ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

Tuesday, September 6, 2016

=>+*"+<+>††† ዻጉሜን-1 +" ወርኀ ዻጉሜን "+ †††<+>+"*

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ዻጉሜን-1
+" ወርኀ ዻጉሜን "+
=>#እግዚአብሔር አዝማናትን የፈጠራቸው ለሰው ልጆች
ጥቅም መሆኑ ይታወቃል:: እርሱ ባወቀ: በረቂቅ ሥልጣኑ
ዓለምን ፈጥሮ: ጊዜያትን እንዲከፍሉ ብርሃናትን (ፀሐይ:
ጨረቃ: ከዋክብትን) ፈጥሮልናል::
+ጊዜያትንም በደቂቃ: በሰዓት: በቀን: በሳምንት: በወር:
በዓመታት: በኢዮቤልዩ: በክፍላተ ዘመናት እንድንቆጥር
ያስማረንም እርሱ ነው:: የሰከንድ 540,000 ክፋይ
ከሆነችው 'ሳድሲት' እስከ ትልቁ ቀመር (532 ዓመት) ድረስ
እርሱ ለወደዳቸው እንዲያስተውሉት ገልጧል::
+በየዘመኑም በቅዱስ #ድሜጥሮስ: በቅዱስ #ዮሐንስ
ዘደማስቆ: በቅዱስ #አቡሻኽር እና በሌሎቹም አድሮ
መልካሙን አቆጣጠር አስተምሯል:: ሃገራችን ኢትዮዽያ
ደግሞ የ13 ወራት የፀሐይ ጸጋ (thirteen months sun
shine) ያላት: 4ቱ ወቅቶች የተስማሙላት ናት::
+ሌላው ዓለም ወሮችን 31,30,29 እያደረገ ሲጠቀም እኛ
ግን እንደ ኖኅ (ዘፍ) አቆጣጠር ወሮችን በ30 ቀናት ወስነን:
ዻጉሜንን ለብቻዋ እናስቀምጣለን:: ዻጉሜን 'ኤዻጉሚኖስ'
ከሚል የግሪክ (ጽርዕ) ቃል የተወሰደ ሲሆን ትርጉሙም
'ትርፍ: ጭማሪ' እንደ ማለት ነው::
+የወርኀ ዻጉሜን 5ቱ (6ቱ) ቀናትም ወደ አዲስ ዓመት
መሸጋገሪያ እንደ መሆናቸው ብዙ ምሳሌያት (ምሥጢራት)
አሏቸው:: ዋናው ግን በዚህ ጊዜ ዳግም ምጽዓት ይታሠባል::
ጊዜውንም በጾምና በጸሎት ሊያሳልፉት ይገባል:: ግን በፈቃድ
ነው እንጂ የግዴታ አይደለም::
+" ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ "+
*የቅዱሳኑ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ልጅ
*በማሕጸን ሳለ መንፈስ ቅዱስ የሞላበት
*በበርኀ ያደገና በገዳማዊ ቅድስና ያጌጠ
*እሥራኤልን ለንስሃ ያጠመቀ
*የጌታችንን መንገድ የጠረገ
*ጌታውን ያጠመቀና
*ስለ እውነት አንገቱን የተቆረጠ ታላቅ ሰው ነው::
*ስለዚሕም ቤተ ክርስቲያን ነቢይ: ሐዋርያ: ሰማዕት: ጻድቅ:
ገዳማዊ: መጥምቀ መለኮት: ጸያሔ ፍኖት: ቃለ ዐዋዲ ብላ
ታከብረዋለች::
+ቅዱሱ በዚህች ዕለት ወደ እሥር ቤት ገብቷል:: ይሕስ እንደ
ምን ነው ቢሉ:-
ንጉሡ ሔሮድስ የወንድሙን የፊልዾስን ሚስት ሔሮድያዳን
በማግባቱና በመሰል ክፋቶቹ ቅዱስ ዮሐንስ ይገስጸው ነበር::
ቅዱስ ዮሐንስ "መምሕር ወመገስጽ: ዘኢያደሉ ለገጽ - ፊት
አይቶ የማያዳላ" ነውና ገሰጸው::
+ሔሮድስ ቅዱሱን ይፈራው: ያከብረውም ነበር:: በኋላ ግን
ፈቃደ ሥጋው ስላየለበት: በተለይ ደግሞ ከ7 ቀናት በሁዋላ
ልደቱን ሲያከብር እንዳይረብሸው በመስጋት በዚህች ቀን
በወታደሮቹ አስይዞ እሥር ቤት ውስጥ ጥሎታል:: ለ7 ቀናት
በጨለማ ውስጥ አሥሮ መስከረም 2 ቀን አንገቱን እንዴት
እንዳስቆረጠው ዕለቱን ጠብቀን እንመለከታለንና የዚያ ሰው
ይበለን::
+" ቅዱስ ዑቲኮስ ሐዋርያ "+
=>ቅዱሱ ሐዋርያ ጭራሽ ከነ ስማቸው እንኩዋ እየተዘነጉ
ከሔዱ ሐዋርያት አንዱ ሲሆን ቁጥሩም ከ72ቱ አርድእት
ነው:: በወጣትነት ዘመኑ የጌታችን ደቀ መዝሙር መሆንን
መርጦ ለ3 ዓመታት ከ3 ወራት ምሥጢረ ወንጌልን ጠንቅቆ
ተምሯል::
+መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜም እንደ መጠኑ ተቀብሎ
ለአገልግሎት ወጥቷል:: በመጀመሪያ የወንጌላዊው ዮሐንስ
ተከታይ ሁኖ ብዙ ምሥጢራትን ተካፍሏል:: ቀጥሎም ቅዱስ
ዻውሎስን ተከትሎ ብዙ አሕጉራትን በስብከተ ወንጌል
አዳርሷል::
+በመጨረሻም በእስያ አካባቢ ለብቻው ተጉዞ: ብዙ ነፍሳትን
ማርኮ: ጣዖታትን አጥፍቷል:: ስለዚህ ፈንታም በእሳት:
በስለትና በግርፋት ብዙ መከራዎችን አሳልፏል:: በዚህች
ቀንም በበጐው እርግና (ሽምግልና) ዐርፏል::
+" ቅዱስ ብሶይ ቀሲስ "+
=>በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ካህናት አንዱ የነበረው አባ ብሶይ
ለአገልግሎት ወጥቶ ሲመለስ የቤተሰቦቹ ቤት ሰው
አልነበረበትም:: "የት ሔዱ?" ብሎ ቢጠይቅ "ወንድምህ አባ
ሖርና እናትህ ቅድስት ይድራ ወደ እስክንድርያ ሔደዋል::
በዚያም ስለ ክርስቶስ ፍቅር ተሰውተዋል" አሉት::
+በማግስቱ የኔ ብጤዎችን ጠርቶ ሃብቱን: ንብረቱን: ቤቱን
አካፈላቸው:: ለራሱ ግን አንዲት በትር እና 3 የዳቦ ቁራሾች
ይዞ ጉዞ ተነሳ:: ወደ እስክንድርያ እንደ ደረሰ አፈላልጐ
የቤተሰቦቹን መቃብር አገኘ:: ከፊታቸው ወድቆም የናፍቆት
ለቅሶን አለቀሰ::
+ወዲያውም እንዲህ አላቸው:- "ፈጥኜ ወደ እናንተ
ስለምመጣ ጠብቁኝ:: ደግሞም ጸልዩልኝ::" ከዚያ ተነስቶ
በመኮንኑ ፊት ስለ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት መሰከረ::
በዚህ ምክንያት ብዙ ተሰቃይቶ በዚህች ቀን ሰማዕት ሆኗል::
ከወገኖቹም ጋር ተቀብሯል::
=>አምላከ ቅዱሳን ተረፈ ዘመኑን ባርኮ ለአዲሱ ዘመን በቸር
ያድርሰን:: ከወዳጆቹም ጸጋ በረከትን ይክፈለን::
=>ዻጉሜን 1 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ (የታሠረበት)
2.ቅዱስ ዑቲኮስ ሐዋርያ (ከ72ቱ አርድእት)
3.ቅዱስ ብሶይ ቀሲስ (ሰማዕት)
4.አባ ዻኩሚስ / ባኹም (የ3,000 ቅዱሳን አባት)
5.አባ ሰራብዮን / ሰራፕዮን (የ10,000 ቅዱሳን አባት)
=>+"+ ጌታ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ሊናገር ጀመረ. . .
ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችሁአለሁ ከነቢይም
የሚበልጠውን. . . እውነት እላቹሃለሁ ከሴቶች ከተወለዱት
መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሳም. . .
ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናገሩ::
ልትቀበሉትስ ብትወዱ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይሕ ነው::
የሚሰማ ጀሮ ያለው ይስማ:: +"+ (ማቴ. 11:7-15)
<ወስብሐት ለእግዚአብሔር>

=>+*"+<+>††† ጳጉሜ †††<+>+"*

ጳጉሜን
በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከነሐሴ በኋላ ጳጉሜን የምትባል
አምስት ቀን አለች፡፡ ወር እንዳትባል አቅም ያንሳታል፡፡
ሳምንት እንዳትባል አምስት ቀን ብቻ ኾናለች፡፡ ጳጉሜን
የሚለው ስያሜዋ ግን “ኤፓጉሜኔ” ከሚለው የግሪክ ቃል
የመጣ መኾኑ በአበው ቃል ተነግሯል፡፡
“ኤፓጉሜኔ” ማለት ጭማሪ ማለት ነው ፡፡ በግእዝ
ቋንቋችን ተውሳክ ማለት ነው፡፡ ተውሳክ ማለት ተጨማሪ
ማለት ነው፡፡ “ወሰከ - ጨመረ” ከሚለው የግእዝ ግስ
የተገኘ ነው፡፡ ኤውሮፓዎች ጳጉሜን የወር ተጨማሪ
አድርገዋታል፡፡ ይኸውም ይታወቅ ዘንድ እኛ የወርን ቁጠር
ሠላሳ ስናደርግ እነርሱ ሠላሳ አንድ ብለው የሚቆጥሩት ወር
አላቸው፡፡ ይኹን እንጂ የኢትዮጵያ ሊቃውንት ጳጉሜን የወር
ተጨማሪ ሳያደርጉ የዓመት ተጨማሪ አድርገዋታል፡፡
የዓመቱንም ቀን ቁጥር ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ቀን ከነሱ
ብለው ደምረውታል፡፡
በቅድስት ቤተክርስቲያን ካሉት ሁለት የፈቃድ አጽዋማት
መካከል አንዱ በዚህ በጳጉሜ ወር የምንጾመው የፈቃድ ጾም
ነው፡፡ ይህም ጾመ ዮዲት በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ ግን እንደ
አንደኛው የፈቃድ ጾም /ጽጌ ጾም/ በብዙዋኑ ዘንድ የታወቀ
አይደለም፡፡ የዮዲት ጾም የሚባለውም እርሷ ስለ ጾመችው
ነው፡፡ እዚህ ላይ ዮዲት ተብላ የተጠቀሰችው በቤተክርስቲያን
ታሪክ ትምህርት ላይ በጥፋት ሥራዋ በተደጋጋሚ
የምትጠቀሰው ዮዲት ጉዲት እንዳልሆነች ለማሳወቅ
እንወዳለን፡፡ ወደ ታሪኩ ስንመለስ የፋርስ ንጉስ ናቡከደነጾር
በሠራዊቱ ተመክቶ ሹም ጠላት አጥፋ ድንበር አስፋ ካመነው
እጅ መንሻ እየተቀበልህ ያላመነውን እያሳመንህ ና ብሎ ለጦር
አበጋዙ ለሆሎፎርኒስ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ ዮዲ 2፡-2-7፡፡ እርሱም
እንደታዘዘው በኃይላቸው የታመኑ 12ሺህ እግረኞችንና በፈረስ
የተቀመጡ 12ሺህ ጦረኞችን እየመራ ዘምቶ ካመነው እጅ
መንሻ እየተቀበለ ያላመነውን እያሳመነ ብዙ ሀገሮችን እያጠፋ
ሲሔድ ከአይሁድ ከተማ ደረሰ በዚህም ብዙ ጥፋ በመድረሱ
የእስራኤል ልጆች አለቀሱ፡፡
ዮዲት ባሏ ሞቶባት ከወንድ ርቃ ንጽሕናዋን ጠብቃ በጾም
በቀኖና በሀዘን ተወስና ትኖራለች በተፈጠረው ጥፋት ህዝቡ
ላይ ለመጣው መከራ ማቅ ለብሳ በራስዋ ላይ ትብያ ነስንሳ
ወደ እግዚአብሔር አለቀሰች፡፡ የፍጥረቱን ጥፋት የማይሻ
እግዚአብሔር አምላክም ሕዝቡን የሚያድኑበትን መንገድ
ለመጠየቅ ሱባኤ በገባች በሦስተኛው ቀን ገለፀላት፡፡ ዮዲ
8፡-2 ፡፡ ከዚህ በኋላ ጠላታቸውን በዮዲት ምክንያት
እስራኤላውያን እስከ ዮርዳኖስ እየተከተሉ አጥፍተዋቸዋል፡፡
ዮዲት ጠላቷን ለማጥፋት የቻለችው በጾምና በጸሎት
ከእግዚአብሔር አምላክ ኃይል አግኝታ ነው፡፡ ስለዚህ
ምዕመናን ጥንተ ጠላታችን ሰይጣንን ፈቃደ ሥጋን ለማሸነፍ
በጾም ከፈጣሪያችን ኃይልን መጎናጸፍ አለብን ብለው ጳጉሜን
በፈቃድ ይጾማሉ፡፡
የጳጉሜ ወር ዕለተ ምጽአት የሚታሰብበትም ወር ነው፡፡
ይህም ጳጉሜ የዓመታት መሸጋገሪያ ጨለማው የክረምት
ወቅት ወደ ማብቂያው የምናልፍባት እንደሆነች ሁሉ
ምጽአትም ከጊዜያዊው ወደ ዘላለማዊ ከምድራዊ ወደ
ሰማያዊ ከዚህ ዓለም ወደ ወዲያኛው መሸጋገሪያ ነውና ነው፡፡
ሊቃውንቱ እንደ ሱባኤ ቀን ቀኖና እንዲፈጽምባት ለብቻ
ለይተው አኑረውታል፡፡ “ይህ ዓለም ኑሮ፣ ኑሮ በመጨረሻ
ያልፋል፡፡ ጌታ ዓለምን ለማሳለፍ ይመጣል” ሲሉ የገታ
የመምጣቱ ነገር እንዲነገርባት፣ መሥዋዕት እንዲሠዋባት፣
ጾም እንዲያዝባት፣ ምጽዋት እንዲመጸወትባት ለይተው
መድበዋታል፡፡
ሕዝቡ ሳይቀር “ጳጉሜን ዕድሜ ትሰጠናለች፤ በኋላም
ታድነናለች” ብለው ጾም ይጾሙባታል፡፡ የዚሁም ማስረጃ
በቅዱስ መልከ ጸዴቅ ድርሳን ይገኛል፡፡ ንግሥት ዘውዲቱ
ምኒልክ የጾም ሥርዐት ይፈጽሙባት ነበር፡፡ ሌሎችም
ሽማግሌዎችና ባልቴቶች አክብረው ይጾሙባታል፡፡ ኾኖም
የጳጉሜን አቆጣጠር አንዱ ከወር ጋራ፣ ሌላውም ከዓመት
ጋራ ቢያደርገውም በሀሉም አቆጣጠር ውስጥ ሕያዊት ኾና
መገኘቷ የታወቀ ነው፡፡
የነቢዩ ኄኖክ መጽሐፍም ጳጉሜን ጨርሶ አልዘነጋትም፡፡
ክርስቲያኖች ሁሉ በየዓመቱ በጳጉሜ ወር ሁሉም ተሰብስበው
ከሌሊት ጀምረው በቤተክርስቲያን ተገኝተው ጸበል
ይጠመቃሉ፡፡ ይህንን የምናደገውም እግዚአብሔር የተባረከ
ዓመት እንዲሰጠን፣ ባሳለፍነው ዓመት የሰራነውን ኃጢአት
ይቅር እንዲለን ነው፡፡ የምንጠመቀውም ንስሐ ገብተን
ነው፡፡ በእግዚአብሔር ስም የተቀደሰው ጸበል ደግሞ
ከበሽታችን ያድነናል፣ የተቀደስንም ያደርገናል፣ መጪውንም
ህይወታችን የተባረከ ያደርግልናል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
መልካም የአዲስ ዓመት ዋዜማ (ጷጉሜ) ይሁንላችሁ፡፡
ተዋሕዶ ሀይማኖታችን ለዘለአለም አለም ፀንታ ትኑርልን!!!
ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተክርስትያን!!!

=>+*"+<+>††† ጾመ ዮዲት - ጾመ ጳጉሜም †††<+>+"*

<< ጾመ ዮዲት - ጾመ ጳጉሜም >>
በቤተክርስቲያናችን የፈቃድ ጾም ተብለው የሚታወቁት ጾመ
ጽጌ እና ጾመ ዮዲት ናቸው። የዮዲት ጾም የሚባለውም እርሷ
ስለ ጾመችው ነው፡፡ ለፋርስ ንጉሥ ለናቡከደነፆር የጦር አበጋዝ
የነበረው ሆሎፎርኒስ ፈቃድ ተሰጥቶት እስራኤልን ለመውረር
ሲመጣ በሠራዊቱ (ዮዲ2፣2-7) የእሥራኤል ልጆችም
ሆሎፎርኒስ የአሕዛብን አገር እንዳጠፋና ንብረታቸውን
እንደዘረፈ ሰምተው ስለ ቤተ መቅደሱ መፍረስና ሰለ ንዋያተ
ቅድሳት መርከሰ ማቅ ለብሰው አመድ ነስንሰው ከቤተ
መቅደሱ በር ወድቀው አለቀሱ።(ዮዲ4፡2-15)
ሆሎፎርኒስ ግን የሚጠጡትን ምንጫቸውን በመያዙ ፣
የእሥራኤል ልጆች በውኃ ጥም ከመቸገርና ከመሞት ይልቅ
እጃቸውን ለጠላት ለመስጠት ወሰኑ፡፡ ነገር ግን ዖዝያን
የአባቶቻቸው አምላክ መልስ እስኪሰጣቸውና ቸርነቱን
እስኪመልስላቸው መከራውን በትዕግሥት እንዲቀበሉ
ስለመከራቸው ጸኑ፡፡ዮዲ7 ፣10-32)
፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
በዚያም ባሏ ምናሴ የሞቶባት፣ ከወንድ ርቃ ንጽሕናዋን
ጠብቃ በጾም፣ በቀኖና፣ በትኅርምት፣ በኀዘን፣ በጸሎት ተወስና
የምትኖር የሜራሪ ልጅ ዮዲት ማቅ ለብሳ በራስዋ ላይ ትቢያ
ነስንሳ፣ ሱባዔ ገባች! አምላክም ሕዝቡን የሚያድንበትን
ዕውቀትና ጥበብ ግብር በገባች በሦስተኛ ቀን ገለጸላት፡፡
(ዮዲ8፡2) ከዚያም “ወዴት ትሔጃለሽ አትበሉኝ አምላክ
እሥራኤል ይከተልሽ ብሉኝ” ብላ የኀዘን ልብሷን ጣለች፡፡
ሰውነቷን ታጠበችና ሽቱ ተቀባች፣ ባሏ በሕይወት ሳለ
የምትለብሰውን የክት ልብሷን ለበሰች፣ የጠላት ሰዎች ሁሉ
እስኪወዷት ድረስ ፈጽማ አጊጣ ሄደች፡፡(ዮዲ.10፡2-3 )
እነርሱም ለእኔ ትገባለች ለእኔ ትገባለች እያሉ ተሻሙባት፡፡
የንጉሥ ጃንደረባ ጋይ የሚባል ይህችስ ለጌታዬ ትገባለች አለ፣
ለምን እንደመጣች ጠይቀዋት ለመልካም ነገር እንደመጣች
ሲረዱ ከጦር አበጋዙ አደረሷት፡፡(ዮዲ10፡12 -22)
፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
በአንዲትም ዕለት ሆሎፎርኒስ የአሽከሮች የምሣ ግብዣ
አድርጎ ሲያበላ ሲያጠጣ ያችን እብራዊት ጥሩ ብሎ አስጠርቶ
ከፊቱ አስቀምጦ ሲበላ አብዝቶ ሲጠጣ ውሎ ሰከረ፡፡(ዮዲ12፡
1-20 ) ከዚያም አሽከሮችን ከሁሉ አስወጥቶ ድንኳኑን
ቆልፎ እንደተኛ ከባድ እንቅልፍ ያዘው ዮዲትም ከፀለየች
በኋላ ከራስጌው ያለውን ሰይፍ አንስታ የራስ ጠጉሩን ይዛ
አንገቱን ቆርጣ በድኑን ከመሬት ጥላ ቸብቸቦውን በአቁማዳ
ቋጥራ ለብላቴናዋ አሸክማ ግንዱን በታች ገልብጣ ዙፋኑን
በላይ አድርጋ ወደ ሃገሯ ተመለሰች፡፡ (ዮዲ13፡1-10) ሕዝበ
እሥራኤል በዚህ ድርጊቷ እጅግ ተደነቁ፣ ጠላታቸውን
በእጃቸው የጣለላቸውን አግዚአብሔር አምላካቸውንም
አመሰገኑ፡፡ በኋላም የሆሎፎርኒስን ራስ በተራራው ላይ
ሰቅለው መዋጋት ጀመሩ፡፡ እስከዮርዳኖስም እየተከተሉ
አጥፍተዋቸዋል፡፡ ቅድስት ቤ.ክንም እግዚአብሔር የዮዲት
ጾም ተቀብሎ ከጠላት እጅ እንዳዳናቸው፣ ለእኛም ከሰይጻም
ወጥመድ እናመልስ ዘንድ ይህንን ጾም እንጾመው
ታበረታታለች ( የፈቃድ ጾም ነውና)። ለእኛም ለሃገራችን
ፍቅር ሰላምና አንድነትን፣ የመከፋፈልን አዚም
የምንቆርጥበት ጾም ያድርግልን!

=>+*"+<+>††† ጳጉሜ፦3 ቅዱስ ሩፋኤል †††<+>+"*

ጳጉሜ፦3
ቅዱስ ሩፋኤል
ሥንክሳር፦
1)የስሙ ትርጉም፦ "የእግዚአብሔር መድኃኒት"
2)ምድብ፦ ከ7ቱ ሊቃነ-መላእክት እንዱ።
3)ትውልድ፦ መላእክት የሥጋ ልደትና ሞት የለባቸውም
(ለመጠቆም ያክል ነው)
4)ዓቢይ ተልእኮ፦ ፈታሄ ማህፀን፣ ሕክምና፣ የቀንና የዓመታዊ
የሰዎችን ሥራ ለእግዚአብሔር ዘገባ ማቅረብ፣ የሌሊት
3ሰዓት ተረኛ ጥበቃ፣ ከአውሬዎች ጥበቃ፣ መንገድ መምራትና
ሌሎችም፤
5)ተኣምር፦"ከከበሩት ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ እኔ
ሩፋኤል ነኝ" እንዳለ:: ጦቢት 12፥13
እንግዲህ ከባህሪው ቅድስና ፍጥረቱን በጸጋ ቅድስና መርጦ
የሚለይ እግዚአብሔር አክብሮ እንዲህ ያለ ሰማያዊ ፀጋ
ከሰጣቸው ቅዱሳን መላእክት መካከል በስልጣኑ
ሊቀመናብርት (የመናብርት አለቃ) የሆነ በሹመት ፈታሔ
ማኅጸን (ማሕጸን የሚፈታ) ከሳቴ እውራን (የእውራንን ዓይን
የሚያበራ) ሰዳዴ አጋንንት (አጋንንትን የሚያባርር) ፈዋሴ
ዱያን (ድውያንን የሚፈውስ)፣ አቃቤ ኆኅት (የምህረትን ደጁ
የሚጠብቅ) ተብሎ የተገለጠ ከሊቃነ መላእክቱ ቅዱስ
ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል ተከትሎ የሚነሳ መልአክ ራሱን
እንዲህ በማለት ገለጠ « የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ ወደ
ከበረ ወደ ገነነ ወደ እግዚአብሔር ጌትነት ከሚያገቡ ከከበሩ
ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል
ነኝ» (ጦቢ.12÷15)
ይህ የከበረ ታላቅ መልአክ ሰሙ ሩፋኤል የሚለው ከአምላክ
ለሰዎች የተሰጠ ፈውስ የሚለውን ይተካል «በሰው ቁስል
የተሾመ ከከበሩ ከመላእክት አንዱ ሩፋኤል ነው፡» (ሄኖ.6÷3)
ይህ መልአክ እንደሌሎቹ ሊቃነ መላእክት ሁሉ የሰው ልጆችን
ይጠብቃቸዋል(ዳን.4÷13 ዘጸ. 23÷20 መዝ.
90÷11-13 )
ያማልዳል፣ ከፈጣሪ ያስታርቃቸዋል፡፡(ዘካ.1 ÷12)
በፈሪሀ እግዚአቤሔር እና በአክብሮተ መላእክት ያሉትን
ያድናቸዋል (ዘፍ.49÷15 መዝ.3÷37)
« እግዚአብሔር ሃይሉን የሚገልጥበትን ቅጣቱን ሊያሳይ
ቢወድ አስቀድሞ መርጦ በወደዳቸው ለይቅርታ የተዘጋጁ
የይቅርታ መላእክትን ያመጣል» (ሮሜ.9÷22)
የወላድ ማኅፀን እንዲፈታ ስለተሸመ ከጌታ አዋላጅ ብትኖርም
ባትኖርም ሐኪም ሩፋኤል አይታጣም በምጥ ጊዜ ሲጨነቁ
ሴቶች ሁሉ የመልአኩን መልክ አንግተው ማርያም ማርያም
ይላሉ ማየጸሎቱን ጠጥተው ቶሎ ፈጥነው ይወልዳሉ እያሉ
ደጅ ጠንተው ይማጸኑታል፡፡
ዜና ግብሩን ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ ከተናገረለት በመነሳት
በቅዱሳን ላይ ድንቅ የሆነ እግዚአብሔር በመልአኩ አድሮ
ያደረጋቸውን ተግባራት አበው የበረከት ምንጭ በሆነ ድርሳኑ
ላይ አኑረው የበረከቱ ተካፋይ እንድንሆን ሰጥተውናል፡፡
በጉልህ ሠፍረው ከምናገኛቸው ብዙ ድንቅ ሥራዎች መሀል
ጥቂቶቹን እነሆ፦
~> በሥነ-ስዕሉ የተማጸኑ፣ በምልጃው ታምነው የጸኑ
ቴዎዶስዮስንና ዲዮናስዮስን በገሃድ ተገልጾ ለንግስናና ለጵጵስና
ክብር አብቅቷቸዋል፡፡
~> የንጉስ ቴዎዶስዮስ ልጅም ጻድቁ አኖሬዋስም በፈጣሪው
ህግ እየተመራ የሊቀ መናብርቱን መታሰቢያ ቤተ መቅደስ
አሳንጾ ሲያስመርቅ ለበለጠ ክብር ልቡን አነቃቅቶ ለታናሽ
ወንድሙ ለአርቃዴዋስ የነጋሢነት ስልጣኑን ትቶ መንኖ
በስውርና በጽሙና እዲኖር ረድቶታል፡፡
~> በሊቀጳጳሳት ቴዎፍሎስ ዘመን አባቶች ለሊቀመናብርቱ
ክብር በአሣ አንበሪ ጀርባ ላይ ያሳነጹትን መታሰቢያ ቤተ
መቅደስ በወደቡ አጠገብ በእስክንድሪያ ሳለች ጠላት ዲያቢሎስ
አነዋውጾ ለምስጋና የታደሙትን ምዕመናን ሊያጠፉ አሣ
አንበሪውን ቢያውከው ወደ ሊቀመናብርቱ ተማጽነው እርዳን
ቢሉ ፈጥኖ ደርሶ በበትረ መስቀሉ (ዘንጉ) ገሥጾ ከጥፋት
ታድጓቸዋል፡፡
በቅዱስ መጽሐፍም እንደተገለጠው
~> ሣራ ወለተ ራጉኤልን አስማንድዮስ ከተባለው የጭን
ጋንኤን ሲታደጋት የጦቢያን አባት የጦቢትን ዓይን አበራለት
(መጽሐፍ ጦቢት)
ከዚህም አልፎ የይስሐቅን እናት ሣራን፣ የሶምሶንን እናት
(እንትኩይን) ምክነታቸውን የቆረጠ ወልዶ ለመሳም
ያበቃቸው ይኸው ፈታሔማኅጸን የልዑል እግዚአብሔር
መልአክተኛ ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡
የመልአኩ ጥበቃና የክንፎቹ መጋረድ ከተዋህዶ ምእመናን
ጋር! አሜን!
ለቅዱሳን ክብርን ከማይሰጥ ከተሸወደ ትውልድ ያድነን!