ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

Tuesday, May 31, 2016

=>+*"+<+>ግንቦት 24<+>+"*+

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
አሜን
ግንቦት 24-ጌታችን ከቅድስት ድንግል እናቱ፣ ከአረጋዊ ዮሴፍና
ከሰሎሜ ጋር ወደ ግብፅ የተሰደደበት ዕለት ነው፡፡
+ በዚህችም ዕለት ጌታችን በአረጋዊ ዮሴፍ በትር ብዙ አስደናቂ
ተአምራትን አድርጓል፡፡ ዳግመኛም እመቤታችንና የተወደደ
ልጇን መድኃኔዓለምን በእጆቹ ሥራ ይመግባቸው የነበረና
እነርሱንም ከሄሮድስ ለማዳን ብዙ ሰማዕትንት የተቀበለ
ጻድቁና የ83 ዓመቱ አረጋዊ ዮሴፍ ግብፅ የገባበትና ቅዳሴ ቤቱ
የከበረበት ዕለት ነው፡፡
+ ከ12ቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ የሆነው ነቢዩ ቅዱስ ዕንባቆም
ዕረፍቱ ነው፡፡ ቅዳሴ ቤቱም በዚኹ ዕለት ነው፡፡
+ የአሮን ልጅ አልዓዛር ዕረፍቱ ነው፡፡
+ ከእንጽና አገር የተገኘው የከበረ አባት ቀሲስ አብቁልታ
በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡
የእመቤታችንና የልጇ የመድኃኔዓለም ስደት-ከገድለ አረጋዊ
ዮሴፍ ላይ የተገኘ፡- የእመቤታችን ስደት የመጀመሪያው የአዲስ
ኪዳን ስደት ነው፡፡ ከገነት የተሰደደውን አዳምን ወደ ቀደመ
ክብሩና መንበሩ ከዚያም ወደ ሚበልጥ ክብር ለመመለስ
የተወለደው ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ገና
ከሕፃንንቱ ጀምሮ ስደትንና መከራን ተቀብሏል፡፡ ወላዲተ
አምላክ ቅድስት እናቱ እሳትን አዝላ በብርድ ተንገላታለች፣ ለእኛ
የሕይወት እንጀራን ተሸክማ እርሷ ተርባለች፣ የሕይወትን ውሃ
ተሸክማ እርሷ ተጠምታለች፣ የሕይወት ልብስን ተሸክማ ሳለ
እርሷ ተራቁታለች፣ የሕይወት ሀሴት ደስታ ተሸክማ እርሷ
አዝናለች፡፡ እመ አምላክ ስለ ልጇ ብላ ተርባ፣ ተጠምታ፣
ታርዛለች፤ ደክማና አዝና አልቅሳለች፡፡ እግሯ ደምቷል፣ እሾህ
ወግቷት አንቁረው አውጥተውላታል፡፡ እርሷም ይህንን ሁሉ
መከራ የተቀበለችው ልጃን ለማዳንና ለእኛ ለዘላለማዊው
ድኅነት ነውና አባቶች እንዲህ ብለው አመስግነዋታል፡- «ድንግል
ሆይ ርጉም በሆነ ሄሮድስ ዘመን ከልጅሽ ጋር ከሀገር ሀገር
ስትሸሺ ከአንቺ ጋር መሰደዱን አሳስቢ ፤ ድንግል ሆይ ከዓይንሸ
የፈሰሰውንና በተወደደ ልጅሽ ፊት የወረደውንመሪር እንባ
አሳስቢ፤ ድንግል ሆይ ረሀቡንና ጥሙን፣ ችግሩንና ኀዘኑን፣
ከእርሱ ጋር የደረሰብሽንም ጭንቅ ሁሉ አሳስቢ›› ቅዳሴ
ማርያም፡፡
የእመቤታችንን የስደቷን ጥንተ ነገር ስናየው እመቤታችን
በቤተ መቅደስ ሳለች ከአባቷ የሚመጣላትን የትረፈረፈ ሀብት
ለድኆችና ጦም አዳሪዎች ትመጸውት ነበር፡፡ 7 ዓመት በሆናት
ጊዜ ግን ወላጆቿ ዐረፉና እነርሱ የተውላትን ወርቅና ብዙ
ገንዘብ እግዚአብሔርና ለጦም አዳሪዎች ሰጠች እንጂ ምንም
አልወሰደችም፡፡ ካህናቱ እንደ በባሕላቸው መሠረት በቤተ
መቅደስ በብፅዓት ያደገን ሰው (ሴትም ይሁን ወንድ) ለአካለ
መጠን ሲደርስ በቤተ መቅደስ እያገለገለ እንዲኖር ወይም
ከካህናቱ ወገን መርጦ እንዲያገባና ሀብት ሰጥተው እንዲሸኙት
ሁለት ምርጫ ይሰጡታል፡፡ እመቤታችንም 12 ዓመት በሆናት
ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስይህንኑ ምርጫ ሲያቀርብላት
እመቤታችንም በልቧ የሰው ልጅ ሀሳብ የላትምና ‹‹እኔስ
በእግዚአብሔር ቤት እያገለገልኩ መኖርን እመርጣለሁ››
አለችው፡፡ ካህናቱም ‹‹ስለእርሷ ወደ ቤተ መቅደስ ገብተህ
እግዚአብሔር የሚነግርህን በጸሎት ጠይቅ›› አሉትና እርሱም
የክህነት ልብሱን ለብሶ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ገብቶ በጸሎት
ሲጠይቅ እግዚአብሔር መልአኩን ልኮለት ሚስቶች
የሌሏቸውን የዳዊት ወገን የሆኑ ወንዶችን ሰብስቦ በበትራቸው
ላይ ስማቸውን ጽፎ ወደ ቅድስተቅዱሳኑ እንዲያገባው ነገረው፡፡
ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስም በአዋጅ አስነግሮ 1985 ብሮችን
ሰብስቦ ሲጸልይባቸው ቢያደር በአረጋዊ ዮሴፍ በትር ላይ
ምልክት ታየ፡፡ በትሩንም ሲሰጠው ነጭ ርግብ መጥታ በዮሴፍ
ላይ አረፈች፡፡ እርሱም ድንግልን እንዲወስዳት ሲነገረው
አለቀሰ፡፡‹‹ይቅር በሉኝ እኔ ሽማግሌ ነኝና ልጆችም አሉኝ፤
ዕድሜዬም 83 ዓመት ነውና›› እያለ አለቀሰ፡፡ ዘካርያስም
‹‹ይህ ሥራ ከእኛ ዘንድ አይደለም፣ እግዚአብሔር አዞናል
እንጂ፡፡ እነሆ እርሷን ትጠብቃት ዘንድ ሰጥቶሃልና
የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እምቢ አትበል፤ ትእዛዙን አንቀበልም
ያሉትን ፈጣሪህ እግዚአብሔር እንዴት እንዳደረጋቸው አስብ…››
እያለ አጽናናው፡፡ አገራዊ ዮሴፍም እየፈራ ድንግል ማርያምን
ወደቤቱ ወሰዳት፡፡ እቤቱወስዶም ልጆቹና ቤተሰቦቹ ይጠብቋት
ዘንድ አደራ ሰጥቷቸው ወደ ንግድ ሄደ፡፡ እመቤታችንም ወደ
ዮሴፍ ቤት በገባች ጊዜ ልጆቹ እናታቸውበልጅነታቸው
ሞታባቸዋልችና የሙት ልጆች ሆነው አገኘቻቸው፡፡ ዮሴፍ
አስቀድሞ ማርያም የምትባል ሚስት አግብቶ ነበር፡፡
ከእርሷም 3 ሴቶችና 4 ወንዶች ልጆች ነበሩት፡፡ እነርም
ስምዖን፣ ያዕቆብ፣ ይሁዳና ዮሳ ናቸው፡፡ ማቴዎስና ማርቆስም
ይህንን በወንጌላቸው ጽፈውታል፡፡
እመቤታችንም በመልአኩ ብስራት ጌታችንን ስትፀንስ ያንጊዜ
ዕድሜዋ 14 ዓመት ከ11 ወር ነበር፡፡ አረጋዊ ዮሴፍም ከ3
ወር በኋላ ሥራውን ጨርሶ ወደ ቤት ሲመለስ ደንግልን ፀንሳ
አገኛትና እጅግ ደነገጠ፡፡ በራሱም ላይ ትቢያን ነስንሶ በምድር
ላይ ወደቆ መራራ ልቅሶን አለቀሰ፡፡ ‹‹ማርያም ሆይ ካህናቱ
ስለ አንቺ ቢመረምሩኝ ምን እመልሳለሁ? በፈጣሪዬ
በእግዚአብሔር ፊትስ እንዴት እቆማለሁ? ከሚያገኘኝ ስድብም
የተነሣ ወዮልኝ፡፡ የእስራኤል ልጅ ሆይ ከማን ፀንስሽ?
ክብርሽንስ የደፈረ ማን ነው?...›› እያለ ጠየቃት፡፡ ድንግልም
‹‹እኔ ንጹሕ እንደሆንኩ እግዚአብሔር ያውቃል፤ ይህን
ያደረገው እግዚአብሔር ነው…›› እያለች ሁኔታውን በደንብ
አስረዳችው፡፡ እርሱም የሚያደርገው ግራ ገብቶት ሳለ
ይገልጥለት ዘንድ በልቅሶ ወደ እግዚአብሔር አመለከተ፡፡
እመቤታችንም ‹‹ጌታዬ ሆይ ይህን ምሥጢር ለአገልጋይህ
ለዮሴፍ ግለጥለት…›› ብላ ጸለየች፡፡ ወዲያውም እግዚአብሔር
ልአኩን ልኮ ለዮሴፍ በሕልም ተነጋገረው፡፡ በማኅፃኗ ያለው
በግብረ መንፈስ ቅዱስ ነውና አትፍራ… ሕዝቡንም ሁሉ
ከኃጢአታቸው ያድናቸዋል…›› እያለ አስረዳው፡፡ ከእንቅልፉም
ነቅቶ እጅግ ደንግጦ ወደ እመቤታችን ቢሄድ ስትጸልይ አገኛትና
ሰገደላት፡፡ ከዚህም በኋላ በናዝሬት ከሚኖሩ ከካህናት ወገን
የሆነ አንድ ካህን አረጋዊ ዮሴፍን ሰላምታ ይሰጠው ዘንድ ወደ
ቤቱ መጥቶ ‹‹ምነው ወደ ቤተ መቅደስ አልመጣህም?››
ቢለው ዮሴፍም ‹‹ከመንገድ የመጣሁት ገና ትናንት ነውና አረፍ
ልበል ብዬ ነው›› አለው፡፡ እንዲህ ሲጨዋወቱ ያም ካህን ወደ
ንጽሕት ደንግል አይኖቹን አንሥቶ ተመለከተና እንደፀነሰች
ዐወቀ፡፡ ወዲያው ሮጦ በፍጥነት ወደ ካህናቱ በመሄድ ‹‹ስለ
እርሱ ምስክር የሆናችሁለት ዮሴፍ እነሆ በደለ፣ ኃጢአትንም
ሠራ፣ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የወሰዳትን፣ እናንተም
ጠባቂዋ ያደረጋችሁት ድንግል ማርያምን ዐወቃት ፀነሰችም››
ብሎ ነገራቸው፡፡
እነርሱም ወደ ዮሴፍ መልእክተኞች ልከው ‹‹ማርያም ይዘሃት
ና›› ብለው ላኩበት፡፡ የሴፍም አምጥቷት ሁሉም ቢመለከቷት
ፀንሳች፡፡ ወደ ካህናቱም ሁሉ መልአክተኞችን ልከው ሁሉም
ካህናት ተሰበሰቡና ዮሴፍንና ድንግል ማርያምን በአደባባይ
አቆሟቸው፡፡ እመቤታችንንም ‹‹በእስራኤል ደናግል ላይ
ለምን ስድብን አደረግሽ?›› እያሉ ወቀሷት፡፡ በሙሴም ሕግ
መሠረት ሆድን የሚሰነጥቅ ማየ ዘለፋ አጠጧትና
የሚያደርጋትን ለማየት ተሰበሰቡ፡፡ ነገር ግን ማየ ዘለፋው
እንኳንስ በእርሷ ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይቅርና ፊቷን እንደ
ሚያዝያ ጨረቃ አደመቀው፡፡ የመንፈስ ቅዱስን ሥራ
የማያምኑትን ብዙዎችን ግን አቃጠላቸው፡፡ እነርሱም
የድንግልን ንጽሕናዋን ባዩ ጊዜ እጅግ ተደነቁ፡፡ ዮሴፍንና
እመቤታችንንም ‹‹እግዚአብሔር ካልፈረደባችሁ እኛ
አንፈርድባችሁ በሰላም ወደ ቤታችሁ ሂዱ›› ብለው
አሰናበቷቸው፡፡
በአውግስጦስ ቄሣር ትእዛዝ መሠረት ሄሮድስ በሀገረ ይሁዳ
ሰው ሁሉ በየወገኑ፣ በየሀገሩ፣ በየአባቱ ይቆጠር ዘንድ አዘዘ፡፡
አይሁድም ለመቆጠር ብቻ ሳይሆን ሄሮድስን አይወዱትም
ነበርና ከቄሣር ጋር ያጣሉት ዘንድ ተሰበሰቡ፡፡ እመቤታችንም
የመውለጃዋ ወቅት ደርሶ ነበርና አረጋዊ ዮሴፍ ወደ ቤተልሄም
ወስዳትና ከአንዲት የእረኞች ዋሻ ውስጥ ይዟት ገባና በዚያ
አደሩ፡፡ በዚያም ከብቶች የሚያድሩበት የፈረሰ ግንብ ነበረ፡፡
ይህም በኬብሮን ትይዩ ሲሆን አቀድሞ የእሴይ ቤት ነበርና
ዳዊት በዚህ ቤት ተወልዷል፣ በዚያም በሳሙኤል እጅ
የመንግሥት ቅባት ተቀብቶበታል፡፡ ቦታው በባቢሎን ስደት ጊዜ
ፈርሶ የፈረሰው ግንብ ከሩቅ ለሚመጡ ነጋዴዎች ማደሪያ ሆኖ
ነበር፡፡ በአጠገቡም ዋሻ ነበርና ጌታችን በታኅሣሥ ወር
በመንፈቀ ሌሊት ማክሰኞ ቀን በዚያ ዋሻ ተወለደ፡፡ ጌታችንም
በተወለደ ጊዜ ዋሻው በእጅጉ ስላበራ ዮሴፍ ደንግጦና
ተንቀጥቅጦ መሬት ላይ ወደቀ፡፡ እመቤታችንም ስትወልድ
እንደሴቶች ሁሉ ልማድ ሕማም አላገኛትም፡፡ መልአኩም
ለእረኞቹ አብስሯቸው ወደ ዋሻው ሄደው የተወለደውን ሕፃን
ከእናቱና ከዮሴፍ ጋር አገኙት፡፡ ከእረኞቹም አንዱ
የቤተልሔሙና በኋላም በይሁዳ ተተካው ማትያስ ነበር፡፡
እረኞቹም የበግ ጠቦትና የላም ወተትን፣ ማርንና ቅቤን
አምጥተው እጅ መንሻ አቀረቡ፡፡ የሕፃኑንም መለኮታዊ እግር
ስመው ከሁሉም በፊት አስቀደመው ሰገዱለት፡፡
ለእመቤታችንና ከዮሴፍም ከሰገዱ በኋላ ተመልሰው ሄደው
በይሁዳ ሀገር ሁሉ ዜናውን ተናገሩ፡፡
ሰሎሜም እመቤታችን በድንግልና የበኩር ልጇን እንደወለደች
ስትሰማ መጀመሪያ ‹‹በዓይኖቼ ካላየሁ በእጆቼም ካልዳሰስኩ
አላምንም›› ብላ ወደ ዋሻው ሄደች፡፡ ወደ እመቤታችንም
ቀርባ ሰውነቷን ዳሰሰች፡፡ ወዲያውም መለኮታዊ እሳት
የወጣበትን ሰውነቷን ዳሥሣለችና እጆቿ ተቃጠሉ፤ ደረቁም፡፡
ወዲያውም በታላቅ ቃል እየጮኸችና እያለቀሰች ‹‹የአምላክ
እናት ሆይ ይቅር በይኝ የሃይማኖቴ ጉድለት ታላቅ መከራ
አመጣብኝ›› እያለች በእመቤታችን ፊት መሪር ልቅሶን
አለቀሰች፡፡ ድንግል ማርያምም ወደ ልጇ ማለደችላት፡፡
በዚህም ጊዜ መልአክ መጥቶ ሰሎሜን ‹‹እግዚአብሔር ይቅር
ብሎሻል፣ ወደ ሕፃኑ ሂጂና በተቃጠሉ እጆቺሽ ያዥውና ታቀፊው
ተድኛለሽ›› አላት፡፡ እመቤታችንም ትታቀፈው ዘንድ ሕፃኑን
ልጇን ሰጠቻት፡፡ ሰሎሜም ታቀፈችው ጊዜ እጇ ወዲያው
ዳነላትና የእመቤታችንን ደንግልናዋን አምና ሰገደችላት፡፡
ሰሎሜም ያየችውንና የሆነውን ሁሉ ለኢየሩሳሌም ነዋሪዎች
ሁሉ ለማውራት እጅግ ተቻኩላ ከዋሻው ወጥታ ስትሄድ ከሰማይ
ድምጽ መጣላትና ያየችውን ተአምር ሕፃኑ ወደ ቤተ መቅደስ
እስኪገባ ድረስ ለማንም እንዳትናገር አስጠነቀቃት፡፡ ጌታቸንም
እንደ አይሁድ ልማድ በ8ኛ ቀኑ ግዝረትን በግብረ መንፈስ
ቅዱስ ፈጽሞ በ40ኛውም ቀን ወደ ቤተ መቅደስ ወሰዱት፡፡
ጌታችን ከመወለዱ ከ277 ዓመት በፊት በንጉሥ በጥሊሞስ
ትእዛዝ 72ቱ ሊቃውንት መጻሕፍቶቻቸውን ከዮናናውያን ቋንቋ
ወደ ጽርዕ ቋንቋ ሲተረጉሙ የ123 ዓመቱ ስምዖን አንዱ
ነበር፡፡ ትንቢተ ኢሳይያስን የተረጎመው እርሱ ነበርና ድንግል
ድንግልና ፀንሳ በድንግልና እንደምትወልድ ይህንንም ሳያይ
እንዳይሞት እግዚአብሔር ቃል ገብቶለት ነበር፡፡ ወደ
መቅደስም ሲመጣ መልአኩ ለስምዖን ተገልጦለት ሲጠብቀው
የኖረው ተስፋው ዕውን ሆኖ ዛሬ መሢሑን በክንዶቹ
እንደሚታቀፈው ነገረው፡፡ በቤተ መቅደስም ጌታችንን
አገኘውና ታቅፎ ‹‹ጌታ ሆይ ዓይኖቼ ማዳንህን አይተዋልና
ባሪያህን ሰላም አሰናብተው›› አለው፡፡ ለእመቤታችንም
‹‹ጦርና ሰይፍ በልብሽ ውስጥ ይገባል›› ብሎ በልጇ ምክንያት
የሚደርስባትን መከራ በትንቢት ነገራት፡፡ ‹‹ጦርና ሰይፍ››
ያለውም የክርስቶስን መከራ ነው፡፡ በሕማሙና በመቸንከሩ
ልቧ መሪር በሆነ የኀዘን ጦር ተወግቷልና አንጀቷም በተሳለ
የሰይፍ ኀዘን ተነዋውቷልና፡፡ ልጇ የተቀበላቸው መከራዎችንም
እንደ እርሱ በልቡናዋ እመቤታችንም ተቀብላቸዋለችና
ስለዚህም የሰማዕታት እናት ትባላለች፡፡
ከሰብዓ ሰገል አንዱ ዘሮአስተር የሚባለው ስለ ኮከብ መውጣትና
ስለ ክርስቶስ ትንቢት ተናግሮ ነበርና ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የጥበብ
ሰዎች መጻሕፍትን ተምረው በትንቢቱም ታምነው ይኖሩ
ነበር፡፡ ስለዚህም በየዓመቱ ሁሉም አንድ ቀን ከፍ ባለ ተራራ
ላይ ይሰበሰቡና ኮከቡን ይመለከቱታል፡፡ ክርስቶስም በተወለደ
ጊዜ አዲስ ኮከብ በሕፃን መልክ ታያቸው፡፡ በላዩም የመስቀል
ምልክት አለው፡፡ ‹‹የአሕዛብ ተስፋቸውና መስፍናቸው፣
የአይሁድ ንጉሣቸው ወደ ምድር ወረደ›› የሚል ቃልም ሰሙ፡፡
‹‹እጅ ለመንሳትና ለመስገድም ፈጥናችሁ ሂዱ›› አላቸው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ የጥበብ ሰዎችን ቁጥር ባይገልጸውም
አውግስጦስና ዮሐንስ አፈወርቅ 12 ናቸው ብለዋል፡፡ በሦስት
የትውልድ ቅርን መስለው ሦስት ናቸው የሚሉም አሉ፡፡
ዮሐንስ አፈወርቅ እንደተናገረው በ5 ወር ደርሰው ደብረ ዘይት
እግር ሥር ከተሙ፡፡ ተጉዘውም ኢየሩሳሌም ከተማ ገብተው
‹‹የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ የት ነው?›› ብለው ሲጠይቁ
ሄሮድስና መላዋ ኢየሩሳሌም ታወኩ፡፡ ሰብዓ ሰገልም በኮከቡ
ተመርተው ወደ ቤተልሔም ዋሻ ገብተው ሕፃኑን ከእናቱና
ከዮሴፍ ጋር አገኙትና ወድቀው ሰገዱለት፡፡ እጅ መንሻቸውን
አቀረቡለት፡፡ መልአኩም ከሄሮድስ እንዲሰወሩ ነግሯቸው በሌላ
መንገድ ተመለሱ፡፡ እመቤታችንና ዮሴፍም ሥርዓቱን ሁሉ
ፈጽመው ሲጨርሱ ወደ ሀገራቸው ተመለሱ፡፡ የስምዖንም
ትንቢት ይፈጸም ዘንድ የሄሮድስ ቁጣ ነደደችና 2 ዓመትና ከዚያ
በታች ያሉ ሕፃናት ሁሉ ይገደሉ ዘንድ አዘዘ፡፡ የነቢዩ
ኤርሚያስም ትንቢት ተፈጸመችና 144 ሺህ ሕፃናትም ተገደሉ፤
መቃብራቸውም በራማ ሀገር በበለስ ዛፍ ሥር ነው፡፡
መልአኩም ለዮሴፍ ተገልጦለት ‹‹ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው
ይፈልገዋልና ተነሥ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ››
አለው፡፡ እርሱም ወዲያው በሌሊት ተነሥቶ ይዟቸው ሸሸ፡፡
ከናዝሬት ጀምረው የባሕሩን ዳርቻ ይዘው እስከ ፍልስጤም
ደረሱ፡፡ በ6ኛው ቀን ደክሟቸው አንድ ዋሻ ውስጥ ገቡ፡፡
እመቤታችንም በጸሎቷ ውኃን አመነጨችና ጠጡ፡፡ ያም
ምንጭ ስሙ የማርያም ውኃ ተብሎ እስከዛሬ አለ፡፡
በሌሎችም ቦታዎች እመቤታች ስትጸልይ ውኃ እየፈለቀ
በእርሱ ልጇን ገላውን ታጥበዋለች፡፡ ዐሥር ቀን ያህል በይሁዳ
ሀገር፣ ዐሥር ቀን ያህል በምድረ በዳ እጅግ አስቸጋሪ ጉዞ
ከተጓዙ በኋላ ግብፅ ደረሱ፡፡
ጌታችንም ምድረ ግብፅ በደረሰ ጊዜ በነቢዩ ኢሳይያስ ትንቢት
መሠረት የግብፅ ጣዖታት ከመሠረታቸው ተነዋውጠው ምድር
አፏን ከፍታ ዋጠቻቸው፡፡ በግብፅ ኤሌዎጶሊዎስ ሀገር ገብተው
ዮሴፍ ማረፊያ ሠራ፡፡ በዚያም ባለች ተራራ ሥር ጌታችን ውኃን
አፈለቀ፡፡ ይህችውም በእኛና በቅብጥ ሰዎች ዘንድ ሰኔ 8 ቀን
የምትታሰበው ዕለት ናት፡፡ ደም ማፍሰስ የለመደ ርጉም ሄሮድስ
ሚስቱን ማርያናንም ከገደላት በኋላ ይበቀሉኛል በማለት
ከእርሷ የወለዳቸውን የገዛ ልጆቹንም ገደላቸው፡፡ ከዚህም
በኋላ በሥጋው ጽኑ መከራ መጣበትና እግዚአብሔር የደዌውን
ዘመን አስረዘመበት፡፡ ቢበላ ቢበላ ይጠግብም
ይልቁንምረሀብና ጥም ይበዛበታል፣ አንጀቱም ተቋጠረ፣
ሰውነቱም ተልቶ ሰው ሁሉ አልቀርበው አለ፡፡ ማቆ ሲያበቃ
በመጨረሻም ክፉ አሟሟት ሞተ፡፡ የእግዚአብሔርም
መልአክ ዮሴፍን ሄሮድስ ስለሞተ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ ወደ
እስራኤል እንዲመለስ ነገረው፡፡ ተመልሰውም በፍልስጤም
አልፈው ድልማጥያ ወደምትባል አንዲት ገር ደርሰው በበረሃ
ውስጥ ተቀመጡ፡፡
እመቤታችንም ከነልጇ ረሃቡ ቢጠናባት ትዕማን ወደምትባል
አንዲት ከበርቴ ባለሀብት ቤት ሄዳ ቁራሽ እንጀራንና ለልጇም
ጥቂት ወተትን ለመነቻት፡፡ ያቺ ክፉ ሴት ግን ልብን በሀዘን
የሚሰብር ክፉ ንግግርን ተነጋረቻት፡፡ ጻድቅ ዮሴፍም
‹‹እንግዳን ካለ ይሰጡታል ከሌለ በሰላም ይሸኙታል እንጂ
ለምን ክፉ ንግግርን ትናገሪያታለሽ›› እያለ ሲነጋገሩ አሽከሯ
ኮቲባ የእመቤቷን ቁጣ ሰምታ መጥታ ጌታችንን ከመሬት ላይ
ጥላ እንደ ድንጋይ አንከባለለችው፡፡ እመቤታችንም ደንግጣ
እያለቀሰች ልታነሣው ስትል ዮሴፍ ‹‹ተይው አታንሽው ኀይሉን
ያሳይ›› አላት፡፡ ያንጊዜም ምድር አፏን ከፍታ ዋጠቻት፣ ገረዷ
ኮቲባም በለምጽ ተመታች፡፡ በቤታቸውም ውስጥ በሕይወት
የቀረ የለምና ቤተሰቦቿ ጦጣ ሆነው ከተራራ ወደ ተራራ ሸሹ፡፡
እመቤታች፣ ዮሴፍና ሰሎሜም በትዕማን ቤት 6 ወር
ከተቀመጡ በኋላ መልአኩ ተገልጦ ከዚያ እንዲወጡ አዘዛቸውና
ወጡ፡፡ አርዲስ ወደምትባል ሀገርም ደርሰው የሀገሪቱ ሰዎች
በሰላም ተቀብለው አስተናገዷቸው፡፡ እመቤታችንም ከሀገረ
ገዥው ሆድ ውስጥ በጸሎቷ እባብ ላወጣችለትና ከሕመሙ
ስላደ በጣም አከበሯቸው፡፡ ዕውሮችን፣ አንካሶችን፣
ለምፃሞችንና አጋንንት ያደሩባቸውን ሁሉ እያመጡላት የልጇን
እጆች ይዛ ከሩቅ እያማተበች ፈወሰቻቸው፡፡ ሄሮድስም
እንደሚያፈላልጋቸው መልአኩ ሲነግራቸው ከአንዱ ሀገር ወደ
ሌላው ሀገር እየተዘዋወሩ ታችኛው ግብፅ ንሂሳ ድረስ ደረሱ፡፡
እመቤታችንም በዚያ ያሉ ሕመምተኞችን ፈወሰችላቸው፡፡
ከዚህም በኋላ አሁንም መልአኩ ነግሯቸው ደመናም መጥታ
ነጥቃ ወሰደቻቸውና የ38ቱን ወራት መንገድ በአንድ ጊዜ
አደረሰቻቸው፡፡ በዚያም ትንሽ ከቆዩ በኋላ ወደ ቤጎር ቆላ
ደረሱ፡፡ በዚያም ግብፃውያን እንደ ሕጋቸው ለአማልክቶቻቸው
ላሞችን አርደው ሠውላቸው፡፡ በጎሽ፣ በአውራሪስ፣ በነጭ
ዝንጀሮ የሚመሰሉ አጋንንትም መጡ፡፡ እመቤታችንም ከሩቅ
ሆና ተመልክታቸው እነዚያን አጋንንት በጸሎቷ እንደጢስ
በተነቻቸው፡፡ ግብፃውያንም ፈርተው እየጮኹ ሸሹ፡፡ በዚያም
ወራት ‹‹ረዳት አማልክቶቻችንን ጠፉብን›› ብለው እያዘኑ ሳለ
ዮሴፍን ሲጸልይ አግኝተውት አስረው በምድር ላይ አስተኝተው
40 ግርፋት ገረፉት፡፡ እርሱም በዚህ ጊዜ ‹‹እመቤቴ ሆይ ስለ
አንቺና ስለ ልጅሽ ይህ መከራ አግኝቶኛልና እርጂኝ›› ብሎ
በኀይል ጮኸ፡፡ እመቤታችንም ድምጹን ስትሰማ የሄሮድስ
ጭፍሮች የመጡ መስሏት እጅግ ደነገጠች፡፡ ቅዱስ
ገብርኤልም ተገልጦ ካረጋጋት በኋላ ዮሴፍን በኀይል ይደበድቡ
የነበሩትን በእሳት ሰይፉ ጨረሳቸው፡፡ ዮሴፍንም በእጆቹ
ዳሰሰውና ፈወሰው፡፡ እመቤታችንም ዮሴፍን ባየችው ጊዜ
‹‹ይህ ሁሉ መከራ ያገኘህ በእኔና በልጄ ምክንያት ነው››
ብላውአንገት ለአንገት ተቀቅፈው ተላቀሱ፡፡ መልአኩም ‹‹ይሄ
ሀዘናችሁ በደስታችሁ ጊዜ ይረሳል…›› እያለ አረጋጋቸውና
ዐረገ፡፡
የሀገሩ ሰዎችም ይወጓቸው ዘንድ ወጡና ክፉ ውሾችን
ለቀቁባቸው፡፡ ነገር ግን ውሾቹ በሰው አንደበት እመቤታችንን
እያነገሯት ሰግደው የእግሯን ትቢያ ልሰው በመመለስ
ባለቤቶቻቸውን መልሰው መናከስ ጀመሩ፡፡ ብዙዎቹንም
ገደሏቸው፡፡ ዮሴፍም ‹‹እመቤቴ ሆይ በዚህ ሀገር ከምንኖርስ
በዱር በበረሀ ብንኖር ይሻለናል›› ብሏት ወደለሌላ ትርጓሜዋ
የሰላም ሀገር ወደሆነች ዲርዲስ ሀገር ደረሱ፡፡ ሰዎቹም
‹‹ይህችስ የነገሥታት ወገን ትመስላለች በላያችን ላይ
ትነግሥብናለች›› ብለው በክፉ ሲነሱባቸው በማግስቱ ደመና
ነጥቃ ወስዳ ኤልሳቤጥ በሞት ካረፈችበት በረሀ አደረሰቻቸው፡፡
ዮሐንስ በእናቱ በድን ላይ ሆኖ እያለቀሰ ሳለ ዮሴፍንና ሰሎሜን
ባያቸው ጊዜ ደነገጠ፡፡ ጌታችንም አረጋጋው፡፡ እመቤታችንም
ስለ ኤልሳቤጥ ሞት እጅግ መሪር የሆነ ልቅሶን ስታለቅስ ልጇ
ድንቅ ምሥጢርን ከነገራት በኋላ አረጋጋት፡፡ እመቤታችንም
‹‹እናቱ ሞታበታለችና በዚህም በረሀ ማንም የለመውና
ዮሐንስን ከእኛ ጋር እንውሰደው›› ስትለው ጌታችን ‹‹ዕድሉ
በዚህ በረሀ ነው›› ብሎ አረጋጋት፡፡ ከዚህም በኋላ ደመና ነጥቃ
ወስዳ ወደ ጋዛ ምድር አደረሰቻቸውና በዚያ አተር የሚያበራዩ
ሰዎችን አግኝታ እመቤታችን ‹‹ለልጄ አተር ስጡኝ››
አለቻቸው፡፡ እነርሱም ክፉዎች ነበሩና ‹‹ይህ አተር ሳይሆን
ድንጋይ ነው›› አሏት፡፡ ሕፃኑ ልጇም ‹‹እናቴ ሆይ እንደቃላቸው
ይሁንላቸው ተያቸው›› አላት፡፡ ያንጊዜም አተሩ ድንጋይ ሆነ፣
ይህም እስከዛሬም ድረስ አለ፡፡ ከዚህም በኋላ እመቤታችን ወደ
ተወለደችበት ሀገር ወደ ሊባኖስ ተራራ ሄደው በዚያ ያሉ
ሰዎችም በሰላም ተቀበሏቸው፡፡ እመቤታችንም ብዙ
ተአምራት አደረገችላቸው፡፡ ገዥው ደማትያኖስም ሄሮድስን
ሊወጋው ጦሩን አዘጋጅቶ ሳለ ነገር ግን ፈቃደ እግዚአብሔር
ከለከለችው፡፡ መልአክም ተገልጦለት በእርሱ ምክንያት ብዙ
ሰማዕታት ይሰየፉ ዘንድ አላቸውና ጊዜው ገና መሆኑን
አስረድቶት ሄሮድስን በጦር እንዳይገድለው ከለከለው፡፡
ደማትያኖስም ኃይሉና ጦሩ እጅግ የበረታ ነበር፡፡ ቅዱስ ጊጋርም
በዚህ ወቅት ስለ እመቤታችንና ስለልጇ ሰማዕት ሆነ፡፡ ቅዱስ
ገብርኤልም ለእመቤታችን ተገልጦ ወደ ግብፅ እንድትሄድ
ነገራት፡፡ ዳግመኛም መልአኩ ለገዥው ለደማትያኖስ
ተገልጦለት ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ እንዲያሰናብታት ነገረው፡፡
እርሱም አስቀድሞ ‹‹በዙፋኔ ተቀመጪ እኔና ሚስቴ
አገልጋይሽ እንሁን እንጂ ከዚህስ አትሄጂም›› ብሎ ግድ ብሏት
ነበርና፡፡ ከዚህም በኋላ የአንድ ቀን መንገድ ሸኝቷት እንዲህ
አላት፡- ‹‹እመቤቴ ሆይ ሄሮድስ ቢፈልግሽ ወደኔ መልእክት
ላኪብኝ ፈጥኜ እመጣለሁ፡፡ የእስራኤል አምላክ ቢፈቅድልኝ
ከዛብሎን፣ ከንፍታሌምና ከሐሴቦን ጀምሮ ይሁዳንና
ኢየሩሳሌምን ሁሉ አጠፋቸዋለሁ፡፡ ሰውን ብቻ የምገድል
አይደለሁ ዛፎቻቸውን ቆመው እንዲታዩ አልፈቅድም፡፡
ሀገሪቱንም ፍርስራሽ አደርጋታለሁ›› አላት፡፡ ይህ
የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዳልሆነ አስረድታው መርቃ
አሰናበተችውና በበነጋታው ተለያዩ፡፡
ወደ ቤተልሔምም ከደረሱ በኋላ አሁንም መልአኩ አዘዛቸውና
በሌሊት ተነሥተው ወደ ግብፅ ተጓዙ፡፡ ሄሮድስም ሀገሪቱን
መጥቶ ከበባት፡፡ እነርሱንም ቢያጣ በዚያ ያገኘውን ሁሉ ሰየፈ፡፡
2 ዓመትና ከዚያ በታች ያሉ ሕፃናትን ሁሉ ሰብስበው
እንዲያመጡአቸው አዘዘና 144 ሺህ የቤተልሔም ሕፃናትን
ከእናቶቻቸው ላይ እየቀማ ሰየፋቸው፡፡ መላእክትም እጅግ
ደንግጠው ይህ ለምን እንዲሆን ፈቀድክ ብለውም
አምላካቸውን ጠየቁ፡፡ እንዲህ የሚል ቃልም ከዙፋኑ ወጣ፡-
‹‹ኢየሩሳሌም በሰው ደም እንደምትታጠብ በነቢያት እንዲሁ
ተጽፏልና እነዚህ ሕፃናት ለመንግሥተ ሰማያት ቀድመው
ተዘጋጁ ናቸው›› እመቤታችንና እነ ዮሴፍም ግብፅ ደርሰው
በዚያ ቢቀመጡም ነገርን ግብፅ አልተመቸቻውም፡፡ ሕዝቡም
በሰላም አልተቀበላቸውም፡፡ ወደ ኢትዮጵያ በመጡ ጊዜ ግን
ሕዝቡ ሁሉ በሰላም ተቀበላቸው፡፡
ከመንገዱና ከርሃብ ጥሙ ጽናት የተነሣ እጅግ ደክማለችና
የኢትዮጵያ ሰዎች እመቤታችንን አይተው እጅግ አዘኑላት፡፡
‹‹ይህችስ የነገሥታት ዘር ትመሥላለች ነገር ግን አንዳች ችግር
አጋጥሟት ተሰዳ ወደ ሀገራችን መጥታለች..› ብለው
እንክብካቤን አደረጉላት፡፡ እግራቸውን አጥበው በክብር
ማረፊያዎች ላይ አሳረፏቸው፡፡ መልካም መስተንግዶም
አደረጉላቸው፡፡ እመቤታችንም ከድካሟ ካረፈች በኋላ ሀገሪቱን
በእጅጉ ወደደቻትና የተወደደ ልጇን ‹‹ይህን ሀገርና ሕዝቧን
በመላ ወድጃቸዋልሁና በዚህ እስከ መጨረሻው እንኑር››
አለችው፡፡ ጌታችንም ክብርት እናቱን ‹‹ይህች ቅድስት ሀገር
ናት፣ በኋለኛው ዘመን የቅዱሳን መነኮሳት ቦታ ትሆናለች፡፡
በውስጧም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ እመሰገንባታለሁ፤
የአንቺም ስም ሳይጠራ አይውልባትም›› አላት፡፡ ከዚህም በኋላ
ጌታችን ደመና ጠቅሶ በእርሷ ላይ ተቀመጡ፡፡ መልአኩ ቅዱስ
ዑራኤልም መጣና እየመራቸው መላ ኢትዮጵያን ጎበኟት፡፡
እመቤታችንም ሀገሪቱንና ሕዝቦቿን ወዳቸዋለች ደስም
ተሰኝታባቸዋለችና ጌታችን ለክብርት እናቱ ‹‹ይህችን ቅድስት
ሀገር አሥራት አድርጌ ሰጠሁሽ›› አላት፡፡ እመቤታችንም እጅግ
ተደስታ ‹‹ልጄ አምላኬ›› ብላ አመሰገነችው፡፡ ከዚህም በኋላ
ከአብዱ ቦታ ወደ አንዱ ቦታ እየተዘዋወሩ መላዋ ኢትዮጵያን
በኪደተ እግራቸው ባረኳት፡፡
ጌታችንም ‹‹በዚህ ቦታ እንዲህ ዓይነት ቤተ ክርስቲያን
ይታነጻል፤ እከሌ የሚባል እንዲህ ዓይነት ቅዱስ ይነሣል…››
እያለ ብዙ ምሥጢራትን ለእናቱ ነገራት፡፡ ከዚህም በኋላ የስደቱ
ዘመን ሲያልፍ ሄሮድስም በመጨረሻ ክፉ አሟሟትን ሲሞት
መልአኩ ወደ ገሊላ አውራጃ እንዲመለሱ ነገራቸው፡፡
እመቤታችንም ‹‹ከዚህች ሀገርስ ባንሄድ እመርጣለሁ›› ስትል
የተወደደ ልጇ ‹‹እናቴ ሆይ ጽድቅንና ፈቃድን ሁሉ ልንፈጽም
ይገባናል›› ብሎ አጽናናትና ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ሄዱ፡፡
እመቤታችን ልጇን መድኃኔዓለምን ይዛ ለምን ተሰደደች?
1ኛ.ትንቢተ ነቢያትን ለመፈጸም፡- እግዚአብሔር ሊያደርግ
ያሰበውን ፈቃዱን ሁሉ ለሰው ልጅ እየገለጠ ነቢያትን ትንቢት
እያናገረ መምህራንን እየላከ መጽሐፍትን እያጻፈ መሆኑን ልብ
ማለት ተገቢ ነው፡፡ ‹‹እግዚአብሔር ለህዝቡ በመጽሐፍ
ይናገራቸዋል››፣ ‹‹በቀንና በሌሊት ባሪያዎቼን ነቢያትን ሁሉ
ልኬባቸው ነበር፣ አዎ ልኬባቸዋለሁ›› እንዲል፡፡ መዝ 87:6፣
ኤር 7፡25፡፡ ከነዚህም ትንቢታት መካከል ስለ እመቤታችንና
ስለ ልጇ ስደት ሲሆን ነቢዩ ኢሳይያስ 19፡1 ላይ ‹‹እነሆ
እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እየበረረ ወደ ግብጽ ይመጣል››
በማለት ሲናገር ከሙሴና ከአሮን ጸሎት የተነሳ የግብጻውያን
የእጃቸው ሥራ መጥፋቱን፣ እግዚአብሔር በናቡከደነጾር አድሮ
ወደ ግብጽ መምጣቱን፣ ጣዖታትን ማጥፋቱን የተነበየበት
ከመሆኑ በላይ በእመቤታችን ጀርባ ታዝሎ በፈጣን ደመና
በተመሰለች ከእመቤታችን ጋር ወደ ግብጽ ተሰደደ፡፡ ሊቃውንት
እመቤታችንን ሲመስሏት ደመና ኢሳይያስ የሚሏትም ስለዚህ
ነው፡፡
በዚህ ትንቢት ላይ እንደተገለጸው ግብጽ በጣዖታት የተሞላች
በመሆኗ የጌታችን ስደት በግብጽ ያሉ ጣዖታትን ለማጥፋት
እንዲሆን ተጠቅሷል፡፡ ግብጻውያን ከጥንት ጀምሮ የላም፣
የፍየል፣ የአንበሳ ምስልን በመቅረጽ ያመልኩ ነበር፡፡ እነዚህን
ለማጥፋት የጌታ ስደት ወደ ግብጽ ይሆን ዘንድ ትንቢት አናገረ፡፡
ከዚህም ባሻገር በኛ ሕይወትም ውስጥ ጌታችንን ለመቀበልና
ሥራ እንዲሠራብን በቅድስና ለመኖር የልብን ጣዖታት ማጥፋት
ማጽዳት ይገባል፡፡ ጌታንና ጣዖትን በልባችን ማኖር
አንችልም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን
ኅብረት አለው? ክርስቶስ ከቤልሆር ጋር መስማማት አለው
ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው
ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም
አለው፡፡ እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነንና›› ያለው
ለዚሁ ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት መዝ 83፡3 ‹‹ወፍ ለእርስዋ ቤትን
አገኘች ዋኖስም ጫጭቶችዋን የምታኖርበት ቤት አገኘች››
በማለት ሲተነብይ ወፍ ለእርስዋ ቤትን አገኘች ሲል ነቢያት
የተነበዩት ፍጻሜውን በእመቤታችን ማግኘቱን አንድም
እመቤታችን በስደት ግብጽ መኖርያዋ ማድረጓን ዋኖስም
ጫጭቶችዋን የምታኖርበት ሲል ዮሴፍና ሰሎሜም
የሚኖሩበት ቤት ማግኘታቸውን ተናገረ፡፡ ለእመቤታችን
ማደሪያ ጠፍቶ ማደሪያዋን ግብጽ ማድረጓን ተንብየዋል፡፡ ነቢዩ
ሆሴዕ ‹‹እስራኤልን ሕጻን በነበረ ጊዜ ወደድኩት ልጄንም
ከግብጽ ጠራሁት›› እንዳለ (11፡1) እስራኤል በግብጽ ሳሉ
እንደተመረጡ ከዚያም አገር አውጥቶ መንግስት ይሆኑ ዘንድ
እንዳበቃቸው የተናገረበት ትንቢት ከመሆን ጋር የጌታችን ወደ
ግብጽ መሰደድ ሔሮድስ እስኪሞት በዚያ መቀመጡን ከዚያም
መመለሱን የሚያመለክት መሆኑን ቅዱስ ማቴዎስ የነቢዩን
ቃል ፍጻሜ አድርጎ ተናግሯል፡፡ ማቴ 2፡15፡፡
2ኛ. የቅዱሳንን ስደት ለመባረክ ጌታችን ከድንግል እናቱ ጋር
ተሰደደ፡-የክርስትና ሕይወት የመስቀል ላይ ጉዞ በመሆኑ
ክርስቶስን አምነው ለተከተሉት ሁሉ በመከራና በስደት
እንደሚያልፍ ጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ከአለም ተመርጠው
ለተከተሉት ደቀ መዛሙርቱ ሲያስተምር ‹‹እኔን መከተል
የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ››
በማለት ተናገረ፡፡ ማቴ. 16፡24፡፡ በዚህም ቃል መሠረት
ከቅዱሳን ሐዋርያት ጀምሮ የተነሡ ክርስቲያኖች በብዙ መከራ
ውስጥ አለፉ በበረሃ ተሰደዱ፣ በዱር በገደሉ ተቅበዘበዙ በሰይፉ
ተተረተሩ፣ በድንጋይ ተወገሩ፡፡ ዛሬም ቢሆን በእምነት
የተሰደድን የተጨነቅን የምንጸልየው ስደትን ከኛ በፊት
በሕጻንነቱ በቀመሰ ስደትን በሚያውቅ አምላክ ፊት ነው፡፡
3ኛ.ጣኦታተ ግብጽን ለማጥፋት ተሰደደ፡- ግብጽ ከነገሥታቶቿ
ጀምሮ ጣኦትን የሚያመልኩ አሕዛብ የነበሩ ህዝቦች ነበሩ፡፡
እነዚህ ጣኦታት ደግሞ የእንስሳትን ምስል በማስመሰል ደንጊያ
ጠርበው እንጨት አለዝበው ማዕድን አቅልጠው የበሬ፣ የላም፣
የአንበሳ፣ የወፍ ምስል አስቀርጸው ያመልኩ ስለነበር ከተማዋ
በጣኦታት የተሞላች ነበር፡፡ ለዚህም ጌታችን ጣኦታትን
ሊያፈርስ ወደ ግብጽ ተሰደደ፡፡ ገና ከተማዋ ሲገባ በጣኦታቱ ላይ
ያደሩ አጋንንት ጮኸው ወጡ፣ ጣኦታቱም ተሰባበሩ፡፡
4ኛ.ጌታችን ሰው መሆኑን ለመግለጽ ተሰደደ፡- ኢየሱስ ክርስቶስ
አገሩን ሳይለቅ ከሄድሮስ ዓይን መሠወር ይችል ነበር፡፡ ነገር
ግን በአምላካዊ ጥበቡ ከሄሮድስ ዓይን ተሰውሮ ቢሆን ሥጋ
መልበሱ ሰው መሆኑን አይገለጽም ነበር፡፡ በሄሮድስ ዓይን
የማይታይ ከሆነ ሥጋ ሳይለብስ የለበሰ መስሎ የተገለጸ ሥጋና
አጥንት የሌለው (ምትሐት) ነው በተባለም ነበር፡፡ ከአዳም
አካል አንድም ያልጎደለው ሙሉ ዳግማዊ አዳም መሆኑን እና
የለበሰው ሥጋ የሚደማ የሚቆስል በሰይፍም ሆነ በጦር ቢወጋ
ጉዳት የሚደርስበት ሰብአዊ ባሕርይ ያለው መሆኑን
ለማስረዳት ስደተኛ ሆነ፡፡ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ከጠላቱ ማምለጥ
የሚችለው ከጠላቱ ፊት ዞር በማለቱ እና በመሸሹ ስለሆነ
ጌታም ከጠላቱ ከሄሮድስ ለማምለጥ ሰው እንደመሆኑ ወደ
ግብጽ ሸሸ፡፡
5ኛ. ምሳሌውን ለመፈጸም ተሰደደ፡- ጌታችን የሥጋ አባቶቹ እነ
አብርሃም፣ ያዕቆብ፣ ኤርምያስ ሁሉ አስቀድመው ወደ ግብጽ
ተሰደው ስለነበር፡፡
6ኛ.ጌታችን የግብፅና የኢትዮጵያ ገዳማትን ይቀድስ ዘንድ
ከድንግል እናቱ ጋር ተሰደደ፡፡
7ኛ.የአዳምን ስደት በስደቱ ለመካስ ጌታችን ተሰደደ፡፡
8ኛ.ዲያብሎስን ለማሳደድ ተሰደደ፡- አዳም ዕፀ በለስን በልቶ
ከፈጣሪው ጋር ተጣልቶ ከገነት ከወጣ በኋላ የእግዚአብሔርና
የሰው ግንኙነት የተራራቀ ሆነ፡፡ ይህን የፈጣሪና የፍጡር
መራራቅ ያመጣው ዲያብሎስ የአዳምን ልጆች ሁሉ
ተቆጣጠራቸው፡፡ ልባቸውን በፍቅረ ጣኦት ሸፍኖ አምልኮተ
እግዚአብሔር እንዳያዩ አደረጋቸው ብዙ የአዳም ልጆችም
የአግዚአብሔርን ፈቃድ ሳይሆን የሰይጣንን ፈቃድ ሲፈጽሙ
ኖሩ፡፡ ጌታም ‹‹አሁን የዚህ ዓለም ገዥ ወደ ውጪ
ይጣላል›› (ዮሐ12፡31) በማለት ሰይጣን ዓለሙን
ተቆጣጥሮት እንደነበረ ይገልጻል፡፡ እግዚአብሔር ወልድ
የሰውን ሥጋ በለበሰ ጊዜ የፈጣሪና የፍጡር ግንኙነት እንደገና
ተመሠረተ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ዲያብሎስን ከተቆጣጠረው
ከሰው ልቡና አስወጣው ጌታ ከሄሮድስ ፊት እየራቀ ሲሄድ
ያብሎስም ከሰው ፊት እየራቀ ሄደ፡፡ ጌታችን የሚቀበለው
መከራ ሁሉ ዲያብሎስን በርቀት የሚመታ መሣርያ ነበር፡፡
መጨረሻም በመስቀል ላይ የሆነው የጌታችን ሞት
የዲያብሎስ ሞት ሆነ፡፡

=>+*"+<+>አቡነ_ተክለሀይማኖት<+>+"*+

#አቡነ_ተክለሀይማኖት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::
እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፥ ጽድቅን አደረጉ፥
የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ፥ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፥ የእሳትን
ኃይል አጠፉ፥ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፥ ከድካማቸው በረቱ፥
በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ፥ የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ። ሴቶች
ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ
የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ
ተደበደቡ፤ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም
በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤ በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥
ተፈተኑ፥ በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን
እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ
ለብሰው ዞሩ፤ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥
በዋሻና በፍርኩታ በምድር ጕድጓድም ተቅበዘበዙ። ዕብ.11፡
33-40
ስለ አምላካቸውም ሲሉ ሁሉን ትተው፣ ሁሉን ንቀው
አምላካቸውን እንደተከተሉ መጽሐፍ ቅዱሳችን ያስረዳል።
ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔ ግን ነፍሱን
የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል። ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ
ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ
ቤዛ ምን ይሰጣል? የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር
ይመጣ ዘንድ አለውና፤ ያን ጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው
ያስረክበዋል።(ማቴ.16፡ 25-27
ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊትም ስለቅዱሳኑ ሲናገር፤
“እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው።” ይላል። መዝ.
67/68፡35
ስለ ጽድቅ የሚራቡና የሚጠሙ፣ እንዲሁም የሚሰደዱ ብጹዓን
ናቸው ይጠግባሉና፣ መጽናናትንም ያገኛሉና…+++ ጌታ በተራራ
ስብከቱ ከተናገራቸው፣ ካስተማራቸው የሕይወት ምግብ የሆነ
ቃሉ በማቴ.5፡1-ፍጻሜ
እግዚአብሔር አምላካችን ሰማዕታትን በደም፤ ቅዱሳንን
በገዳም፤ ሐዋርያትን በአጽናፈ ዓለም፤ መላእክትን
በአጽራርያም እንዳጸናቸው እኛ ሁላችንንም በኦርቶዶክስ
ተዋህዶ እምነታችን በቅድስት ቤተክርስቲያን በበጎ ምግባር
በጾም በጸሎትና በትሩፋት ያጽናን ስለ አባታችን ተክለሀይማኖት
ታሪክ ትንሽ ልበል
አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቡልጋ ደብረ ጽላልሽ ወይም ዞረሬ ቅዱስ
ሚካኤል ቤተክርስቲያን የሰበካ ክልል ከአባታቸው ከካህኑ ቅዱስ
ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ቅድስት እግዚእ ኃረያ መጋቢት ፳፬ ቀን
ተፀንሰው፤ በ፲፩፻፺፯ ዓ.ም ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ተወለዱ፡፡
በተወለዱ በሦስት ቀናቸው ከእናታቸው እቅፍ ወርደው «አሐዱ
አብ ቅዱስ፣አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ»
ብለው ሥላሴን አመስግነዋል፡፡ ወላጆቻቸውም ፍስሐ ጽዮን
አሏቸው፡፡ ትርጓሜውም የጽዮን ተድላዋ ደስታዋ ማለት ነው፡፡
በወላጅ አባታቸው በካህኑ ቅዱስ ጸጋ ዘአብ ግብረ ዲቁናን
ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ሲያጠኑ ቆይተው በአሥራ አምስት
ዓመታቸው ከእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቄርሎስ /
ጌርሎስ/ ዲቁናን ተቀብለዋል፡፡ በዚህም ቅድስት
ቤተክርስቲያንን በወጣትነት ዕድሜያቸው ሲያገለግሉ
ቆይተዋል፡፡
ከዕለታት በአንዱ ቀን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
ከጓደኞቻቸው ጋር ወደ ዱር አደን ሄደው ሳለ ጌታችን
አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጾ
ለኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ሐዲስ ሐዋርያ አድርጎ
መረጣቸው። ስማቸውንም «ተክለ ኃሃይማኖት» አለው፡፡
ትርጓሜውም የኃይማኖት ፍሬ ማለት ነው፡፡
አባታችንም ሐዋርያዊ ጉዟቸውን ሲጀምሩ «አቤቱ ጌታዬ
ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! የመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ
ዘንድ እነሆ ቤቴን እንደተከፈተ ተውኩልህ . . . ደካማ ለሆንኩ
ለእኔ ያለ አንተ የሚያፀናኝ የለም። ለምፍገመገም ለእኔ ያለ
አንተ ደጋፊ የለኝም። ለወደቅሁ ለእኔ ያለአንተ የሚያነሳኝ
የለም። ለአዘንኩ ለእኔ ያለአንተ የሚያረጋጋኝ የለም። ለድሀው
ለእኔ ያለ አንተ መጠጊያ የለኝም፡፡» /ገድለ ተክለ ሃይማኖት
ምዕ ፳፰ ቁ ፪ - ፫/
ይህን ብለው ትሕትና በተሞላበትና በተሰበረ ልብ ወደ
ፈጣሪያቸው ከለመኑ በኋላ በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገራት
ከኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ፣ ከክህደት ወደ ሃይማኖት
መልሰዋል፡፡ በዚህም የተነሣ ለኢትዮጵያውያን ብርሃን ፀሐይ
ተብለዋል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን ክታቡ ስለ ቅዱሳን መንፈሳዊ
ተጋድሎ ሲገልፅ:-
«እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሱ» /ዕብ. ምዕ ፲፩ ቁ
፴፫ / እንዳለ አባታችን ቅዱስ ተክለ ሃይማኖትም በመንፈሳዊ
ተጋድሎ እንዲሁም በትህትና በተአምራት አላዊ የነበረውን
ንጉሥ ሞቶሎሚን ወደ ክርስትና መልሰዋል፡፡
«ጽድቅን አደረጉ» እንዳለው አባታችን ወንጌልን በተጋድሎ
ሕይወታቸው ተርጉመዋል፡፡
«የአንበሶችን አፍ ዘጉ» ምዕ ፲፩ ቁ ፴፫ /ምዕ ፲፩ ቁ ፴፬ /
እንዳለው አባታችንም የአውሬውን ፥ የዘንዶውን ራስ
ቀጥቅጠዋል።
«ከሰይፍ ስለት አመለጡ» እንዳለው አባታችንም ሞቶሎሚ
ከወረወረው ጦር በተአምራት ድነዋል፡፡
«ከድካማቸው በረቱ» እንዳለው አባታችንም ያለ ዕረፍት በብዙ
ተጋድሎ በጾምና በስግደት በብዙ መከራ በርትተዋል፡፡
ይህን ሁሉ ገድልና ትሩፋት እየፈጸሙ ዕረፍታቸውም በደረሰ ጊዜ
ደቀመዝሙሮቻቸውን «ልጆቼ ሆይ ሁሉም መነኮስ መንግሥተ
ሰማይ ይገባል ማለት አይደለም፤ ዓለምን በሚገባ የናቀ ብቻ
ይገባል እንጂ መጀመሪያ የእግዚአብሔርን ጽድቁን ብቻ ፈልጉ፤
ጾምና ጸሎትን አዘውትሩ፤ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤
ትእዛዛቱንም አጥብቃችሁ ጠብቁ እያሉ ይመክሯቸው ነበር. . .»
በኋላም «ለዓለም ጨው ለራሴ አልጫ ሆንኩ፤ ለዓለም
ብርሃን ለራሴ ጨለማ ሆንኩ፣ ከእውነተኛው ዳኛ ከጌታዬ ፊት
ስቆም ምን እመልሳለሁ?» እያሉ በፍጹም ትህትና እና በልዩ
መንፈሳዊ ተመስጦ ይጸልዩ ነበር፡፡
በመጨረሻም አባታችን በነሐሴ ፳፬ ቀን ዕረፍታቸው ሆነ።
በዚህም መሠረት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን
ለእኚህ ዕረፍታቸው በእግዚአብሔር ፊት ለከበረና ብዙ ክብር
ለተሰጣቸው ለጻድቁ ተክለ ሃይማኖት በየዓመቱ በነሐሴ ፳፬
ቀን በዓለ ዕረፍታቸውን በታላቅ ድምቀት ታከብራለች፡፡
እኛንም ከጻድቁ ረድኤት በረከት ይክፈለን፡፡
ሰላም ለዝክረ ስምከ በጥንተ ፊደሉ መስቀል ስም ክቡር
ወስም ልዑል።
ተክለሃማኖት ማቴዎስ በዓለ ቀዳማይ ወንጌል
ከመ እወድሰከ መጠነ አውሥኦተ እክል።
ማዕሠረ ልሳንየ ትፍታሕ ማርያም ድንግል።
ትርጉም ‹‹ የስምህ መነሻ ፊደል የመስቀል ምልክት ለሆነው
እና ክቡር ገናና ለሆነው ስም አጠራርህ ሰላም እላለው ።
የወንጌል ተቀዳሚ ስም ማቴዎስ የተባልክ ተክለሃይማኖት ሆይ
እንደ ችሎታዬ አመሰግንህ ዘንድ አንደበቴ ትፈታልኝ ዘንድ
ድንግል ማርያምን እማልዳለሁ።››
የአባታችን የአቡነ ተክለሃይማኖትን ታሪክ በዘመን እየከፈልን
ባጭሩ ስንመለከተው ደግሞ፡-
የአባታችን የአቡነ ተክለሃይማኖት አባት ቅዱስ ፀጋዘአብ በሸዋ
ቡልጋ ደብረ ጽላልሽ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አገልጋይ
ካህን ነበሩ፡፡ መጋቢት 24 ቀን አባታችን ተክለሃይማኖት
ተፀነሱ በታህሣስ 24 ቀን በ1190 ዓ.ም አባታችን ጻድቁ አቡነ
ተክለሃይማኖት ከእናታቸው ከቅድስት እግዚሐሪያ እና
ከአባታቸው ከቅዱስ ፀጋዘአብ ተወለዱ፡፡ በተወለዱ በ3ኛው ቀን
አሐዱ አብ ቅዱስ፣ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ
ቅዱስ ብለው ፈጣሪያቸውን አመሠገኑ፡፡ በተወለዱ በ40ኛው
ቀን ክርስትናን በመነሳት ፍስሐ ጽዮን “የጽዮን ደስታ” ተበለው
ተጠሩ፡፡ አባታችን 7 ዓመት እስከሞላቸው ድረስ ከአባታቸው
ከፀጋዘአብ ዘንድ እየተማሩ አደጉ፡፡ አባታችን በ15 ዓመታቸው
ዲቁናን ከጌርሎስ ዘንድ ተቀበሉ፡፡ አባታችን በ22 ዓመታቸው
ከአቡነ ጌርሎስ ዘንድ ቅስናን ተቀበሉ፡፡ በከተታ አውራጃ 3
ዓመት ወንጌልን እያስተማሩ ብዙ ድንቅ ነገርን አደረጉ፡፡
አባታችን በዳዊት ፀሎት ከነቢያት ምስጋና ሌሊቱን ሙሉ ይተጉ
ነበር በያንዳንዱ መዝሙርም 10፣ 10 ስግደትን ይሰግዱ
ነበር፡፡ በሕዳር 24 ቀን ቅዱስ ሚካኤል ወደ ላይ ነጠቃቸው
(አወጣቸው) ከ24ቱ ካህናተ ሰማይ ጋር 25ኛ ካህን ሆነው
የሥላሴን መንበረን “አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ
አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ” በማለት አጥነዋል፡፡ በሐይቅ
10 ዓመት በደብረዳሞ 12 ዓመት ኖረዋል፡፡ አባታችን አቡነ
ተክለሃይማኖት በ1267 ዓ.ም ደብረ ሊባኖስን በአት አድርገው
ኖሩ፡፡ ለ22 ዓመት ቆመው በመፀለይ የአንድ እግራቸው አገዳ
ተሠበረ ደቀ መዝሙሮቻቸው በጨርቅ ጠቅልለው ቀበሩት፡፡
በአንድ እግራቸው ለ7 ዓመት በፀሎት ቆሙ በጠቅላላው ለ29
ዓመት በፀሎት ከቆሙ በኋላ በ99 ዓመት ከ10 ወር ከ10 ቀን
ነሐሴ 24 ቀን 1290 ዓ.ም አረፉ አባታችን ባረፉ 54
ዓመታቸው በ1354 ዓ.ም ለአባታችን ለአቡነ እዝቅያስ
ተገልጸው አጽማቸው ከደብረ አስቦ ወደ ደብረ ሊባኖስ ግንቦት
12 ቀን እንዲፈልስ አድርገዋል፡፡
ህዳር 24 ቀን 25ተኛ ካህናተ ሰማይ ሆነው በሠማይ የሥላሴን
መንበር ያጠኑበት
ታህሳስ 24 ቀን የአባታችን ልደት
ጥር 24 ቀን የአባታችን ስባረ አጽም
መጋቢት 24 ቀን የአባታችን ጽንሠት
ግንቦት 12 ቀን የአባታችን ፍልሰተ አጽም
ነሐሴ 24 ቀን የአባታችን እረፍት
የአባታችን ቡራኬ ይድረሰን አሜን!
“ልጆቼ ሆይ ሁሉም መነኩሴ መንግሥተ ሰማይ ይገባል ማለት
አይደለም ዓለምን በሚገባ የናቀ ብቻ ይገባል እንጂ መጀመሪያ
የእግዚአብሔርን ጽድቁን ብቻ ፈልጉ ጾምና ጸሎትን አዘውትሩ
እርስ በእርሳችሁም ተዋደዱ ትዕዛዛቱንም ጠብቁ” የሐዲስ
ኪዳኑ ሙሴ የአባታችን የተክለሃይማኖት ምክር
በደብረ አሚን ከሚገኘው ገድላቸው ደግሞ ባጭሩ፡-
የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው መ ምሳሌ 10፡ 7
የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው እንዳሉ ነቢያት እኛም ነብያትን
ሐዋርያትን ጻድቃንን ሰማእታትን አክብረን ብንቀበላቸው
በረከተ ስጋ በረከተ ነፍስ የምናገኝበት መሆኑንን በማሰብ
ከጻድቃን መካከል አንዱ የሆኑትን የቅዱስ ተክለሃይማኖት ተጋድ
ሎ በትንሹ እንመልከት::አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት ቡልጋ
ደብረ ጽላሎሽ ወይም ዞረሬ ቅዱድ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን
ክልል ከአባታቸው ከጸጋዘአብ ከእናታቸው ከእግዟእኅረያ
ታኅሣሥ 24 ተወለዱ ::በወላጅ አባታቸው በካህኑ ጸጋዘአብ
ግብረ ዲቁናን ስርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ሲያጠኑ ቆይተው
ቄርሎስ ከተባሉት ግብጻዊ ጳጳስ በ15 አመታቸው ዲቁናን
ተቀበሉ::እንዲሁም እድሜያቸው 22 አመት ሲሆን ከላይ
ስማቸው ከተገለጹት ጳጳስ የቅስናን ማዕረግ ተቀበሉ ከዚህ
በኋላ ለህዝቡ ወንጌል እየሰበኩ ጣዖት አጋንንትን እያደቀቁ
ህዝቡን አምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር
መልሰው አባኢየሱስ ሞዓ ወደ ሚገኙበት ገዳም ሐይቅ
እስጢፋኖስ በቅዱስ ሚካኤል መሪነት ሃይቁን በእግራቸው እንደ
ደረቅ መሬት በመርገጥ ወደ ደሴቱ በመግባት የምንኩስናን
በመቀጠል ከአባ ኢየሱስ ሞዓ እጅም የምንኩስናን ቀሚስ
የንጽህናን ምልክት ተቀብለው ለ12 ዓመታት አቡነ አረጋዊ
ወዳቀኑበት ገዳም ደብረ ዳሞ በመግባት በጊዜው ከነበሩት
አበምኔት ከአባ ዮሐኒ ቆብና አስኬማ ተቀብለው በገድል
በቱሩፋት መንፈሳዊ ተጋድሎዋቸውን ቀጠሉ::ከዚህ ሁሉ በኋላ
በደብረ ሊባኖስ ካለችው ገዳመ አስቦ ዋሻ በመግባት ስምንት
ጦሮችን ሁለቱን በፊት ሁለቱን በኋላ ሁለቱን በቀኝ ሁለቱን
በግራ አስተክለው እጆቻቸውን በትምህርተ መስቀል አምሳል
በመዘርጋት የክርስቶስን ህማምና ሞት ነገረ መስቀሉን
በማሰብ በተመስጦ ሌትና ቀን ያለ ማቋረጥ በጾም በጸሎት
በአርምሞ ተወስነው ሲጋደሉ ከቁመት ብዛት የተነሳ ጥር 24
ቀን የእግራቸው አገዳ ተሰብራለች እግራቸው እስኪሰበር
በጸሎት የቆዩባቸው አመታት 22 ናቸው ::በመአልትና በሌሊት
በትጋትና በቁመት በተጋድሎ ብዛት አንዲት የእግራቸው አገዳ
ስትሰበር ዕድሜያቸው 92 አመት ሆኖ ነበር::ከዚህ በኋላ ለ7
አመታት በአንድ እግራቸው ብቻ በመቆም ያለ ምግብ ሌትም
ቀን ምእንቅልፍ በአይናቸው ሳይዞር እንደ ምሰሶ ጸንተው
በተመስጦ በትጋት ለሰው ዘር ሁሉ ድኅነት ሲለምኑ ኖረዋል
::በመጨረሻም አባታችን በነሐሴ ፳፬ ቀን ዕረፍታቸው ሆነ::
የአባታችን የአቡነ ተክለ ሀይማኖት ምልጃና ጸሎታቸው
ረድዔትና በረከታቸው በኛ በልጆቻቸው ላይ ይደርብን አሜን!
ምንጭ ታምረ ተክለሐይማኖት ዘደብረ አሚን
የእግዚአብሔር፣ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት፣
የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣
የቅዱሳን ሐዋርያት፣ የቅዱሳን አበው መነኮሳት፣ የቅዱሳት
አንስት፣ የደናግላንና የቅዱሳን ሁሉ ምልጃና ቃል-ኪዳናቸው
ባለንበት ከሁላችን ጋር
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ
ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡