ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

Monday, February 20, 2017

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ: =>+*"+<+>†† ዘወረደ /ዘመነ አዳም/- ††

ዘወረደ /ዘመነ አዳም/
የዐቢይ ጾም የመጀመሪያ ሳምንት ዘወረደ: ሙሴኒ:ሕርቃል
ይባላል፡፡ ዘወረደ ማለት፣ ከላይ የመጣ፣ የወረደ ማለት ነው፡፡
ይህም የአምላካችን ሰው መሆን ያመለክታል፡፡ ከሰማይ
ከወረደው በቀር ወደሰማይ የወጣ የለም ካለው ከጌታችን
ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ቃል በመነሳት ሊቁ ቅዱስ
ያሬድ በዚህ ዕለት ምስባክ “ዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ
ወሚመ ኢያእመሩ እግዚአ ኩሉ ዘየሐዩ በቃሉ” በማለት
በጾመ ድጓው መጀመሪያ ላይ ገልጾት ይገኛል፡፡
አዳምን ለማዳን ከሰማይ የወረደውን አይሁድ ሰቀሉት፣
የሰማይን ሥልጣን ያለው የሁሉ ጌታ እንደሆነም ምንም
አላወቁም ብሎ ተናግሮ ነበር፡፡ ይህም ድርሰት በቤተ
ክርስቲያናችን የጾም መጀመሪያ የሆነው ዕለተ ሰንበት
ዋዜማ፣ መግቢያ፣ /መሐትው/ ሆኖ ከዋዜማ በፊት
ምንጊዜም በየዓመቱ ይቆማል፡፡ ይዘመራል፡፡ ይመሰገናል
ማለት ነው፡፡
ስለዚህ የሳምንቱ ስያሜ ከዚህ የተወሰደ ነው፡፡ እንዲሁም
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራውን
የጀመረው፤ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ሰው በመሆን ፣
በዮርዳኖስ ተጠምቆ በማስተማር እንደሆነ ሁሉ የመጀሪያው
ሳምንት ዘወረደ ይባላል፡፡
በዚህ ሳምንት በተለይም እሑድና ሰኞ የሚነገሩት ውዳሴያት
ከመጻሕፍተ ኦሪትና ነቢያት የተወሰዱ ናቸው፡፡ ሁለተኛም
ሙሴኒ በመባል ይታወቃል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ አዳምን
ለማዳን ከሰማይ መውረዱንና በመስቀል መሰቀሉን
ስለሚያወሳ ነው፡፡
በተጨማሪም ይህ የመጀመሪያው ሳምንት ጾመ ሕርቃል
ይባላል፡፡ በ714 ዓ.ም.ሕርቃል /ኤራቅሊየስ/ የቤዛንታይን
ንጉሥ ነበረ፡፡ይህ ሳምንት በስሙ የተጠራበት ምክንያት
በዘመኑ ፋርሶች ኢየሩሳሌምን ወርረው የጌታችን መስቀል
ማርከው ወስደው ነበር፡፡ እርሱ ወደፋርስ ዘመቶ መስቀሉን
ከእነርሱ ነጥቆ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሷል፡፡
ሕርቃል ከፋርሶች ጋር ከመዋጋቱ በፊት ሐዋርያት
በሲኖዶሳቸው ነፍስ የገደለ ሰው እስከ እድሜ ልኩ ይጹም
ብለው ሥርዓት ሠርተዋልና ጾሙን ፈርቶ ስለነበር
በኢየሩሳሌም የነበሩ ምእመናን አሳቡን ደግፈው “አንተ
ጠላታችንን አጥፋልን ፣መስቀሉን አስመልስልን እንጂ የአንድ
ሰው እድሜ ቢበዛ ሰባ ሰማንያ ነው ፡፡ጾሙንአምስት አምስት
ቀን ተከፋፍለን እኛ ተከፋፍለን እንጾምልሃለን፡፡”ብለው
ጾመውለታል፡፡
ይህንን መሠረት በማድረግ ያላወቁት አንድ ጊዜ ጾመው
ትተውታል፡፡ ያወቁት ግን ቀድሞም ሐዋርያት ጾመውታል
ብለው ሥርዓት አድርገው በዓመት በዐቢይ ጾም መጀመሪያ
ላይ ጾመ ሕርቃል እያሉ የሚጾሙት ሆነዋል፡፡ስለዚህ
ቤተክርስቲያናችን ይህንን መሠረት በማድረግ በጌታችን
ከመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጾም የመጀመሪያውን
ሳምንት ጾመ ሕርቃል በሚል ስያሜ ሰማይ እንዲጾም
አድርጋለች፡፡ /መጋቢት 10 ስንክሳር ይመልከቱ፡፡/
የቤተ ክርስቲያናችን ታሉቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ፣ በዘወረደ ጾመ
ድጓው ሰንበት ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን፣ ሕይወት ላለው
ነገር ሁሉ ጸጥታና ሰላም የሰፈነባት የዕረፍት ቀን ስለመሆኗ
“አዘዞ እግዚአብሔር ለሙሴ ወይቤሎ ሰብዕከ ወላህምከ
ወኲሉ ቤትከ ያዕርፍ በሰንበት” ዘፀ.20፥10፣23፣12፣ ጾመ
ድጓ፣ እግዚአብሔር ሙሴን ሕዝብህ የከብትህ መንጋህ
ቤተሰብህ ሀሉ በሰንበት ቀን ከድካማቸው ይረፉ በማለት
አዘዘው ይላል፡፡ በዚህም ዘመነ ጾም፣ ወይም ጾመ ሙሴ
ይባላል፡፡
በጾመ ድጓው ዘወረደ እየተባለ የሚታወቀው፣ በጾመ አርባው
ወቅት በተለይም በመጀመሪያው ሳምንት የሚገኘው ያሬዳዊ
ድርሰት በነግህ በሠለስት፣ በቀትርና በሠርክ እንዲሁም
ቅዳሜና እዡድ በሌሊት የሚዘመር ነው፡፡ በውስጡም
የያዘው ፍሬ አሳብ፣ የጾምን፣ የጸሎትን፣ የምጽዋትንና
የፍቅርን ጠቃሚነት አጉልቶ የሚያስተምር ነው፡፡
በዚህ በጾም ወቅት በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት በአብዛኛው
ከቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች ውስጥ የሚዘመረው ምዕራፍ
የተባለው ነው፡፡ ምዕራፍ የተባለበት ምክንያትም
በየመዝሙራቱ መሀል ሃሌታና ድጓ እያስገባ ለመዝሙሩ
ማረፊያ ስላበጀለት በዚህ ምክንያት ምዕራፍ የሚል ስያሜ
ሊያገኝ ችሏል፡፡ ይህ የዜማ መጽሐፍ በሁለት ታላላቅ ክፍሎች
ይከፈላል፡፡ ይኸውም የዘወትር ምዕራፍና የጾም ምዕራፍ
በመባል ይታወቃል፡፡የዘውትር ምዕራፍ የሚባለው በዓመቱ
ውስጥ ባሉት ቀናት ውስጥ ሳምንታትና በዓላት ሁልጊዜ
በአገልግሎት ላይ የሚውል ሲሆን፣ የጾም ምዕራፍ የሚባለው
ደግሞ በጾመ አርባ ብቻ ለአገልግሎት የሚውል ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በዐሥሩ ምህላት አርዕስተ ምህላ በዚሁ
ክፍል ይካተታል፡፡ የምዕራፍ ቅንብር ከመዝሙረ ዳዊት፣
ከድጓና ከጾመ ድጓ ጋር የተቀናጀ ነው፡፡ የትምህርት
አሰጣጡም እንደ ድጓው ወይም እንደ ዝማሬ መዋሥዕቱ
መጽሐፍ ተዘርግቶ ሳይሆን በቃል የሚጠናና የሚወሰን ነው፡፡
ስለሆነም ምዕራፍን ለመማር 150 መዝሙረ ዳዊትን፣
ከነቢያት 15 ምዕራፎችንና 5 መኃልያተ ሰሎሞንን በቃል
ሸምድዶ መያዝ ይጠበቅበታል፡፡ ወይም ግድ ነው፡፡
ጾምን መጾም የፈቃድ ብቻ ሳይሆን የትእዛዝም ነው፡፡
በዘመነ ብሉይ ነቢዩ ኢዩኤል “ቀድሱ ጾመ ወስብኩ ምህላ”
ጾምን ያዙ አጽኑ ምሕላንም ዐውጁ ሸማግሌዎቹን
ከፈጣሪያችን ቤት ሰብስባችሁ በአንድነት ሁናችሁ ወደ
እግዚአብሔር ጩሁ /ለምኑ/ ብሏል፡፡ ኢዮ.ምዕ.1፥11፣
2፣12፣15-16 ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ወኲኑ ላዕካነ፣
ለእግዚአብሔር በጾም ወበንጽሕ፡፡ በጾም፣ በንጽሐና
ተወስናችሁ እግዚአብሔርን አገልግሉ ብሏል 2ቆሮ.6፥4-6፡፡
ጾም ከሌለ ወይም ተገቢ ካልሆነ ጌታችን በምትጾሙበት ጊዜ
እንደ ግብዞች አትሁኑ ስለ ጽድቅ የሚራቡ የሚጠሙ ንዑዳን
ክብራን ናቸው ለምን አለ? ማቴ.5፥፣6፣16፡፡ ነቢዩ ዳዊትም
ሰውነቴን በጾም አሳመምኳት በቀጠና፣ በሰልት አደከምኳት
ለምን አለ መዝ.34፥68፣ ት.ዳን. 9፥3-4፣ 14፥5
ነብዩ ሚኪያስ ሐዋርያት ሙሸራውን ከነሱ ለይተው
የሚወስዱበት ጊዜ ይመጣል ያን ጊዜ ይጾማሉ ያለውን የጌታን
ቃል መሠረት በማድረግ ክርስቶስ በሞት ከተለያቸው በኋላ
ጾመዋል፡፡ ጾምንም ሠርተዋል የሐዋ.ሥራ 13፥3፡፡ ሠለስቱ
ምዕትም ሐዋርያት የጾሙትንና እንዲጾም የወሰኑትን መጾም
ይገባል ብለው ቤተ ክርስቲያን የተቀበለቻቸውን አጽዋማት
እንዲጾሙ መወሰናቸው ይህን የጌታ ቃል መሠረት በማድረግ
ስለሆነ፣ የትእዛዝ መሆኑን ተገንዝበን መጾም አለብን፡፡
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሠራዔ ሕግ
እንደመሆኑ አርባ ቀን አርቦ ሌሊት ጾመ እንጂ እርሱ ሳይጾም
ጾሙ አላለንም ማቴ.4፥2፡፡ ጾመን ለማበርከት ያብቃን፡፡
አሜን!

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ: =>+*"+<+>†† የዐቢይ ጾም የመጀመሪያው ሳምንት ዘወረደ ††

. ዘወረደ ወይም ሕርቃል ወይምሙሴኒ
✔ የዐቢይ ጾም የመጀመሪያው ሳምንት ዘወረደ ይባላል፡፡
‹‹ዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ›› የሚልና ይህንን
የመሳሰለ ጌታ እኛን ለማዳንና ፍቅሩን ሊገልጽልን ከሰማያት
መውረዱን ከድንግል ማርያም የእኛን ሥጋ መዋሐዱን
የሚያዘክር ምስጋና የሚቀርብበት ሳምንት ነው፡፡
✔ ሌላም ስም አለው ጾመ ሕርቃል ይባላል፡፡ ይህ ጾም
የጾም መግቢያ የመጀመሪያ ሳምንት የምንጾመው ጾም
ሲሆን ሕርቃል የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡
✔ ሕርቃል ማን ነው? ለምንስ በስሙ ተሰየመ? በ614
ዓ.ም ኪርዮስ የተባለ የፋርስ ንጉሥ ኢየሩሳሌምን በመውረር
ጥቃት አደረሰ፡፡
✔ በዚህ ወቅት በኢየሩሳሌም ንግሥት ዕሌኒ በሠራችው
ቤተመቅደስ ውስጥ ሲገባ ንግሥቷ በክብር አስቀምጣው
የነበረው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል
እንደ ፀሐይ ሲያበራ አገኘው፡፡
✔ ቢነካው አቃጠለው ዲያቆናቱን አሸክሞ ሌላውን ንዋየ
ቅድሳት ዘርፎ 60ሺ የሚደርሱትን አቁስሎ ገድሎ 3ሺ
የሚሆኑትን ማርኮ ከተማዋንም አቃጥሎ ወደ ፋርስ ባቢሎን
ይመለሳል፡፡
✔ በዚህ ጊዜ ከጦርነቱ ያመለጡ በየዋሻው በየጉራንጉሩ
ገብተው የተሸሸጉ ተሰብስበው ከ14 ዓመት በኋላ በ628
ጩኸታቸውንና የደረሰባቸውን በደል ለክርስቲየኑ የሮም
ንጉሥ ሕርቃል ይነግሩታል፡፡
✔ እርሱም ሐዋርያት ሰውን የገደለ እድሜውን በሙሉ
ይጹም ስላሉ እንዴት ላድርገው አላቸው እኛ የአንተን እድሜ
ተከፋፍለን እንጾማለን ብለው አንድ አንድ ሳምንት ደርሷቸው
ጾሙን በሚገባ ጾመውታል፡፡
✔ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልና የተማረኩ
ክርስቲያኖችን ለመመለስ ሕርቃል ጦር መዝዞ በኪርዮስ ላይ
ተነሳበት ድል ለሕርቃል ሆነና መስቀሉን ያለበትን አጥቶ
ሲቸገር መስቀሉን ሲቀብርና ዲያቆናቱን ሲያስገድል በመስኮት
ሆና ያየችው ከኢየሩሳሌም የተማረከች አንዲት ብላቴና
አሳይታው አውጥቶ በልብሰ መንግሥቱ ጠቅልሎ ወደ
ቁስጥንጥንያ ተመለሰ፡፡
✔ የተማረኩት በሙሉ ነጻ ወጡ ይህን ለማሰብ ለማስታወስ
በተጨማሪ በኃጢአት ላይ ድል እንድናገኝ መንፈሳዊ ጦር
በውስጣችን እንዲበዛልን መስቀልህ ከምርኮ እንደተመለሰ
እኛንም ከኃጢአት ምርኮ መልሰን ለሕርቃል ድል መንሳትንና
በጠላቶቹ ላይ ኃይልን እንደሰጠኸው ለእኛም በኃጢአት ላይ
ድል መንሳት መንፈሳዊ ኃይልን ስጠን እያልን እንጾመዋለን፡፡
✔ በጌታ ጾም ላይ እንዲጾም የሆነበት ምክንያት ጾሙ
የጌታ ጾም በሚጾምበት ወቅት ላይ ስለተጾመ
ቤተክርስቲያናችን አብራ ደንግጋዋለች፡፡
✔ እዚህ ላይ በዚያን ጊዜ ለሕርቃል ሕዝቡ ሱባኤ
ይዞለታል፡፡ ዛሬም እኛ ለቤተክርስቲያን ያደረግነውን በማሰብ
እግዚአብሔር አምላክ ለሕርቃል የሰጠውን በጠላቶቹ ላይ
ድል መንሳትን ለእኛም እንዲሰጠን የምንጠይቅበት ስለሆነ
የመጀመሪያውን ሳምንት በሕርቃል ሰይመን ጾሙን
እንጾማለን፡፡
✔ የእኛ ጠላት የጨለማ ገዥ የሆነው ዲያቢሎስ ነውና
እሱን ደግሞ በጾም እንደምናሸንፈው ጌታችን መድኃኒታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮናል፡፡
✔ «ዘወረደ» ማለትም በቀጥታ፣ ቃል በቃል ሲተረጐም
«የወረደ» ማለት ነው፡፡ ይህም በምስጢሩ አምላክ ወልደ
አምላክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤዛ ዓለም በቅዱስ ፈቃዱ
ሰው ሆኖ ከሰማየ ሰማያት = ከባሕርይ ልዕልናው በትሕትና
ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱን የሚያመላክት፣
ይህም የሚታወስበት፣ የሚወሳበት የዐቢይ ጾም አንደኛው
ሳምንት ነው፡፡ 《ዮሐ.3-13》፡፡
✔ ሳምንቱ ሙሴኒ የተባለበትም ምክንያት በዚሁ ሳምንት
መጀመሪያ የሰኞ ዕዝል «ከመዝ ይቤ ሙሴ ፀዓቱ
እምትእይንት» «ሙሴ ከከተማ መውጣቱ እንደዚህ ነው አለ»
ስለሚል እንደዚሁም የዚሁ ዕለት ማለት የሰኞ አቡን «ሙሴኒ
ይቤ በውስተ ኦሪት ምድር ሰናይት» እያለ የሙሴን ታሪክ
ስለሚያጠቃቅስ ሳምንቱ ሙሴኒ ተባለ፡፡
✔ ነቢያትም አርባ አርባ ቀን ጾመው ከአለፉ በኋላ የሙሴ
ሕግና ትንቢተ ነቢያት ፈጻሚ የሆነው ምላካችን እንደ እነሱ
40 ቀንና 40 ሌሊት መጾሙን የሚያስታውስ ነው፡፡
《ዘፀ.24-18》፤ 《1ኛ.ነገ.19-8》፤ 《ማቴ. 4-1-4》፡፡
↪ ወስብሐት ለእግዚአብሔር
↪ ምንጭ፡- ጾምና ምጽዋት