ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

Saturday, May 21, 2016

=>+*"+<+>#መልዐኩ_ቅዱስ_ሩፋኤል<+>+"*+

#መልዐኩ_ቅዱስ_ሩፋኤል
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
“እንግዶችን መቀበል አትርሱ፤ በዚህ አንዳንዶች ሳያውቁ
መላእክትን እንግድነት ተቀብለዋልና።” ዕብ.፲፫፡፩
ሩፋኤል ማለት ፈታሄ መሕፀን ማለት ነው። ሣልሳይ ሊቀ
መላእክት ነው። ለሄኖክ ወልደ ያሬድ 6 ዓመት በእግረ ገነት
ወድቆ ሳለ ህበዓቱን ክሡታቱን አሳይቶታል። መ/ሄኖክ 8፡5
ቅዱስ ሩፋኤል የጦቢትን ዓይን ያበራና ወለተ ራጉኤልን
ተቆራኝቷት ከነበረው ጋኔን ያላቀቃት መሆኑ በመጽሐፈ ጦቢት
በስፋት ተገልጿል፡፡ ቤቱንም በበረከት ሞልቶታል።
ጦቢት በፋርስ ንጉሥ በስልምናሶር ዘመን የተማረከ ከነገደ
ንፍታሌም የተወለደ ጽኑዕ እሥራኤላዊ ነው፡፡ እግዚአብሔር
በስልምናሶር ፊት የመወደድን ግርማና ባለሟልነትን ስለ
ሰጠው አለቃ አድርጎ ሾሞት ነበር፡፡ ለወገኖቹ ምጽዋት
በመስጠት ሕገ ርትዕን በመሥራት የተጋ ሰው ነበር፡፡ ሐና
የምትባል ሚስት አግብቶ አንድ ልጅ ወልዷል፡፡ ስልምናሶር
ሞቶ ሰናክሬም በነገሠ ጊዜ ከሹመቱ ስለሻረው ደግሞ ወደ
ምድያም መሔድ አልቻለም፡፡
ሣራ ወለተ ራጉኤል ከፍተኛ ችግር ደርሶባት ነበር፡፡ ችግሯም
ሕፃናት ወልጄ ቤት ንብረት ይዤ እኖራለሁ በማለት ባል
አገባች። ነገር ግን በዚች ሴት አስማንድዮስ የሚባል ጋኔን
አድሮ ያገባችውን ሰው ገደለባት ሌላም ባል ብታገባ ሞተባት
እንደዚህ እየሆነ በጠቅላላ ሰባት ድረስ ያሉትን ባሎችን
ገደለባት፡፡
የራጉኤል ልጅ ሣራ በዚህ ሁኔታ በኀዘን ተውጣ ስትኖር
በነበረበት ጊዜ ጦቢት ሸምግሎ ስለ ነበር ልጁ ጦብያን ጠርቶ
በዚህ ዓለም እስካለ ድረስ ሊሠራው የሚገባውን መንፈሳዊ
ሥራ እንዲሠራ በጥብቅ ከመከረው በኋላ በመጨረሻ ልጄ እኔ
ሳልሞት የኑሮ ጓደኛህን ፈልግ፣ ስትፈልግም ዕወቅበት፣ እኛ
የአብርሃም የይስሐቅና የያዕቆብ ዘሮች ነን ስለዚህ ከእነርሱ
ወገን የሆነችውን እንድታገባ ከዚህም ሌላ ከገባኤል ዘንድ
በአደራ ያስቀመጥኩት ገንዘብ አለና እኔ በሕይወት እያለሁ
ብታመጣው የተሻለ ነው አለው፡፡
ጦብያም ያባቱን ምክር ሁሉ በጽሞና ካዳመጠ በኋላ ‹አባባ
የነገርከኝን ነገር ሁሉ በተቻለኝ መጠን እፈጽማለሁ ግን
ከገባኤል ጋር ስላለው ገንዘብ እንዴት ለማምጣት እችላለሁ?
ሀገሩን አላውቀውም› አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ነገሩ አሳሳቢ ሆኖ
ስላገኘው ጦቢት ልጁ ጦብያን ‹አብሮህ የሚሄድ ሰው እስቲ
ፈልግ ምናልባት አብሮ የሚሄድ ጓደኛ ታገኝ ይሆናል
ደመወዝም ሰጥተን ቢሆን ካንተ ጋር የሚሄድ አንድ ሰው ግድ
ያስፈልግሃልና ሂድ ሰው ፈልግ› አለው፡፡
አብሮት የሚሄደው ሰው ለመፈለግም ቢሄድ አንድ መልካም
ጐበዝ አገኘ ይኸውም መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ጦብያ ግን
መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል መሆኑን ፈጽሞ አላወቀም ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ጦብያ መልአኩን ሰው መስሎ እንዳገኘው
‹የሜዶን ክፍል ወደ ምትሆነውና ራጌስ ወደ ምትባለው ሀገር
ከእኔ ጋር ለመሄድ ትችላለህን የድካምህን ዋጋ የጠየቅኸውን
ያህል እሰጥሃለሁ› ሲል ጠየቀው ቅዱስ ሩፋኤልም ‹እሺ ካንተ
ጋር ለመሄድ ፈቃኛ ነኝ መንገዱንም ሆነ ሀገሩን በሚገባ
አውቀዋለሁ ከገባኤል ቤት ብዙ ጊዜ ኑሬአለሁና› አለው፡፡
ከዚህ በኋላ ጦብያ በል ከአባቴ ጋር ላስተዋውቅህ ብሎ ወደ
አባቱ ወስዶ አስተዋወቀው ከእኔ ጋር የሚሄደው ሰው ይህ ነው
በማለት ካስተዋወቀው በኋላ ጦቢትም ከወዴት እንደ መጣ
ማን ተብሎ እንደሚጠራ ጠየቀው፡፡ መልአኩ ቅዱስ
ሩፋኤልም የታላቅ ወንድምህ ወገን ከመሆንም ሌላ ስሜም
አዛርያስ ይባላል አለው፡፡ ጦቢ. 5.12 ፡፡ ጦቢትም የወንድሙ
ዘመድ መሆኑን ከሰማ በኋላ ‹አንተስ ወንድሜ ነህ በል የልጄ
የጦብያን ነገር አደራ ከሀገር ወጥቶ አያውቅምና እንዳይደነግጥ
ደኅና አድርገህ እንድትይዝልኝ› ብሎ ስንቃቸውን አስይዞ
ሸኛቸው፡፡
አዛርያስ /ቅዱስ ሩፋኤል/ በመንገድ ይመራው ነበር፡፡ በዚህም
ቅዱስ ሩፋኤል ‹መራኄ ፍኖት› /መንገድ መሪ/ ይባላል፡፡
እነርሱ ሲሄዱ ውለው ማታ ጤግሮስ ከተባለው ታላቅ ወንዝ
ደረሱና ከዚያም ለማደር ወሰኑ፡፡ በዚህ ጊዜ ከድካሙ ጽናት
የተነሣ ጦብያ ሊታጠብ ወደ ወንዙ ወረደና ልብሱን አውልቆ
መታጠብ ሲጀምር አንድ ዓሣ ሊውጠው ከባሕር ወጣ፡፡
ወዲያውም መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ጦብያን ያዘው ፤ ዓሣውን
እንዳትለቀው አለው ፤ ጦቢያም ከዓሳው ጋር ግብ ግብ ገጥሞ
እየጐተተ ወደ የብስ አወጣው ፡፡ከዚህ በኋላ ቅዱስ ሩፋኤል
ጦብያን እንዲህ ሲል አዘዘው፡፡ ዓሣውን እረደው ጉበቱንና
ሐሞቱን ተጠንቅቀህ ያዘው ሌላውን ግን ጠብሰን እንበላዋለን
አለው፡፡
ጦብያም መልአኩ እንዳዘዘው ዓሣውን አርዶ ሐሞቱንና ጉበቱን
ያዘ፣ ሌላውን ሥጋውን ግን ጠብሰው ራታቸው አደረጉት፡፡
ጦብያም ያንን የዓሣውን ጉበትና ሐሞት ለምን
እንደሚያገለግል ለመረዳት ‹ይህን ያዘው ያልከኝ ለምንድን
ነው?› ሲል ጠየቀው ቅዱስ ሩፋኤልም ጋኔን ያደረበት ሰው
ሲገኝ ይህንን ከዕጣን ጋር ቢያጤሱበት ጋኔኑ ይለቃል ሲል
መለሰለት፣፡
በዚህ ሁኔታ አንድ ባንድ ሲነጋገሩ ከቆዩ በኋላ መልአኩ ቅዱስ
ሩፋኤል ጦብያን ‹ዛሬ ከራጉኤል ቤት እናድራለን፡፡ እርሱ
ዘመድህ ነው፡፡ የእርሱም ልጅ ሣራ የምትባል ቆንጆ ልጅ
አለችው፡፡ እሷን ለሚስትነት ይሰጥህ ዘንድ ለራጉኤል
እነግርልሃለሁ› አለው፡፡
ጦብያም ‹ያች ልጅ ከዚህ በፊት ሰባት ሰዎች እንዳገቧትና
ሰባቱም ባገቧት ሌሊት ደርቀው /ሞተው/ እንደሚያድሩ
ሰምቻለሁ፡፡ ስለዚህ እኔ ላባቴና ለእናቴ አንድ ልጅ ነኝ እርስዋን
አግብቼ ከዚህ በፊት እንዳገቧት ሰዎች እኔም የሞትኩ እንደሆነ
አባቴንና እናቴን የሚረዳቸው የለም ቢሞቱም የሚቀብራቸው
አያገኙምና እፈራለሁ› አለው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ግን
‹አባትህ ከዘመዶችህ ወገን ካልሆኑ በስተቀር ሌላ ሴት
እንዳታገባ ሲል የነገረህን ረሳኸውን? በል ሰባት ባሎቿ
ሙተውባታል ስለምትለው እኔ መድኃኒቱን አሳይሃለሁ ፤ አይዞህ
አትፍራ አትሞትም የዓሣውን ሐሞትና ጉበቱን ለምን መሰለህ
ያዘው ያልኩህ ? እንግዲህ ሐሞቱንና ጉበቱን ከዕጣን ጋር
ጨምረህ ስታጤስበት በሣራ አድሮ የነበረው አስማንድዮስ
የተባለው ጋኔን ወጥቶ ይሄዳል ፈጽሞም ወደ እርሷ በገባህም
ጊዜ ሁለታችሁ ይቅር ባይ ወደ ሆነው እግዚአብሔር ጸልዩ
እርሷም የተዘጋጀች ናት፡፡ ከእኛ ጋርም ወደ ሀገርህ ይዘናት
እንሄዳለን› አለው፡፡ ጦብያም ይህንን ቃል በሰማ ጊዜ ደስ
አለውና ከእርሷ በስተቀር ሌላ እንዳያገባ በሙሉ አሳቡ ወሰነ፡፡
ከዚህ በኋላ ወደ ራጉኤል ቤት እንደ ደረሱ ሣራ በደስታ
ተቀበለቻቸው የሣራ አባትም ጦብያን ገና እንዳለው ሚስቱ
አድናን ‹ይህ ልጅ የእኔ ዘመድ ጦቢትን ይመስላል› አላት
ከዚያም ጋር አያይዞ ‹ልጆች ከየት ሀገር መጣችሁ?› አላቸው፡፡
እነሱም ‹ከነነዌ ሀገር ነው የመጣን› አሉት፡፡ ‹ከዚያም ሀገር
ጦቢት የሚባል ወንድም ነበረኝ ታውቁት ይሆን?› ሲል
ጠየቃቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ጦቢያ አባቱን ሲጠራለት
‹እናውቀዋለን፡፡ እኔም ራሴ የጦቢት ልጅ ነኝ› አለው፡፡ ከዚያ
በኋላ ራጉኤል ‹የወንድሜ ልጅ ነህን?› ብለ እቅፍ አድርጐ
ሳመው፡፡ አድናም ሳመችውና ሁሉም ተያይዘው የናፍቆት ልቅሶ
ተላቀሱ፡፡ ከወንድሙ እንደ መጡም ሲገነዘብ በግ አርዶ በጥሩ
ሁኔታ ጋበዛቸው፡፡
ትም ከበሉ በኋላ ጦብያ ቅዱስ ሩፋኤል በመንገድ የነገረውን
በልቡ ሲያወጣ ሲያወርድ ስለ ዋለ ቅዱስ ሩፋኤልን ያንን
በመንገድ የነገርከኝን አሁን ፈጽምልኝ ሲለው ሰምቶ ስለ ልጅቷ
መሆኑን ስለ ገባው ራጉኤል ጦብያን ‹ልጄ ይህች ልጅ ላንተ
የምትገባ ናት ሰጥቸሃለሁ አይዞህ አትጠራጠር አሁንም ብላ
ጠጣ ለዛሬም ደስ ይበልህ አለውና ሣራ ካለችበት የጫጉላ ቤት
አግብተው ዘጉት፡፡ ጦብያም ሣራን በይ እኅቴ ኑሮዋችን
እንዲቃናልንና ጋብቻችን እንዲባረክልን አስቀድመን ወደ
ፈጣሪያችን ጸሎት እናድርግ› አላትና አብረው ጸሎት ካደረጉ
በኋላ ያንን የያዘውንና የዓሣ ጉበትና ሐሞት ከዕጣን ጋር
ጨምሮ ቢያጤስበት በሣራ አድሮ ባሎችዋን ይገድልባት
የነበረው አስማንድዮስ የተባለው ጋኔን ከሣራ ለቆ ወጥቶ ሄደ
ሁለተኛም ሊመለስ አልቻለም፡፡ እነርሱም በሰላምና በጤና
አደሩ፡፡ የጦብያንና የሣራን ጋብቻ የባረከ ቅዱስ ሩፋኤል ስለሆነ
‹መልአከ ከብካብ› ይባላል፡፡
ከዚያ በኋላ የጤንነታቸውን ነገር ሲረዱ የሰርጉ ቀን የሚሆን
የ14 ቀን በዓል እስኪፈጸም ድረስ ጦብያ ወደ ሀገሬ እሄዳለሁ
ብሎ እንዳያውከው በማለት አማለው፡፡
የ14 ቀን በዓለ መርዓ ከተፈጸመ በኋላ ግን ጥሬ ገንዘብና
የከብት ስጦታ አድርጐ መርቆ ወደ ሀገሩ ሰደደው፡፡ ወላጆቹ
ጦቢትና አድና ግን በመዘግየቱ ልጃችን ምን አግኝቶት ይሆን?
እያሉ ለጊዜው ሳያዝኑ አልቀሩም፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ
ሚስቱንና ግመሎቹን ይዞ ሲመጣ በክብርና በደስታ ተቀበሉት፡፡
የጦብያ አባት ጦቢትም ልጅህ መጣ ሲሉት ዓይነ ሥውር ስለ
ነበር እርሱን እቀበላለሁ ሲል ስለ ወደቀ ወዲያው ጦብያ
የዓሣውን ሐሞትና ጉበቱን ይዞ ስለ ነበር የአባቱን ዓይን ቀባው
ወዲያውም ዓይኖቹ ተከፈቱ፡፡
በመጨረሻም ከጦብያ ጋር ሄዶ የነበረው መልአኩ ቅዱስ
ሩፋኤልን የድካሙን ዋጋ ገንዘብ ለመስጠት ጠሩት እርሱ ግን
ጦቢትንና ጦብያን ‹ፈጣሪያችሁን አመስግኑ እናንተ እስከ ዛሬ
ድረስ ከየት እንደመጣሁ ማን እንደ ሆንኩ አላወቃችሁኝም፡፡
የእግዚአብሔር ምሥጢር ግን በክብር ሊገለጥ ይገባል እንጂ
ሊሰውሩት ስለማይገባ የእኔን ተፈጥሮና ስም ልነግራችሁ
እፈልጋለሁ ተፈጥሮዬ መልአክ ነኝ፣ ሥራዬም የቅዱሳንን ጸሎት
ከሚያሳርጉ ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ እኔ ሩፋኤል ነኝ›
ሲል ገለጠላቸው፡፡ እነርሱም ወድቀው የአክብሮት ስግደት
ሰገዱለት፡፡ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርንም
አመሰገኑት፡፡ /መጽ. ጦቢት/፡፡
ስለዚህ እንግዶችን መቀበል አንርሳ፡፡ በዚህም ምክንያት
አንዳንዶች ሳያውቁ የመላእክትን እንግድነት ተቀብለዋልና፡፡
ዕብ. 13.1-2 ፡፡
ጦቢት ከእህሉ ከፍሎ ለተራበ የሚያበላ ከልብሱ ለተራቆተ ሰው
የሚያለብስ እግዚአብሔርን ዘወትር የሚያመሰግን ለወገኖቹ
የሚራራ አሥራት በኩራት የሚያወጣ ሰው ነበር፡፡ በመሆኑም
በሥራው ሁሉ እንዲረዳው በችግሩ ጊዜ እንዲያጸናው ቅዱስ
ሩፋኤል ተልኮለታል፡፡ እኛም በሕይወታችን የጐደለብንን ነገር
እንዲሞላልን ጐዳናችንን እንዲያስተካክልልን ከክፉ ጋኔን
እንዲጠብቀን አምላክ ቅዱስ ሩፋኤል ተለመነን ቅዱስ
ሩፋኤልንም አማልደን ማለትን ገንዘብ እናድርግ፡፡
ጳጉሜ የዘመን መሸጋገሪያ እንደ ሆነች ዕለተ ምጽአትም ወደ
እግዚአብሔር መንግሥት የምንሸጋገርባት ስለሆነች ከወዲሁ
የቅዱስ ሩፋኤልን የመታሰቢያ በዓሉን ስናከብር በአማላጅነቱ
ከቅዱሳን ኅብረት እንዲደምረን በንስሐ ታጥበን ደጅ ልንጠና
ይገባል፡፡
የሊቀ መልአኩ የቅዱስ ሩፋኤል ምልጃው፣ ጥበቃውና
ቃልኪዳኑ ይደረግልን በረከቱ ይደርብን፡፡ አሜን፡፡
ልመናው ከእኛ ከሀገራችንም ከኢትዮጵያ ጋር ለዘላለሙ ጸንቶ
ይኑር።
“ስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘአብጽሐና እስከ ዛቲ ሰዓት”
ወስብሔት ለእግዚአብሔር ወለ ወላዲቱ ድንግል ወለ መስቀሉ
ክቡር አሜን ይቆየን።

=>+*"+<+>ቅዱስ ሩፋኤል<+>+"*+

#ቅዱስ_ሩፋኤል
#ከከበሩት_ከ_ሰባቱ_ሊቃነ _መላእክት_አንዱ
#እኔ_ሩፋኤል_ነኝ ::
ጦቢት 12 : 13
እንግዲህ ከባህሪው ቅድስና ፍጥረቱን በጸጋ ቅድስና መርጦ
የሚለይ እግዚአብሔር አክብሮ እንዲህ ያለ ሰማያዊ ፀጋ
ከሰጣቸው ቅዱሳን መላእክት መካከል በስልጣኑ ሊቀመናብርት
(የመናብርት አለቃ) የሆነ በሹመት ፈታሔ ማኅጸን (ማሕጸን
የሚፈታ) ከሳቴ እውራን (የእውራንን ዓይን የሚያበራ) ሰዳዴ
አጋንንት (አጋንንትን የሚያባርር) ፈዋሴ ዱያን (ድውያንን
የሚፈውስ)፣ አቃቤ ኆኅት (የምህረትን ደጁ የሚጠብቅ) ተብሎ
የተገለጠ ከሊቃነ መላእክቱ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል
ተከትሎ የሚነሳ መልአክ ራሱን እንዲህ በማለት ገለጠ «
የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ ወደ ከበረ ወደ ገነነ ወደ
እግዚአብሔር ጌትነት ከሚያገቡ ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ
አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ» (ጦቢ.12÷15)
ይህ የከበረ ታላቅ መልአክ ሰሙ የእብራይስጥ ሁለት ቃላት
ጥምረት ውጤት ነው፡፡ ሩፋ ማለት ጤና፣ ፈውስ፣ መድኃኒት
ማለት ሲሆን ኤል ሚለው በሌሎቹም መላእክት ስም ላይ
የሚቀጠል ስመ አምላክ ነው ይህም « መልአኬን በፊትህ
እሰዳለሁ….. ስሜ በእርሱ ስለሆነ .
አታስመርሩት» (ዘጸ.23÷20-22) እዳለው ነው፡፡
ታዲያ ሩፋኤል የሚለው በጥምረት ከአምላክ ለሰዎች የተሰጠ
ፈውስ የሚለውን ይተካል «በሰው ቁስል የተሾመ ከከበሩ
ከመላእክት አንዱ ሩፋኤል ነው፡» (ሄኖ.6÷3)
ይህ መልአክ እንደሌሎቹ ሊቃነ መላእክት ሁሉ የሰው ልጆችን
ይጠብቃቸዋል(ዳን.4÷13 ዘጸ. 23÷20 መዝ.
90÷11-13 )
ያማልዳል፣ ከፈጣሪ ያስታርቃቸዋል፡፡(ዘካ.1 ÷12)
በፈሪሀ እግዚአቤሔር እና በአክብሮተ መላእክት ያሉትን
ድናቸዋል (ዘፍ.49÷15 መዝ.3÷37)
« እግዚአብሔር ሃይሉን የሚገልጥበትን ቅጣቱን ሊያሳይ ቢወድ
አስቀድሞ መርጦ በወደዳቸው ለይቅርታ የተዘጋጁ የይቅርታ
መላእክትን ያመጣል» (ሮሜ.9÷22)
ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀመናብርትን ድንቅ ገቢር ተአምራቱን ያዩ
ምዕመናን
……የወላድ ማኅፀን እንዲፈታ
ስለተሸመ ከጌታ
አዋላጅ ብትኖር ባትኖርም
ሐኪም ሩፋኤል አይታጣም
በምጥ ጊዜ ሲጨነቁ የባላገር ሴቶች ሁሉ
የመልአኩን መልክ አንግተው ማርያም ማርያም ይላሉ
ማየጸሎቱን ጠጥተው ቶሎ ፈጥነው ይወልዳሉ ……
እያሉ ደጅ ጠንተው ይማጸኑታል፡፡
ዜና ግብሩን ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ ከተናገረለት በመነሳት
በቅዱሳን ላይ ድንቅ የሆነ እግዚአብሔር በመልአኩ አድሮ
ያደረጋቸውን ተግባራት አበው የበረከት ምንጭ በሆነ ድርሳኑ
ላይ አኑረው የበረከቱ ተካፋይ እንድንሆን ሰጥተውናል፡፡ በጉልህ
ሠፍረው ከምናገኛቸው ብዙ ድንቅ ሥራዎች መሀል ጥቂቶቹን
እነሆ
~~~> በሥነ-ስዕሉ የተማጸኑ፣ በምልጃው ታምነው የጸኑ
ቴዎዶስዮስንና ዲዮናስዮስን በገሃድ ተገልጾ ለንግስናና ለጵጵስና
ክብር አብቅቷቸዋል፡፡
~~~> የንጉስ ቴዎዶስዮስ ልጅም ጻድቁ አኖሬዋስም
በፈጣሪው ህግ እየተመራ የሊቀ መናብርቱን መታሰቢያ ቤተ
መቅደስ አሳንጾ ሲያስመርቅ ለበለጠ ክብር ልቡን አነቃቅቶ
ለታናሽ ወንድሙ ለአርቃዴዋስ የነጋሢነት ስልጣኑን ትቶ መንኖ
በስውርና በጽሙና እዲኖር ረድቶታል፡፡
~~~> በሊቀጳጳሳት ቴዎፍሎስ ዘመን አባቶች ለሊቀመናብርቱ
ክብር በአሣ አንበሪ ጀርባ ላይ ያሳነጹትን መታሰቢያ ቤተ
መቅደስ በወደቡ አጠገብ በእስክንድሪያ ሳለች ጠላት ዲያቢሎስ
አነዋውጾ ለምስጋና የታደሙትን ምዕመናን ሊያጠፉ አሣ
አንበሪውን ቢያውከው ወደ ሊቀመናብርቱ ተማጽነው እርዳን
ቢሉ ፈጥኖ ደርሶ በበትረ መስቀሉ (ዘንጉ) ገሥጾ ከጥፋት
ታድጓቸዋል፡፡
በቅዱስ መጽሐፍም እንደተገለጠው
~~~> ሣራ ወለተ ራጉኤልን አስማንድዮስ ከተባለው የጭን
ጋንኤን ሲታደጋት የጦቢያን አባት የጦቢትን ዓይን አበራለት
(መጽሐፍ ጦቢት)
ከዚህም አልፎ የይስሐቅን እናት ሣራን፣ የሶምሶንን እናት
(እንትኩይን) ምክነታቸውን የቆረጠ ወልዶ ለመሳም ያበቃቸው
ይኸው ፈታሔማኅጸን የልዑል እግዚአብሔር መልአክተኛ ቅዱስ
ሩፋኤል ነው፡፡ከመልአኩ ከቅዱስ ሩፋኤል ረድኤት ያሳድርብን
አሜን !!!

=>+*"+<+>◆ ቅዱስ ሩፋኤል + አቡነ ዘርዓ ብሩክ ◆<+>+"*+

◆ ቅዱስ ሩፋኤል + አቡነ ዘርዓ ብሩክ ◆
ፈታሄ ማህጸን ቅዱስ ሩፋኤል
ለዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት ሰባት አለቆች አሏቸዉ፡፡እነዚህ
የተመረጡ ሊቃነ መላእክት ለተልእኮ ፤ለምስጋና ፤ለማማለድ
በቧለማልነት ዘወትር በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙ
ናቸዉ፡፡‹‹‹ርኢኩ ሰብዐተ መላእክትተ እለ ይቀዉሙ ቅድመ
እግዚአብሐየር ሰባት ሊቃነ መላኢክት በእግዚአብሐየር ፊት
ቆመሁ አየሁ ››››እንዲል ራእ 8፡2፡፡ከእነዚህ ሊቃነ መላኢክት
አንዱ ቅዱስ ሩፋኤል ሲሆን በማእረግ ሦስተኛ ነዉ፡፡በሰዉ
ቁስል የተሸመ ፤በፈዉስ ላይ የተሸመ፤ ከከበሩ መላእክት አንዱ
ቅዱስ ሩፋኤል ነዉ፡፡ሄኖክ 6፡3 ፡፡ቅዱስ ሩፋኤል ራሱም
‹‹‹የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ ወደ ከበረ ወደ ገነት ወደ
እግዚአብሐሔር ጌትነት ከሚያ...ስገቡ ሰባት አለቆች አንዱ
ቅዱስ ሩፋኤል ነኝ ብሎል፡፡ጦቢት 12፡15 እግዚአብሔርም
በሃያ ሦስቱ ነገደ መላእክትም ላይ ሾሞታል፡፡
ቅዱስ ሩፋኤል ሰማያዉያን መዛግብት በእጁ የሚጠበቁ
በመሆናቸዉ‹‹ዐቃቤ ኖኀቱ ለአምላክ ›››ይባላል፡፡እግዚአብሔ
ር እንዳዘዘዉ የሚከፍታቸዉ የሚዘጋጋቸዉ እርሱ ቅዱስ
ሩፋኤል ነዉ፡፡በዚያች በድህነትና በደስታ ቀን ለሕዝበ ክርስቲያን
ከዕፀ ህይወት ይሰጣቸዉ ዘንድ እግዚአብሔር ያዘዘዉ ቅዱስ
ሩፋኤልን ነዉ፡፡ይህ የከበረ መላእክት ‹‹‹ፈታሄ ማህጸን››››
ይባላል፡፡እናቶች ሲወልዱ ምጥ እንዳይበዛባቸዉ የሚራዳ
መልአክ ነዉ፡፡በመሆኑም አያሌ ክርስቲያኖች ማርገዛቸዉን
ካወቁ ጀምሮ ድርሳኑን በማንበብ መልኩን በመድገም ጠበሉን
በመጠጣት ሰዉነታቸዉን በመቀባት ይለምኑታል፡፡እንደ
እምነታቸዉ ጽናት ይደረገላቸዋል፡፡
◆◆◆+++ አቡነ ዘርዓ ብሩክ +++
የጻድቁ አባታችን የዘርዓ ብሩክ አባት እና እናት የተባረኩ
ከቅዱሳን ወገን የሚሆኑ ነበሩ የአባታቸው ስምም ቅዱስ ደመ
ክርስቶስ ሲባል እናታቸው ደግሞ ቅድስት ማርያም ሞገሳ
ትባላለች ጻድቁ አባታችን ገና በናታቸው ማህጸን እያሉ ነበር
ብዙ ተአምራት የሚያደርጉት እግዚአብሄር መርጡአቸዋልና
በሁአላም ከክርስቶስ ልደት በሁአላ በስምንተኛው መቶ ክ/
ዘመን መጨረሻ ላይ በነሃሴ 27 ጻድቁ አባታችን ተወለዱ
በ40ኛ ቀናቸውም ተጠምቀው በካህናት አፍ "ጸጋ ክርስቶስ"
ተባሉ ከዛም ቤተሰቦቻቸው በጥሩ እድገት አሳደጉአቸው 7
አመትም በሞላቸው ግዜ በልጅነቴ የዚን አለም ክፋቱን
እንዳላይ ብለው ቢጸልዩ አይናቸው ታውሩአል:ቤተሰቦቻቸውም
የዚን አለም ትምህርት ሊያስተምሩአቸው አስተማሪ ጋር
ቢወስዱአቸው ታመው ተመልሰዋል:የእግዚአብሄር ፈቃድ
አይደለምና ነገር ግን የሚያስፈልጋቸውን እውቀት ፈጣሪ
አምላክ ራሱ ገልጾላቸዋል:: ክህነትን እስከ ጵጵስና እራሱ
መድሃኒአለም ክርስቶስ ሰቶአቸዋል:12 አመትም በሞላቸው
ግዜ አይናቸው በርቶላቸው ታላላቅ ተጋድሎን ማድረግ ጀመሩ :
የሃጥያት ማሰርያን ያስሩና ይፈቱ ዘንድ ጵጵስናን በሾማቸው ግዜ
እግዚአብሄር ያወጣላቸው ሁለተኛ ስም "ዘርዓ ብሩክ" ይባል
ነበር 3ኛውም ስማቸው ደግሞ "ጸጋ እየሱስ"ይባላል:: ጻድቁ
አባታችን በዚ አለም በህይወተ ስጋ ሳሉ አቡቀለምሲስ
እንደሚባል እንደ ዮሃንስ ወልደነጎድጉአድ እግዚአብሄር እሱ
ወዳ...ለበት ወደ ሰማይ አውጥቶ በገነት መካከል ያኖራቸው
ነበር:: እግዚአብሄር አምላክ ለወዳጁ ለብጹዕ አባታችን ዘርዓ
ብሩክ በጎ ነገር እንዳደረገለትና ያለ ድምጽ የሰማይ ደጆችን
አልፎ የእሳት ባህርን ተሻግሮ ፈራሽ በስባሽ ሲሆን እንደ ህያዋን
መላእክት በፍጥነት ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ከአድማስ እስከ አድማስ
ይደርስ ዘንድ 12 ክንፍን ሰጣቸው:መላእክትም ለሌሎች
ቅዱሳን ያልተሰጠ ይህንን ስልጣን አይተው ለምድራዊ ሰው ይህ
ነገር እንዴት ይቻላል እያሉ አደነቁ: ከዛም በሁአላ ጻድቁ
አባታችን ከፈጣሪ ዘንድ የመላእክትን አስኬማ,የሾህ አክሊል
አምሳያ የሆነውን መንፈሳዊ ቆብን,ሰማያዊ ቅናትን እና የደረት
ልብስን(ስጋ ማርያም) ተቀብሎ በጾም እና በጸሎት በልመና
እና በስግደት እግዚአብሄርን ሲያገለግል ኖረ ከዛም በላይ
ወንጌልን እጅግ ብዙ በማስተማር ደከመ ከኢትዮጵያም አልፎ
ግብጽ ድረስ ገባ የእስክንድርያውን ሊቀ ፓፓስ አባ ዮሃነስን
አገኘውና እርስ በርስ ሰላምታን ተለዋውጠው እጅ ተነሳሱ
ከዛም ተመልሶ ወደ ሃገሩ መጣ ከዛም ኢትዮጵያ ውስጥ
እየተመላለሰ ወንጌልን አስተማረ እጅግ ስጋን በሚያስጨንቅ
ትጋትም የኢትዮጵያን ህዝብ ማርልኝ እያለ እያለቀሰ ይጸልይ
ነበር: አንድ ቀን አባታችን በንጉስ ጭፍሮች ተይዘው ሲሄዱ
ዳዊታቸውን ለግዮን ወንዝ አደራ ሰተዋት ከ5 አመት በሁአላ
ሲመለሱ ግዮን ሆይ ዳዊቴን ግሺ መልሺሊን ቢሉአት አንድም
የውሃ ጠብታ ሳይኖርባት ዳዊታቸውን ብትመልስላቸው ለደቀ
መዝሙራቸው ዘሩፋኤል አሳዩትና ግዮንንም "ግሽ አባይ"
ብለውታል እስካሁንም በዚሁ ስም የሚጠራው ከዚ በመነሳት
ነው:: ከዚህም ሌላ ጻድቁ አባታችን በዚሁ ወንዝ አካባቢ ለ 30
አመት ሲጸልዩ ፈጣሪ አምላክ ጸሎታቸውን ሰምቶ እጅግ ልዩ
የሆነ ቃል ኪዳን ሰቶአቸዋል:በስተመጨረሻም የሚያርፉበት
እለት በደረሰ ሰአት መልአከ ሞት መቶ እስኪደነግጥ እና ወደ
ሁአላው እስኪያፈገፍግ ድረስ ነው ነው እግዚአብሄር ጸጋውንና
ክብሩን ያበዛላቸው: በስተመጨረሻም ጥር በገባ በ13 ቀን
በ482 አመታቸው ስጋቸው ከነፍሳቸው ተለይታ ገነትን
ወርሰዋል::ምንጭ ገድለ አቡነ ዘርዓ ብሩክ የጻድቁ አባታችን
ገድለ ዜና እንኩአን በዚች በምታህል ጽሁፍ አይደለም
የገድላቸውም መጽሃፍም አልበቃውም እንደው እግዚአብሄር
አምላክ ከበረከታቸው እንዲያሳትፈን አስቤ ይችን ጥቂት
የገድላቸውን ዜና ከገድላቸው መጽሃፍ ላይ
አስቀመጥኩ:ለእግዚአብሄር ምስጋና ይሁን እኛንም በኚህ
ጻድቅ ጸሎት ይማረን በረከታቸውንም ያድለን አሜን
የቅዱስ ሩፋኤል ልመናዉ በረከቱ ይደርብን ፡፡አሜን ፡