ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

Sunday, May 15, 2016

=>+*"+<+>+ግንቦት 8+<+>+"*+

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
አሜን
ግንቦት 8
+ አርባ ዓመት በአስቄጥስ ገዳም ሲኖር ከቅጠል በቀር
ተመግቦ የማያውቀው የገዳመ አስቄጥሱ ገድለኛው አባት አቡነ
ዳንኤል የዕረፍቱ ዓመታዊ መታሰቢያ በዓሉ ነው፡፡
+ ሰማዕቱ አቡነ ዮሐንስ ከ224 ማኅበርተኞቹ ጋር
ምስክርነቱን በድል ፈጸመ፡፡
ሰማዕቱ አቡነ ዮሐንስ፡- ይህንንም ቅዱስ ግብፅ ስንሑት
በምትባል ሀገር በ14 ዓመቱ የአባቱን በጎች ሲጠብቅ
የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦለት እየመራው ወስዶ ከገዳም
አስገባው፡፡ ሃይማኖትን ጠንቅቆ ከተማረ በኋላ በ21 ዓመቱ
መንኩሶ ተጋድሎውን ጀመረ፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ በገዳም በተጋድሎ ሲኖር መልአኩ ድጋሚ
ተገልጦለት የብርሃን አክሊል አሳይቶ ወደ አትሪብ ከተማ ሄዶ
በክርስቶስ ስም ሰማዕት እንዲሆን ነገረው፡፡ በጥሪውም
መሥረት እናትና አባቱን ተሰናብቶ ወደ አትሪብ ሄዶ በከሃዲው
መኰንን ፊት የክርስቶስን አምላክነት መመስከር ጀመረ፡፡
ብዙዎቹ የመኰንኑ ወታደሮች በእርሱ እምነት አመኑ፡፡ ነገር
ግን መኰንኑና ክፉዎች ተባብረው በልዩ ልዩ ዓይነት መንገድ ጽኑ
መከራን አደረሱበት፡፡ መልአኩም እየተገለጠ እያጽናናው
ቁስሎቹን ይፈውስለት ጀመር፡፡ መኰንኑም ወደ እንዴና ሀገር
ላከውና በዚያም እጅግ አሠቃዩት፡፡ በተአምራትም ብዙዎችን
አሳመነ፡፡ የእንዴናውም መኰንን ማሠቃየት በሰለቸው ጊዜ
ግንቦት 8 ቀን አንገቱን በሰይፍ አስቆረጠውና ሰማዕትነቱን
በድል ፈጽሞ የክብር አክሊልን ተቀዳጀ፡፡ ማኅበርተኞቹ የሆኑ
224 ሰዎችም ከእርሱ ጋር ተሰይፈው ዐረፉ፡፡ በቅዱስ
ዮሐንስም በመቃብሩም ላይ 12 ቀን ሙሉ ቀስተ ደመና
ተተክሎና መቃብሩን ሸፍኖት ታይቷል፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ
ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን፡፡
+ + + + + + + + + + + + + + +
የገዳመ አስቄጥሱ አባ ዳንኤል፡- በመቃርስ ገዳም በደብረ
ሲሐት ይኖር የነበረ ሲሆን እርሱም እጅግ ገድለኛ አባት ነው፡፡
40 ዓመት በአስቄጥስ ገዳም ሲኖር ከቅጠል በቀር ተመግቦ
አያውቅም፡፡ በአስቄጥስ ገዳም ዜናው ሁሉ በዓለም በተሰማ
ጊዜ የነገሥታት ልጆችም ወደ እርሱ እየመጡ እየተባረኩ ይሄዱ
ነበር፣ ግማሾቹም በዚያው ይመነኩሱ ነበር፡፡ ይህም አባ
ዳንኤል ስሟን እንጣልዮስ አስብላ የነበረች ንግሥት
የነበረችውን ቅድስት በጥሪቃን የገነዛት ነው፡፡ እርሷም ወንድ
የነበረች ሲሆን ይህም የታወቀው ከሞተች በኋላ ነው፡፡
አውሎጊስ የሚባለውን የወፍጮ ድንጋይ እየወቀረ በመሸጥ
ለድኆች የሚመጸውትን ጻድቅ ሰው ዋስ እሆነዋለሁ በማለት
ከእግዚአብሔር ዘንድ ለምኖ ሥልጣንና ብዙ ወርቅ እንዲያገኝ
ያደረገው ይህ አባ ዳንኤል ነው፡፡ በኋላም አውሎጊስ ሀብቱና
ንብረቱ ከእግዚአብሔር የሚያርቀው ቢሆን አባ ዳንኤል
በጸሎቱ መልሶ ሀብቱን እንዲያጣ አድርጎታል፡፡
አውሎጊስ የሚባል ጻድቅ የወፍጮ ድንጋይ እየወቀረ
(እየጠረበ) በመሸት የሚየገኘውን ለድኆችና ጦም አዳሪዎች
ይመጸውት ነበር፡፡ አባ ዳንኤልም የአውሎጊስን መልካም ሥራ
ተመልክቶ እጅግ ደስ ብሎት ለአውሎጊስ የሀብቱን መጠን
እንዲጨምርለትና ይበልጥ እንዲመጸውት በማሰብ ወደ
እግዚአብሔር በጸሎት አሳሰበ፡፡ ለአውሎጊስም ዋስ ሆነውና
ሀብቱ ተጨመረለት፡፡ አንድ ቀን የሚወቅረውን ድንጋይ
ሲፈቅል በሸክላ ዕቃ የተደፈነ ሙሉ ወርቅ አገኘ፡፡ ወደ
ቁስጥንጥንያም ከተማ ሄዶ ለንጉሡ አስረከበና የንጉሡ
የሠራዊት አለቃ ሆኖ ተሾመ፡፡ ከተሾመም በኋላ የቀድሞውን
የጽድቅ ሥራውን ተወ፡፡ አባ ዳንኤልም ስለ እርሱ ሰምቶ
ሊያየው ቢሄድ በፈረስ ላይ ተቀምጦ በሠራዊት ታጅቦ በትዕቢት
ተመልቶ አገኘው፡፡ ክፉ የትዕቢት መንፈስ አድሮበት ነበር፡፡ አባ
ዳንኤልም አውሎጊስ ሀብት እንዲያገኝ በመለመኑ አዘነ፡፡
በሌሊትም የአውሎጊስ ነፍስ በእርሱ ምክንያት እንደጠፋች ራሱ
አባ ዳንኤልም ሲሰቀልና እመቤታችን ስለ እርሱ ስትማልድ
ራእይ አየ፡፡ ከእንቅልፉም በቃ ጊዜ የአውሎጊስ ሀብት
እንዲጠፋና ወደ ቀደመ ግብሩ እንዲመለስ በጾም ጸሎት ሱባኤ
ያዘ፡፡ መልአክም ተገልጦለት በእግዚአብሐር የፍርድ ሂደት
ውስጥ ጣልቃ በመግባቱ ከገሠጸው በኋላ አውሎጊስም
ምሕረት እንደሚያገኝ ነገረው፡፡ አውሎጊስን የሾሸመው
ንጉሥም ሞተና ሌላ ንጉሥ ነገሠ፡፡ አውለጊስንም ንብረቱን
ሁሉ ቀምቶ ነፍሱንም ለመግደል አሳደደው፡፡ አውሎጊስም
ነፍሱን ለማዳን ሽሽቶ ወደ ሀገሩ በመግባት የቀድሞ ሥራውን
መሥራት ጀመረ፡፡ ነዳያንንም እንደዱሮም መመገብ ጀመረ፡፡
አባ ዳንኤል ከታለቁ ጻድቅ ንጉሥ ከቅዱስ አኖሬዎስ ጋር
የተገናኘ ታሪክ አለው፡፡ ይኸውም አባ ዳንኤል 40 ዓመት ሙሉ
በአስቄጥስ ገዳም ሲኖር ከቅጠል በቀር ተመግቦ አያውቅም
ነበርና ከጽድቁና ከብቃቱ የተነሣ ከብዙ ዘመን በኋላ የመመካት
ክፉ ሀሳብ መጣበት፡፡ ‹‹በገዳም ውስጥ እንደእኔ ትርሕምትን
ገንዘብ ያደረገ ይኖር ይሆን?›› ብሎም አሰበ፡፡ ሰውን ወዳድ
የሆነ ጌታችንም ይህን ክፉ ሀሳቡን ሊያርቅለት ሽቶ ብርሃናዊ
መልአኩን ላከለት፡፡ መልአኩም አባ ዳንኤልን ስለ ትምክህቱ
ቢቆጣውም አባ ዳንኤል መልአኩን መልሶ ‹‹ጌታዬ ከእኔ
የሚሻል ካለ ንገረኝ፣ ወደ እርሱ ሄጄ አየው ዘንድ እወዳለሁ፣
በመመካቴም ወደ ፈጣሪዬ በልመና እመለስ ዘንድ›› አለው፡፡
መልአኩም ‹‹እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው የሮሜና
የቁስጥንጥንያ ንጉሥ አኖሬዎስ በመንግሥተ ሰማያት
ባልንጀራህ ነው›› አለው፡፡
‹‹ንጉሥ አኖሬዎስም የመነኮሳትን ሥራዎች ሁሉ ስለሚሠራ
ከልብሰ መንግሥቱ ሥር በሥጋው ላይ ማቅ ይለብስ ነበር››
ተብሎ በስንክሳሩ ላይ የተጻፈለት ጻድቅ ንጉሥ ሲሆን
ሰማያውያን የሆኑ ቅዱሳን መላእክትም ቅድስናውን
የመሰከሩለት በንግሥና ያለ ታላቅ የእግዚአብሔር አገልጋይ
ነው፡፡ አባ ዳንኤልም ይህ በሰማ ጊዜ መሬት ላይ ወድቆ
በራሱም ላይ አመድ ነስንሶ የዚህን የሮም ንጉሥ አኖሬዎስን
ግብር ያሳየው ዘንድ ጌታችንን ለመነ፡፡ ደመናም መጥታ ነጥቃ
ወሰደችውና ንጉሥ አኖሬዎስ ደጅ አደረሰቸውና ንጉሡን በዙፋኑ
ላይ ሆኖ ባየው ጊዜ ከግርማው የተነሣ አይቶት በታላቅ ፍርሃት
ውስጥ ሆኖ ከእግሩም በታች ሰገደለትና አኗኗሩንም ይነግረው
ዘንድ በጌታችን ስም አማፀነው፡፡ ንጉሥ አኖሬዎስም ሰሌን
በመታታት በእጅ ሥራው ደክሞ ከሚያገኘው በቀር ምንም
ሳይበላና ሳይለብስ 40 ዓመት እንደሆነው፣ ሰሌን ታቶ ሸጦ
ካገኘውም ውስጥ ከዕለት ምግቡ መግዣ የሚተርፈውን
ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች እንደሚመጸውት፣ ምግቡም
እንጀራና ጨው፣ ቅጠል መጻጻም እንደሆነ፣ የማንንም ንብረት
ፈጽሞ እንዳልንካ፣ ድንግልናውንም ጠብቆ እንደሚኖር
ነገረው፡፡ አባ ዳንኤልም ድጋሚ ከእግሩ ሥር ወድቆ ሰግዶለት
ስለ ትምክህቱም ፈጽሞ እያዘኑ ወደ በዓታቱ ተመልሷል፡፡
አባ ዳንኤል አንድ ቀን ከረድኡ ጋር ወደ እስክንድርያ ሲጓዝ
ስሙ ምህርካ የሚባል እብድ አገኘ፡፡ ብዙ እብዶችም ይከተሉት
ነበር፡፡ እርሱም ለአገሩ ሰዎች ሁሉ በእውነት ያበደ ይመስላቸው
ነበር፡፡ አባ ዳንኤልም እጁን ይዞ ወደ ሊቀ ጳጳሳቱ ወስዶ
ትሩፋቱን ተጋድሎውን ነገረው፡፡ ከሊቀ ጳጳሳቱም ጋር ሆነው
እብዱን ስለራሱ እንዲነግራቸው በእግዚአብሔር ስም ባማሉት
ጊዜ ከዝሙት ጦር በመሸሽ ራሱን እብድ እንዳስመሰለ
ነገራቸው፡፡
አንድ ቀን አባ ዳንኤል በሌሊት በበረሃ ውስጥ በጨረቃ ብርሃን
ሲጓዝ በተራራ ላይ ቀምጣ ጠጉሯ መላ ሰውነቷን የሸፈናት
በዚያም በረሃ ስትኖር በተሰነጠቀ ዓለት ውስጥ 38 ዓመት
ብቻዋን ማንም ሳያያት የኖረች ጻድቅ እናት አግኝቶ ምሥጢሯን
ሁሉ ነግራዋለች፡፡ እርሷም ቅድስት አመተ ክርስቶስ ናት፡፡ አባ
ዳንኤልም 38 ዓመት ሙሉ በዚህ በረሃ ምንም ሰው ሳታይ
የኖረችበትን ተገድሎዋን በዝርዝር ነግራቸዋለች፡፡ እርሳቸውም
ወደ ገዳማቸው ተመልሰው ለአበ ምኔቱና ለመነኮሳቱ ታሪኳን
በመንገር ልብስ ይዘውላት ቢመጡ ዐርፋ አግኝተዋታል፡፡
አባ ዳንኤል የልዮንን የክህደት ደብዳቤ ወታደሮቹ አምጥተው
በመነኮሳቱ ፊት ሲያነቡ ደብዳቤውን ተቀብሎ በሕዝቡ ፊት
ቀዶታል፡፡ ወታደሮቹም አባ ዳንኤልንደብደበው ከገዳሙም
አሳደውታል፡፡ ብዙ ሥቃይም አድርሰውበታል፡፡
አባ ዳንኤል በአንዲት ዕለት ከደናል ገዳም ደርሶ ደጁን አንኳኳ፡፡
እነርሱም አባ ዳንኤል መሆኑን ዐውቀው ከፈቱለት፡፡ አንዲት
ሴትም ራሷን ዕብድ አስመስላ በደጅ የምትተኛ ሴት ነበረች፡፡
እርሱም ዕብድ መስላ በደጅ ስለተቀበጠችው ሴት አበምነቷን
ሲጠይቃት እብድ መሆኗን ነገረችው፡፡ አባ ዳንኤል ግን ዕብድ
የመሰለቻቸው ሴት እብድ ሳትሆን በድብቅ በታላቅ ተጋድሎ
የምትኖር ቅድስት ሴት መሆኗን ነገራት፡፡ ዕብድ የተባለችውም
ሴትም አባ ዳንኤል ምሥጢሯን እንደገለጠባት በስውር ዐውቃ
ወዲያው ደብዳቤ ጽፋ ይኸውም ‹‹የተከበራችሁ እኅቶቼ
ስላስቀየምኳችሁና ስላሳዘንኳችሁ ይቅር በሉኝ›› ብላ ጽፋ
ደብዳቤውን አስቀምጣ ጥላቸው ጠፋች፡፡ እነርሱም ከዚያ በኋላ
ዳግመኛ አላዩአትም፡፡
ደናግል ወደሚኖሩበት ገዳም አንድ የወንበዴዎች አለቃ ሰይጣን
አነሳስቶት ወደ ገዳሙ በአባ ዳንኤል ተመስሎ ቆቡን ደፍቶ
በሩን አንኳኳ፡፡ ደናግላኑም ሊዘርፋቸው መምጣቱን ምንም
ባለማወቅ ይልቁንም አባ ዳንኤል መጣ ብለው በሩን
ከፈቱለትና አስገቡት፡፡ እግሩንም አጥበው ለበረከት ብለው
የእግሮቹን ዕጣቢ በፊታቸው ላይ ረጩት፡፡ ከመካከላቸውም
አንዷ ዐይነ ሥውር ነበረችና ዐይኗ ወዲያው በራላት፡፡ በዚህም
ደናግሉ እጅግ ተደስተው ‹‹አባ ዳንኤል አንተ ንዑድ ክቡድ ነህ››
ብለው ሰገዱለት፡፡ ይህን ጊዜ የሽፍቶቹ አለቃ በጣም ደንግጦ
በመጸጸት ወደ አባ ዳንኤል ዘንድ ሄዶ ያደረገውን ሁሉ በመናገር
ንስሓ ገባ፡፡ መንኩሶም በታላቅ ተጋድሎ መኖር ጀመረ፡፡
እርሱም ተአምራት እስከማድረግ ደርሶ በሰላም ዐረፈ፡፡ የአባ
ዳንኤልም ተጋድሎና ተአምር ምን ቢጽፉት የሚያልቅ
አይደለም፡፡ ዕረፍቱም በደረሰ ጊዜ ጌታችን ታላቅ ቃልኪዳን
ሰጥቶት ቅድስት ነፍሱን ወደ እርሱ ወስዷታል፡፡ የአባ ዳንኤል
ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን፡፡

=>+*"+<+>+ኢየሱስ ክርስቶስ ተማላጅ እንጂ አማላጅ አይደለም+<+>+"*+

“ያመኑትም ሕዝብ አንድ ልብ አንዲትም ነፍስ ነበሩአቸው”።
የሐ.ሥራ ፬፡፴፪
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተማላጅ
እንጂ አማላጅ አይደለም::
የተሐድሶ መናፍቃኑ አንደበት “ክርስቶስ አማላጅ ነው” በማለት
በዛሬው ዕለት የእምነት አቋሙን የገለጹበት ጽሑፍ
አውጥቶዋል::
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
#ጌታችን_መድኃኒታችን_ኢየ ሱስ_ክርስቶስን
#አምላክ_ወልደ_አምላክ_ብ ላ_ታምናለች፤
ታስተምራለችም:: ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ተማላጅ እንጂ አማላጅ እንዳልሆነ ቅዱሳን መጻሕፍ
ይናገራሉ:: በዚህ በተሐድሶ ለወጣው የምንፍቅና ትምህርት
ምላሽ ይሆን ዘንድ የሚከተለውን የቤተ ክርስቲያናችን
አስተምህሮ የሚገልጽ ጽሑፍ አቅርበንላችኋል::
+++
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእርሱን
ማንነት ገልጦ ያስተማረበት ትምህርት ነው። በዚህም
ትምህርቱ፥ እርሱ የበጎች እረኛ እንደሆነ፥ የበረቱም በር እርሱ
መሆኑን ተናግሯል። እውነት የባህርይ ገንዘቡ ስለሆነም፥
ትምህርቱን «እውነት እውነት እላችኋለሁ፤» በማለት
ጀምሯል። በዚህም አማናዊ በሆነ ትምህርቱ «ወደ በጎች በረት
በበሩ የማይገባ፥ በሌላም በኲል የሚገባ ሌባ፣ ወንበዴም
ነው፤» ብሏል። ይኽንንም ስለ ሦስት ነገር ተናግሮታል።
፩ኛ፦ #ጌታችን_አምላካችን_መድኃ ኒታችን #ኢየሱስ_ክርስቶስ
፥ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ዕውር ሆኖ የተወለደውን ብላቴና
በምራቁ ጭቃ አድርጐ፥ በሰሊሆም ጠበልም እንዲጠመቅ
በማድረግ ፈጽሞ ስለፈወሰው፥ አይሁድ ብላቴናውንም
ወላጆቹንም አስቸግረዋቸው ነበር። ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ፦
«ይህ ሰው (ኢየሱስ) ከእግዚአብሔር አይደለም፥ ሰንበትንም
አይከብርምና፤» እያሉ ብላቴናውን ተከራክረውታል። እርሱ
ግን፦ «ኃጢአተኛ ሰው እንዲህ ያለ ተአምራት ማድረግ (በደረቅ
ግንባር ላይ ዓይን መፍጠር) እንዴት ይችላል? . . . እርሱ ነቢይ
ነው፤» አላቸው። ይኸውም፦ የነቢያት አለቃ ሙሴ፥
ከእግዚአብሔር አግኝቶ፥ «እግዚአብሔር ከወንድሞቻችሁ
መካከል (ከእናንተ ወገን) እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣላችኋልና
እርሱን ስሙት፤» በማለት ለእስራኤል ዘሥጋ የነገራቸው ቃለ
ትንቢት ነው። የሐዋ ፯፥፴፯። ምክንያቱም በብዙ መንገድ
ሙሴ ለኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነውና። የነቢያት አምላካቸው
ኢየሱስ ክርስቶስ «ነቢይ» መባሉም ነቢያት በአንድም ሆነ
በሌላ ምሳሌዎቹ በመሆናቸው ነው።
የብላቴናው ወላጆች ደግሞ አይሁድ ወጥረው በጠየቋቸው ጊዜ፥
«ይህ ልጃችን እንደሆነ፥ እውር ሆኖም እንደተወለደ
እናውቃለን። አሁን ግን እንዴት እንደሚያይ፥ ዓይኖቹንም ማን
እንደ አበራለት እናውቅም፥ እርሱን ጠይቁት፥ አዋቂ ነውና፥
ስለራሱም መናገር ይችላልና፤» አሉ። እንዲህም ማለታቸው
«እርሱ ክርስቶስ ነው፥ ብሎ በእርሱ የሚያምን ቢኖር
ከምኲራብ ይውጣ፤» የሚለውን የአይሁድን ዓዋጅ ፈርተው
ነው። ብላቴናው ግን ደጋግመው በጠየቁት ጊዜ «አትሰሙኝም
እንጂ ነገርኋችሁ፥ እንግዲህ ምን ልትሰሙ ትሻላችሁ? እናንተም
ደቀመዛሙርቱ ልትሆኑ ትሻላችሁን?» ብሎ ሳይፈራ
ተከራከራቸው። በዚህን ጊዜ «ራስህ በኃጢአት የተወለድህ አንተ
እኛን ታስተምራለህን?» ብለው ከምኲራብ አወጡት። በዚህም
ንግግራቸው በጌታ ቃል፦ «የእግዚአብሔር ሥራ ሊገለጥበት
ነው እንጂ እርሱ አልበደለም፥ ወላጆቹም አልበደሉም፤»
የተባለውን ሰው በልበ ደንዳናነት ኰነኑት። ከቤተ መቅደስም
አስወጡት። ዮሐ ፱፥፫። ጌታችንም አግኝቶት «አንተ
በእግዚአብሔር ልጅ ታምናለህን?» አለው። ብላቴናውም፦
«አቤቱ፥ አምንበት ዘንድ እርሱ ማነው?» ብሎ መለሰለት።
ጌታችን ኢየሱስም «የምታየው፥ ከአንተ ጋርም የሚነጋገረው
እርሱ ነው፤» አለው። ይኸውም «ነቢይ ነው፤» እንዳለ
በምሳሌው እንዳይቀር «አምላክ ወልደ አምላክ» ብሎ
እንዲያምን ነው። እርሱም «አቤቱ ፥ አምናለሁ፤» ብሎ
ሰገደለት። ከዚህ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ «እኔ
የማያዩት እንዲያዩ (አላዋቆች ነን የሚሉ ሐዋርያት አዋቆች
ይሆኑ ዘንድ) የሚያዩትም እንዲታወሩ (አዋቆች ነን የሚሉ
ፈሪሳውያን አለዋቆች ይሆኑ ዘንድ) ለፍርድ መጥቻለሁ።
(ላመነብኝ ልፈርድለት ላላመነብኝ ልፈርድበት፥ ለሰው
መፈራረጃ ለመሆን ከሰማይ ወርጃለሁ)። አለው። በዚህን ጊዜ
ይኽንን የሰሙ ፈሪሳውያን፦ «እኛ ደግሞ ዕውሮች ነን?»
አሉት። ጌታችን ኢየሱስም ዕውሮችስ ብትሆኑ ኃጢአት
ባልሆነባችሁ ነበር፤ (ነውረ ሥጋ ከመንግሥተ ሰማይ
አያወጣምና)፤ አሁን ግን እናያለን (እናውቃለን) ትላላችሁ፥
አታዩምም፤ (አታውቁምም)፤ ስለዚህም ኃጢአታችሁ ጸንቶ
ይኖራል፤ (ንስሐ ስለማትገቡ ኃጢአታችሁ አይሰረይላችሁም)፤
አላቸው። ዮሐ ፱፥፩፥፵፩። እንግዲህ በዚህ ምክንያት «ለሰው
መፈራረጃ እሆን ዘንድ መጥቻለሁ።» በማለቱ፥ ለምሕረትም
እንደመጣ ለማጠየቅ በዮሐንስ ወንጌል በምዕራፍ አሥር
ያለውን አስተምሯል።
፪ኛ፦# ይህ_ዕውር_ሆኖ_ተወልዶ_ ጌታ #የፈወሰው_ብላቴና፥
ፈሪሳውያን፦ እንዴት እንዳየ ደጋግመው በጠየቁት ጊዜ፥ ደጋግሞ
እውነቱን ነግሯቸዋል። በተጨማሪም፦ «እናንተም ደቀ
መዛሙርቱ ልትሆኑ ትሻላችሁን?» ብሎም ጠይቋቸዋል።
እነርሱ ግን፥ «አንተ የእርሱ ደቀመዝሙር ሁን፥ እኛስ የሙሴ
ደቀመዛሙርት ነን። እግዚአብሔር ሙሴን እንደተነጋገረው
እናውቃለን፥ ይህን ግን ከወዴት እንደሆነ አናውቅም፤» አሉት።
በዚህን ጊዜ «. . . ከወዴት እንደሆነ፥ አታውቁምና እጅግ ድንቅ
ነው፤ ነገር ግን ዓይኖቼን አበራልኝ። ይህ ሰው ከእግዚአብሔር
ባይሆን ኖሮ ምንም ማድረግ ባለቻለም ነበር፤» ብሎአቸዋል።
እንግዲህ፦ «ከወዴት እንደሆነ አናውቅም፤» ብለውት ስለነበረ
ከወዴት እንደሆነ ለማጠየቅ አንቀጸ አባግዕን አስተምሯል።
፫ኛ፦ «ቸር እረኛ አይደለህም፤» ብለውት ስለነበር፥ ቸር እረኛ
መሆኑን ለማጠየቅ ነው። ይኽንንም፦ «ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ፥
ቸር ጠባቂ ስለ በጎቹ ነፍሱን ይሰጣል። ጠባቂ ያይደለ፥ በጎቹም
ገንዘቡ ያይደሉ ምንደኛ ግን፥ ተኲላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ
ይሻላል፤ ተኲላም መጥቶ በጎቹን ይነጥቃቸዋል፥
ይበትናቸዋልም። ምንደኛስ ይሸሻል፥ ስለ በጎቹም አያዝንም፥
ምንደኛ ነውና።» በማለት ነግሯቸዋል።
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ በጎች
ያላቸው ምእመናንን ነው። የዕለተ ምጽአት ፍርድ እንዴት
እንደሆነ ለደቀመዛሙርቱ በነገራቸውም ጊዜ፥ ጻድቃንን በበጎች
መስሎ፥ «በጎቹን በቀኝ ያቆማቸዋል፤» ብሏል። ማቴ
፳፭፥፴፫። ቅዱስ ጴጥሮስንም፦ «በጎቼን ጠብቅ፤» ብሎታል።
ዮሐ ፳፩፥፲፭። ተኲላ ያለው ደግሞ ሰይጣንን እና መልክተኞቹን
ነው። ቅዱስ ዳዊት፦ በልዑል ረድኤት የሚያድር፥ በሰማይ
አምላክ ጥላ ውስጥ የሚቀመጥ፥ እግዚአብሔርን፦ «አንተ
መጠጊያዬና አምባዬ፥ አምላኬና ረዳቴ ነህ፥ በአንተ
እታመንብሃለሁ፤» የሚል ሰው፥ የሚያገኘውን ጸጋ ሲናገር፥
«ክፉ ነገር ወደ አንተ አይቀርብም፥ መቅሠፍትም ወደ ቤትህ
አይገባም። በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ
አንተ ያዝዛቸዋልና፥ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል
በእጆቻቸው ያነሡሃል። በተኲላና በእባብ ላይ ትጫናለህ፥
አንበሳውንና ዘንዶውን ትረግጣለህ፤» ብሏል። መዝ ፺፥፩-፲፫።
ካልተጠነቀቁ በስተቀር ተኲላት (መናፍቃን) አደገኞች ናቸው።
ይኽንንም ጌታችን «የበግ ለምድ ለብሰው ወደ እናንተ
ከሚመጡ ከሐሰተኞች ነቢያት (ከመናፍቃን) ተጠንቀቁ፥
በውስጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኲላዎች ናቸው።» በማለት
ነግሮናል። ማቴ ፯፥፲፭። ከዚህም ሌላ «እነሆ እኔ እንደ በጎች
በተኲላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ . . . ከክፉዎች ሰዎች
ተጠበቁ፤» ብሎናል።
ተኲላ ተንኰለኛ አውሬ ነው፥ ተመሳስሎ ከበጎች ጋር መደባለቅ
ያውቅበታል፥ ሥጋ በል ሲሆን ሣር እንደሚነጭ እንስሳ
አንገቱን ቀብሮ ይውላል፥ ቢርበውም ምቹ ጊዜ እስኪያገኝ
ይታገሣል። በጎች በራሳቸው አቅም ይኽንን መከላከል
አይችሉም፥ ምክንያቱም የዋሃን ናቸውና። በመሆኑም ተግቶ
የሚጠብቅ እረኛ ያስፈልጋቸዋል። እረኛ ከሌላቸው ግን
ይጠፋሉ። ይኽንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ
ከምእመናን ሕይወት ጋር በማገናዘብ፦ «እንደ በጎች ትቅበዘበዙ
ነበርና፥ አሁንም ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመለሱ፤»
ብሏል። ፩ኛ ጴጥ ፪፥፳፭። በጎች የምእመናን ብቻ ሳይሆን
የክርስቶስም ምሳሌዎች ናቸው። መጥምቀ መለኰት ቅዱስ
ዮሐንስ፦ «እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ
የእግዚአብሔር በግ፤» ያለው ለዚህ ነው። ዮሐ ፩፥፳፱። ነቢዩ
ኢሳይያስም፦ «እርሱ ግን በመከራው ጊዜ አፉን አልከፈተም፥
እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፥ የበግ ጠቦትም በሸላቾቹ ፊት
ዝም እንደሚል እንዲሁ አፉን አልከፈተም።» በማለት
አስቀድሞ ተናግሯል። ኢሳ ፶፫፥፯።
፩፥፩፦ #በበሩ_የሚገባና_የማይገባ ፤
#በበሩ_የሚገባ_ማለት፦ ትንቢት ተነግሮለት፥ እግዚአብሔር
አብ መስክሮለት፥ ምእመናን ወደ አሉበት ወደ ኢየሩሳሌም
በመምሕርነት የሚመጣ ማለት ነው። ጌታችን አምላካችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣው
ትንቢት ተነግሮለት፥ ሱባዔ ተቆጥሮለት ነው። ኢሳ ፯፥፲፬፤ ፱፥፪-
፮፤ ፲፩፥፩። የባህርይ አባቱም በዮርዳኖስ፦ «በእርሱ ደስ
የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤» በማለት መስክሮለታል።
ማቴ ፫፥፲፯። ከዚያም በፊት የልደቱን ብሥራት ለእመቤታችን
ለቅድስት ድንግል ማርያም የነገረ፥ ቅዱስ ገብርኤል፥
«ማርያም ሆይ፥ በእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን
አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆ ትፀንሻለሽ፥ ወንድ ልጅንም
ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ። እርሱም ታላቅ
ነው፥ የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል፤» ብሏል። ሉቃ
፩፥፴-፴፪። በተወለደ ጊዜም ቅዱሳን መላእክት፥ ለእረኞች
ተገልጠው፥ «እነሆ፥ ለእናንተና ለሕዝቡ ሁሉ ደስታ የሚሆን
ታላቅ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ እነሆ፥ ዛሬ በዳዊት
ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋል፥ ይኸውም ቡሩክ ጌታ ክርስቶስ
ነው።» በማለት መስክረውላቸዋል። ሉቃ ፪፥፲፥፲፩።
መጥምቀ መለኰት ቅዱስ ዮሐንስም፦ «ጫማውን እሸከም
ዘንድ ከማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ
ይበረታል፥እርሱ በእሳትም በመንፈስ ቅዱስም ያጠምቃችኋል፤
መንሹም በእጁ ነው፥ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፥
ስንዴውን በጎተራ ይከታል፥ ገለባውን በማይጠፋ እሳት
ያቃጥለዋል።» ማቴ ፫፥፲፩። «ተጐንብሼ የጫማውን ጠፍር
መፍታት ከማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ በኋላዬ ይመጣል።» ማር
፩፥፯፣ ሉቃ ፫፥፲፭። «ዳሩ ግን እናንተ
የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል፤ እኔ የጫማውን ጠፍር
ልፈታ የማይገባኝ፥ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ ይልቅ
የሚከብር ይህ ነው። . . . አንድ ሰው ከእኔ ይልቅ የከበረ
ሆኖአል ብዬ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነው። እኔም አላውቀውም
ነበር፥ ነገር ግን ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ ስለዚህ በውኃ
እያጠመቅሁ መጣሁ።» ዮሐ ፩፥፳፮። «ከሰማይ ካልተሰጠው
ሰው አንዳች ሊቀበል አይቻለውም። እናንተ እኔ ክርስቶስ
አይደለሁም፥ ነገር ግን ከእርሱ በፊት ተልኬአለሁ እንዳልሁ
ራሳችሁ ትመሰክሩልኛላችሁ። ሙሽራይቱ ያለችው እርሱ
ሙሽራ ነው፥ ቆሞ የሚሰማው ሚዜው ግን በሙሽራው ድምፅ
እጅግ ደስ ይለዋል። እንግዲህ ይህ ደስታዬ ተፈጸመ። እርሱ
ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ይገባል።» ብሏል። ዮሐ ፫፥፳፯።
ከእግዚአብሔር አብ፥ ከነቢያት ትንቢት፥ ከቅዱሳን መላእክት
ብሥራትና የምሥራች፥ እንዲሁም ከመጥምቀ መለኰት ቅዱስ
ዮሐንስ ምስክርነት እንደተማርነው፦ ጌታችን አምላካችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ በበሩ የገባ ቸር እረኛ ነው።
በመሆኑም «ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፥ በጎቹም ቃሉን
ይሰሙታል፥ እርሱም በጎቹን በየስማቸው ይጠራቸዋል፥
አውጥቶም ያሰማራቸዋል።» ብሎአል። በረኛ የተባለ መንፈስ
ቅዱስ ነው፤ ሕዋሳቱን በሰበሰበ፥ ዐሠርቱ ቃላትን በያዘ፥ በሰቂለ
ኅሊና፥ በነቂሐ ልቡና በሚኖር ሰው የሚያድር እርሱ ስለሆነ
የሰውን አእምሮ ለበጎ ይከፍተዋል። አንድም በረኛ የተባለ ራሱ
ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ምክንያቱም፥ ለጊዜው አምስት ሺ
አምስት መቶ ዘመን የተዘጋች ገነትን በቤዛነቱ የሚከፍት፥
ለፍጻሜውም በዕለተ ምጽአት መንግሥተ ሰማያትን የሚከፍት
እርሱ ነውና። «በጎቹ ቃሉን ይሰሙታል፥» እንዳለ፥ አሥራ ሁለቱ
ሐዋርያት፥ ሰባ ሁለቱ አርድእት፥ ሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት
ትምህርቱን ተቀብለውታል። በየስማቸውም ዮሐንስ፥ ያዕቆብ፥
ስምዖን፥ ታዴዎስ፥ ዲዲሞስ፥ ቶማስ እያለ ጠርቶአቸዋል።
«አውጥቶም ያሰማራቸዋል፤» የተባለው ደግሞ፦ «በጠባቢቱ
በር ግቡ፤ . . . እኔን ሊከተል የሚወድ ራሱን ይካድ፥ ጨክኖም
የሞቱን መስቀል ተሸክሞ ይከተለኝ፤» እያለ ያስተምራቸዋል
ማለት ነው። መሰማሪያ የተባለው ትምህርተ ወንጌል ነው፥
አንድም መከራ ነው፥ አንድም በመጨረሻ የሚወርሱት ክብረ
መንግሥተ ሰማያት ነው።
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስት
ዓመት ከሦስት ወር ካስተማራቸው በኋላ ይሰቀልላቸዋል
(ነፍሱን አሳልፎ ይሰጥላቸዋል)። «በጎቹም ይከተሉታል»፤
እርሱን አብነት አድርገው ወንጌልን ያስተምራሉ፥ መከራን
ይቀበላሉ፥ በመከራ ይመስሉታል። «ቃሉን ያውቃሉና።»
ትምህርቱን ተቀብለውታልና። «ሌላውን ግን ይሸሹታል እንጂ
አይከተሉትም፥ የሌላውን ቃሉን አያውቁምና።» ትንቢት
ሳይነገርለት፥ መጻሕፍት ሳይመሰክሩለት የመጣውን ግን ሌባ
ወንበዴም በመሆኑ አብነት አያደርጉትም፥ አይመስሉትም፤
ይነቅፉታል፥ ያወግዙታል እንጂ ትምህርቱን አይቀበሉም።
ጌታችን ይኽንን ምሳሌ ቢነግራቸውም እረኛ የተባለ እርሱ፥
አባግዕ የተባሉ ደግሞ እነርሱ እንደሆኑ አልገባቸውም።
ዳግመኛም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ፥ «እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የበጎች በር እኔ ነኝ።
ከእኔ በፊት የመጡ ሁሉ ሌቦችና ወንበዴዎች ናቸው፥ ነገር ግን
በጎች አልሰሙአቸውም። እውነተኛው የበጎች በር እኔ ነኝ፥ በእኔ
በኲልም የሚገባ ይድናል፤» (ወደ ሃይማኖት ወደ ወንጌል
ይገባል)፤ «ይወጣልም፤» (ከፈቃደ ሥጋ ይወጣል፤ አንድም በጎ
ሥራ ለመሥራት ለማስተማር ይወጣል)፤ መሰማሪያም
ያገኛል። (መከራን ማለትም እስራቱን፣ ግርፋቱን፣ እሳቱን፣
ስለቱን፣ ያገኛል)። አንድም በጉባኤ ምእመናንን ያገኛል፤
አንድም ክብረ ሥጋን ክብረ ነፍስን ያገኛል)። ሌባ ግን ሊሰርቅና
ሊያርድ፥ ሊያጠፋም ካልሆነ በቀር አይመጣም። (ሌባው
ወንበዴው ግን በነፍስም በሥጋም ሊጐዳ ሊያጠፋ ነው እንጂ
ሊያለማ ሊጠቅም አይመጣም)። እኔ ግን የዘለዓለም ሕይወትን
እንዲያገኙ፥ እጅግም እንዲበዛላቸው መጣሁ።» አላቸው።
በበሩ የማይገባ ማለት ደግሞ፦ ትንቢት ሳይነገርለት፥ ሱባዔ
ሳይቆጠርለት፥ እግዚአብሔር አብ ሳይመሰክርለት፥ ቅዱሳን
መላእክትም ብሥራቱንም የምሥራቹንም ሳይናገሩለት የመጣ
ማለት ነው። ይኸውም እንደ ይሁዳ ዘገሊላ አንድም እንደ
ቴዎዳስ ዘግብፅ ነው። የአይሁድ ሸንጎ በቅዱሳን ሐዋርያት
ተቆጥተው ሊገድሉአቸው በወደዱ ጊዜ፥ በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ
የከበረ ስሙ ገማልያል የሚባል የኦሪት መምህር ነበረ።
እርሱም ቅዱሳን ሐዋርያትን ፈቀቅ እንዲያደርጉአቸው ካዘዘ
በኋላ፥ «እናንተ የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ በእነዚህ ሰዎች
በምታደርጉት ነገር ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ቀድሞም ከዚህ
ዘመን በፊት ቴዎዳስ ተነሥቶ ራሱን ከፍ ከፍ አደረገ፤ (እኔ
አምላክ ነኝ አለ)፤ አራት መቶ ሰዎችም ተከተሉት፥ ነገር ግን
እርሱም ጠፋ፥ የተከተሉትም ሁሉ ተበታተኑ፥ እንደ ኢምንትም
ሆኑ። ከእርሱም በኋላ ሰዎች ለግብር በተቈጠሩበት ወራት
ገሊላዊ ይሁዳ ተነሣ፥ ብዙ ሕዝብም ተከተሉት፥ እርሱም ሞተ፥
የተከተሉትም ሁሉ ተበታተኑ። አሁንም እላችኋለሁ፥ ከእነዚህ
ሰዎች (ከቅዱሳን ሐዋርያት) ራቁ፥ ተዉአቸውም፥ ይህ
ምክራቸው ይህም ሥራቸው ከሰው የተገኘ ከሆነ ያልፋል፥
ይጠፋልም። ከእግዚአብሔር የመጣ ከሆነ ግን ልታፈርሱት
አትችሉም፥ ከእግዚአብሔርም ጋር እንደሚጣላ አትሁኑ።»
ብሎአል። የሐዋ ፭፥፴፬፥፴፱።
፩፥፪፦ #ቸር_ጠባቂ_እኔ_ነኝ፤
ቅዱስ ዳዊት እግዚአብሔር እረኛ ጠባቂ መሆኑን ሲናገር፦
«እግዚአብሔር ይጠብቀኛል፥ የሚያሳጣኝም የለም።
በለመለመ መስክ ያሳድረኛል፥ በዕረፍት ውኃ ዘንድ አሳደገኝ፤»
ብሎአል። መዝ ፳፪፥፩። ቸር እረኛ የጠፋውን በግ እስኪያገኘው
ድረስ ይፈልገዋል። ይኽንንም፦ «የሰው ልጅ (ወልደ ዕጓለ
እመሕያው ክርስቶስ) የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን
መጥቶአልና። ምን ትላላችሁ? መቶ በጎች ያለው ሰው ቢኖር፥
ከመካከላቸውም አንዱ ቢጠፋው፥ ዘጠና ዘጠኙን በተራራ ላይ
ትቶ የጠፋውን ሊፈልግ ይሄድ የለምን? እውነት እላችኋለሁ፥
ባገኘው ጊዜ ካልጠፉት ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ ጠፍቶ ስለተገኘው
ፈጽሞ ደስ ይለዋል፤» በማለት ነግሮናል። ማቴ ፲፰፥፲፩-፲፫።
እግዚአብሔር ቅዱሳን መላእክትን የፈጠራቸው በነገድ መቶ
አድርጎ ነበር። አንደኛው ነገድ (የሳጥናኤል ነገድ) በክህደት
በመጉደሉ ምክንያት አዳም መቶኛ ሆኖ ተቈጥሯል።
በመሆኑም የጠፋው በግ የተባለው አዳም ነው። ነቢዩ
ኢሳይያስም፦ «እነሆ እግዚአብሔር በኃይሉ ይመጣል፥
በክንዱም (በሥልጣኑ፥ በባህርይ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ)
ይገዛል፥ እነሆ ዋጋው ከእርሱ ጋር ሥራውም በፊቱ ነው።
መንጋውን እንደ እረኛ ይመራል፥ ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ
በብብቱ ይሸከማል፥ የሚያጠቡትንም በቀስታ ይመራል።»
በማለት እርሱ አምላካችን የሕይወታችን እረኛ እንደሆነ
ተናግሯል። ኢሳ ፵፥፲፩። ነቢዩ ሕዝቅኤል ደግሞ፦ «ጌታ
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ እኔ ራሴ በጎቼን እሻለሁ፥
እጎበኛቸዋለሁ። ከአሕዛብም ዘንድ አወጣቸዋለሁ፥ ከሀገሮችም
ሁሉ እሰበስባቸዋለሁ፥ ወደ ገዛ ሀገራቸውም አመጣቸዋለሁ፥
በእስራኤልም ተራሮች ላይ፥ በፈሳሾችም አጠገብ፥ በምድርም
ላይ ሰዎች በሚኖሩባት ስፍራ ሁሉ አሰማራቸዋለሁ።
በመልካም ማሰማርያ አሰማራቸዋለሁ፥ ጉሮኖአቸውም
በረዥሞቹ በእስራኤል ተራሮች ላይ ይሆናል፥ በዚያ በመልካም
ጉረኖ ውስት ይመሰጋሉ፥ በእስራኤልም ተራሮች ላይ በለመለመ
መሰማሪያ ይሰማራሉ። እኔ ራሴ በጎቼን አሰማራለሁ፥
አስመስጋቸውማለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደሆንሁ
ያውቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የጠፋውንም እፈልጋለሁ፥
የባዘነውንም እመልሳለሁ፥ የተሰበረውንም እጠግናለሁ፥
የደከመውንም አጸናለሁ፥ የወፈረውንና የበረታውንም
እጠብቃለሁ፥ በፍርድም እጠብቃቸዋለሁ።» ብሏል። ሕዝ
፴፬፥፲፩-፲፮።
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጎቹን
ፍለጋ የመጣ ቸር እረኛ በመሆኑ፥ «ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ፥ ቸር
ጠባቂ ስለ በጎቹ ነፍሱን ይሰጣል። ጠባቂ ያይደለ፥ በጎቹም
ገንዘቡ ያይደሉ ምንደኛ ግን ተኲላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ
ይሸሻል፥ ተኲላም መጥቶ በጎቹን ይነጥቃቸዋል፥
ይበትናቸዋልም። ምንደኛስ ይሸሻል፥ ስለ በጎቹም አያዝንም፥
(የምእመናን ጥፋት አያሳዝነውም)፥ ምንደኛ ነውና። (ሥጋዊ፥
ዓለማዊ በመሆኑ መናፍቅ ጳጳስ፥ አላዊ ንጉሥ በተነሣ ጊዜ
ይክዳል፤ ምዕመናንን አሳልፎ ይሰጣቸዋል፥ ሐሰተኛ ነውና)።
ቸር ጠባቂ (እውነተኛ መምህር) እኔ ነኝ፥ የእኔ የሆኑትን
መንጋዎቼን (ወልድ ዋሕድ ብለው ያመኑብኝን) አውቃለሁ፥
የእኔ የሆኑትም ያውቁኛል፤ (በእኔ ያመኑብኝ እኔን አብነት
አድርገው መከራን ይቀበላሉ)፤ ብሏል።
፩፥፫፦ #አብ_እኔን_እንደሚያውቀኝ _እኔም_አብን
#አውቀዋለሁ፤
አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ህልዋን ናቸው። አብ በወልድ
በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነው፥ ወልድም በአብ በመንፈስ ቅዱስ
ህልው ነው፥ መንፈስ ቅዱስም በአብ በወልድ ህልው ነው።
«እኔ በአብ እንዳለሁ፥ አብም በእኔ እንዳለ እመኑ፤» ብሏል።
ዮሐ ፲፩፥፲፩። በስም በአካል በግብር ሦስት የሆኑ ሥላሴ
በህልውና አንድ እንደሆኑ ሁሉ በመለኰት፥ በሥልጣን፥
በባህርይ፥ በፈቃድ አንድ ናቸው። «እኔና አብ አንድ ነን፤» ያለው
ለዚህ ነው። ዮሐ ፲፥፴። እንግዲህ፥ አይሁድ በክፋታቸው «ይህ
ከወዴት እንደመጣ፥ ማን እንደሆነ አናውቅም፤» ብለውት
ስለነበረ፥ እናንተ ባታውቁኝ የባህርይ አባቴ አብ ያውቀኛል፥
እንደማለት፥ «አብ እኔን እንደሚያውቀኝ እኔም አብን
አውቀዋለሁ፤» ብሎባቸዋል። ይኸውም፦ «እኔ ልሰቀል ልሞት
መምጣቴን አብ እንደሚያውቅ ሁሉ እኔም የመጣሁበትን
ዓላማ አውቃለሁ፤» ሲል ነው። ለዚህ ነው ከዚያው አያይዞ፥
«ለበጎችም ቤዛ አድርጌ ሰውነቴን አሳልፌ እሰጣለሁ፤»ያለው።
በማቴዎስ ወንጌልም፦ «ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቀው
የለም፤ (ያለ አብ ወልድን በባሕርዩ የሚያውቀው የለም፥
በባሕርይ አንድ ናቸውና)፤ አብንም ከወልድ በቀር፥ ወልድም
ሊገልጥለት ከሚፈቅደው በቀር የሚያውቅ ማንም የለም።
(ያለ ወልድ አብን በባሕርዩ የሚያውቀው የለም)፤» የሚል
አለ። ማቴ ፲፩፥፳፯።
ትንቢት ተነግሮለት፥ ሱባዔ ተቆጥሮለት፥ ወደዚህ ዓለም የመጣ
ቸር እረኛ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ «ከዚህ ቦታ ያይደሉ ሌሎች
በጎችም አሉኝ፤ (በኢየሩሳሌም የሌሉ በአራቱ ማዕዘን ያሉ
ሌሎች አሉኝ)፤ ቃሌንም ይሰሙኛል፤ (ትምህርቴን
ይቀበሉኛል)፤ ለአንድ እረኛ አንድ መንጋም ይሆናሉ። (ለአንድ
ለክርስቶስ አካሉ ይሆናሉ፤ አንድም ለአንድ ሊቀ ጳጳስ አንድ
ማኅበር፥ አንድ ቤተሰብእ ይሆናሉ)፤ ብሎአል። ይህም ወደዚህ
ዓለም መምጣቱ ለቤተ አይሁድ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም
መሆኑን ያስተምረናል።
፩፥፬፦ #ሥልጣን_አለኝ፤
ነፍስንም ሥጋንም ከእመቤታችን ነስቶ (ወስዶ) በተዋሕዶ ሰው
የሆነ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ዓለምን ለማዳን መከራ
የተቀበለው፥ የሞተውም በፈቃዱ ነው። ይህም ይታወቅ ዘንድ፦
«ስለዚህም አብ ይወድደኛል፤» ካለ በኋላ «እንደ ገና አስነሣት
ዘንድ እኔ ነፍሴን እአጣለሁና። ከእኔ ማንም አይወስዳትም፤
ነገር ግን እኔ በፈቃዴ እሰጣታለሁ፥ እኔ ላኖራት ሥልጣን አለኝ፤
(ነፍሴን በገነት፥ ሥጋዬን በመቃብር ላኖራቸው ሥልጣን አለኝ)፤
መልሼ እወስዳት ዘንድ ሥልጣን አለኝ። (ነፍሴን ከሥጋዬ
አዋሕጄ በማስነሣት፥ በዕርገት፥ በየማነ አብ፥ በዘባነ ኪሩብ
አስቀምጣት ዘንድ ሥልጣን አለኝ)፤ ብሏል። መከራውን፥
ትንሣኤውን እና ዕርገቱን በተመለከተም ነቢያት አስቀድመው
ተናግረውታል።
- «እርሱ ስለ ኃጢአታችን ቈሰለ፥ ስለበደላችንም ታመመ፤
የሰላማችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቊስል እኛ
ተፈወስን። . . . እግዚአብሔርም ስለ ኃጢአታችን ለሞት
አሳልፎ ሰጠው።» ኢሳ ፶፫፥፭-፮።
- «እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ፤» መዝ
፸፯፥፷፭።
- «እግዚአብሔር በእልልታ፥ ጌታችንም በመለከት ድምፅ
አረገ።» መዝ ፵፮፥፭።
በመጨረሻ የምንመለከተው፥ ጌታችን አምላካችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «እውነተኛ የበጎች በር እኔ
ነኝ፤»ያለበትን ዋና ምክንያት ነው። ይኸውም በር የተከፈተለት
እንደሚገባ፥ የተዘጋበት ደግሞ በአፍአ እንደሚቀር ሁሉ፥
በጌታችን ያመነ የመንግሥተ ሰማያት በር ይከፈትለታል፥
ያላመነበት ደግሞ በሩ ተዘግቶበት በአፍአ እንደሚቀር ነው።
በመሆኑም በር የተባለው በእርሱ ላይ ያለን እምነት እንደሆነ
ከትርጓሜው እንረዳለን። የበሩንንም ቊልፍ ለቅዱሳን
አስረክቧል። ይኸውም ይታወቅ ዘንድ ቅዱስ ጴጥሮስን «አንተ
ብፁዕ ነህ፥ በሰማይ ያለው አባቴ ነው እንጂ ሥጋና ደም ይህን
አልገለጠልህምና። እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ዐለት ነህ፥ በዚያች
ዐለት ላይም ቤተክርስቲያኔን እሠራታለሁ፥ የሲኦል በሮችም
(ደጅ ጠባቂ አጋንንት) አይበረቱባትም። የመንግሥተ ሰማያትም
መክፈቻ እሰጥሃለሁ፥ በምድር የምታስረው በሰማይ የታሰረ
ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው በሰማይ የተፈታ ይሆናል።»
ብሎታል። ማቴ ፲፮፥፲፯-፲፱። ሌሎችን ግን፦ «መንግሥተ
ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ ወዮላችሁ! እናንተም
አትገቡም፥ የሚገቡትንም ከመግባት ትከለክላላችሁ።»
ብሏቸዋል። ማቴ ፳፫፥፲፬። ስለዚህ በር በተባለ በኢየሱስ
ክርስቶስ ፈጽመን ልናምን ይገባል። እናምናለን ማለት ብቻም
ሳይሆን የምናምነውስ ማን እና ምን ብለን ነው ማለትም
ያስፈልጋል። ምክንያቱም ስሙን እየጠሩ፥ እንምንበታለን
እያሉ፥ ስለ እርሱ የሚያስተምሩት ትምህርት ፈጽሞ መስመር
የለቀቀባቸው ብዙዎች ናቸውና። የእኛ ግን መስመሩን
የጠበቀው ፍጹም እምነታችን እንደሚከተለው ነው።
፩ኛ፦ #ፈጣሪ_ነው፥ ብለን እናምንበታለን። «ሁሉም በእርሱ
ሆነ፥ (በእርሱ ተፈጠረ)፥ ከሆነውም (ከተፈጠረውም) ሁሉ ያለ
እርሱ ምንም የሆነ የለም። ዮሐ ፩፥፫።
፪ኛ፦ #የፈጠረውን_ፍጥረት_የሚገ ዛ_የባሕርይ አምላክ ነው።
«የእግዚአብሔር ልጅ እንደመጣ፤ እውነተኛም የሆነውን
እግዚአብሔርን እናውቅ አንድ ልቡናን እንደሰጠን እናውቃለን፤
እውነተኛውም በሆነው በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ
በማመን እንኖራለን፤ እርሱም እውነተኛ አምላክና የዘለዓለም
ሕይወት ነው።» ፩ኛ ዮሐ ፭፥፳።
፫ኛ፦# ፈጣሪ፥ የባሕርይ አምላክ በመሆኑም እግዚአብሔር
ነው። «በመጀመሪያ ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ
(በፈጣሪነት ከአብ ተካክሎ) ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ።
ይህም በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ (በፈጣሪነት
ከመንፈስ ቅዱስም ተካከልሎ) ነበረ። . . . ያም ቃል ሥጋ ሆነ፥
በእኛም አደረ፤ (ነፍስንና ሥጋን ነስቶ በተዋሕዶ ሰው ሆነ)።»
ዮሐ ፩፥፩፣ ፩። «አሁንም በገዛ ደሙ የዋጃትን
የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ትጠብቁ አንድ መንፈስ ቅዱስ
እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ
ተጠንቀቁ፤» የሐዋ ፳፥፳፰።
፬ኛ፦ #ወልድ_በተለየ_አካሉ_ከሰ ማይ_ወርዶ፥ በተዋሕዶ ሰው
ሆኖ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በመወለዱ
በሥልጣን ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ አላነሰም። «እኔና አብ አንድ
ነን፤» ዮሐ ፲፥፴። በሕልውናም አንድ ነው። «እኔ በአብ
እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑ፤» ዮሐ ፩፥፲፩። «እኔን
የሚጠላ አቤን ይጠላል። . . . አሁን ግን እኔንም አባቴንም
አይተዋል፥ ጠልተውማል።» ዮሐ ፲፭፥፳፫።
፭ኛ፦ #ከእመቤታችን_ከቅድስት_ድ ንግል
#ማርያም_ከሥጋዋ_ሥጋ_ከነ ፍሷም_ነፍስ_ነስቶ የተወለደ
እርሱ የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ ነው። «እነሆም፥ በእርሱ
ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው።» ማቴ ፫፥፩።
፮ኛ፦ #ሰው_የሆነው_በተዋሕዶ_ነ ው፥ በመሆኑም ከተዋሕዶ
በኋላ ሁለትነት የለም፥ ይህ የሥጋ ነው፥ ይህ ደግሞ የመለኰት
ነው ተብሎ መከፈል የለበትም። አብ «ልጄ ነው፤» ያለው
በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ የሆነውን ኢየሱስ
ክርስቶስን ነው። ወደ ሠርግ ቤት የተጠራውም ውኃውን ወደ
ወይን ጠጅ የለወጠውም ከተዋሕዶ በኋላ ሁለትነት የሌለበት
አንድ እርሱ ነው። ዮሐ ፪፥፩-፲። ሥጋን እንደተዋሐደ
ለማጠየቅ «አልዓዛርን የት ቀበራችሁት?» ያለም ከሞት
ያስነሣም አንድ እርሱ ነው። ዮሐ ፲፩፥፴፬፣፵፫። ከዚህም ሌላ
መቃብሩ ሳይከፈት ከመቃብር የወጣው (ሞትን ድል አድርጐ
የተነሣው) አንዱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ማቴ
፳፯፥፷፮፣፳፰፥፩። በተዘጋ ቤትም በሩ ሳይከፈት ከአንዴም ሁለት
ጊዜ የገባው አንዱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ዮሐ ፳፥፲፱፣፳፮።
፯፦ #ኢየሱስ_ክርስቶስ_ፈራጅ_ ዳኛ ነው። «አሁንም
በእግዚአብሔር ፊትና በመንግሥቱ በሚመጣበት ጊዜ፥
በሕያዋንና በሙታን ይፈርድ ዘንድ ባለው በጌታችን በኢየሱስ
ክርስቶስ እመክርሃለሁ። . . . እንግዲህስ የጽድቅ አክሊል
ይቆየኛል፥ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው እግዚአብሔር በዚያ
ቀን ለእኔ ያስረክባል።» ፪ኛ ጢሞ ፬፥፩፣፰።
፰፦ #እኛ_የምንለምነውን_በቅዱ ሳንም_ጸሎት
የምናስለምነውን ሁሉ እርሱ ያደርገዋል። «እኔ ወደ አብ
እሄዳለሁና፤ አብ በወልድ ይከብር (ይገለጥ) ዘንድ በስሜ
የምትለምኑትን ሁሉ አደርግላችኋለሁ። በስሜ የምትለምኑት
ነገር ቢኖር ያን አደርግላችኋለሁ።» ዮሐ ፲፬፥፲፪-፲፫።
እንግዲህ ሥጋን መዋሐዱን ለማጠየቅ የተናገረውን ቃል፥
አብነት ለመሆንም የሠራውን የትህትና ሥራ ሁሉ በትርጓሜ
እያስታረቅን በትክክለኛው እምነት ጸንተን ልንቆም ይገባናል።
በአምልኮታችን ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስን፥ እንደ ቅዱስ
እስጢፋኖስ፥ ከአብ ተካክሎ ልናየው ይገባል እንጂ ዝቅ
ልናደርገው አይገባም። «እነሆ ሰማይ ተከፍቶ፥ የሰው ልጅም
በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ፤» ይላል። ጸሎታችንም፦
ጌታዬ ኢየሱስ ሆይ፥ ነፍሴን ተቀበል፤ . . . አቤቱ ይህን ኃጢአት
አትቊጠርባቸው፤» የሚል መሆን አለበት። የእግዚአብሔር
ቸርነት፥ የድንግል ማርያም አማለጅነት አይለየን። አሜን።

=>+*"+<+>+ ሰርግ በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትምህርት +<+>+"*+

ሰርግ በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትምህርት
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ቅዱስ ጳውሎስ ለቈላስይስ ሰዎች
በላከው መልእክት ም.፬፥፲፪ ላይ ያለውን ኃይለ ቃል
በተረጎመበት ፲፪ኛው ድርሳኑ በዘመኑ የሚፈጸመውን የሰርግ
ሥርዐት መሠረት በማድረግ ሰርግን አስመልክቶ ሰፋ ያለ
ትምህርትን ሰጥቶአል ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በሰርግ
ምክንያት የሚወጡትን ወጪዎችና ግርግርና ሁካታ አጥብቆ
የሚቃወም አባት ነው ፡፡ በዚህም ጽሑፍ ይህን ወደማስተዋል
ልንመጣም እንችላልን ፡፡ መልካም ንባብ
ስለዚህ እንዲህ ብሎ ያስተምራል ፡- ትዳር ምንድን ነው?
ትዕይንት(ትያትር) ነውን ? አይደለም፡፡ ምንም እንኳ እናንተ
ለትዳርና ለምሳሌው አክብሮት ባይኖራችሁ ትዳር ግሩም
ምሥጢርና የታላቅ መንፈሳዊ ምሥጢር ምሳሌ ነው ፡፡ ቅዱስ
ጳውሎስ ስለዚህ ሲያስተምር “ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው”
ይልና ጨምሮ “እኔ ግን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን
እላለሁ” ይላል ፡፡(ኤፌ.፭፥፴፪) ጋብቻ የቤተ ክርስቲያንና
የክርስቶስ ምሳሌ ነው ፤ እንዲህ በከበረ ምሥጢር ላይ
ዳንኪረኞችን በመጋበዝ ዝሙትን ታስተዋውቁበታላችሁን ?
ነገር ግን ከእናንተ መካከል አንዱ እኔን፡- እንዲህ ስትል ደናግል
ወይም ያገቡት አይጨፍሩ እያልክ ነው ፤ እንግዲያ እነርሱ በዚህ
ሰርግ ላይ ካልጨፈሩ ማን ሊጨፍር ነው ? ብሎ ሊጠይቅ
ይችላል ፡፡ ማንም አይጨፍር ነው መልሴ ፡፡
በአሕዛብ ዘንድ ይህን በመሰሉ ሥርዐቶቻቸው ዳንኪረኞች
ዳንኪራቸውን ያቀርባሉ፡፡ በእኛ ግን ማንኛውም ምሥጢራት
ሲከናወኑ በጸጥታ፣ በትሕትናና በጥሩ ሥነምግባር እንዲሁም
በመልካም ሥርዐት ነው፡፡ ይህ የጋብቻ ሥርዐት አመንዝሮች
ከተጠሩበት እግዚብሔርን የማይፈሩ ከተጋበዙበት እንዴት ብለን
ነው መንፈሳዊ ጋብቻ ብለን ልንጠራው የምንችለው ? እንዲህ
ከሆነ እንዴት ተብሎ ነው ሁለቱ አካላት አንድ ሆነዋል ልንል
የምንችለው ?
ክርስቶስ በተገኘበት ጋብቻ ግን ዳንኪራ የለም የእምቢልታም
ድምፅ አይሰማበትም፡፡ ነገር ግን ግሩም የሆነ ጸጥታ
የሰፈነበት፣ በታላቅ መንፈሳዊ ሥርዐት የሚከናወን ነው፡፡ በዚህ
ሥርዐት አንድ አካል ወደመሆን ሲመጡ አንድነታቸው ሕይወት
አልባ ፍጥረታት እንደሚኖራቸው አንድነት ወይም በዚህ ምድር
የሚታየውን ዓይነት አንድነት አይደለም፡፡ ነገር ግን
የእግዚአብሔር አርዓያና አምሳል ሆነው አንድ ይሆናሉ፡፡ ይህ
ታላቅ የሆነ ምሥጢር በሚከናወንበት ሥፍራ እንደ አራዊት
ታላቅ ሁካታና ረብሻ እንዲሁም ነፍስን የሚያሳድፉ ታላቅ የሆነ
በደል ይፈጸማልን ?
ሁለቱ አንድ አካል በመሆናቸው በዚህ ያለውን የፍቅርን
ምሥጢር አስተውል ፡፡ እነዚህ ሁለት አካላት ሁለትነታቸውን
ይዘው የሚቀጥሉ ከሆነ ብዙ ሊሆኑ አይችሉም ፡፡ ነገር ግን
አንድ ወደመሆን ሲመጡ ብዙዎች ይሆናሉ ፡፡ ከዚህ ምን
እንማራለን ? የትዳርን ታላቅነት አይደለምን ? ሥላሴ ሁለት
የሆነው አካል አንድ አድርጎ ፈጠረው ስሙንም ሰው አለው፡፡
ይህን አንድ የሆነው አካልንም ሁለት በማድረግ ገለጠው ፡፡
ምንም እንኳ እነዚህ አካላት ሁለት ቢሆኑ የእግዚአብሔር ፈቃድ
ግን አንድ ይሆኑ ዘንድ ነበር ፡፡
በዚህም ምክንያት አንዱ አምሳሉን ለመውለድ ብቻውን ብቁ
እንዲሆን አላደረገውም ፡፡ ስለዚህ ከተቃራኒው አካል ጋር
አንድነትን ላልመሠረተ ሰው አንድ አካል የሚባለው ስያሜው
አይሰጠውም ነገር ግን የሌላኛው ግማሽ አካል ይባላል ፡፡
ለዚህም ምስክሩ ልጅን መውለድ አለመቻሉ ነው ፡፡ ይህ
እግዚአብሔር አስቀድሞ የሠራው ሥርዐት ነው፡፡ የጋብቻን
ምሥጢር አስተዋላችሁን ? አስቀድሞ አንድ አድርጎ ፈጠራቸው
በኋላም ነጣጠላቸው ፤ እንደገና ሁለት የነበሩትን እነዚህን
ወገኖች ወደ አንድነት አመጣቸው ፡፡ እንዲህም አድርጎ
ስለሠራው ሰው በትዳር አንድ ከሆኑ ወገኖች እንዲፈጠር ሆነ ፡፡
ባልና ሚስት ሁለት አካላት አይደሉም ነገር ግን አንድ አካል
ናቸው ፡፡…. ይህን “ሰውን በአርዓያችንና በአምሳላችን እንፍጠር
…ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” (ዘፍ.1፡27) በሚለው ቃል
ማረጋገጥ ይቻላል ፡፡ ባል ራስ ነው ፤ ሚስት ደግሞ ቀሪው
አካል ናት ፡፡ ስለዚህ አንዱ የደቀመዝሙርነት ማዕረግ ሲኖረው
አንዱ የመምህርነት ቦታ ይይዛል አንዱ መሪ ሲሆን ሌላው
ደግሞ ታዛዥ አደረገው ፡፡ ሔዋን ከአዳም ጎን ትገኝ እንጂ ወደ
ኋላ መለስ ብለን የእርሱዋን ልደት ስንመረምረው አንድ አካል
እንደነበሩ ማስተዋል እንችላለን ፡፡በዚህ ምክንያት አንድ አካል
እንደሆኑ ለማስረዳት ሲል እግዚአብሔር አምላክ ሴቲቱን ረዳት
አላት፡፡ (ዘፍ.2፡18) በአንድነት ከመኖራቸውና አባትና እናት
ከመሆን ባለፈ አንድ አካል በማድረግ አከበራቸው፡፡ (ዘፍ.2፡
24)
በሌላ መልኩ ደግሞ አባት ወንድ ልጁ ወይም ሴት ልጁ
የራሳቸውን አካል አግኝተው በመጣመራቸው እጅግ ደስ
ይሰኛል፡፡ አባት ምንም ሀብት የተረፈው ባለጠጋ ቢሆን ወንድ
ልጁ ወይም ሴት ልጁ ያላገቡ ከሆኑ ውስጡ ምንም ዓይነት
መረጋጋት አይኖረውም፡፡ ይህን ታግሶ መኖርም አይቻለውም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ምንም ልጅ ከእናቱ አካል ተከፍሎ
የተወለደ ቢሆን በዚህ ምድር ዘሩ እንዲቀጥል ብቻውን በቂ
አይደለም፡፡ ስለዚህም በራሱ ሙሉ አይደለም ማለት ነው፡፡
ስለዚህም ነቢዩ ሚልክያስ “እግዚአብሔር የሕይወትን መንፈስ
አንድ አድርጎ ጠብቆልን የለምን? እርሱም የሚፈልገው
ምንድን ነው? ዘር አይደለምን? (ሚል.፪፥፲፭) ይለናል፡፡
እንዴት ነው ታዲያ አንድ ሥጋ ወደ መሆን የሚመጡት ? እጅግ
ንጹሕ የሆነን ወርቅን ማግኘት ከፈለግህ ወርቅህን ከሌላ
ወርቅ ጋር ትቀይጠዋለህ፤ ከእነዚህም አንድነት ልዩ የሆነ
ወርቅ ይገኛል፡፡ በዚሁ መልክ እናት በደስታ ዘርን ተቀብላ
ከራሱዋ ጋር በማዋሐድ፣ ፅንሱን በመመገብና እንክብካቤ
በማድረግ ሰው ሆኖ ወደዚህ ዓለም እንዲመጣ የራሱዋን ድርሻ
ትወጣለች፡፡ልጅ እንደ ድልድይ ነው ፡፡ በእርሱም ምክንያት
ሦስቱ አንድ ሥጋ ይባላሉ ፡፡ ልጅ ሁለቱ አካላት ፍጹም አንድ
እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ፡፡ በመካከላቸው ባለው ታላቅ ወንዝ
ምክንያት የተለያዩ ከተሞች በወንዙ ላይ በሚሠራው ድልድይ
ምክንያት ሁለት መሆናቸው ቀርቶ አንድ እንዲሆኑ እንዲሁም
ልጅም እንዲህ ነው ፡፡
ልጅ በፊት በባልና በሚስት መካከል የተፈጠረውን አንድነት
ይበልጥ ያጠናክረዋል ፡፡ ለባልና ሚስት ድልድይ የሆነው ልጅ
የሁለቱ ተዋሕዶ ውጤት ነውና ፡፡ ራስና ቀሪው አካል በአንገት
አንድ እንዲሆን ፣ እንዲሁ ልጅም በባልና በሚስት መካከል ሆኖ
በእነርሱ መካከል ያለውን አንድነት ይበልጥ ያጠብቀዋል ፡፡
ከልዩነታቸው ይልቅ አንድነታቸውን በልጅ ምክንያት ይበልጥ
እየጠበቀ ይመጣል ፡፡
እንዲሁም ዘማርያን በአንድነት ሲዘምሩ ዝማሬው አንድ ሆኖ
ይወጣል ፡፡ ወይም ሁለት ወገኖች እጃቸውን እርስ በእርሳቸው
ቢያቆላልፉ ከእንግዲህ አንድ እንጂ ሁለት አይደለንም
ማለታቸው እንደሆነ እንዲሁ ባልና ሚስትም በአንድነታቸው
በሚፈጠሩት በልጅ በኩል ፍጹም የሆነ አንድነትን ይመሠርታሉ
፡፡ ስለዚህ ጌታችን ግሩም በሆነ ቃሉ “ሁለቱም አንድ ሥጋ
ይሆናሉ አለ” በተለይ በልጆቻቸው ፡፡ እንዲህ ሲባል ባልና
ሚስት ልጅ ካልወለዱ ሁለት እንደሆኑ አይቀጥሉም ማለት
ነውን ? በፍጹም አይደለም ፤ ሁለቱ በሥጋ ሲተባበሩ አንድ አካል
ወደ መሆን ይመጣሉ ፡፡ የሽቶ ዘይትን ከሌላ የሽቶ ዘይት ጋር
ሲደባልቁት አንድ እንዲሆኑ ከተቀየጡም በኋላ አንድ የሽቶ
ዘይት እንዲሆኑ እንዲሁ በዚህም እንዲሁ ነው ፡፡
እኔ አሁን እንዲህ በግልጽ ስለዚህ ጉዳይ በመናገሬ አንዳንዶች
ነውር ነው በማለት ትምህርቴን እንደሚጠየፉት እረዳለሁ ፡፡
ለዚህ ምክንያቱ ምንድነው ? ይህን አሁን የምናገረውን እንደ
ብልግና ንግግር ስለሚቆጥሩት ነው ፡፡እነዚህ ወገኖች በትዳር
ውስጥ የሚፈጠረውን እንደዚህ ላለው አንድነት ልዩ የነቀፋ ስም
ይሰጡታል (ብልግና ይሉታል) ፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ጳውሎስ
“መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ
ይሁን”(ዕብ.፲፫፥፬) ብሎ አስተምሮናል ፡፡
ስለምን እናንተ ክቡር የሆነውን እንደ ነውር ፣ ንጹሕ የሆነውን
እንደ ርኩስ ትቆጥሩታላችሁ ? ይህ ጋብቻን እንደ ርኩሰት
የሚቆጥሩትና በራሳቸው አካል ላይ ዝሙትን የሚፈጽሙ
የከሃድያን አመለካከት ነው፡፡ ስለዚህም ነው ይህን ክፉ
አስተሳሰብ ለማጥራትና ወደ ቀድሞው ክብሩ ለመመለስ ስል
በዚህ መልክ ያስተማርኩት፡፡ በዚህም እስተምህሮ የከሃድያን
አፍ ይዘጋል፡፡
እነርሱ የእግዚአብሔርን ድንቅ ስጦታንና የልደታችን መሠረት
የሆነውን ተራክቦን ሲነቅፉት ይሰማሉ፡፡
ይህን የመገኛችን ምንጭ የሆነውን ተራክቦ እንደ ቆሻሻና
እንደማይጠቅም ረብ የለሽ ከንቱ ነገር አድርገው ይቆጥሩታል፡፡
ስለዚህ እኛ ይህን አስተምህሮ ከዚህ ዓይነት አመለካከት ንጹሕ
ልናደርገው ይገባናል፡፡ተወዳጆች ሆይ ይህ ጉዳይ ሲነሣ
እንደሚጠየፉት ከሃዲያን እንድንሆን አልሻም፤ ይልቁንስ
ከእነርሱ አጸያፊ ሥራ ትሸሹ ዘንድ እመክራችኋለሁ፡፡ ነገር ግን
በዚህ እነርሱን የምትመስሉዋቸው ከሆነ በቀጥታ
እግዚአብሔርን እየተሳደባችሁ ነው፡፡
ትዳር ለቤተ ክርስቲያን የተፈጸመላት ምሥጢር ምሳሌ
እንደሆነ ላስረዳችሁን? ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
ቤተ ክርስቲያንን የራሱ ሲያደርጋትና በመንፈሳዊ ተዋሕዶ
ከእርሱዋ ጋር አንድ ሲሆን ቅዱስ ጳውሎስ “እንደ ንጽሕት
ድንግል” ይልና “እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ
አጭቻችኋለውና” ይለናል፡፡ (፪ቆሮ.፲፪፥፪) ታዲያ እኛ ምን
ሆንን ? የእርሱ የአካል ሕዋሳቶችና “ሥጋው” ሆንን፡፡ ይህን
ሁሉ በማስተዋል ታላቅ ምሥጢር የሆነውን ትዳርን ከማቃለል
እንቆጠብ፡፡ ሰርግ ማለት የክርስቶስ በሰዎች መካከል
ሰለመገኘቱ የሚመሰልበት ታላቅ ምሥጢር ነው፡፡ ታላቅ
የሆነው ይህ ምሥጢር በሚፈጸምበት ቦታ ስካር የሚገባ
ነውን? ንገረኝ የንጉሥ ምስል በቆመበት ስፍራ ሆነህ እርሱን
ማዋረድ ትጀምራለህን? ይህን ፈጽሞ አታደርገውም፡፡
አሁን ግን ሰርግ ሲሲረግ ሰርጉ ለተመሰለበት ምሳሌ ተገቢውን
አክብሮት ከመስጠት ይልቅ ቦታውን የኃጢአት መፍለቂያ
ምንጭ አድርገነዋል፡፡ ሥርዐቱ ሙሉ ለሙሉ ተለውጦ
ሕገወጥ ሥራዎች የሚፈጸሙት ሥርዐት ሆኗል፡፡ ቅዱስ
ጳውሎስ “የሚያሳፍር ነገርም የስንፍና ንግግርም ወይም ዋዛ
የማይገቡ ናቸው” አላለንምን? እንዲሁም “ለሚሰሙት ጸጋን
ይሰጥ ዘንድ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም
በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ
አይውጣ፡፡” (ኤፌ.፭፥፬፤፬፥፳፱) ብሎ አላስተማረንምን? አሁን
ግን በዚህ ታላቅ በሆነ ምሥጢር ላይ የስንፍና ንግግር፣ ዋዛ
ፈዛዛ ነገሮች፣ ፌዝና ቀልዶች ሞልተውበታል፡፡
እነዚህ ከንቱ ነገሮች በቀላሉ የሚቀርቡም አይደሉም እኮ
እነዚህ ከንቱ ነገሮች እንደ ጥበብ ተቆጥረው በአቅራቢዎቻቸው
ተቀናብረው በሰርጉ ለታደሙት ይቀርባሉ፡፡ ይህንንም
ለሚያቀርቡ ሰዎችም ታላቅ ክብርና ምስጋና ይሰጣቸዋል፡፡
ይገርማል ኃጢአት እንደ ጥበብ ተቆጠረ፡፡ ከዚህም በላይ
ኃጢአትን ለእኛ የሚያስተዋውቁንን ወገኖች ትዕይንት
የምንከታተለው ትኩረት ሰጥተንና በጸጥታ ነው፤ ከአንደበታቸው
የሚያወጡትንም ቃል በአጽንዖት በመስማት ጭምር እንጂ
እንዲያው በከንቱ አናዳምጣቸውም፡፡ ስለዚህ ዲያብሎስ በዚህ
የሰርግ ቤት ለእርሱ ወታደሮች ይሆኑ ዘንድ ሠራዊቶችን
ይመለምላል፡፡ ስካር ባለበት ቦታ ዝሙት አለ፡፡ ከንቱ ንግግር
ባለበት ቦታ ሰይጣን የራሱን አስተዋጽኦ ለማድረግ ይመቸዋል፡፡
እስቲ ንገረኝ እንዲህ በሆነ ቦታ ሰይጣን እንዲገኝ እየጋበዝህ
ክርስቶስ የሚገኝበትን ምሥጢር እየፈጸምኩ ነው ትላለህን?
አንተ እኔን ለዚህ ነገር ጠንካራ ተቃዋሚ እንደሆንኩ አድርገህ
ትቆጥረኛለህ ፡፡ ከዚህ ጥመትህ ትድን ዘንድ አንተን በጽኑ
የሚገሥጽህንም ሰው እንዲህ እንድትመለከተው አውቃለሁ ፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ አንተን “የምትበሉም የምትጠጡም ብትሆኑ
ወይም ማናቸውም ተግባር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር
ክብር አድርጉት”(፩ቆሮ.፲፥፴፩ ) አላለህምን ? አንተ ግን
ሥራዎችህን ሁሉን ራስህን ለማዋረድና የሰውን ልጅ ለሚጎዱ
ነገሮች ታውላዋለህ ፡፡ ነቢዩስ “ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ
በረዓድም ደስ ይበላችሁ”(መዝ.፪፥፲፩) አላለህምን ? አንተ
ግን ሥርዐት አልባ ሆነህ ትመላለሳለህ ፡፡
በአንድ ጊዜ ደስታውንና ጥንቃቄውንም ማስኬድ
ትፈልጋላችሁን? አጥንትን የሚያለመልም መዝሙርን
መስማትስ ትሻላችሁን? በእርግጥ ከመዝሙሮች ሁሉ የሚልቅ
መዝሙርን ልትሰሙ ትችላላችሁ፡፡ እናንተ ግን አትፈቅዱም፤
ብትፈቅዱ ግን ሰይጣናዊ ዘፈኖች ከመስማት ይልቅ መንፈሳዊ
ዝማሬን ለመስማት ትበቃላችሁ፡፡ የመዘምራንን ግሩም የሆነ
መጓደድ መመልከት ትሻላችሁ? እነሆ የመላእክት ዝማሬና
መጓደድ፡፡ እንዴት ሆኖ ነው የእነርሱን ዝማሬን መስማት
በልዑል ፊት መጓደዳቸው መመልከት የሚቻለው ብሎ
የሚጠይቀኝ ካለ “እነዚህን ግሳንግሶችን ከነአካቴው ከተውክና
በሰርግህ ክርስቶስ እንዲገኝ ከፈቀድክ ይህ ይሆናል፡፡ ክርስቶስ
በሰርግህ የታደመ ከሆነ መላእክትም ከእርሱ ጋር በሰርግህ
ይገኙልሃል፡፡
ከአንተ ዘንድ ፈቃዱ ካለ እርሱ በአንተ ሰርግ መገኘት ብቻ
አይደለም ውኃውን ወደ ወይን ጠጅነት በመቀየርም ሰርግህን
ያደምቅልሃል፡፡ እንደ ውኃ ቀዝቃዛና ወራጅ የሆነውን የዚህን
ዓለም ደስታና ፈንጠዝያ አጥፍቶ መንፈሳዊ ደስታን
ከሚያጎናጽፈው ከዚህ ተአምር በላይ ምን ድንቅ ተአምር አለ!!
ይህ ነው ውኃውን ወደ ወይንነት የመቀየሩ ትርጉም፡፡ እንቢልታ
ነፊዎች ባሉበት ክርስቶስ ፈጽሞ አይገኝም፡፡ እርሱ በዚህ ሰርግ
ቢገኝ እንኳ መጀመሪያ ይህንን አስወግዶ ነው፡፡ ከዚያም የራሱን
ተአምርን ይፈጽማል፡፡ ከዚህ የሰይጣን መሳሪያ ከሆነ እቢልታ
በላይ ምን የሚጠላ ነገር አለ? ሁሉ በሥርዐት ካልሆነ ምንም
ነገር ያለጥቅም ይሆናል፡፡ ድካማችን ሁሉ ያለፍሬ ይቀራል
እኛንም ወደ ውርደት ይጥለናል፡፡
ከመልካም ሥነምግባር የበለጠ አስደሳች ነገር የለም፣ ሥርዐት
ወዳድ ከመሆን የበለጠ ጣፋጭ የሆነ ነገር የለም፣ ጽድቅ
ለመፈጸም ቆራጥ ከመሆን የበለጠ ተወዳጅ ነገር የለም፡፡
ሁሉም ሥርዐቶቻችን ልክ እኔ ስለጋብቻ ሥነ ሥርዐት
ባስተማርኩት መልክ ይሁኑ፡፡ እንዲህ ከሆነ ደስተኛ ልንሆን
እንችላለን፡፡
ነገር ግን ጋብቻን ሊያደርግ የሚሻ ሰው ከማን ጋር ጋብቻውን
መፈጸም እንዳለበት ይጠንቀቅ፡፡ ሴት ልጅ ያለችው ሰው
አስቀድሞ እውነተኛና እርሱዋን ሊንከባከባት የሚችል ባልን
ሊፈልግላት ይገባል፡፡ እንዲህ ዓይነት ወንድ ለአካል ራስ
እንዲሆን ሊመረጥ ይገባዋል፡፡ ለእርሱ ስትሰጥም እንደ ባሪያ
አድርጎ ሊይዛት ሳይሆን እንደ ልጁ ሊያያት ሊሆን ይገባል፡፡
ሀብት ስላለው ወይም ከከበረ ቤተሰብ በመሆኑ ወይም ሰፊ
ግዛት ስላለው እርሱን ለልጃችሁ ባል ይሆን ዘንድ አትምረጡ፡፡
ነገር ግን በነፍሱ ትሑት፣ አስተዋይ፣ ቅንነት ያለውና
እግዚአብሔርን የሚፈራ የሆነን ሰው ለልጃችሁ ባል ይሆን
ዘንድ ምረጡ፡፡ እንዲህ ከሆነ የምታፈቅሩዋት ልጃችሁ በደስታ
ልትኖር ትችላለች፡፡ ባለጠጋ ሆኖ በምግባሩ ግን ብልሹ የሆነን
ሰው ለልጃችሁ ባል ይሆን ዘንድ ያጫችሁት ከሆነ እርሱዋን
አለመጥቀማችሁ ብቻ ሳይሆን እርሱዋን ነጻ ሰው ከማድረግ
ይልቅ የእርሱ ባሪያ በማድረግ ትጎዱአታላችሁ፡፡ ልጃችሁ
የእርሱ ሚስት በመሆኑዋ ምክንያት በምታገኛቸው ሀብት ደስ
ከመሰኘት ይልቅ እርሱዋን እንደ ባሪያ ቆጥሮ በእርሱዋ ላይ
የሚያደርስባት በደል የከፋ ይሆናል፡፡
እንዲህ ዓይነት ድርጊትን ከመፈጸም ትቆጠቡ ዘንድ
እለምናችኋለሁ ፡፡ ነገር ግን ከእርሱዋ ጋር ተቀራራቢ ኑሮ
ያለውን ለልጃችሁ ባል ይሆን ዘንድ ታጩ ዘንድ እመክራችኋለሁ
፡፡ ይህ ባይሆን ምንም ሀብት ለሌለው ነገር ግን በጎ ሕሊና
ላለው ሰው ትድሩዋት ዘንድ አሳስባችኋለሁ ፡፡ እንዲህ
በማድረጋችሁ ልጃችሁን ሌላው ቢቀር ለአንድ ጌታ ልጃችሁን
እንደባሪያ ከመሸጥ ተቆጥባችሁ በትክክለኛው ትርጉም እንደ
ባል ሊሆናት ለሚችል ሰው መስጠት ይቻላችኋል ፡፡
ለልጅህ ባል የሚሆናትን ጥሩ ሥነ ምግባር የተላበሰውን ሰው
በጥንቃቄ መርምረህ በማግኘት ልትድራት ስትዘጋጅ ክርስቶስ
ኢየሱስ በጋብቻው ሥነ ሥርዐት ላይ እንዲገኝልህ ጥራው፡፡
በዚህ የደስታ ቀንህ እርሱን በእንግድነት እንዲገኝ ስለጋበዝከው
ቅር አይሰኝም፡፡ ምክንያቱም እርሱ የሚገኝበት ምሥጢር
ነውና፡፡ አዎን ከዚሀ ይልቅ ግን አስቀድመህ ለልጅህ ባል
አድርገህ ያጨኸውን ሰው እርሱ እግዚአብሔር ተወዳጅ ባል
ያደርገው ዘንድ ለምነው፡፡
የአብርሃም ባሪያ እንኳ ያላደረገውን አስከፊ ድርጊት ከማድረግ
ግን ራስህን ጠብቅ፡፡ እርሱ በጌታው በአብርሃም በተላከ ጊዜ
እግዚአብሔርን መንገዱን ያቀናለት ዘንድ ለምኖት ነበር፡፡
እንዲህ በማድረጉም ሁሉን ነገር ሰመረለት፡፡ እንዲሁ አንተም
ለልጅህ ባልን በመፈለግ አእምሮ ቢባክን ወደ እግዚአብሔር
“ጌታ ሆይ አንተ የፈቀድከውን አድርግ” ብለህ ጸልይ፡፡ ለእርሱን
እንዲህ በማለት ፈቃድህን አሳልፈህ ስጠው፡፡ በዚህ መልክ
ለእርሱ ክብርን ስጥ፤ እርሱም በምላሹ ፈቃድህን በመፈጸም
ያከብርሃል፡፡ በእርግጥ አንተን ሁለት ሥራዎች ይጠብቁሃል፡፡
እነርሱም ፈቃድህን ለእርሱ ሙሉ ለሙሉ መስጠትና፣ እርሱ
የመሰከረለትን በጥሩ ሥነ ምግባር የታነጸውን ሰው መሻት
ናቸው፡፡
የልጅህን ሰርግ ለመሰረግ በምትዘጋጅበትም ጊዜ እቃዎችንና
ልብሶችን ለመዋስ ስትል ቤት ለቤት አትዙር፡፡ ምክንያቱም
ሰርጉ የሚፈጸመው ትዕይንትን ልታቀርብ ወይም የልጅህን
ቁንጅና ልታሳይበት አይደለምና፡፡ በመሆኑም ሰርግህን
ልትፈጽም በምትዘጋጅበት ጊዜ ባለህ ነገር ብቻ ቤትህ
ለማስዋብ ሞክር፡፡ በመቀጠል ጎረቤቶችህን ወዳጆችህንና
የቅርብ ዘመዶችህን ጥራ፡፡ እንዲሁም ጥሩ ባሕርይ አላቸው
የምትላቸውን ሰዎች በሰርጉ እንዲታደሙልህ ጋብዝ፡፡
ሙዚቀኞችን ግን ፈጽመህ አትጥራ ለእነርሱ የምታወጣው
ወጪ በራሱ ከፍተኛና ሊሆን የማይገባ ነው፡፡
ከእነዚህ ሁሉ አስቀድሞ ግን ክርስቶስን በሰርግህ እንዲገኝ
ጋብዘው፡፡ እርሱን እንዴት አድርገህ እንደምትጋብዘው
ታውቃለህን ? “ንጉሡም መልሶ፡- እውነት እላችኋለሁ ከሁሉ
ከሚያንሱት ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት
ለእኔ አደረጋችሁት ይላቸዋል”(ማቴ.፳፭፥፵) እንዲል ድሆችን
በሰርግ እንዲገኙ በማድረግ ክርስቶስን በሰርግህ እንዲገኝ
ማደረግ ይቻልሃል፡፡ ስለክርስቶስ ብለህ ድሆች በሰርግህ
እንዲገኙ ስላደረግህ ሰርግህ የተበላሸ አድርገህ አትቁጠር፤ ነገር
ግን ሴሰኞችን በሰርግህ ብትጋብዝ ሰርግህ በእርግጥ የረከሰ
ይሆናል፡፡ ድሆችን ወደ ሰርግህ መጥራትህ ሀብት ወደ ቤትህ
እንዲገባ መጥራትህ ነው፡፡ ቅምጥሎችን ከሰርጉ እንዲታደሙ
የጠራህ እንደሆነ ግን ውርደትን እየጠራህ ነው፡፡
ሙሽሪትን በወርቅ ጌጣ ጌጦች አታስጊጣት ነገር ግን በጥሩ ሥነ
ምግባርና በጭምትነት አስጊጣት እነዚያን ነገሮች ፈጽመህ
አትፈልጋቸው፡፡ ግርግርና ሁካት በሰርግህ ፈጽሞ አይኑር፡፡
ሙሽራውን ጥራና ሚስቱን ይዞ ወደ ቤቱ ይግባ፡፡ በምሳና በራት
ግብዣህ ላይ አስካሪ መጠጦች አይገኙ፡፡ ነገር ግን ሰርግህ
በደስታ የሞላበት ይሁን፡፡
እንዲህ አድርገህ ሰርግህን በመከወንህ ምን ያህል ተጠቃሚ
እንደሆንክ ለማስተዋል እንድትችል በዘመኑ ሰርግ ተብለው
ከሚቆጠሩት ጋር ያንተን የሰርግ ሥነ ሥርዐት አስተያይ፡፡ ሌላው
ይቅርና ያንተን ሰርግ የተመለከተ ሰው ሁሉ የቁንጅና ውድድር
ሳይሆን በእውነተኛ ትርጉም ሰርግን እንዳየ ምስክርነትን
ይሰጥሃል፡፡ በዘመኑ ሰርግ ተብለው ከሚጠሩት ውስጥ ግን
እጅግ የበዙ ክፋቶች ታጭቀው ይገኙበታል፡፡ በአዳራሽ
የሚፈጸመው ሰርግ በጥንቃቄና እግዚአብሔርን በመፍራት
ከሚደረገው ጋር ሲነጻጸሩ በቶሎ የሚጠናቀቁ ሰርጎች
አይደሉም ፡፡ ከዚህም ባለፈ በውሰት የመጡት እቃዎች
ሊጠፉም ስለሚችሉ ፍጻሜው ከደስታ ይልቅ ሊቋቋሙ
ከማይችሉት ከባድ ሃዘን ውስጥ ሊጥል ይችላል ፡፡ ይህ የከበደ
ሃዘን በአማች ላይ የሚታይ ነው ፡፡ ነገር ግን ሙሽሪትም ከዚህ
ሃዘን ነጻ ልትሆን አትችልም ፡፡ በሰርጉም ፍጻሜም የቤቱ
ውበቱ ጠፍቶ በሃዘን ታወሮ ይታያል ፡፡
በጥንቃቄና እግዚአብሔርን በመፍራት በሚከናወነው ሰርግና
በአሕዛብ ልማድ በሚፈጸመው ሰርግ መካከል ሰፊ የሆነ ልዩነት
አለ፡፡ በዚህ ክርስቶስ ሲገኝ በዚያ ግን ሰይጣን ነግሦ ይታይበታል
፡፡ በዚህ ፍጽም የሆነ ፍስሐ ሲታይ በዚያ ደግሞ ጥቅ ያጣ
አለባበስ ይተዋወቅበታል ፡፡ በዚህ ፍጹም ደስታ ሲኖር በዚያ
ግን ሕማምና ሰቆቃ ይተርፈዋል ፡፡ በዚያ የወጣው ወጪ
ታላቅ ሲሆን በዚህ ግን እዚህ ግባ የማይባል ወጪ ብቻ
ያስተናግዳል ፡፡ በዚያ ግርግርና ሁካታ ሲታይ በዚህ ግን ግብረ
ገብነት ጎልቶ ይንጸባረቅበታል፡፡ በዚያ ኃጢአት ሠልጥና ስትታይ
በዚህ ግን ኃጢአት ፈጽማ አትኖርም ፡፡ በዚያ ስካሮች ሲኖሩባት
በዚህ ግን ሰላም ወዳዶች ይታዩባታል ፡፡ በዚያ ሁካታና ጠብ
ሲኖር በዚህ ግን እርጋትና ሰላም ሰፍነው ይታዩበታል ፡፡
እነዚህን ሁሉ ልብ በሉ ፡፡ እግዚአብሔርን ደስ በማሰኘት
እርሱን ለሚያፈቅሩት ካዘጋጀው ከመንግሥቱ ተካፋዮች
እንድንሆን ከዚህ ቀን ጀምረን ይህን ክፉ ልማድ ከራሳችን
አርቀነው እናስወግደው ፡፡ የሰውን ልጅ ከመውደዱ የተነሣ ሰው
በሆነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር አብ
ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጋር ክብር ምስጋና ዛሬም
ዘወትርም እስከዘለዓለሙ ይሁን አሜን !!

=>+*"+<+>+#ቅድስት_ሥላሴ +<+>+"*+

#ቅድስት_ሥላሴ
#ሥላሴ_የሚለው_ቃል ሠለሰ፤ ሦስት አደረገ ከሚለው የግእዝ
ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙ ሦስት ማለት ነው፡፡ ይህን
ሦስትነት ለጌታ ስንቀጽለው ልዩ የሆነ ሦስትነት የሚለውን ፍቺ
ያመላክታል፡፡
#የእነርሱን /የቅድስት ሥላሴን/ ሦስትነት ልዩ የሚያደርገው
በሦስትነት ውስጥ አንድነት፣ በአንድነት ውስጥ ሦስትነት ያላቸው
በመሆኑ ነው፡፡ ይህን በሚመለከት የሚሰጠው ትምህርተ
ሃይማኖት ምሥጢረ ሥላሴ ይባላል፡፡ ይህ ትምህርት ምሥጢር
መባሉ በዐይነ ሥጋ የማናየው፣ በዕደ ሥጋ የማንዳስሰው፣
በሥጋዊ ምርምር ፈጽሞ የማይደረስበት በመሆኑ ነው፡፡
ሆኖም ምሥጢረ ሥላሴ የሰላም ወንጌልና የእምነታችን
መሠረት ነው፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ትምህርተ ሰላምነ
ነአምን አበ ፈናዌ ወነአምን ወልደ ተፈናዌ ወነአምን መንፈሰ
ቅዱስ ማኅየዌ አሐደ ህላዌ፤ በሰላማችን ትምህርት ላኪ አብን
እናምናለን፤ ተላኪ ወልድንም እናምናለን፤ አዳኝ መንፈስ
ቅዱስንም በአንድ ባሕርይ እናምናለን እንዲል፡፡
#ቅድስት_ሥላሴ የእግዚአብሔር ልዩ መጠሪያው ነው፡፡
እግዚአብሔር ስንልም ስለ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ
መናገራችን ነው፡፡ ሊቁ አንሰ ሶበ እቤ እግዚአብሔር በእንተ
አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ እንዲል፡፡ ቢሆንም ግን
የእርሱን ነገር ልንመረምረው አንችልም፡፡ አንዳንድ ጊዜ
ሰዎች እግዚአብሔር ቅዱስ ተብሎ በወንድ አንቀጽ፣ ቅድስት
ተብሎ ደግሞ በሴት አንቀጽ /ቅድስት ሥላሴ/ ተብሎ ሲጠራ
እውነትም ከምርምር በላይ ነው ይላሉ፡፡ ይሁን እንጂ
የሚመራመር አእምሮን ስለሰጠን በተወሰነ መልኩ ቅዱስ እና
ቅድስት፣ ልዩ ሦስትነት የሚባልበትን ሃይማኖታዊ ምሥጢር
በጥቂቱ እንመለከታለን፡፡
1. #ቅዱስና_ቅድስት_መባል
ቅዱሳት መጻሕፍት ጾታ የሌላቸውን አካላት በወንድና በሴት
አንቀጽ መጥራት ልማዳቸው ነው፡፡ ለምሳሌ ቅዱሳን
መላእክትን በወንድ አንቀጽ ሲጠራቸው ወይሴብሕዎ ኩሎሙ
መላእክቲሁ፤ መላእክቱ ሁሉ ያመሰግኑታል ሲል በሴት አንቀጽ
ሲጠራቸው ደግሞ ሰማያት ይነግራ ስብሐተ እግዚአብሔር፤
ሰማያት (መላእክት) የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ ይላል
(መዝ. 148:1-2)፡፡ ነፍስንም በወንድ አንቀጽ ሲጠራ መንፈስ
እምከመ ወጽአ ኢይገብእ፤ ነፍስ ከተለየ በኋላ አይመለስም ሲል
በሴት አንቀጽ ደግሞ ትባርኮ ነፍስየ ለእግዚአብሔር፤ ነፍሴ
እግዚአብሔርን ታመሰግነዋለች ይላል /መዝ. 77:39፣ መዝ.
102:1/፡፡ እንዲሁም ፀሐይን በወንድ አንቀጽ ሲጠራ ፀሐይኒ
አእመረ ምዕራቢሁ፤ ፀሐይ መግቢያውን ዐወቀ ሲል በሴት
አንቀጽ ደግሞ ወድቀት እሳት ወኢርኢክዋ ለፀሐይ፤ እሳት
ወደቀች ፀሐይን አላየኋትም ይላል /መዝ. 103:19፣ መዝ.
57:8/፡፡ ስለዚህ ልማደ መጻሕፍት መሆኑን በዚህ ይረዷል፡፡
ሌላው ምክንያት ደግሞ የቅድስና ሕይወት ለወንዱም ሆነ
ለሴቷ የተሰጠ መሆኑን ያመላክታል፡፡ እዚህ ላይ የሚጠቀሰው
የሰው ልጅ የእኩልነት ሚዛን ደግሞ ቅድስና ነው፡፡
በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን ወንዶች
እንዳሉ ሁሉ ቅዱሳት ሴቶች መኖራቸው ለዚህ ማሳያ ነው፡፡
ይልቁንም የእመቤታችን የቅድስተ ቅዱሳን የድንግል
ማርያምን ቅድስና ስናስብ እንዲያውም በወንድ ምን ቅድስና
አለና! ያሰኛል፡፡ በእግዚአብሔር መንግሥት /በቤተ ክርስቲያን/
ፍትሕ፣ ርትዕ እንጂ ዓመፅና አድልዎ የለም፡፡ ዘአኮ ይዔምፅ
እግዚአብሔር ከመ ይርሳዕ ምግባሪክሙ ወተፈቅሮተክሙ
ዘአርአይክሙ በስሙ ወተልእክምዎሙ ለቅዱሳን
ወትትለአኩሂ፤ እግዚአበሔር ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ
አሁንም ስለምታገለግሉአቸው ያደረጋችሁትንም ሥራ
ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለምና፡፡እንዲል /
ዕብ. 6:10፡፡ እኛም ሃይማኖታችን የእኩልነት፣ የነጻነት፣
የሰላምና የአንድነት ሥርዓት እንጂ የሴቶች መጨቆኛ መሣሪያ
አይደለም የምንለውም ለዚህ ነው፡፡ አሁንም ቤተ ክርስቲያንን
የሚቃወሙ ወገኖች ይህን የጠራ አስተምህሮዋን በእምነት
መነፅር መረዳት አለባቸው፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ቅዱስ እና ቅድስት የመባሉን ነገር ሊቁ
አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በምሳሌዊ አገላለጽ ኀበ ርኅራኄክሙ
በዝኀ ወኀበ አልቦቱ መሥፈርት እለ ትሠመዩ በስመ ብእሲት
ሥላሴ ዕደወ ምሕረት ግናይ ለክሙ፤ ቸርነታችሁ ከበዛና
መሥፈሪያም ከሌለው ዘንድ ቅድስት ተብላችሁ በሴት ስም
የምትጠሩ የይቅርታ ወንዶች ሥላሴ ሆይ ለእናንተ መገዛት
ይገባል በማለት ምሥጢሩን እንደ ወርቅ አንከብልሎ እንደ
ሸማ ጠቅልሎ አስተምሯል፡፡
የሥላሴ በወንድና በሴት አንቀጽ መጠራት ምሳሌነት አለው
ማለት ነው፡፡ ወንድ ኃያል ነውና ቢመታ ያደቅቃል፤ ቢወረውር
ያርቃል፤ ቢያሥር ያጠብቃል፡፡ ሥላሴም ከቸርነታቸው በቀር
ፍጥረቱን ሁሉ እናጥፋው ቢሉ ይቻላቸዋል፡፡ አንድም ወንድ
ወጥቶ ወርዶ ነግዶ ሚስቱን ይመግባል፤ ልጆቹን ያሳድጋል፡፡
ሥላሴም በፈጢር ወላድያነ ዓለም ናቸውና የፈጠሩትን ፍጥረት
በዝናብ አብቅለው፣ በፀሐይ አብስለው ይመግቡታልና በወንድ
አንቀጽ ቅዱስ ይባላሉ፡፡
#ቅድስት_ተብለው በሴት አንቀጽ መጠራታቸው ደግሞ ሴት /
እናት/ በልጁዋ ወለደችው /አልወለደችው/ ተብላ
እንደማትጠረጠረው ሁሉ ሥላሴም ይህን ዓለም ፈጠሩት
አልፈጠሩት ተብለው አይጠረጠሩም፡፡ ሁሉም ከእነርሱ፣
ለእነርሱ፣ በእነርሱ ሆኗልና፡፡ ሴት /እናት/ ልጅዋ ቢታመምባት
ወይም ቢሞትባት አትወድም፤ ሥላሴም ከፍጥረታቸው አንዱ
እንኳ በዲያብሎስ እጅ ቢገዛባቸው አይወዱም፡፡ አንድም ሴት /
እናት/ ፈጭታ ጋግራ ቤተሰቦቿን ትመግባለች፤ ሥላሴም
በዝናም አብቅለው በፀሐይ አብስለው ፍጥረቱን ሁሉ
ይመግባሉና በሴት አንቀጽ ቅድስት ሥላሴ እያልን
እንጠራቸዋለን፡፡
2. #ልዩ_ሦስትነት
ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ልዩ ሦስትነት የሚለው
የምሥጢረ ሥላሴ ሃይማኖታዊ ትምህርት በቅድምና፣
በፈጣሪነት፣ በሥልጣን፣ በማሰገድ፣ በመመስገን፣ በክብር፣
በፈቃድ አንድ /እግዚአብሔር/ ሲሆኑ በስም፣ በአካል፣ በግብር
ሦስት (ሥላሴ) የሚለውን ይገልጻል፡፡
2.1. #በስም
የስም ሦስነታቸው አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ መባል ነው፡፡
ይኸንንም ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል /ወልድ/ እንግዲህ ሒዱና
አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ
እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርቴ አድርጓቸው ሲል
አስተምሯል /ማቴ. 28:19/ ታዲያ አብ በራሱ ስም አብ ቢባል
እንጂ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አይባልም፡፡ ወልድም ወልድ ቢባል
እንጂ አብ መንፈስ ቅዱስ አይባልም፡፡ መንፈስ ቅዱስም
መንፈስ ቅዱስ ቢባል እንጂ አብ ወልድ አይባልም፡፡ ስማቸው
ፈጽሞ የማይፋለስ (የማይተባበር) ነውና፡፡
አንዳንድ የእምነት ድርጅቶች ይህን ትምህርት በአግባቡ
ካለመረዳታቸው የተነሣ # ኢየሱስ ብቻ /Only Jesus/
በማለት የአብንና የመንፈስ ቅዱስን ስም ለኢየሱስ (ለወልድ)
ብቻ በመስጠት ስመ ተፋልሶ እያመጡ ኑፋቄን ይዘራሉ፡፡ እኛ
ግን በቅድስት ሥላሴ ዘንድ ስመ ተፋልሶ እንደሌለ እናምናለን፡፡
በአንጾኪያ ከቅዱስ ጴጥሮስ ቀጥሎ በሦስተኛነት ተሹሞ
የነበረው ቅዱስ አግናጥዮስ አብሂ አብ ውእቱ ወኢኮነ ወልደ
ወመንፈሰ ቅዱሰ፣ ወልድሂ ወልድ ውእቱ ወኢኮነ አበ
ወኢመንፈሰ ቅዱሰ፣ መንፈስ ቅዱስሂ መንፈስ ቅዱስ ውእቱ
ወኢኮነ አበ ወኢወልደ፣ ኢይፈልስ ስመ አብ ለከዊነ ስመ ወልድ
ወመንፈስ ቅዱስ፣ ወኢይፈልስ ለከዊነ ስመ አብ ወወልድ፤ አብ
አብ ነው ወልድን መንፈስ ቅዱስን አይደለም፣ ወልድም ወልድ
ነው አብን መንፈስ ቅዱስንም አይደለም፡፡ መንፈስ ቅዱስ
መንፈስ ቅዱስ ነው፤ አብን ወልድን አይደለም፤ አብ ወልድንና
መንፈስ ቅዱስን ለመሆን አይለወጥም፣ ወልድም አብንና
መንፈስ ቅዱስን ለመሆን አይለወጥም፣ መንፈስ ቅዱስም
አብንና ወልድን ለመሆን አይለወጥም ሲል፣ ዮሐንስ
ዘአንጾኪያም አስማትሰ ኢየኀብሩ፤ ስሞች ግን አይተባበሩም
ብሏል/ ሃይ አበው ዘቅዱስ አግናጥዮስ ምዕ. 11 ገጽ. 18፣ ሃይ
አበው ዘዮሐንስ/፡፡
ይህ የቅድስት ሥላሴ ስም እንደ ሰው ስም አካል ቀድሞት ኋላ
የተገኘ አይደለም፡፡ የሰው ስሙ አካሉ ቀድሞት ኋላ ይገኛል፡፡
ወንዱን በ40 ቀኑ እገሌ ሲሉት ሴቲቱን በ80 ቀኗ እገሊት
ይሏታል፡፡ የተወለደ ዕለትም እናት አባቱ ዓለማዊ የመጠሪያ
ስም ያወጡለታል፡፡ ሰው ሲባል ስሙ ከአካሉ አካሉ ከስሙ
ሳይቀድም እንደተገኘ ሁሉ የሥላሴም ስማቸው ከአካላቸው፣
አካላቸው ከስማቸው ሳይቀድም ቅድመ ዓለም የነበረ ስም ነው
እንጂ ድኅረ ዘመን የተገኘ አይደለም፡፡ ቅድምናቸው ዘመኑን
ቢወስነው እንጂ ዘመኑ ቅድምናቸውን አይወስነውምና፡፡
(መንገደ ሰማይ-በብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ገጽ. 32/፡፡
ሊቁ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ገባሬ መንክራት ወናሁ ንቤ ካዕበ አብ
ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ወአኮ እሉ አስማት ዘቦኡ ላዕሌሆሙ
ድኅረ አላ እሙንቱ እስመ አካላት ወብሂለ ሰብእሂ አኮ ውእቱ
ስም ዳዕሙ ፍጥረት ውእቱወአካሎሙኒ ለሥሉስ ቅዱስ
ወአስማቲሆሙ አልቦ ውስቴቶሙ ዘይዴኀር አላ እሉ እሙንቱ
ብሉያነ መዋዕል እምቀዲሙ ዘእንበለ ጥንት ወዘመን፤ አሁን
ደግሞ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ እንላለን ግን አካላት
ተቀድመው ተገኝተው እሊህ ስሞች ኋላ የተጠሩባቸው
አይደለም፤ ሰው ማለት ኋላ የወጣ ስም ሳይሆን ባሕርዩ ነው
የሥላሴ አካላቸውም ቀድሞ ስማቸው ከአካላቸው በኋላ የተገኘ
አይደለም፡፡ ጥንት ሳይኖራቸው ዘመን ሳይቀድማቸው የነበሩ
ናቸው እንጂ እንዲል /ሃይ-አበው ዘቅዱስ ጎርጎርዮስ ገባሬ
መንክራት 13-4-8/፡፡
2.2. #በአካል
የቅድስት ሥላሴን የአካል ሦስትነት ስናይ ደግሞ አብ በተለየ
አካሉ ፍጹም አካል፣ ፍጹም ገጽ፣ ፍጹም መልክእ አለው፡፡
ወልድም በተለየ አካሉ ፍጹም አካል፣ ፍጹም ገጽ፣ ፍጹም
መልክእ አለው፡፡ መንፈስ ቅዱስም በተለየ አካሉ ፍጹም አካል፣
ፍጹም ገጽ፣ ፍጹም መልክእ አለው፡፡ ይህን እውነት ሊቁ
አቡሊደስ ነአምን በአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ከመ ሠለስቱ
ገጻት ፍጹማነ መልክእ ወአካል እሙንቱ እንዘ አሐዱ
መለኮቶሙ፤ ባሕርያቸው በእውነት አንድ ሲሆን በመልክ፣
በአካል ፍጹማን የሚሆኑ ሦስት ገጻት እንደሆኑ በአብ በወልድ
በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን ብሏል /ሃይ አበው ዘአቡሊደስ
ምዕ. 39-3/፡፡
ይህ አካላቸው ምሉዕ በኩለሄ፣ ስፉሕ፣ ረቂቅ ሲሆን ዳር
ድንበር፣ ወሰን የለውምና ከጽርሐ አርያም በላይ ቁመቱ፣
ከበርባሮስ በታች መሠረቱ፣ ከአድማስ እስከ ናጌብ ስፋቱ ተብሎ
አይመረመርም፤ ቢመረመርም አይደረስበትም፡፡ ሁሉን ሥላሴ
ይወስኑታል እንጂ የሚወስናቸው የለምና፡፡«ንሕነ ናገምሮ
ለኩሉ ወአልቦ ዘያገምረነ አልቦ ወኢምንትኒ እምታሕቴነ እስመ
ለኩሉ የዐውድ ዕበየ ኃይልነ አልብነ ውሳጤ ወአፍአ አልቦ
ሰማይ ዘያገምረነ ወኢምድር ዘይጸውረነ፤ ሁሉን እኛ
እንሸከመዋለን እንጂ እኛን የሚሸከመን የለም፤ ከእኛ በላይ
ከእኛም በታች ቦታ የለም፣ ባሕርያችን ሁሉን ይወስናል እንጂ
የሚወስነው የለም» እንዲል /መጽ. ቀሌምንጦስ/፡፡
2.3. #በግብር
በግብር ሦስትነታቸው ደግሞ የአብ ግብሩ መውለድ ማሥረጽ
ነው፤ ወልድን ወልዷል፣ መንፈስ ቅዱስንም አሥርጿልና፡፡
የወልድ ግብሩ መወለድ ነው፤ ከአብ ተወልዷልና፡፡ የመንፈስ
ቅዱስ ግብሩ መሥረጽ ነው፤ ከአብ ሠርዷልና፡፡ እግዚአብሔር
አለኝ አንተ ልጄ ነህ ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ
ጊዜ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል እንዲል /መዝ. 2:7፣ ዮሐ.
3:16/፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተረዳነው /ከሊቃውንተ
ቤተ ክርስቲያን እንደተማርነው) አብ ወልድን ቢወልድ፣ መንፈስ
ቅዱስንም ቢያሠርፅ እንጂ አይወለድም፣ አይሠርጽም፡፡ ወልድ
ቢወለድ እንጂ አይወልድም፤ አይሠርጽም፤ አያሠርጽም፡፡
በመሆኑም ቅድስት ሥላሴ በዚህ ግብራቸው አብ ወላዲ፣ ወልድ
ተወላዲ፣ መንፈስ ቅዱስ ሠራጺ ተብለው ይጠራሉ፡፡
የወልድ ከአብ መወለዱና የመንፈስ ቅዱስ ከአብ መሥረጹ
እንደምንድን ነው? ቢሉ ቃልና እስትንፋስ ልብ ሳይቀድማቸው
አካላቸው ከልብ ሳይለይ ቃል እንደሚወለድና እስትንፋስ
እንደሚወጣ ሁሉ ወልድና መንፈስ ቅዱስም ቅድመ ዓለም አብ
ሳይቀድማቸው እንበለ ተድኅሮ አካል ዘእም አካል ባሕርይ
ዘእምባሕርይ ወልድ ከአብ ተወለደ፤ መንፈስ ቅዱስም ከአብ
ሠረጸ፡፡ ከመ ልደተ ቃል ወጸአተ እስትንፋስ እምልብ ከማሁ
ልደቱ ለወልድ ወጸአቱ ለመንፈስ ቅዱስ እም አብ፤ ወልድ ከአብ
የሚወለድበት ልደትና መንፈስ ቅዱስ ከአብ የሚወጣበት
አወጣጥ ከልብ እንደሚሆን እንደ ቃል መወለድና ከልብ
እንደሚሆን እንደ እስትንፋስ አወጣጥ ነው እንዲል /ርቱዐ
ሃይማኖት/፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ድንቅ ምሥጢር አሁንም
ቢሆን በዕፁብ ይወሰናል እንጂ በምርምር አይደረስበትም፡፡
ሆኖም ኦርቶዶክሳውያን አበው የመጽሐፍ ቅዱስን የቀና
አስተምህሮ መሠረት በማድረግ መንፈስ ቅዱስ ከአብ ብቻ እንደ
ሠረጸ አስተምረዋል፡፡ ዳግመኛም በቁስጥንጥንያ በተካሔደው
ዓለም አቀፍ ጉባኤም ላይ መቅዶንዮስን ተከራክረው የረቱ
መቶ ሃምሳው ቅዱሳን ሊቃውንት ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ
እግዚእ ማኅየዊ ዘሠረጸ እም አብ ንስግድ ሎቱ ወንሰብሖ
ምስለ አብ ወወልድ፤ ሕይወትን በሚሰጥ ጌታ ከአብ በሠረጸ
ከአብና ከወልድ ጋር በሚሰገድለት በነቢያት አድሮ በተናገረ
መንፈስ ቅዱስ እናምናለን በማለት ከቅዱስ ወንጌል እውነታ
በመነሣት ትክክለኛውን እምነት ገልጸዋል /ጸሎተ
ሃይማኖት/፡፡
በአንጻሩ ግን ይህን ትምህርተ ሃይማኖት ወደ ኋላ በመተው
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከጊዜ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ዘሠረጸ
እም አብ ወወልድ፤ ከአብ ከወልድም የሠረጸ የሚል ሥርዋጽ
አስገብተዋል፡፡ ይህ የስሕተት አስተምህሮ በላቲን ፊሊዮኬ
(Filio tve)ሲባል ትርጉሙ እንዲሁም ከወልድ ማለት ነው፡፡
ይህ አመለካከት ኑፋቄ በመሆኑ በእኛ ቤተ ክርስቲያን መቼም
ቢሆን ተቀባይነት የሌለው ትምህርት ሲሆን በላቲኖች ዘንድ ግን
ተቀባይነትን ያገኘ አስተምህሮ ነበር፡፡
ለእነርሱ የስሕተት ትምህርት መሠረት የሆናቸው አውግስጢኖስ
የተባለው ሰው (dusia is the Sours of trinity)፣ አብ
ፍቅር ነውና ልጁን ወዳጅ ነው (The father is the one
who loves or/over)፣ ወልድ ደግሞ በአብ ዘንድ ተወዳጅ
ነው /The son is the one who is Loved or
Beloved፣ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በሁለቱ ፍቅር መካከል ያለ
አያያዥ ነው /The Sprit is Love bond)በማለት
አስቀድሞ ያስተማረውን ችግር ያለበት ትምህርት
በመቀበላቸውና መመሪያ በማድረጋቸው ሲሆን ይህን ተከትለው
በ589 ዓ.ም በስፔን ቶሌዶ ካካሔዱት ጉባኤ ጀምሮ በ1014
ዓ.ም ተቀብለውት በቅዳሴያቸው አስገብተውታል፡፡ /The
Doctrine of God P. 172/.
በእርግጥ ምሥጢረ ሥላሴን በሚገባ መረዳት ለማንም ቢሆን
አይቻለውም፡፡ እርሱ ባወቀ ግን ምሥጢረ ሥላሴ በምሥጢረ
ጥምቀት ተገልጧል፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በመጽሐፈ
ሰላምታው ላይ ለምህሮ ትሥልስት ሥላሴ በሌሊተ ጥምቀት
ሐዲስ ዘአስተርአይክሙ በዮርዳኖስ በአምሳል ዘይሤለስ ግናይ
ለክሙ፣ በዐዲሲቱ ጥምቀት ሌሊት ሦስትነታችሁን ለማስተማር
በሦስት አካላት በዮርዳኖስ የተገለጣችሁ ሥላሴ መገዛት
ለእናንተ ይገባል እንዲል፡፡
እንግዲህ እምነታችንን በቅድስት ሥላሴ ላይ በማድረግ
በርትዕት ሃይማኖት ልንጸና ይገባል፡፡ወአኮ ዘንብል አሐዱ ከመ
አዳም ቀዳሜ ኩሉ ፍጥረት አላ ሠለስቱ እንዘ አሐዱ ህላዌ ናሁ
ንሰምዖሙ ለአይሁድ እኩያን ወለእስማኤላውያን ጊጉያን እለ
ይብሉ አሐዱ ገጽ እግዚአብሔር ወአሐዱ አካል በኢለብዎቶሙ
ዕውራነ ልብ እሙንቱ፤ የሰው ሁሉ መጀመሪያ እንደሆነ እንደ
አዳም አንድ ነው አንልም፤ ነገር ግን በባሕርይ አንድ ሲሆን
በአካሉ ሦስት ነው እንላለን እንጂ፡፡ ክፉዎች አይሁድን በደለኞች
እስማኤላውያንን እነሆ እናያቸዋለንና እግዚአብሔርን አንድ
አካል አንድ ገጽ ሲሉ ባለማወቃቸው በልቡናቸው የታወሩ
ናቸውና በሚል ተግሣጽ አዘል ምክር ተችሮናልና /ቅ.ማርያም
ቁ. 70/፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

=>+*"+<+>+ ግንቦት 7 +<+>+"*+

<<< በስመ አብ: ወወልድ: ወመንፈስ ቅዱስ: አሐዱ አምላክ . . . አሜን:: >>>
+<+>+ ግንቦት 7 +<+>+
+*" ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ "*+
=>በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከሐዋርያት ቀጥሎ የቅዱስ
አትናቴዎስን ያሕል ስለ ሃይማኖት የተዋጋ ቅዱስ ፈልጐ
ማግኘት አይቻልም::
=>ቅዱስ አትናቴዎስ ማን ነው?
=>ቅዱስ አትናቴዎስ በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት
በዘመነ ሰማዕታት መጠናቀቂያ በ300 (296) አካባቢ
እስክንድርያ (ግብፅ) ውስጥ ነው የተወለደው:: ወላጆቹ
አረማውያን በመሆናቸው ክርስትናን አልተማረም ነበር::
+ሕጻን እያለ ለጭዋታ ከቤቱ ሲወጣ የክርስቲያን ልጆች
ሃይማኖታዊ ጨዋታ ሲጫወቱ ተመለከተ:: ሊቀላቀላቸው
ቢፈልግም ክርስቲያን ባለመሆኑ ከለከሉት:: አትናቴዎስም
"ክርስቲያን ልሁንና አጫውቱኝ" ብሏቸው "እሺ" ስላሉት
ሕጻናቱ ዕጣ ተጣጣሉ::
+ላንዱ ቄስ : ላንዱም ዲያቆን መሆን ሲደርሳቸው ለአትናቴዎስ
ፓትርያርክ መሆን ስለ ደረሰው ሌሎቹ ሕጻናት ይሰግዱለት
ጀመር:: በአጋጣሚ ሕጻናቱ ይሕንን ሁሉ ሲያደርጉ የወቅቱ
ፓትርያርክ ቅዱስ እለ እስክንድሮስ በመገረም ያያቸው ነበርና
ለሕጻኑ አትናቴዎስ ትንቢት ተናገረለት::
+ከዚያም የአትናቴዎስ አባቱ ሲሞት ሊቀ ዻዻሳቱ ከእናቱ ወስዶ
አጥምቆ : የሚገባውን መንፈሳዊ ትምሕርት ሁሉ በልቡናው
ላይ ቀረጸበት:: ከዚሕ በሁዋላ ዲቁናን ሹሞ አስተምር አለው::
ምንም ሕጻን ቢሆንም ከሊቅነቱ : ከአመላለሱና ከአንደበቱ
ጣፋጭነት የተነሳ የሰማው ሁሉ ይደነቅ ነበር:: ጸጋ
እግዚአብሔር በእርሱ ላይ አድራለችና::
+ቅዱስ አትናቴዎስ ሊቀ ዲቁና በተሾመ ወራት አርዮስ ቤተ
ክርስቲያንን በመረበሹ ኒቅያ ላይ 318ቱ ሊቃውንት ሲሰበሰቡ
ጸሐፊ አድርገው ሾሙት::
+በጊዜውም በዕድሜ የስንት ጊዜ ትልቁ የሚሆነውን አርዮስን
ተከራክሮ ምላሽ አሳጣው:: ቅዱስ አትናቴዎስ ከሊቃውንቱ ጋር
ሆኖ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ : እግዚአብሔር
መሆኑን በአደባባይ መሠከረ:: ጸሎተ ሃይማኖትንም ያረቀቀው
እርሱ ነው::
+ከዚሕ በሁዋላ የእስክንድርያ (የግብፅ) 20ኛ ፓትርያርክ ሆኖ
ተሾመ:: ቤተ ክርስቲያንን በመልካም እረኝነት ለ48 ዓመታት
ሲመግብ ብዙ መከራዎችን ተቀበለ:: ለ5 ጊዜ ከመንበሩ
አፈናቅለው ወደ በርሃ ሲያግዙት : በስደት ከ15 ዓመታት በላይ
አሳልፏል::
+በተሰደደባቸው ቦታዎች መከራን እየተቀበለ ያላመኑትን
አሳምኗል:: በጎቹ እንዳይባዝኑበት ደግሞ በጦማር (በደብዳቤ)
ይጠብቃቸው ነበር:: ዛሬ በሃይማኖተ አበው የምናገኘው ቃለ
ሃይማኖት በዚሕ ዘመን የተጻፈ ነው::
+በወቅቱ የነበረው ንጉሥ (ትንሹ ቆስጠንጢኖስ) የአባቱን
(ታላቁ ቆስጠንጢኖስን) ዕረፍት ተከትሎ ነገሠ::
+ወዲያውም አርዮሳዊ (መናፍቅ) ሆነ:: ሃይማኖታቸው የቀና
አባቶችንም ያሳድድ ገባ:: ከአበው ቅዱሳን መካከል ግን የዚህ
መከራ ቀዳሚው ገፈት ቀማሽ ታላቁ ሊቅ ቅዱስ አንትናቴዎስ
ነበር::
+በተለይ አንድ ጊዜ ንጉሡ ቅዱሱን ወደ በርሃ አግዞ : መናፍቅ
ዻዻስ በግብጽ ሹሞ : ብዙ ክርስቲያኖችን በግፍ ሲያስገድል:
ቅዱሱን ለ6 ዓመታት አሰቃየው:: የወገኖቹ (የልጆቹን) ስቃይ
የሰማው ቅዱስ አትናቴዎስ ግን በድፍረት ወደ ቤተ መንግስት
ገብቶ ተናገረው::
+2 አማራጭን አቅርቦ "ወይ ግደለኝና እንደ አባቶቼ ሰማዕት
ልሁን: ካልሆነ ግን ወደ መንጐቼ (ምዕመናን) መልሰኝ"
አለው:: መናፍቁ ንጉሥም ቢገድለው ብጥብጥ እንደሚነሳ
ስለሚያውቅ በስልት ሊያጠፋው ወሰነ::
+ቀዛፊ: መቅዘፊያ: ምግብና ውሃ በሌላት ጀልባ ውስጥ ከቶ
ሜዲትራኒያን ባሕር ውስጥ ጣለው:: ድንገት ግን ከሰማይ
ጌታችን መላእክቱን አስከትሎ ወረደ::
+ሚካኤልና ገብርኤል ባሕሩን እየቀዘፍ : ሌሎች መላእክት
እየመገቡት እስክንድርያ (ግብጽ) አድርሰውት ተሠውረዋል::
ሕዝቡም በታላቅ ሐሴት እየዘመሩ አባታቸውን
ተቀብለውታል::
+ሐዋርያዊው ቅዱስ ስለ ኦርቶዶክስ ተዋግቶ : ብዙ ስቃይንም
ተቀብሎ በ373 ዓ/ም አካባቢ አርፏል:: ቤተ ክስርቲያን "ሊቀ
ሊቃውንት : ርዕሰ ሊቃውንት : የቤተ ክርስቲያን (የምዕመናን)
ሐኪም (Doctor of the Church) : ሐዋርያዊ . . ." ብላ
ታከብረዋለች::
=>አምላከ አበው ምሥጢራቸውን አይሰውርብን::
ከበረከታቸውም ያድለን::
=>ግንቦት 7 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
2.የባሕታውያን አለቃ ታላቁ አባ ሲኖዳ (ጽንሰቱ)
3.ቅዱስ ዮሐንስ ጻድቅ (ሃብቱን : ንብረቱን : ልብሱን ሳይቀር
መጽውቶ ራቁቱን የተገኘ ደግ ሰው ነው)
4.አባ ሐርስዮስ ገዳማዊ
=>+"+ ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብጹዐን ናቸው:: መንግስተ
ሰማያት የእነርሱ ናትና:: ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም
ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብጹዓን ናችሁ::
ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ:: ሐሴትም
አድርጉ:: ከእናንተ በፊት የነበሩ ነቢያትን እንዲሁ
አሳደዋቸዋልና:: +"+ (ማቴ. 5:10)
<ወስብሐት ለእግዚአብሔር