ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

Monday, May 30, 2016

=>+*"+<+>ሰማእቱ ጊዮርጊስ<+>+"*+

ሰማእቱ ጊዮርጊስ
በስመ ሥላሴ
ጊዮርጊስ ማለት ኮከብ፣ ብሩህ፣ ሐረገወይን፣ ፀሐይ ማለት ነው።
ቶማስስ ዘልዳ እንዲለው ሀገሩ ልዳ ነው። አባቱ ዞሮንቶስ
(እንስጣስዮስ) በልዳ መስፍንነት ተሹሞ ይኖር ነበር። እናቱ
ትዎብስታ (አቅሌስያ) ትባላለች። ማርታ ድስያ የሚባሉ እህቶች
ነበሩት።
አስር አመት ሲሆነው አባቱ ሞቶ ሞቶ ሌላ መስፍን ተሾመ።
ደግ ክርስታናዊ ነበርና ወስዶ እያስተማረ አሳደገው። እርሱም
ፈረስ መጋለብ ቀስት መወርወር ለመደ። ጦር ሜዳ ወጥቶ
ከጠላቶቹ መሀል ገብቶ “እኔ የክርስቶስ ወታደር ጊዮርጊስ
መጣሁባችሁ” ሲላቸው ደንግጠው ይሸሹ ነበር።
ጽኑ የእምነት አርበኛ በመኳንንቱ በሹማምንቱ በነገስታቱ ፊት
የማይፈራ ድንቅ ወጣትም ነበር። ሃያ ሲሞላው መስፍኑ የ 15
ዓመት ቆንጆ ልጅ ነበረችውና እሷን ድሮለት ሀብቴን ወርሶ
ይኑር ብሎ ድግስ ሲያስደግስ ዳስ ሲያስጥለ ጌታ ቅዱስ
ጊዮርጊስን ለዚህ አላጨውምና የመስፍኑን ነፍስ ወሰደ።
እርሱም ሀዘኑን ጨርሶ ወደ ቤሩት ሄደ። ቤሩት በኢያርኮ
አቅራቢያ ያለች ሀገር ናት። በዚያ በቤሩት ሰዎች
እግዚአብሔርን የማያውቁ ለዴጎን የተንበረከኩ ናቸው።
ቤሩታዊቷንም የሹም ልጅ ለዚሁ ዘንዶ ግብር ሊገብሩለት
ከግንድ ወስዶ አሰሩለት። ቅዱስ ጊዮርጊስም በዚያ ሲያልፍ
የልጅቱን የጩኸት ድምጽ ሰማ። እሱም ምን ሆነሽ ነው?
አላት። ለደራጎን ተሰጥቼ ነው አለችው። አምላካችሁ ወዴት አለ
አላት ምግቡን ሊፈልግ ሄዷል አለችው። ይህን እያነጋገራት እያለ
ደራጎኑ ምድሪቱን እያነዋወጠ መጣ። ሂድ ይበለሃል ስትለው፤
እኔማ ምን አለኝ ከኔ ጋር ያለው ግን ከሱ ይበልጣል አላት።
ሊበላው ሲቀርብ ስመ እግዚአብሔር ጠርቶ ቢያማትብበት በላዩ
ያደረው ሰይጣን እንደ ጉም ተኖ እንደትቢያ በኖ ጠፋ፤ ሃይሉም
ደከመ። ቤሩታዊቷ አንገቷን በታሰረችበት ገመድ አስሮት እሷ
እየጎተተች እሱ በፈረስ ሆኖ ከተማ ደረሰ። ሕዝቡን ሊያስፈጅ
ነው ብለው ይሸሹ ጀመር። አጽናንቶ መለሳቸው። ንጉሱ
ዱድያኖስ ግን ተነሳስቶበት ክርስቶስን ካድ ባለው ጊዜ አምላኬ
ክርስቶስን አልክድም በማለቱ ተቆጥቶት ጥጋውን በመቃጥን
አስተፍትፎታል፤ ረጅም ችንካሮች ያለበት የብረት ጫማ
አጫምቶታል፤በችንካር አስቸንክሮታል፤ በፈላ ውሃ ውስጥ
አስጨምሮታል።
አጥንቱን አስከስክሶታል። መሄድ እስኪያቅተው ድረስ፤
መርዝም በጥብጦ አጠጥቶታል። በመንኩራኩር አስፈጭቶት
ከጥልቅ ጉድጓድ ጥሎታል። ብዙውን ጊዜ በመንኩራኩር
ተፈጭቷል፤ በኋላም በደብረ ይድራስ ላይ አጥንቱን በትኗል።
መከራ ፈተና አብዝቶበታል። ፯ ጊዜ ሞቶ ፯ ጊዜ ተነስቷል።
አቤት የቅዱሳን መከራቸ፤ ለዚህ እኮ ነው ቅዱስ ጳውሎስ
“እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፥ ጽድቅን አደረጉ፥
የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ፥ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፥ የእሳትን
ኃይል አጠፉ፥ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፥ ከድካማቸው በረቱ፥
በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ፥ የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ። ሴቶች
ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ
የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤
ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ
በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤ በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ተፈተኑ፥
በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ
መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው
ዞሩ፤ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና
በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ። እነዚህም ሁሉ በእምነታቸው
ተመስክሮላቸው ሳሉ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አላገኙም፥ ያለ
እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ እግዚአብሔር ስለ እኛ አንዳች
የሚበልጥ ነገርን አስቀድሞ አይቶ ነበርና። (ዕብ.፲፩፡፴፫-፵)
11፡33-40
ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔ ግን ነፍሱን
የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል። ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ
ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ
ቤዛ ምን ይሰጣል? የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር
ይመጣ ዘንድ አለውና፤ ያን ጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው
ያስረክበዋል።(ማቴ.16፡ 25-27
እኔን የሚወድ ቢኖር እራሱን ይካድ መስቀሌንም ተሸክሞ /
መከራዬን ሳይሰለች/ ዕለት ዕለት ይከተለኝ፡፡ ማቴ 10፡38-42
እንዲል ወንጌል
ስለ ጽድቅ የሚራቡና የሚጠሙ፣ እንዲሁም የሚሰደዱ ብጹዓን
ይጠግባሉና፣ መጽናናትንም ያገኛሉና… ጌታ በተራራ ስብከቱ
ከተናገራቸው፣ ካስተማራቸው የሕይወት ምግብ የሆነ ቃሉ
ማቴ.5፡1-ፍጻሜ
ጊዮርጊስ ሆይ ጨካኝ ቁጡ በሆነው በዱድያኖስ አደባባይ ልዩ
ልዩ ተዓምራትህን እንደማድረግህ በጠዋት በማታ በከንቱ ነገር
የሚነሳሱብኝ ጠላቶቼ ሁሉ እንደ አመድ በነው እንደ ጢስ ተነው
ይጥፉ፡፡
ጊዮርጊ ሆይ ሰማዕታት ሁሉ አለቃ እንደመሆንህ ቀድሞ ሰብዓ
ነገስታትን እንደደመሰስካቸው ነበልባላዊ በምትሆን ጸሎትህ
ጠላቶቼን ደምስሳቸው፡፡
ተዓምረኛው ሰማዕት ሆይ ቀድሞ የቢፋሞንን ልጅ ከሰዕበተ
ሃጢአት ሰውነቱን እንድቀደስከው መንግስተ ሰማያትን
ለመውረስ እበቃ ዘንድ ሰውነቴን በፍጹም መቀደስ ከሃጢአት
ርኩሰት ንጹህ አድርግልኝ፡፡
ተዓምረኛው ሰማዕት ሆይ ሙታንን የማስነሳት ሥልጣን
ተሰጥቶሃልና አቤቱ ቤሩታዊትን ከአፈ ዘንዶ እንዳዳንካት እኔን
ከእለተ እኪት ከዘመነ መንሱት በጸሎትህ አድነኝ፡፡
አቤቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ አምላክ ሆይ ማረን፤አቤቱ የቅዱስ
ጊዮርጊስ አምላክ ሆይ ራራልን፤ አቤቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ
አምላክ ሆይ ይቅር በለን፡
እግዚአብሔር አምላካችን ሰማዕታትን በደም ቅዱሳንን
በገዳም ሐዋርያትን በአጽናፍ ዓለም መላዕክትን በአጽራርያም
እንዳጸናቸው እኛ ሁላችንንም በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነታችን
በቅድስት ቤተክርስቲያን በበጎ ምግባር በጾም በጸሎትና
በትሩፋት ያጽናን አሜን አሜን አሜን!!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር