ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

Monday, April 4, 2016

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ: መጋቢት 27

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
አሜን
መጋቢት 27
ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባውና ቸሩ አምላካችን
መድኃኔዓለም ክርስቶስ ያደረገው ድንቅ ተአምር ይህ ነው፡-
በዚህች ዕለት ጌታችን በእስክንድርያ ባደረገው ታላቅ ተአምር
ብዙ አይሁድ በስሙ አምነው በአባ ቴዎፍሎስ እጅ
ተጠምቀዋል፡፡ ይኸውም እንዲህ ነው፡- በእስክንድርያ አገር
ስሙ ፈለስኪኖስ የሚባል አይሁዳዊ ባለጸጋ ሰው ነበር፡፡
እርሱም እንደ አባቶቹ የኦሪትን ሕግ ብቻ የሚጠብቅ ሰው
ነው፡፡ እንዲሁም ድሀ የሆኑ ሁለት ክርስቲኖች ነበሩ፡፡
በአንደኛው ላይ ሰይጣን የስድብ መንፈስ አሳድሮበት ጓደኛውን
‹‹ወንድሜ ሆይ ክርስቶስን ለምን እናመልከዋለን? እኛ ድኆች
ነን፡፡ ይህ ክርስቶስን የማያመልክ አይሁዳዊ ፈለስኪኖስ ግን
እጅግ ባለጸጋ ነው›› አለው፡፡ ጓደኛውም ‹‹ዕወቅ አስተውል፣
የዚህ ዓለም ገንዘብ ከእግዚአብሔር የሆነ አይደለም፤ ምንም
አይጠቅምም፡፡ ጥቅም ቢኖረው ጣዖትን ለሚያመልኩ፣
ለአምነዝራዎች፣ ለነፍሰ ገዳዮችና ለአመፀኞች ሁላ
ባልሰጣቸውም ነበር፡፡ አስተውም ነቢያትም ሆኑ ሐዋርያት
ድኆች ነበሩ ነገር ግን ጌታችን ‹ወንድሞቼ› ይላቸው እንደነበር
አስተውል…›› እያለ መከረው፡፡ ነገር ግን ጓደኛውን ሰይጣን
አድሮበታልና ምክሩን ሊሰማው አልቻለም፡፡
ከዚህም በኋላ ይህ ክፉ ሰው ወደ ባለጸጋው አይሁዳዊ ወደ
ፈለስኪኖስ ዘንድ ሄዶ ‹‹አንተን እንዳገለግል ተቀበለኝ›› አለው፡፡
ባለጸጋውም አይሁዳዊ ‹‹በሃይማኖቴ የማታምን አንተ
ልታገለግለኝ አይገባህም›› አለው፡፡ ዳግመኛም ያ ጎስቃቋላ
‹‹ተቀበለኝ እንጂ ወደ ሃይማኖትህ እገባለሁ፣ ያዘዝከኝንም ሁሉ
እፈጽማለሁ›› አለው፡፡ አይሄዳዊውም ‹‹ቆየኝ ከመምሀሬ ጋር
ልማከር›› አለው፡፡ መምህሩም ‹‹ክርስቶስን የሚክድ ከሆነ
ግረዘውና ተቀበለው›› አለው፡፡ አይዳዊውም ተመልሶ መጥቶ
መምህሩ እንደነገረው አድርጎ ተቀበለው፡፡ ከዚህመ በኋላ ወደ
ምኩራባቸው ወሰደው፡፡ የምኩራባቸውም አለቃ ‹‹ክርስቶስን
ክደህ አይሁዳዊ ትሆናለህን?›› አለው፡፡ እርሱም ‹‹አዎን
እክደዋለሁ›› አለው፡፡ የምኩራባቸውም አለቃ መስቀል
ሰርተው በላዩ የክርስቶስን ሥዕል እንዲያደርጉ መጻጻንም
የተመላች ሰፍነግ በዘንግ ላይ አሥረው ከጦር ጋር እንዲሰጡት
አዘዘ፡፡ ከዚያም ‹‹ከተሰቀለው ሥዕል ላይ ምራቅህን ትፋ፣
መጻጻውንም ወደ አፉ አቅርብለት፣ ክርስቶስ ሆይ ወጋሁህ
እያልክ በጦሩ ውጋው›› አሉት፡፡ እርሱም እንዳዘዙት አድርጎ
ሥዕሉን በጦር ወጋው፡፡ ወዲያውም የዕውነት ሆኖ በተደጋጋሚ
ውኃና ደም ከሥዕሉ ፈሰሰ፡፡ ለረጅም ጊዜም በድምድር ላይ
እየፈሰሰ ታየ፡፡ በዚያም ጊዜ ያ ከሃዲ ደርቆ እንደ ድንጋይ ሆነ፡፡
በአይድም ላይ ሁሉ ታላቅ ፍርሃት ወደቀባቸው፡፡ ‹‹እውነትም
የአብርሃም ፈጣሪ ስለእኛ ተሰቅሏል፤ እኛም ዓለምን ለማዳን
የመጣ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ እርሱ እንደሆነ
አመንበት›› እያሉ ጮኹ፡፡
ከዚህም በኋለ አለቃቸው ከዚያ ከደሙ ወስዶ የአንዱን ዐይነ
ሥውር ዐይኖቹን አስነካው፡፡ ወዲያውም ዐይነ ሥውሩ ማየት
ቻለና ሁሉም አመኑ፡፡ ወደ ሊቀ ጳጳሳት አቡነ ቴዎፍሎስ ሄደው
የሆነውን ሁሉ ነገሩት፡፡ አቡነ ቴዎፍሎስም ከካህናቱ ሁሉ ጋር
ወደ አይሁድ ምኩራብ ሄዶ ውኃና ደም ከእርሱ ሲፈስ መስቀሉን
አገኘው፡፡ ከደሙም ወስዶ የራሱንና በዚያ ያሉትንም ሁሉ
ግንባራቸውን በመቀባት በረከትን ተቀበሉ፡፡ መስቀሉንም
በክብር ቀስደው በቤተ ክርስያን ውስጥ አስቀመጡት፡፡ ደሙ
የፈሰሰበትንም ምድር አፈሩን አስጠርጎ ለበረከትና ለሕሙማን
ፈውስ ሊሆን በሸክላ ዕቃ ውስጥ አኖረው፡፡ ከዚህም በኋላ
አይዳዊው ፈለስኪኖስ ከነቤተሰቡ አቡነ ቴዎፍሎስን ተከተለው፡፡
ከአይሁድም ብዙዎቹ የቀደሙ አባቶቻቸው በሰቀሉት የክብር
ባለቤት በሆነ በመድኃኔዓለም ክርስቶስ አመኑ፡፡ አቡነ
ቴዎፍሎስም በስመ ሥላሴ አጥምቆ ሥጋ ወደሙን
አቀበላቸው፡፡ እነርሱም ጌታችንን እያመሰገኑና ክብሩን
እየመሰከሩ ኖሩ፡፡
/////////////// /////////////
ዳግመኛም በዚህች ዕለት ኢትዮጵያዊው ሰማዕት ቅዱስ
ገላውዲዮስ ዐረፈ፡፡ ይኽም ቅዱስ አባቱ ልብነ ድንግል
ሃይማኖቱ የቀና ነበርና ልጁን ገላውዲዮስንም በሃይማኖት አንጾ
አሳደገው፡፡ በዘመኑም አህመድ ግራኝ ተነሥቶ አብያተ
ክርስቲያናትን አቃጠለ፣ ክርስቲያኖችን ፈጀ፡፡ ንጉሡ ልብነ
ድብግልም ሠራዊቱን እስኪያሰባስብ ድረስ ከእርሱ ሸሸ፡፡
በስደትም ላይ እንዳለ ድንገት ታሞ ሞተ፡፡ ግራኝም አብያተ
ክርስቲያናትን እያቃጠለና ክርስቲያኖችን እየፈጀ 15 ዓመት
ኖረ፡፡ ብዙዎችንም በኃይል አሰለማቸው፡፡ ‹‹የሚቃወመኝና
የሚችለኝ የለም›› እያለ ሲታበይ ቅዱስ ገላውዲዮስ ተነሣና
በየቦታው ያሉ የግራኝን መኳንንቶች አሸነፋቸው፡፡ ግራኝም
ይህን ሲሰማ ተቆጣና ከቱርክ አርበኞች ጋር ሆኖ ገላውዲዮስን
ገጠመው፡፡ ገላውዲዮስም ግራኝን ገደለው፡፡ አብያተ
ክርስቲያናትም መልሰው ታነጹ፣ የቀናች ሃይማኖትም
ተመለሰች፡፡
ቅዱስ ገላውዲዮስም በመጋቢት 27 ቀን የጌታችንን የስቅለቱን
በዓል እያከበረ እያለ የሙስሊሞች ወገን የሆኑ ብዙ ጭፍሮች
ድንገት ደርሰው ከበቡት፡፡ ከእርሱ ጋር የነበሩት ጥቂት ሰዎችም
ገላውዲዮስን ‹‹የጦር መኰንኖቻችን እስከሰበሰቡ ድረስ ፈቀቅ
እንበል›› ቢሉት ሰማዕትነቱን ተመኝቶት ነበርና እምቢ
አላቸው፡፡ እስላሞቹም በአንድነት ከበው በጦር ወግተው
ገደሉት፣ አንገቱንም ቆረጡትና የሰማዕትነትን አክሊል
ተቀዳጀ፡፡ ዳግመኛም በዚህች ዕለት ታላቁ አባት አባ መቃርስ
ዕረፍታቸው ነው፡፡ በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው
ይማረን፡፡
የከበሩ ቅዱሳን አባቶቻችን በሠሩልን ሥርዓት መሠረት
የመጋቢት 27 የመድኃኔዓለም ክርስቶስ የስቅለቱን በዓል ወደ
ጥቅምት 27 ቀን መጥቶ እንዲከበር አባቶቻችን ወስነዋል፡፡
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ያበሠራትና
የጌታችንም ፅንሰት የተከናወነው በመጋቢት ወር በ29ኛው ቀን
በዕለተ እሁድ በ3 ሰዓት ነው፣ ነገር ግን ብሥራቱና ፅንሰቱ ግን
ታኅሣሥ 22 ቀን እንዲከበር ቅዱሳን አባቶች እነ ቅዱስ
ደቅስዮስ ወሰኑ፡፡ እነርሱም በዓሉን በዚሁ ዕለት
አክብረውታል፡፡ አንድም ነገረ ልደቱን ከማክበር አስቀድሞ
ነገረ ፅንሰቱን ማዘከር ማክበር ተገቢ ስለሆነ ነው፡፡ በዓቢይ
ጾም ወቅት ደግሞ ፍጹም ሐዘን ልቅሶ ጾም ጸሎት ይያዛል
እንጂ ደስታ ፌሽታ እልልታ ጭብጨባ የለም፡፡ ዓቢይ ጾም
ፍጹም የሐዘን ወራት ነው፡፡ ታቦት አውጥቶ በዓል ማክበር
ስህተት ነው፤ የአባቶችንም ሥርዓት ማፍረስ ነው፡፡ ምስጋና
ይድርሳቸውና ቅዱሳን አባቶቻችን ሁሉንም ነገር በሥርዓት
በሥርዓቱ አድርገው ሰፍረው ቆጥረው አስቀምጠውልናል፡፡
ከዓቢይ ጾም በኋላ ያሉትን 50 ቀናት ረቡዕና ዓርብንም
ጭምር ሥጋ እንኳን እንድንበላ ነው ሥርዓት የሠሩልን፡፡
አባቶቻችን የሠሯት ሕግ ፍጽምት ናት፡፡ በዚህም መሠረት
አባቶቻችን ሥርዓትን ሠሩልንና የመጋቢት 27 የጌታችንን
የስቅለቱን በዓል ወደ ጥቅምት 27 ቀን አምጥተው እንዲሁም
የመጋቢት 5 የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን የዕረፍት በዓል ወደ
ጥቅምት 5 ቀን አዙረው እንዲከበር አድርገዋል፡፡
በዚህ ታላቅ የዐቢይ ጾም ወቅት ለጾም፣ ጸሎት፣ ስግደታችን
ብዙ ጊዜ የምንሰጥበት ተጋድሎአችንን በእጅጉ በመጨመር
ከአምላካችን ሞት ጋር የምትተባበርበት ወቅት ነው፡፡
አባቶቻችን እንዳሉት ጌታችንን ‹‹ከእኛ ጋራ መከራን
ስለተቀበልክ እኛም ከአንተ ጋራ መከራን እንቀበላለን፡፡
በመስቀል ላይ የተቀበልከው የመከራህ ተሳታፊዎች
አድርገኸናልና በመከራ ስለመሰልንህ እንደዚሁ በጌትነትህ
በምትመጣበት ጊዜ በዕለተ ምጽዓት ከአገልጋዮችህ ከወዳጆችህ
ቅዱሳን ጋራ ክብርን አድለን›› እያልን ጾም ጸሎት ስግደት
ምጽዋት ተጋድሎአችን በመጨመር በእጅጉ የምንተጋበት
ወቅት ነው፡፡ ሞቱን በሚመስል ሞት ከመድኃኔዓለም ክርስቶስ
ጋር ተባብረን በኋላም ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ከእርሱ
ጋር ለመተባበር ዝግጁ የምንሆነበት ታላቅ ወቅት ነው፡፡ ሮሜ
6፡5፡፡ ስለዚህ እኔም ገድለ ቅዱሳኑንና ስንክሳሩን ሳላቋርጥ
በየቀኑ መጻፌን የምቀጥለው ዐቢይ ጾሙ እንዳለቀ ነው፡፡
አምላከ ቅዱሳን መድኃኔዓለም ክርስቶስ መዋዕለ ጾሙን
በሰላም ያስፈጽመን!!!
እጅግ የከበሩ ቅዱሳን አባቶቻችን እነ አቡነ ዘርዐ ቡሩክ፣ እነ
አቡነ መብዓ ጽዮን ራሱ ጌታችን እንደነገራቸውና እነርሱም
ሲያደርጉት የነበረውን ነገር እንደነገሩን ‹‹የመድኃኔዓለምን
የሞቱን መታሰቢያ ያደረገ የተኮነኑ ነፍሳትን ከደይን ያወጣል፣
በሞቱም ጊዜ ሥቃይን አያያትም፡፡›› ስለዚህም የጥምቀት
ወገኖች የሆንን የተዋሕዶ ልጆች ሁላችን የመድኃኒታችንን
ሞቱን በአንክሮ እናዘክር ዘንድ የልቡናችን ዐይን ወደ ቀራንዮ
አደባባይ ይመልከት፡፡
እነሆ ክፉዎች አይሁድ ሰይጣን ልባቸውን አስቶታልና እንደ
ወረንጦና እንደ ወስፌ እንደመርፌም ያለ 300 እሾህ ያለው
ስረወጽ አድርገው አክሊል ሠርተው ከፍላት አግብተው በጉጠት
አንስተው ‹ኢየሱስ ናዝራዊ ንጉሥ ነህ ዘውድ ይገባሃል› ብለው
በራሱ ላይ ደፉበት፡፡ ለአክሊለ ሦኩም 73 ስቁረት ነበረው፡፡
እራሳቸው እንደ መሮ፣ ወርዳቸው እንደ ሞረድ 4 ማዕዘን
አሠርተው ቁመታቸውን ክንድ ከስንዝር፣ ስለታቸውን እንደ
ወስፌ አድርገው 73 ችንካር ሠርተው በ73ቱ ስቁረት
አግብተው በጌታችን በራሱ ላይ ቢመቱበት ሥጋ ለሥጋ ገብቶ
መሐል ልቡን ወጋው፡፡ አክሊለ ሦኩን በራሱ ላይ አድርገው
ሲያበቁ ከቤት ወደ አደባባይ እያመላለሱ ‹‹ንጉሥ ሆይ!...››
እያሉ ምራቃቸውን እየተፉበት ተዘባበቱበት፡፡ መስቀል
አሸክመው ከሊቶስጥራ እስከ ቀራኒዮ ድረስ እያዳፉ ሲወስዱት
136 ጊዜ በምድር ላይ ጣሉት፡፡ ከኋላ ያሉት ‹‹ፍጠን›› እያሉ
ገፍትረው ይጥሉታል፣ ከፊት ያሉት ደግሞ ‹‹ምን
ያስቸኩልሃል?›› እያሉ መልሰው ገፍትረው ይጥሉታል፡፡ ከዚህ
በኋላ ክፉዎች አይሁድ ቁመታቸውን ክንድ ከስንዝር ስለታቸው
ደግሞ እንደ ወስፌ የሆኑ 5 ችንካሮችን ሠርተው ሳዶር
በሚባለው ችንካር ቀኝ እጁን፣ በአላዶር ግራ እጁን፣ በዳናት
ሁለት እግሮቹን፣ በአዴራ መሐል ልቡንና በሮዳስ ደረቱን
ቸንክረው የአዳም ራስ ቅል ባለበት ቀራኒዮ አደባባይ ላይ
ሰቅለውታል፡፡
ክፉዎች አይሁድ መድኃኔዓለም ክርስቶስን እንደያዙት የኋሊት
አስረው አፍንጫውን 25 ጊዜ ቢመቱት ደሙ በመሬት ላይ
እንደ ውኃ ፈሰሰ፡፡ ከጌቴሴማኒ እስከ ሐና ቤት ድረስ አስረው
የፊተኞቹ ሲጎትቱት የኋለኞቹ እየለቀቁት የኋለኞቹም በተራቸው
ሲጎትቱት የፊተኞቹ ይለቁታል፡፤ እንዲህ እያደረጉ 65 ጊዜ
ከመሬት ጋር አጋጭተውታል፡፡ ሳውል በእግሩ ሲረግጠው
ጌታችን ‹‹መመለስህ ላይቀር ለምን ትረግጠኛለህ?›› ቢለው
ስለዚህ ንግግርህ ብሎ ሳውል 440 ጊዜ አስገረፈው፡፡
ክፉዎች አይሁድ መድኃኒታችንን በሁለት ግንዶች መካከል
አድርገው 65 ጊዜ ከግንዱ ጋር አጋጩት፡፡ ቀያፋ
በሚመረምረው ጊዜ ጌታችን ‹‹አምላነቴን አንተው ራስህ
ተናገርኽ›› ቢለው አይሁድ በእጃቸው ሲመቱት እጃቸውን
ቢያማቸው ድንጋይ ጨብጠው 120 ጊዜ ፊቱን ጸፉት፡፡ አይሁድ
ወደ ጲላጦስ ዘንድ ሲወስዱት ‹‹ምናልባት ጲላጦስ ባይፈርድበት
እንኳ እንዳይቆጨን›› ብለው 305 ጊዜ በሽመል
ደብድበውታል፡፡ በአምላክነቱ ቻለው እንጂ የአንዱ ምት ብቻ
በገደለው ነበር፡፡ በርባን የይሁዳ የሚስቱ ወንድም (አማቹ)
ስለነበር እርሱ እንደፊታለትም ከዋጋው ከ30ው ብር ጋር አብሮ
ተደራድሮበት ነበር፡፡
ሰይጣን ልባቸውን ለክፋት ያስጨከናቸው ክፉዎች አይሁድ
በጲላጦስ አደባባይ የጌታችንን ፂሙን 80 ጊዜ ነጭተውታል፡፡
ጲላጦስ እንደ ሕጋቸው 41 ብቻ ገርፈው እንዲለቁት ቢያዝም
ክፉዎች አይሁድ ግን ጌታችንን ሲገርፉት ‹‹አሠቃቂ ግርፋቱን
አይተን ልባችን እንዳይራራ›› ብለው ሰንጠረዥ ገበጣ ሰርተው
ሲጫወቱ አንዱ ተነስቶ እስከ 60 እና 70 ድረስ ይገርፍና
ሲደክመው ‹‹ቆጠራችሁን?›› ብሎ ይጠይቃል፡፡
‹‹አልቆጠርንም›› ሲሉት ከድካሙ የተነሣ ‹‹እኔው ልግረፍ
እንደገና እኔው ልቁጠር›› ብሎ ትቶት ሲቀመጥ ሌላኛው
ይነሣና እንደዛኛው ሁሉ በተራው 60 እና 70 ይገርፈዋል፡፡
ሁሉም እንዲህ እያሳሳቱ የራሳቸውን ሕግ እየተላለፉ አይሁድ
ጌታችንን ሥጋው አልቆ አጥንቱ እንደበረዶ ነጭ ሆኖ እስኪታይ
ድረስ 6666 ጊዜ ጽኑ ግርፋትን ገረፉት፡፡ በእነዚህ ሁሉ ግርፋቱ
ወቅት 366 ጊዜ ሥጋው ተቆርሶ መሬት ላይ ወድቋል፡፡
የመድኃኔዓለም ወገኖች ሆይ! የጌታችን ሞቱ በፈቃዱ መሆኑንና
የትዕግሥቱን ብዛት አይተን እናደንቅ ዘንድ ከመጻሕፍት ጠቅሰን
እንነግራችኋለን፡፡ አይሁድ ጌታችን አብርሃም ሳይወለድ በፊት
እርሱ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ
ጋር በአንድነት በሦስትነት የሚመሰገን አምላክ መሆኑን
ቢነግራቸው ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ፡፡ እሱ ግን ጊዜው ገና
ነበርና ተሰውሮአቸው በመካከላቸው አልፎ ሲሄድ በፍጹም
አላዩትም ነበር፡፡ በቅዱስ ወንጌል ላይ እንዲህ ተብሎ
እንደተጻፈ፡- ‹‹አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤት
አደረገ፥ አየም ደስም አለው። አይሁድም:- ገና አምሳ ዓመት
ያልሆነህ አብርሃምን አይተሃልን? አሉት። ኢየሱስም:- እውነት
እውነት እላችኋለሁ፥ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ አላቸው።
ስለዚህ ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ፤ ኢየሱስ ግን ተሰወራቸው
ከመቅደስም ወጥቶ በመካከላቸው አልፎ ሄደ፡፡›› ዮሐ 8፡
56-59፡፡
ዳግመኛም በዮሐንስ ወንጌል ላይ እንደተጻፈው አይሁድ
መድኃኔዓለምን ሊይዙት የጦር መሣሪያቸውን ሰብስበው ወደ
ጌቴሴማኒ በመጡ ጊዜ ‹‹ማንን ትፈለጋላችሁ?›› ቢላቸው
‹‹የናዝሬቱን ኢየሱስን እንፈልጋለን›› ሲሉት ‹‹እኔ ነኝ››
ቢላቸው ከአንደበቱ የወጣውን መለኮታዊ ቃል ብቻ መቋቋም
አቅቷቸው መሬት ላይ ወድቀው ተዘርረዋል፡፡ ይህም ክስተት
በተደጋጋሚ ተከስቷል፡፡ (ዮሐንስ ወንጌል ላይ ምዕራፍ 18
ከቁጥር አንድ ጀምሮ ይመለከቷል፡፡) እናም የጌታችን ሞቱ
በፍጹም ፈቃዱ ባይሆን ኖሮ በጌቴሴማኒ ሊይዙት የመጡት
ክፉዎች አይሁድን እንደመጀመሪያው ሁሉ በተሠወራቸው ነበር
አሊያም ከአንደበቱ በሚወጣው አምላካዊ ቃሉ ብቻ ባጠፋቸው
ነበር፡፡ በመጨረሻ ግን ጌታችን ወደዚህች ምድር የመጣበትን
ዓላማ ይፈጽም ዘንድ እንዲገድሉት በፈቃዱ ራሱን አሳልፎ
ቢሰጣቸው ያን ሁሉ እጅግ አሠቃቂ መከራ አደረሱበትና
ለመስቀል ሞት አበቁት፡፡
ወዮ ለዚህ ለመድኃኒዓለም ፍጹም ትዕግስት አንክሮ ይገባል!
ዓለምን በመዳፉ የያዘ አምላክ በአይሁድ እጅ እንደሌባ ተያዘ፡፡
ሠራዊተ መላእክት ለምሥጋና በፊቱ የሚቆሙለት
መድኃኔዓለም እርሱ ሊፈረድበት በፍርድ አደባባይ ቆመ፡፡
በእስራት ያሉትን የሚፈታ እርሱ በብረት ችንካር ተቸነከረ፡፡
ሰማይን በከዋክብት ምድርም በአበባ ያስጌጠ እርሱ ግን የእሾህ
አክሊል በራሱ ላይ ደፋ፡፡
ዓለሙን ሁሉ በቸርነቱ የሚመግብ እርሱ ተጠማሁ አለ፡፡
ወዮ የመድኃኔዓለም የማዳኑ ምሥጢር ምንኛ ድንቅ ነው!!!
ለዚህ ባሕርይው አንክሮ ይገባል፡፡
በመድኃኔዓለም ክርስቶስ ሞት በአንድነት እናለቅስ ዘንድ
ቅዱሳን ሁላችሁ ኑ! መድኃኒታችን ሙቷልና ፍጥረታት ሁሉ
ያለቅሳሉ፤ መያዝንና መታሠርን የተቀበለ መድኃኒታችን
ሙቷልና፡፡ ጥፊንና ግርፋትን የተቀበለ መድኃኒታችን ሞተ፡፡
መደብደብንና መመታትን የታገሰ መድኃኒታችን ሞተ፡፡ ሄኖክ
እግዚአብሔር ‹‹በሴም ቤት ይደር›› ብሎ አብ ስለራሱ
የተናገረለት የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ አብርሃም
ቃልኪዳን የገባልህን የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡
ይስሐቅ ከሰይፍ ቤዛ የሆነህን የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ
ዘንድ ና፡፡ ያዕቆብ በበረሃ የታገለህ የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ
ዘንድ ና፡፡ ኢዮብ በደመና የታየህ የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ
ዘንድ ና፡፡ ሙሴ ስለ እርሱ ‹እንደእኔ ያለ ነቢይ ይነሣል› ብለህ
የተናገርኽለት የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ዳዊት
‹‹እነሆ በኤፍራታ ሰማነው፣ በበረሃ ዛፍም አገኘነው›› ብለህ
የተናገርኽለት የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ኤርሚያስ
‹‹የክቡሩን ዋጋ ሠላሳ ብር ተቀበሉ›› ብለህ የተናገርኽለት
የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡
ኢሳይያስ ‹‹ወልድ ሰው ለመሆን ተገለጠልን፣ ሕፃን ተወለደልን፣
ድንቅ መካር ኃያል አምላክ›› ብለህ የተናገርኽለት
የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ሕዝቅኤል ‹‹አምላክ
ወደ ተዘጋች ደጃፍ ገባ፣ ከተዘጋች በርም ወጣ›› ብለህ
የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ዳንኤል ነጭ ሐር ለብሶ
ያየኸውን የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ኤልያስ ከሞት
በፊት የሰወረህ በእሳት ፈረሶች ያሳረገህ የመድኃኒታችንን ሞቱን
ታይ ዘንድ ና፡፡ ሕዝቅያስ የፀሐይ መግባቱን ያሳየህ
የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ምናሴ ችንካሮችህን
ከእግር ብረት የፈታ የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡
ኢዮስያስ ፋሲካውን ያደረግህ የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ
ና፡፡ አናንያ፣ አዛርያና ሚሳኤል ከእሳት ምድጃ ያዳናች
የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ኑ፡፡ አብያና ሲላ ፌንቶስ
ከመወለዱ አስቀድሞ ያመናችሁበት የመድኃኒታችንን ሞቱን
ታይ ዘንድ ኑ፡፡ የቀድሞ አባቶች ነቢያት ሁላችሁ ከፋራን ተራራና
ከቴማን ይመጣል ያላችሁት የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ
ኑ፡፡ አሞፅ በአድማስ ቅጥር ያየኸው የመድኃኒታችንን ሞቱን
ታይ ዘንድ ና፡፡ ዘካርያስ በተራራዎች መካከል ያየኸው
የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ዕዝራ በአርፋድ በረሃ
ያየኸው የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡
ስምዖን በክንድህ የታቀፍከውን ሕፃን የመድኃኒታችንን ሞቱን
ታይ ዘንድ ና፡፡ ዮሴፍ እንደ አንተ የተሸጠ የመድኃኒታችንን
ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡ ጠራቢ ዮሴፍ በትከሻህ ያዘልከው በክንድህ
የተሸከምከው ሕፃን የመድኃኒታችንን ሞቱን ታይ ዘንድ ና፡፡
መጥምቁ ዮሐንስ ከሕፃንነትህ ጀምሮ በበረሃ ያለ እናት ያለ
አባት ያሳደገህ መንገዱንም እንድትጠርግለት ያዘጋጀህና
መለኮትን እንድታጠምቅ የመረጠህ የመድኃኒታችንን ሞቱን
ታይ ዘንድ ና፡፡
ኢያቄምና ሐና ሆይ የልጃችሁን ልቅሶዋን የልቧንም መዘንጋት
ታዩ ዘንድ ኑ፡፡ ከሔዋን እስከ ፋኑኤል ልጅ እስከ ሐና ያላችሁ
ሁላችሁ ቅዱሳት ሴቶች የድንግልን ልቅሶዋን ታዩ ዘንድ ኑ፣
አንድ ልጇ ሙቷልና፡፡ የለመለመ የሥጋ ሞት ሕንፃ
የተጀመረበት የአቤል ተከታዩ፣ ከጎኑ የፈሰሰው ደም ሔዋንን
ከጥፋት ያዳናት የተገደለ መድኃኒታችን ነው፡፡ የናቡቴ ጓደኛው
የተገፋው መድኃኒታችን ነው፡፡ አቤል ስለሚስቱ ሞተ፡፡ ናቡቴም
ስለ ወይኑ ቦታ ሞተ፡፡ መድኃኒታችን ግን በቀኙ ያነጻት ዘንድ
ስለቤተክርስቲያን ሞተ፡፡ ነፍሳችሁን ይወስዷታልና
መውረዱንም አላወቁምና ስለ ወገኖቹ ኃጢአት እስከ ሞት
ደረሰ ብሎ ስለ እርሱ የተናገረ አባቱን እንስማው፡፡ ሙሴም
እርሱን ያውቁት ዘንድ አላሰቡትም፣ በሚመጣበት ቀንም
አላወቁትም አለ፡፡ ዕዝራ በባሕር ጥልቅ ያለውን ማወቅ
እንዳይችሉ ወልድንም ማወቅ እንዲሁ ሆነባቸው አለ፡፡
ጳውሎስም ብታውቁትስ ኖሮ የክብርን ጌታ እግዚአብሔርን
ባልሰቀላችሁት ነበር አለ፡፡
በመሰደድ፣ ያለምንም በደልም በፍርድ አደባባይ በመቆም
መከራ መስቀልን በመሸከም አብነት የሆናችሁ ሰማዕታት
ሁላችሁ ኑ የመድኃኔዓለምን የሞቱን ዕለት አስባችሁ በጋራ
አልቅሱለት፡፡ ሁሉ የእርሱ ከእርሱ ለእርሱ ተፈጥሮ ሳለ በምድር
ላይ ምንም ሳይኖረው ራሱን እንኳን የሚያስጠጋበት ቤት
ሳይኖረው አብነት የሆናችሁ ባሕታውያንና መነኮሳት ሁላችሁ ኑ
በዛሬዋ ዕለት ስለሞተው አምላካችሁ መሪር ዕንባን
አልቅሱለት፡፡ ሕግ ጠብቆ፣ ሥርዓት አክብሮ፣ ነዳያንን
በመመገብና ያዘኑትን በማጽናናት 33 ዓመት በምድር ላይ ኖሮ
አብነት የሆናችሁ እናንት በዓለም ሆናችሁ ሕግ ጠብቃችሁ፣
አሥራት በኩራቱን አውጥታችሁ፣ ድሆችን በመርዳት የምትኖሩ
ክርስቲያኖች ሁላችሁ የመድኃኔዓለምን የሞቱን ዕለት ታስቡ ኑ፡፡
‹‹የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን
እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን
ተቀብሎአልና›› ብሎ ቅዱስ ጴጥሮስ እንደጻፈልን (1ኛ ጴጥ
2፡21) እርሱ ንጹሕ ባሕርይ ሲሆን ወደ መጥምቁ ቅዱስ
ዮሐንስ ዘንድ ወደ ዮርዳኖስ በመሄድ ለተጠመቅን ለእኛ
ለተነሣሕያን ለሁላችን አብነት የሆነን መድኃኒታችን ስለእኛ
ሞቷልና ሞቱን እናስብ ዘንድ ኑ በቤቱ ተሰብስበን
እናልቅስለት፡፡ መታሰያውንም እናድርግለት፡፡ ጌታችን ሞቶ
ተቀብሮ ካረገ በኋላ ለቅዱሳን ሐዋርያትና ለቅዱሳን አባቶቻችን
ለእነ አቡነ መባዓ ጽዮን፣ ለእነ አቡነ ዘርዐ ቡሩክ እንደነገራቸው
የሞቱን መታሰቢያ የሚያደርግ ኃጠአተኛ እንኳ ቢሆን ሲኦልን
አያያትም፡፡ የመድኃኔዓለምን የሞቱን መታሰቢያ የሚያድርግ
ቢኖር ሲኦል ራሷ አፍ አውጥታ ‹‹ይህችን ነፍስ ወደኔ
አታምጡብኝ›› ብላ ትጮሃለች እንጂ ችላ አትቀበለውም፡፡
የጌታችን ወዳጆቹ ዮሴፍ ኒቆዲሞስ በድርብ በፍታና በመቶ
ወቄት ሽቱ ገንዘው በሐዲስ መቃብር ሊቀብሩት ቢሉ ጌታችን
ያን ጊዜ ዐይኑን ክፍቶ ‹‹በሰውነቴ መዋቲ ብሆን በመለኮቴ
ሕያው ነኝ እንጂ ምነው እንደ እሩቅ ብእሲ ዝም ብላችሁ
ትገንዙኛላችሁን?›› አላቸው፡፡ ይህን ጊዜም ዮሴፍ ኒቆዲሞስ
በታላቅ ድንዳጤ ሆነው ‹‹አቤቱ ጌታችን ሆይ! እንግዲያስ ምን
እያልን እንገንዝህ?›› አሉት፡፡ መድኃኒታችንም እንዲህ እያላችሁ
ገንዙኝ አላቸው፡- ‹‹ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ
ሕያው ዘኢይመውት ዘተወልደ እማርያም እምቅድስት ድንግል
ተሣሃለነ እግዚኦ፡፡ ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ
ሕያው ዘኢይመውት ዘተጠምቀ በዮርዳኖስ ወተሰቅለ ዲበ ዕፀ
መስቀል ተሣሃለነ እግዚኦ፡፡ ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል
ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ዘተንሥአ እሙታን አመ ሣልስት
ዕለት ዐርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት ወነበረ በየማነ አቡሁ
ዳግመ ይመጽእ በስብሐት ይኰንን ሕያዋነ ወሙታነ ተሣሃለነ
እግዚኦ› እያላችሁ ገንዛችሁ ቅበሩኝ አላቸው፡፡›› ከዚህም በኋላ
መድኃኒታችን ለወዳጆቹ ለ12ቱ ሐዋርያት፣ ለ72ቱ አርድእት፣
ለ36ቱ ቅዱሳት አንስት ‹‹እስከ ሦስት ቀን እነሣላችኋለሁ እዘኑ
አልቅሱ፣ እህል ውኃ አትቅመሱ በሏቸው›› ብሎ ለዮሴፍና
ለኒቆዲሞስ አክፍሎት አስተማራቸው፡፡
ዳግመኛም መድኃኔዓለም ክርስቶስ ከዕርገቱ በኋላ ለቅዱሳን
ሐዋርያት የሞቱን መታሰቢያ እንዲያደርጉ ነግሯቸዋልና፡፡
ሕማሙንና ሞቱንም እንዲዘክሩ አዟቸዋልና አሁንም ያንን
ሁሉ የመድኃኔዓለምን ሞቱን ያላሰበና የሞቱን መታሰቢያ በዓል
ያላከበረና እርሱንም የማይወደው ቢኖር ዕድል ፈንታው ጽዋ
ተርታው ከአይሁድ ጋር ነው፡፡
የመድኃኔዓለምን የሞቱን መታሰቢያ አድርገን ሞቱን
በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ተባብረን ትንሣኤውን በሚመስል
ትንሣኤ ከእርሱ ለመተባበር ያብቃን፡፡
ሰኞ የሚፀለይ አምላክን የወለደች የድንግል ማርያም ምስጋና
ጌታ በልቡ ያዘነና የተከዘ አዳምን ነፃ ያወጣውና ወደ ቀድሞው
ቦታው ይመልሰው ዘንድ ወደደ ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
ከድንግል ያለወንድ ዘር በሥጋ ተወለደና አዳነን። ከይሲ
(ዲያብሎስ) ያሳታት ሔዋንን እግዚአብሔር ምጥሽንና ጻርሽን
አበዛዋለው ቢሎ ፈረደባት ሰውን ወደደና ነፃ አደረጋት። ቅድስት
ሆይ ለምኝልን።
ሰው የሆነና በኛ ያደረ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ክብሩንም
ለአባቱ አንደ እንደመሆኑ ክብር አየን። ይቅር ይለን ዘንድ
ወደደ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
ነቢዩ ኢሳያስ በመንፈስ ቅዱስ የአማሩኤልን ምሥጢር አየ
ስለዚህም ሕፃን ተወለደልን ወልድም ተሰጠን ብሎ አሰምቶ
ተናገረ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
ሰው ሆይ ፈጽመህ ደስ ይበልህ እግዚአብሔር ዓለሙን
ወዶታልና አንድ ልጁንም የሚያምንበት ሁሉ እስከ ዘለዓለም
ፈጽሞ ይድን ዘንድ አሳልፎ ሰጥቷልና ልዑል ክንዱን ሰደደልን።
ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
የተበረው የሚኖረው የመጣው ዳግመኛ የሚመጣውም ቃል
ኢየሱስ ክርስቶስ ያለመለወጥ ፍጹም ሰው ሆነ አንዱ ወልድ
በሥራው ሁሉ አልተለየም የእግዚአብሔር ቃል መልኮት አንድ
ነው እንጂ ። ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
የነቢያት ሀገራቸው ቤተልሔም ሆይ ደስ ይበልሽ ሁለተኛው
አዳም ክርስቶስ በአንቺ ዘንድ ተወልዷልና ከምድር (ከሲኦል)
ወደ ገነት ይመልሰው ዘንድ አዳም ሆይ መሬት ነበርክና ወደ
መሬት ትመለሳለህ ብሎ የፈረደበትንም የሞት ፍርድ ያጠፋለት
ዘንድ፤ ቡዙ ኃጢያት ባለችበት የእዚአብሔር ጸጋ ትበዛለች።
ቅድስት ሆይ ለምኝልን።
የሰው ሁሉ ሰውነት ደስ ይላታል በሰማይ ለእግዚአብሔር
ምስጋና ይሁን በምድርም ሰላም ለሰውም እርሱ በሚፈቅደው
እያሉ አሰምተው ንጉሥ ክስርቶስን ከመላእክት ጋር
ያመስግኑታል። የቀድሞውን እርግማን አጥፍቷልና የጠላትን
ምክሩን አፈረሰበት ለአዳምና ለሔዋን የዕዳ ደብዳቤያቸውን
ቀደደላቸው በዳዊት ሀገር የተወለደ መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ አዳምና ሔዋንን ነፃ አደረጋቸው ።ቅድስት ሆይ
ለምኝልን።
በዚህ ዓለም ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ የምታበራ እውነትኛ ብርሃን
ስለሰው ፍቅር ወደ ዓለም የመጣው ፍጥረት ሁሉ በመጣትህ
ደስ አለው አዳምን ከስህተት አድረኸዋልና ሔዋንንም ከሞት
ጻዕረኝነት ነፃ አድርገኻታልና የምንወለድበትን መንፈስ (ረቂቁን
ልደት) ሰጠኸን ከመላእክት ጋርም አመስገንህ ቅድስት ሆይ
ለምኝልን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ