ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

Thursday, May 5, 2016

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ: +*"#ሚያዝያ 27 "*+

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
አሜን
ሚያዝያ 27-በወላጅ አባቱ በህርማኖስ ትእዛዝ ሰማዕትነትን
የተቀበለው ታላቁ ሰማዕት ቅዱስ ፊቅጦር ዕረፍቱ ነው፡፡
ዳግመኛም ሚያዝያ 23 የሊቀ ሰማዕታት የቅዱስ ጊዮርጊስ
ዕረፍቱ ቢሆንም ዕለቷ የከበረች የትንሣኤ ዕለት ስለሆነች
በዚኽች የከበረች ዕለት ሌላ በዓል ማክበር ተገቢ አይደለምና
ብዙዎቹ የሰማዕቱ መታሰቢያ አብያተ ክርስቲያናት ዛሬ ሚያዝያ
27 ቀን ታቦት አውጥተው በዓሉን ያከብሩለታል፡፡ አ.አ ያሉት
ገነተ ጽጌዎች የቅዱስ ጊዮርጊስን የዕረፍቱን በዓል በዚኹ ዕለት
ታቦት አውጥተው እንደሚያከብሩ በትንሣኤ ዕለት
አሳውቀዋል፡፡ ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ያደረገውን
ታላቅ ተአምርና ገድሉን በኋላ እናያለን፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ ከትንሣኤ እሑድ እስከ ቀጣዩ እሑድ
ያለው ሳምንት ‹‹ሰሙነ ትንሣኤ›› ተብለው ሌሎች የጌታችን
በዓላት ተደርገው ይቆጠራሉና ከትንሣኤ እሑድ እስከ ቀጣዩ
እሑድ ያለው ሳምንት ‹‹ሰሙነ ትንሣኤ›› ሲባል በዚህ ሳምንት
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በፍጹም ደስታና ሐሴት የቤዛዋን
የመድኀኔዓለምን ትንሣኤ የምታስብበት ወቅት ነው፡፡ እነዚህን
ዕለታት እንደ እሑድ ማክበር ይገባል፡፡ ዕለታቱ በሌላ አገላለጽ
የሰሙነ ሕማማቱ (የፍጹም ሐዘኑ፣ ስድግደቱ፣ ጾሙና ጸሎቱ)
አጸፋዎች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ፍትሐ ነገሥቱም
እንደሚያዘው እነዚህን ዕለታት እንደ ዕለተ እሑድ አድርጎ
ማክበር ይገባል፡፡
ዳግመኛም በዚኽች ዕለት ሚያዝያ 27 ቀን የዛሬን አያድርገውና
የቀደሙ አባቶቻችን ሀገር፣ እምነት፣ ታሪክ፣ ባሕልና
ማንነታችንን ለጠላት አሳልፈው ላለመስጠት ብዙ መከራ
ተቀብለው ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥትታቸውን ከስክሰው
ያረፉበት 75ኛ ዓመት ክብረ በዓላቸው ነው፡፡
ታላቁ ሰማዕት ቅዱስ ፊቅጦር፡- ቅዱስ ፊቅጦር በዓለም ላይ
ያሉ ከ470,000 በላይ የሚሆኑ ክርስቲያኖችን ከሃዲው ንጉሥ
ዲዮቅልጥያኖስ በግፍ ያስገድል በነበረበት ወቅት የተገኘ ታላቅ
ሰማዕት ነው፡፡ የቅዱስ ፊቅጦር እናቱ ማርታ አማኝ ክርስቲያን
ነበረችና ገና ከመጀመሪያው ተወዳጅ ልጇን ከመውለዷ በፊት
የአምላክ እናት የቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ወዳለችበት
ሄዳ ‹‹እመቤቴ ማርያም ለኢየሱስ ክርስቶስ ደስ የሚያሰኘውን
ልጅ ስጪኝ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን ደስ የማያሰኝ ልጅ ከሆነ ግን
ማኅፀኔን ዝጊ›› እያለች ትለምናት ነበር፡፡ እመቤታችንም
ጌታችን ከሰማዕታት ሁሉ አብልጦ የሚወደውን ልጅ ቅዱስ
ቅዱስ ፊቅጦርን ሰጠቻት፡፡ ማርታም ተወዳጅ ልጇን የካቲት
13 ቀን ወለደችው፡፡
ቅዱሳን የሆኑ የከበሩ የመንግሥት ልጆች እነ ፋሲለደስ፣
ፊቅጦር፣ ዮስጦስ፣ አባድር፣ ገላውዲዮስ፣ ቴዎድሮስ በናድልዮስ፣
መቃርስ ሰማዕት፣ አውሳብዮስና ሌሎቹም በየቦታው ከፋርስና
ከቁዝ ሰዎች ጋር ተዋግተው ጠላቶቻቸውንም ሁሉ ድል
ነሥተው ወደ ሀገራቸው በተመለሱ ጊዜ ንጉሡ ዲዮቅልጥያኖስ
ወጥቶ በደስታና በታላቅ ክብር ተቀበላቸው፡፡ ከዚህም በኋላ
የቅዱስ ፊቅጦር አባት የሆነው መኰንኑ ህርማኖስ ለጣዖት
እንዲግዱና ምስጋና እንዲያቀርቡ ለንጉሡ መከረው፡፡ ንጉሡም
እንደተመከረው ለአጵሎን ሰግደው ዳግመኛ ደስ እንደዲያሰኙት
ሲጠይቃቸው ቅዱሳኑ እጅግ ተቆጡት፡፡ ቅዱስ አውሳብዮስም
ንጉሡን ለመግደል ሰይፉን ሲመዘዝ አባቱ ቅዱስ ፋሲለደስ
ከለከለው፡፡ በንዴትም ከንጉሡ ጭፍሮች ብዙዎችን ገደሉ፡፡
የከበረ ፋሲለደስም ባይከለክላቸው ኖሮ ከንጉሡ ቤት ምንም
ሰው ባልቀራቸው ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ ህርማኖስ ቅዱስ
አውሳብዮስን ወደ ግብፅ እንዲልከው መከረው፡፡ ይህም የንጉሡ
መኰንን ህርማኖስ የገዛ ልጁን ቅዱስ ፊቅጦርን ወደ ግብፅ
በማስላክ አሠቃይቶ ያስገደለ አረመኔ ነው፡፡
ቅዱስ ፊቅጦርን ገና 15 ዓመት እንደሆነው ንጉሡ ‹‹ከፍ ባለ
ስልጣን አስቀምጥሃለሁ፣ እጅግ ብዙ ወርቅና ንብረትም
እሰጥሃለሁ፣ በእስክንድሪያም ላይ ገዥ አድርጌ እሾምሃለሁ
ክርስቶስን ማመንህን ተውና ወደ ቤተ መንግሥቴ ግባ››
አለው፡፡ ቅዱስ ፊቅጦር ግን ብዙ መከራንና ስቃይን ተቀብሎ
ሰማዕት መሆንን መረጠ፡፡ ቅዱሱም 20 ዓመት በሆነው ጊዜ
ንጉሡ በመንግሥቱ 3ኛ አድርጎ ሾመው፡፡ ነገር ግን ቅዱስ
ፊቅጦር በመንግሥት ሥልጣን ላይ ሆኖ በጾም በጸሎት
ምጽዋትም በመሥጠት ይተጋ ነበር እንጂ ሥጋ አይበመገብም፣
ጠጅም አይጠጣም ነበር፡፡ በቀንና በሌሊትም እየጸለየ
የታሠሩትም ይጠይቃቸዋል፡፡
የወንድማማቾቹ ሰማዕታት የቆዝሞስና ድምያኖስ እናት
ቅድስት ቴዎዳዳ አንገቷን ተሰይፋ በሰማዕትነት ባረፈች ጊዜ
ሥጋዋ በመሬት ላይ ወድቆ ቀረ፡፡ በዚህም ጊዜ የንጉሡ
የቅርብ አማካሪና ባለሥልጣን የነበረው የህርማኖስ ልጁ ቅዱስ
ፊቅጦር ከንጉሡ የሚመጣውን ቅጣት ሳይፈራ ከመንግሥት
ሰዎች መካከል ደፍሮ ሥጋዋን አንሥቶ ገንዞ ቀበራት፡፡ በዚህም
ቅዱስ ፊቅጦር ተከሰሰና ንጉሡ ፊት ቆመ፡፡ ለንጉሡም
‹‹ክርስቶስን በምታፈቅረው ጊዜ አፈቀርኩህ ወደ አንተም
መጣሁ፤ ክርስቶስን በጠላኸው ጊዜ ግን እኔም ጠላሁህ፣
ቤትህንም ጠላሁ አለው፡፡›› የቅዱስ ፊቅጦር አባቱ ህርማኖስ
የከሃዲው ንጉሥ የዲዮቅልጥያኖስ የቅርብ እንደራሴና መስፍን
ሲሆን ልጁ ፊቅጦርን የንጉሡን ሹመትና ልመና እንዲቀበል
ሲያግባባው ነበር፡፡ ሀሳቡንም እንዳልተቀበለው ሲያውቅ ወደ
ንጉሡ ሄዶ የገዛ ልጁን አሠቃይቶ ይገድለው ዘንድ ተማከረ፡፡
ቅዱስ ፊቅጦርም በአባቱ ምክር ንጉሥ በዲዮቅልጥያኖስ
ትእዛዝ ወደ እስክንድርያና ወደ እንዴና አገሮች በግዞት ተልኮ
በዚያም እጅግ ተሠቃይቷል፡፡ በእስር ቤት ያሉና ይመግባቸው
የነበሩ ክርስቲያኖችን በእምነት ሲያጸናቸው ቢሰሙት አፉን
ለጉመው ነው ወደ እስክንድርያ የወሰዱት፡፡ መኮንኑ
ኄርሜኔዎስም ይዞ እጅግ አስጨናቂ በሆኑ ሥቃዮች
አሠቃየው፡፡ የታዘዘ መልአክም መጥቶ ቅዱስ ፊቅጦርን ነጥቆ
ወደ ሰማያት ወስዶ ክብራቸውን ለመናገር የማይቻል የብርሃን
ማደሪያዎችን አሳይቶት የእርሱንም ማረፊያ አሳይቶት
መለሰው፡፡ ከዚህም በኋላ መኮንኑ በእሳት ባፈሉት በዝፍጥና
በድን አሠቃየው፡፡ በብረት አልጋም ላይ አስተኝቶ ከሥር እሳት
አነደደበት፡፡ ዳግመኛም ከውሽባ ማንደጃ ውስጥ ጨመረው፡፡
ጌታችንም ከመከራው ሁሉ ያስታግሠውና መልአኩን እየላከ
ከቁስሉ ይፈውሰው ነበር፡፡
ከዚህም በኋላ የእስክንድርያው መኮንን ማሠቃየት በሰለቸው
ጊዜ ወደ እንዴና ላከው፡፡ በዚያም ያለው መኮንን በእጅጉ
አሠቃየው፡፡ ምላሱን ቆረጠው፡፡ በእሳት በጋሉ የብረት
ችንካሮች ጎኖቹን ወግቶ አቃጠለው፡፡ ነገር ግን ጌታችን
ያለምንም ጉዳት አስነሣው፡፡ ዳግመኛም በረሃብ ይሞት ዘንድ
በዱር ከሚገኝ ግምብ ውስጥ አሠሩት፡፡ መኮንኑም ዳግመኛ
ካሠቃየው በኋላ ቁልቁል ሰቅሎ በእጆቹ ላይ ከባድ ድንጋይ
አንጠለጠለ፡፡ ከዚያም በሚነድ እሳት ውስጥ ጨመሩት፡፡
በማበራያም አበራዩት፡፡ ሐሞትና እሬትም በአፉ ጨመሩበት፡፡
ዐይኖቹንም ካወለቁት በኋላ ዳግመኛ ዘቅዝቀው ሰቀሉት፡፡
ጌታችንም በዚህ ጊዜ ተገልጦት አረጋጋውና ሥሮቹንና
ሕዋሳቶቹን ሁሉ ቦታቸው መለሰለትና አዳነው፡፡ ታላቅ
ቃልኪዳንም ገባለት፡፡ ጌታችን ለሌሎቹ ሰማዕታት ቃልኪዳን
ሲገባላቸው ‹‹እንደ ወዳጄ ፊቅጦር…›› እያለ ነው፡፡ ይኽም
ከሌሎቹ ሰማዕታት አብልጦ እንደሚወደው ያሳያል፡፡ በዚህም
ጊዜ አንዲት የ15 ዓመት ብላቴና የብርሃን መላእክት ለሰማዕቱ
ለቅዱስ ፊቅጦር የክብር አክሊል ሲያቀዳጁት አይታ ጮሃ
ተናገረች፡፡ የሰማዕቱንም ተአምራት ያዩት ሕዝቦች ‹‹በቅዱስ
ፊቅጦር አምላክ አምነናል›› እያለ በመመስከር ከዚያች ብላቴና
ጋር ተሰይፈው የክብርን አክሊል ተቀዳጁ፡፡
ቅዱስ ፊቅጦርም ሚያዝያ 27 ቀን አንገቱን ተሰይፎ
ሰማዕትነቱን በድል ፈጽሞ የክብር አልክሊልን ተቀዳጅቷል፡፡
ምእመናንም ሥጋውን በክብር ገንዘው አስቀመጡት፡፡ እናቱ
ማርታም ከአንጾኪያ መጥታ ወሰድው፡፡ ያማረች ቤተ
ክርስቲያንም ሠርታ ሥጋውን በውስጧ አኖረች፡፡ የሰማዕቱ
ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡
ይህ ታላቅ ሰማዕት ስለ አገራችን ኢትዮጵያ የተናገረው አንድ
ትልቅ ትንቢት አለ፡፡ ይኸውም ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሮም
በሃይማኖት አንድ እንደሚሆኑ የተነገረው ትንቢት ነው፡፡
በቅዱስ ገድሉ ላይ እንዲህ ተብሎ ነው የተጻፈው፡-
‹‹እግዚአብሔር ዲዮቅልጥያኖስን ፈጽሞ ከአጠፋው በኋላ
ቈስጠንጢኖስን አነገሠው፡፡ ቈስጠንጢኖስም ሃይማኖትንና
በክርስቶስ ማመንን አጸና፡፡ ጣኦታትንና የጣኦታትን ቤቶች
አፈራረሰ፣ ቤተክርስቲያንን አነጸ፡፡ የፊቅጦር እናት ማርታም
ብዙ አናፂዎችን ይዛ፣ ብዙ ገንዘብ፣ ወርቅና ብርን፣ የከበሩ
አልባሳትን፣ ታላላቅ እንጨቶችን በመርከቦች ሞልታ ወደ
እስክንድርያ ሄደች፡፡ የልጇ የፊቅጦር ሥጋ ወዳለበት ገባች፡፡
ሥጋውንም አቅፋ መሪር ለቅሶን አለቀሰች፡፡ ነገር ግን በስደት
በሄደበት ሀገር ሁሉ ስለ እርሱ ተአምራትና ድንቅ እንደተደረገ
ስለ ክርስቶስም ሰማዕት እንደሆነ በሰማች ጊዜ ተደሰተች፡፡
ሰማዕት በሆነበትና ደሙ በፈሰሰበት ቦታ ላይ ትልቅ
ቤተክርስቲያን አነጸች፡፡
በቤተክርስቲያኑ እንጨት ሁሉ ላይ ወርቅንና ብርን
አደረገችበት፡፡ ማርታም ከሚያንጹት ባለሙያዎች መካከል
አንዱ ወርቅ ሲሰርቅ አየችው፡፡ በዚህም ምክንያት በልቧ አዝና
‹እኔ እያለሁ ወርቁን የሠረቁ እንዴት በኋለኛው ዘመን
ይተውታል?› አለች፡፡ ሌሊት ተኝታ ሳለች በሕልሟ ልጇ ቅዱስ
ፊቅጦር ተገልጾላት ‹እናቴ ማርታ ሆይ ሰላም ላንቺ ይሁን›
አላት፡፡ ‹አሁንም እናቴ ሆይ ስሚኝ አስረዳሻለሁ፡፡ በእንጨቱ
ላይ ሁሉ ወርቅንና ብርን በዚህች ቤተክርስቲያን ላይ አታድርጊ፤
እስላሞች የሚመጡበትና በግብፅ ሀገር የሚነግሡበት ጊዜ
ይመጣልና፡፡ (እስላሞች የሚለውን ግእዙ ተንባላት ይለዋል)
እነዚያ እስላሞችም በሚመጡበት ዘመን በቤተክርስቲያኗ ላይ
የተሠራውን ወርቅና ብር ባዩ ጊዜ ስለ ወርቅና ብር ፍቅር
ብለው ይዘርፏ፣ ያፈርሷታል፡፡ አንቺ ግን በድንጋይ በእንጨትና
በብረት ሥሪ፡፡ ቤተክርስቲያኗም ብዙ ዘመን ትኖራለች› አላት፡፡
ማርታም እስላሞች በግብፅ ሀገር እንደሚነግሡ በሰማች ጊዜ
ስለ ክርስቶስ ሕግ አዘነች፡፡ ‹እንደዚህ ከሆነማ ቤተክርስቲያን
በመሥራት ለምን እደክማለሁ?› አለች፡፡ ፊቅጦርም ‹እናቴ
ሆይ አትዘኚ፤ በእስላሞችም ጊዜ በግብፅ ሀገር ሁሉ የክርስቶስ
ሕግ አይቋረጥም፡፡ የጾም፣ የጸሎትና የቁርባን እምነት
ይኖራል፡፡ ከእስላሞች ጋር እየኖሩ የሃይማኖት ጽናት ትበዛለች፤
በማርቆስ መንበርም የሊቀ ጳጳሳት መሾምም አይቋረጥም፤
በሊቀ ጳጳሳት እጅ በየደረጃው የጳጳሳት፣ የኤጲስ ቆጶሳት፣
የቀሳውስትና የዲያቆናት ሹመትም አይቋረጥም› አላት፡፡
‹የኢስላሞችም መንግሥት ጥቂት ዘመናት ናቸው፡፡ ከጥቂት
ዘመናት በኋላ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ ሀገር ክርስቶስን
የሚወድ ቅዱስ ሰው ያነግሣል፡፡ አረማውያንም በእርሱ እጅ
ይደመሰሳሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ ግብፅ ሀገር ሄዶ እስላሞችንና
መንግሥታቸውን ሁሉ ያጠፋል› አላት፡፡ ‹እግዚአብሔር
በቁስጥንጥንያ እርሱን የሚወድ ስሙ ትውልደ አንበሳ የተባለ
ሰው ያነግሳል፡፡ ከኢትዮጵያ ንጉሥ ጋር ይገናኝ ዘንድ ይመጣል፡፡
በግብፅ መሀል ቦታ ላይ ይገናኛሉ፡፡ ከእርሱ ጋርም የእስክንድሪያ
ሊቀ ጳጳሳትና የቁስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት ይገናኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ ንጉሥ ሠራዊቱን በደቡብ በኩል ትቶ
የቁስጥንጥንያም ንጉሥ ሠራዊቱን በሰሜን በኩል ትቶ ሁለቱ
ነገሥታትና ሁለቱ ሊቃነ ጳጳሳት ተገናኝተው እርስ በእርሳቸው
ሰላምታ ይሰጣጣሉ፤ ሊቃነ ጳጳሳቶቹ በመንበራቸው ላይ
ተቀምጠው ነገሥታቱን ‹በየመንበራችሁ ላይ ተቀመጡ›
ይሏቸዋል፡፡ የቁስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት ‹የእኛ ሃይማኖት
ትበልጣለች› ይላል፡፡
የእስክንድሪያውም ሊቀ ጳጳሳት ‹እግዚአብሔር የሰጠኝን ቃል
እኔ እነግራችኋለሁ› ይላል፡፡ ሁለቱ ነገሥታትም ‹አባታችን በል
ንገረን› ይሉታል፡፡ ‹የአባ ሲኖዳ ወደምትሆን ወደዚህች ታላቅ
ቤተክርስቲያን ገብተን በአንዲት ታቦት ላይ እኔ እቀድሳለሁ፣ ይህ
ባልደረባዬ ሊቀ ጳጳሳት በአንዲቷ ታቦት ላይ ይቀድስ፤ ሁሉም
ሕዝብ ሠራዊቶቻችሁም መጥተው ይመልከቱ› ይላል፡፡
‹መንፈስ ቅዱስ እያያችሁት ከሁለታችን በአንዱ ቁርባን ላይ
ከወረደ በዚያ ሃይማኖት ሁላችን እንሂድ፣ ሃይማኖቷም
ትታወቃለች ቀንታለችና› ይላቸዋል፡፡ ሁለቱ ነገሥታት ‹እሺ
በዚህ ቃል ተስማምተናል፣ የእግዚአብሔር ምክር ናትና›
ይሉታል፡፡ ‹ያን ጊዜ ሁለቱ ነገሥታትና ሊቃነ ጳጳሳት
ሠራዊቶቻቸውም ሁሉ ካህናቶቻቸውም፣ ሕዝቡም ወደዚህች
ታላቅ ቤተክርስቲያን ይገባሉ፡፡ ሁለቱ ሊቃነ ጳጳሳትም በሁለቱ
ታቦታት ላይ ይቀድሳሉ፡፡ በዚያ ያሉ ሁሉ እያዩ መንፈስ ቅዱስ
በነጭ ርግብ አምሳል ከብርሃን ጋር የእስክንድሪያው ሊቀ
ጳጳሳት በቀደሰው ቁርባን ላይ ይወርዳል፡፡ ያን ጊዜ የኢትዮጵያ
ንጉሥ ይደሰታል፣ የእርሱም ሊቀ ጳጳሳት ነውና፡፡
በእግዚአብሔር ፊትም የእርሱ የሃይማኖት ሕግ የተወደደ
ይሆናል፡፡ የሮም ንጉሥ ግን ከሕዝቦቹ ጋራ ያዝናል፡፡
መጻሕፍቶቻቸውን ሁሉ ሰብስበው ወደ ባሕር
ይወረውሯቸዋል፡፡ ሃይማኖታቸውንም ስለአጠፋና መናፍቃን
ስላደረጋቸው የቀድሞውን ሊቀ ጳጳሳቸውን ሊዎንን
ይረግሙታል፡፡ ሁሉም ወደ አንዲት የእስክንድሪያ ሊቀ ጳጳሳትና
የኢትዮጵያ ንጉሥ ሃይማኖት ይመለሳሉ፡፡ ሮምም፣ ግብፅም፣
ኢትዮጵያም ሁሉም የተስማሙ ይሆናሉ፤ በመካከላቸውም ጽኑ
ፍቅር ይሆናል፡፡ ሁሉም ሃሌ ሉያ እያሉ እግዚአብሔርን
ፈጽመው ያመሰግኑታል፡፡ የኢትዮጵያ ንጉሥና የሮም ንጉሥ
እርስ በእርሳቸው እጅ መንሻንና ሰላምታን ተሰጣጥተው
ወደየሀገራቸው ይመለሳሉ፡፡ ቅዱስ ፊቅጦርም ለእናቱ
የሚነግራትን ይህንን ሁሉ ትንቢት ከጨረሰ በኋላ ‹እናቴ ማርታ
ሆይ ሰላም ላንቺ ይሁን› ብሎ ከእርሷ ተሰወረ፡፡››
/////////////// //////////////
ሊቀ ሰማዕታት ፀሐይ ዘልዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ፡- ሊቀ ሰማዕታት
ቅዱስ ጊዮርጊስ ሀገሩ ፍልስጤም ልዩ ስሟ ልዳ ሲሆን
የተወለደው በ277 ዓ.ም ጥር 20 ቀን ነው፡፡ ጊዮርጊስ ማለት
ኮከብ፣ ብሩህ፣ ሐረገ ወይን፣ ፀሐይ ማለት ነው፡፡ አባቱ ዞሮንቶስ
ወይም አንስጣስዮስ የልዳ መኳንንት ሆኖ ተሹሞ ይኖር ነበር፤
እናቱ ቴዎብስታ ወይም አቅሌስያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ሌላ
ማርታና እስያ የሚባሉ ሁለት ሴት ልጆችን ወልዳለች፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ዐሥር ዓመት በሆመው ጊዜ አባቱ ስለሞተ ሌላ
ደግ ክርስቲያናዊ መስፍን ወስዶ አሳደገው፡፡ መድፍኑም በጦር
ኃይል አሰለጠነው፡፡ ሃያ ዓመትም በሞላው ጊዜ መስፍኑ የ15
ዓመት ቆንጆ ልጅ ነበረችውና እርሷን አግብቶ ሀብቴን ወርሶ
ይኑር ብሎ ድግስ ሲያስደግስ ጌታችን ቅዱስ ጊዮርጊስን ለዚህ
አላጨውምና የመስፍኑን ነፍስ ወሰደ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም
ኀዘኑን ጨርሶ ወደ ቤሩት ሀገር ሄደ፡፡ በቤሩት ደራጎንን
ያመልኩና ሴት ልጆቻቸውን ይገብሩለት ስለነበር ሰማዕቱ
ደራጎኑን በኃይለ መስቀል ድል ነስቶት ሕዝቡን ወደ አምልኮተ
እግዚአብሔር አስገብቷቸዋል፡፡
ወደፋርስ ቢመለስ ዱድያኖስ ሰባ ነገሥታት ሰብስቦ ሰባ ጣዖታት
አቁሞ ሲሰግድ ሲያሰግድ ቢያገኛቸው ለሃይማኖቱ ቀናዒ ነውና
ከቤተመንግስቱ ገብቶ በከሃዲያኑ ሰባው ነገሥታት ፊት
ክርስቲያን መሆኑን በመመስከር የጌታችን የመድኃኒታችን
የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት መሰከረ፡፡ ዱድያኖስም
ማንነቱን ከተረዳ በኋላ ‹‹አንተማ የኛ ነህ በዐሥር አህጉር ላይ
እሾምሃለሁ የኔን አምላክ አጵሎንን አምልክ›› አለው፡፡ ቅዱስ
ጊዮርጊስም ‹‹ሹመት ሽልማትህ ለአንተ ይሁን እኔ አምላኬ
ኢየሱስ ክርስቶስን አልክደውም›› አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ዱድያኖስ
እጅግ ተናዶ ብዙ አሠቃቂ መከራዎችን አደረሰበት፡፡ ቅዱስ
ጊዮርጊስ ግን ጌታችንን ‹‹ይህን ከሃዲ እስካሳፍረው ድረስ ነፍሴን
አትውሰዳት›› በማለት መከራውን ይታገስ ዘንድ ለመነው፡፡
እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰምቶ ፈቃዱን ይፈጽምለት ብዙ
በመከራው ሁሉ ጽናትን ሰጥቶታል፡፡ ሦስት ጊዜም ከሞት
አስነሥቶታል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም የደረሱበት እጅግ አሠቃቂ
መከራዎች የሰው ኅሊና ሊያስባቸው እንኳን የማይችላቸው
ናቸው፡፡
በመጀመሪያም ዱድያኖስ በእንጨት ላይ ካሰቀለው በኋላ
ሥጋውን በመቃን አስፈተተው፣ ረጃጅም ችንካሮች ያሉበት
የብረት ጫማ አጫምቶት ሂድ አለው፡፡ ጌታችንም ቅዱስ
ሚካኤልን ልኮለት ፈውሶታል፡፡ ዳግመኛም በሰባ ችንካሮች
አስቸንክሮ በእሳት አስተኩሶ አናቱን በመዶሻ አስቀጥቅጦ በሆዱ
ላይ የደንጊያ ምሰሶ አሳስሮ እንዲያንከባልሉት አደረገ፡፡
ሥጋውንም በመጋዝ አስተልትሎ ጨው ነሰነሰበት፡፡ ሥጋውም
ተቆራርጦ መሬት ላይ ወደቀ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ በመንፈቀ ሌሊት በእጁ ዳስሶ ከፈወሰውና ‹‹ገና
ስድስት ዓመት ለስሜ ትጋደላለህ፣ 3 ጊዜ ትሞታለህ፣
በ4ኛውም ታርፋለህ›› ካለው በኋላ በመከራውም ሁሉ እርሱ
እንደማይለየው ነገረው፡፡
ዱድያኖስ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከዚያ ካደረሰበት አሠቃቂ
መከራዎች ሁሉ ድኑ ፍጹም ጤነኛ መሆኑን በተመለከተ ጊዜ
እጅግ ደንግጦ ‹‹የሚያሸንፍልኝ ቢኖር ብዙ ወርቅ
እሰጠዋለሁ›› ብሎ ተናገረ፡፡ አትናስዮስ የተባለ መሰርይ
አንዲትን ላም በጆሮዋ ሲያንሾካሹክባት ለሁለት ተሰንጥቃ
ስትሞት ለንጉሡ አሳየውና ቅዱስ ጊዮርጊስን እንዲሚያሸንፍ
ምልክት አሳየ፡፡ ንጉሡም ያሸንፍልኛል ብሎ ደስ አለው፡፡
መሰርይውም ሆድ በጥብጦ አንጀት ቆራርጦ የሚገድል መርዝ
ቀምሞ አስማተ ሰይጣን ደግሞበት እንዲጠጣው ለቅዱስ
ጊዮርጊስ ሰጠው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን ስመ እግዚአብሔርን
ጠርቶ ቢጠጣው እንደ ጨረቃ ደምቆ እንደ አበባ አሸብርቆ
ተገኝቷል፡፡ በዚህም ጊዜ ጠንቋዩ ማረኝ ብሎ ከእግሩ ሥር
ወደቀ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም መመለሱን አይቶ የቆመባትን
መሬት በእግሩ ረግጦ ውሃን አፍልቆ ወደ ጌታችን በጸሎት
ቢያመለክት ሐዋርያው ቶማስ በመንፈስ መጥቶ አጠመቀው፡፡
እርሱም ስለጌታችን አምላክነት መስክሮ ጥር 23 ቀን አንገቱን
ለሰይፍ ሰጥቶ በሰማዕትነት ዐርፏል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን በመንኰራኩር አስፈጭቶ ከትልቅ ጉድጓድ
ጥሎት ደንጊያ ዘግቶበት አትሞበት ሄደ፡፡ ጌታችንም
የተፈጨውን የቅዱስ ጊዮርጊስ ሥጋ በእጁ ዳስሶ ፈውሶታል፡፡
ወደ ከሃዲውም ንጉሥ ተመልሶ ‹‹አምላኬ ከሞት አዳነኝ››
በማለት መሰከረ፡፡ ንጉሡም ዳግመኛ በብረት አልጋ አስቸንክሮ
ከበታቹ እሳት አነደደበት ነገር ግን እሳቱ ደሙ ሲንጠባጠብበት
ጠፍቷል፡፡ ጌታችንም ፈወሰው፡፡ ከዚህም በኋላ ዱድያኖስ ቅዱስ
ጊዮርጊስን ‹‹ኢየሱስ አምላክ መሆኑን አሳየኝ›› ቢለው
የለመለሙትን ዕፅ አድርቆ፣ የደረቁትን ደግሞ አለምልሞ፣
ከሞቱ 430 ዓመት የሆናቸውን ሙታንን አስነሥሰቶ
አሳይቶታል፡፡ ነገር ግን ንጉሡ ልቡ ክፉ ነውና በርኃብና በጽም
ይሙት ብሎ ምንም ከሌላት መበለት ቤት አሳስሮታል።
እርሷም የሚቀመስ ስትፈልግ ቤቷን በእህል አትረፍርፎ
የታሰረበትን ግንድ ማለትም የቤቱን ምሰሶ አለምልሞታል፡፡
ልጇም ጆሮው የማይሰማ ነበርና ፈወሰላት፡፡ መበለቲቷንም
ከነልጆቿ አጥምቆአቸው መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ከእስራቱ
ፈትቶት ተመልሷል፡፡
ዳግመኛም ንጉሡ ዱድያኖስ ጭፍሮቹን ‹‹በመንኰራኩር
ፈጭታችሁ አጥንቱን ደብረ ይድራስ ተራራ ላይ ወስዳችሁ
ዝሩት›› ብሎ አዘዛቸው፡፡ ጭፍሮቹም የቅዱስ ጊዮርጊስን ሥጋ
በመንኰራኩር ፈጭተው ወስደው በተራራው ላይ ቢረጩት
ሥጋው ያረፈበት ሳር፣ ቅጠሉ፣ ደንጊያው፣ እንጨቱ ሁሉ
‹‹ጊዮርጊስ ቅዱሱ ለእግዚአብሔር፣ ጊዮርጊስ ሰማዕቱ
ለእግዚአብሔር›› እያሉ አመስግነዋል፡፡ አሁንም ጌታችን
ለሦስተኛ ጊዜ ከሞት አስነሣውና ሥጋውን ፈጭተው በተራራም
ላይ ሥጋውን በትነውት ወደ ንጉሡ የሚመለሱትን ወታደሮች
በመንገድ ከኋላቸው ሄዶ ደረሰባቸውና ‹‹ቆዩኝ ጠብቁኝ››
አላቸው፡፡ እነርሱም እጅግ ደንግጠው ይህ እንዴት እንደሆነ
ሲጠይቁት ‹‹አምላኬ ከሞት አዳነኝ›› አላቸው፡፡ ጭፍሮቹም
እጅግ ደንግጠው ከእግሩ ስር ወድቀው ይቅር በለን ብለው
በአምላኩ እንደሚያምኑ መሰከሩለት፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም
ከመሬት ላይ ውሃ አመንጭቶ በጸሎት ጌታችንን ቢጠይቅ
ቅዱስ ዮሐንስ መጥቶ አጥምቋቸዋል፡፡ እነርሱም በንጉሣቸው
ፊት ሄደው ስለጌታችን በመመስከር በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡
ንጉሡም ዳግመኛ ቅዱስ ጊዮርጊስን ‹‹በመንግሥቴ ልሹምህ
ለአጵሎን ስገድ›› ቢለው ቅዱስ ጊዮርጊስም ሊያሾፍበት በማሰብ
‹‹እሺ›› ብሎ ወደ ንጉሡ ቤተ መንግሥት ገብቶ የንጉሱን
ሚስት ንግሥቲቱን እለእስክንድርያን አስተምሮ አሳምኗታል፡፡
በነጋም ጊዜ ንጉሡ በአዋጅ ሕዝቡን ሁሉ ሰብስቦ ‹‹ጊዮርጊስ
ለጣዖቴ ሊሰግድ ነውና ኑ ተመልከቱ›› ብሎ ተናገረ፡፡ ቅዱስ
ጊዮርጊስም በተሰበሰበው ሕዝብ መካከል አንድን ብላቴና ጠርቶ
‹‹የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ ጊዮርጊስ ይጠራሃል ብለህ ለጣዖቱ
ንገረው›› ብሎ ላከው፡፡ ብላቴናውም ወደ ጣዖት ቤቱ ገብቶ
ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዳለው ተናገረ፡፡ በዚህም ጊዜ በጣዖቱ ላይ
ያደረው ሰይጣን እየጮኸ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለበት ቦታ ድረስ
መጣ፡፡ በንጉሡና በሕዝቡም ሁሉ ፊት አምላክ አለመሆኑን
ይልቁንም አሳች ሰይጣን መሆኑን በመናዘዝ ከተናገረ በኋላ
ቅዱስ ጊዮርጊስ መሬት ተከፍታ እንድትውጠው አደረገው፡፡
ይህንንም ተዓምር ያዩ ሁሉ ብዙዎች ‹‹በጊዮርጊስ አምላክ
አምነናል›› እያሉ በጌታችን አመኑ፡፡ የንጉሡም ሚስት
እለእስክንድርያ በቅዱስ ጊዮርጊስ አምላክ ካመነች በኋላ ባሏን
ከክፋቱ ተመልሶ እንዲያምን ብትለምነውና ብትመክረውም
አልሰማት አለ፡፡ ይልቁንም ንጉሡ በአደባባይ በሕዝቡ ሁሉ ፊት
የገዛ ሚስቱን አሠቃይቶ ሰውነቷን ቆራርጦ ሰቅሎ አንገቷን
በመሰየፍ ሰማዕትነት እንድትቀበል አደረጋት፡፡ ቅድስት
እለእስክንድርያም ቅዱስ ጊዮርጊስን ‹‹ሳልጠመቅ አልሙት››
ስትለው እርሱም ‹‹ደምሽ ጥምቀት ሆኖልሻልና እነሆ የክብር
አክሊል እየጠበቀሽ ስለሆነ አይዞሽ›› ብሎ አጽንቷታል፡፡
በመጨረሻም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ዘንድ ታላቅ ቃልኪዳን ከተቀበለ በኋላ በ27 ዓመቱ
በሚያዝያ 23 ቀን ሰማዕትነቱን ፈጽሟል፡፡ አንገቱም ሲቆረጥ
ውሃ፣ ደምና ወተት ወጥቷል፡፡ ከሥጋውም እጅግ ብዙ አስገራሚ
ተአምራት ተፈጽመው ታይተዋል፡፡ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣
በጸሎቱ ይማረን፡፡
(ምንጭ፡- ሐይቅ ቅዱስ እስጢፋኖስ ያሳተመው ገድለ ቅዱስ
ፊቅጦር፣ ገድለ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ስንክሳር ዘወርሃ የካቲት፣
ሚያዝያ)