በጽሞና እንመልከታቸው። ነገረ ተዋሕዶንም
ያስተምሩናል።
ያንቀላፋው ከእንቅልፉም ተነስቶ ማዕበሉንና ነፋሱን
የገሠፀው አንዱ ክርስቶስ ነው። /ማቴ 8፥23-27/
ወደ ሠርግ ቤት የተጠራው፣ በዝያ ተገኝቶ ውኃውን
ወደወይን ጠጅ የለወጠው አንዱ ሥግው ቃል ነው:: /
ዮሐ 2፥1-11/
ምራቁን ወደ መሬት የተፋው: ምራቁንም በጭቃ ለውሶ
ለዓይነ ሥውሩ ዓይን የፈጠረለትም እርሱ አንዱ ክርስቶስ
ነው:: /ዮሐ 9፥1-10/
የተጠማውና የማያስጠማ የሕይወትን ውኃ የሚሠጠው
አንዱ ኢየሱስ-ክርስቶስ ነው:: /ዮሐ 4፥6-15፣ ራእ
21፣6-7/
40 ቀንና 40 ሌሊት ከመጸሙ የተነሳ የተራበው ጥቂቱን
ዓሣና እንጀራ ያበረከተውም አንዱ ክርስቶስ ነው። /ማቴ
4፥1-3፣ 14፣ 13-21/
መለኮትና ትስብእት ከጽንሰት ጀምሮ አንድ አካል አንድ
ባሕርይ ሆነዋል። ለትምህርት ሲባል መለኮት፥ ትስብእት
እያልን እንጠራለን እንጂ ከተዋሕዶ በኋላ መለኮት፥
ትስብእት እያሉ መለያየት የለም።
የተዋሕዶ ተቃራኒዎች:
**************
ቢዚህ ዓለም ተቃራኒ የሌለው አንድም ነገር የለም።
ስለሆነም ለተዋሕዶም ተቃራኒ ነገሮች አሉት። እነሱም
የሚከተሉት ናቸው።
1. ውላጤ፦ ውላጤ ማለት መለወጥ ማለት ነው።
አንዳንዶች ቃል ተለውጦ ሥጋ ሆነ ይላሉ። ይህም ማለት
የሎጥ ሚስት ወደጨው ሓውልትነት (ዘፍ 19፦ ......)
የቃና ውኃ ወደ ወይን ጠጅነት እንደተለወጠ /ዮሐ 2፥5/
ማለት ነው ብለው ያምናሉ።
ነገር ግን መለኮት ሥጋን በለበሰ ጊዜ ሥጋ ወደ መሆን
አልተለወጠም በፍፁም ተዋሕዶ ፀና እንጂ። እንደዚያማ
ባይሆን ኖሮ ጌታ ራሱ፦
- እኔና አብ አንድ ነን:: (ዮሐ 10፥30)
- እኔን ያየ አብን አይቷል ባለለም ነበር ዮሐ 14፥19
2. ኅድረት:- ኀድረት ማለት ''ማደር'' ማለት ነው። ይህም
መለኮት በሥጋ ውስጥ አደረ የሚሉ መናፍቃን የሚከተሉት
እምነት ነው። የሚያቀርቡት ማስረጃም፦
- ውኃ በማድረግ - ዳዊት በማኅደር - ሰይፍ በሰገባ
እንደሚያድር መለኮት በሥጋ አድሮ ወጣ ይላሉ።
ለመለኮት ግን እንዲህ አይደለም ተዋሕደው አንደ ነፍስና
ሥጋ ነው እንጂ። ስለዚህም፦
- (ማቴ 3፦27) የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ እንጂ
በእርሱ ያደረው ነው አላለም'' የእግዚአብሔር አብን
ምስክርነት በመከተል ብዙዎችን መስክሯል። ጴጥሮስ
(ማቴ 16፥13-17፣ ዮሐ 6፥ ናትናኤል ዮሐ 1፥50)
እግዚአብሔር ማስተዋሉን ያድለን!
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የቀደመችው እውነተኛይቱ መንገድ፡፡
ወስብሀት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ
ክቡር!!!

+*"የክርስቲያን ሁሉ ዓርማ ማዕተብ"*+

ማዕተብ በቤተክርስቲያን ምን ማለት ነው????
ማዕተብ የክርስቲያን ሁሉ ዓርማ
“ማህተብህን በአንገትህ እሰረው ስትሔድ ይመራሃል ስትተኛ
ይጠብቅሃል ” ምሳ 6÷21
ማተብ (አተበ፤ አመለከተ ፤ባረከ)
ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ነው፡፡ይህም ማለት መታወቂያ ፤
ምልክት ማለት ነው፡፡ይህም ያሙትንና የተጠመቁትን
ካላመኑትና ካልተጠመቁት የሚለዮበት የክርስቲያን መታወቂያ
ነው፡፡
የዚህ ምልክት መሠረቱና ምሳሌውም ጌታችን መድኀኒታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ ከተቀበለው ጸዋትወ መከራ አንዱ በገመድ
ታሥሮ መጎተቱ መሆኑንየሚያመለክት ነው፡፡
ዮሐ19፤12 ቅዱስ ዳዊትም በመዝ59፤4 ላይ ”ወወሀብኮሙ
ትእምርተ ለእለ ይፈርሁከከመያምሥጡእምገጸ ቅስት ፤
ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ ለሚፈሩ ምልከትን ሰጠሃቸው”
ይላል፡፡
አጋንንት የክፋትን ቀስት በዚህ ዓለም በመወርወር የሰውን ልብ
ስለሚወጉ ከዚህ ለመዳን ማዕተብን ማድረግ ታላቅ መንፈሳዊ
እውቀት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
ሲያስረዱ ሥላሴ ማዕተበ ብርሃን ኃይል ሃይማኖቶሙ
ለክርስቲያን፤ሥላሴ ለክርስቲያን ሁሉ የሃይማኖታቸው ጉልበት
መታወቂያ የብርሃን ማዕተብ (ምልክት) ናቸው ብለዋል፡፡
ማዕተብ ያላሠረ ኦርቶዶክሳዊ በውግዘት ከቤተክርስቲያኒቱ እንደ
መናፍቅ ተቆጥሮ ባይለይም ማዕተብ አለማሠሩ ግን የአባቶቹ
ትውፊት እንዳልተቀበለ ያስቆጥረዋል፡፡
በምሳሌያዊ አነጋገርም ሃይማኖት አልባውን ማለትም
ክርስቲያን ያልሆነውን ማዕተብ የለሽ ያልተጠመቀ
አረሚይሉታል ክርስቲያን በማተቡ መነኩሴ በቆቡ እንዲታወቅ
ማዕተብ አልባ መሆን። ደግሞ ክርስቲያን
ይሁን ያልተጠመቀ መሆኑ ለማወቅ ያስቸግራል፡፡
በመለዮዋቸው ሌሎች እንዲታወቁ ክርስቲያን በማዕተቡ
ክርስትናውን ሲያሳውቅኖሯል፡፡ በተለመደው አነጋገር እገሌ
ማዕተብ አለው ባለማዕተብ ነው ሲባል እገሌ ታማኝ ክርስቲያን
ነው።
እውነተኛ :ሐቀኛ ነው የሚል ትርጉምን ይሰጣል
“ባለማዕተቢቱ” ሲባል ከአሚን ባሏ የረጋች ከባሏ
ሌላ የማታውቅ እውነተኛ ታማኝ ክርስቲያን የማል ፍች
አለው፡፡በዚህ ምክንያት በክርስቲያኑ ኅብረተሰብ የማዕተብ
ትርጉም ከፍተኛ ቁም ነገርን አዝሎ ይገኛል፡፡ አንዲት ሀገር ነፃ
መሆኗ የሚታወቀው ወይም ራሷን የቻለች የራሷ መንግሥት
ያላት ከባዕድ ቀንበር ቅኝ ግዛትነፃየወጣችመሆኗየሚታ
ወቀውበባንዲራዋ ምልክትነት እንደሆነ እንደዚሁም አንድ
ክርስቲያን በክርስቶስ አምኖ በጥምቀት ከዲያብሎስ ቁራኝነት
ነፃ መውጣቱ ነፃነት ያለው አማኝ መሆኑ የሚታወቀው
በማዕተቡ ምልክት ነው፡፡
ለደብዳቤ ለጽሑፍ ዓርማ ማኅተም ፊርማ እንደሚያስፈልገው
ያም ለመተማመኛ እንደሚያገለግል ጥቅሙ ታውቆ
ይሠራበታል፡፡
የክርስቲያን ማዕተብም በዚሁ አንፃር ብዙ ኃይማኖታዊ
ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡
መጀመሪያ በልቡ የሚያምነው ሃይማኖት ክርስትናን ሳያፍርበት
በአንገቱ ባለው ማተብ መግለጹ በክርስትናው አለማፈሩን
ክርስትናህን ካድ ማተብህን በጥስ የሚል ዓላዊ ቢመጣና ያንን
ምልክት ዓይቶ
ቢሰዋው የሰማዕትነትን ክብር ያገኝበታል፡፡ ያም ባይሆን
በማተቡ ምልክትነት በመናፍቃንና በኢአማንያን የሚቀበለው
ዘለፋ ስለ ክርስቶስ መስቀል እንደተሸከመ ያስቆጥረዋል፡፡
ሁለተኛው ከክርስቲያን ወገኖች ጋር
ያለጥርጥርማለትምየክርስቲ ያንመሆኑታውቆለት በቀላሉ
ክርስቲያናዊ ተሳትፎውን ማከናወን ይችላል፡፡ ማተብ ከሌለው
ግን ክርስቲያን ይሁን ያልተጠመቀ ስለማይታወቅ በሃይማኖት
ዜጎች ዘንድ በቀላሉ ተቀባይነት ማግኘት አይችልምሦስተኛ
ከማይታወቅበት ሀገር በአደጋም ይሁን በበሽታ እንደወጣ ሞት
ቢደርስበት በማዕተቡ መታወቂያነት የክርስቲያን ሥርዓት
ተፈጽሞለት አስክሬኑ ተፈርቶ በቤተክርስቲን ሊቀበር ይችላል፡፡
ማተብ ከሌለው ምስከር በአካባቢው ለክርስቲያንነቱ
ማረጋገጫ የሰው ያውም በሰበካው ቤተክርስቲያን የሚታመን
ክርስቲያን ከሌለ እንደአልተጠመቀ ተቆጥሮ እንደ አሕዛብ
ሥጋው ዱር ከበረሃ ወድቆ ይቀራል፡፡
ዐራተኛ ማተብና መስቀል ያለው ክርስቲያን በውሃ ዋና ወይም
በበረሃ ጎዳና በውሃ የሚኖሩ ወይም በበረሃ ያሉ አጋንንት
በቀላሉ ሊለክፉት አይችሉም፡፡ ይህምበየጠበሉ ሥፍራ
በተአምራት ተረጋግጧል፡፡ አጋንንት የለከፋቸው ሰዎች ማተብና
መስቀል አይወዱም፡፡ የሠፈረባቸው ርኩስ መንፈስ ማተብ
እንዲበጥሱ መስቀል እንዲጥሉ ያደርጋቸዋል፡፡
ማተብ በሰይጣን ዘንድ ከተጠላ በአጋንንት ላለመለከፍ የማተቡ
መኖር ይጠቅማል ማለት ነው፡፡
አንዳንድ ሰዎች የማዕተብ ሥርዓትን ለመቃወምና ዘመናውያን
መስለው ለመታየት “ሃይማኖት በልብ ነው” ይላሉ
ተሳስተዋል፡፡ ሃይማኖት የልብ ብቻ አይደለም የጠቅላላው
ሕዋሳት ሁሉ ናት እግዚአብሔርን ስንወደውና ስናመልከው
በልባችን ብቻ ሳይሆን በአፋችንም በአንገታችንም በጠቅላላው
ሰብአዊ ተፈጥሮአችን ሁሉ መሆን ይገባዋል፡፡
ምክንያቱም እግዚአብሔር የጠቅላላው ሰውነታችን አምላክና
ፈጣሪ ስለሆነ ነው፡፡ “ስለዚህ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝvሁሉ
እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ በሰው
ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው
በአባቴ ፊት እክደዋለሁ፡፡ “ማቴ ፲፤፴፪-፴፫በዚህ ቃል
መሠረት በኢአማንያን ዘንድ ክርስቲያን መሆናችንን
የምንገልፀው በልባችን ብቻ ሳይሆን በቃላችንና በሥራችንም
ጭምር ነው፡፡
በአንገታችንስ እንዳንመሰክርለት ማን ያግደናል? በአንገታችን
ባለው ማዕተብም ለእግዚአብሔር
እንመሰክራለን የስሙን ምልክት በአንገታችን እናኖራለን
አናፍርበትም ፡፡ የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ በጥምቀታችን
እንደምንመሰክር የጥምቀታችንንም አርማ በማተባችን
እናረጋግጣለን፡፡ (ሮሜ ፲፤፮-፲፫፡፡ ኢዮኤል ፪፤፴፪፡፡ ሮሜ
፮÷፩-፭ ፣ ማቴ ፭÷፲፩-፲፪፡፡ ፩ጴጥ ፫÷፳፩-፳፪ ፩ጴጥ ፬÷፲፪-
፲፮)ተመልከት፡፡
የማዕተብ ጥቅም
1. የክርስትናን ማዕተብ በአንገት ማሰር በልብ ያለውን እምነት
ሳያፍሩ በኃጢአተኛው ትውልድ መካከል ስለ ክርስቶስ
መመስከር እንዲሁም ለሰይፍ ለመከራ መዘጋጀትን ማመልከት
ነው፡፡
2. ክርስቲያን ከሆኑ ምእመናን ጋር ሃይማኖታዊ የሆነውን
ተሳትፎ በቀላሉ ለማከናወንና በክርስቲያን ወገኖች ዘንድ
ተቀባይነት ለማግኘ
3. በጉዞ ላይ ያልታሰበ አደጋ ቢያጋጥምና ሞት ቢደርስ አደጋው
ደርሶበት ያረፈው ክርስቲያን ቤተሰቦቹ ባይገኙ በቅርበት
በማዕተቡ ክርስትናው ተረጋግጦ ጸሎተ ፍትሐት ተደርጎለት
በእምነቱ ተከብሮ አስከሬኑ በክርስቲያኖች መካነ መቃበር
ያርፋል፡፡
ወስበሐት ለእግዚአብሔር!

Saturday, May 7, 2016

+*"ከትንሳኤ እስከ ዕርገት"*+

ጌታችን እና መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፣ ሐዋርያትና ቤተ
ክርስቲያን ከትንሳኤ እስከ ዕርገት
ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን
በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን
አሠሮ ለሰይጣን
አግአዞ ለአዳም
ሰላም
እምይእዜሰ
ኮነ
ፍሥሐ ወሰላም።”
የጌታችን ትንሳኤ በአበው ዘንድ በምሳሌ የተመሰለ፣ በነቢያት
በትንቢትና በምልክት የተነገረ፣ በተስፋ የተጠበቀ የድኅነታችን
ታላቅ በር ነው፡፡ የጌታችንን የወንጌል ምሥራች የሰበኩ
ሐዋርያትም የጌታን ትንሳኤ በደስታና በጽናት መስበካቸው
ትንሳኤው በኃጢአትና በሞት ላይ የተደረገ ታላቅ ድልና የድኅነት
የምሥራች በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህም የትንሳኤው ምስክሮች
ሆነዋል፡፡ /የሐ.ሥራ 2፡32/ ጌታ የተነሳበት ሰንበተ
ክርስቲያንም የበዓላት በኩር፣ የዘላለም ሕይወት ቀብድ፣
ዘላለማዊት መባሏ የጌታ ትንሳኤ የምዕመናን የዘላለም
ሕይወት ትንሳኤ በኩር በመሆኑ ነው፡፡ /1ኛቆሮ. 15፡20/
በዚህ ጽሑፍ በመጀመሪያ ጌታ ከትንሳኤው ጀምሮ እስከ ዕርገቱ
ድረስ ከሐዋርያት ጋር እንዴት እንደቆየና ሐዋርያዊት ቤተ
ክርስቲያንም እነዚህን ቀናት በእንዴት ያለ ትውፊት
እንደምታሳልፋቸው በአጭሩ ጠቅለል በማድረግ ይቀርባል፡፡
ቀጥሎም በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው የቤተ ክርስቲያንን
ስርዓት የሰሩ አበው በእነዚህ ቀናት /ከትንሳኤ እስከ ዕርገት/
ባሉ እሁዶች የቅዳሴ ምንባባት ስለትንሳኤ ያስተላለፏቸውን
ትምህርቶች በተረዳነው መጠን ከብዙ በትንሹ እናቀርባለን፡፡
እነዚህ 40 ቀናት የደስታ ቀናት ናቸው፡፡ የጌታን የትንሳኤ
የምሰራች ያሰፈሩ ወንጌላውያን፣ በሐዋርያት ትውፊት ላይ
የተመሠረተው የቤተ ክርስቲያን አኗኗር ስለነዚህ ቀናት ምን
ያስተምሩናል? ከቅዱስ መጻሕፍና ከቤተ ክርስቲያን ትውፊት
ስለነዚህ ዕለታት ከምንማራቸው ብዙ ትምህርቶች ጥቂቶች
የሚከተሉት ናቸው፡፡
በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ አስከፊውና የመጨረሻው ጠላት
ሞት ነው /1ኛ ቆሮ. 15፡26/ የበደል ፍርዳችን በሞት ፍርድ
ተጀምሮ፣ ሞትን በማሰብ በጭንቀትና በፍርሃት በመራራ
ሕይወት ኖሮ በመጨረሻ በሞት የሚፈጸም ሆኗልና ሞት የሰው
ልጆች የብክነትና የጥፋት መሳሪያ ክፉ ጠላት ነው፡፡ የጌታ
ትንሳኤም በዚህ ክፉ ጠላት ላይ የተደረገ ድል ነውና
ለክርስቲያኖች ታላቅ ደስታ ነው፡፡ ይህንንም ሲገልጽ ሐዋርያው
እንዲህ ብሏል፤ «እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ
እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ስልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፤
ይኸውም ዲያብሎስ ነው በሕይወታቸውም ሁሉ ስለሞት
ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ በሥጋና
በደም እንዲሁ ተከፈለ፡፡» በማለት የጌታ ሥጋዌ በሞቱና
በትንሳኤው ሞትን ለመሻር እንደሆነ ተናግሯል /ዕብ. 2፡
14-16/፡፡ በጥንት ዘመን ሞት አስከፊ፣ ሁሉም የሚፈራው፣
በዲያብሎስ እጅ የመውደቂያ መንገድ ስለነበር ሙት አካል
መንካት እንኳ መርከስ እስዲሆን ድረስ የሚጠሉትና የሚፈሩት
ነገር ግን ከጥቂቶች በቀር የማያመልጡት የሕይወት መጥፎ
ፍጻሜ ነበር፡፡
ከጌታ ሞትና ትንሳኤ በኋላ ግን ሞት ሃይሉን በማጣት
«ክርስቲያኖች የሚረግጡት፣ ጥርሱ የወለቀ፣ ሃይሉ የደከመ
ያረጃ አንበሳ» ሆኗል /ቅዱስ አትናቴዎስ/፡፡ ጥንታውያን
አበውና ነቢያት በሰቆቃ የተቀበሉት፣ ጌታ በአልዓዛር መቃብር
ያለቀሰለት፣ የሰው ዘርን ያጐሰቆለውና ያጠፋው ክፉ ሞት በጌታ
ሞትና ትንሳኤ ድል ተደርጓልና፤ ቅዱሳን የሚናፍቁት /ፊሊ. 1፡
23/፣ ሰማዕታት ትንሳኤያቸውን ክርስቶስን እየመሰከሩ
በድፍረት የሚቀበሉት፣ ጻድቃን በፈቃዳቸው በሕይወታቸው ላይ
የሚያውጁት የመንግስተ ሰማያት ማለፊያ /ፋሲካ/ ሆኗል፡፡
ስለነዚህ ምክንያቶች በእውነትም የጌታ ትንሳኤ ታላቅ ደስታ
ነው፡፡ ሃዋርያትም በትንሳኤው መደሰታቸው፣ የስብከታቸው
ማዕከል ማድረጋቸው በዚህ የተነሳ ነው፤ «ደቀ መዛሙርቱም
ጌታን ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው» እንዲል /ዮሐ. 20፡20/፡፡ ጌታም
ቀድሞ በትንሳኤው እንደሚደሰቱ እንዲህ ብሎ ነግሯቸው ነበር
«እንግዲህ እናንተ ደግሞ አሁን ታዝናላችሁ ነገር ግን እንደገና
አያችኋለሁ ልባችሁም ደስ ይለዋል ደስታችሁንም
የሚወስድባችሁ የለም፡፡» /ዮሐ. 16፡22/፡፡
በእነዚህ ቀናት ጌታችን ሃዋርያትን እየታያቸውና ከፍርሃታቸው
እያጽናናቸው አብሯቸው ቆይቷል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
ጌታችን ቶማስ ምንም ሳይጠይቀው ቀድሞ የተወጋውን ጐኑንና
እጆቹን አሳይቶ «እመን እንጅ የማያምን አትሁን» ማለቱ፣
ምንም እንኳ ከእነርሱ የተለየ ቢመስልም «እጆቹንና ጐኑን
ካልዳሰስኩት አላምንም» ሲል መስማቱንና በመካከላቸው
መሆኑን ለማሳየት፣ በዚህም ሐዋርያትን ለማስደሰትና
ከነበሩበት ፍርሃት ማጽናናት ነው» በማለት ገልጦታል፡፡
መጽሐፍም «ደግሞ አርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔር
መንግሥት ነገር እየነገራቸው፣ በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ
ሕያው ሆኖ ለእነርሱ ራሱን አሳያቸው» ይላል፡፡ /ሐዋ. 1፡3/፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በእነዚህ ቀናት ከጌታ ጋር አንድ
የሚያደርጓትን ምስጢራት አዘውትራ ትፈጽማለች፡፡ በጥንት
ቤተ ክርስቲያን ንዑሰ ክርስቲያኖች ከወጡ በኋላ ቤተ ክርስቲያን
ተዘግቶ ነበር ቅዳሴ የሚቀደሰው፡፡ ይህም ቅዳሴ የጌታ
የትንሳኤው ምሥጢር በመሆኑ ነው፡፡ ከትንሳኤ በኋላ ጌታ
ከሐዋርያት ጋር በተዘጋ ቤት ውስጥ እንደተገናኘ አሁንም
በምስጢራቱ ይገኛልና ይህን ለማዘከር ነው፡፡ በዚህም የተነሳ
በእነዚህ ቀናት ዘወትር ቅዳሴ ይቀደሳል፡፡ ምዕመናንም
በሚቻላቸው መጠን ስጋወደሙ አዘውትረው በመቀበል
እነደሐዋርያት አብረውት ይቆያሉ፡፡
ጌታ መንግሥተ ሰማያተን በማዕድ መስሎ ተናግሯታል /ማቴ.
22፡1-14/፡፡ በመንግሥተ ሰማያት ሥጋዊው ምግብና መጠጥ
ባይኖርም የእግዚአብሔርን ፍቅር እየበላን እየጠጣን፣
እግዚአብሔርን በማወቅ እየረካን፣ ራሱ እግዚአብሔር ምግብና
መጠጥ ሆኖን እንኖራለንና በርግጥም መንግሥተ ሰማያት ራሷ
ማዕድ ናት፡፡
በእነዚህ ቀናት ሰንበታት የሚነበቡ የቅዳሴ ምንባባት በመብል
ላይ ያተኩራሉ፡፡ ጌታም ከትንሳኤው በኋላ ከሐዋርያት ጋር
ደጋግሞ ሲበላ ታይቷል።
በእነዚህ ቀናት መጾም መስገድም በቤተ ክርስቲያን ስርዓት
አይፈቀድም፡፡ በመሰረቱ ትንሳኤ የሥጋም የነፍስም ደስታ
ስለሆነ በእነዚህ ቀናት ሁለቱም ይደሰቱ ዘንድ ቤተ ክርስቲያን
ጾምን ከልክላለች፡፡ ነገር ግን ይህ ማለት እንደፈለጋችሁ
እየበላችሁ ኃጢኣት ሰሩ ማለት አይደለም፡፡ ምንጊዜም ግማሽ
እውነት ሙሉ እውነት አይሆንም፤ እንዲያውም ግማሽ እውነት
ብቻውን ውሸትም ሊሆን ይችላል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን
በእነዚህ ቀናት የሥጋ ምግብን ብቻ ሳይሆን የነፍስ ምግብንም
በብዛት ታቀርባለች፡፡ በየቀኑ ቅዳሴ ይቀደሳል፤ ቃለ
እግዚአብሔርን እንድንመገብ ታዛለች፡፡ የሥጋን ምግብ
ተቀብለን ነፍሳችንን ግን ካስራብናት ግማሽ እውነት ነውና
ውሸት ሆኖ ችግር ውስጥ ይከተናል፡፡
በእነዚህ ቀናት እንዳንጾምና እንዳንሰግድ መከልከሉ አንዱ
ምክንያት ጸጋ እግዚአብሔርን እንድናስብ ነው፡፡ በቤተ
ክርስቲያናችን ሥርዓት ከዓመቱ አብዛኞቹ ቀናት የጾም ቀናት
መሆናቸው እውነት ነው፡፡ ነገር ግን አብዝቶ መጾምና መስገድ
ለክርስቲያን አስፈላጊ ቢሆንም የድኅነት መጠበቂያ እንጅ
የድህነት ምንም አይደለም፡፡ ጾምና ስግደትም ቢሆን ያለ ጸጋ
እግዚአብሔር አጋዥነት አይሆንም፡፡ /ዮሐ. 15፡5/
አንዳንዶቻችን በእነዚህ ቀናት ጾምና ስግደት ስለሌለ
እንቸገራለን፤ ቀናቱንም ከመደሰት ይልቅ የምንጠላቸው፤
ከመናፈቅ ይልቅ እስከሚያልቁ የምንጓጓላቸው ይሆናሉ፡፡
ይህም በእነዚህ ቀናት ጸጋ እግዚአብሔር ይጠብቀኛል ብሎ
ካለማመንና ይህም እንዲሆን ካለመጸለይ የተነሳ የሚመጣ
ነው፡፡ ጾምና ስግደት /ትህርምት/ ንጽሕናን ለመጠበቅ አስፈላጊ
ቢሆንም ያለነዚህ ነገሮች ጸጋ እግዚአብሔር ሰውን በንጽሕና
መጠበቅ ይቻለዋልን? ብሎ መጠራጠር ግን በራስ ጽድቅ
መተማመን ነውና ኃጢኣት ነው፡፡ ስለዚህ በረቂቅ የመንፈስ
ቅዱስ ጥበብ የምትመራ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ይህን
ችግራችንን የምንመረምርበት ወቅት ይሆነን ዘንድ እነዚህን
ቀናት አዘጋጅታልናለች፡፡
ምንም እንኳን ከብዙ በትንሹ ጠቅለል አድርገን ያየናቸው
ቢሆንም እያንዳንዶቹ እሁዶች የራሳቸው መልዕክት ስላላቸው
በአጭሩ እንደሚከተለው እናቀርባለን፤
ምንባባት፡- 1ኛ ቆሮ. 15፡20-47
2ኛ ጴጥ. 1፡1-13
3ኛ የሐ. ሥራ. 2፡22-37
ምስባክ፡- እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት
ሐሴትንም እናድርግ በርሷም ደስ ይበለን
አቤቱ እባክህ አሁን አድን
ወንጌል፡- ዮሐ. 20፡1-19
መልዕክት
የትንሳኤ መልዕክት የድኅነት ደስታ ነው፡፡ ሰው የሚደሰተው
በድኅነት ነው፡፡ ስለዚህም ምስባኩ ድኅነትን ደስታንና ይህችን
የትንሳኤ ዕለት አጣምሯቸዋል፡፡ እመቤታችንም በመድኃኒቴ
በእግዚአብሔር ሐሴት አደርጋለሁ /ሉቃ. 1፡47/ ማለቷ
ይህንኑ ያሳያል፡፡ የመጀመሪያውን የጥፋት የሞት የፍርድ ሃዘን
ቀጸሜ የሰማች ሄዋን ናትና፤ የጌታን የትንሳኤ ደስታም ቀድማ
ማርያም መግደላዊት መስማቷን ወንጌሉ ይነግረናል፡፡ ሁሉም
ምንባባት በትንሳኤ ያገኘነውን ድህነትና በዚህም የሚጠብቀንን
ዘላለማዊ ደስታ በተለያየ መንገድ የሚገልጡ ናቸው፡፡
ምንባባት፡- 1ኛ ቆሮ. 15፡1-20
2ኛ ዮሐ 1፡1-ጳጉሜ
ዮሐ. ሥራ 23፡1-10
ምንባባት፡- እግዚአብሔር ይነሳ ጠላቶቹም ይበተኑ
የሚጠሉትም ከፊቱ ይሸሹ
ጢስ እንደሚበን እንዲሁ ይሁኑ
ወንጌል፡- ዮሐ. 20፡19 - ፍጻሜ
መልዕክት
የጌታ ትንሳኤ ድል ነው፡፡ ጌታችን በትንሳኤው ሞትንና
ዲያብሎስን ድል አድርጓል፡፡ የሰው ዘር ሁሉ በዚህ ድኅነት
እንዳይጠቀም የሚያደርገው በጌታ ትንሳኤ አለማመኑ ነውና
ጌታ በትንሳኤው ድል እያደረጋቸው ያሉት ጠላቶቹ ጥርጥርና
ተጠራጣሪዎች ናቸው፡፡ በዚህ ዕለት የሚነበቡት ምንባባት በዚህ
ይተባበራሉ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ጌታ መነሳቱን፣ ለሐዋርያትና
ለርሱ ለብዙዎችም መታየቱን ከገለጠ በኋላ በትንሳኤ
የማያምኑ ግን፣ የክርስትናን ወንጌል ከንቱ የሚያደርጉ፣
ለሆዳቸው የሚኖሩ፣ ምስኪኖች ይላቸዋል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ
በበኩሉ እንደታማኝ ሐዋርያነቱ የህይወትን ቃል ማየቱን፣ አካሮ
መብላቱን መጠጣቱን፣ መዳሰሱን ተናግሮ ደስታችን ከእርሱ ጋር
ይፈጸም ዘንድ በትንሳኤ እንድናምን «ሕይወት ተገለጠ» ብሎ
ይመሰክራል፡፡ በሐዋርያት ሥራም በትንሳኤ ሙታን ምክንያት
በፈሪሳውያንና በስዱቃውያን መካከል መከፋፈል መሆኑን
ያሳያል፡፡ ወንጌሉ በበኩሉ ቶማስ መጠራጠሩንና ጌታ ጐኑንና
እጆችን አሳይቶ እንዳሳመነው፣ ነገር ግን «ያመንክ እንጂ
ያላመንከ አትሁን» ብሎ እንደገለጸው ያስረዳል፡፡ ምስባኩም
ጠቅለል አድርጐ የጌታ የትንሳኤው ጠላቶች እንደሚበተኑ፣
የጌታን ትንሳኤ የሚጠራጠሩ እንደሚጠፉ ይናገራል፡፡
በአጠቃላይ የዚህ እሁድ መልዕክት «የጌታን ትንሳኤ ያመኑ
እንደሚድኑና ሐሴት እንደሚያደርጉ ያላመኑ ግን ጠላቶች
ናቸውና እንደሚጠፉ» ያሳያል፡፡
ምንባባት፡- 2ኛ ቆሮ. 5፡11-ፍጻሜ
2ኛ ጴጥ. 3፡14- ፍጻሜ
ዮሐ. ሥራ 21፡31- ፍጻሜ
ምንባባት፡- እግዚአብሔር አሁን እነሳአሁ ይላል
መድኃኒት አደርጋለሁ በላዩም እገለጣለሁ
የእግዚአብሔር ቃላት የነጹ ቃላት ናቸው፡፡
ወንጌል፡- ሉቃ. 24፡13-33
መልዕክት
በዚህ እሁድ የሚታሰቡት የኤማሁስ መንገደኞች ናቸው፡፡ ጌታ
በተነሳበት ዕለት ስለሞቱ እያወሩ እየተጨነቁ ሲሄዱ ቀርቦ
እንደጠየቃቸውና እነርሱም ሳያውቁት በኢየሩሳሌም ስለሆነው
ነገር እንደነገሩት፣ ጌታ በመሞቱም «እስራኤልን ይበዣል
ያልነው እርሱ ነበር» በማለት ተስፋቸው እንደጠፋ እንደነገሩት፣
ጌታችንም መጻሕፍትን ተርጉሞ ክርስቶስ ሊሞትና በሦስተኛው
ቀን ሊነሳ እንደሚገባው እንዳስረዳቸው፣ ህብስቱን ሲቆርስም
እርሱ መሆኑን እንዳወቁትና ከመካከላቸው እንደተሰወረ
ያስረዳል፡፡ የዚህ እሁድ ትኩረት ቅዱሳት መጻሕፍት የጌታ
የትንሳኤው ምስክሮች መሆናቸውን ማሳየት ነው፡፡ የቅዱስ
ጳውሎስ መልዕክት ቅዱስ ጳውሎስ ለእግዘብሔር የሚኖርና
ለማንም ሳይል ስለ እግዚአብሔር ሲል የሚሰብክ መሆኑን
ተናግሮ ሁሉም ክርስቲያኖች እንዲህ መሆናቸውን ይናገራል፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ በበኩሉ ለድኅነታችን እንድንጠነቀቅ በመምከር
አንዳንዶች የቅዱስ ጳውሎስን ጨምሮ ብዙ መጻሕፍትንም
ቢያጣምሟቸውም በትክክል ለተረዳቸው ግን መጻሕፍት የጌታ
የትንሳኤው ምስክሮች፣ የድህነት ቃላት መሆናቸውን
ይናገራል፡፡ የሐዋርያት ሥራው ታሪክም ቅዱስ ጳውሎስ
በአይሁድ እጅ የተቀበለውን መከራ በማሳየት ታመኝነቱን
ያረጋግጣል፡፡ ሁሉንም ጠቅለል አድርጐ የዕለቱ ምስባክ
እግዚአብሔር መነሳቱን መድኃኒትም ማድረጉን፣ በትንሳኤው
ለአለም ሁሉ መድኃኒትነቱ መገለጡን፣ የእግዚአብሔር ቃላት
መጻሕፍትም ንጹሐን ምስክሮቹ መሆናቸውን ይናገራል፡፡
ከወንጌሉ ታሪክ እንደምንማረው መጻሕፍት ከእውነተኛው
ምንጭ ከክርስቶስ ስንማራቸው ልቦናን እስከማቃጠል
ደርሰው ጽኑ ምስክሮች ቢሆኑም ጌታ ህብስቱን ቆርሶ
እስኪሰጣቸው ድረስ ግን አላወቁትም ነበር፡፡ ይህም መጻሕፍት
የጌታን ትንሳኤና ሕማማት ቢገልጡም ይህ መገለጥ ፍጹም
የሚሆነው ግን በሥጋወደሙ መሆኑን ያሳያል፤ በሥጋወደሙ
የጌታን ሞትና ትንሳኤ በተግባር እንመሰክራለንና፡፡
ምንባባት፡- ቆላ. 3፡1- ፍጻሜ
1ኛ ጴጥ. 3፡15- ፍጻሜ
የሐ. ሥራ. 11፡1-19
ምስባክ፡- እኔ ተኛሁ አንቀላፋሁም
እግዚአብሔር ደግፎኛልና ነቃሁ
ከሚከብቡኝ ከአእላፍ ሕዝብ አልፈራም፡፡
ወንጌል፡- ሉቃ. 24፡33-45
መልዕክት
ክርስትና ትንሳኤ ልቦና፣ ዕርገተ ልቦና ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ
«ሕይወታችሁ ከክርስቶስ ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ
ተሰውሯል» በማለት የክርስቲኖች ሕይወት ሰማያዊ መሆኑን
ከገለጠ በኋላ ሁሉም በየበኩሉ ይህን ሕይወቱን እንዲኖር
ይመክራል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም «በበጐ ህሊና» እንድንኖር
ይመክርና ስለዚህ ስንል መከራ ብንቀበል ከክርቶስ ጋር
እንደምንከብር ይናገራል፡፡ የሐዋርያት ስራም አህዛብን
እግዚአብሔር መቀበሉንና በዚህም ከአይሁድ የመጡ
ክርስቲያኖች መደሰታቸውን ያሳያል፤ ይህም በጐ ህሊና ነውና፡፡
ወንጌሉም የሚገለጠው ሐዋርያትና አርድእት በነበሩበት ጌታ
መታየቱንና በዚያም የሆነውን ደስታ ያበስራል፡፡ የሁሉም
ሃሳቦች ማጠቃለያ ከምስባኩ ይገኛል፡፡ ጌታ መሞቱን፣
መነሳቱን በዚህም ለሰማያዊ ህይወት፣ ለበጐ ህሊና የሚሆኑ
አእላፍ ምዕመናንን «በትንሳኤ ልቦና» ማስነሳቱን፣ ይህም
የቅድስት ሥላሴ ፈቃድ ስለሆነ የጸና መሆኑን ይገናራል፡፡
ምንባባቱ፡- ሮሜ. 4፡14
ራዕይ. 20፡1- ፍጻሜ
የሐ. ሥራ. 10፡39-44
ምስባክ፡- በሉ እጅግም ጠገቡ
ምኞታቸውንም ሰጣቸው
ከወደዱትም አላሳጣቸውም
ወንጌል፡- ዮሐ. 21፡1-15
መልዕክት
ቅዱስ ዮሐንስ ይህንን የወንጌል ክፍል የጻፈው ወንጌልን
ከፈጸመ በኋላ ነው፡፡ ይህም የጥብርያዶስ ባህር ማዕድ
በሊቃውንት ትርጓሜ ከዚህ ዓለም በኋላ ጌታ ከምዕመናን ጋር
ከሚያደርገው ዘላለማዊ ማዕድ ጋር እንዲያያዝ አድርጐታል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ በተዘዋዋሪ መንገድ ከህግ በላይ የሆነውን
ሰማያዊውን ህይወት በአብርሃም የተስፋ ቃል መቀበላችንን
ሲገልጽ ጌታንም በዳግም ምጽአት የሚፈርድ መሆኑን
ገልጧል፡፡ በራዕይ ዮሐንስም ጌታ በህያዋንና በሙታን
እንደሚፈርድና ለዘላለም የሚሆን ክብርን ለቅዱሳን
እንደሚሰጥ፣ ይገልጣል፡፡ በአጠቃላይ በዚህ ምድር ላይ
እግዚአብሔርን እንቀምሰዋለን እንጅ አንጠግበውም፤
በዘላለም ህይወት ግን እንጠግበዋለን፤ ከወደድነውም
አያሳጣንም፤ ምኞታችን መንግሥተ ሰማያትንም ይሰጠናል፤
እርሷም ዘላለማዊት ማዕድ ናት፡፡ ሐዋርያት ያጠመዷቸውን
አሳዎች የያዘው መረብም አለመቀደዱ መንግሥተ ሰማያት
ሰላም ያለባት፣ ለሁሉም የምትበቃ መሆኗን ያሳያል፤ «ጌታ
በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ» ያለው ይህንኑ ነው፡፡
ምንባባት፡- ሮሜ. 6፡1-15
1ኛ ጴጥ. 4፡4-12
የሐ. ሥራ. 23፡15-22
ምስባክ፡- መዝ. 16፡16 የናሱን ደጆች ሰብሯልና
የብረቱንም መወርወሪያ ቆርጧልና
ከበደል ጐዳናቸው ተቀበላቸው፡፡
ወንጌል፡- ዮሐ. 21፡15- ፍጻሜ
መልዕክት
በጌታችን ሞትና ትንሳኤ ድኅነትን አግኝተናል፡፡ ይህንንም
ሞትና ትንሳኤ በጥምቀት መካፈላችንን ቅዱስ ጳውሎስ በዕለቱ
ምንባብ ይናገራል፡፡ ትንሳኤውን መካፈላችንም አሁን በትንሳኤ
ልቦና ከኃጢአት በመራቅ በኋላም በመጨረሻ ትንሳኤ ነው፡፡
ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ የጥምቀት ልጆች ኃጢአትን ይሰሩ ዘንድ
እንደማይገባቸው ይናገራል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ይህን የትንሳኤ
ሕይወት እንኖር ዘንድ፣ በፍቅርም የኃጢአታችን ብዛት
ይሸፍናልና እንዋደድ ዘንድ ይመክረናል፡፡ የዕለቱ የወንጌል
ምንባብም ጌታ በትንሳኤው ምሽት ለሐዋርያት ሐጢአትን
ይቅር የማለት ስልጣን መስጠቱንና በዚህም የጌታ የትንሳኤው
ኃይል የኀጢአት ሥርየትና ትንሳኤ ልቦና ሆኖ መሰጠቱን
ያሳየናል፡፡ በዚህም ቅዱስ ጴጥሮስን ከክህደት በመመለስና
«መሞት እንኳ ቢያስፈልገኝ ከአንተ ጋር እሞታለሁ» ያለው
ቃል በትንሳኤ ልቦና ምዕመናንን በመጠበቅ፣ በኋላም
በሰማዕትነት እንደሚያገኘው አመልክቶታል፡፡ ምስባኩም
የሞትና የኃጢአት ደጆች መሰበራቸውንና፣ ዓመጻና ኃጢአትን
በትንሳኤው ማሳደዱን በትንሳኤው ያመኑትንም ከበደል ጐዳና
አውጥቶ ወደ ትንሳኤ ልቦና እንደመለሳቸው ይገልጣል፡፡
በአጠቃላይ የዕለቱ ምንባባት መልእክታቸው ይህ ነው፤
በትንሳኤ ዘጉባኤ ተነስተን በመንግስት ሰማያት ከጌታ ጋር
እስክንኖር ድረስ በዚህ ምድር ላይ ትንሳኤ ልቦና ቀርቶልናል፤
ትንሳኤ ልባናም ከኃጢአት በመራቅ ልቦናን ሰማያዊ አድርጐ
መኖር ነው፡፡ ድቀተ ልቦና /የልቦና መውደቅ/ በኃጢኣት መኖር
እንደሆነ ሁሉ፣ ትንሳኤ ልቦና /የልቦና ትንሳኤ/ ከኃጢአት ርቆ
በንጽሕና መኖር ነውና፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ትንሳኤ
ልቦናን ያድለን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር