ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

Saturday, April 9, 2016

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ: የአብይ ፆም 6ኛ ሰንበት ገብርኄር!!!!!

የአብይ ፆም 6ኛ ሰንበት ገብርኄር!!!!!
+++++++++++++++ +++++++++++++++
+++++++++++++++ +++
ስያሜው የቅዱስ ያሬድ ሲሆን በዚህ ቀን ስለ ቅን አገልጋዮች ፤
ለአገልጋዮች የሚያገለግሉበት ፀጋ የሚሰጥ ፤አገልጋዮችን
‹ገብርኄር› እያለ ዋጋ የሚሰጥ አምላክ መሆኑ እየታሰበ
ይመለካል፡፡
1. የዕለቱ የቅዱስ ያሬድ መዝሙር ርዕስ
መኑ ውእቱ ገብርኄር
(ቸር አገልጋይ ማን ነው?)
2. የዕለቱ ቅዳሴ …የባስልዮስ
በቅዳሴ ሰዓት የሚነቡ የመፅሃፍ ቅዱስ ክፍሎች
1ኛ ጢሞ 2፡1-16(በዲያቆን)
1ኛ ጴጥ5፡1-12(በንፍቀ ዲያቆን)
ሀዋ 1፡6-9(በንፍቀ ካህን)
3. የዕለቱ ምስባክ
ከመ እግበር ፈቃድከ መከርኩ አምላኪየ
ወሕግከኒ በማእከለ ከርስየ
ዜኖኩ ጽድቅከ በማኅበር ዐቢይ
አምላኬ ሆይ ፈቃድህን ለማድረግ ወደድኩ
ህግህም በልቤ ውስጥ ነው
በታላቁም ጉባኤም ጽድቅህን አወራለሁ፡፡ መዝ 39፡8
4. በዕለቱ የሚነበብ ወንጌል ማቴ 25፡14-31
5. የዕለቱ ትምህርት(ቸር አገልጋይ ማን ነው?)
ቸር አገልጋይ(ገብርኄር) ማቴ 25፡14-30 በዚህ ዕለት
በቅዳሴ ሰዓት የተነበበው ቃለ ወንጌል እንዳመለከተን
መድሃኒታችን የወንጌል አደራ በምሳሌ እናዳስተማረ
ተገንዝበናል፡፡ ትምህርቱም እንድ ባለፀጋ ሰው ነበር፡፡ ወደሩቅ
አገር ለመሄድ ባሰበ ጊዜ አገልጋዮችን ጠርቶ ከመንገዱ
እስኪመለስ ድረስ ይስራበት ዘንድ ለአንዱ አምስት መክሊት፤
ለሁለተኛው ሁለት ፡ ለሶስተኛው አንድ መክሊት ሰጣቸው፡፡
አምስት
መክሊት የተቀበለው ወጥቶ ወርዶ ሌላ አምስት መክሊት
በማትረፍ አስር መክሊት አደረገው፡፡ ሁለት መክሊት
የተቀበለውም ወጥቶ ወርዶ እጥፍ አትርፎ አራት መክሊት
አደረገው፡፡አንድ መክሊት የተቀበለው ግን ወደ ስራ ከመግባቱ
በፊት በልቡ ውስጥ ስጋት ፤ጥርጥር ፤ፍርሃትንና አለማመንን
ስላነገሰ ስሰራበት ቢጠፋብኝስ ፤ ቢሰርቁኝስ
ቢቀሙኝስ እያለ በማሰብ እሰራለሁ ብዬ ያለኝን ከማጣ ለምን
ደብቄ አስቀምጬ በመቆየት ሲመጣ የሰጠኝን አልመልሰም
ብሎ መክሊቱን ቆፍሮ ቀበረው፡፡ ጊዜው ሲደርስ ባለንብረቱ
መጣና አገልጋዮቹን ይተሳሰባቸው ጀመር፡፡
በቅድሚያ አምስት የወሰደው መጣና ‹ጌታዬ ሆይ አምስት
መክሊት ሰጠኸኝ ነበር፡፡ ይኸውና ሌላ አምስት መክሊት
አትርፌያለሁ› ብሎ አስር መክሊት ለጌታው ሰጠ፡፡ ጌታውም
መልካም አደረክ አንተ መልካም አገልጋይ (ገብርኄር) በጥቂቱ
ስለታመንክ በብዙ ላይ እሾምሃለሁ› ተባለ፡፡
ሁለተኛው ‹ሁለት መክሊት ሰጠኸኝ ነበር እነሆ አራት መክሊት›
ብሎ እጥፍ ማትረፉን ገልፆ ለጌታው አስረከበ፡፡ እንደ ባለ
አምስቱ ‹መልካም አደረግህ ቸር አገልጋይ ነህ በጥቂቱ
ስለታመንክ በብዙ ላይ እሾምሃለሁ›› ተባለ
ሶስተኛው መጣ ሰነፍ ቃሉም መራራ ነው፡፡ የሰነፍ አካሉ ብቻ
ሳይሆኑ አእምሮውም ሰነፍ ነው፡፡ ጌታው ገንዘቡን ሲጠይቀው
‹ጌታ ሆይ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ ፤ ካልበተንክበት
የምትሰበሰብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ
ፈራሁህ ሄጄም መሬት ቆፍሬ መክሊቴን ጉድጓድ ውስጥ
ቀበርኩ፡፡ ገንዘብህን ይኸውልህ ውስድ አለው፡፡ ጌታውም ይህን
ያህል ጨካኝ እንደሆንኩ ካወቅህ ንብረቴን ከነወለዱ
ልትመልስው ይገባህ ነበር፡፡ገንዘቤን ልትሰራበት ሲገባህ ለምን
ቀበርከው ብሎ መክሊቱን ወደ እርሱ ወስዶ ለባለ አምስቱ
ጨምሩለት ‹ላለው ይጨመርለታል ይትረፈረፍለታልም
ለሌላው ግን ያው ያለው ይወሰድበታል › ይህን የማይረባ
አገልጋይ ግን ልቅሶ ፤ጥርስ ማፏጨት ወዳለበት ጽኑ የፍርድ
ቦታ ውሰዱት አለ ይላል
በምሳሌ የተሰጠው የመድሃኒታችን ትምህርት፡፡ የትምህርቱም
ትርጉም
እንደሚከተለው ነው፡፡
የንብረቱ ባለቤት መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ሶስቱ
አገልጋዮች ልዩ ልዩ ፀጋ ተሰጥቶአቸው ያሉ ህዝበ ክርስቲያኖች
ምሳሌዎች ናቸው፡፡ስጦታው በአኃዝ ሲታይ ልዩነት መኖሩ አንዱ
ፀጋ ከሌላው የሚለይ መሆኑን ያሳያል፡፡
የአገልጋዮቹ ባህሪ
1. የመጀመሪያውና የሁለተኛው አገልጋዮች መንፈስ ሁለቱም
ሰርቶ ማግኘት እንደሚቻል የሚያምኑ ፤ ከጌታቸው ታማኞች ፤
በስራ ላይ የሚያጋጥማቸውን ችግር በማሰብ ጊዜያቸውን
የማያጠፉ ናቸው፡፡
ሁለተኛው አገልጋይም እንደ መጀመሪያው አገልጋይ ለምን
አምስት አልተሰጠኝም ብሎ ያለኩርፊያ በተሰጠው የሚሰራ
ነው፡፡ ባለ አምስቱ አምስት ሲያተርፍ ባለሁለቱም ሁለት
በማትረፍ ተመሳሳይ ትጋት የታየባቸው አገልጋዮች ናቸው፡፡
ዋጋቸው እኩል ነው ፤ለሁለቱም የተሰጠው የክብርም ስም
አንድ ነው፡፡ ገብርኄር የሚል የገቡበት የክብር ስፍራ አንድ
ነው፡፡ ያም ‹ጌታችን ደስታ ነው› ሁለቱም በጥቂት የታመኑ
ነበሩ፡፡ከሰጪው አንጻር ሲታይ የባለ አምስቱ እንደ ባለ ሁለቱም
፤ የባለ ሁለቱ እንደ ባለአምስቱ ጥቂት ነበር፡፡ ሰው በተሰጠው
ሳያንጎራጉር ፈጣሪውን ቢያገልግል ክብር ያገኛል፡፡ ለስው ልጅ
የሚጠቅመውን ችሎታውን ፤ፀጋውን መቁጠር ሳይሆን
በተሰተው ፀጋ ማገልገል ነው፡፡ እነዚህን አገልጋዮች በእውነት
በፍቅር በእምነት የሚያገለግሉ የቤተክርሰቲያን አገልጋዮች
ያመለክታሉ፡፡
2. የሶስተኛው አገልጋይ ባህሪ ፤ መልካም ጎኑ ስጦታው አነሰኝ
አለማለቱ ነው፡፡ በርግጥ ስንፍናውን ስለሚያውቅ ይሆናል፡፡
ይህ ሰው ከስራ ይልቅ በስጋ ጊዜ የሚፈጠረው ችግር አስቀድሞ
ይታየዋል፡፡አንዱን ሁለት ሲያደርግ ሳይሆን ያንኑ ያለውን
ሲቀማ ይታየዋል፡፡በጌታው ፊት እንደወንድሞቹ አይነቱን ትርፍ
ይዞ ቀርቦ ሲሸለም ሳይሆን ዓይነታውም ጠፍቶበት ለጌታው
የሚመልሰውን ሲያጣ ይታየዋል፡፡
በመሆኑም ምንም መስራት አልቻለም፡፡ የተሰጠውን መክሊት
ኪሱን አላምነው ብሎ መሬት ቆፍሮ ቀበረው፡፡‹ጨካኝ
መሆንህን ስላወቅሁ ይጠፋብኛል ብዬ ብርህን
አስቀምጬዋለሁ ይþውልህ ና ወሰድ› ነው ያለው፡፡ ሰነፍ
የሚናገረውም አያምርም ተቀምጦ መዐት ከማውራት ዝም
አይልም፡፡
ዛሬም ቢሆን ተቀምጠው መዐት የሚያወሩ የእግዚአብሄር ፀጋ
የቀበሩ ፤ ባስተምርና መናፍቅ ተከራክሮ ቢረታኝስ ?
የማውቀውን እውነት ለመስበክ ስጀምር ቢያሳስሩኝስ?
በቤተክርስቲያን ህዝብ በገበያ በልዩ ልዩ ቦታዎች ያሉትን
ሃጢያተኞች ብቃወም ጠላት ሆነው ቢነሱብኝ? ለምን ዝም
ብዬ ደመውዜን ሳልስራ አልበላም ብለው የሚኖሩ ስንት
አገልጋዮች አሉ፡፡ የዚህ ሰው ችግሩ መክሊቱ አንድ መሆኑ
ሳይሆን
በዚያው በተሰተው አለመስራቱ ነው፡፡ እያንዳንዱ አምኖ
በመቀበል ሊያገለግል ይገባዋል፡፡ ባለ ሁለት በባለ አምስቱ ፤
ባለ አንዱ በባለ ሁለቱ ሊቀና አይገባውም፡፡ ሁሉም ሊቀ ጳጳስ ፤
ጳጳስ ፤ ቄስ አይሆንም፡፡ ሁሉም ግን በተሰጠው ፀጋ ቢያገለግል
እውነተኞች ሊቃነ ጳጳሳት ፤ ጳጳሳት ፤ ቀሳውስት የሚያገኙትን
ዋጋ ያገኛል፡፡ ሁሉም ባለ ራዕይ ፤ ወንጌላዊ ፤ዘማሪ ፤ፈዋሽ
ሊሆን አይችልም፡፡ ለእያንዳንዱ ልዩ
ልዩ ፀጋ አለው፡፡ ሁሉም በፀጋው ቢያገለግል እኩል ዋጋ
ያገኛል፡፡
ወንድሜ አንተስ ፀጋህ ምንድን ነው? ፀጋህን ታውቀዋለህ?
ታገለግልበታለህን? አንቺስ እህቴ? መቼም ክርስቲያን ሁሉ
የክርስቶስ አካል ነው፡፡ የስራ ክፍል የሌለው የአካል ክፍል
ደግሞ የለም፡፡ አንተም/ አንቺም የክርሰቶስ አካል ነህ /ነሽ፡፡
ስለዚህ አካሉ በመሆንህ ደግሞፀጋ አለህ/አለሽ ፡፡ በመሆኑም
እንደ ፀጋችን እናገልግል፡ ፀጋውን እንቀበለው፤ ወንጌልን
በጊዜውም አለጊዜውም ሲሞላልንም ሲጎድልብንም እንስበክ
፤ ሀብታሙ ይመፅውት ፤ መምህሩ ያስተምር ፤ ዘማሪው
ይዘምር ፤ ፀሃፊው ይፃፍ ፤ ሁሉም በፀጋው ያገልግል፡፡እንድ
መክሊት እንደተቀበለው ሰው ነገ እንዲህ ብሆንስ ፤እንደዚያ
ቢፈጠርስ እያልን ባለማመን ዕለታችንን ጊዜአችንን አናባክን፡፡
መልካሙን እረኛም ያድለን! አሜን!
ወስብሃት ለእግዚአብሄር!!!!!!