ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

Thursday, March 31, 2016

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ:እመቤታችን_እና_ኤልሳቤጥ

#እመቤታችን_እና_ኤልሳቤጥ
_
በመከራው ያልተለየችው ፣ በመስቀሉ ሥር ከነበሩት ቅዱሳት
አንስት ዝርዝር ውስጥ በቀዳሚነት የተጠቀሰችው
#እመቤታችን እሑድ ደርሶ ሴቶች ወደ መቃብሩ ሽቱ ይዘው
ማልደው ሲሔዱ ግን ከእነርሱ ጋር አልነበረችም፡፡ #ለምን
ይሆን? መልሱ ቀርቧልና ይነበብ...
21 21 21 21 21
21
ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ ‹‹ስለ ድንግል ማርያም ገና ማሰላሰል
ስጀምር ‹የቆምክባት ሥፍራ የተቀደሰች መሬት ናትና ወደዚህ
አትቅረብ›
የሚል ድምፅ ሲጮኽ ይሰማኛል›› በማለት እንደተናገረ ስለ
እመቤታችን
ልንጽፍ ብዕራችንን ባነሣን ቁጥር የኃጢአት ጫማችንን
ሳናወልቅ ወደ
እርስዋ መቅረብ እንደማይገባን ይሰማናል፡፡ ሰውና መላእክት
ተናግረው
ለመፈጸም የማይቻላቸውን ምስጋናዋን ለመናገር ስንነሣም
ድካማችንን
አውቀን እንሰቀቃለን፡፡ ‹ስለ እርስዋ መናገር የሚቻለው ምን
አንደበት
ነው? አስቦትስ ሊደርስበት የሚቻለው እንደምን ያለ ኅሊና ነው?
ነገር
ግን የሚቻለንን ያህል ከምስጋናዋ ጥቂት እንነግራችኋለን ›
ብለው
እስከመናገር የደረሱ አባቶቻችንን ስናይ ከምስጋናዋ ሰልፍ
መደመር
ያስጨንቀናል፡፡ አባቷ ዳዊት ‹በአባቶችሽ ፈንታ ልጆች
ተወለዱልሽ ፣
ስምሽን ለልጅ ልጅ ያሳስባሉ› ያላትን ስናስብ ደግሞ
የአባቶቻችን ልጆች
እንደመሆናችን የእመቤታችንን ስሟን ማሳሰብ ለእኛም
እንደተሠጠን
በማሰብ እንደሰታለን፡፡ እርስዋም ‹ትውልድ ሁሉ ብፅዕት
ይሉኛል›
ብላለችና ከትውልድ እንደመቆጠራችን የተናገረችው ትንቢት
ይፈጸማል
ብለን ስለ እመቤታችን ክብር እንናገራለን፡፡ ነቢዩ "በቀንና
በሌሊት
ደጆችዋ አይዘጉም" ሲል እንደተናገረላት ቀንና ሌሊት ምስጋናን
ሲሰሙ
የማይዘጉት የጆሮዎቿን ደጆች ተስፋ አድርገን ቅድስት ሆይ
ለምኚልን
ሳንላት አናድርም፡፡ እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደ ምድር አሸዋ
በበዛው
ኃጢአታችን ምክንያት ስለ እመቤታችን መናገራችን የሚገባን
ባይሆንም
አባቷ ዳዊት በታላቅ ትሕትና ‹ልጄ ሆይ ስሚ እዪም ጆሮሽንም
አዘንብዪ›
እያለ እየተማጸነ እንዳመሰገናት እኛም ‹እናታችን ሆይ ስሚ እዪ
ጆሮሽንም አዘንብዪ› ብለን እየተማጸንን እናመሰግናታለን፡፡
ከአባ
ጊዮርጊስም ጋር ‹‹እመቤቴ ሆይ የኃጢአተኛ ሰው ምስጋና ለምኔ
ነው
አትበዪ የእኔ ኃጢአት የአንቺን ቅድስና አያረክሰውምና›
እንላለን፡፡ /
አርጋኖን/
21
ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ ማርያም ተብለው የተጠሩ አምስት
ሴቶችን በስም ጠቅሶ ሲጽፍ ለዐሥራ አራት ዓመታት በቤቱ
የኖረችውን
እመቤታችንን ግን ስምዋን ከመጥራት ይልቅ ‹የኢየሱስ እናት›
፣ ‹የጌታ
እናት› ፣ ‹እናቱ› ብሎ መጥራትን እንደመረጠ እኛም በዚህ
ጽሑፍ
እመቤታችን ብቻ ብለን እየጠራን ስለ እርስዋ ክብር
እንናገራለን፡፡ ይህ
ጽሑፍ ጥናታዊ ጽሑፍ አይደለም፡፡ የጽድቅ ፀሐይ የወጣበትን
ሰማይ ማን
አጥንቶ ይዘልቀዋል? የማይቻለውን ስለ ቻለችው ፣
የማይወሰነውን
ስለወሰነችው እመቤታችን ከምስጋና በቀር ማንም ሰው
ምሁራዊ
ትንታኔን ሊሠጥ አይችልም፡፡ ስለዚህ ስለ እመቤታችን በቅዱስ
ሉቃስ
ወንጌል ብቻ የተጻፉ አንዳንድ ነጥቦችን እናነሣለን፡፡
21 21 21
#እመቤታችን_እና_ቅዱስ_ገ ብርኤል
°
አምላክ በሰው ላይ የፈረደውን ፍትሐ ሞት በራሱ ለማድረግ
ሰው ሊሆንና ሊያድነው የገባውን ቃል ለመፈጸም በእርሱ ዘንድ
አምስት
ቀን ከግማሽ በእኛ ዘንድ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን
አስቆጥሮአል፡፡ ‹‹የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ›› ግን አምላክ
‹‹ከሴት››
ሊወለድ ፈቃዱ ሆነ፡፡ (ሊቁ ኤጲፋንዮስ እንዳብራራው እኛ
ከሴትና
ከወንድ እንደተወለድን ፤ እርሱ ግን በሁለተኛው ልደት ያለ ዘርዐ
ብእሲ
ከሴት ብቻ እንደተወለደ ልብ ይሏል) /ገላ.4/ አምላክ ይህንን
የማዳን
ሥራ ለመፈጸም የመረጣት ንጽሕት እመቤታችን ነበረች፡፡ ነገር
ግን
የሰውን ነጻ ፈቃድ /Free will/ የሚያከብር ነውና ሊወለድ
እንደወደደ
በራሱ ፈቃድ ብቻ ልወለድ ሳይል ወደ መረጣት ቅድስት
መልአኩን ላከ፡፡
ለመልእክት የተመረጠው መልአክ መላእክቱን ‹ባለንበት
እንጽና› ብሎ
ያረጋጋው መልአከ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ነበረ ፡፡ ይህ መልአክ
ሦስቱን
ወጣቶች ከእሳት መካከል ሊያወጣ እንደተላከ አሁን ደግሞ
የሰው
ልጆችን ከሲኦል እሳት መውጣት ለማብሠር ተላከ፡፡ ቅዱስ
ገብርኤል
እመቤታችን ፊት ለማብሠር ቆመ፡፡
21
የተላከው ከኃያሉ ባለ ሥልጣን ከእግዚአብሔር ዘንድ ቢሆንም
አነጋገሩ ከላይ እንደተላከ ሆኖ የተናገረው የሥልጣን ንግግር
ሳይሆን
የፍጹም ትሕትና ንግግር ነበር፡፡ ‹አምላክ ከአንቺ ሊወለድ
ወስኖአል!›
ብሎአትም አልተሠወረም፡፡ መልእክተኛ የሚያደርሰው
እንደተላከው
አድርጎ ነውና ይህችን ከፍጥረት ሁሉ የከበረች ንግሥት አደግድጎ
አመስግኖ አክብሮ አበሠራት፡፡ ‹ደስ ይበልሽ ጸጋን የሞላብሽ
ሆይ ጌታ
ከአንቺ ጋር ነው ፣ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ›
አላት፡፡ ለሰው
የተለያየ ጸጋ ይሠጠዋል፡፡ ‹‹የጸጋ ሥጦታ ልዩ ልዩ ነው መንፈስ
ግን
አንድ ነው›› ይላል ሐዋርያው፡፡ የእመቤታችን ጸጋዋ ምን
ይሆን? ሰንል
ግን ይህ ነው ብሎ መወሰን አይቻልም፡፡ እግዚአብሔር
ለእርስዋ
ያልሠጠው ሀብት የለም ቅዳሴው ‹ወሀብተ ሰማያት ለማርያም
ድንግል›
‹የሰማያት ሀብት ለማርያም ድንግል ተሠጣት› እንደሚል
እመቤታችን
ጸጋ ሁሉ የተሞላች ናት፡፡ ስለዚህ መልአኩ በታላቅ አክብሮት
አመሰገናት፡፡
21 21 21
#ከንግግሩ_በጣም_ደነገጠች
°
እርስዋም ባየችው ጊዜ ‹ከንግግሩ በጣም ደነገጠች› የሶምሶን
ቤተሰቦች ማኑሔና አንትኮዬ የእግዚአብሔርን መልአክ ባዩ ጊዜ
እጅግ
ደንግጠው ነበር፡፡ ታላቁ መስፍን ጌዴዎን ደግሞ ‹ወዮልኝ
የእግዚአብሔርን መልአክ ፊት ለፊት አይቼአለሁና› ብሎ
እንዳይሞት
ፈራ፡፡ እግዚአብሔር ግን አይዞህ አትሞትም ብሎ አረጋጋው፡፡ /
መሳ. 5፡
22/ ታላቁ ነቢይ ዳንኤል ደግሞ መልአክ ባየ ጊዜ ‹‹ደም
ግባቴም ወደ
ማሸብሸብ ተለወጠብኝ፥ ኃይልም አጣሁ። …. ቀጥ ብለህም
ቁም
አለኝ። ይህንም ቃል ባለኝ ጊዜ እየተንቀጠቀጥሁ ቆምሁ።››
በማለት
እንዴት እንደፈራ ይገልጣል፡፡ እመቤታችን ቅዱስ ገብርኤልን
ስታየው ግን
የደነገጠችው መልአኩን በማየትዋ አልነበረም፡፡ ‹‹የቃሉን
አነጋገር
አይታ›› እንጂ፡፡ (አይታ ሲል ሰምታ ለማለት ነው፡፡
ትርጓሜውም ርዕያ
ቅሉ ሰሚዓ ሲል ነው ይላል፡፡) መልአኩን ስታይ ተንቀጠቀጠች
፣ መቆም
አቅቷት ተብረከረከች የሚል ቃል የለም እርስዋ የደነገጠችው
በንግግሩ
ብቻ ነበር፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ነቢያቱ ሳይቀር
የደነገጡባቸው
መላእክት እንዴት አላስደነገጡአትም? አዎ እርስዋ ያደገችው
በመላእክቱ እቅፍ ስለሆነ ነው፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ
በአንድ ክንፉ
አቅፎ በአንድ ክንፉ ደግፎ ሰማያዊ ምግብ እየመገበ ያሳደጋት
እመቤታችን እንዴት መልአክ አይታ ትደነግጣለች? ነገሩን አልን
እንጂ
ራሳቸው መላእክት ሊያዩት የማይቻላቸውን አምላክ በማኅጸኗ
የምትይዘው እርስዋ እንዴት መላእክቱን ትፈራለች? ለእስዋ
እንግዳ
የሆነባት መልአክ መሆኑ ሳይሆን ሰላምታው ነበር፡፡
21 21 21
‹‹ #ይህ_እንዴት_ያለ_ሰላምታ _ነው; #ብላ_አሰበች››
°
አንዳንዶች እመቤታችን ስላደረገችው ነገር ብዙ አልተጻፈም
ብለው በመናገር ስለ እመቤታችን ለመናገር ስንነሣ ሊያሳቅቁን
ይሞክራሉ፡፡ ይህችን ጥቅስ ልብ ስንላት ግን ሐሴት
እናደርጋለን፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ እመቤታችን ያደረገችውን ብቻ ሳይሆን
‹ያሰበችውንም›
ጭምር ጽፎልናል፡፡ ቅዱስ ሉቃስ መንፈስ ቅዱስ ገልጦለት
የእመቤታችንን ሃሳቧን ጻፈ! ሐዋርያቱ ሐሳቧን ሳይቀር ከጻፉ
እኛ
ተአምሯን ብንጽፍ ምን ጥፋት አለብን? ሃሳብ ከተጻፈ እንዴት
ተግባር
አይጻፍም?
እዚህ ላይ የምንማረው ታላቅ ትምህርት ልጅዋ ‹እኔ የዋህ
በልቤም ትሑት ነኝ› እንዳለው የእርስዋም ትሕትና የልብ
መሆኑን ነው፡፡
ሰው ሲመሰገን ‹ኸረ ለእኔ ይህ አይገባኝም› እያለ ላይ ላዩን በአፉ
ይቃወማል፡፡ በውስጡ ግን በምስጋናው ደስ ይለዋል፡፡
እመቤታችን ግን
ምስጋናን ስትሰማ ‹አይገባኝም› የሚል የአንደበት ንግግር
አልተናገረችም፡፡ ትሕትናዋ የልብ ነበርና ‹እንዴት ያለ ሰላምታ
ነው ብላ
አሰበች› መልአከ እግዚአብሔር ከፊቱ ቆሞ እያነጋገረው
የመልአኩን
ሰላምታ የሚመረምር ማን ነው; መልአክ ተገልጾ አመሰገነኝ
ብሎ
ሳይደነቅና ሳይደሰት ስለ ሰላምታው ምንነት ‹ይህ እንዴት ያለ
ሰላምታ
ነው;› ብሎ የሚያገናዝብስ ከሰው ልጅ መካከል ከእመቤታችን
በቀር
ማን ይገኛል;
21
መልአኩም ‹‹መልአኩም እንዲህ አላት፦ እርሱ ታላቅ ይሆናል
የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን
ዙፋን
ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፥
ለመንግሥቱም
መጨረሻ የለውም።›› አላት፡፡
እመቤታችን ሔዋንን ያሳተው የዲያቢሎስ ሽንገላ ወደ እርስዋ
የመጣ ይሆንን ስትል ከመልአኩ የቀረበላት ሰላምታ
አስደንግጦአት
ነበር፡፡ ምስጋና ከሆነ ዘንድ ብላ ጆሮዋን የምትሠጥ
ስላልነበረች ‹ጸጋን
የተመላሽ› ፣ ‹ከሴቶች ሁሉ የተባረክሽ› ያላትን ምስጋናም
ከደስታ ይልቅ
በፍርሃት ተመለከተችው፡፡ ግእዙ እንዲያውም ‹‹እፎኑ ዘከመዝ
እንጋ
አምኃ ይትአምኁ›› ‹‹እንዲህ ያለውን ሰላምታ እንደምን
ይቀበሉታል››
ብላ አሰበች ይላል፡፡ ቅዱስ ገብርኤል ‹‹ማርያም ሆይ፥
በእግዚአብሔር
ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ።›› በማለት ‹ጸጋን የተሞላሽ›
ያላት
በእግዚአብሔር ፊት ያገኘችው ጸጋ እንደሆነ ነገራት፡፡ ከዚያም
‹‹እነሆም፥ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም
ኢየሱስ
ትዪዋለሽ።›› በማለት አበሠራት፡፡ ቅዱስ ገብርኤል ‹ኢየሱስ›
የሚለውን
ስም ለዓለም አስታወቀ፡፡ ክርስትናም በገብርኤል አንደበት ወደ
እኛ
መጣ፡፡
21 21 21
‹ #ወንድ_ስለማላውቅ_ይህ_እ ንዴት_ይሆናል?›
°
አንዲት በጋብቻ ለመኖር ፍላጎትና ዕቅድ ያላት ድንግል
‹ትወልጂያለሽ› ተብሎ /ያውም በመልአክ አንደበት/ ቢነገራት
ማንን
እንደምታገባ ፣ ነገሩ መቼ እንደሚፈጸም ወዘተ ትጠይቅ
ይሆናል እንጂ
ሊሆን እንደሚችል ስለምታውቅ ‹‹ወንድ ስለማላውቅ ይህ
እንዴት
ይሆናል?›› አትልም፡፡ ሣራ ትወልጂአለሽ መባሉን ስትሰማ
‹‹እንዴት
ይሆናል?›› ያለችው አርጅቼአለሁ ብላ ነበር፡፡ እመቤታችን ግን
ገና
የዐሥራ አምስት ዓመት ብላቴና ሆና ሳለ የከበረ መልአክ
ትወልጂያለሽ
ሲላት ‹እንዴት ይሆናል?› ማለትዋ ለምንድር ነው? ሊቃውንቱ
‹‹ዘንተ ትቤ
ድንግል በእንተ ዘኢዓርገ ሕሊና እጓለ እመሕያው ውስተ ልባ››
ሲሉ
ይመልሳሉ ‹‹ድንግል የሰው ልጆች ሃሳብ ወደ እርስዋ ልብ
ስላልደረሰ
ይህንን አለች›› ማለት ነው፡፡ እመቤታችን ‹እርሱ ታላቅ
ይሆናል የልዑል
ልጅም ይባላል ፤ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን
ይሠጠዋል ፤
በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘላለሙ ይነግሣል ለመንግሥቱ ፍጻሜ
የለውም›› ብሎ ስለምትወልደው ልጅ እየነገራት እንኳን
‹ወንድ
ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል?› ብላ የምትጠይቅ የደናግል
መመኪያ
ናት፡፡ እግዚአብሔርም ነጻ ፈቃድዋን ሳይነካ ማኅተመ
ድንግልናዋን
ሳይለውጥ ከእርስዋ በኅቱም ድንግልና ተወለደ፡፡
21
በእስራኤል ብዙ ደናግል መሲሑን እንወልደዋለን ብለው
ድንግልናቸውን ጠብቀው የኖሩ አሉ፡፡ የቅዱስ ገብርኤል
ብሥራት
ከእነዚህ ደናግል ለአንዲቱ የተነገረ ቢሆን ኖሮ ‹ምኞቴ
ተፈጸመልኝ› ብላ
በተደሰተች ነበር፡፡ እመቤታችን ግን ራስዋን ለእግዚአብሔር
በንጽሕና
ስታቀርብ ለዚህ ክብር ራስዋን አስባ አታውቅም፡፡ ‹የባሪያዪቱን
ትሕትና
አይቶ› አምላክ ሲመርጣት እንዴት ይሆናል ያለችውም ለዚህ
ነበር፡፡
ቅዱስ ገብርኤል በእመቤታችን ፊት ቆሞ በጥያቄ ተያዘ፡፡
‹ቃሌን
ስላላመንህ ይህ ነገር እስከሚሆን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ› ብሎ
ከስድስት
ወራት በፊት የካህኑ ዘካርያስን አንደበት የዘጋው መልአክ
በአምላኩ እናት
ፊት ግን የተግሣጽን ቃል እንኳን አልተናገረም፡፡ ‹‹መንፈስ
ቅዱስ በአንቺ
ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ
ከአንቺ
የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል።›› ብሎ
ጽንሰቱም
ልደቱም በረቂቅ አምላካዊ ጥበብ በግብረ መንፈስ ቅዱስ
እንደሚፈጸም
ነገራት ፤ በዘር በሩካቤ የተፈጸመ በመሆኑ በቂ ማስረጃ
ባይሆንም
የኤልሳቤጥን ከእርጅና ወዲያ መጽነስ ነገራት፡፡ በመጨረሻም
‹‹ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም›› አላት፡፡ እመቤታችን
የማይናወጥ እምነት አላትና ለእግዚአብሔር የሚሣነው ነገር
የለም
ስትባል በእርሱ ክሂሎት ላይ አንድም ቃል አልተናገረችም፡፡
12 21 2
‹‹#እነሆኝ_የጌታ_ባሪያ_እን ደቃልህ_ይደረግልኝ››
°
‹እነሆኝ› የሚለው ንግግር ራስን የማቅረብ ንግግር ነው፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ በአብዛኛዎቹ ቦታዎች ይህ ቃል የተቀመጠው
የተጠሩ
ሎሌዎች በጌቶቻቸው ፊት ሲቀርቡ በሚሠጡት መልስ ላይ ፣
እግዚአብሔር በቀጥታ የጠራቸው እንደ ሳሙኤል ያሉ ነቢያትና
ቅዱሳን
ያቀረቡት ራሴን አቅርቤአለሁ የሚል የትሕትና ንግግር ነው፡፡
እመቤታችንም ራስዋን ለአምላክ ማደሪያነት ‹እነሆኝ› ብላ
አቀረበች፡፡
ሌላው አስደናቂ ነገር ደግሞ ‹የጌታ ባሪያ› ብላ ራስዋን
መጥራትዋ
ነው፡፡ ‹የአምላክ እናት› ትሆኚ ዘንድ ተመርጠሻል ተብላ እንኳን
በትሕትና
የምትናገረዋ ተራራ እመቤታችን ‹የጌታ ባሪያ› ብላ ራስዋን
ጠራች፡፡
እንደ ቃልህ ይደረግልኝ ስትል አምላክ በማኅጸንዋ አደረ፡፡
ምሥጢረ ተዋሕዶ ተከናወነ፡፡ የማይታየው ታየ ፤ የማይወሰነው
ተወሰነ፡፡
የአምላክ የማዳን ሥራ የእመቤታችንን የይሁንልኝ ንግግር
ተከትሎ
ተወጠነ፡፡ እመቤታችን ‹ይሁንልኝ› እስክትል ድረስ የተጀመረ
የማዳን
ሥራ አልነበረም፡፡ ሁሉ የሚቻለው አምላክ እንኳን የከበረ
መልአኩን ልኮ
‹ይሁንልኝ› ስትል ጠብቆ ነው ሥራውን የጀመረው፡፡
21
ምናልባት እዚህ ላይ አንድ ሰው ተነሥቶ የእመቤታችንን ድርሻ
አልታየኝም ሊል ይችላል፡፡ ሌላውን እንተወውና እመቤታችን
ይሁንልኝ
የሚለውን ቃል ሳትናገር ለጥቂት ደቂቃዎች ብትዘገይ እንኳን
የሰው ልጅ
መዳን የዚያኑ ያህል ይዘገይ ነበር፡፡ አንድ ቀን ሙሉ ዝም
ብትልም አንድ
ቀን ይዘገይ ነበር፡፡ ቅዱስ ገብርኤል እንደሆን ተልዕኮውን
ሳይፈጽም
አይሔድም ፤ በግድ እሺ ሊያሠኛትም አይችልም፡፡
እግዚአብሔር ነጻ
ፈቃድዋን ጠብቋል፡፡ እንኳን ከእርስዋ ሊወለድ ለመረጣት
ቅድስት ቀርቶ
ከሕመሙ ሊፈውሰው ያሰበውንም ድውይ ፈቃድ የሚጠይቅ
የነጻነት
አምላክ ነው፡፡ ስለዚህ የእመቤታችን ‹ይሁንልኝ› ማለት ለእኛ
ድኅነት
ወሳኝ ነበር፡፡ የእመቤታችን ንግግር በሲኦል ያሉ ነፍሳት ሳይቀር
‹እሺ
በይ› ብለው የሚጮኹበት የተስፋቸው መጀመሪያ ነው፡፡
እመቤታችንም
ሙሉ ፈቃደኛ ነበረች፡፡ ‹‹ይሁንልኝ›› እንጂ ‹‹ይሁንብኝ››
አላለችም፡፡
ይሁንልኝ የሚለው ቃል በሙሉ ደስታ መቀበልን ያሳያል፡፡
ንግግርዋ
‹መቼስ ከታዘዘብኝ› የሚል ዓይነት በቅሬታ መቀበል
አልነበረም፡፡ በሙሉ
ደስታ ‹‹ይሁንልኝ›› ብላ ተቀበለች እንጂ፡፡
21 2
#እመቤታችን_እና_ኤልሳቤ ጥ
‹‹ወደ ይሁዳ ከተማ ፈጥና ወጣች … ኤልሳቤጥንም
ተሳለመቻት››
°
እመቤታችን በብሥራተ መልአክ በፈቃደ አምላክ ጌታን
ከጸነሰች
በኋላ በቀጥታ በመልአኩ አንደበት መጽነስዋ ወደተነገረላት
ዘመድዋ
ወደ ኤልሳቤጥ ለጉዞ ተነሣች፡፡ ይህ ጉዞ ላይ ላዩን ስናየው
ከአንድ ቦታ
ወደ ሌላ ቦታ መሔድ ይምሰል እንጂ በውስጡ እጅግ ትልቅ
ትምህርት
አለው፡፡ ኤልሳቤጥን ለመጠየቅ መሔድዋ ፣ ፈጥና መሔድዋ
እመቤታችን እንደምን ያለ ትሕትና ቢኖራት ነው የሚያሰኝ እና
በትዕቢት
ለተሞላው ዓለም እጅግ ትሕትናን የሚያስተምር ነው፡፡
ሰማያዊ መልአክ መጥቶ አመስግኖ አምላክን እንደምትወልድ
ነግሯት ፣ ከሴቶች ሁሉ የተባረከች እንደሆነች በእግዚአብሔር
ፊትም
ጸጋን እንዳገኘች ነግሯት ፣ ከተነገራትም በላይ ደግሞ ሰማይን
ያለ ባላ
ምድርን ያለ ካስማ ያቆመን አምላክ በማኅጸንዋ ይዛ
እመቤታችን
ዘመድዋን ኤልሳቤጥን ልትጠይቅ ሔደች፡፡ ይህን ማን
ያደርገዋል?
21
ሰው ችግርን ማጣትን ረሃብ ወዘተ መቋቋም እየቻለ ክብርን
ግን መቋቋም አይችልም፡፡ ከፍ ከፍ ባለ ቁጥር ብዙ ሰው
በትዕቢት
ይፈተናል፡፡ ሥልጣን ሲሠጠው የብዙ ሰው መልካምነት
ይጠፋል፡፡
መንፈሳዊ ጸጋ ሲሠጠው ደግሞ የበለጠ ይፈተናል፡፡ በሥልጣን ፣
በዕውቀት ፣ በጸጋ ወዘተ ብዙዎች ማንነታቸውን አጥተዋል፡፡
እመቤታችን
ከፍጥረት ሁሉ በላይ ናት፡፡ ሰው ምንም ዓይነት የቅድስና ደረጃ
ላይ
ሊደርስ ይችላል ፤ ከእመቤታችን ክብር ግን ማንም
አይደርስም፡፡ ሰማዕት
መሆን ፣ ጻድቅ መሆን ይቻላል፡፡ የአምላክን እናት መሆን ግን
አይቻልም፡፡
(ንግሥት ዕሌኒ ‹የክርስቲያኖች እመቤት አንቺ ትሆኚ;› ብለው
ሲጠይቋት
‹‹የእግርዋን እጣቢ እንኳን አላህልም›› እንዳለችው ነው)
እመቤታችን
በሥልጣን ቢባል ከፍጥረት ሁሉ በላይ ናት እንኳን ስለ እርስዋ
ስለ ስሟ
እንኳን ‹‹ስምሽም በእግዚአብሔር ዘንድ የሠለጠነ ነው››
ብሏል ሊቁ፡፡
በዕውቀት ቢባል ብትናገረው ሰማይና ምድር የማይሸከሙት
እርስዋ ግን
በልብዋ የጠበቀችው ከሰው አእምሮ በላይ የሆነ የጥበብ
መዝገብ ናት
፤ እኛ ተምረን የማንጨርሰው ምሥጢረ ሥጋዌ የተፈጸመው
በእርስዋ
ሰውነት ነው፡፡ በጸጋም ለእርስዋ ያልተሠጣት ምንም የለም፡፡
ሆኖም
በትሕትና ዘመድዋን ልትጠይቅ ተነሣች፡፡ አካሔድዋም
የንግሥትነት
የኩራት አልነበረም፡፡ ይልቁንም ‹ፈጥና ወጣች› ነው
የሚለው፡፡ መቅደስ
ሆና ሳለ ፍጥረት ሊሳለማት የሚገባት ሆና ሳለ ‹‹ኤልሳቤጥን
ተሳለመቻት›› አምላክን በማኅጸንዋ ይዛ ፍጥረት የሚሳለማት
እመቤታችን በትሕትና ኤልሳቤጥን ተሳለመቻት፡፡
ሰዎች /እውነትነቱ ያልተረጋገጠ/ ራእይ አይተናል ፣
ተገልጦልናል ፣ እንፈውሳለን ወዘተ ብለው ራሳቸውን ክበው
በሚኖሩበት
፣ በሀብታቸው በዝናቸው በእውቀታቸው ምክንያት ጠባያቸው
በሚከፋበት
፣ ወዳጅነታቸው በሚለወጥበት ዓለም ላይ ሆነን እመቤታችንን
ስናስባት
ምን ይሰማን ይሆን?
21 21
#የጌታዬ_እናት_ወደ_እኔ_ ትመጣ_ዘንድ_እንዴት_ይሆ ንልኛል
?
°
ሕገ ኦሪት ሲሠራ እንደነበረችው የካህኑ አሮን ሚስት ኤልሳቤጥ
ሁሉ ሕገ ወንጌል ስትሠራ ለመመስከር የታደለችው ሁለተኛዋ
ኤልሳቤጥ
ወደ እርስዋ የመጣችውን የዐሥራ አምስት ዓመት ብላቴና
እናትዋ
ልትሆን የምትጅልበት እድሜ ላይ ብትሆንም እንደ ታናሽ ልጅ
አልተቀበለቻትም፡፡ እመቤታችን በትሕትና ብትሳለማትም
ዝም ብላ
አልተመለከተቻትም፡፡ ገና የእመቤታችንን ሰላምታ በሰማች
ጊዜ መንፈስ
ቅዱስ ሞላባት፡፡ የእመቤታችን ሰላምታ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ
እምዲመላብን ያደርጋልና ኤልሳቤጥን መንፈስ ቅዱስ
አናገራት፡፡
በታላቅ ድምፅም ጮኻ እንዲህ አለች። ‹‹አንቺ ከሴቶች
መካከል የተባረክሽ ነሽ፥ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው።
የጌታዬ እናት
ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል? እነሆ፥ የሰላምታሽ
ድምጽ
በጆሮዬ በመጣ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና። ከጌታ፤
የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብፅዕት ናት።››
የዕድሜ ባለጸጋዋ ኤልሳቤጥ ኃይል አግኝታ ታላቅ ድምፅ
አሰማች፡፡ ኤልሳቤጥ ውዳሴ ማርያም ነው የጮኸችው፡፡
መንፈስ ቅዱስ
የሞላበት ሰው ንግግሩ እመቤታችንን ከነልጅዋ ምስጋና
ማቅረብ ነው፡፡
ኤልሳቤጥ ‹አንቺ የተባረክሽ ነሽ የማኅጸንሽም ፍሬ የተባረከ
ነው› ብላ
ጌታን ከእናቱ ጋር እንዳመሰገነች እኛም አባታችን ሆይ ብለን
እመቤታችን
ሆይን እናስከትላለን፡፡ ቅዱስ ገብርኤል ‹አንቺ ሴቶች ተለይተሸ
የተባረክሽ
ነሽ› ሲል ኤልሳቤጥ ‹የማኅጸንሽም ፍሬ ቡሩክ ነው› ብላ
እንደጨመረችበት እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ እየተቀባበልን
እናመሰግናታለን፡፡
ኤልሳቤጥ እመቤታችንን ‹የጌታዬ እናት› አለቻት ወላዲተ
አምላክ ፣ እመ አምላክ ፣ እመ ብርሃን የምንለው እንግዲህ
ከዚያ
ወዲህ ነው፡፡ የካህን ሚስት ናትና መቅደስ እመቤታችንን
እንደምን
መጥራት እንዲገባን አስተማረችን፡፡ አስከትላም አንዳች
አስደናቂ
ምስክርነት ሠጠች፡፡ ‹የሰላምታሽ ድምፅ በጆሮዬ በመጣ ጊዜ
ጽንሱ
በማኅጸኔ በደስታ ዘሎአል› አለች፡፡
መቼም ሳይንስ አዋቂ እንደሚረዳው ያም ባይሆን እናቶቻችን
እንደሚያውቁት የስድስት ወር ጽንስ በማኅጸን ሳለ መዝለሉ
የተለመደ
ተፈጥአዊ ክስተት ነው፡፡ እርግጥ አንድ ክስተት ሲደጋገም ድንቅ
መሆኑ
ስለሚቀር ነው እንጂ እንኳን የጽንስ መዝለል የጽንስ መፈጠር
ራሱ እጅግ
አስደናቂ ነበር፡፡ ግን አንዱ ተነሥቶ ‹‹ማንኛዋም ተራ ሴት
ልታውቀው
የምትችለውን ነገር ለምንድን ነው ተአምር አድርጋችሁ
የምታወሩት?››
ሊለን ይችላል፡፡ አዎ ማንኛዋም ጻድቅት ያልሆነች ወይም
እንደ
ኤልሳቤጥ መንፈስ ቅዱስ ያልሞላባት ሴት ጽንስ በማኅጸንዋ
መዝለሉን
ልታውቅ ትችላለች፡፡ ማንኛዋም ሴት ግን ጽንሱ በማኅጸንዋ
የዘለለው
በደስታ ይሁን በኀዘን ልታውቅ አትችልም፡፡ ልብ አድርጉ
ኤልሳቤጥ
ያለችው ‹‹ጽንሱ በማኅጸኔ ዘለለ›› ሳይሆን ‹‹ጽንሱ በማኅጸኔ
በደስታ
ዘለለ›› ነው፡፡
21
እኛ ኢትዮጵያውያን ምዕመናን መቼም ‹ማርያም ማርያም›
ተብለን ተወልደን ፣ ‹እንኳን ማርያም ማረችሽ› ‹ማርያም
ታኑርህ/ሽ›
ተባብለን ነው የኖርነው፡፡ በብዙ ሆስፒታሎች የማዋለጃ ክፍል
ውስጥ
የእመቤታችንን ሥዕል ማኖር የተለመደ ነው፡፡ አንዳንዶች
ታዲያ ‹ድንግል
ማርያምን ከጽንስ ጋር ምን ያገናኛታል?› ብለው ይንገሸገሻሉ፡፡
መጽሐፍ
ቅዱስን የሚያውቅ ሰው እንዴት ይኼን የሚያስገምተውን
ጥያቄ
ይጠይቃል? በመጽሐፍ ቅዱስ ባሕር ሲዋኙ ለኖሩና ባሕላችንን
በመጽሐፍ ቅዱስ ቃኝተው ላስረከቡን አበው ሊቃውንት ምስጋና
ይሁንና
ጽንስና እመቤታችንን ምን ያገናኛቸዋል የሚለውን ጥያቄ
እንግዲህ
‹የሰላምታሽ ድምፅ በጆሮዬ በመጣ ጊዜ ጽንሱ በማኅጸኔ
በደስታ
ዘሎአል› ያለችውን ኤልሳቤጥን መጠየቅ ነው፡፡ እኛ
የእመቤታችንን
ድምጽ ለጸነሱ ሴቶች ማሰማት ባንችል ስሟን እንዲሠሙ
ብናደርግ ማን
ይከለክለናል?
ቅዱስ ዮሐንስ ገና በእናቱ ማኅጸን ሳለ የእመቤታችንን ድምፅ
ሰምቶ
ዘለለ፡፡ ሐዋርያት በሲኖዶስ ፣ ቅዱስ ያሬድም እንዲሁ ሰገደ
ብለው
ተርጉመወታል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ተፈጥሮ ገድቦት ነው እንጂ
ከእናቱ
ማኅጸን ወጥቶ ቢሆን ኖሮ ‹የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጪ
ዘንድ እንዴት
ይሆንልኛል?›› ይል እንደነበር ጥርጥር የለውም፡፡ ይህን
እንዴት
አወቃችሁ ብንባል የመጥምቁን ጠባይ መች አጣነውና ጌታ
ሊጠመቅ
ወደ እርሱ ሲሔድ ‹‹እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል አንተም
ወደ እኔ
ትመጣለህን?›› ብሎ ሲናገር አየነው አይደል? በእናቱ ወጥቶ
ይሆን?
ለነገሩ የወጣው እንኳን በሁለቱም ነው፡፡ እናቱ ‹‹አንቺ ከሴቶች
ተለይተሸ
የተባረክሽ ነሽ የማኅጸንሽ ፍሬ ቡሩክ ነው›› ስትል ሰማን ፣
አባቱ ደግሞ
አንደበቱ ሲከፈትለት ‹‹የእስራኤል ጌታ አምላክ ይባረክ›› አለ
(ሉቃ.
፩፥፰፰) በወላጆቹ የወጣው ዮሐንስም አምላኩን ሲያጠምቅ
‹የቡሩክ
ልጅ ብርሃንን የምትገልጥ ይቅር በለን…› ብሎ አጠመቀው፡፡
የተባረከ
ቤተሰብ!
ከዚህ በኋላ እመቤታችን ‹ነፍሴ እግዚአብሔርን ታላቅ
ታደርገዋለች› የሚለውን ጸሎት ተናገረች፡፡ ይህ የእመቤታችን
ጸሎት ሰፊ
ምሥጢር ያለው ነው፡፡ ሁለት ነገሮች ብቻ ግን እናነሣለን፡፡
የመጀመሪያው አስደናቂ ነገር ለነቅዱስ ኤፍሬም ለነአባ
ሕርያቆስ
ምሥጢር ገልጣ ‹የጸጋህን ማዕበል ያዝ› እስኪሉ ድረስ እንግዳ
ድርሰት
እንዲደርሱ ያደረገች እመቤታችን ራስዋ በጸለየችው ጸሎት ግን
አብዛኛው ክፍል የአባቶቿ ነቢያት ጸሎት መሆኑ የእመቤታችንን
ትሕትና
ሲያስደንቀን ይኖራል፡፡
ሁለተኛው ነገር ‹ከእንግዲህስ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል
እርሱ ታላቅ ሥራን ለእኔ አድርጓልና› ያለችው ነው፡፡
እመቤታችን ሥጋዊ
የመመስገን ፍላጎት ኖሯት ‹ብፅዕት ይበሉኝ› የሚል ትእዛዝ
አልሠጠችም፡፡ የተናገረችው ትንቢት ነው እንጂ፡፡ ‹‹ትንቢት
ከቶ በሰው
ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን
ሰዎች
በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።›› ይላል መጽሐፉ (፪ጴጥ.
፩፥፳፩)
እመቤታችንን ማመስገን ሰዎች ሊያስቆሙት የማይችሉት
ከመላእክት
የተቀበልነው ፣ ከኤልሳቤጥ የተማርነው በትንቢት የጸና አደራ
መሆኑን
እናስታውሳለን፡፡
21 21 21
#እመቤታችን_ለምን_አልመጣ ችም?
°
በሉቃስ ወንጌል የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እና በሌሎቹም
ወንጌላት ጌታችን በመቃብር ባደረ ጊዜ የነበረውን ሁኔታ
እናነባለን፡፡
በተለይም በተነሣበት ሌሊት ሴቶች ሽቱ ይዘው ሥጋውን ሊቀቡ
መጥተው
ነበር፡፡ ሆኖም መቃብሩ ባዶ ሆኖ አገኙት ፤ በመላእክትም
አንደበት ስለ
ጌታችን ትንሣኤ ተነገራቸው፡፡ ለሐዋርያትም ተናገሩ፡፡ ይህ ሁሉ
ሆኖ ግን
ቅዠት መስሎ የታያቸው ይበዙ ነበር፡፡
ጌታችን በመስቀል መከራ ተቀብሎ በሞተ ጊዜ ልብዋ በኀዘን
የቆሰለው እመቤታችን ነበረች፡፡ ምንም እንኳን የመሰቀሉን
ዓላማ
ብታውቅም የተቀበለው ለኅሊና የሚከብድ መከራ ግን እንኳን
አቅፋ
ያሳደገችውን ቅድስት እናቱን ለሚሰማው ሁሉ የሚያስለቅስ
ነበር፡፡
እመቤታችን እስከመጨረሻው ድረስ በመከራው አብራው
ነበረች፡፡ እንደ
ቅዱስ ጴጥሮስ ‹አይሁንብህ!› ብላ ከማዳን ሥራው ወደ ኋላ
ያልጎተተችው የፍቅርዋ ጽናት ጎድሎ አይደለም፡፡ ያለ እሱ ሞት
የዓለም
ድኅነት እንደማይሆን ተረድታ እንጂ፡፡
21
በመከራው ያልተለየችው ፣ በመስቀሉ ሥር ከነበሩት ቅዱሳት
አንስት ዝርዝር ውስጥ በቀዳሚነት የተጠቀሰችው እመቤታችን
እሑድ
ደርሶ ሴቶች ወደ መቃብሩ ሽቱ ይዘው ማልደው ሲሔዱ ግን
ከእነርሱ
ጋር አልነበረችም፡፡ ለምን? ከእርስዋ በላይ የልጅዋ ሥጋ ሽቱ
እንዲቀባ
ማን ሊያስብ ይገባል? እንደምንስ አስቻላት? ነገሩ ወዲህ ነው!
እመቤታችን ልጅዋ ሞትን ድል አድርጎ እንደሚነሣ ታውቅና
ታምን ነበር፡፡
ስለዚህ ሕያዉን ከሙታን መካከል ልትፈልግ አልተነሣችም፡፡
አባቷ
አብርሃም ልጁን ይስሐቅ እንዲሞት ሲፈቅድ እግዚአብሔር
ልጄን ከሞት
ያስነሣልኛል ብሎ እንዳመነ እመቤታችንም የተወደደ ልጅዋን
እግዚአብሔርነቱ ‹ከሙታን እንኳን ሊያስነሣው እንዲቻለው
አስባለች፡፡› (ዕብ. ፲፩፥፲፱)
21
ምንጭ:-
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ነሐሴ 2005
የዚህን ጽሑፍ የትግርኛ ትርጉም ማንበብ ለምትችሉ ወይም
የምትፈልጉ https:// www.facebook.com /
photo.php?
fbid=8933399507 28526&set=a.363
600530369140.84 551.10000157588
2711&type=1&pnr ef=story
21
የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የድንግል ማርያም አማላጅነት፣
የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣
የቅዱሳን ሐዋርያት፣ የቅዱሳን አበው መነኮሳት፣ የቅዱሳት
አንስት፣ የደናግላንና የቅዱሳን ሁሉ ምልጃና ቃል-ኪዳናቸው
ባለንበት ከሁላችን ጋር ይሁን!!!
†† † † ††
ለአባ ሕርያቆስ ፤
ለቅዱስ ኤፍሬም ፤
ለቅዱስ ያሬድ ፤
ለአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
የተገለጸች እመቤታችን እኛንም በበረከት እና በረድኤት
ትጎብኘን ፤ ከልጅዋ ከወዳጅዋ ከመድኃኔዓለም ዘንድ ታማልደን
፤ አሜን!!!
†† † † ††
ከዋክብት የሚያመሰግኑት
በስማቸውም የሚጠራቸው:
የፀጋው ብዛት የማይታወቅ
ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ
ለሐዋሪያት እንዲሁም ለቀደሙ አባቶቻችን ምሥጢሩን
እንደገለጽክላቸው ለእኛም ግለጽልን። አሜን አሜን አሜን!!!
†† † † ††
ወ ስ ብ ሐ ት ለ እ ግ ዚ አ ብ ሔ ር
ወ ለ ወ ላ ዲ ቱ ድ ን ግ ል
ወ ለ መ ስ ቀ ሉ ክ ቡ ር