ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

Saturday, April 2, 2016

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ: የዐቢይ ጾም አምስተኛ እሑድ ደብረ ዘይት

የዐቢይ ጾም አምስተኛ እሑድ ደብረ ዘይት
ተብሎ ይጠራል፡፡ የጌታችን ዳግም መምጣትና የዘመኑ
ምልክት የሚነገርበት ቀን በመሆኑ ዕለቱ ደብረ ዘይት
ተብሎ ተጠርቷል፡፡ ጌታችን ስለ ዓለም መጨረሻና ስለ
መምጣቱ ምልክት የተናገረው በደብረ ዘይት ተራራ ላይ
በመሆኑ ዕለቱ ደብረ ዘይት ተባለ (ማቴ. 24÷ 3)፡፡
ቅዱስ ያሬድ ዕለቱን ደብረ ዘይት ብሎ መሰየሙ ብቻ
ሳይሆን በዕለቱም ያቀረበው ዝማሬ እንዲህ የሚል
ነው፡-
“ወአመ ምጽአቱሰ ለወልደ እጓለ እመሕያው ይትከወሰ ኲሉ
ኃይለ ሰማያት ወምድር አሜሃ ይበክዩ ኲሎሙ ኃጥአን ምድር
ወይወርድ እግዚእነ እምሰማይ ዲበ ምድር በትእዛዙ ወበቃሉ
ወበአእላፍ መላእክቲሁ በንፍሐተ ቀርን ዘእም ኀበ
እግዚአብሔር ይምሐረነ አብ በይእቲ ሰዓት እሞተ ኃጢአት
እስመ ገባሬ ሕይወት”
ትርጉም፡-
“የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ የሰማይና የምድር
ሠራዊት ሁሉ ይነቃነቃል። ያን ጊዜ በምድር የሚኖሩ
ኃጢአተኞች ሁሉ ያለቅሳሉ፡፡ ጌታችንም ከአእላፍ
መላእክት ጋር በትእዛዙና በቃሉ መሠረት ከሰማይ ወደ
ምድር ይወርዳል፡፡ የእግዚአብሔር መለከትም
ይሰማል፡፡ በዚያች ሰዓት እርሱ ያድነን። እርሱ የሕይወት
ባለቤት ነውና።”
ቅዱስ ያሬድ የዘመረው የማቴዎስ ወንጌል
ምዕራፍ 24ን ነው፡፡ ጌታችን ሲመጣ ፍጥረት
እንደማይፀና ኃጢአተኞች ደስታ እንደማይሰማቸው
ይገልጣል፡፡ በኃይሉ ፊት ፍጥረት፣ በፍርዱ ፊት ኃጥአን
መቆም አይችሉምና፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይመጣል። በብሉይ
ኪዳን እመጣለሁ ብሎ መጥቷል፡፡ በአዲስ ኪዳንም
እመጣለሁ ብሎ ቤተ ክርስቲያንን በተስፋ አስገዝቷታል፡፡
ፍጥረት ሁሉ የሚጠብቀው አንድ ታላቅ እንግዳ
ከፊታችን ባለው ባልራቀው ዘመን ይመጣል፡፡
የሚመጣው በትሕትና ሳይሆን በልዕልና ነው፡፡
በከብቶች በረት ሊጣል ሳይሆን በደመና በዙፋን
ተገልጦ ይመጣል፡፡ ስምዖን አረጋዊ እንደ ታቀፈው ሆኖ
አይመጣም፣ ሰማይና ምድር የማይችሉት ሆኖ
ይመጣል፡፡ ከእናቱ ጡትን እየለመነ አይመጣም፣
ለፍጥረት ሁሉ የሩጫውን ዋጋ ለመስጠት ይመጣል፡፡
ከሄሮድስ ፊት የሚሸሽ ሆኖ አይመጣም፡፡ ሰማይና
ምድር ሲያዩት ከፊቱ ይሰደዳሉ፡፡ ለእኛ ለክርስቲያኖች
መጣልን የምንለው እንግዳችን፣ ፈራጃችን እንጂ
መጣብኝ የምንለው አይደለም፡፡
የጌታችን ዳግም ምጽአት፡-
1. የጸሎታችን መልስ ነው።
2. የፍጥረት ምጥ ዕረፍት ነው።
3. የዘመናት ናፍቆት መልስ ነው።
4. የተስፋችን ፍጻሜ ነው።
5. የእምነታችን ክብር ነው።
6. የአዲስ ዓለም ጅማሬ ነው።
7. የዘላለም ሕይወት መክፈቻ ነው፡፡
የጸሎታችን መልስ ነው
ብዙ ሰዎች ክርስቶስ ዳግም ይመጣል ሲባሉ
ይፈራሉ፡፡ ፍርሃታቸው ግን ለንስሐ አያዘጋጃቸውም። ልበ
ሙሉ ሆነው ኃጢአት እንዳይሠሩ የመምጣቱ ዜና
ስለሚረብሻቸው ነው፡፡ የጌታችን ዳግም ምጽአት
በሚታሰብበት ቀን እንኳ ብዙ የኃጢአት መታሰቢያ
ሲደረግ ይውላል፡፡ ለብዙ ሰዎች እኩለ ጾም ከሥጋና
ከስካር ከተላቀቁ አንድ ወር መሆኑን ለመገናኘትም ወር
እንደሚቀራቸው የሚያስቡበት ቀን ነው፡፡ በጊዜያዊ
ጨዋነት የሰነበቱትም ሲሰክሩ የሚውሉበት የተውኔት
ቀናቸው ነው፡፡ ሃይማኖት የማይሞት ኃይል ነው፡፡ ከሰው
ልብ ግን ሊሞት የሚችለው ሰዎች እንደ ባሕል
ቆጥረውት ሲኖሩ ነው፡፡
የጌታችን መምጣት ግን የጸሎታችን መልስ
ነው፡፡ የምንፈራውና ያርቅልኝ የምንለው ሳይሆን
በየዕለቱ “መንግሥት ትምጣ” እያልን የምንጸልይበት
ትልቅ ርዕሳችን ነው፡፡ የዚህ ዓለም መንግሥት በግፍ
ተጀምሮ በግፍ የሚጠናቀቅ፣ በውሸትና በሐሰተኛ ተስፋ
ሰውን የሚያደክም፣ በጭካኔ ሲወዳደር የሚኖር፣ ደም
በደም የሆነ መንገድ ነው፡፡ በዚህ ክፉ ሥርዓት
የተጨነቁ ሁሉ ጽድቅና ሰላም የነገሠባትን የክርስቶስን
መንግሥት ይናፍቃሉ (ሮሜ. 14÷17)፡፡ የክርስቶስ
መንግሥቱ የምትገለጠው ጌታችን ምድራውያን
ነገሥታትን አሳልፎ ንጉሠ ነገሥት ሆኖ በሚነግሥበት
በዳግም ምጽአቱ ነው፡፡ ዳግም ምጽአቱ ምድራዊውን
ሥርዓት አሳልፎ አንድ መንግሥትን በሁሉ የሚያፀና
ነው፡፡
የፍጥረት ምጥ ዕረፍት ነው
ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “ የፍጥረት ናፍቆት
የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና” ይላል
(ሮሜ. 8÷19)፡፡ ዳግመኛም “ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን
ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን
እናውቃለንና” ይላል (ቁ.22)፡፡ በሰው ኃጢአት
የተጨነቀው ሰው ብቻ ሳይሆን ፍጥረት በሙሉ ነው፡፡
እንስሳቱ አራዊቱ ሁሉ የሰውን ኃጢአት ቅጣት
እየተካፈሉ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ የሚያርፉት ክርስቶስ
ልጆቹን በክብር በሚገልጥበት በምጽአቱ ቀን ነው፡፡
ስለዚህ ፍጥረት ሳይወድ በግድ የሰውን ማረፍ
ይናፍቃል፡፡ የራሱም ዕረፍት ነውና፡፡ ዛሬ በብዙ ነገር
እናለቅሳለን፡፡ ብዙ ጭንቀቶችም ከበውን እንኖራለን፡፡
የክርስቶስ መምጣት ግን የፍጥረት ምጥ ዕረፍት ነው፡፡
የዘመናት ናፍቆት እርካታ ነው
ማራናታ ማለት ጌታ ይመጣል ወይም ጌታ
መጣ ማለት ነው (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት
ገጽ 609)፡፡ ይህ ቃል ዮሐንስ ራእዩን ሲዘጋ
ተጠቅሞታል፡- “ አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና” (ራእ.
22÷20)። ዮሐንስ በራእዩ ስለሚመጣው የዘመናት
ጣር ካየ በኋላ የዚህ ሁሉ ማብቂያው ምንድነው? ብሎ
ሲያስብ የጌታ መምጣት ነው፡፡ ስለዚህ ማራናታ አለ፡፡
የጌታችን መምጣት የመከራው ድንበር ነው፡፡
በመጀመሪያ ምጽአቱ ሞት ተገደበ፣ በዳግመኛ ምጽአቱ
መከራ ገደብ ያገኛል፡፡
የተስፋችን ፍጻሜ ነው
የምንጠባበቃቸው ብዙ ተስፋዎች ቢኖሩም
ትልቁ ተስፋችን ክርስቶስ ነው፡፡ የምንጠብቃቸው
ነገሮች ቢሆኑልን እንኳ ሌላ መመኘታችን አይቀርም፡፡
ክርስቶስ ከመጣልን ግን ምንም እስከማያምረን
ለዘላለም ያረካናል። ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “የተባረከው
ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና
የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ክብር መገለጥ
እየጠበቅን ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ
እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር
ያስተምረናል” (ቲቶ. 2÷12-13) ይላል፡ ሰዎች ተስፋ
ካላቸው ራሳቸውን ከሚጎዳ ነገር ይከላከላሉ፡፡
እንዲሁም ክርስቶስ ተስፋቸው የሆነ ይቀደሳሉ፡፡
በኃጢአት መጫወት ተስፋ መቁረጥ ነው፡፡ የክርስቶስ
ምጽአት የተስፋችን ፍጻሜ ነው፡፡ ለቤተ ክርስቲያን
የቀረላት ተስፋ የክርስቶስ መምጣት ነው፡፡
የእምነታችን ክብር ነው
ጌታችን ዳግመኛ የሚመጣው በናቀን ዓለም
ፊት እምነታችንን ሊያከብር ነው፡፡ የዘበቱብንና
ያስጨነቁን ለዘላለም ያፍራሉ፡፡ ዛሬ ቃሉን የረገጡ፣ ያን
ቀን ፍርዱን መርገጥ አይችሉም፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች
የሆንም በዚያን ቀን በዘላለም ክብር ተውበን በጉን
እረኛችን አድርገን ወደ ፍስሐ ዓለም እንገባለን፡፡
የአዲስ ዓለም ጅማሬ ነው
በዮሐንስ ራእይ ላይ እንደ ተጻፈው “አዲስ
ሰማይና አዲስ ምድርን አየሁ ፊተኛው ሰማይና
ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፤ ባሕርም ወደፊት የለም”
ይላል (ራእ. 21÷1)፡፡ አዲስ ነገር የሚያስፈልገው
ፊተኛው ሲያረጅ ነው። ያረጀ ነገር መልኩ የወየበ፣
ጉልበቱ ያለቀ፣ ወደፊት ሊጠቅም የማይችል ነው፡፡
አሁን ፍጥረት አርጅቷል፡፡ በረዶ እየቀለጠ፣ የምድር
ሙቀት እየጨመረ፣ መሬቱ ማዳበሪያ እየፈለገ፣ ሰውም
በብዙ መድኃኒት እየኖረ ነው። ይህ የማርጀት ምልክት
ነው፡፡ ይህን አዲስ የሚያደርገው የክርስቶስ መምጣት
ነው፡፡ ሰውም ሞት ላይዘው በትንሣኤ፣ የሚመጣው
ዓለምም ማርጀት ላያገኘው በአዲስነት ይኖራል፡፡
የዘላለም ሕይወት መክፈቻ ነው
ጌታችን ሲመጣ ዘላለማዊት የምትሆን
መንግሥተ ሰማያት ትከፈታለች፡፡ ዛሬ በክርስቶስ ያመኑ
በበጎ ሥራ የፀኑ አማንያን በጊዜያዊ ማረፊያቸው
በገነት ይኖራሉ፡፡ ገነት ጊዜያዊ የነፍሶች ማረፊያ ናት፡፡
ክርስቶስ ሲመጣ ገነትና ሲኦል ያልፋሉ፡፡ መንግሥተ
ሰማያትና ገሀነመ እሳት ይከፈታሉ (ማቴ.
25÷34.41)፡፡
የዘላለም ዘመንም ይከፈታል፡፡ ዘወትር አዲስ
የሆነውን ጌታ እያየን በዘላለም ደስታ እንኖራለን፡፡
የጌታችን መምጣት ብዙ ትርፎች ያሉት ወደማይነገርም
ክብር የምንገባበት ነው፡፡ ዛሬ በዓለም ላይ የምናየው
መከራና ሰቆቃ የምጽአቱ ዋዜማ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ጭንቅ
በክርስቶስ መምጣት ይጠናቀቃል፡፡ “አሜን፣ ጌታ
ኢየሱስ ሆይ፣ ቶሎ ና” /ራእ.22÷20/።

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ: ደብረ ዘይት

3 እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ
ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው። ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል?
የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው?
አሉት።
4 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። ማንም እንዳያስታችሁ
ተጠንቀቁ።
5 ብዙዎች። እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤
ብዙዎችንም ያስታሉ።
6 ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን
ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና
ነው።
7 ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ
ይነሣልና፥ ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ
ስፍራ ይሆናል፤
8 እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።
9 በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል
ይገድሉአችሁማል፥ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ
ትሆናላችሁ።
10 በዚያን ጊዜም ብዙዎች ይሰናከላሉ እርስ በርሳቸውም
አሳልፈው ይሰጣጣሉ እርስ በርሳቸውም ይጣላሉ፤
11 ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ፤
12 ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር
ትቀዘቅዛለች።
13 እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።
14 ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት
ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፥ በዚያን ጊዜም መጨረሻው
ይመጣል።
15 እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋትን ርኩሰት
በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፥
16 በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ፥
17 በሰገነትም ያለ በቤቱ ያለውን ሊወስድ አይውረድ፥
18 በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው
አይመለስ።
19 በዚያችም ወራት ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው።
20 ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን
ጸልዩ፤
21 በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ
ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና።
22 እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር፤
ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለ ተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ።
23 በዚያን ጊዜ ማንም። እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ ወይም።
ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፤
24 ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥
ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ
ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ።
25 እነሆ፥ አስቀድሜ ነገርኋችሁ።
26 እንግዲህ። እነሆ፥ በበረሀ ነው ቢሉአችሁ፥ አትውጡ፤ እነሆ፥
በእልፍኝ ነው ቢሉአችሁ፥ አትመኑ፤
27 መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥
የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና፤
28 በድን ወዳለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ።
29 ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ
ይጨልማል፥ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፥ ከዋክብትም
ከሰማይ ይወድቃሉ፥
30 የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ
ምልክት በሰማይ ይታያል፥ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ
ዋይ ዋይ ይላሉ፥ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ
ደመና ሲመጣ ያዩታል፤
31 መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፥
ከሰማያትም ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ለእርሱ
የተመረጡትን ይሰበስባሉ።
32 ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ
ቅጠልዋም ሲያቈጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ
ታውቃላችሁ፤
33 እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ
እወቁ።
34 እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ
አያልፍም።
35 ሰማይና ምድር ያልፋሉ፥ ቃሌ ግን አያልፍም።
36 ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር
የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም።
37 የኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ
ይሆናልና።
38 በዚያች ወራት ከጥፋት ውኃ በፊት፥ ኖኅ ወደ መርከብ
እስከገባበት ቀን ድረስ፥ ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡም እንደ
ነበሩ፥
39 የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ
እንዳላወቁ፥ የሰው ልጅ መምጣት ደግሞ እንዲሁ ይሆናል።
40 በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል
አንዱም ይቀራል፤
41 ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዲቱ ትወሰዳለች
አንዲቱም ትቀራለች።
42 ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ
ንቁ።
43 ያን ግን እወቁ፤ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል ሌባ
እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ በነቃ ቤቱም ሊቈፈር ባልተወም
ነበር።
44 ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፥ የሰው ልጅ
በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።
የማቴዎስ ወንጌል 24 : 3-44