ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

Thursday, June 2, 2016

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ: =>+*"+<+>ግንቦት 25<+>+"*+

ግንቦት 25-
እመቤታችንን በስደቷ ጊዜ አብራት ተሰዳ ድካሟን
የተካፈለቻትና ልጇን መድኃኔዓለምን በጀርባዋ አዝላ ገላውንም
አጥባ ትንከባከበው የነበረችው ቅድስት ሰሎሜ ዕረፍቷ ነው፡፡
+ በዚኽችም ዕለት ጌታችን የደረቁ በትሮችን ያለመለመበት
ዕለት ነው፡፡ ይኸውም የአረገዊ ዮሴፍን በትሮች በአረንጓዴ ቦታ
ላይ ቢተክላቸው ወዲያው ዛፎች ሆኑ፡፡
+ ከበሬዎች ጋር ተጠምደው ሰማዕትነትን የተቀበሉት አቡነ
ሕፃን ሞዐ በዓለ ፅንሰታቸው ነው፡፡
+ ከእንዴና አገር የተገኘው የከበረ ቅዱስ ኮጦሎስ በሰማዕትነት
ዐረፈ፡፡
+ ስብስጣ ከሚባል አገር የተገኘው የከበረ አባ ኄሮዳ
በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡
ቅድስት ሰሎሜ፡- ይኽችም ቅድስት የእመቤታችን የአክስት
ልጅ ናት፡፡ እርሷም የማጣት ልጅ፣ የሌዊ ልጅ፣ የሚልኪ ልጅ፣
የካህን አሮን ልጅ ናት፡፡ ማጣትና ሄርሜላ ሶፍያ፣ ማርያምና
ሐና የሚባሉ ሴቶች ልጆችን ወልደዋል፡፡ ቅድስት ሐና ድንግል
ማርያምን ወለደች፣ ድንግል ማርያምም መድኃኔዓለም
ክርስቶስን ወለደች፡፡ ሶፍያ ኤልሳቤጥን ወለደች፣ ኤልሳቤጥም
መጥምቁ ዮሐንስን ወለደች፡፡ ማርያምም ሰሎሜን ወለደች፡፡
እመቤታችን ጌታችንን በወለደችው ጊዜ ቅድስት ሰሎሜ
የእመቤታችን አወላለድ እንደ ሌሎቹ ሴቶች ያለ አወላለድ
መስሏት ነበርና የእመቤታችንን ሆዷን ዳሰሰቻት፡፡ በዚህም
ጊዜ እጇ ተኮማትሮ ተቃጠለ፡፡ ሕፃኑን በዳሠሠችው ጊዜ ግን
እጇ ዳነችላት፡፡ በዚህም እመቤታችን አምላክን እንደወለደች
ዐወቀች፡፡ እመቤታችንን በስደቷ ጊዜ አብራት ተሰዳ ድካሟን
ተካፍላታለች፡፡ ጌታችንንም በጀርባዋ አዝላ፣ በክንዶቿ
ታቅፋዋለች፡፡ ገላውንም የምታጥብበትም ጊዜ ነበር፡፡ ጌታችን
ሰው በሆነበት ወራት ሁሉ ከእርሱ አልተለየችም፡፡
በመከራውም ጊዜ እያለቀሰች ተከትላዋለች፡፡ ከሙታን ተለይቶ
በተነሣም ጊዜ ወደ መቃብሩ ገስግሳ ትንሣኤውን ከሐዋርያት
ቀድማ ያየች ናት፡፡ በ50ኛም ቀን መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ
ከሌሎቹ ሴቶች ጋር ሆና ሰማያዊ ሀብትን ከተቀበለች በኋላ
ቅድስት ሰሎሜ በጌታችንም ስም ወንጌልን አስተራለች፡፡
ብዙዎችንም አሳምና ያስጠመቀች ድንቅ እናት ናት፡፡
ከአይሁድም የሚደርስባት መከራ በጸጋ ተቀብላ ግንቦት 25
ቀን ዐርፋለች፡፡ የቅድስት ሰሎሜ ረድኤት በረከቷ ይደርብን፣
በጸሎቷ ይማረን፡፡
+ + + + + + + + + + + + + + +
ሰማዕቱ ቅዱስ ኮጦሎስ፡- የዚኽም ቅዱስ ወላጆቹ
እግዚአብሔርን የሚፉ ደጋግ ክርስቲያኖች ናቸውና ጌታችንን
ልጅ እንዲሰጣቸው አጥብቀው ከለመኑትና እርሱም የተባረከ
ልጅ ከሰጣቸው በኋላ ልጃቸውን በሃይማኖት በምግባር
አሳደጉት፡፡ አባቱም የእንዴናው ገዥ መኮንን ነው፡፡
ቅዱስ ኮጦሎስም ለራሱ ሥርዓትን በመሥራት በቀን አንድ
መቶ በሌሊትም አንድ መቶ ጸሎታትን ይጸልያል፡፡ ዕድሜውም
በደረሰ ጊዜ ወላጆቹ ሊያጋቡት ሲሹ እርሱ ግን እምቢ አላቸው፡፡
ነገር ግን ወላጆቹ ታናሽ እኅቱ የሆነችውን ሴት ልጃቸውን
ከአርያኖስ ጋር አጋቧት፡፡ አባቱም ከሞት በኋላ ቅዱስ ኮጦሎስ
የስደተኞችና መጻተኞች መቀበያ ቤት ሠርቶ እንግዳን ሁሉ
የሚቀበል ሆነ፡፡ ከዚኽም በኋላ የጥበብ መጻሕፍትን ተምሮ
ሐኪም ሆነ፡፡ ሕሙማንም ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ ያለምንም
ዋጋ የሚፈውሳቸው ሆነ፡፡
ከሃዲው ዲዮቅልጥያኖስም ጌታችንን በካደ ጊዜ አርያኖስ
ስለሹመቱ ከንጉሡ ጋር ተስማምቶ ሰማዕታትን የሚያሠቃይ
ሆነ፡፡ በዚኽም ጊዜ ቅዱስ ኮጦሎስ ሰማዕት ይሆን ዘንድ
ተመኝቶ ወደ ሰማዕትነት አደባባይ ወጥቶ አርያኖስን፣ ንጉሡን
ዲዮቅልጥያኖስንና አለቆቹን ሁሉ ስለ ጣዖት አልኮአቸው
ሰደባቸው፣ ጣዖታቱንም ሰደበ፡፡ አርያኖስም ስለ እኅቱ ብሎ
በቅዱስ ኮጦሎስን ከእሥር ፈታው፡፡ ከአርያኖስም በኋላ ሌላ
መኮንን በተሾመ ጊዜ የቅዱስ ኮጦሎስን ዜና እና ገድል ነገሩት፡፡
ጭፍራ ልኮ ወደ እርሱ ካስመጣው በኋላ ለአማልክት
እንዲሰግድ አስገደደው፡፡ ቅዱስ ኮጦሎስም ‹‹ከዕውነተኛው
አምላክ ከክርስቶስ በቀር የሚገዙለት አምላክ የለም፣ ለእርሱ
ብቻ እሰግዳለሁ›› አለው፡፡ በዚኽም ጊዜ መኮንኑ ተቆጥቶ ልዩ
ልዩ በኾኑ ሥቃዮች አሠቃየው፡፡ ነገር ግን የታዘዘ መልአክ
እየመጣ ቅዱስ ኮጦሎስን ከቁስሉ ሁሉ ይፈውሰውና ያጽናናው
ነበር፡፡ ጌታችንም በዚኽ ቅዱስ እጆች ብዙ ድንቅ ድንቅ
ተአምራትን አደረገ፡፡
መኮንኑም ቅዱስ ኮጦሎስን ማሠቃየት በሰለቸው ጊዜ አንገቱን
በሰይፍ ይቆርጡት ዘንድ አዘዘ፡፡ እንደትእዛዙም ሰየፉትና
የሰማዕትነት ፍጻሜው ሆነ፡፡ ከሥጋውም ብዙ ተአምራት
ተገልጠው ታዩ፡፡ የሰማዕቱ የቅዱስ ኮጦሎስ ረድኤት በረከቱ
ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡
+ + + + + + + + + + + + + + +
ሰማዕቱ አባ ኄሮዳ፡- ይኽም ቅዱስ አባ ኄሮዳ ከሕጻንነቱ
ጀምሮ በፈሪሃ እግዚአብሔር ያደገ ነው፡፡ በዘመኑም ከሃዲው
ንጉጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ነግሦ ነበርና አባ ኄሮዳ አንድ ቀን
ተኝቶ ሳለ ስለዚኽች ከንቱ አላፊ ዓለም አሰበ፡፡ ጌታችን ‹‹ይኽን
ዓለም ያልካደ ሊያገለግለኝ አይችልም›› ያለውን አስታውሶ
በስሙ ሰማዕት ይኾን ዘንድ ወደደ፡፡ ይኽንንም በልቡ ሲያስብ
ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ወደ እርሱ መጥቶ ‹‹የከበርክና
የተመሰገንክ ኄሮዳ ሆይ! ሰላም ለአንተ ይሁን፡፡ እግዚአብሔር
የክብር ዙፋን አዘጋጅቶልሃልና እኔም የመላእክት አለቃ
ሚካኤል ወደ ፍርድ አደባባይ ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፣
ከመከራውም አጸናሃለሁና ሰማዕትነትህን በድል ትፈጽማለህ››
ብሎት ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡
ከዚኽም በኋላ ቅዱስ አባ ኄሮዳ ወደ ምዕራባዊ ክፍል ወጥቶ
ከጸለየ በኋላ ወደ ፍርድ አደባባይም ሄዶ ‹‹እኔ የክብርን ባለቤት
ክርስቶስን የማመልክ ክርስቲያን ነኝ›› ብሎ በግልጥ ጮኸ፡፡
ከሃዲው መኮንን ሉክያኖስም ይዞ የመጣበትን ጠየቀው፡፡ አባ
ኄሮዳ ከብሕንሳ አውራጃ ስብስጣ ከምትባል አገር እንደሆነና
አስቀድሞም የምድራዊ ንጉሥ ባለሟል እንሆነ ነገረው፡፡
መኮንኑም ‹‹ለአማልክት ሠዋና ብዙ ገንዘብ ሰጥቼህ
ከጭፍሮቼ ሁሉ የበላይ አድርጌ ልሹምህ›› አለው፡፡ አባ ኄሮዳ
ግን ስለ አምኮተ ጣዖቱ ሉክያኖስን ገሠጸው፣ ጣዖታቱንም
ረገመበት፡፡ መኮንኑም እጅግ ተቆጥቶ እሾህ ባላቸው የብረት
ዘንጎች በጽኑ አስደበደበው፣ ከሥቃዩም የተነሣ የቅዱሱ ደሙ
እንደውኃ ፈሰሰ፡፡ ጌታችንም መልአኩን ልኮ ፈወሰውና ፍጹም
ጤነኛ አደረገው፡፡ ዳግመኛም ልዩ ልዩ በሆኑ ሥቃዮችም
አሠቃየው፡፡ ይኽንንም ተአምር ያዩ ሰዎች ‹‹በአባ ኄሮዳ
አምላክ በክርስቶስ አምነናል›› ብለው እየመሰከሩ ሰማዕትነትን
ተቀበሉ፡፡ ቁጥራቸውም ሠላሳ ሺህ አምስት መቶ ሆነ፡፡
መኮንኑም አባ ኄሮዳን ማሠቃየት በሰለቸው ጊዜ ራሱን በሰይፍ
እንዲቆርጡት አዘዘ፡፡ በዚኽም ጊዜ ጌታችን ለአባ ኄሮዳ
ተገለጠለትና ‹‹በችግርና በመከራ ውስጥ ያለ ሰው ቢኖር
በስምህ ቢማጸን ፈጥኖ ከችግሩና ከመከራው ይድናል›› የሚልና
ሌላም ብዙ ታላቅ የምሕረት ቃልኪዳን ገባለት፡፡ ከዚኽም
በኋላ አባ ኄሮዳ ወደ ሕዝቡና ወደ ሰያፊዎቹ ተመልሶ ካረፈ
በኋላ ስለ ሥጋው ነገራቸው፡፡ በታላቅ ደስታም ተመልቶ
ለሰያፊዎቹ ‹‹የታዘዛችሁትን ፈጽሙ›› ብሎ አንገቱን አውጥቶ
ሰጣቸው፡፡ በዚኽችም ዕለት ሰማዕትነቱን በድል ፈጽሞ
አስቀድሞ ጌታችን ቃል የገባለትን የድል አክሊል ተቀዳጀ፡፡ ከ3
ወርም በኋላ ቅዱስ ሥጋውን ወደ አገሩ ወስደው ያማረች ቤተ
ክርስቲያን ሠርተው በውስጧ አኖሩት፡፡ ከሥጋውም ብዙ
ተአምራት ተገልጠው ታዩ፡፡ ለሕሙማንም ፈውስ ሆነ፡፡ የአባ
ኄሮዳ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡
+ + + + + + + + + + + + + + +
አቡነ ሕፃን ሞዐ፡- በአባታቸው አርከሌድስ እናታቸው ትቤ ጽዮን
ይባላሉ፡፡ የተወለዱት ጥር 25 ነው፡፡ አቡነ ሕፃን ሞዐ እና ከእነ
አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጋር የሥጋ ዝምድና አላቸው፡፡ ይኸውም
አባታቸው አርከሌድስና ጸጋ ዘአብ ወንድማማቾቸ ናቸው፡፡
አርከሌድስና ጸጋ ዘአብ ሌሎች ሌሎች 4 ወንድሞች አሏቸው፡፡
እነርሱም እንድርያስ፣ ዘርዐ አብርሃም፣ ቀሲስ ዮናስ እና ቀሲስ
ዮሐንስ ናቸው፡፡ አርከሌድስ ሕፃን ሞዐን ይወልዳል፣ ጸጋ ዘአብ
ተክለ ሃይማኖትን ይወልዳል፣ እንድርያስ ሳሙኤል ዘወገግን፣
ዘርዐ አብርሃም ታላቁ አኖሬዎዮስን፣ ቀሲስ ዮናስ
ገላውዲዮስንና የፈጠጋሩን ማትያስን፣ እና ቀሲስ ዮሐንስ
ዜናማርቆስን ይወልዳሉ፡፡ እነዚህ የከበሩ ቅዱሳን አባቶቻችን
በእናታቸውም ወገን ቢሆን እንዲሁ በዝምድና የተቆራኙ
ናቸው፡፡ አቡነ ሕፃን ሞዐ በሌላኛው ስማቸው ሕፃን ዘደብረ
በግዕ ተብለውም ይጠራሉ፡፡ ይኸውም የደብረ በግዕን ገዳም
የመሠረቱት እርሳቸው ስለሆኑ ነው፡፡ ከ47ቱ የሀገራችን
ቀደምት ቅዱሳን ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡ በመንዝና በተጉለት
የሚገኙ ታላላቅ ገዳማትን አብዛኞቹን የመሠረቷቸው አቡነ
ሕፃን ሞዐ ናቸው፡፡ ጻድቁ በክፉዎች ወሬና ሴራ ምክንያት ከበሬ
ጋር ተጠምደው ሰማዕትነት የተቀበሉ አባት ናቸው፡፡ ከበሬ ጋር
ሲታረሱ ውለው በእጅጉ ከደከማቸው በኋላ በኃይል የተነፈሱባት
ምድሪቱ ዛሬም ድረስ ልክ እንደሰው የሚሞቅ ትንፋሽ
ታወጣለች፡፡ ያም በጻድቁ እስትንፋስ አምሳል ከመሬት ውስጥ
የሚወጣው እስትንፋስ ለአስም በሽታ መድኃኒት ሆኖ ብዙዎችን
እየፈወ ነው፡፡ ገዳማቸው ከደብረ ብርሃን ከተማ በእግር የ2
ሰዓት መንገድ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ይኸውም ከወንይዬ ተክለ
ሃይማኖት ገዳም አጠገብ ነው፡፡ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣
በጸሎታቸው ይማረን፡፡