ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

Friday, March 17, 2017

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ:=>+*"+<+>††ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ††

ዮሐንስ ማለት ፍሰሓ ወሐሴት ሠላም ርህራሄ ወሳህል
ማለት ነው። ወልደ ነጎድጓድ፣ አቡቀለምሲስ፣ ነባቤ መለኮት፣
ታዖሎጎስ ይለዋል፡፡ “ቃዳሚሁ ቃል ውእቱ” ብሎ ምስጢረ
ሥላሴን አምልቶ አስፍቶ ይናገራልና፡፡ ፍቁረ እግዚእ
ይለዋል፡፡ “ዝኩ ካልዕ ረድዕ ዘያፈቅሮ እግዚእ ኢየሱስ”
ይለዋልና፡፡ ዮሐንስ 21፡7 መውደድንስ ሁሉንም ይወዳቸው
የለምን ቢሉ የርሱ የተለየ ነውና፡፡ ከቶማስም የሱ መወደድ
ይበልጣል፡፡ ቶማስ በጦር የተወጋ ጎኑን ቢዳስሰው እጁ ከእሳት
እንደገባ ጅማት ተኮማትሯል፡፡ እርሱን ግን በከናፍሩ ቢስመው
በጭኑ ቢያስቀምጠው ምንም ምን አልሆነም ::
ንጹህ ወድንግል ይለዋል፡፡ ጌታን ከመውደዱ የተነሳ ጌታም
እናቱን እነዃት እናትህ ሲል ድንግል ማርያምን በሱ በኩል
ተሰታናለች፡፡ እኛም ዛሬ ልጆቿ ነንና ደስ ይበለን ይበላችሁ
የድንግል ማርያም የአስራት፣ የተስፋና የስስት ልጆች፡፡ ዮሐንስ
19፡26፡፡ ዮሐንስ ሀገሩ ገሊላ አውራጃ ሲሆን ከታላቅ
ወንድሙ ከያዕቆብና ከአባቱ ከዘብድዮስ ጋር ዓሣ እያጠመደ
ይኖር ነበር። እናቱ ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት አንዷ ስትሆን
ማርያም ትባላለች።
ዮሐንስ ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ ሲሆን በሕይትም በኑሮም
ጌታ ስለሚመስል (ፍቁረ እግዚእ) ይባለል። ነገረ መለኮትን
በበለጠ ከሌሎች አምልቶ አስቶ በጥልቀት በማስተማሩ ነባቤ
መለኮት (ታዖሎጎስ)ተሰኝቷል። ስለጌታም ባለው ቅናት ባሳየው
የሀይል ሥራ በኦኔርጌስ (ወልደ ነጎድጓድም) ተብሏል። ፍጥሞ
በምትባል ደሴት በራዕይ መጻእያትን በመግለጡ ባለራዕይ
(በግሪክ አቡቀለምሲስ) ይባለል። በዕለተ ዓርብ በመስቀል ሥር
ተገኝቶ የጌታን መከራ መስቀል በማየቱ ፊቱ በሀዘን
ስለተቋጠረ ቁጽረ ገጽ (ፊቱ በሀዘነ የተቋጠረ) ስምም
ተሰቶታል። ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር የፋሲካን እራት ያዘጋጀ
አንካሳን የፈወሰ ታለቅ ሐዋርያ ነው። (ሊቃስ 22፡8) እስከ
መስቀል አምላኩን ተከትሎ እመቤታችንን በአደራ የተረከበ
ባለአደራ ሐዋርያ ሲሆን ከጰራቅሊጦስ በዓል በኋላ ከቅዱስ
ጴጥሮስ ጋራ በኢየሩሳሌም በአንጾኪያ በሎዶቅያ በእስያ
ከተሞች በተለይ በኤፌሶን በአሁኑ ቱርክ አስተምሯል።
(ዮሐ.19፡26) በወጣትነት ዕድሜው ተጠርቶ በዕለተ ዓርብ
የጌታን መከራ እያሰበ ያነባ የነበረ በፍቅር በታማኝነት
እስከመጨረሻ ድረስ የጸና ከጌታ ያልተለየ ወንጌላዊ ሲሆን
ወንጌልን ጨምሮ 3 መልዕክታትን የጻፈ እንዲሁም ሐዋርያው
ዩሐንስ በፍጥሞ ደሴት በዛሬቱ ቱርክ ለሰባት አመታት ታስሮ
በነበረበት ወቅት ወንጌሉንና ራዕዩን ጽፏል። አይገርምህም
ሐዋርያው ዩሐንስ በእስር እያለ ነው ራዕዩን የጻፈው!!!
ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ ደግሞ በቀዝቃዛ እስር ቤት እያለ ብዙ
መልእክታቱን ጻፈ!!! ሐዋርያቱ በእስር ቢሆኑ እንኳን
ስለቅድስት ቤተክርስቲያን አገልግሎት አብዝተው ያስቡ ነበር።
የሐዋርያቱ ብርታት ያበርታን።
ዩሐንስ ወንጌሉን በፍጥሞ ደሴት ሲጽፍ እንዲህ ብሎ ጀመረ፦
ዩሐንስ 1:1
+++ በመጀመሪያ ቃል ነበረ; ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ
ነበረ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ።እኛም በቅዳሴ ላይ ሁሌ
የዩሐንስ ወንጌል ሲነበብ ቀዳሚሁ ቃል ሥጋ ኾነ ወሃደረ
ላዕሌነ ብለን እንቀበላለን። ግሩም ዜማ ከግሩም ሚስጢር
ጋር አባቶቻችን አወረሱን።
እስቲ ሚስጢሩን እንይ፦
በመጀመሪያ ቃል ነበረ፦ እንደምናውቀው ቃል ኢየሱስ
ክርስቶስ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ አልፋና ዖሜጋ መጀመሪያና
መጨረሻ ነውና ራዕ 22:12። ቃልም እግዚአብሔር ነበር፦
መጽሃፍ አንባቢው ያስተውል ይላል; ምን እንደሚል ልብ
እንበል “ቃልም እግዚአብሔር ነበር” ሐዋርያው በመጀመሪያ
ቃል ነበር ብሎን ነበር; ያ ቃል እግዚአሔር እንደሆነ
አስረዳን!!! በዚሁ ምዕራፍ ላይ ወረድ ብሎ /ዩሐንስ 1:14/
“ያ ቃል ሥጋ ሆነ ይለናል” እስቲ ጥያቄ እንጠያየቅ; ሐዋርያው
ያ ቃል ሥጋ ሆነ ብሏል ከማን? ከማን ሥጋን ነሳ?
ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ
ነፍስ ነስቶ በኤፍራታ በቤቴልሔም ተወለደ።
+++ የፍጥሞ ደሴት ታሪክ እነሆ፦ ሐዋርያው ዩሐንስ በፍጥሞ
ደሴት ወንጌሉን መጻፍ ሲጀምር የመለኮትን ነገር ጽፎ
የሚጨርስ መስሎት ብእሩን አነሳ። በመጀመሪያ ቃል ነበረ
አለና ሊጨርስ አሰበ፤ ያኔ መልአኩ ቅ/ሚካኤል ተገልጦ
በፍጥሞ ደሴት ያለችውን ባህር በእንቁላል ቅርፊት እየቀዳ
ወደ መሬት ሲያፈስ አየው; ሐዋርያው ዩሐንስም እንዴት ይህ
ታላቅ ባሕር በእንቁላል ቅርፊት ያልቃል ብሎ ጠየቀው;
መልአኩም እኔስ ብሞክር ፍጥረትን ነው አንተስ የፈጣሪን
ባሕርይ የሚያልቅ መስሎህ ትሞክር አይደለምን አለው። ያኔ
ሐዋርያው ዩሐንስ ይህን ተረድቶ ወዲያው ከእግዚአብሔር
የተላከ ስሙ ዩሐንስ የሚባል አንድ ሰው አውቃለሁ ብሎ
ስለመጥምቁ ዩሐንስ ታሪክ የቀጠለውም በዚሁ ምክንያት
ነበር። ዩሐንስ 1:19
ከሐዋርያው፣ ከዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ረድኤትና በረከት
ይክፈለን ምልጃና ጸሎት ከሁላች ጋር ይሁን አሜን !!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ
ክቡር ይቆየን አሜን።

No comments:

Post a Comment