ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

Sunday, May 15, 2016

=>+*"+<+>+ ግንቦት 7 +<+>+"*+

<<< በስመ አብ: ወወልድ: ወመንፈስ ቅዱስ: አሐዱ አምላክ . . . አሜን:: >>>
+<+>+ ግንቦት 7 +<+>+
+*" ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ "*+
=>በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከሐዋርያት ቀጥሎ የቅዱስ
አትናቴዎስን ያሕል ስለ ሃይማኖት የተዋጋ ቅዱስ ፈልጐ
ማግኘት አይቻልም::
=>ቅዱስ አትናቴዎስ ማን ነው?
=>ቅዱስ አትናቴዎስ በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት
በዘመነ ሰማዕታት መጠናቀቂያ በ300 (296) አካባቢ
እስክንድርያ (ግብፅ) ውስጥ ነው የተወለደው:: ወላጆቹ
አረማውያን በመሆናቸው ክርስትናን አልተማረም ነበር::
+ሕጻን እያለ ለጭዋታ ከቤቱ ሲወጣ የክርስቲያን ልጆች
ሃይማኖታዊ ጨዋታ ሲጫወቱ ተመለከተ:: ሊቀላቀላቸው
ቢፈልግም ክርስቲያን ባለመሆኑ ከለከሉት:: አትናቴዎስም
"ክርስቲያን ልሁንና አጫውቱኝ" ብሏቸው "እሺ" ስላሉት
ሕጻናቱ ዕጣ ተጣጣሉ::
+ላንዱ ቄስ : ላንዱም ዲያቆን መሆን ሲደርሳቸው ለአትናቴዎስ
ፓትርያርክ መሆን ስለ ደረሰው ሌሎቹ ሕጻናት ይሰግዱለት
ጀመር:: በአጋጣሚ ሕጻናቱ ይሕንን ሁሉ ሲያደርጉ የወቅቱ
ፓትርያርክ ቅዱስ እለ እስክንድሮስ በመገረም ያያቸው ነበርና
ለሕጻኑ አትናቴዎስ ትንቢት ተናገረለት::
+ከዚያም የአትናቴዎስ አባቱ ሲሞት ሊቀ ዻዻሳቱ ከእናቱ ወስዶ
አጥምቆ : የሚገባውን መንፈሳዊ ትምሕርት ሁሉ በልቡናው
ላይ ቀረጸበት:: ከዚሕ በሁዋላ ዲቁናን ሹሞ አስተምር አለው::
ምንም ሕጻን ቢሆንም ከሊቅነቱ : ከአመላለሱና ከአንደበቱ
ጣፋጭነት የተነሳ የሰማው ሁሉ ይደነቅ ነበር:: ጸጋ
እግዚአብሔር በእርሱ ላይ አድራለችና::
+ቅዱስ አትናቴዎስ ሊቀ ዲቁና በተሾመ ወራት አርዮስ ቤተ
ክርስቲያንን በመረበሹ ኒቅያ ላይ 318ቱ ሊቃውንት ሲሰበሰቡ
ጸሐፊ አድርገው ሾሙት::
+በጊዜውም በዕድሜ የስንት ጊዜ ትልቁ የሚሆነውን አርዮስን
ተከራክሮ ምላሽ አሳጣው:: ቅዱስ አትናቴዎስ ከሊቃውንቱ ጋር
ሆኖ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ : እግዚአብሔር
መሆኑን በአደባባይ መሠከረ:: ጸሎተ ሃይማኖትንም ያረቀቀው
እርሱ ነው::
+ከዚሕ በሁዋላ የእስክንድርያ (የግብፅ) 20ኛ ፓትርያርክ ሆኖ
ተሾመ:: ቤተ ክርስቲያንን በመልካም እረኝነት ለ48 ዓመታት
ሲመግብ ብዙ መከራዎችን ተቀበለ:: ለ5 ጊዜ ከመንበሩ
አፈናቅለው ወደ በርሃ ሲያግዙት : በስደት ከ15 ዓመታት በላይ
አሳልፏል::
+በተሰደደባቸው ቦታዎች መከራን እየተቀበለ ያላመኑትን
አሳምኗል:: በጎቹ እንዳይባዝኑበት ደግሞ በጦማር (በደብዳቤ)
ይጠብቃቸው ነበር:: ዛሬ በሃይማኖተ አበው የምናገኘው ቃለ
ሃይማኖት በዚሕ ዘመን የተጻፈ ነው::
+በወቅቱ የነበረው ንጉሥ (ትንሹ ቆስጠንጢኖስ) የአባቱን
(ታላቁ ቆስጠንጢኖስን) ዕረፍት ተከትሎ ነገሠ::
+ወዲያውም አርዮሳዊ (መናፍቅ) ሆነ:: ሃይማኖታቸው የቀና
አባቶችንም ያሳድድ ገባ:: ከአበው ቅዱሳን መካከል ግን የዚህ
መከራ ቀዳሚው ገፈት ቀማሽ ታላቁ ሊቅ ቅዱስ አንትናቴዎስ
ነበር::
+በተለይ አንድ ጊዜ ንጉሡ ቅዱሱን ወደ በርሃ አግዞ : መናፍቅ
ዻዻስ በግብጽ ሹሞ : ብዙ ክርስቲያኖችን በግፍ ሲያስገድል:
ቅዱሱን ለ6 ዓመታት አሰቃየው:: የወገኖቹ (የልጆቹን) ስቃይ
የሰማው ቅዱስ አትናቴዎስ ግን በድፍረት ወደ ቤተ መንግስት
ገብቶ ተናገረው::
+2 አማራጭን አቅርቦ "ወይ ግደለኝና እንደ አባቶቼ ሰማዕት
ልሁን: ካልሆነ ግን ወደ መንጐቼ (ምዕመናን) መልሰኝ"
አለው:: መናፍቁ ንጉሥም ቢገድለው ብጥብጥ እንደሚነሳ
ስለሚያውቅ በስልት ሊያጠፋው ወሰነ::
+ቀዛፊ: መቅዘፊያ: ምግብና ውሃ በሌላት ጀልባ ውስጥ ከቶ
ሜዲትራኒያን ባሕር ውስጥ ጣለው:: ድንገት ግን ከሰማይ
ጌታችን መላእክቱን አስከትሎ ወረደ::
+ሚካኤልና ገብርኤል ባሕሩን እየቀዘፍ : ሌሎች መላእክት
እየመገቡት እስክንድርያ (ግብጽ) አድርሰውት ተሠውረዋል::
ሕዝቡም በታላቅ ሐሴት እየዘመሩ አባታቸውን
ተቀብለውታል::
+ሐዋርያዊው ቅዱስ ስለ ኦርቶዶክስ ተዋግቶ : ብዙ ስቃይንም
ተቀብሎ በ373 ዓ/ም አካባቢ አርፏል:: ቤተ ክስርቲያን "ሊቀ
ሊቃውንት : ርዕሰ ሊቃውንት : የቤተ ክርስቲያን (የምዕመናን)
ሐኪም (Doctor of the Church) : ሐዋርያዊ . . ." ብላ
ታከብረዋለች::
=>አምላከ አበው ምሥጢራቸውን አይሰውርብን::
ከበረከታቸውም ያድለን::
=>ግንቦት 7 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
2.የባሕታውያን አለቃ ታላቁ አባ ሲኖዳ (ጽንሰቱ)
3.ቅዱስ ዮሐንስ ጻድቅ (ሃብቱን : ንብረቱን : ልብሱን ሳይቀር
መጽውቶ ራቁቱን የተገኘ ደግ ሰው ነው)
4.አባ ሐርስዮስ ገዳማዊ
=>+"+ ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብጹዐን ናቸው:: መንግስተ
ሰማያት የእነርሱ ናትና:: ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም
ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብጹዓን ናችሁ::
ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ:: ሐሴትም
አድርጉ:: ከእናንተ በፊት የነበሩ ነቢያትን እንዲሁ
አሳደዋቸዋልና:: +"+ (ማቴ. 5:10)
<ወስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment