ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

Tuesday, September 13, 2016

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ: =>+*"+<+>††† መስከረም 2-መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ †††<+>+"*

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
አሜን
መስከረም 2-መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በሰማዕትነት
ያረፈበት
ዕለት ነው፡፡ ይኸውም ጌታችን አስቀድሞ "በመወለዱም
ብዙዎች ደስ
ይላቸዋል" (ሉቃ1:14) በማለት የመጥምቁ መወለድ ለእኛ
የደስታ
ቀናችን መሆኑን ነግሮናል፡፡ ዳግመኛም ጌታችን የመጥምቁን
ክብር
ሲገልጥለት "እውነት እላችኋለሁ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል
ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ ማንም የለም" በማለት
መስክሮለታል፡፡
ማቴ 11:11፣ ሉቃ 7:28፡፡ በዚህም መሠረት ቅዱስ ገድሉ
ላይ
እንደተጠቀሰው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ
ለመጥምቁ ዮሐንስ ዓሥር እጅግ አስደናቂ ቃል የድኅነት
ኪዳኖችን
እንደገባለት ከቅዱስ ገድሉ ላይ ያገኘነውን ቀጥሎ
እንናገራለን፡-
ገድለ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ (በጎል ሰከበ ደብረ መንክራት
ሚጣቅ
ቅዱስ አማኑኤል ማኅበረ ሰላም አንድነት ገዳም
ያሳተመው-2003
ዓ.ም)
‹‹እግዚአብሔር ወደ በራክይ ልጅ ወደ ዘካርያስ ልጅ
እንደሚወልድ
ይነግረው ዘንድ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤልን ላከው፡፡
እርሱም
በመሠዊያው በስተቀኝ በኩል ተገልጦ ለዘካርያስ ታየው፡፡
ለሰይጣን ቀኝ
የለውምና መልአክ ግን ብርሃናዊ የማናዊ ነውና መልአክ
እንደሆነ
ለማጠየቅ በቀኝ በኩል ተገልጦ ታየው፡፡ አንድም ሰው ሁሉ
ወደ የማናዊ
ግብር የሚመለስበት ዘመን ደረሰ ሲል በቀኝ በኩል ታየው፡፡
አንድም
ሰውን ሁሉ መክሮ አስተምሮ ወደ ቀኝ ወደ መንፈስ ቅዱስ
ሥራ
የሚመልስ ልጅ ትወልዳለህ ሲለው በቀኝ በኩል ተገልጦ
ታየው፡፡››
የእግዚአብሔርን ስጦታ በልብ ብቻ በድብቅ መያዝ
እንደሚገባ፡-
‹‹የአካባቢዋ ሰዎችም ሁሉ መካን በመሆኗ አልሳቤጥን ‹ጡተ
ደረቅ፣
ማኅፀንሽም የተዘጋ፣ በረከትን ያጣሽ፣ መርገምንም
የተመላሽ፣ የበቅሎ
ዘመድ፣ ቢወልዷት እንጂ አትወልድ…› እያሉ ይሰድቧት ነበር፡፡
አልሳቤጥም ‹በዚህ ወራት መፀነሷን ባወቀች ጊዜ ስድቤን
ሁሉ ከሰው
ያርቅልኝ ዘንድ እግዚአብሔር በረድኤት በጎበኘኝ ጊዜ እንዲህ
አደረገኝን!› ብላ አምስት ወር ፅንሷን ሠወረች (ለማንም
አልተናገረችም)፡፡ እነርሱም ‹ይህቺ ሴት የበላችው ቂጣ
ቢነፋት ፀነስኩ
ትላለች› ብለው ቢሰድቧት እንጂ ሌላ ረብ (ጥቅም)
ባልነበረው ነበር፡፡
ኤልሳቤጥም ስድስት ወር በሆናት ጊዜ መልአኩ ለቅድስት
ድንግል
ማርያም አምላክን እንደምትወልድ አበሰራት፡፡ ድንግል
ማርያምም
መልአኩ ስለ ኤልሳቤጥ መፀነስ የነገራትን ለማረጋገጥ ወደ
እርሷ
ሄደች፡፡ እመቤታችንም ‹እንዴት ነሽ?› ስትላት ኤልሳቤጥ
በሰማች ጊዜ
በማኅፀኗ ያለው ፅንስ በደስታ ሰገደ፡፡››
መንፈስ ቅዱስ የተለየው ሰው የክርስቶስን አምላክነትና
የድንግል
ማርያምን አማላጅነት ማወቅ አይችልም፡- ‹‹ኤልሳቤጥም
‹እንዴት ነሽ?›
ስትላት የእመቤታችንን ድምፅ በሰማች ጊዜ የፈጠረው
አምላክ
በማርያም ማኅፀን ውስጥ መኖሩን አወቀ፡፡ የዓለሙ
መድኃኒት ፈጣሪው
በድንግል ማርያም ማኅፀን ውስጥ መኖሩን ለማየት
የመጥምቀ መለኮት
ቅዱስ ዮሐንስ ዐይኖች በመንፈስ ቅዱስ ፀጋ በእናቱ ማኅፀን
ውስጥ
የተገለጡ ሆኑ፡፡ የሁለቱም የማኅፀን መጋረጃዎች ሳይገለጡ
ፈጣሪውን
ለማየት የዮሐንስ ዐይኖች በመንፈስ ቅዱስ ፀጋ ተገልጠው
እንደ
መስታዎት ሆኑለት፡፡ የሁለቱም የማኅፀን መጋረጃዎች
ፈጣሪውን ለማየት
የዮሐንስ ዐይኖች አልከለከሉትም፡፡ መልአኩ ለአባቱ
ለዘካርያስ ‹ከእናቱ
ማኅፀን ጀምሮ መንፈስ ቅዱስን የተመላ ይሆናልና› ብሎ
እንደነገረው
በእናቱ ማኅፀን ሆኖ በማርያም ማኅፀን ውስጥ ያለውን
ፈጣሪውን
አየው፡፡ ፈጣሪውንም ለመቀበል ሰገደለት፣ እንደ እንቦሳ
ጥጃም በደስታ
ፈንድቆ ዘለለ፡፡ በእርሱ ላይም የመላው መንፈስ ቅዱስ
በኤልሳቤጥም
ላይ መላባትና እንዲህ ብላ ተናረች፡- ‹ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ
አንቺ
የተባረክሽ ነሽ፣ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው፡፡ የጌታዬ
እናት ወደ እኔ
ትመጪ ዘንድ እኔ ምንድነኝ?› አለቻት፡፡››
መጥምቁ ዮሐንስ ምግቡ የበረሃ አንበጣ ነበር›› የሚለው
አነጋገር
ስሕተት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በተለምዶ ሲነገር እንደምንሰማው
መጥምቁ
ዮሐንስ የበረሃ አንበጣ እየተመገበ ይኖር ነበር ይባላል፡፡ ነገር
ግን ቅዱስ
ገድሉ የሚናገረው ቅዱስ ዮሐንስ ይመገብ የነበረው ‹‹የበረሃ
አንበጣ››
ሳይሆን ‹‹አንቦጣ›› ተብላ የምትጠራ አንዲት የበረሃ
ቅጠልንና የጣዝማ
ማርን እንደነበር ነው፡፡ ቅዱስ ገድሉ ላይ የተጻፈውን እንይ፡-
‹‹ዮሐንስና
እናቱ ኤልሳቤጥ ወደ በረሃ ከገቡ አምስት ዓመት በሆናቸው
ጊዜ እርሱ
ዕድሜው ሰባት ዓመት ከመንፈቅ ከሆነው በኋላ እናቱ
ኤልሳቤጥ
ሞተችበትና ብቻውን ከበረሃ ውስጥ ተወችው፡፡ ዮሐንስም
በሰፊዋ በረሃ
ውስጥ በአራዊቶች መካክል ብቻውን ቀረ፡፡ ለዮሐንስ ግን
በእርሱ ላይ
ምንም መጥፎ ነገር ሳያደርጉ የቶራና የአንበሳ፣ የነብርም
ልጆች እንደ
ወንድምና እንደ እኅት ሆኑት፡፡ አራዊቶችም ሁሉ ወዳጅ ሆኑት
እንጂ፡፡
ምግቡም የበረሃ ቅጠል ነው፤ መጠጡም ከተቀመጠባት
ድንጋይ ሥር
የምትፈልቀው ውኃ ነበረች፡፡ ዮሐንስ ሰውነትን
አለምልመው፣ ሥጋን
አለስልሰው፣ ገጽንና ፊትን የሚያሳምሩትን የበረሃ
ቅጠሎችንም
አልተመገበም፡፡ አንቦጣ ከተባለችው ከአንዲት የበረሃ ቅጠልና
ከጣዝማ
ማር በስተቀር ከሚበሉት ምግቦች ሁሉ ዮሐንስ ሕርምተኛ
ሆኖ የተለየ
ነበር›› ይላል ቅዱስ ገድሉ፡፡ እስመ ሕሩም ውእቱ ዮሐንስ
እምኲሉ
መባልዕት ዘእንበለ አሐቲ ዕፅ እንተ ይእቲ አንቦጣ ወመዐረ
ጸደንያ
ባሕቲቱ እንዲል መጽሐፍ፡፡
ዮሐንስ ጌታችንን ሲያጠምቀው ሁለቱ ምን ብለው
እንደተነጋገሩ፡-
‹‹በዚያን ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ
በዮርዳኖስ ወንዝ
ያጠምቀው ዘንድ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወደ ዮሐንስ መጣ፡፡
ዮሐንስም
በእርሱ ላይ አድሮበት ባለው በመንፈስ ቅዱስ ፀጋ ጌታችን ወደ
እርሱ
ሲመጣ ባየው ጊዜ አሰምቶ ጮኸ፤ በታላቅ ቃልም እንዲህ
አለ፡- ‹እኛን
ለማዳን የመጣው የእግዚአብሔር በግ እነሆ፡፡ ነቢያትም ስለ
እርሱ
ትንቢት የተናገሩለት ንጉሠ ነገሥት ይህ ነው፡፡ በዕውነት
ቀዳሚና ተከታይ
የሌለውና ለመንግሥቱም ፍጻሜ የሌለው አምላክ ይህ ነው፡፡›
ዮሐንስም
ይህን ቃል እየተናገረ ሳለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጠርቶ
እንዲህ
አለው፡- ‹ዮሐንስ ሆይ! ስለ እኔ የተጻፈውን ሕግ ሁሉ ትፈጽም
ዘንድ እነሆ
ይገባሃል፤ እነሆ በአየኸው ሁሉ ምስክር ትሆን ዘንድ በአንተ
እጅ
የምጠመቅበት ጊዜ ስለደረሰ አጥምቀኝ› አለው፡፡ ዮሐንስም
ለጌታችን
እንዲህ ብሎ መለሰለት፡- ‹ወደ አንተ መጥቼ መጠመቅ ለእኔ
ይገባኛል
እንጂ እኔ ባሪያህ ሆኜ ሳለሁ በእኔ እጅ ትጠመቅ ዘንድ
ስለምን ወደ እኔ
መጣህ? አንተ ጌታ ሆነህ ይህ ነገር ፈጽሞ አይገባም› አለው፡፡
ጌታችንም ‹ዮሐንስ ሆይ! በአንተ እጅ ስለመጠመቄ ደስ
መሰኘት
ይገባሃል፤ አትፍራም፡፡ አንተ እጅህን በራሴ ላይ ታኖራለህ፤
ሰውነቴንም
እኔ አጠምቃታለሁ፡፡ ዮሐንስ ሆይ! እንቢ አትበለኝ እነሆ
ነቢያት ስለ እኔ
የተናገሩትን ሕግና ትእዛዝን ሁሉ ልፈጽም መጥቻሁና›
አለው፡፡ ጌታችንም
ይህን ቃል ለዮሐንስ ነግሮት ከጨረሰ በኋላ ወደ ዮርዳኖስ
ውኃ ውስጥ
ገባ፡፡ ያንጊዜ ዮርዳኖስ አርባ ክንድ ወደኋላው ተመለልሶ ሸሸ፣
ውኃውም
በእሳት እንዳፈሉት ሆነ፡፡ በጸናችው የጥበቡ ኃይል አዳምን
ከነልጆቹ
ለማዳን ወደዚህ ዓለም ከመጣው ከጌታችን ፊት ዮርዳኖስ ስለ
መሸሿና
ወደ ኋላዋ ስለ መመለሷ ነቢዩ ዳዊት ትንቢት ተናግሮአል፡-
‹አቤቱ
ውኆች አዩህ፣ ውኆችም አይተውህ ፈሩ፡፡› አንቺ ባሕር
የሸሸሽው፣ አንቺ
ዮርዳኖስ ወደ ኋላ የተመለሽው ምን ሆናችኋል? ጌታችንም
ዮርዳኖስን
እንዲህ በማለት ገሠፀው፡- ‹ዮርዳኖስ ሆይ! በጥምቀቴ ጊዜ
አትሽሽ፣
ባለህበት ቦታም ተመልሰህ ቁም› አለው፡፡ ጌታችንም ይህን
ቃል
በተናገረው ጊዜ የነቢዩ ዳዊት ትንቢት ይደርስ ዘንድ ውኃው
ወደ ቦታው
ተመልሶ ቆመ፤ ከጌታችንም ፊት ሰገደ፡፡ ዮሐንስም ዮርዳኖስ
ወደ ኋላዋ
ተመልሳ መሸሿንና በጌታችን ትእዛዝ ወደ ቀድሞ ቦታዋ
ተመልሳ
ከጌታችን ፊት ስትሰግድ ባየና በተመለከተ ጊዜ ፈራ፣ ደነገጠ፣
ታላቅ
መንቀጥቀጥም አደረበት፣ በፊቱም ሰገደለት፡፡ ‹እነሆ አንተ
ጌታዬና
ፈጣሪዬና ነህ እኔ አገልጋይህ ባሪያህ ነኝ፣ አቤቱ ጌታዬ ሆይ!
ይህን ሁሉ
ደካማነቴን ተመልክተህ እጁን በራስህ ላይ ያኖር ዘንድ
ባሪያህን
አታስገድደው› አለው፡፡ ጌታችንም ለዮሐንስ እንዲህ አለው፡-
‹ይህ ለእኛ
ተድላ ደስታ ነውና እውነትን ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና
ያዘዝኩህን
አድርግ› አለው፡፡ ‹አንተም መጥምቀ መለኮት ተብለህ
ክብርህ
ይነገራልና እኔም በባሪያው እጅ ተጠመቀ ተብዬ ትሕትናዬ
ይነገራልና›
አለው፡፡ ይህንንም ሲናገረው ዮሐንስ ተወው፡፡ ዮሐንስም
እንዲህ
አለው፡- ‹የአብ ስም በአንተው አለ፣ የወልድ ስም አንተው
ነህ፣ የመንፈስ
ቅዱስም ስም በአንተው ሕልው ሆኖ አለ፡፡ ሌላውን በአንተ
ስም
አጠምቃለሁ፣ አንተን ግን በማን ስም አጠምቃለሁ?›
አለው፡፡ ጌታም
ዮሐንስን እንዲህ እያልክ አጥምቀኝ አለው፡- ‹እንደ
መልከጼዴቅ ሹመት
የዓለሙ ካህን፣ ብርሃንን የምትገልጽ፣ የአብ የባሕርይ ልጅ፣
አቤቱ ይቅር
በለን፣ የዓለምን ኃጢአት የምታስወግደው የእግዚአብሔር በግ
ይቅር
በለን እያልክ አጥምቀኝ› አለው፡፡ ያንጊዜ ዮሐንስ ጌታችን
ኢየሱስ
ክርስቶስን ጥር ዐሥራ አንድ ቀን ከሌሊቱ በአሥር ሰዓት
አጠመቀው፡፡››
አስቀድሞ መሐላ መማል ፈጽሞ ተገቢ እንደልሆነ፡-
‹‹የሄሮድያዳ ልጅ
ንጉሥ ሄሮድስን በዘፈኗ በጣም አድርጋ ስላስደሰተችው
እርሱም በተራው
ሊያስደስታት ፈለገ፡፡ ‹እስከ መንግሥቱ እኩሌታ ድረስም
ቢሆን
የለመነችውን ይሰጣት ዘንድ በሕዝቦቹና በመኳንንቱ ሁሉ ፊት
እንዳይከዳት በፅኑ ቃልኪዳን ማለላት፡፡› እንዲህም እያለ
‹የፈለግሽውን
ጠይቂኝ፣ የመንግሥቴንም እኩሌታ ቢሆን እሰጥሻለሁ ምን
ላድርግልሽ?›
እያለ በመሐላ ባላት ጊዜ በእናቷ ምክር የዮሐንስን አንገት
ቆርጦ
ይሰጣት ዘንድ ለመነችው፡፡ ንጉሥ ሄሮድስም ይህን ልመና
ከአፏ በሰማ
ጊዜ ‹የፈለግሽውን እሰጥሻለሁ› ብሎ በሕዝቡ ፊት ስለማለ
ለሰው
ይምሰል አዘነ፣ ተከዘ፡፡ ኃዘኑም ስለ ዮሐንስ መሞት
አይደለም፣ ዮሐንስን
ሕዝቡ ይወደው ስለነበር እነርሱን ስለ መፍራቱና መሐላ ምሎ
ከዳ
እንዳይባል ነው እንጂ፡፡ ስለ ዮሐንስ አዝኖ ቢሆን ኖሮ
ቀድሞውንም
በግፍ እንዲታሰር ባላደረገው ነበር፡፡ ወንድሞቼ እኅቶቼ ሆይ!
ከመሐላ
የተነሣ መፍራት ይገባችኋል፡፡ ‹የለመንሽውን ሁሉ
እሰጥሻለሁ› ብሎ
ስለማለ ሄሮድስ የዮሐንስን አንገት እንድትቆረጥ አደረገ፡፡
ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስም በቅዱስ ወንጌል ‹ፈጽማችሁ አትማሉ›
ብሏል፡፡
ከዚህ በኋላ ወታደሮች ሠይፍ ይዘው የዮሐንስን አንገት
ይቆርጡ ዘንድ
ወደ መኅኒ ቤት ሄዱ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም የሄሮድስ ጭፍሮች
ሊገድሉት
እንደመጡ በመንፈስ ቅዱስ ፀጋ ስላወቀ ከጨለማው ቤት
ውስጥ
አንገቱን በመስኮት አውጥቶ እንደሚመቻቸው አድርጎ
ጠበቃቸው፡፡
የሄሮድስን ቃል እንዳያቃልሉ ጭፍሮቹም የመጥምቀ
መለኮት ዮሐንስን
አንገት ስለ መሐላው ቆረጡት፡፡ በመሐላ ምክንያት ባይሆን
ኖሮ ሄሮድስ
መጥምቀ መለኮት ዮሐንስን ባላስገደለው ነበር፡፡ ስለዚህ
ወንድሞቸ
እኅቶች ሆይ! እናንተም ከመሐላ የተነሣ መፍራት ይገባችኋል፣
ፈጽማችሁም መማል የለባችሁም፡፡››
ስካርና ዘፈን ከሚገኙበት ቦታ አጋንንትና ኃጢአት ከዚያ አሉ፡-
‹‹ወንድሞችና እኅቶች ሆይ! አለልክ መብላና መጠጣት ካለበት
ቦታ
እግዚአብሔርን መበደል፣ ማስቀየምና ማስቆጣት
ይገኝበታል፡፡ ስካር
ከሚገኝበት ቦታ አጋንንትና ኃጢአት ከዚያ አሉ፡፡ ስካርና ዘፈን
ከሚገኝበት
ቦታ የእግዚአብሔር መቅሰፍት የፈጣሪያችን ቁጣና በቀል
ይፈጸምበታልና፡፡ እናንተ ሕዝበ ክርስቲያኖች ሆይ! ከስካር፣
ከዘፈንና
ከዝሙት መራቅ ይገባችኋል፡፡ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስን
ያስገደለው
ዘፈን፣ ስካርና የዘማ ፍቅር መሆኑን ልብ በማለት መገንዘብ
አለባችሁ፡፡››
መድኃኔዓለም ክርስቶስ ለመጥምቁ ዮሐንስ የተገለጠበት ልዩ
ሁኔታ፡-
‹‹ንጉሥ ሄሮድስ በሞተ ጊዜ እነሆ የእግዚአብሔር መልአክ
በግብፅ አገር
ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ ታየው፡፡ እንዲህም አለው፡- ‹እነሆ
የዚህን
ሕፃን ነፍስ የሚሹ ሙተዋልና ተነሥተህ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ
ወደ
ምድረ እስራኤል ተመለስ› አለው፡፡ ዮሴፍም ተነሥቶ ሕፃኑንና
እናቱን ይዞ
ወደ ምድረ እስራኤል ገባ፡፡ ‹ልጄ ናዝራዊ ይባላል› ተብሎ
በነቢይ
የተነገረው ቃል ይደርስ ይፈዘም ዘንድ መጥቶ ናዝሬት
በምትባል አገር
ተቀመጠ፡፡ ለሞት ይፈልገው የነበረው የተረገመ ከሐዲ
ሄሮድስ ከሞተ
በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከድንግል ማርያም ጋር
ከምድረ
ግብፅ ተመልሶ በናዝሬት ተቀምጦ ሳለ እነሆ የዕድሜ ባለፀጋ
የሆነችው
የዮሐንስ እናት ክብርት ኤልሳቤጥ ልጇን ዮሐንስን ይዛው ወደ
ደብረሲና
በረሃ ከገቡ ከአምስት ዓመት በኋላ ዐረፈች፡፡ ዮሐንስም በእናቱ
አስክሬን
አጠገብ ተቀምጦ በእጅጉ እያዘነ መሪር ልቅሶንም እያለቀሰ
ሳለ
የተሸሸገውን ሁሉ የሚያውቅ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ
የኤልሳቤጥን መሞት፣ እናቱም ስለሞተችበት ዮሐንስ
ብቻውን ከበረሃ
ውስጥ ተቀምጦ እያለቀሰ መሆኑን ዐወቀ፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የኤልሳቤጥን
መሞት፣ የወዳጁ
ዮሐንስ ኃዘንና ማልቀስ ባወቀ ጊዜ እርሱም በናዝሬት ሆኖ
ያለቅስ
ጀመር፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ልጇ
ወዳጅዋ ሲያለቅስ
ባየችው ጊዜ ‹ልጄ ወዳጄ ሆይ! ምን ሆንክ? ስለምንስ
ታለቅሳለህ?› ብላ
ጠየቀችው፡፡ ጌታችንም ለቅድስት እናቱ እንዲህ በማለት
መለሰላት፡-
‹እነሆ ወገንሽ የሆነችው ኤልሳቤጥ ዐረፈች፤ ዮሐንስንም
ብቻውን ከበረሃ
ውስጥ ተወችው፡፡ ዮሐንስም ሕፃን ስለሆነ የሚያደርገውን
አጥቶ በእናቱ
አስክሬን አጠገብ ከፊት ለፊቷ ተቀምጦ በመረረ ኃዘን
ያለቅሳል፡፡ እናቴ
ሆይ እኔም ዘመድሽ የሆነ የዮሐንስን ልቆሶ ስላወቅሁኝና
የእርሱም ኃዘን
ስለተሰማኝ የማለቅሰው ስለዚህ ነው› አላት፡፡ በድንጋሌ ሥጋ
በድንጋሌ
ነፍስ የፀናች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም
የኤልሳቤጥን
መሞት በሰማች ጊዜ በጣም ምርር ብላ አለቀሰች፡፡
ያንጊዜም ብርሕት
ደመና መጥታ ከፊታቸው ቆመች፤ ፈጥናም ተሸከመቻቸውና
ኤልሳቤጥ
ከሞተችበት ዮሐንስም ካለበት ቦታ ከደብረሲና በረሃ ውስጥ
ወስዳ
አደረሰቻቸው፡፡ ዮሐንስም ባያቸው ጊዜ ደነገጠ፡፡ ከዚያ በፊት
ሰው አይቶ
ስለማያውቅ የእናቱን አስክሬን ብቻውን ትቶ ወደ ጫካ ሸሸ፡፡
ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስም የዮሐንስን ፍርሃት አራቀለትና እንዲህ
አለው፡- ‹እኛን
ከማየትህ የተነሣ አትፍራ፣ አትደንግጥም፤ አይዞህ እነሆ
የእናትህ
ዘመዶች ማርያምና ሰሎሜ በእናትህ አስክሬን ላይ መልካም
ነገር
ሊያደርጉ መጥተዋልና ና ወደ እኛ ቅረብ› አለው፡፡ ዮሐንስም
ይህን ቃል
ከጌታችን አንደበት በሰማ ጊዜ ወደኋላው ተመለሰ፡፡
ከመሬትም ላይ
ወድቆ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ሰገደለት፡፡
ጌታችንም እመቤታችን ማርያምንና ሰሎሜን እንዲህ ብሎ
አዘዛቸው፡-
‹በጠማው ጊዜ ለእርሷ ይጠጣ ዘንድ ለዮሐንስ በፈለቀችለት
ውኃ
የኤልሳቤጥን ሥጋ አጥባችሁ ገንዙ› አላቸው፡፡
እንዳዘዛቸውም
የኤልሳቤጥን አስክሬን አጥበው ገነዙት፡፡ ጌታችንም ቅዱስ
ሚካኤልንና
ቅዱስ ገብርኤልን ይመጡ ዘንድ አዘዛቸው፡፡ እነርሱም
ፈጥነው እንደ
ዐይን ጥቅሻ ከሰማይ ወርደው መጡና ከጌታችን ፊት ቆሙ፡፡
ጌታችንም
‹የኤልሳቤጥን ሥጋ የሚቀበርበትን መሬት ቆፍሩ› አላቸው፡፡
ቅዱስ
ሚካኤልንና ቅዱስ ገብርኤልንም መቃብሩን ይቆፍሩ ዘንድ
ጀመሩ፡፡
ጌታችን ዘካርያስንና ስምዖንን በአካለ ነፍስ ከሰማይ መጥተው
በኤልሳቤጥ አስክሬን ላይ ጸሎተ ፍትሐቱን ያደርሱ ዘንድ
አዘዛቸው፡፡
እነርሱም የኤልሳቤጥ አስክሬን ካለበት ቦታ ላይ ቅዱስ
ሚካኤልና ቅዱስ
ገብርኤል፣ እመቤታችን ማርያምና ሰሎሜ ከጌታችን ፊት
ቆመው ሳለ
ስምዖንና ዘካርያስ በአስክሬኑ አጠገብ ቆመው ጸሎተ
ፍትሐቱን ያደርሱ
ጀመር፡፡ ጸሎተ ፍትሐቱንም በጨረሱ ጊዜ መላእክት
በቆፈሩት መቃብር
ውስጥ ቀበሩዋትና የስምዖንና የዘካርያስ ነፍስ ወደነበረችበት
ቦታዋ
ተመለሰች፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የኤልሳቤጥን
መቃብር
በትእምርተ መስቀል አምሳል ደፈነው፡፡ ኤልሳቤጥም
ያረፈችበት ዕለት
የካቲት አሥራ ስድስት ቀን ሆነ፡፡
ከዚህ በኋላ ዮሐንስን ብቻውን ከበረሃ ውስጥ ትተውት ጌታችን
ኢየሱስ
ክርስቶስ ከእመቤታችን ጋር ወደ ናዝሬት ለመመለስ
ከደመናዋ ላይ
ተሣፍሮ ተነሣ፡፡ ያንጊዜም ክብርት እመቤታችን ልጇን
እንዲህ አለችው፡-
‹ጌታዬና አምላኬ ፈጣሪዬ ሆይ! ስለምን ዮሐንስን ብቻውን
ከበረሃ
ውስጥ ትተወዋለህ? እንዴትስ ትተነው እንሄዳለን? ወደዚህ
ቦታ ይዛው
የሸሸችው እናቱ ጥላው ሞታ በመቃብር ውስጥ ተቀብራለች
ከእኛ ጋር
ይዘነው እንሂድ እንጂ› አለችው፡፡ ዳግመኛም እመቤታችን
እንዲህ
አለችው፡- ‹ነፍስ ያለወቀ ሕፃን ስላሆነ አራዊት ይበሉታልና
ይዘነው መሄድ
አለብን› አለችው፡፡ ጌታችንም ለቅድስት እናቱ እንዲህ
በማለት
መለሰላት፡- ‹በመምህርነት ወጥቶ ለእስራኤል ታይቶ
እስከሚያስተምር
ድረስ የሰማያዊው አባቴ ፈቃድ በበረሃ ውስጥ ብቻውን
እንዲኖር ነው፡፡
አንቺ ብቻውን እንዴት ከበረሃ ይኖራል ትያለሽ፤ አራዊቶች
እንዳይጣሉት
ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ከእርሱ አይለይም፡፡
በፈለገው ነገር ሁሉ
እንዲራዱትና እንዲታዘዙለት መላእክተ ብርሃንን አዝለታለሁ፡፡
ብርሃናዊው
መልአክ ገብርኤልም ሰማያዊ ሕብስትን ለምግቡ
ያመጣለታል፤
በጠማውም ጊዜ እንደ ወተት የነጣችውን፣ እንደ ወለላ
ማርም
የጣፈጠችውን ውኃ ከኤዶም ገነት ያመጣለታል፡፡ ይህችንም
እርሱ
ካለበት ድንጋይ ሥር የምትፈልቀውን ውኃ እንደ እናቱ ጡት
ለአፉ
የጣፈጠች አደርግለታለሁ፡፡ አንቺ ብቻውን እንዴት በበረሃ
ውስጥ ይኖራል
ትያለሽ፤ እስከ ዛሬ ድረስም የጠበቅሁት እኔ ነኝ፣ ሌላ ማን
ጠበቀው
ብለሽ ነው? እኔ አይደለሁምን? ወዳጄ ዮሐንስን ሰማያዊው
አባቴ ከዚህ
ዓለም ፍጥረት ሁሉ በጣም አብልጦ ይወደዋል፡፡ አባቱ
ዘካርያስም
በሥጋው ቢሞት በነፍሱ ሕያው ስለሆነ ዮሐንስን ለማጽናናት
በአካለ
ነፍስ ከእርሱ እንዳይለየው አደርጋለሁ፡፡ እናቱ አልሳቤጥም
በሥጋዋ
ብትሞት በነፍሷ ሕያዊት ስለሆነች ታጽናናው ዘንድ በነፍሷ
በፍጹም
ከእርሱ እንዳትለየው አደርጋለሁ፡፡ ዮሐንስን የተሸከመች
ማኅፀን ንዕድ፣
ክብርት ስለሆነች በሥጋዋ ውስጥ መጥፎ ሽታ፣ ክፉ መዓዛ
አይገኝባት፣
በመቃብሯም ውስጥ ትሎች አይገኙበት፡፡ ድንግል እናቴ ሆይ!
አንቺ እኔን
ፀንሰሽ ሳለሽ ወደ ኤልሳቤጥ በሄድሽ ጊዜ በእጇ ይዛ ጨብጣ፣
በአፏ
በሳመችሽ ጊዜ እንዲህ ብላ ትንቢት ተናግራለች፡፡ ‹አንቺ
ከሴቶች ሁሉ
ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ፤ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው፤
የጌታዬ እናቱ
ወደ እኔ ትመጪ ዘንድ እኔ ምንድነኝ? ከእግዚአብሔር
አግኝተው
የነገሩሽን ቃል ይደረጋል ብለሽ የተቀበልሽ አንቺ ብፅዕት ነሽ፣
ክብርት ነሽ›
ብላ ስላመሰገነችሽ እንኳን ሥጋዋ ሊፈርስ ይቅርና መግነዟም
አይለወጥም፤ መቃብሯም አይጠፋም፤ ነፍሷንም ከሥጋዋ ጋር
እንድትኖር
አደርጋታለሁ፡፡› ይህን የመሰለ ነገር ስለ ወዳጁ ዮሐንስ
ለድንግል እናቱ
ነግሯት ለጨረሰ በኋላ ዮሐንስን ከበረሃ ውስጥ ትተውት
በደመና ላይ
ተጭነው ወደ ናዝሬት ተመለሱ፡፡››
መድኃኔዓለም ክርስቶስ ለመጥምቁ ዮሐንስ የሰጠው ልዩ
ቃልኪዳን፡-
1. ‹‹…ከሚበላውና ከሚጠጣው ከፍሎ በስምህ ለነዳያን
ለሰጠ ሥጋዬን
ደሜን እሰጠዋለሁ፤ በሃይማኖት ፀንቶ፣ በምግባር ሠፍቶ
ሥጋዬን ደሜን
እንዲቀበል አደርገዋለሁ፤ ለሥጋዬ ለደሜ የሚያበቃ ሥራ
እንዲሠራ
አደርገዋለሁ፤ እስከ ሃምሣ አምስት ትውልድም ድረስ
እምረዋለሁ፡፡››
2. ‹‹ሰው ሁሉ ወደ ሥጋዊ ተግባርም ሆነ ወደ መንፈሳዊ
ተግባርም
ቢሆን ሲሄድ ‹ይህ የመጥምቀ መለኮት ዮሐንስ ቤተክርስቲያን
ነው› ብሎ
ቅጽሩን፣ ገራገሩን ቢሳለም የተሳለመው ሰው ቢኖር እኔ
መንበረ
መንግሥቴን አሳልመዋለሁ፡፡ የገድልህንም መጽሐፍ
የተሳለመ ቢኖር እኔ
መንበረ መንግሥቴን አሳልመዋለሁ፡፡››
3. ‹‹ከቤተክርስቲያንህ የተቀበረውን ሰው ከመከራ ሥጋ፣
ከሲኦል እሳት
አድነዋለሁ፤ እኔ ከተቀበርኩበት ኢየሩሳሌም ሄዶ ከእኔ
መቃብር ውስጥ
እንደተቀበረ አደርገዋለሁ፡፡››
4. ‹‹ቤተክርስቲያንህ ከታነፀችበት፣ ስምህ ከሚጠራበት፣
መታሰቢያህ
ከሚደረግበት፣ የተአምርህ ዜና ከሚነገርበት፣ የገድልህ
መጽሐፍ ተነቦ
ከሚተረጎምበት፣ እኔ በረድኤት ከዚያ እገኛለሁ፤ ከዚያ ቦታ
አልለይም፡፡
የገድልህ መጽሐፍ ከሚተረጎምበት ቦታ አጋንንት አይደርሱም፤
ከዚያ ቦታ
ሰይጣናት ይርቃሉ፡፡››
5. ‹‹የገድልህ የተአምርህ መጽሐፍ የተነበበትን ውኃ እኔ
እንደተጠመቅሁበት እንደ ማየ ዮርዳኖስ አደርገዋለሁ፡፡
የገድልህ
መጽሐፍ በተነበበት ውኃ የተጠመቀበት ሰው ቢኖር የሰማንያ
ዓመት
ኃጢአቱን አስተሠርይለታለሁ፤ ወንዱን የአርባ ቀን፣ ሴቷን
የሰማንያ ቀን
ሕጻን አደርጋቸዋለሁ፤ እኔ በተጠመቅሁበት ማየ ዮርዳኖስ
እንደተጠመቀ
ሆኖለት ከኃጢአቱ ይነጻል፡፡››
6. ‹‹ሰውም ሆነ እንስሳ ቢታመም በጽኑ እምነት
ይደረግልኛል ብሎ
አምኖ ያለ ጥርጥር ውኃ አቅርቦ የገድልህን መጽሐፍ በላዩ
ላይ አንብቦ
የተነበበበትን ውኃ ቢታጠብበት ወይም ቢጠጣ ያለ ጥፋት
ፈጥኖ
ከደዌው ይፈወሳል፡፡››
7. ‹‹የገድልህ መጽሐፍ የተነበበትን ማየ ጸሎት በቤቱ ውስጥ
ቢረጭ
ከዚያ ቤት በረከቴን እመላበታለሁ፤ ተድላን፣ ደስታን፣ ጥጋብን
በዚያ ቤት
አሳድራለሁ፤ እስከ ዘለዓለም ድረስ በቤቱ ውስጥ የእህል
መታጣትና
ረሀብ፣ የውኃ ጥማት፣ ተላላፊ በሽታ አይገባበትም፤ ፈጽሜም
አላመጣበትም፡፡››
8. ‹‹ደስ ብሎት በተድላ በደስታ በዓለህን ያከበረውን ሰው ሁሉ
በቅዱሳን መላእክቶቼና በሰማያዊ አባቴ በአብ ማሕያዊ
በሚሆን
በመንፈስ ቅዱስ ፊት እኔ ደስ አሰኘዋለሁ፡፡ እነሆ እኔም
ከበዓልህ ቦታ
ላይ አልለይም፤ በዓልህንም ከሚያከብሩት ጋር እኔ
አብሬያቸው
እቀመጣለሁ፤ እስከ ሃምሣ አምስት ትውልድም
እምረዋለሁ፡፡››
9. ‹‹ለቤተክርስቲያንህ ዕጣን፣ ሻማ፣ ጧፍ፣ ልብሰ ተክህኖ፣
መጎናጸፊያ፣
መጋረጃ፣ ነጭ ስንዴ የሰጠ ሰው ቢኖር እስከ ሃምሣ አምስት
ትውልድም
ድረስ እምረዋለሁ፡፡››
10. ‹‹ሥጋዬን ደሜን መቀበል ያልተቻለው ሰው ቢኖር
ለመታሰቢያህ
ዝክር ከተደረገው ፍርፋሪ ይቅመስ፣ ሥጋዬን ደሜን
እንደተቀበለ እኔ
አደርግለታለሁ፡፡ ፍርፋሪውን ባያገኝ እንጀራውና ዳቦው
የተበላበትን
ገበታ፣ ጠላው የተጠጣበትን ፅዋ በምላሱ ይላስ፣ እኔ ኢየሱስ
ቃሌ
የማያብለው ሥጋዬን ደሜን እንደተቀበለ አደርግለታለሁ፤ ስለ
እምነቱ
ሥጋዬን ደሜን ለመቀበል የሚያበቃውና እውነተኛውን
ምግባር የጽድቅ
ሥራ እንዲሠራ አደርገዋለሁ፡፡››
ጌታችን በቅዱስ ወንጌሉ ስለ ዮሐንስ ሲናገር ‹‹ዮሐንስ
የሚያበራ መብራት ነበረ›› ነው ያለው፡፡ ዮሐ 5፡35፡፡
ዳግመኛም ክብሩን ሲገልጥለት "እውነት እላችኋለሁ ከሴቶች
ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ ማንም
የለም" በማለት መስክሮለታል፡፡ ማቴ 11:11፣ ሉቃ
7:28፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ
ይማረን፡፡

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ: =>+*"+<+>††† መስከረም 1-ሊቀ መላእክት ቅዱስ ራጉኤል †††<+>+"*

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
አሜን
መስከረም 1-ሊቀ መላእክት ቅዱስ ራጉኤል የተሾመበት
ዕለት ነው፡፡
+ ዳግመኛም በዚኽች ዕለት ሐዋርያው ቅዱስ በርተሎሜዎስ
ዕረፍቱ ነው፡፡
+ ታላቁ አባት ጻድቁ አባ ሚልኪ ዕረፍቱ ነው፡፡
+ ጻዲቁ ኢዮብም ከበሽታው የዳነው በዚህች ዕለት ነው፡፡
ጻዲቁ ኢዮብ በፈሳሽ ውኃ ታጥቦ ከደዌው ሁሉ ስለተፈወሰ
ለሰዎች ልማዳቸው ሆኖ ዓመቱ ዞሮ ሲመጣ ፈሳሹ ውኃም
በመላ ጊዜ በአዲስ ውኃ ይጠመቃሉ፣ በእርሱም ይባረካሉ፡፡
ሐዋርያው በርተሎሜዎስ፡- ወንጌልን ይሰብክ ዘንድ ዕጣ
የደረሰው አልዋሕ በሚባል አገር ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ
ሊያደርሰው አብረው ወደ አልዋሕ ሄዱ፡፡ ወደ ከተማው
ለመግባት ምክንያት ፈለጉና ቅዱስ ጴጥሮስ ቅዱስ
በርተሎሜዎስን ‹‹አትክልተኛ ባለሙያ ነው›› ብሎ የወይኑን
ቦታ እንዲጠብቅለት ለአንድ ባለጸጋ መኰንን ባሪያ አድርጎ
ሸጠው፡፡ ባለጸጋውም በርተሎሜዎስን በ30 እስቴታር
ገዝቶት ሄደ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ገንዘቡን ደብቆ ለቅዱስ
በርተሎሜዎስ በድብቅ ሰጥቶት እንዲመጸውተው ነግሮት
ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ፡፡ አልዋሕ ከገባ በኋላ ቅዱስ
በርተሎሜዎስ የወይን ቦታው አለቃ ሆኖ 40 ቀን
ተቀመጠ፡፡ ወንጌሉን ባለመስበኩ በሀዘን እያለቀሰ ጌታችንን
በጸሎት ጠየቀው፡፡ በገንዘቡ ገዝቶት ባሪያው ያደረገው
ባለጸጋውም የወይኑን ቦታ ያይ ዘንድ እንደመጣ መርዘኛ እባብ
ነድፎት ሞተ፡፡ ሕዝቡም ተሰብስቦ ሲያለቅስ በርተሎሜዎስ
ግን ወደ ጌታችን ከጸለየ በኋላ ሄዶ ባለጸጋውን ሰው ከሞት
አስነሣው፡፡ በዚህም ሕዝቡ ሁሉ አምነው ተጠምቀዋል፡፡
በርተሎሜዎስም ወደ ሌሎች አገሮች ሄዶ አስተማረ፡፡
ጌታችን ወደ በርበሮች ዘንድ ሄዶ ወንጌልን እንዲሰብክ
አዘዘው፡፡ ረዳት እንዲሆነውም እንድርያስን ከደቀ መዝሙሩ
ጋር ላከለት፡፡ የሀገሪቱ ሰዎች ግን እጅግ ክፉዎች ነበሩ፡፡
በሐዋርያቱም ፊት በአስማት አስደናቂ ተአምራት እያሳዩ
ትምህርታቸውን የማይቀበሏቸው ሁኑ፡፡ ይህን ጊዜ ጌታችን
ሰውን ከሚበሉ አገር አንዱን ገጸ ከልብ ይታዘዝላቸው ዘንድ
በሚያዙትም ነገር ሁሉ ከትእዛዛቸው እንዳይወጣ አዘዘው፡፡
ሐዋርያትም ወደ በርበሮች አገር ዳግመኛ በገቡ ሰዓት
ይበሏቸው ዘንድ ኃይለኛ አራዊትን አውጥተው ለቀቁባቸው፡፡
ያ ገጸ ከልብም በአራዊቱ ላይ ተነሥቶ እየነጠቀ በላቸው፡፡
ይህንንም የተመለከቱት በርበሮች እጅግ ፈርተው በድንጋጤ
ብቻ የሞቱ አሉ፡፡ በሐዋርያቱም እግር ሥር ወደቁ፡፡
ሐዋርያቱም አስተምረው ካሳመኗቸው በኋላ
አጥምቀዋቸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ቅዱስ በርተሎሜዎስ
እግዚአብሔርን ወደማያውቁ አገሮች ሄዶ ብዙ ተአምራትን
እያደረገ አስተምሮ አጠመቃቸው፡፡ የከሃዲው ንጉሡ
የአግሪጳን ሚስትም ትምህርቱን ሰምታ በጌታችን አመነች፡፡
ንጉሡ አግሪጳም በዚህ እጅግ ተቆጥቶ ቅዱስ
በርተሎሜዎስን ብዙ ካሠቃየው በኋላ አሸዋ በተሞላ ትልቅ
ከረጢት ውስጥ ከቶ ከነሕይወቱ ባሕር ውስጥ እንዲጥሉት
አደረገ፡፡ ምእመናንም ሥጋውን አውጥተው በክብር
ቀብረውታል፡፡ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡
+ + + + + + + + + + + + + + +
አባ ሚልኪ ዘቁልዝም፡- በላይኛው ግብጽ የሚኖሩ ባለጸጋ
ወላጆቻቸው በስዕለት ወለዷቸው፣ ብሉይን ከሐዲስ አጠናቀው
ከተማሩ በኋላ የአባታቸውን ወርቅ ለድኆች ሰጥተው ገዳም
ገብተው መነኩሰው በታላቅ ተጋድሎ ኖሩ፣ የአገረ ገዥውልን
ልጅ ዘንዶ ውጦት ሳለ አባ ሚልኪ ዘንዶውን ጠርቶት ልጁን
ይተፋው ዘንድ አዘዘውና ልጁ ጤነኛ እንደሆነ ከዘንዶው ውስጥ
ወጣ፣ በውስጡ ያደረ ከይሲም በኖ ጠፋ፣ ጻድቁ ቤ/ክ ሲሠሩ
የመሠረቱ ድንጋይ ራሱ በተአምራት እየተፈነቀለ ይተከል
ነበር፣ ለ300 መነኮሳትም አባት ሆነው በተአምራታቸው
የፋርስንና የሮም ሰዎችን አሳመኗቸው፣ ዋሻ ዘግተው ሊኖሩ
በማሉ ጊዜ ሰይጣን መሀላቸውን ሊያፈርስ አስቦ በሮሙ ንጉሥ
ልጅ አድሮ አሳመማትና በአባ ሚልኪ ካልሆነ በቀር
አልወጣም አለ፣ ንጉሡም ልኮባቸው በደመና ተጭነው ሄደው
ልጅቷን ፈውሰው አድሮባት የነበረውን ሰይጣን ገዝተው
አሠሩትና ከንጉሡ ቤት 14 ሰው የማይሸከመውን ድንጋይ
በአንገቱ ላይ አሳስረው አስሸክመውት ሰው ሁሉ እያየው ወደ
ገዳማቸው አስመጡትና ድንጋዩን የበዓታቸው መዝጊያ
አደረጉት፤ ጻድቁ በብርቱ ሲጋደሉ ኖረው የሚያርፉበት ቀን
ከተነገራቸው በኋላ እነ እንጦንስ፣ መቃርስ፣ ሲኖዳ፣ ብሶይ፣
ጳኩሚስ ተገልጠውላቸው ወንድማችን ና ወደ እኛ ብለዋቸው
በሰላም ዐርፈዋል፡፡ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣
በጸሎታቸው ይማረን፡፡
+ + + + + + + + + + + + + + +
ራጉኤል ሊቀ መላእክት:- ራጉኤል ማለት የብርሃናት አለቃ
ማለት ነው። የብርሃናት አለቃ ሲባል ፀሐይን፣ ጨረቃን እና
ከዋክብትን በማመላለስና ለሰው ልጆች፣ ለአዝርዕት፣
ለእንስሳት፣ ለአራዊት ሁሉ ብርሃንን የሚመግብ ነው ማለት
ነው። አንድም ራጉኤል ማለት የሚበቀል ማለት ነው።
የሚበቀል ነው ማለት በቀል የሚገባው ለጠላት ነው የሰው
ልጅ ጠላት ደግሞ ዲያብሎስ ነው፤ ስለሆነም ቅዱስ ራጉኤል
እግዚአብሔርን አምነው ሕገ እግዚአብሔርን ጠብቀው
በፍርሐተ እግዚአብሔር አምልኮቱን ለሚፈጽሙ ሁሉ ጠላት
ዲያብሎስን የሚያርቅላቸው ወደ እነርሱም ፈጥኖ በመድረስ
የሚታደጋቸው ነው ማለት ነው። ሔኖክ 6:4፡፡ አንድም
ራጉኤል ማለት የኃያላን ኃያል እግዚአብሔር ማለት ነው።
የኃያላን ኃያል ያለው የእግዚአብሔርን ኃያልነት ከምድር
ፍጥረታት ዘንድ ኃያል ከሚባሉት ሁሉ ሊገለጽ የማይችል
ኃያልነቱን ለመግለጽ ኃያልነቱም ከ እስከ የሌለው መሆኑን
ለመግለጽ የተቀመጠ ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር ኃያል
የኃያላን ኃያል መሆኑን የሚገልጽ ትርጉም አለው።
አንድም ራጉኤል ማለት ጽኑ እግዚአብሔር ማለት ነው።
የእግዚአብሔር አምላክን ጽኑነት ለማጉላት ሲል ጽኑ አለው።
እግዚአብሔር የማይወላውል የማይዋዥቅ የማይከዳ ነው
ለማለትም ሲል ይህ ስያሜ ተሰጠው። የእግዚአብሔርን ጽናት
የሚያሳይ ትርጉም ያለው ስያሜ ነው። የሊቀ መላእክት
የቅዱስ ራጉኤል አገልግሎት እና ስልጣን፡- እመቤታችን
ቅድስት ድንግል ማርያም ከዚህ ዓለም በ64 ዓመቷ ካረፈች
በኋላ ሥጋዋ ወደ ዕፀ ሕይወት ሲነጠቅ (ሲያርፍ) አብሮ
ለሔደው እና ስጋዋን በእጣን ሲያጥን ለነበረው ለፍቁረ እግዚ
ለቅዱስ ዮሐንስ ኅብስትን የመገበ መልአክ ነው።
በብርሃናት ሁሉ ላይ የሰለጠነ መልአክ ነው። ከአዳም ሰባተኛ
ትውልድ የሆነ በእግዚአብሔር ፊት ግሩም ያማረ ሥራው
የሰመረ እስከዛሬ የሞት ወጥመድ ያልያዘው የሞት ጥላ
ያላረፈበት ነብዩ ሔኖክ "ከቅዱሳን መላእክት አንዱ የሆነ ጸላዒ
ዲያብሎስን የሚበቀለው ራጉኤል በብርሃናት ላይ የሰለጠነ
ነው" ሲል ስለ እርሱ ተናግሯል፡፡
እግዚአብሔር ዓለምን ይቆጣጠር ዘንድ የሾመው ታላቅና
ቅዱስ መልአክ ነው። (ድርሳነ ራጉኤል ዘ ጥቅምት ገጽ 23)
አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ለመተካት ዓለምን የመለወጥ
ሥልጣን የተሰጠው ቅዱስ መልአክ ነው። ከእግዚአብሔር
የጌትነቱ አዳራሽ ይገባና ይወጣ ዘንድ ስልጣን ያለው
ከኪሩቤልና ከሱራፌል ጋር ከፈጣሪ የጌትነት ዙፋን ፊት
የሚቆም ነው። ሎጥን ሚስቱንና ልጆቹን ከእሳተ ጎመራ
ያዳነ የበለአምን እርግማን ወደ በረከት የለወጠ እርሱ ነው።
በቅዱስ ራጉኤል ስነ ሥዕል ላይ የምናየው ይህ ባለ አራት
እራስ ንስር ከአርባእቱ ኪሩቤል አንዱ ገጸ ንስር ነው።
የሥላሴን የጌትነት ዙፋን የሚሸከሙ አርባዕቱ እንስሳት
ናቸው። የሚሸከሙት ሲባል ጫማ የሰውን ልጅ
እንደሚሸከመው እንጂ ችለውትስ አይደለም። እነርሱም
የሰው ገጽ፣ የእንስሳ ገጽ፣ የንስር ገጽ እና የአንበሳ ገጽ ያላቸው
ናቸው። ይህንንም ነብዩ ሕዝቅኤል "ለእያንዳንዱ እንስሳትም
የተለያዩ አራት ገጾች ነበሩት። ይህውም በስተቀኝ በኩል
የእንስሳ መልክ፣ በስተ ግራ የላም ገጽ፣ በበስተ ኋላም የንስር
ገጽ የሚመስሉ ነበሩ" ብሏል ሕዝ 1፡6-13፡፡ ከዚህ
የምንገነዘበው ነገር ቢኖር አራት ገጽ ካላቸው ኪሩቤል
መካከል አንዱ ንስር መሆኑን ነው። ቅዱስ ራጉኤል ደግሞ
የእነዚህ ኪሩቤል አለቃቸው (የጌትነቱ ዙፋን ጠባቂ) በመሆኑ
በዚህ ምክንያት ማለትም እነርሱ ዙፋኑን ተሸካሚ እርሱ
ደግሞ አጠገባቸው መቆሙ መንበሩን ጠባቂ በመሆኑ በዚህ
አይነት የአገልግሎት ድርሻ አብረው ሊሳሉ ችለዋል። ቅዱስ
ያሬድም በድጓው "አርባእቱ እንስሳ አልቄንጥሩ እንደሚባለው
ንስር ፊት ለፊት አይታዩም አንዱም በመራቸው ይሔዳሉ
እነርሱም እያንዳንዳቸው አራት ገጽ ሲኖራቸው ሳያርፉና
ሳይደክሙ የሚያመሰግኑ ናቸው" በማለት ጽፏል። አንድም
መላእክት ነገደ ሱራፌል እና ነገደ ኪሩቤል በመባል
ይከፈላሉ። በነገደ ሱራፌል እነ ቅዱስ ሚካኤል፣ ቅዱስ
ሩፋኤል ወዘተ ሲሆኑ በነገደ ኪሩቤል ደግሞ ቅዱስ ገብርኤል
ቅዱስ ራጉኤል ወዘተ ያጠቃልላል። ስለዚህ ቅዱስ ራጉኤል
ነገዱ ከነገደ ኪሩቤል ነው በዚህም ላይ የነገደ ኪሩቤል
አልቄንጡራ (አራት እራስ ንስር) አለቃቸው ቅዱስ ራጉኤል
ነው። በዚህም ምክንያት አብረው ሊሳሉ ችሏል። አንድም
መላእክትን ሁሉ እንደ እየስራቸው መለያ ስነ ሥዕላቸውን
መሳል ልማድ ነውና። ለምሳሌ ቅዱስ ሚካኤል ከቅድስት
አፎምያ ጋር፣ ቅዱስ ገብርኤል ከሠለስቱ ደቂቅ ጋር፣ ቅዱስ
ዑራኤል ከእዝራ ሱቱኤል ጋር እንደሚሳሉት ሁሉ ማለት
ነው። በዚህም መሰረት ቅዱስ ራጉኤልም ዐቃቤ መንበር
ነውና መንበሩን በሚሸከሙት ኪሩቤል ከሚመሰሉት ንስሮች
ጋር አብረው ሊሳሉ ችለዋል፡፡
ሊቀ መላእክት ቅዱስ ራጉኤል ከአምላክ የተሰጠው ቃል
ኪዳን እግዚአብሔር አምላክ በስሙ ለታመኑት ቅዱሳን፣
ጻድቃን፣ ሰማእታት፣ ሐዋርያት፣ ዘወትር ያለማቋረጥ ስሙን
ለሚጠሩት ቅዱሳን መላእክት ሁሉ ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል።
የሰጣቸውም ቃል ኪዳን ዘላለማዊ እና ሊሻር የማይችል
ነው። ለመላእክት አለቃ ለቅዱስ ራጉኤልም ይህን ቃል ኪዳን
ሰጥቶታል "የራጉኤል አምላክ ይቅር በለኝ በማለት አንዲት
ቃልስ እንኳን ቢናገር እንደ ወዳጄ እንደ አብርሃም፣ እንደ
ባለሟሌም እንደ ይስሐቅ፣ እንደ አከበርኩትም እንደ ያዕቆብ
ክብርን ባለሟልነትን እሰጠዋለሁ በራሱ ላይም አክሊል
አቀዳጀዋለሁ እረጅም ዘመናት ሰፊ ወራትም እሰጠዋለሁ"
ሲል ቃሉን ሰጥቶታል፡፡ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ራጉኤል
መስከረም 1 ቀን ከሊቃነ መላእክት በ4ተኛ ደረጃ
የተሾመበት ዕለት ነው። ግንቦት 1 ቀን ለታላቁ አባት ለሄኖክ
ምሥጢራትን የገለጸበት በዓሉ ነው፡፡ ጥበቃው አይለየን፣
በምልጃው ይማረን፡፡
የቅዱሳን አባቶቻችን አምላክ ሀገራችንን ይጠብቅልን፡፡