ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

Wednesday, May 4, 2016

+*"#ምጽዋት "*+

#ምጽዋት
• ስለ ምጽዋት ምንነት
ምጽዋት የሚለው ሥርወ ቃል የግእዝ ቋንቋ ሲሆን
ትርጉሙም ስጦታ፣ችሮታ፣ልግስና ማለት ነው፡፡
ምጽዋት፡-
• ምሕረት ነው ( ፍት ነገ አንቀጽ 16 ቁ 125 )
• ለአምላክ የሚሰጥ ብድር ነው ( ለድሀ ቸርነትን የሚያደርግ
ለእግዚአብሔር ያበድራል፤ በጎነቱንም መልሶ ይከፍለዋል፡፡
ምሳ 19፡17 )፣ ( ምጽዋትን የሚመጸውት ሰው
ለእግዚአብሔር በማበደሩ ነው በእጁም የሚበቃ ገንዘብ ያለው
ፈቃዱን ያደርጋል፡፡ ሲራ 29፡1 )
• ብልሆች ሰዎች ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስቀምጡት
አደራ ነው ( ሉቃ 12፡33 )፣ ( ማቴ 6፡19-21 )
• ሰው ለሰው ያለውን በጎ ፈቃድ የሚገልጥበት ክርስቲያናዊ
የሥነ ምግባር ዘርፍ ነው፡፡ ( 2ኛ ቆሮ 8፡2 )
• ጠላትህ ቢራብ እንጀራ አብላው፤ ቢጠማ ውሃ አጠጣው፤
መ.ምሳሌ 25፤21
o የምጽዋት ዓይነቶች
ምጽዋት የሚለው ሲነገር ለሕሊና የሚታይን የገንዘብ የምግብ
የቁሳቁስ ስጦታ ነው፤ ነገር ግን ምጽዋት በገንዘብና በዓይነት
ስጦታ ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡ ምጽዋት ካለው ነገር
የሌለውን ነገር መርዳት አስከሆነ ድረስ በሚቆጠርና በሚሰፈር
ብቻ አይወሰንም፡፡ ደካሞችን በጉልበት ያልተማሩትን
በዕውቀት የሙያ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን በሙያ መርዳት
ምጽዋት ነው፡፡ ( ሐዋ 3፡2-10 ፣ ( ማቴ 25፡14-30 )
• ምጽዋት በቅዱሳት መጻሕፍት
“ ለሰው የሚያዝኑና የሚራሩ ብጹዓን ናቸው ” የተባለው
አንቀጽ የሚያስተላልፈው ሰፊ ትምህርት አለ፡፡ ሊቃውንተ ቤተ
ክርስቲያን ምሕረት የሚለውን ቃል ምሕረት ሥጋዊ፣ ምሕረት
መንፈሳዊና ምሕረት ነፍሳዊ በማለት ተንትነው ለእያንዳንዱ
ቃል ተግባራዊ ትርጉም አስቀምጠውለታል፡፡
1. ምሕረት ሥጋዊ ፡- ለተራበ ቆርሶ ማጉረስ፣ ለታረዘ
ማልበስ፣ የባልንጀራን ችግር መካፈል፣ የተበደሉትን መተው
( ይቅር ማለት ) የበደሉትን ይቅርታ መጠየቅ ነው፡፡
2. ምሕረት መንፈሳዊ፡- የትምህርትና የምክር አገልግሎት
ነው፡፡ መንገዱ የጠፋቸውን ክፉውን እንደ መልካም ሥራ፣
የተሳሳተን እምነት እንደ ትክክለኛ እምነት አድርገው ወደ ጥፋት
መንገድ የሚሔዱትን መክሮ አስተምሮ መመለስ፣ ከክፋት ጎዳና
ማዳን ነው፡፡
3. ምሕረት ነፍሳዊ፡- ከእነዚህ ሁሉ ይጠብቃል፣ ይረቃል፡፡
ምሕረት ነፍሳዊ ራስን ለሌላው ሕይወት አሳልፎ መስጠት
ነው፡፡ እራሳቸውን ለሰው ፍቅር አሳልፈው የሚሰጡ ሰዎች
ክርስቶስን በግብር ይመስሉታል፡፡ ( ማቴ. 5፡7 )፣ ( ዮሐ. 3፡
6 )
ሀ. ምጽዋት በብሉይ ኪዳን
ምጽዋት መስጠት እግዚአብሔር ዘንድ አስፈላጊ እንደሆነ
ምጽዋት ሰጪዎችም በእግዚአብሔር ዘንድ የሚጠብቃቸው
ከፍተኛ ዋጋ እንዳላቸው በብሉይና በሐዲስ ኪዳን በሰፊው
ተገልጦ ይገኛል፡፡
• ‹‹ ድሆች በምድር ላይ አይታጡምና በአገርህ ውስጥ ስለድሃ
ለተቸገረውም ወንድምህ እጅህን ትከፍታለህ ብዬ አዝዤሃለሁ
›› (ዘዳ 15፡11)
• ‹‹ ወንድምህ ቢደኸይ እጁ ቢደክም አጽናው እንደ እንግዳ
እንደ መጻተኛ ከአንተ ጋር ይኑር ›› (ዘሌ 25፡35)
• ‹‹ እኔ የመረጥኩት ጾም… እንጀራህን ለተራበ ትቆርስ ዘንድ
ስደተኞች ድሆችን ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ የተራቆተውን ብታይ
ታለብሰው ዘንድ አይደለምን? ›› (ኢሳ 58፡7)
በብሉይ ኪዳን ስለምጽዋት ትምህርት በቃል ብቻ የተገለጠ
አይደለም በተግባርም ጭምር እንጂ
• ማንኛውም እስራኤላዊ ገበሬ የወይራውን፣ የወይኑን፣
የበለሱን የሌሎችንን ተህሎች ውጤት በሚሰበስብበት ጊዜ
ከማሳው ላይ አጣርቶ አይለቅምም፤ ከመሬት ላይ የወደቀውን
አይሰበስበውም ፡፡ የገብሱንና የስንዴውን የሌላውንም ምድር
ያበቀለችውን የሰብል አይነት ሁሉ አያጭድም ቅርምያውንም
ለድሆች ይተዋል፡፡ ይህም ከእግዚአብሔር የታዘዘ ግዴታ ነው፡፡
( ዘሌ 19፡9-10 )፣ ( ዘዳ 24፡19-21)
• ገበሬው በየሦስት ዓመት ከሚያገባው የምድር ፍሬ ሁሉ
አስራት በኩራቱን ለድሆች ይሰጣል፡፡ ( ዘዳ 14፡28 )
• ማንኛውም እስራኤላዊ ገበሬ ስድስት ዓመት ምድሩን እያረሰ
ይዘራል፡ ምርቱንና ፍሬውን ያገባል፡፡ በሰባተኛው ዓመት ግን
ምድር በጠቅላላው የምታበቅለው ሁሉ ለድሆች ይሆናል፡፡
( ዘዳ 23፡3 )
ለ. ምጽዋት በሐዲስ ኪዳን
ሰው ርኅራኄ እና የቸርነት ተግባር የሚማረው ከፈጣሪው ነው፡፡
ለሚሰጠው ስጦታ ምላሽ ሳይሻ ሳይለምኑት ለፍጥረት
የሚያስፈልገውን አውቆ የሚሰጥ ነው፡፡
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየስስ ክርስቶስ ለተራቡት፣ ለተጠሙትና
ለታረዙት ያዝንላቸውና ይራራላቸው ነበር፡፡ ትምህርቱን
ተአምራቱን ይሰበሰቡ የነበሩትን ሁሉ ‹‹ የሚበሉት ስለሌላቸው
አዘነላቸው፤ በመንገድ እንዳይዝሉ ጦማቸውን ሊሰዳቸው
አልወደደም ›› እያለ የተራቡትን ሁሉ ሕብስት አበርክቶ
ይመግባቸው በቸርነቱም ያጠግባቸው ነበር፡፡ ( ማቴ 15፡3 )
ድሆች በምድር ላይ እስካሉ ድረስ ምጽዋትም የማይቀር ግዴታ
መሆኑን ለማመልከት ‹‹ ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ናቸው ››
ሲል ተናግሮዋል፡፡ ( ማቴ 26፡11 )
አበው ሐዋርያትም ለድሆች ያዝኑ፣ ያስቡላቸውም
ይጠነቀቁላቸውም ነበር፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚገባውን
የምጽዋትና የአስራት ገንዘብ ከልዩ ልዩ አስተዋጽኦ ለነዳያን
መድበው ያካፍሏቸው ነበር፡፡ በየሳምንቱ የሚደረገው ተዝካረ
ሰንበት ከፍተኛው ድርሻ ለድሆች የሚሰጥ ነበር፡፡ ( 1ኛ ቆሮ
10፡17-22 )
• የምጽዋት አቀራረብ
ምጽዋት ብድሩ ከእግዚአብሔር ይገኛል በሚል እምነት
ለተቸገሩ ሰዎች የሚሰጥ ልግስና እንደመሆኑ አቀራረቡ
ከግብዝነትና ከውዳሴ ከንቱ የጠራ መሆን እንዳለበት ጌታችን
አስተምሮናል፡፡በግል የሚፈጸም ምጽዋት ፣ ጾምና ጸሎት
በስውር እንዲሆን አዝዞናል፤ ነገር ግን ለስሙ አብነት
( ትምህርት ምሳሌ ) ለመሆን በገሃድ (በግልጽ) ይፈጸማል፡፡
(ማቴ 5፡16)
• ስለ ተዝካርና ቁርባን
ተዝካር የሚለው ሥርወ ቃል ተዘከረ-አሰበ ከሚለው የግእዝ
ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም መታሰቢያ ማለት ነው፤
መታሰቢያውም የሚደረገው በሞት ለተለዩ ሰዎች በጸሎት፣
በመሥዋዕት፣ በመብራት፣ በማዕጠንትና በምጽዋት ነው፡፡
ለሞተው ሰው መታሰቢያ የሚደረግባቸው ጊዜያትም በዕለተ
ሞት ቀን፣ በሣልስት፣ በሰባት ፣በአስራ ሁለት፣ በሠላሳኛው ቀን፣
በአርባኛው ቀን፣ በሰማንያኛው ቀን፣ በመንፈቅ፣ በሙት ዓመት
ጊዜያት ናቸው፡፡
• የአስራት ክፍያ
የአስራት አስተዋጽዖ ትምህርትና ሥርዓት ከሰዎቸወ ፍላጎትና
ውሳኔ የመጣ አይደለም ከእግዚአብሔር የተሰጠ ትእዛዝ እንጂ፤
ገንዘቡም የሚታወቀው የእግዚአብሔር ገንዘብ በመባል ነው፡፡
(ዘሌ 27፡1)
የአስራት ክፍያ በሙሴ አማካኝነት ከተሰጠው የብሉይ ኪዳን
ሕግ አስቀድሞ የነበረና በሥራ ተጀምሮ የቆየ ነው፡፡ አብርሃም
ከገንዘቡ ሁሉ ለመልከ ጼዴቅ ከአስር አንድ አምጥቶለታል፤
መልከ ጼዴቅም ኅብስት አኮቴት ጽዋዐ በረከት አቅርቦለታል ፤
አብርሃምንም ባርኮታል፡፡ ( ዘፍ 14፡18-2) ፣ ( ዕብ 7፡2 )
አባታችን ያዕቆብም ከገንዘቡ ሁሉ ከአስር አንድ
ለእግዚአብሔር አንደሚሰጥ በራሱ ፍቃድ ብጽዓት አድርጎዋል፤
እግዚአብሔርም ብጽዓቱን ተቀብሎ ያዕቆብን በመንገዱ
ጠብቆታል፡፡ (ዘፍ 28፡22)
• የአስራት ክፍያ የታዘዘበት ምክንያት
1. ሀ. ለፍጥረቱ ሁሉ አስፈላጊ የሆነውን ምግብ ባለማቋረጥ
የሚሰጥ እግዚአብሔርን ለማክበር ( ምሳ 3፡9-10 )
ለ. ለመስጠትም ሆነ ለመንሳት፤ ለማብዛትም ሆነ ለማሳነስ
ሥልጣንና ጌትነት የባሕርዩ የሆነ አምላክ መፍራትን ማክበርን
እንማርበት ዘንድ ስንቀበልም መስጠትንም እናስብ ዘንድ
የተሰጠን ሀብት በጥቂቱ ከፍለን መስጠት ብዙ ትርፍና በረከት
እንድናገኝ ነው፡፡ ( ዘዳ 14፡22 )
2. ለሥርዓተ አምልኮ ማስፈጸሚያ
ለእግዚአብሔር ቤት አምልኮ ማስፈጸሚያ ልግስና አስፈላጊ
ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘይት ለመብራት ( ዘጸ 27፡20 )፣ ዕጣን
ለማዕጠንት ( ዘዳ 30፡36 ) እህል ለቁርባን ( ዘሌ 2፡1-3 )
እንስሳት ለመሥዋዕት አሥራት አስፈላጊ ነበር፡፡ በሐዲስ
ኪዳንም ለዕጣኑ፣ ለዘቢቡ፣ ለልብሰ ተክህኖ ወዘተ… አስራት
አስፈላጊ ነው፡፡
3. ካህናት አገልጋዮችን ለመርዳት ( ዘኁ 18፡21 ) ፣ ( ዘዳ
18፡1-5 ) ፣ ( ሚል 3፡7-9 ) ፣ ( ሚል 3፡10-12 )
4. ለነድያን ( ዘዳ 14፡28-29፣ 26፡12-18፣ 14፡27 )
• ስጦታ ስለሚቀርብበት ቦታ
አስራት በኩራትም ሆነ ሌላውም ለአምላካዊ አገልግሎት
የታዘዘው ስጦታ ሁሉ የሚቀርበው በቤተ እግዚአብሔር ነው፡፡
ነቢዩ ሕዝቅያስም ‹‹ ለእግዚአብሔር ቤት ጎተራ ያዘጋጁ ዘንድ
አዘዘ እናሱም አዘጋጁ ቁርባኑንና አስራቱን የተቀደሱትን ወደዚያ
አስገቡት ›› ( 2ኛ ዜና 31፡12 ) ፣ ( ነህ 13፡5
ለእግዚአብሔር ቤት የሚቀርበውን ማንኛውም ሀብትና
ንብረት ሁሉ እየጠበቁ በተገቢው አገልግሎት እንዲውሉ
የሚያደርጉ የተመረጡ አገልጋዮችና አስተናባሪዎች ነበሩ፡፡
( 2ኛዜና
31፡12 ፣13፡4 )
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

+*" #መንገደ_ሰማይ "*+

፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤
#መንገደ_ሰማይ ፡፡
፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤
21
#የመንገደ_ሰማይ_መቅድም፡፡
21
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ዱ አምላክ ፍኖታ ለነፍስ
ዘተኃውር ቦቱ ቅድመ እግዚአብሔር አሜን፡፡
፩. የመንገደ ሰማይ ነገር እንደምን ነው ቢሉ ሰው በናቱ ማኀፀን
ሲፈጠር ከእግዚአብሔር ዘንድ ሁለት መልአክ ዐቃቢ
ይታዘዝለታልና አንዱ በቀኝ ሌላው በግራ ሁነው በየዕለቱና
በየሰዓቱ የሚሠራውን የጽድቅና የኃጢአት ሥራ እየጻፉ እስከ
ዕለተ ሞቱ ድረስ ሲጠብቁት ይኖራሉ፡፡ ስለምን ቢሉ ሰውዬው
ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ ሁለቱም ወገኖች የጻፋትን የሕይወት
ታሪክ መዝገብ ይዘው ወደ እግዚአብሔር ይቀርባሉና፡፡
፪. በቀኝ በኩል ያለው መልአክ የመላእክት ብርሃን ወገን ሲሆን
በግራ በኩል ያለው የመላእክት ጽልመት ወገን ነው፡፡ ደግ
በሚሠራበት ጊዜ መላእክት ብርሃን ሲቀርቡ መላእክት
ጽልመት 40 ክንድ ይርቁታል፡፡ ክፉ ሲሠራ መላእክተ ጽልመት
ሲቀርቡት መላእክተ ብርሃን 40 ክንድ ይርቁታል፡፡
፫. በቀኝ ያለው መልእክ ይመክረዋል ምን ብሎ ይመክረዋል
ቢሉ ሃይማኖት ተማር ምግባር ስራ ሰንበትን አክብር ቤተ
ክርስቲያን ተሳለም አሥራት በኲራት አውጣ እንግዳ ተቀበል
7ቱን አጽዋማት ጹም ጸለይ ከዛር ከጠንቋይ አትሂድ
ወንድምህን ውደድ ትሕትና ስራ ነፍስ አትግደል ቋንጃ አትቁረጥ
ቤት አትተኵስ አትስረቅ አታመንዝር አትቀማ ድንበር አታፍርስ
ዋርሳ አትውረስ በሐሰት አትመስክር ሰውን ከፍ ዝቅ አድርገህ
አትመልከት እያለ ይመክረዋል፡፡
፬. ኃጢአትህንም ሳታውል ሳታሳድር ዕለቱን ተናዘዘው፤ ኢትበል
ለጌሠም ጌሠምሰ ትሔሊ ለርእሳ ወየ አክላ ለዕለት እክያ
ወሥራሃ እንዳለ ጌታ በወንጌል፡፡
፭. አቅድሙ ሰንቀክሙ እምቅድመ ትጻኡ እምቤትክሙ እንዳለ
ድርሳነ ሰንበት ይህን ጊዜ በሕይወት ሳለህ ገንዘብህን መጽውት
ከሞትህ ወዲያ የሚያስከትልልህ የለምና እያለ ይመክረዋል
የመከረውንም ሁሉ የፈጸመ እንደሆነ በጐ ሥራውን
ይጽፍለታል፡፡
፮. በግራ ያለው መልአክ ደግሞ ሃይማኖት አትማር ምግባር
አትስራ ሰንበትን አታክብር ቤተ ክርስቲያን አትሳም አሥራት
በኵራት አታውጣ እንግዳ አትቀበል 7ቱን አጽዋማት አትጹም
አትጸልይ አትሰገድ ከዛር ከጠንቋይ ሂድ ወንድምህን አትውደድ
ትሕትና አትስራ ነፍስ ግደል ቋንጃ ቁረጥ ቤት ተኩስ ወይም
አቃጥል ቀማ ስረቅ ድንበር አፍርስ ዋርሳ ውረስ ሐሰት ተናገር
በሐሰት መስክር እያለ ይመክረዋል፡፡
፯. ተንኰሉንም በማጠናከር ሰንበትን አከብራለሁ ትላላህ በሥራ
ቀን ብቻ ሠርተህ ትከብራለህን አትከብርም ብሎ ሰንበትን
ያሽረዋል፡፡
፰. ዳግመኛ ቤተ ክርስቲያን እሰማለሁ ትላለህ ትናንትና ከሥራ
ውለህ ዛሬ ድካም አይሰማህምን ይደክምሃል ይታክትሃል ተኛ
አንቀላፋ እረፍ ተዝናና ብሎ ያስቀረዋል፡፡
፱. ቀጥሎም እመጸውታለሁ ትላለህ ምን እበላ ብለህ ነው?
ሰጥተህ ትለምን ዘንድ ትወዳለህ ይልቁንስ አከማች እያለ
ከልጅነት እስከ እውቀት ከኩተት እስከ ሽበት ሲያሳስተው
ይኖራል፡፡
፲. ይዘግቡ ወኢየአምሩ ለዘያስጋብኡ እንዳለ ክቡር ዳዊት
ያዕቆብ ሐዋርያም እክልክሙኒ ነቀዝ ወአልባሲክሙኒ ቈንቈነ
ወብሩርክሙኒ ዝኅለ ወዛኅሉኒ ይከውነክሙ ስምዐ ወይበልኦ
ከመ እሳተ ለሥጋክሙ እንዳለ፡፡
፲፩. ዳግመኛ ኃጢአቴን ለንስሐ አባቴ እነግራለሁ እናዘዛለሁ
ትላለህ ጹም ጸልይ ቢልህ ጾም አትችልም ሰገድ ቢልህ ጉልበት
የለህ መጽውት ቢልህ ገንዘብ የለህ፡፡
፲፪. ይልቅስ በምትሞትበት ጊዜ ንገረውና እርሱ ይጨነቅበት
እንጂ አንተን ምን ያስጨንቅሃል? በማለት ንስሐ እንዳይገባ
ይከላክለዋል እሱም የመከረውን ሁሉ የፈጸመ እንደሆነ
ይጽፈዋል ይመዘግበዋል፡፡
፲፫. ሀለው ፪ኤቱ መላእክት በኅ ቤነ ዘየዐቅቡነ ፩ዱ በየማንነ
ወካልኡ በፀጋምነ ወይጽሕፉ ኵሎ ምግባራቲነ እመሂ ሠናይ
ወእመሂ እኩየ እንዳለ ያዕቆብ ዘሥሩግ፡፡
፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤
21
#መንገደ_ሰማይ_ስለ_ኅጥእ _ሰው_ነፍስ
አንደኛ ክፍል
21
በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አምነን የኅጥእ ሰው ነፍስ
ከዚህ ዓለም ከሥጋዋ በሞት ተለይታ፤ በሰማያዊ ወይም በአየር
ጉዞዋ ላይ የሚደርስባትን ፈተናና ሥቃይ ባጭሩ በዚህ መጽሐፍ
እንረዳለን፡፡
፩. ወሎ ወሎ ከቤት ኑሮ ኑሮ ከሞት እንደሚሉ ሁሉ ምን ቢኖሩ
ከሞት አይቀሩምና ሰው በድንገት ወይም በሕመም ይሞታል
በሞተም ጊዜ ለጠንቋይ የሚሰግድ እግዚአብሔርን የሚክድ
የተራበ የማያበላ የጠማ የማያጠጣ የታረዘ የማያለብስ እንግዳ
የማይቀበል ድውይ የማይጠይቅ የታሰረ ተውሶ የማያስፈታ
ከሆነ ገና ነፍሱ ከሥጋው ልትለይ ስትቃረብ ሦስት ሰይጣናት
ይታዘዙባታል፡፡
፪. አድኅነኒ በኪዳንከ እመደንግፃን ፫ቱ ሶበ ይፈልጠኒ ሞት
እምሥጋየ ዝንቱ ዳግመኛም ይዘከር ኵሎ ምዕረ ቀዳማዌ
ሞተ መሪር ወዳግመ ሐዊረ ውስተ መቃብር ወሥልስ ወሪደ
ውስተ ገሃነመ እሳት እንዳለ መቃቢስ፡፡
፫. እንዚህ ሦስት ሰይጣናት አንዱ በራሱ አንዱ በልቡ አንዱ
በእግሩ ላይ ተቀምጠው ከልቡ ላይ ያለ ሰይጣን አቆልቊሎ
በጥርሱ ይሰቀስቀዋል ይሰነጥቀል፡፡ በእግሩ ላይ ያለ ሰይጣን
አሻቅቦ ይሰቀስቀዋል በራሱ ላይ ያለ ሰይጣን ግን ከልጅነትህ
ጀምረህ እስካሁን ድረስ ለእግዚአብሔር እንዳትሰግድ ለጠንቋይ
ሳሰግድህ ኃጢአት ሳሠራህ እኖር የነበርሁት እኔ ነኝ እያለ
ኃጢአቱን ይጽፍበታል፡፡
፬. ሶበ ትረክቦ ኃጢአቱ ይጸልኣ እንዳለ ክቡር ዳዊት እርሱም
በልጅነቱ እንደናቱ ጡት ትጣፍጠው የነበረችው ኃጢአት በዓይነ
ነፍሱ ተጽፋ ባያት ጊዜ ይጠላታል አጥብቆ ያማርራታል፡፡
፭. ኃጢአትከ ቅድመ ትጥዕም ከመ አጥባት ወድኅረ ትመርር
ከመ ዕጕስ ታር አጥባተ እምኒ ለእመት ትኅደግ በኃቤሁ
ኃጢአትኒ ኢትትኃደግ እንዳለ ኤጲፋንዮስ፡፡
፮. ዳግመኛም መልአከ ሞት ከአድማስ እስከ አድማስ ተተከሎ
ቁሞ ጥርሱን አግጥጦ ዓይኑን አፍጥጦ ይታያታል
ያስጨንቃታል ያስጠብባታል፡፡
፯. ጥርሱ በመልአኩ ክንድ 68 ነው፤ የመልአኩ 1ዱ ክንድ
በሰው ክንድ 44 ነው፡፡ ያንድ ዓይኑ መቃድ ስፋቱ ሦስት ዓመት
ከመንፈቅ የሁለተኛው ዓይኑ መቃድ ስፋት ሁለት ዓመት
ከመንፈቅ በጠቅላላው የሁለት ዓይኑ መቃድ ስፋት 7 ዓመት
ያስኬዳል ቁመቱም ከምድር እስከ ሰማይ ይደርሳል፡፡
፰. ከዚህ በኋላ ሦስት ጊዜ ተራምዶ መጥቶ ከፊቷ ይቆማል
ወይበጽሕ በሠለስቱ ምስጋና አንዳለ ድርሳነ ሰንበት፡፡ ሁለተኛም
ንዒ ፃዒ አንቲ ነፍስ ወተፈደዪ ፍዳ አበሳኪ እንዳለ ድርሳነ ሰንበት
ዓይኑን አፍጥጦ ጥርሱን አግጥጦ አንቺ ነፍስ በቁመናሽ ትሠሪው
የነበረውን የኃጢአትሽን ዋጋ ነይ ተቀበይ ብሎ በመጣባት ጊዜ
ያቺ ነፍስ ትጨነቃለች፡፡ ከመ ዝኑ ሞት መሪር እንዳለ አጋግ
ከዚያም ከሥጋዋ ተለይታ ተስፈንጥራ ወጥታ ከአስከሬኑ ራስ ላይ
ትቀመጣለች፡፡
፱. በዚህ ጊዜ መልአከ ሞት በጥፍሩ ወግቶ ቆንጥሮ በጥርሱ
ቆርጥሞ አላምጦ 3 ጊዜ ይተፋታል ስለምን ቢሉ የሥላሴን
አንድነታቸውን ሦስትነታቸውን አላወቅሽም ሲል ነው፡፡
፲. በዚህ ጊዜ መላእክት ብርሃን በጥተው ያችን ነፍስ ባዩዋት
ጊዜ ከቁራ 7 እጅ ጠቁራ ትታያቸዋለች አታስቀርባቸውም
መላእከተ ብርጋንም አንቺ ነፍስ ለመንግሥተ ሰማያት ተፈጥረሽ
ለገሃነመ እሳት ተጣልሽን የዲያብሎስን ፈንታ ሆንሽ? ብለው
አዝነው ተክዘው ርቀዋት ይቆማሉ፡፡
፲፩. ወመጽኡ መላእክተ ብርሃን ወሐተትዋ ወኅጥኡ
መክፈልቶሙ አንዳለ ራእየ ማርያም፡፡
፲፪. በዚህ ጊዜ መላእክተ ጽልመት ይዘዋት ይሄዳሉ ኅበ መኑ
ትበጽሒ ወኅበ አይቴ ምግባዕኪ ዘረሣእኪዮ ለፈጣሪኪ እያሉ
እያዘከሩዋት ይዘዋት ሄደው ከባሕረ እሳት ያደርሷታል፡፡
፲፫. የባሕረ እሳት ሁኔታ እንዴት ነው ቢሉ ቀኙ የእሳት ባሕር
ግራው የእሳት ገደል ፀባቡ አንቀጽ ነው፡፡ ወመቅዓን ፍኖታ
ኢያቀውም ዘእንበለ ፩ዱ ኪደተ እግር እንዳለ ድርሳነ ሰንበት
መካከሏም ከጭራ የቀጠነች ጐዳና ናት ጐዳናይቱም ያለ አንድ
ጫማ አታስቆምም፡፡
፲፬. በዚህም ጊዜ ያቺን ነፍስ ሂጂ ግቢ ተሻገሪ ይሏታል
እርስዋም ጌቶቼ ሆይ ቀኙ የእሳት ባሕር ግራው የእሳት ገደል
ነው መካከሏ እንደ ጨራ የቀጠነች ጐዳና ናት ያላንድ ጫማ
አታስቆምም በምን ቁሜ ምን ጨብጨ ምን ይዤ ልሻገር
ትላቸዋለች ይህንም ማለት ቀድም ነበር፡፡
፲፭. ለጠንቋይ አለመስገድ እግዚአብሔርን አለመካድ ሰንበትን
አለመሻር ጾምን አለመግደፍ ሐሰት አለመናገር አደራ
አለመብላት፡፡
፲፮. የተራበ ማብላት የተጠማ ማጠጣት እንግዳ መቀበል
ለታረዘ ማልበስ ድውይን መጠየቅ የታሰረን ዋስ ሆኖ
ማስፈታት ሕገ እግዚአብሔርን ማጽናት መልካም ነው መሆን
ቀድም ነበር እንጂ ዛሬ ደርሰሽ በምን ቁሜ ምን ጨብጩ
ምን ይዤ ብትይ ይሆናልን ይልንቁስ ሂጂ ግቢ ተሻገሪ ብለው
እያዳፉ እየገፉ ከባሕሩ ይጨምሯታል፡፡
፲፯. እርስዋም አንድ ጊዜ ከእሳቱ ባሕር አንድ ጊዜ ከእሳቱ ገደል
እየገባች ከእሳት እንደገባ ጅማት አራ ተኮማትራ ወጥታ
ትሄዳለች፡፡
፲፰. ስትሄድም እንሆ ዛሬ በዚህ ዓለም የንጉሥ ዓመጸኛ እጁን
በሠንሠለት አሥረው ይዘውት ወደ ንጉሥ ሲሄዱ ወዮ ይቈርጡኝ
ይፈልጡኝ ይገድሉኝ ይሆን እያለ እያዘነ እየተከዘ እንደ ሚሄድ
ሁሉ ያቺም ነፍስ ከእግዚአብሔር መጣሏቷን ከዲያብሎስ
መጨመሯን ገሃነም እሳት መውረድዋን ከመንግሥተ ሰማያት
መውጣቷን እያሰበች እየተጨነቀች ትሄዳለች፡፡
፲፱. በዚህ ጊዜ ጌታ የሚቆርጥ የሚሰቅል የሚገድል ንጉሥ
እሱ ብቻ እንደመሆኑ መጠን በሚያስፈራ ግርማ ያቆያታል፡፡
፳. ያን ጊዜም ደርሳ ደፊቱ ትቆማለች፡፡ መልአከ ዑቃቢዋም
አንቺ ዓመፀኛ ትዕቢተኛ ነፍስ እንደ ቀድሞው ዓመጽ ትዕቢት
መናገር አለ ብለሻልን በአርአያው በአምሳሉ የፈጠረሽ
እግዚአብሔር ነውና ስገጅለት ይላታል፡፡ ዝኬ ውእቱ ፈጣሪከ
ዘለኰኪ ስግዲ ወአሞኒኂ ሎቱ እንዳለ፡፡
፳፩. አልአከ ዑቃቢዋም ቀድሞ ከማኅፀን ጀምረህ ጠብቃት
ያልከኝ እስከ ዛሬ ለጠንቋይ ስትሰግድ አንተን ስትክድ ሰንበትን
ስትሽር ጾምን ስትገድፍ ሐሰት ስትናገር አደራ ስትበላ ለተራበ
ሳታበላ ለታረዘ ዋስ ሆኜ አላስፈታም በማለት ፈጣሪዋን
ስታሳዝንና ስታሰቃይም የኖረች ነችና ምንም ቸርነት
አላፈኘሁባትም አንሆ አንደ ሥራዋ ዋጋዋን ስጣት ብሎ
ያስረክባታል፡፡
፳፪. ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም አይቴ ነበርኪ ምንተ ገበርኪ
በስም ክርስቲያናዊት ወበግብረ አረማዊት ኦ ሕርትምት ነፍስ
ይላታል፡፡ እንዲህም ማለቱ አንቺ ርግምት ጐስቋላ ነፍስ ሆይ
በስም ክርስቲያን ነኝ ብለሽ በሥላሴ ስም ተጠምቄአለሁ
እያልሽ ከቤተ ክርስቲያን እየገባሽ ስትመጻደቂ ትኖሪ ነበር
በግብርሽ ግን አረማዊት ግብር ይዘሽ ኖረሻል የት ነበርሽ ምን
አደረግሽ ምን ፈጠርሽ ምን መጸወትሽ ብሎ ይጠይቃታል፡፡
፳፫. እርሷዋም አቤቱ ጌታዬ እኔ ከዚያው ሙቼ ፈርሼ በስብሼ
አፈር ትቢያ ሁኜ እቀራለሁ ብዬ ነበር እንጂ በረቂቅ አካል
ተነስቼ መከራ እንዲያገኘኝ ባውቅማ እንኳን ገንዘቤን ዓይኔን
እግሬን እጄን ሙሉ አካላቴን ሁሉ እየቆረጥሁ ስለ
እግዚአብሔር እያልሁ እንኳን ለሰውና በየቀኑ ላውሬና ላሞራ
በሰጠሁት ነበር ትላለች፡፡
፳፬. እርሱም በስምዓ ፪ኤቱ ወ፫ቱ ይቀውም ኵሉ ነገር
ተብሏልና በይሆን አንኳ ከ3ቱ አንዳቸውን ሳትፈጽሚ የቀረሽ
ለምን ነው ይላታል፡፡
፳፭. እርስዋም የምትመልሰው አታገኝም፡፡ እስመ ይትፈጸም
አፍ ዘይነብብ ዓመፃ እንዳለ ክቡር ዳዊት እንደበቷ ይታሰራልና፡፡
፳፮. እስመ ወኅብኩኪ ዕዝነ ዘትሰምኢ ቦቱ ወዓይነ ዘትሬእዪ
ቦቱ መምሕራነ ወመጻሕፍተ ዘትትመሐሪ ቦቱ ይላታል፡፡
፳፯. እንዲህም ማለቱ ምነው የምታይበት ዓይን የምትሰሚበት
ጆሮ የሚያስተምሩሽ መምሕራንን የምትማሪያቸው
መጻሕፍትን የምትሰግጅበት ቤተ ክርስቲያንን አልሰጠሁሽ ምን
ከጻድቃን ለይቼ ነሳሁሽ ለምን እንዲህ አደረግሽ ይላታል፡፡
፳፰. እርሷም በመረረ ኀዘን ምነው ባልተወለድሁ ምነው
ባልተፈጠርሁ ከናቴ ማኅፀን ውሃ ሁኜ በቀረሁ ስንኳን እኔ እናቴ
የተፈጠረችበት ቀን ባልጠፈጠረች ምን ርግምት ክፉ ቀን ናት
እያለች የተወለደችነትን ቀን ትረግማለች፡፡
፳፱. ከዚህ በኋላ ጌታ መላእክተ ብርሃንን ይህቺን ነፍስ እኔን
ጠልታ ዲያብሎስን ወዳ መንግሥተ ሰማያትን ንቃ ገሃነመ
እሳትን መርጣ መጥታለችና ሥጋዋን ከመሬት አንስቼ ነፍስዋን
ከሥጋዋ አዋህጄ ኋላ ፍጹም ገሃነመ እሳት እስክትገባ ድርስ 7
ቀን መንግስሥተ ሰማያትን ስታስጐበኛት ሰንብታችሁ በ8ኛው
ወደ ሲኦል አግቧት ብሎ ያዛል፡፡
፴. በዚህ ጊዜ መላእክተ ብርሃን መንግሥተ ሰማያተን 7 ቀን
ሲያስጐኟት ይሰነብታሉ ስለምን ቢሉ የመንግሥተ ሰማያት
ጣዕሟን ሽታዋን መዓዛዋን እያየች ለጠንቋይ ባልሰግድ
እግዚአብሔርን ባልክድ ሰንበትን ባልሽር ጾም ባልገድፍ ሐሰት
ባልናገር አደራዬን ባልዘነጋ ለታረዘ ባለብስ ለተራበ ባበለ
ለተጠማ ባጠጣ እንግዳ ብቀበል ድውየን ብጠይቅ የታሠረ ዋስ
ሆኜ ባስፈታ ሥፍራዬ ቦታዬ ይህ ነበር ወይኔ ወዮልኝ እያለች
ፀፀትና ቁጭት እንዲያድርባት 7 ቀን መንግሥተ ሰማያትን
ሲያስጐበኟት ይሰነብታሉ፡፡
፴፩. በስምታኛው ቀን መላእክት ጽልመት ተቀብለው ይዘዋት
ሲሄዱ ወያትክልዋ ከመ ስቡሐ ላህም አንዳለ በድርሳነ ሰንበት
በዚህ ዓለም የእርድ ሰንጋ ወይም የፍሪዳ በሬ ለእርድ እያቻኰሉ
ይዘውት እንደሚሄዱ ሁሉ መላእክት ጽልመትም ያችን ነፍስ
እያጣዳፉ ያዘዋት ይሄዳሉ፡፡
፴፪. ይዘዋትም ሲሄዱ የሲኦል አጋፋሪዋ ጥብልያኮስ የሚባል
አለና ጥብልያኮስ ጥብልያኮስ ብለው ጠርተው ንሣ ይህቺን ነፍስ
ከሲኦል አግባት ብለው ይሰጡታል፡፡
፴፫. እርሱም እሺ ብሎ ተቀብሎ እነሆ ዛሬ በዚህ ዓለም ልጅ
ኳስ ይዞ ከምድር ወደ ሰማይ እያጓነ እንደሚጫወት መላእክተ
ጽልመጽም ያቸን ነፍስ ከምድር እስከ ሰማይ 13 ጊዜ በእሳት
በሎታ ያንቀረቅቧታል ስለምን ቢሉ አዳም አባትሽ በበላው ዕጸ
በለስ ፈጣሪሽ እግዚአብሔር ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድነግል
ማርያም ተወልዶ በዕለተ ዓርብ የተቀበላቸው 13ቱን
ሕማማተ መስቀል ሰምተሸ አላለቀስሺም ሲሉ ስለዚህ
ከምድር ወደሳመይ 13 ጊዜ ያጐናታል፡፡
፴፬. እርስዋም መከራው በፀናባት ጊዜ በእንተ ሥሉስ ቅዱስ
ጥቂት አሳርፉኝ ትላቸዋለች፡፡ ሦስት ሥላሴን ማወቅ ቀደሞ
ነበር እንጂ ዛሬ ከኛ ስትመጭ ነው ማወቅሽ? ዝክራቸውን
መዘከር በዓላቸውን ማክበር ነበር እንጂ ዛሬ ደርሰሽ እንዲህ
ብትይ ይሆናልን ይልቁንስ በሏት ቀጥቅጧት በማለት መከራ
ያጸኑባታል፡፡
፴፭. ዳግመኛም መከራው ሲጸናባት በጻድቃን በሰማዕታት
ጥቂት አሳርፉኝ ትላቸዋለች፡፡ እንዲህ ማለት ቀድሞ
ዝክራቸውን መዘከር በዓላቸውን ማክበር ነበር እነጂ ዛሬ
ደርስሽ እንዲህ ብትይ ይሆናልን በሏት ቀጥቅጧት በማለት
ከቀድሞው ይልቅ መከራ ያጸኑባታል፡፡
፴፮. ሦስተኛም ስለተሰቀለው መድኃኔ ዓለም ብላችሁ ጥቂት
አሳርፉኝ ትላቸዋለች መድኃኔ ዓለምን ማወቅ ቀድሞ ነበር ዛሬ
ደርስሽ ከኛ ስትመጭ ነው ማወቅሽ? ቀድሞ ዝክሩን መዘከር
በዓሉን ማክበር ነበር እንጂ ዛሬ ደርሰሽ እንዲህ ብትይ ይሆናልን
ይልቁንስ በሏት ቀጥቅጧት በማለት መከራውን በእጥፍ ድርብ
ያጸኑባታል፡፡
፴፯. ዐራተኛም በእንተ እግእእትነ ማርያም ጥቂት አሳርፉኝ
ትላቸዋለች እግዝእትነ ማርያምን ዛሬ ደርሰሽ ከኛ ስትመጭ
ነው ማወቅሽ? ቀድሞ ዝክሯን መዘከር በዓሏን ማክበር ነበር
እንጂ ዛሬ ደርስሽ እንዲህ ብትይ ይሆናልን ይልቁንስ በሏት
ቀጥቅጧት በሚሉበት ጊዜ እግዝእትነ ማርያም ስሟን
ሲጠሯት ፈጥና ደራሽ ናትና ሄዳ ከልጅዋ እግር ወድቃ መሐር
ወልድየ ወተዘከር ኪዳንየ ልጄ ሆይ የሰጠኸኝ ቃል ኪዳን አስበህ
ይህቺን ነፍስ ማርልኝ ትለዋለች፡፡
፴፰. እሱም እናቴ ሆይ እኔን የከዳች አንቺን የበደለች ነፍስ ገዳይ
ወንበዴ ነፍስ ናት በምን ምግባሯ ልማርልሽ ይላታል ለዘጸውዓ
ስመኪ ወለዘገብረ ተዝከረኪ እምሕር ለኪ ብለኸኝ የለምን
የሰጠኸኝ ቃል ኪዳን ይታበላልን? እነሆ በሲኦል ሁና ስሜን
ትጠራለችና ትለዋለች፡፡
፴፱. እርሱም የናት ልመና ፊት አያስመልስ አንገት
አያስቀልስምና ጥቂት ጊዜ ስለናቴ ብላችሁ አሳርፏት
ይላቸዋል፡፡
፵. እነሆ ዛሬ በዚህ ዓለም አንድ ሰው በበረሃ ሲሄድ ከታች
እግሩን ረሞጫ እየፈጀው ከላይ የፀሐይ ዋዕይ እራሱን
እያቃጠለው የሚያርፍበት ጥላ አጥቶ ላብ ጥምቅ እያደረገው
ሲሄድ ትንሽ ጠላ ያገኘ እነደሆነ ከዚያ ተንፍሶ እንደሚሄድ ሁሉ
ያቺን ነፍስ ስለእናቱ ጥቂት አሳርፈው እንደገና በእሳት መዶሻ
እየቀጠቀጡ ወስደው ከሲኦል ይጨምሯታል፡፡
፵፩. እንግዲህ የከፋ ሰው ነፍስ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ቦታዋ
ስፍራዋ እንዲህ ያለ ነው፡፡
፵፪. ሲኦል ያለችው በወዴት ናት ቢሉ በምዕራብ ባፀሐይ
መግቢያ በኩል ናት ሲኦልም ማለት መሠረቱ የማይገኝ እሙቀ
ጥልቅ ማለት ነው፡፡
፵፫. ገሃነመ እሳትም ማለት ወደታች ሲወርዱ እግር
የሚረግጠው መሠረት፤ ወደላይ ቢመለከቱ ዓይን የሚጋርድ
ጠፈር የሌለው እሰትና ጨለማ ብቻ ነው፡፡ የገባውን ሁሉ
የሚውጥ የሥቃይና የመከራ ቦታ ማለት ነው ዲያብሎስም
ማለት ርኵስ የረከሰ የከረፋ ማለት ሲሆን ጋኔን ወይም ሰይጣን
ማለት ውድቅ ውዳቂ ከክብሩ የተዋረደ ማዕረጉን የተገፈፈ
ምቀኛ ተንኮለኛ ማለት ነው መላእክተ ጽልመትም ማለት
የጨለማ አበጋዞች የክፋት ሹማምንቶች ማለት ነው የኃጥእ
ነፍስ ሥቃይዋ ይህን የመሰለ ነው? እግዚአብሔር ከዚህ መከራ
ያድነን አሜን፡፡
፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤
21
#መንገደ_ሰማይ_ስለ_ጻድቅ _ሰው_ነፍስ
ሁለተኛ ክፍል፡፡
21
በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አምነን የጽድቅ ሰው ነፍስ
ከዚህ ዓለም ከሥጋዋ በሞት ተለይታ በሰማያዊ ጉዞዋ ላይ
የሚደረግላትን አቀባበል ባጨሩ በዚህ መጽሐፍ እንረዳለን፡፡
፩. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ በምድራዊው ዓለም ሳላችሁ
ሃይማኖት ተማሩ ምግባር ስሩ ብሎ አዟል እንዲህ ማለቱ
ስለምን ነው ቢሉ አንደ እንቦሳ ጥጃ አንደ ሚዳቋ እንደ ጐሽ
እንደ ድኩላ አንደ አንበሳ እንደ በሆር እንደ ነምር አንደ ሰሳ
ሲዘሉ ቢኖሩ ውሎ ውሎ ከቤት ኑሮ ኑሮ ከመሬት ኋላ በዕለተ
ሞት በጌታ ቃል መጠየቅ አይቀርምና ሃይማኖት ተማሩ
ምግባር ስሩ ማለቱ ስለዚህ ነው፡፡
፪. ማንኛውም ሰው በድንገት ወይም ታሞ ይሞታል፤ በሞተም
ጊዜ የመልካም ሰው ነፍስ የሆነች እንደሆነ ገና በፃዕረ ሞቷ
ሳለች ነፍስ ከሥጋ ሳትለይ መላእክተ ብርሃን በቀኝ መላእክተ
ጽልመት በግራ ሁነው ወደእሷ ይመጣሉ መጥተውም ባዩዋት
ጊዜ የብርሃን ቀሚስ ለብሳ የብርሃን መጐናጸፊያ ተጐናጽፋ
የብርሃን አክሊል ደፍታ የብርሃን ዘውድ ተቀዳጅታ የብርሃን
ዝናር ታጥቃ የብርሃን ጫማ ተጫማታ የመስቀል ምልክት
ያለበት የብርሃን ዘንግ ይዛ ከፀሐይ 7 እጅ አብርታ ከመብረቅ 7
እጅ አስፈርታ ፍጹም እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስን መስላ አምራ
ሰምራ ትቆያቸዋለች፡፡
፫. በዚህ ጊዜ መላእክተ ጽልመትን እንደ እሳት ትፈጃችለች
አንደ ፀሐይ ታንፀባርቃቸዋለች ትገለምጣቸዋለች፡፡ ይፈሯታል
የሸሿታል ከፊቷ ርቀው ይቆማሉ፡፡
፬. ምንም ከሷ ርቀው ቢቆሙ ጠርተው ይጠይቋታል ምን
ብለው ይጠይቋታል ቢሉ አንቺ ነፍስ በማን ታምኛለሽ በማንስ
ታመልኪያለሽ የሥላሴን ሦስትነት አንድነት ምልዓት ስፋት
ርቀት የጌታን መውረዱን መወለዱን ወልደ አብ ወልደ
ማርያምነቱን መገፈፍ መገረፉን መስቀል መሞቱን አምስቱን
አዕማደ ምሥጢር 13ቱን ሕማማተ መስቀል ተምረሻል?
የእግዚአብሔርን እንግዳ ተቀብለሻል? ሰንበትን አክብረሻልን
ብለው ይጠይቋታል፡፡
፭. እርስዋም የተማረች ቃሏም የታመነ ነውና አዎን የሥላሴን
አንድነት ሦስትነት ምላት ስፋት ርቀት መውረድ መወለዱን
ወልደ አብ ወልደ ማርያምነቱን መገፈፍ መገረፉን መስቀል
መሞቱን 5ቱን አዕማደ ምሥጢር 13ቱን ሕማማተ መስቀል
አውቃለሁ የእግዚአብሔርን እንግዳ ተቀብዬ ሰንበትንም
አክብሬ እኖር ነበርሁ ግን እንደናንት ያለ የከፋ የከረፋ ሻጋታ
አይቼም ሰምቼም ደርሶብኝም አላውቅ ብላ
ትመልስላቸዋለች፡፡
፮. መላእክተ ጽልመትም መርምረው የእነርሱ ድርሻ
አለመሆኗን ካረጋገጡ በኋላ አንች ነፍስ እኛ ያጣናትን መንግሥተ
ሰማያት አንች አገኘሻት? እያሉ እያዘኑ እየተከዙ ትተው
ይሄዳሉ፡፡
፯. ወመጽኡ መላእክተ ጽልመት ውኅተትዋ ለይእቲ ነፍስ
ወኀጥኡ መክፈልቶሙ እንዳለ ዮሐንስ በራእዩ፡፡
፰. ከዚህም በኋላ መላእክተ ብርሃን በገነት መልካም
መልካሙን የሽቱ አበባ ቆርጠው ይዘው መጥተው በአጠገቧ
ከበዋት ይቆሙና ይጠይቋታል፡፡
፱. ምን ብለው ይጠይቋታል ቢሉ አንቺ ነፍስ በማን ታምኛለሽ
በማን ታመልኪያለሽ የሥላሴን አንድነት ሦስትነት ምልዓት
ስፋት ርቀት የጌታ መውረዱን መወለዱን ወልደ አብ ወልደ
ማርያምነቱን መገፈፍ መገረፉን መስቀል መሞቱን
ታውቂያለሽን ብለው ይጠይቋታል፡፡
፲. እርስዋም ቃሏ እውነት የተማረችም ናትና አዎን የሥላሴን
አንድነት ሦስትነት ምልዓት ስፋት ርቀት የጌታን መውረዱን
መወለዱን ወልደ አብ ወልደ ማርያምነቱን መገፈፍ መገረፉን
መስቀል መሞቱን አውቃለሁ ትላቸዋለች፡፡
፲፩. ዳግመኛም 5ቱን አዕማደ ምሥጢር 13ቱን ሕማማተ
መስቀል ተምረሻል? ሰንበትን አክብርሻል? የእግዚአብሔርን
እንግዳ ተቀብለሻልን ብለው ይጠይቋታል፡፡
፲፪. እርስዋም አዎን አውቃለሁ እናንተማ ወዳጆቼ ዘመዶቼ
አይደላችሁም ያዘዛችሁኝ ሠርቼ የመከራችሁኝ ሰምቼ እኖር
አልነበረምን ብላ ትመልስላቸዋለች፡፡
፲፫. የጻድቅ ነፍስ መላእክተ ብርሃንን እንዲህ የምትላቸው
ወዴት ታውቃቸዋለችና ነው ቢሉ የመልካም ሰው ነፍስ የሆነች
እንደሆነ በዓለመ ሥጋ ሳለች በአካለ ነፍስ ከመላእክተ ብርሃን
ጋራ ከሰማየ ሰማያት እየወጣች እየወረደች ጌታዋን ፈጣሪዋን
ስታመሰግን ትኖር ነበርና ስለዚህ አውቃችኋለሁ ትላቸዋለች፡፡
፲፬. መላእክተ ብርሃንም ያቸን ነፍስ መርምረው የነሱ ወገን
መሆኗን ካረካገጡ በኋላ እኛማ እናውቅሽ የለምን ከቃልሽ
እናገኘው ብለን ነው እንጂ ብለው ይመስክሩላታል፡፡
፲፭. ወመጽኡ መላእክተ ብርሃን ወሐተትዋ ለይእቲ ነፍስ
ወረከቡ መክፈልቶሙ እንዳለ ዮሐንስ በራእዩ፡፡
፲፮. ከዚህም ሁሉ በኋላ ነቢዩ ዳዊት በገናውን ዕዝራ
መሰንቆውን ይዘው ጌታም እልፍ አዕላፍት መላእክተን ጻድቃን
ሰማዕታትን ደናግል መነኮሳትን አስከትሎ ወርዶ በቁመናዋ
የሰራችውን የምግባሯን ዋጋ ቃል ኪዳን ጸጋ ክብር ሰጥቷት
ተመልሶ ሰማየ ሰማያት ያርጋል፡፡
፲፯. መውጣት መውረዱ ለእኛ ክብር ሲል በለበሰው ሥጋ ነው
እንጂ በመለኮትነቱስ በሁሉ የመላ ስለሆነ መውጣት መውረድ
የለበትም፡፡ ውስተ ኵሉ በሐውርት መለኮቱ እንዳለ ክቡር
ዳዊት፡፡
፲፰. ከዚህም በኋላ መልአከ ሞት አምሮ ሠምሮ ፍጹም
መልአከ ሣህ መልአከ ብርሃን መስሎ ይታያታል ከመ ዝኑ ሞት
ሠናይ እንዳለ አብርሃም፡፡
፲፱. ስለምን መልአከ ሞት መልአከ ሣህል መልአከ ብርሃን
መስሎ ይታያታል ቢሉ እንዳትባባ ነው፡፡
፳. ከዚህም በኋላ መላእክተ በርሃን ያንን ከገነት ቆርጠው
ያመጡትን የሽቱ አበባ ከአፍንጫዋ ላይ ጣል አድርገው
ሲያነሱት በዚያ የሽቱ መዓዛ ተመስጣ ነፍስዋ ከሥጋዋ ትለያለች
በጻድቃን ሰው ነፍስ ፃዕር ጋዕር የለባትምና ድንግል ጊዜ
ዕረፍታየ ጽጌ ዕፀ ገነት ገሪ ላዕሌየ በመዓዛሁ ትትመስጥ ነፍስየ
እንዳለ፡፡
፳፩. ከዚህም በኋላ መላእክተ ብርሃን በፊት በኋላ በቀኝ በግራ
ሁነው ይዘዋት ሲሄዱ ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ
ወለመንፈስ ቅዱስ ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት
ለመንፈስ ቅዱስ እያሉ ያመሰግናሉ፡፡
፳፪. ዳዊት ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር ዝክረ
ጻድቅ ለዓለም ይሄሉ እንዳለ ዕዝራም ሞቶ ሙሰ ለጻድቃን
ሕይወቶሙ ውእቱ ብጽዕት ነፍስ መላእክተ ሰማይ ይትለ አኩኪ
እያሉ ዕዝራ መሰንቆውን ዳዊት በገናውን እየደረደሩ እያመሰገኑ
በይባቤ በዝማሬ ወደ ጌታ ይዘዋት ይሄዳሉ፡፡
፳፫. ከዚህም በኋላ መላእክተ ጽልመት ከጌታ ትእዛዝ ሣይቀበሉ
አይለቁምና እራስ እራሷን እየተመለከቱ ሲከታተሏት ከባሕረ
እሳት ይደርሳሉ፡፡ የባሕረ እሳት ቦታው ስፍራዋ ወዴት ነው
መጠኗስ ምን ያህል ነው ቢሉ ቦታዋ ከጠፈር በላይ ከሐኖስ
በታች ከመካከል በምጽንዓተ ሰማይ ነው፡፡
፳፬. መጠኗም ይህችን ሰው የሠራባትን ዓለም ታህላለች ቀኝዋ
እሳት ግራዋ ባሕር ነው፤ ውስጧ ገደል ነው በመካከሏም እንደ
ጭራ የቀጠነ ጠባብ መንገድ አለ፡፡
፳፭. ፀባብ አንቀጽ ወመቅዓን ፍኖታ የማና እሳት ወፀጋማ ማይ
ወኢታገምር ዘእንበለ መጠነ አሐቲ ኪደተ እግር እንዳለ ዕዝራ
እንኪህም ማለቱ በእግረ ነፈስ ነው እንጂ በእግረ ሥጋስ
አታስቆምም፡፡
፳፮. እንዲህማ ከሆነ ምን አድርጋ ትሻገረዋለች ቢሉ በዚህ
ዓለም ያሉ አዕዋፍ ዱሩን ገደሉን ባሕሩን እሳቱን ላይ ላዩን
በክንፍ እየበረሩ ተሸግረው እንዲሄዱ የርስዋም ሃይማኖቷና
ግብሯ ክንፍ ሁናት መላእክተ ብርሃን ላይ ላዩን በክንፍ ይዘዋት
ይሻገራሉ፡፡
፳፯. እርስዋም ከመካከል ስትደርስ አቈልቁላ አይታ መላእክተ
ብርሃንን ይህ እሳቱ ባሕሩ ገደሉ ዱሩ ምንድር ነው ብላ
ትጠቃቸዋለች፡፡
፳፰. መላእክተ ብርሃንም አንቺ ምግባር ብትሰሪ ሃይማኖት
ብትማሪ ሰንበትን ብታከብሪ በዚህ መጣሽ እንጂ ምግባር
ያልሰሩ ሃይማኖት ያልተማሩ ዘመዶችሽስ በዚያው አረው
ከስለው እንደ ጅማት ተኮማትረው መከራ አይተው ነው
የሚሻገሩት ይሏታል፡፡
፳፱. እርስዋም ወየው ወየው በዚያ ዓለም ላሉ ሰዎች እንዲህ
ያለ ብርቱ መከራ እንዳለባቸው ማን በነገራቸው ብላ አዝና
ተክዛ አልቅሳ ወጥታ ትሄዳለች፡፡
፴. መኑ እምዜነዎሙ ለሰብእ ዓለም አንዳለ ሰቆቃው ነፍስ፡፡
፴፩. ስትሄድም ዛሬ በዚህ ዓለም ያለች ሙሽራ አባቷ እናቷ
መልስ ጠርተዋት በፍሥሐ በደስታ እንድትሄድ እርስዋም
ከፈጣሪዋ ለመገናኘት ስትሄድ በፍሥሐ በደስታ ትሄዳለች፡፡
፴፪. ዳግመኛ ዛሬ በዚህ ዓለም ያሉ እናት አባት ልጃቸው
የሚበላውን የሚጣጣውን አሰናድተው እንዲቆዩ ለርስዎም
ፈጣሪዋ የመኖሪያዋን ቦታ መንፈሳዊ ምግብና መጠጥ አዘጋጅቶ
በፍሥሐ በደስታ ይቆያታል፡፡
፴፫. እርስዋም ከገሃነመ እሳት መውጣቷ ደስ ደስ እያላት ከጌታ
ዘንድ ስትደርስ ሰግዳ ትቆማለች፡፡
፴፬. ወታቀድም ሰጊዶ ለልዑል እንዳለ እዝራ
፴፭. ከዚህም በኋላ ጌታ ይጠይቃታል ሲጠይቃትም የወንድ
ነፍስ የሆነች እንደ ሆነ አንች ነፍስ እንጨት መቁረጥ ቤት
ማነጽ ፈረስ መጋለብ ውሀ ዋና ሠንጠረዥ በገና እርሻ ቁፋሮ
ጸናጽል ከበሮ ጽሕፈት ድጉሰት ታውቂያለሽን ብሎ
አይጠይቃትም፡፡
፴፮. የሴትም ነፍስ ብትሆን አንች ነፍስ አልሞ መደቆስ
አለስልሶ መፍተል ወጥ መሥራት እንጀራ መጋገር ጠጅና ጠላ
መጥመቅ ታውቂያለሽን ብሎ አይጠይቃትም፡፡
፴፯. እንግዲያ ምን ብሎ ይጠይቃታል ቢሉ አንቺ ነፍስ በማን
ታምኛለሽ በማንስ ታመልኪያለሽ አንድነቴን ሦስትነቴን
ምልዓት ስፋቴን ርቀቴን ከሰማየ ሰማያት መውረዴን ወልደ
አብ ወልደ ማርያምነቴን መገፈፍ መገረፌን በመስቀል
መሞቴን 5ቱን አዕማደ ምሥጢር 13ቱን ሕማማተ መስቀል
ታአውቂያለሽን ብሎ ይጠይቃታል፡፡
፴፰. እርስዋም የተማረች ቃልዋም እውነተኛ ነውና አቤቱ ጌታ
ሆይ ሦስትነትህ አንድነተህን ምልዓት ስፋትህን ርቀትህን
መውረድ መወለድህን ወልደ አብ ወልደ ማርያምነትህን
መገፈፍ መገረፍህን መስቀል መሞትህን አውቃለሁ ብላ
ትመልሳለች፡፡
፴፱. ከዚያም የጌታ ቃሉ እውነት ነውና መላእክት ብርሃንን
ጠርቶ ይህች ነፍስ ምዕመን ክርስቲያናዊት ናትና መንግሥተ
ሰማያት እንጂ ገሃነመ እሳት አይገባትም ነፍሷን ከሥጋዋ ጋራ
አዋህጄ ፍጹም መንግሥተ ሰማያትን እስካወርሳት ድረስ ዐራት
ቀን መንግሥተ ሰማያትን ሦስት ቀን ገሃነመ እሳትን አዙራችሁ
አስጐብኝታችሁ ከጻድቃን ጋራ በገነት አኑሯት ብሎ ያዛል፡፡
፵. ከዚህ በኋላ መላእክተ ብርሃን ይዘዋት ወጥተው መንግሥተ
ሰማያትን ብሔረ ጻድቃንን ሦስት ቀን አዙረው አሳይተው
አስጐብኝተው ሽታዋን ጣዕሟን በልቡናዋ አሥርፀው አንቺ
ነፍስ ሃይማኖት ብትማሪ መግባር ብትስሪ ከእንዲህ ያለ ኅዘን
ከሌለበት የደስታ ቦታ ያኖረሻል ብለው ወደ ገሃነመ እሳት
ይዘዋት ይወርዳሉ፡፡
፵፩. ከገሃነመ እሳት ውስጥ ያለውን የእሰቱን ዘውድ የእሳቱን
አክሊል የእሳቱን ዘንዶ የእሳቱን እባብ የእሳቱን አንበሳ የእሳቱን
ዝናር የእሳቱን ጫማ የእሰቱን ነብር የእሳቱን ውሻ የእሳቱን
ዝሆን የእሰቱን መጋዝ የእሰቱን ሰይፍ የእሳቱን ጦር የእሳቱን
ወፍጮ የእሳቱን ሙቀጫ ክፋቱን ክርፋቱን ዐራት ቀን አዙረው
አስጐብኝተው ይመልሷታል፡፡
፵፪. ወያዓውድዋ ሰቡዓ ዕለታተ እንዳለ ዩሐንስ በራእዩ፡፡
፵፫. ከዚህም አውጥተው ሀገረ ሕያዋንን ሀገረ ሰማዕታትን ሀገረ
ደናግልን ሀገረ መነኮሳትን ሀገረ ሕጋውያንን እያዞሩ እያሳዩ አንቺ
ነፍስ ሃይማኖት ብትማሪ ምግባር ብትሰሪ ጌታ በቸርነቱ
ከዲያብሎስ መገዛት ከእንዲህ ያለ መከራ አውጥቶ ከእንዲህ ያለ
ተድላ ደስታ አበቃሽ ብለው ወስደው ከጻድቃን ጋር በገነት
ያኖሯታል፡፡
፵፬. ገነት ያለችው በወዴት ናት ቢሉ በፀሐይ መውጫ ወይም
በስተምሥራቅ በኩል ናት በዐራቱ ማዕዘኗ ዐራት ተራሮች አሏት
በዐራቱ ተራሮች መካከል ዐራት አፍላጋት ገብተው ያጠጧታል፡፡
፵፭. ዐራቱ አፍላጋት ማን ማን ናቸው ቢሉ አንደኛው ዐባይ
ግዮኖ ሲሆን እሱም ወይን ነው፡፡ በኢትዮጵያና ግብጽ ያሉትን
የወንዝ ውሃዎች ሁሉ ሰብስቦ ይዞ ይሄድና ገነትን አጠጥቶ
ተመልሶ ኢያሪኮ ይገባል፡፡
፵፮. ሁለተኛው ኤፌሶን የሚባለው ወንዝ ሲሆን እሱም ወተት
ነው፤ (በመሊጡ?) በሕንደኬ አገር ያሉትን የወንዝ ውሃዎች
ሁሉ አሰባስቦ ይዞ ይሄድና ገነትን አጠጥቶ ተመልሶ ውቅያኖስ
ይገባል፡፡
፵፯. ሦስተኛው ጤግሮስ የሚባለው ወንዝ ማር ነው በዮናንያን
አገር ያሉትን የወንዝ ውሃዎች ሁሉ አሰባስቦ ይዞ ይሄድና ገነትን
አጠጥቶ ተመልሶ ባሕረ ኤርትራ ይገባል፡፡
፵፰. ዐራተኛው ኤፍራጥስ የሚባለው ወንዝ ዘይት ነው
በአውሮፓ፤ በፋርስ፤ በባቢሎን ያሉትን የወንዝ ውሃዎች ሁሉ
አሰባስቦ ይዞ ይሄድና ገነትን አጠጥቶ ተመልሶ ባሕረ ኤርትራ
ይገባል፡፡
፵፱. ከነዚህ ከዐራቱ አፍላጋት እየመነጩ ወደገነት የሚገቡት
ዐራት ዓይነት ፈሳሾች በገነት የሚኖሩ ጻድቃንን ሳይበሉ ሳይጠጡ
በጣዕማቸውና በመዓዛቸው ሽታ ብቻ ሲያረኳቸው ይኖራሉ፡፡
፶. ወደቀድሞው ነገራችን እንመለስና ያች ደገኛይቱ ነፍስ
ከገሃነመ እሳት መውጣቷን መንግሥተ ሰማያት መግባቷን
የገሃነመ እሳትን ሥቃይ እያሰበች ፈጣሪዋን እያመሰገነች እስከ
ጊዜ ምጽአት ድረስ በፍሥሐ በደስታ ትኖራለች ከምጽአትም
በኋላ ከሥጋዋ ጋራ ተዋህዳ ተድላ ደስታ ካለበት ፍጹም
መንግሥተ ሰማያት ትገባለች፡፡
፶፩. መንግሥተ ሰማያት ያለችው በወዴት ነው ቢሉ በኢዮር
በላይ ከሰማይ ውዱድ በታች በመካከላቸው ናት መንግሥተ
ሰማያት የተባለችውም ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ናት የኸውም
ቀድሞ ዲያብሎስ በክብሩ ሳለ የእሱ ከተማ ነበረች፡፡ እሱ
ከተሻረ ወዲህ ግን አዳምን የፈጠረው በእሱ ምትክ ስለ ነበረ
ከነልጅ ልጆችህ እርስት ትሁንህ ብሎ ጌታ ሰጥቶታል፡፡
የመልካም ሰው ነፍስ ሁኔታ ባጭሩ ይህ ነው፡፡ እግዚአብሔር
ይህን ክብር ያድለን አሜን፡፡ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤
፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤
ምንጭ፡ መዝገበ ጸሎት ወመጽሐፈ ጸሎት የሰሙነ ሕማማት
ሥራዓተ ስግደት ወጸሎት የጽዋማትና የበዓላት ማውጫ
በአማረኛ ባለ ሰባ ስምንት ከሚባል የጸሎት መጽሐፍ ላይ
(2000 ዓ.ም ሚሊኒየም አሣታሚ ገብረሥላሤ ብርሃኑ
ዘብሔረ አክሱም ) ከገጽ 687 እስከ 728 በእጅ ተጽፎ
የተወሰደ በዘሪሁን እሸቱ 13/8/2008 ዓ.ም ተዘጋጀ፡፡
፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤ ፤፤
የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የድንግል ማርያም አማላጅነት፣
የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣
የቅዱሳን ሐዋርያት፣ የቅዱሳን አበው መነኮሳት፣ የቅዱሳት
አንስት፣ የደናግላንና የቅዱሳን ሁሉ ምልጃና ቃል-ኪዳናቸው
ባለንበት ከሁላችን ጋር ይሁን!!!
†† † ♥ † ††
ለአባ ሕርያቆስ ፤
ለቅዱስ ኤፍሬም ፤
ለቅዱስ ያሬድ ፤
ለአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
የተገለጸች እመቤታችን እኛንም በበረከት እና በረድኤት
ትጎብኘን ፤ ከልጅዋ ከወዳጅዋ ከመድኃኔዓለም ዘንድ ታማልደን
፤ አሜን!!!
†† † ♥ † ††
ከዋክብት የሚያመሰግኑት
በስማቸውም የሚጠራቸው:
የፀጋው ብዛት የማይታወቅ
ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ
ለሐዋሪያት እንዲሁም ለቀደሙ አባቶቻችን ምሥጢሩን
እንደገለጽክላቸው ለእኛም ግለጽልን። አሜን አሜን አሜን!!!
†† †♥ † ††
ወ ስ ብ ሐ ት ለ እ ግ ዚ አ ብ ሔ ር
ወ ለ ወ ላ ዲ ቱ ድ ን ግ ል
ወ ለ መ ስ ቀ ሉ ክ ቡ ር