ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

Saturday, February 25, 2017

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ:=>+*"+<+>†† የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት ቅድሰት ††+*"+<+>

ቅድስት ( የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት )
«ቅድስት» ማለት የዘይቤ ፍችው « የተቀደሰች የተለየች »
ማለት ነው፡፡ ምስጢራዊ መልእክቱ ግን የምስጢረ አድኅኖት
ታላላቅ ሥራውን ለመጀመር መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶሰ
በገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ ከቆመ ሳያርፍ፣ ከዘረጋ ሳያጥፍ
የጾማት የአርብዓው ቀንና ሌሊት ልዩ የሆነችና ክብርት ጾም
የምትጀመርበትን ሁለተኛ ሳምንት ከልብ ያሳስበናል፡፡ ማቴ.
4-2
ቅድሰት የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሰንበት ስያሜ ነው፡፡
ስያሜውም
ከኢትዮያዊው የዜማ ሊቅ ከቅዱስ ያሬድ የተገኘ ነው፡፡ ከዚህ
ሰንበት ዋዜማ ጀምሮ ስለ ዕለተ ሰንበት ቅድስና ይዘመራል፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ሰንበቱን ስለ ቅድስና ልጆቿን
ታስተምርበታለች ፡፡ በቅዳሴ ጊዜ የሚሰበከው ምስባክ ፤
የሚነበቡ መልዕክታት ፤የሐዋርያት ሥራ ና ወንጌል ስለ
ቅድስት
የሚያስተምሩ ናቸው፡፡
‹‹ቅዱስ›› ማለት ልዩ፤ክቡር ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር
አምላካችን በባሕርዩ ቅዱስ ነው፡፡ ይህም ቅድስና ከማንም
ያላገኘው የባሕርይ ገንዘቡ ነው፡፡ መጻሕፍትም የባሕርይ
ቅድስናውን ተባብረው መስክረዋል፡፡ ባባሕርዩ ቅዱስ ስለሆነ
‹‹ቅዱስ፡ቅዱስ፡ቅዱስ›› እየተባለ ይመሰገናል፡፡( ኢሳ 6፡
1-3፤40፡25 ራዕ 15፡4 ፤ 1ሳሙ2፡2-3፡፡) እኛም ቅዱስ
ልጁ
በሥጋ ተገልጦ እንዳስተማረን በየዕለት ጸሎታችን ‹‹ስምህ
ይቀደስ›› እንለዋለን፡፡ የቅድስና ምንጭ ፡ ቅድስናን የሚሰጥ
እርሱ ብቻ ነው፡፡ ‹‹ ቅዱስ›› የሚለው ቃል ለሰዎች ፡
ለመላእክት ፡ ለቦታ ፡ለዕቃ፡ ለዕለታት … ቢቀጸልም
ቅድስናቸው
በባሕርይው ቅዱስ ከሆነው ከእግዚአብሔር የተገኘ ነው፡፡
ይህም
የጸጋ ቅድስና ይባላል፡፡
እግዚአብሔር ቅዱስ ስለሆነ በመልኩና በምሳሌው አክብሮ
የፈጠረንን እኛም ቅዱሳን እንድንሆን ይፈለጋል፡፡ቅዱስ
ጴጥሮስ
‹‹ዳሩ ግን እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁን›› ተብሎ ስለተጻፈ
የጠራቸው ቅዱስ እንደሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ
ቅዱሳን ሁኑ ›› ያለንም ይህንን ሲያስተምረን ነው፡፡
ከመፈጠራችን አስቀድሞ መጠን በሌለው ፍቅር የወደደን
እግዚአብሔር ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣን ፤ለውርደት
ሳይሆን ለክብር፤ለርኩሰት ሳይሆን ለቅድስና፤ለሞት ሳይሆን
ለሕይወት ነው፡፡የመፈጠራችንም ዓላማ በፊቱ በፍጹም
ምግባርና ሃማኖት በመመላለስ ከእርሱ ጋር እንድንኖር ነው፡፡
ብርሃን ከጨለማ፡ ጽድቅ ከኃጢአት፡ጋር ኅብረት የለውምና
ከእርሱ ጋር ለዘላለም ነግሰን ለመኖር በቅድስና መኖር
ይጠበቅብናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ እግዚአብሔር ለቅድስና
እንጂ ለርኩሰት አልጠራንምና ›› ያለንም ለዚህ ነው፡፡/1ተሰ
4*7/ እግዚአብሔር እኛን የፈጠረበትን አላማ ለኤፌሶን
ክርስቲያኖች እንዲህ ገልጾላቸዋል ‹‹ በክርስቶስ ኢየሱስ
ሰማያዊ ሥፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን
የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ ብሎ
ካመሰገነ በኋላ ‹‹ ዓለም ሳይፈጠር በፊቱ ቅዱሳን ፡ንጹሐንና
ያለነውር በፍቅር ያደርገን ዘንድ ለእርሱ መረጠን›› ኤፌ 1፡
3-4
አስቀድሞ ስለወደደንና ስላከበረንም ከሌሎች ፍጥረታት
በተለየ
መልኩ የሚያስፈልገንን ሁሉ አዘጋጅቶ በእጆቹ ካበጀን በኋላ
የሥነ ፍጥረት ዘውድ አድርጎ በገነት አኖረን ፡፡( ዘፍ 1፡26
፤መዝ 8፡1)
የቀደመው አዳም አታድርግ የተባለውን በማድረጉ
በንዝህላልነትና በስንፍና በከይሲ ዲያብሎስም ምክር
ተዋረደ፡፡
በሞተ ሥጋ ላይም ሞተ ነፍስ ፤በርዕደተ መቃብር ላይ ርዕደተ
ሲኦል ተፈረደበት፡ በባሕርዩ ሞት ገባበት፡ተዳደፈ፡፡ ክፉ
ፍትወታት የሚያጠቁትና የሚያሸንፉት የዲያብሎስና የኃጢአት
ባርያ ሆነ፡፡ በማይለወጥ ፍቅር የወደደን እግዚአብሔር ግን
ጠፍተን እንድንቀር አልተወንም፡፡ በሰጠን ተስፋ፡በተቆጠረው
ሱባኤና በተነገረው ትንቢት መሰረት ዘመኑ ሲደርስ በተዋህዶ
ሰው ሆነ፤ የተዋረደ ሥጋችንን አከበረ፡፡ በከበረ ደሙ
ዋጀን፤ከኃጢአታችን አጠበን፡፡ በእርሱ ምክንያት
የእግዚአብሔር
ልጆች ተባልን ፡፡ጌታችንና መድኃኒታችን ሰው የሆነውና
ለመዳናችን የሆነውን ዋጋ ሁሉ የከፈለው ለእኛ ያለውን
ፍቅርና
ለኃጢአት ያለውን ጥላቻ ለእኛ ለማሳየት ነው፡፡ ‹‹ ነገር ግን
የኃጢአትን ሥራ ይሽር ዘንድ ከእርሱ ጋር የተሰቀለውን
አሮጌውን ሰውነታችን እንደሆነ ይህን እናውቃለን ››
የተባለውም
ለዚህ ነው፡፡ (ሮሜ 6፡6) እኛን ወደ ቀደመ ክብራችን
ለመመለስ የተከፈለውም ዋጋ ታላቅ ከሆነው የጋብቻ
ምስጢር
ጋር በማያያዝ እንዲህ ገልፆታል ‹‹ ክርስቶስ አካሉ ለሆነችው
ቤተ ክርሰቲያን ራስዋ አዳኝዋም እንደሆነ ወንድ ለሴት ራስዋ
ነውና … ወንዶችም ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደወደዳት
ራሱንም ስለእርስዋ ቤዛ አድርጎ እንደሰጠላት ሚስቶቻቸውን
ይውደዱ፡፡ በውኃ ጥምቀትና በቃሉ ይቀድሳትና ያነጻት ዘንድ
የነጻችና የተቀደሰች ትሆን ዘንድ እንጂ በላይዋ እድፈት ወይም
ርኩሰት እንዳይገኝባት ቤተ ክስቲያኑን ለእርሱ የከበረች
ያደርጋት ዘንድ…›› ኤፌ 5፡23-28
ስለዚህ ጌታችን በደሙ ኃጢአታችንን እንደ ቸርነቱ ይቅር
ብሎናል፡፡ኤፌ 1፡7 ከእንግዲህ የራሳችን አይደለንም ፡፡
በሰውነታችንም ኃጢአትና ዐመፃን ልናደርግበት አይገባም
፡፡‹‹በዚህ በሚሞት ሥጋችሁ ኃጢአት አታንግሷት፤ለምኞቱ
እሺ
አትበሉት፡፡ ከሙታን ተለይቶ እንደተነሳ ራሳችሁን
ለእግዚአብሔር
መሥዋዕት አድርጉ እንጂ ሰውነታችሁን ለኃጢአት የዐመፅ
የጦር መሣሪያ አታድርጉት፤ ሰውነታችሁንም ለእግዚአብሔር
የጽድቅ የጦር መሣሪያ አድርጉ››ተብለናል፡፡ (ሮሜ6፡
12-13)
የተወደዳችሁ ምዕመናን እግዚአብሔር ደስ ብሎት
የሚቀበለውን ህይወት ለመኖር አንፈልጋለን ፡፡ ለመሆኑ ይህ
ሊሆን የሚችለው እንዴት ብንመላለስ ነው? መልሱን
ሐዋርያው
ቅዱስ ያዕቆብ ‹‹አንደበቱን ሳይገታ ልቡን እያሳተ
እግዚአብሔርን የሚያመልክ የሚመስለው ማንም ቢኖር
የእርሱ
አምልኮቱ ከንቱ ነው፡፡ ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት
አምልኮ
በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፤ወላጆች የሌሉአቸውን
ልጆች ባልቴቶችንም በችግራቸው መጠየቅ በዓለምም
ከሚገኝ
ርኩሰት ሰውነትን መጠበቅ ነው፡፡››በማለት ይመልስልናል
( ያዕ
1፡26-27)፡፡ በክርስቶስ ደም የተቀደሰና የእግዚአብሔር
ማደሪያ የሆነውን ሰውነታችንን በዓለም ከሚገኝ ርኩሰት
መጠበቅ የሰማያዊ ርስት ወራሾች ያደርገናል፡፡ በዓለም
የሚገኘውን ርኩሰትም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የሥጋ
ሥራ
›› በማለት ገልጾታል፡፡‹‹እርሱም ዝሙት
፣ርኩሰት፣መዳራት፣ጣዖት ማምለክ፣ሥራይ ማድረግ፣መጣላት፣
ኩራት፣የምንዝር ጌጥ ፣ቅናት፣ቁጣ ፣ጥርጥር፣ፉክክር፣
ምቀኝነት፣ መጋደል፣ ስካር ፣ይህንም የመሰለ ሁሉ
ነው፡፡››እነዚህን የሚያደርጉ ሰዎችም ከመንግስተ
እግዚአብሔር
በአፍአ ወይም በውጭ እንደሚቀሩ ሲያስረዳ‹‹አስቀድሜ
እንደነገርኋችሁ ይህን የሚያደርግ የእግዚአብሔርን መንግስት
አያይም›› ብሏል ( ገላ5፡19)።
በሕይወታችን ሁሉ የምግባርና የሃይማኖት ፍሬ አፍርተን
መገኘት ለቅድስና የጠራንን እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት
ነው፡፡
እነዚህንም ነገሮች ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የመንፈስ ፍሬዎች ››
ብሏቸዋል፡፡ እነርሱም ‹‹ፍቅር፣ደስታ
፣ሰላም፣ትዕግስት፣ምጽዋት ፣ቸርነት ፣እምነት ፣ገርነት ንጽሕና
››ናቸው፡፡ገላ 5፡22 እግዚአብሔር ማደርያው ይሆን ዘንድ
የመረጠውን ሰውነታችንን እርሱ የሚከብርበትን ሥራ
ልናደርግበት ያስፈልጋል፡፡ ‹‹በሕይወት የሚኖሩትም ስለ
እነርሱ
ቤዛ ሆኖ ለሞተውና ለተነሣውም እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው
የሚኖሩ እንዳይሆኑ እርሱ ስለሁሉ ቤዛ ሆኖ ሞተ›› እንደተባለ
በሕይወታችን ሁሉ ፋቃዱን በመመርመርና በመፈጸም
በቅድስና
ልንኖር ይገባናል፡፡2ቆሮ 5፡15
ቅድስናችን በኑሮአችን ሁሉ እንዲሆን ታዘናል (1ጴጥ1፡15)
፡፡
ስለዚህ በተሰማራንበት የሥራ መስክ ፣በማኅበራዊ ኑራአችን
፣በምንበላው ምግብ ፣በምንለብሰው ልብስ ፣በንግግራችንና
በመሳሰለው ሁሉ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኘውን
በማድረግ
እግዚአብሔርን በሚሞት ሥጋችን እናክብረው፡፡ ‹‹እኛ ደግሞ
ሸክምን ሁሉ የኃጢአትንም ጭንቀት ከእኛ አስወግደን
በፊታችን
ያለውን ሩጫ በትዕግስት እንሩጥ፡፡ የእምነታችንንም ራስና
ፈጻሚውን ኢየሱስን እንከተለው፤ እርሱ ነውርን ንቆ ፣
በፊቱም
ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ
ተቀምጧል ›› ተብሎ እንደተጻፈ ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ
ተጋድሎ አድርገን ከኃጢአት ርቀት በቅድስና እንድንኖር
ይገባናል(ዕብ 12፡1)። ሥጋዊ ምኞታችንንና መሻታችንን
ሰቅለን አሮጌው ሰዋችንን አስወግደን ንስሐ ገብተን ቅዱስ
ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብለን በቅድስና እንድናኖር
ረድኤተ
እግዚአብሔር አይለየን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Wednesday, February 22, 2017

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ:=>+*"+<+>††7ቱ ኪዳናት+*"+<+>††

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን
እንኩዋን ለእመቤታችን ቅድስት #ድንግል_ማርያም
ዓመታዊ "የኪዳን በዓል" በሰላም አደረሳችሁ +"+"+
+*" 7ቱ ኪዳናት "*+
=>"ተካየደ" ማለት "ተስማማ : ተማማለ" እንደ ማለት
ሲሆን "ኪዳን" በቁሙ "ውል : ስምምነት" እንደ ማለት
ነው:: ይኸውም እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር: ሰዎችም ከሰዎች
ጋር የሚያደርጉት ሊሆን ይችላል:: ልዩነቱ የእግዚአብሔር
ቃል ኪዳን ቅዱስና የማይለወጥ መሆኑ ነው::
+እግዚአብሔር አምላክ ከሥነ ፍጥረት ጀምሮ በየጊዜው
ከብዙ ወዳጆቹ ጋር ኪዳንን አድርጉዋል:: ቅድስት ቤተ
ክርስቲያንም እነዚህን ኪዳናት ጥቅልል አድርጋ 7 እንደ ሆኑ
ታስተምራለች:: ስለዚህም ዛሬ ፈጣሪ ቢረዳን እነዚሁን 7
ኪዳናት በጥቂቱ እንመለከታለን::
"ኪዳነ ተካየድኩ ምስለ ኅሩያንየ"
"ከመረጥኩዋቸው ጋር ቃል ኪዳንን አደረግሁ" (መዝ. 88:3)
1. +*" ኪዳነ አዳም "*+
=>አዳም ማለት የእግዚአብሔር ድንቅ ፍጥረት: የፍጡራን
አስተዳዳሪ: ነቢይ: ካህንና ንጉሥ ነው:: እግዚአብሔር ከአዳም
ጋር አስቀድሞ በእጸ በለስ አማካኝነት ቃል ኪዳን ነበራቸው::
ነገር ግን አባታችን በዲያብሎስ ሴራ በመረታቱ ኪዳኑ ፈረሰ::
(ዘፍ. 3:1)
+አዳምና ሔዋን ተጸጽተው ቢያለቅሱ ግን አዲስ የኪዳን
ተስፋ: "ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ" የሚል ኪዳንን
ተቀበሉ:: (ቀሌምንጦስ: ገላ. 4:4)
2. +*" ኪዳነ ኖኅ "*+
=>ከአዳም እስከ ኖኅ ድረስ ባሉት 10 ትውልድ ዓለም
በዓመፃ ተሞላች:: ቅዱስ ኖኅ በደግነቱ መርከብ ሠርቶ
ቤተሰቡን ሲያተርፍ ዓለም በማየ ሥራዌ ጠፋች:: ከመርከቡ
ከወጣ በሁዋላ ኖኅና እግዚአብሔር በቀስተ ደመና ምልክትነት
ቃል ኪዳን ተጋቡ:: "ኢያማስና ለምድር ዳግመ በማየ አይኅ"
እንዲል:: (ዘፍ. 9:12)
3. +*" ኪዳነ መልከ ጼዴቅ "*+
=>መልከ ጼዴቅ የእግዚአብሔር ካህኑ: የክርስቶስም
ምሳሌው የሆነ የሳሌም ንጉሥ ነው:: በ15 ዓመቱ መንኖ:
አጽመ አዳምን ይዞ: በቀራንዮ በሕብስትና በወይን ያስታኩት
ነበር::
+እግዚአብሔር ለመልከ ጼዴቅ: በሐዲስ ኪዳን ለምትሠራው
ክህነትና ምሥጢረ ቁርባን ምሳሌ አድርጐ በቃል ኪዳን
አትሞታል:: በዚህም ተሰውሮ ይኖራል እንጂ ሞትን እስካሁን
አልቀመሰም:: ይህም ካህኑ መልከ ጼዴቅ ከአብርሃም ጋር
በተገናኙበት ጊዜ ተገልጧል:: (ዘፍ. 14:17, ዕብ. 7:1)
4. +*" ኪዳነ አብርሃም "*+
=>ቅዱስ አብርሃም የሕዝብና የአሕዛብ አባት: ሥርወ
ሃይማኖት: የጽድቅም አበጋዝ ነው:: ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር
ሲል ከርስቱና ከወገኖቹ ተለይቶ በቅድስና ኑሯልና
እግዚአብሔር "በዘርሕ አሕዛብ ይባረካሉ" አለው:: (ዘፍ.
12:1) የቃል ኪዳን ምልክትም ይሆነው ዘንድ ግዝረትን
ሰጠው:: (ዘፍ. 17:1-14)
5. +*" ኪዳነ ሙሴ "*+
=>ቅዱስ ሙሴ የነቢያት አለቃ: የእሥራኤል እረኛ:
የእግዚአብሔር ሰው እና ፍጹም ትሑት (የዋህ) ሰው ነው::
በፈጣሪው ትዕዛዝ እሥራኤልን ከግብጽ ባርነት አውጥቶ ለ40
ዘመናት በበርሃ ሲመራቸው ከእግዚአብሔር የኪዳንን ጽላትና
አሠርቱን ትዕዛዛት ተቀብሏል:: (ዘጸ. 20:1, 31:18)
6. +*" ኪዳነ ዳዊት "*+
=>ቅዱስ ዳዊት ሥርወ ነገሥት: ጻድቅ: የዋህና ቡሩክ የሆነ
አባት ነው:: እግዚአብሔር ከእረኝነት ጠርቶ ንጉሥ አድርጐ
ሹሞት "ከሆድህ ፍሬ በዙፋንህ ላይ አኖራለሁ" (መዝ.
131:11) ሲል ምሎለታል:: አክሎም ሰፊ ቃል ኪዳን ሰጥቶ
"አልዋሽህም" ብሎ ሲምልለት እንመለከታለን:: (መዝ.
88:35)
7. +*"+ ኪዳነ ምሕረት +"*+
=>በብሉይ ኪዳን የነበሩ 6ቱ ኪዳናት በዘመናቸው ክቡርና
ሕዝቡን ከመቅሰፍት ይታደጉ የነበሩ ቢሆንም ከሲዖል ማዳን
ግን አልቻሉም:: ስለዚህም አንድ ፍጹም ኪዳን ያስፈልግ
ነበር:: ይህን ፍጹም ኪዳን ይፈጽም ዘንድም ከቅድስት ሥላሴ
አንዱ ወልድ ከሰማያት ወርዶ በድንግል ማርያም ማሕጸን
አደረ::
+በፍጹም ተዋሕዶም በሕቱም ድንግልና ተወልዶ: አድጎ:
ተጠምቆ: አስተምሮ: ሙቶ: ተነስቶና ዐርጐ ሥጋ ማርያምን
በዘባነ ኪሩብ አስቀመጠው:: ኪዳነ ምሕረት (የምሕረት
ኪዳን) የምንለው አንዱ ታዲያ ይሔው ነው::
+የጌታችን መጸነሱ: መወለዱ: መሰደዱ: መጠመቁ:
ማስተማሩ: ሥጋውንና ደሙን መስጠቱ: መሰቀሉ: መሞቱና
መነሳቱ: ማረጉና መንፈስ ቅዱስን መላኩ በአንድ ላይ "ኪዳነ
ምሕረት" ይባላል:: ታዲያ ይህ ሁሉ የተደረገው በሥጋ
ማርያም ነውና የኪዳኑ ባለቤት እመቤታችን ቅድስት ድንግል
ማርያም ናት::
+የእርሷ ኪዳን የ6ቱን አበው ኪዳናት ፍጹም በማድረጉ
የኪዳናት ማሕተም ይባላል:: የድንግል ማርያም ኪዳኗ
ከሲዖልና ከገሃነም ሊታደገን አቅሙ አለውና:: መድኃኒታችን
ክርስቶስ ለድንግል እናቱ ቃል ኪዳኑን ያጸናላት ደግሞ ካረገ
ከዓመታት በሁዋላ ጐልጐታ ላይ ነው::
+እመ ብርሃን በዚያ ቁማ ስለ ኃጥአን ስታለቅስ "እናቴ ሆይ!
በስምሽ ያመነውን: በቃል ኪዳንሽ የተማጸነውን
እምርልሻለሁ" ብሎ ደስ አሰኝቷታልና:: ይሔው በእመ ብርሃን
ምልጃና ቃል ኪዳን ምዕመናን ከመቅሰፍትና ከገሃነመ እሳት
ማምለጥ ከጀመሩ 2ሺ ዓመታት ሆኑ:: ዛሬም እኛ ኃጥአን
ልጆቿ ከእሳት እንደምታድነን አምነን በጥላዋ ሥር
እንኖራለን::
+*" ኢትዝክሪ ብነ አበሳነ (ኃጢአተነ : ወጌጋየነ)
ማርያም እሙ ለእግዚእነ:
በኪዳንኪ: ወበስደትኪ ድንግል ተማሕጸነ:: "*+
"ድንግል ሆይ! ኃጢአታችን: አበሳችንና በደላችንን አታስቢብን
ዘንድ በስደትሽና በኪዳንሽ ተማጽነናል::"
=>የአርያም ንግሥት: የሰማያውያንና ምድራውያን ኁሉ
እመቤት: የአምላክ እናት: ቅድስት: ስብሕት: ክብርት:
ልዕልት: ቡርክት: ፍስሕትና ጥዕምት የሆነች ድንግል ማርያም
የድኅነታችን መሠረት: ላመኑባት አንገት የማታስደፋ እውነተኛ
አማላጅ ናት::
+በዚህች ዕለት የካቲት 16 ስለ ወገኖቿ የሰው ልጆች ፍቅር
በእንባ ያቀረበችውን ልመና የባሕርይ አምላክ የሆነ ልጁዋ
ተቀብሎ በማይዋሽ ንጹሕ አንደበቱ ቃል ኪዳን ገብቶላታል::
በስምሽ ያመነ በቃል ኪዳንሽ የተማመነ እሳትን አያይም
ብሏታል::
=>ቸሩ ልጇ ከበረከተ ኪዳኗ አይለየን:: በዓሉንም የሰላም :
የፍቅርና የበረከት ያድርግልን::
=>የካቲት 16 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ኪዳነ ምሕረት (የሰባቱ ኪዳናት ማሕተም)
2.ቅድስት ኤልሳቤጥ (የመጥምቁ ዮሐንስ እናት /
የእመቤታችን አክስት / የሶፍያ ልጅ)
3.ቅዱስ ገብረ ማርያም ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮዽያ (የቅ/ላሊበላ
ወንድም)
=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ አኖሬዎስ ንጉሥ ጻድቅ
2.አባ አቡናፍር ገዳማዊ
3.አባ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ
4.አባ ዳንኤል ጻድቅ
=>+"+"+ . . . ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች
ጊዜ ፅንሱ በማኅፀንዋ ውስጥ ዘለለ:: በኤልሳቤጥም መንፈስ
ቅዱስ ሞላባት:: በታላቅ ድምፅም ጮኻ እንዲህ አለች:-
አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ: የማኅፀንሽም ፍሬ
የተባረከ ነው:: የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት
ይሆንልኛል? እነሆ የሰላምታሽ ድምፅ በጀሮየ በመጣ ጊዜ
ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና:: ከጌታ የተነገረላት ቃል
ይፈፀማልና ያመነች ብፅዕት ናት:: +"+"+ (ሉቃ. 1:39)
<ወስብሐት ለእግዚአብሔር>

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ:=>+*"+<+>†† የእመ ቤታችን የቅድስት ኪዳነ ምህረት የንግስ በዓል ††

""የእመ ቤታችን የቅድስት ኪዳነ ምህረት የንግስ
በዓል"!!!
ኪዳነ ምህረት ማለት የምህረት መሐላ ማለት ነው፡፡
ከ" 33"በዓላተ እግዝእትነ ድንግል ማርያም አንዱ ነው፡፡
እመቤታችንም ከጌታችን መቃብር እየሄደች በምትለምንበት
ጊዜ አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉምና ምን ልታመጣብን ነው
በማለት ሊጣሏት ሲመጡ ጌታችንም ከዓይናቸው ሰውሯታል
አይሁድም ጠባቂ ቢያቆሙ እመቤታችን ዕለት ዕለት መሄዷን
አላቋረጠችን እመቤታችንም እንዲህ ብላ ስትጸልይ ልጄ
ወዳጄ ሆይ ከስጋዬ ስጋ ከነፍሴ ነፍስ ነስተህ ሰው በመሆንህ
ዘጠኝ ወር ከ5 ቀን በቻለችህ ማሕጸኔ ከአንተ ጋር ሀገር
ለሀገር ስለ መሰደዴ መትተህ ልምናዬን ትሰማኝ ዘንድ
እለምንሃለሁ አለች በዚህ ጊዜ ንውጽውጽውታ ሆነ መቃብራት
ተሰነጣጠቀ ጌታችንም እልፍ ከእልፍ መላዕክቱ ጋር መጥቶ
ሰላም ለኪ ማርያም ምን እንዳደርግልሽ ትለሚኚኛለሽ
አላት፡፡ እርሷም መታሰቢያዬን ያደረገውን ስለ ስሜ ለችግረኛ
የሚራራውን በስሜ ቤተ ክርስቲያን ያነጻውን መባዕ
የሰጠውን ከሃይማኖት ከፍቅር ጽናት ልጁን በስሜ የጠራውን
ሁሉ ማርልኝ ከሞተ ስጋ ከሞተ ነፍስ አድንልኝ አለችው፡፡
ጌታችንም ይህን ሁለ እንዳደርግልሽ መሐልኩ ለኪ በርእስየ
ወበአቡየ ሕያው ወበመንፈስ ቅዱስ ብሎ ቃል ገብቶላት
አርጓል፡፡
ሌላው በላዔ ሰብ በአማርኛ ሰው በላ ማለት ነው፤ ትክክለኛ
ስሙ ግን ስምዖን ይባላል ቅምር በሚባል አገር የሚኖር
እጅግ ባለጸጋ ነበር፤ እንደ አብርሃም እንግዶችን እየተቀበለ
ድሆችን እየመገበ የሚኖር ጻድቅ ነበር፤ ሰይጣን በዚህ ስራው
ቀናበት ሊፈትነውም በሦስት አረጋዊ ሽማግሌዎች ስላሴ ነን
ብሎ ተገለጠለት ልክ እንደ አብርሃም፤ ሐዋርያው ጳውሎስ
ሰይጣን የብርሃን መልአክ መስሎ ይመጣል እንዳለ፤ እርሱም
ሥላሴ መስለውት ተቀበላቸው ተንከባከባቸውም፤ ምግብ
አቀረበላቸው ምግብ አንበላም የምንጠይቅህን ግን
ትፈጽምልን ዘንድ ቃል ግባልን አሉት ቃል ገባላቸው
እንግዲያውስ የምትወደን ከሆነ አንድያ ልጅህን ሰዋልን
አሉት፤ መጀመሪያ ደነገጠ ኃላ አብርሃም ልጁን ሊሰዋ
አልነበረምን እኔንም ሊፈትኑኝ ይሆናል ብሎ ለማረድ
ተዘጋጀ፤ተው የሚለው ድምጽ አልሰማም፤ አረደው
አወራረደው ይዞላቸው ቀረበ፤ መጀመሪያ ቅመስልን አሉት
ቀመሰው ወዲያው እነዚያ ሰዎች ተሰወሩበት እርሱም
አህምሮውን ሳተ ተቅበዘበዘ ከዚያ በኃላ ምግብ አላሰኘውም
የሰው ስጋ እንጂ መጀመሪያ ቤተሰቦቹን በላ ከዚያም ጓደኞቹን
ጦርና የውኃ መንቀል ይዞ ከቤቱ ወጣ ያገኘውን ሰው እየገደለ
ይበላል የበላቸው ሰው ቁጥር 78 ደረሰ፤ በመንገድ ተቀምጦ
የሚለምን በደዌ የተመታ አንድ ደሃ አገኘ ሊበላው ወደ እርሱ
ተጠጋ ግን ቁስሉን አይቶ ተጸየፈው፤ ደሃውም “ስለ
እግዚያብሔር ከያዝከው ውኃ አጠጣኝ” አለው “ዝም በል
ደሃ” ብሎት አለፈ፤ “ኸረ በውኃ ጥም ልሞት ነው ስለ ጻድቃን
ስለ ቅዱሳን” አለው አሁንም ዝም ብሎት ሄደ ለሦስተኛ ጊዜ
“ስለ አዛኝቷ ስለ እምዬ ማርያም” አለው፤ ሰውነቱን አንዳች
ነገር ወረረው “አሁን የጠራከውን ስም እስኪ ድገመው ስለ
ማን አልከኝ” አለው፤ ስለ አዛኝቷ ስለ እመቤቴ ማርያም
አለው፤ ይህቺስ ደግ እንደሆነች በምልጃዋም ከሲኦል
እንደምታወጣ ህጻን እያለው እናትና አባቴ ይነግሩኝ ነበር፤ በል
እንካ አለው እጁን ዘረጋለት ጥርኝ ውኃ ጠብ አደረገለት ወደ
ጉሮሮው አልወረደም የተሰነጠቀ እጁ ውስጥ ገባ እንጂ፤ በለዔ
ሰብ ከዚያች ደቂቃ በኃላ አዕምሮው ተመለሰለት እንዲህም
አለ “በአንድ ዋሻ ውስጥ ገብቼ ስለ ኃጢያቴ አለቅሳለሁ ስጋዬ
ከአጥንቴ እስኪጣበቅ እጾማለሁ ወዮሊኝ ወዮታም አለቢኝ
አለ፤ ወደ ዋሻ ገባ ምግብ ሳይበላ ውኃም ሳይጠጣ 21 ቀን
ኖሮ በርሃብ ሞተ ይላል ተአምረ ማርያም። ጨለማ የለበሱ
ሰይጣናት እያስፈራሩ እያስደነገጡ ነፍሱን ወደ ሲኦል ሊወስዷት
መጡ፤ እመቤታችን ፈጥና በመካከላቸው ተገኘች፤ ልጄ ወዳጄ
ይህችን ነፍስ ማርሊኝ አለችው እናቴ ሆይ 78 ነፍሳትን የበላ
እንዴት ይማራል አላት፤ የካቲት 16 ቀን በጎለጎታ የገባህልኝ
ቃል ኪዳን አስብ ስምሽን የጠራ መታሰቢያሽን ያደረገን
እምርልሻለው ብለኸኝ የለምን አለችው፤ እርሱም እስኪ
ይህቺን ነፍስ በሚዛን አስቀምጧት አለ ቢያስቀምጧት ጥርኝ
ውኃው መዝኖ ተገኘ፤ ስላቺ ስል ምሬታለው ሰባት ቀን
ሲኦልን አስጎብኝታችሁ ወደ ገነት አግቧት አላቸው። ቦታሽ
እዚህ ነበር እያሉ ሲኦልን አስጎብኝተው ወደ ገነት አገቧት።
ልመናዋ ክብሯ የልጇም ቸርነት ከሁላችን ጋር ይሁን።
ተአምረ ማርያም
ድንግል ማርያም በቃል ኪዳኗ አትለየን

Monday, February 20, 2017

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ: =>+*"+<+>†† ዘወረደ /ዘመነ አዳም/- ††

ዘወረደ /ዘመነ አዳም/
የዐቢይ ጾም የመጀመሪያ ሳምንት ዘወረደ: ሙሴኒ:ሕርቃል
ይባላል፡፡ ዘወረደ ማለት፣ ከላይ የመጣ፣ የወረደ ማለት ነው፡፡
ይህም የአምላካችን ሰው መሆን ያመለክታል፡፡ ከሰማይ
ከወረደው በቀር ወደሰማይ የወጣ የለም ካለው ከጌታችን
ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ቃል በመነሳት ሊቁ ቅዱስ
ያሬድ በዚህ ዕለት ምስባክ “ዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ
ወሚመ ኢያእመሩ እግዚአ ኩሉ ዘየሐዩ በቃሉ” በማለት
በጾመ ድጓው መጀመሪያ ላይ ገልጾት ይገኛል፡፡
አዳምን ለማዳን ከሰማይ የወረደውን አይሁድ ሰቀሉት፣
የሰማይን ሥልጣን ያለው የሁሉ ጌታ እንደሆነም ምንም
አላወቁም ብሎ ተናግሮ ነበር፡፡ ይህም ድርሰት በቤተ
ክርስቲያናችን የጾም መጀመሪያ የሆነው ዕለተ ሰንበት
ዋዜማ፣ መግቢያ፣ /መሐትው/ ሆኖ ከዋዜማ በፊት
ምንጊዜም በየዓመቱ ይቆማል፡፡ ይዘመራል፡፡ ይመሰገናል
ማለት ነው፡፡
ስለዚህ የሳምንቱ ስያሜ ከዚህ የተወሰደ ነው፡፡ እንዲሁም
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራውን
የጀመረው፤ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ሰው በመሆን ፣
በዮርዳኖስ ተጠምቆ በማስተማር እንደሆነ ሁሉ የመጀሪያው
ሳምንት ዘወረደ ይባላል፡፡
በዚህ ሳምንት በተለይም እሑድና ሰኞ የሚነገሩት ውዳሴያት
ከመጻሕፍተ ኦሪትና ነቢያት የተወሰዱ ናቸው፡፡ ሁለተኛም
ሙሴኒ በመባል ይታወቃል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ አዳምን
ለማዳን ከሰማይ መውረዱንና በመስቀል መሰቀሉን
ስለሚያወሳ ነው፡፡
በተጨማሪም ይህ የመጀመሪያው ሳምንት ጾመ ሕርቃል
ይባላል፡፡ በ714 ዓ.ም.ሕርቃል /ኤራቅሊየስ/ የቤዛንታይን
ንጉሥ ነበረ፡፡ይህ ሳምንት በስሙ የተጠራበት ምክንያት
በዘመኑ ፋርሶች ኢየሩሳሌምን ወርረው የጌታችን መስቀል
ማርከው ወስደው ነበር፡፡ እርሱ ወደፋርስ ዘመቶ መስቀሉን
ከእነርሱ ነጥቆ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሷል፡፡
ሕርቃል ከፋርሶች ጋር ከመዋጋቱ በፊት ሐዋርያት
በሲኖዶሳቸው ነፍስ የገደለ ሰው እስከ እድሜ ልኩ ይጹም
ብለው ሥርዓት ሠርተዋልና ጾሙን ፈርቶ ስለነበር
በኢየሩሳሌም የነበሩ ምእመናን አሳቡን ደግፈው “አንተ
ጠላታችንን አጥፋልን ፣መስቀሉን አስመልስልን እንጂ የአንድ
ሰው እድሜ ቢበዛ ሰባ ሰማንያ ነው ፡፡ጾሙንአምስት አምስት
ቀን ተከፋፍለን እኛ ተከፋፍለን እንጾምልሃለን፡፡”ብለው
ጾመውለታል፡፡
ይህንን መሠረት በማድረግ ያላወቁት አንድ ጊዜ ጾመው
ትተውታል፡፡ ያወቁት ግን ቀድሞም ሐዋርያት ጾመውታል
ብለው ሥርዓት አድርገው በዓመት በዐቢይ ጾም መጀመሪያ
ላይ ጾመ ሕርቃል እያሉ የሚጾሙት ሆነዋል፡፡ስለዚህ
ቤተክርስቲያናችን ይህንን መሠረት በማድረግ በጌታችን
ከመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጾም የመጀመሪያውን
ሳምንት ጾመ ሕርቃል በሚል ስያሜ ሰማይ እንዲጾም
አድርጋለች፡፡ /መጋቢት 10 ስንክሳር ይመልከቱ፡፡/
የቤተ ክርስቲያናችን ታሉቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ፣ በዘወረደ ጾመ
ድጓው ሰንበት ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን፣ ሕይወት ላለው
ነገር ሁሉ ጸጥታና ሰላም የሰፈነባት የዕረፍት ቀን ስለመሆኗ
“አዘዞ እግዚአብሔር ለሙሴ ወይቤሎ ሰብዕከ ወላህምከ
ወኲሉ ቤትከ ያዕርፍ በሰንበት” ዘፀ.20፥10፣23፣12፣ ጾመ
ድጓ፣ እግዚአብሔር ሙሴን ሕዝብህ የከብትህ መንጋህ
ቤተሰብህ ሀሉ በሰንበት ቀን ከድካማቸው ይረፉ በማለት
አዘዘው ይላል፡፡ በዚህም ዘመነ ጾም፣ ወይም ጾመ ሙሴ
ይባላል፡፡
በጾመ ድጓው ዘወረደ እየተባለ የሚታወቀው፣ በጾመ አርባው
ወቅት በተለይም በመጀመሪያው ሳምንት የሚገኘው ያሬዳዊ
ድርሰት በነግህ በሠለስት፣ በቀትርና በሠርክ እንዲሁም
ቅዳሜና እዡድ በሌሊት የሚዘመር ነው፡፡ በውስጡም
የያዘው ፍሬ አሳብ፣ የጾምን፣ የጸሎትን፣ የምጽዋትንና
የፍቅርን ጠቃሚነት አጉልቶ የሚያስተምር ነው፡፡
በዚህ በጾም ወቅት በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት በአብዛኛው
ከቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች ውስጥ የሚዘመረው ምዕራፍ
የተባለው ነው፡፡ ምዕራፍ የተባለበት ምክንያትም
በየመዝሙራቱ መሀል ሃሌታና ድጓ እያስገባ ለመዝሙሩ
ማረፊያ ስላበጀለት በዚህ ምክንያት ምዕራፍ የሚል ስያሜ
ሊያገኝ ችሏል፡፡ ይህ የዜማ መጽሐፍ በሁለት ታላላቅ ክፍሎች
ይከፈላል፡፡ ይኸውም የዘወትር ምዕራፍና የጾም ምዕራፍ
በመባል ይታወቃል፡፡የዘውትር ምዕራፍ የሚባለው በዓመቱ
ውስጥ ባሉት ቀናት ውስጥ ሳምንታትና በዓላት ሁልጊዜ
በአገልግሎት ላይ የሚውል ሲሆን፣ የጾም ምዕራፍ የሚባለው
ደግሞ በጾመ አርባ ብቻ ለአገልግሎት የሚውል ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በዐሥሩ ምህላት አርዕስተ ምህላ በዚሁ
ክፍል ይካተታል፡፡ የምዕራፍ ቅንብር ከመዝሙረ ዳዊት፣
ከድጓና ከጾመ ድጓ ጋር የተቀናጀ ነው፡፡ የትምህርት
አሰጣጡም እንደ ድጓው ወይም እንደ ዝማሬ መዋሥዕቱ
መጽሐፍ ተዘርግቶ ሳይሆን በቃል የሚጠናና የሚወሰን ነው፡፡
ስለሆነም ምዕራፍን ለመማር 150 መዝሙረ ዳዊትን፣
ከነቢያት 15 ምዕራፎችንና 5 መኃልያተ ሰሎሞንን በቃል
ሸምድዶ መያዝ ይጠበቅበታል፡፡ ወይም ግድ ነው፡፡
ጾምን መጾም የፈቃድ ብቻ ሳይሆን የትእዛዝም ነው፡፡
በዘመነ ብሉይ ነቢዩ ኢዩኤል “ቀድሱ ጾመ ወስብኩ ምህላ”
ጾምን ያዙ አጽኑ ምሕላንም ዐውጁ ሸማግሌዎቹን
ከፈጣሪያችን ቤት ሰብስባችሁ በአንድነት ሁናችሁ ወደ
እግዚአብሔር ጩሁ /ለምኑ/ ብሏል፡፡ ኢዮ.ምዕ.1፥11፣
2፣12፣15-16 ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ወኲኑ ላዕካነ፣
ለእግዚአብሔር በጾም ወበንጽሕ፡፡ በጾም፣ በንጽሐና
ተወስናችሁ እግዚአብሔርን አገልግሉ ብሏል 2ቆሮ.6፥4-6፡፡
ጾም ከሌለ ወይም ተገቢ ካልሆነ ጌታችን በምትጾሙበት ጊዜ
እንደ ግብዞች አትሁኑ ስለ ጽድቅ የሚራቡ የሚጠሙ ንዑዳን
ክብራን ናቸው ለምን አለ? ማቴ.5፥፣6፣16፡፡ ነቢዩ ዳዊትም
ሰውነቴን በጾም አሳመምኳት በቀጠና፣ በሰልት አደከምኳት
ለምን አለ መዝ.34፥68፣ ት.ዳን. 9፥3-4፣ 14፥5
ነብዩ ሚኪያስ ሐዋርያት ሙሸራውን ከነሱ ለይተው
የሚወስዱበት ጊዜ ይመጣል ያን ጊዜ ይጾማሉ ያለውን የጌታን
ቃል መሠረት በማድረግ ክርስቶስ በሞት ከተለያቸው በኋላ
ጾመዋል፡፡ ጾምንም ሠርተዋል የሐዋ.ሥራ 13፥3፡፡ ሠለስቱ
ምዕትም ሐዋርያት የጾሙትንና እንዲጾም የወሰኑትን መጾም
ይገባል ብለው ቤተ ክርስቲያን የተቀበለቻቸውን አጽዋማት
እንዲጾሙ መወሰናቸው ይህን የጌታ ቃል መሠረት በማድረግ
ስለሆነ፣ የትእዛዝ መሆኑን ተገንዝበን መጾም አለብን፡፡
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሠራዔ ሕግ
እንደመሆኑ አርባ ቀን አርቦ ሌሊት ጾመ እንጂ እርሱ ሳይጾም
ጾሙ አላለንም ማቴ.4፥2፡፡ ጾመን ለማበርከት ያብቃን፡፡
አሜን!

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ: =>+*"+<+>†† የዐቢይ ጾም የመጀመሪያው ሳምንት ዘወረደ ††

. ዘወረደ ወይም ሕርቃል ወይምሙሴኒ
✔ የዐቢይ ጾም የመጀመሪያው ሳምንት ዘወረደ ይባላል፡፡
‹‹ዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ›› የሚልና ይህንን
የመሳሰለ ጌታ እኛን ለማዳንና ፍቅሩን ሊገልጽልን ከሰማያት
መውረዱን ከድንግል ማርያም የእኛን ሥጋ መዋሐዱን
የሚያዘክር ምስጋና የሚቀርብበት ሳምንት ነው፡፡
✔ ሌላም ስም አለው ጾመ ሕርቃል ይባላል፡፡ ይህ ጾም
የጾም መግቢያ የመጀመሪያ ሳምንት የምንጾመው ጾም
ሲሆን ሕርቃል የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡
✔ ሕርቃል ማን ነው? ለምንስ በስሙ ተሰየመ? በ614
ዓ.ም ኪርዮስ የተባለ የፋርስ ንጉሥ ኢየሩሳሌምን በመውረር
ጥቃት አደረሰ፡፡
✔ በዚህ ወቅት በኢየሩሳሌም ንግሥት ዕሌኒ በሠራችው
ቤተመቅደስ ውስጥ ሲገባ ንግሥቷ በክብር አስቀምጣው
የነበረው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል
እንደ ፀሐይ ሲያበራ አገኘው፡፡
✔ ቢነካው አቃጠለው ዲያቆናቱን አሸክሞ ሌላውን ንዋየ
ቅድሳት ዘርፎ 60ሺ የሚደርሱትን አቁስሎ ገድሎ 3ሺ
የሚሆኑትን ማርኮ ከተማዋንም አቃጥሎ ወደ ፋርስ ባቢሎን
ይመለሳል፡፡
✔ በዚህ ጊዜ ከጦርነቱ ያመለጡ በየዋሻው በየጉራንጉሩ
ገብተው የተሸሸጉ ተሰብስበው ከ14 ዓመት በኋላ በ628
ጩኸታቸውንና የደረሰባቸውን በደል ለክርስቲየኑ የሮም
ንጉሥ ሕርቃል ይነግሩታል፡፡
✔ እርሱም ሐዋርያት ሰውን የገደለ እድሜውን በሙሉ
ይጹም ስላሉ እንዴት ላድርገው አላቸው እኛ የአንተን እድሜ
ተከፋፍለን እንጾማለን ብለው አንድ አንድ ሳምንት ደርሷቸው
ጾሙን በሚገባ ጾመውታል፡፡
✔ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልና የተማረኩ
ክርስቲያኖችን ለመመለስ ሕርቃል ጦር መዝዞ በኪርዮስ ላይ
ተነሳበት ድል ለሕርቃል ሆነና መስቀሉን ያለበትን አጥቶ
ሲቸገር መስቀሉን ሲቀብርና ዲያቆናቱን ሲያስገድል በመስኮት
ሆና ያየችው ከኢየሩሳሌም የተማረከች አንዲት ብላቴና
አሳይታው አውጥቶ በልብሰ መንግሥቱ ጠቅልሎ ወደ
ቁስጥንጥንያ ተመለሰ፡፡
✔ የተማረኩት በሙሉ ነጻ ወጡ ይህን ለማሰብ ለማስታወስ
በተጨማሪ በኃጢአት ላይ ድል እንድናገኝ መንፈሳዊ ጦር
በውስጣችን እንዲበዛልን መስቀልህ ከምርኮ እንደተመለሰ
እኛንም ከኃጢአት ምርኮ መልሰን ለሕርቃል ድል መንሳትንና
በጠላቶቹ ላይ ኃይልን እንደሰጠኸው ለእኛም በኃጢአት ላይ
ድል መንሳት መንፈሳዊ ኃይልን ስጠን እያልን እንጾመዋለን፡፡
✔ በጌታ ጾም ላይ እንዲጾም የሆነበት ምክንያት ጾሙ
የጌታ ጾም በሚጾምበት ወቅት ላይ ስለተጾመ
ቤተክርስቲያናችን አብራ ደንግጋዋለች፡፡
✔ እዚህ ላይ በዚያን ጊዜ ለሕርቃል ሕዝቡ ሱባኤ
ይዞለታል፡፡ ዛሬም እኛ ለቤተክርስቲያን ያደረግነውን በማሰብ
እግዚአብሔር አምላክ ለሕርቃል የሰጠውን በጠላቶቹ ላይ
ድል መንሳትን ለእኛም እንዲሰጠን የምንጠይቅበት ስለሆነ
የመጀመሪያውን ሳምንት በሕርቃል ሰይመን ጾሙን
እንጾማለን፡፡
✔ የእኛ ጠላት የጨለማ ገዥ የሆነው ዲያቢሎስ ነውና
እሱን ደግሞ በጾም እንደምናሸንፈው ጌታችን መድኃኒታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮናል፡፡
✔ «ዘወረደ» ማለትም በቀጥታ፣ ቃል በቃል ሲተረጐም
«የወረደ» ማለት ነው፡፡ ይህም በምስጢሩ አምላክ ወልደ
አምላክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤዛ ዓለም በቅዱስ ፈቃዱ
ሰው ሆኖ ከሰማየ ሰማያት = ከባሕርይ ልዕልናው በትሕትና
ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱን የሚያመላክት፣
ይህም የሚታወስበት፣ የሚወሳበት የዐቢይ ጾም አንደኛው
ሳምንት ነው፡፡ 《ዮሐ.3-13》፡፡
✔ ሳምንቱ ሙሴኒ የተባለበትም ምክንያት በዚሁ ሳምንት
መጀመሪያ የሰኞ ዕዝል «ከመዝ ይቤ ሙሴ ፀዓቱ
እምትእይንት» «ሙሴ ከከተማ መውጣቱ እንደዚህ ነው አለ»
ስለሚል እንደዚሁም የዚሁ ዕለት ማለት የሰኞ አቡን «ሙሴኒ
ይቤ በውስተ ኦሪት ምድር ሰናይት» እያለ የሙሴን ታሪክ
ስለሚያጠቃቅስ ሳምንቱ ሙሴኒ ተባለ፡፡
✔ ነቢያትም አርባ አርባ ቀን ጾመው ከአለፉ በኋላ የሙሴ
ሕግና ትንቢተ ነቢያት ፈጻሚ የሆነው ምላካችን እንደ እነሱ
40 ቀንና 40 ሌሊት መጾሙን የሚያስታውስ ነው፡፡
《ዘፀ.24-18》፤ 《1ኛ.ነገ.19-8》፤ 《ማቴ. 4-1-4》፡፡
↪ ወስብሐት ለእግዚአብሔር
↪ ምንጭ፡- ጾምና ምጽዋት