ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

Wednesday, May 11, 2016

=>+*"ግንቦት 3"*+

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
አሜን
ግንቦት 3
+ ጌታችን ከመረጣቸው ከሰባ ሁለቱ አርድእት ውስጥ አንዱ
የሆነውና ቅዱስ ጳውሎስ በጠርሴስ አገር ላይ ኤጲስቆጶስነት
የሾመው ሐዋርያው ቅዱስ ያሶን ዕረፍቱ ነው፡፡
+ ሰማዕቱ አባ ብሶይ ሰማዕትነቱን በድል ፈጸመ፡፡
+ ‹‹የንጉሥ ወግና ሰገድ እናቱ የሆነች የተባረከች ንግሥት ወለተ
ማርያም›› ዕረፍቷ መሆኑን ስንክሳሩ በስም ይጠቅሳታል፡፡
እርሷም በምግባር፣ በሃይማኖትና በመንፈሳዊ ተጋድሎ
የከበረችና የተመሰገነች ናት፡፡
+ + + + + + + + + + + + + + +
ሰማዕቱ አባ ብሶይ፡- ይኽንንም ቅዱስ ክፉዎችና ጣኦት
አምላኪዎች ይዘውት ሰውነቱን በማጣመምና በመቆልመም
ብዙ አሠቃዩት፡፡ የእግዚአብሔርም መልአክ በእጁ አክሊል ይዞ
‹‹አትፍራ ጽና፣ እነሆ በእጄ ውስጥ አክሊል አለ›› አለው፡፡
ደግሞም ብዙ ካሠቃዩት በኋላ ወደ እሳት ውስጥ ጨመሩት፡፡
ጌታችንንም በማመን እስከመጨረሻው ጸንቶ ተጋድሎውንም
በዚኹ ፈጸመ፡፡ መልአኩም አስቀድሞ አሳይቶ ተስፋ
እንደሰጠው የሰማዕትነት አክሊልን አቀዳጀው፡፡ የሰማዕቱ
የቅዱስ ብሶይ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡
+ + + + + + + + + + + + + + +
ሐዋርያው ቅዱስ ያሶን፡- ይኽም ቅዱስ ሐዋርያ ከከበሩ
ሐዋርያት ጋራ ወንጌልን በሰበከ ጊዜ ብዙ አሠቃቂ መከራዎችን
በጌታችን ስም ተቀበለ፡፡ በ50ኛው ቀን ከሐዋርያት ጋራ አጽናኝ
መንፈስ ቅዱስን ተቀብሏልና ድንቅ ድንቅ የሆኑ ብዙ
ተአምራትን አደረገ፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ያሶን ትውልዱ ከጠርሴስ አገር ነው፡፡
ጠርሴስም ሰዎች አስቀድሞ በወንጌል ያመነው እርሱ ነው፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከተጠራና ካመነ በኋላ ወንጌልን ዞሮ
ሲሰብክ ቅዱስ ያሶን ተከትሎት በብዙ አገሮች በወንጌል
ትምህርት አገልግሎታል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ያሶን
በተሰሎንቄ ከተማ ወንጌልን ሲሰብኩ ክፉዎች ይዘዋቸው
እየጎተቱ ወስደው ከተሰሎንቄ አገር ገዥ ፊት አቅርበዋቸዋል፡፡
ከዚህም በኋላ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ቅዱስ ያሶንን
በጠርሴስ አገር ላይ ኤጲስቆጶስነት ሾመው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ
ያሶንም ቤተ ክርስቲያንን በመልካም አጠባበቅ ጠበቃት፡፡
ምእመናንን በቀናች ሃይማኖት ካጸናቸውና በበጎ ምግባር
ካነጻቸው በኋላ ወደ ምዕራብ አገር ሄዶ በዚያ ወንጌልን ሰበከ፡፡
ስሟ ኮራኮራስ ወደምትባል ደሴትም ገብቶ በውስጧ ወንጌልን
ሰብኮ ነዋሪዎቿን እግዚአብሔርን ወደማመን መለሳቸው፡፡
በደሴቷም ውስጥ በዲያቆናት አለቃ በሰማዕቱ በቅዱስ
እስጢፋኖስ ስም ቤተ ክርስቲያን ሠራላቸው፡፡ የአገሪቱ ገዥም
ይኽንን ባወቀ ጊዜ ቅዱስ ያሶንን ይዞ ከእሥር ቤት ጣለው፡፡
ሐዋርያው ግን በእሥር ቤት ያገኛቸውን ሰባት ኃይለኛ
ወንበዴዎችን አስተምሯቸው ካሳመናቸው በኋላ አጠመቃቸው፡፡
እነርሱም በከሃዲው መኮንን ፊት በጌታችን ታመኑ፡፡ ‹‹በቅዱስ
ያሶን አምላክ እናምናለን›› ብለውም በጮኹ ጊዜ መኮንኑ
ዝፍጥና ድን በተመላ ምጣድ ውስጥ አግብቶ አቃጠላቸው፡፡
የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበሉ፡፡ ረድኤት በረከታቸው
ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን፡፡
ከዚኽም በኋላ መኮንኑ ቅዱስ ያሶንን ከእሥር ቤት አውጥቶ ብዙ
አሠቃየው ነገር ግን ጌታችን መከራውን ያስታግስለት ነበርና
ምንም እንዳልነካው ሆነ፡፡ በተአምራቱም ብዙዎችን
አሳመናቸው፡፡ የንጉሡም ሴት ልጅ ከቤቷ መስኮት ሆና አይታ
በክብር ባለቤት በጌታችን አመነች፡፡ ልብሶቿንና ጌጦቿንም ሁሉ
አውጥታ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች ሰጠችና በሐዋርያው
በቅዱስ ያሶን አምላክ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ
ክርስቶስ ስም ታመነች፡፡ ንጉሡ አባቷም ይኽንን በሰማ ጊዜ
ይዞ አሠራት፡፡ ጌታችንንም በማመን ስለጸናች አባቷ ብዙ
ሥቃጦችን አደረሰባት፡፡ በጢስ አፍኖ አሠቃያት፣ ልብሷን
አውልቆ ካራቆታት በኋላ ሰውነቷን በፍለጻ ነደፋት እርሷም
በዚሁ ሰማዕትነቷን ፈጽማ ነፍሷን ለእግዚአብሔር ሰጠች፡፡
ረድኤት በረከቷ ይደርብን፣ በጸሎቷ ይማረን፡፡
ከዚኽም በኋላ ሐዋርያው ቅዱስ ያሶንን አሠቃይተው ይገድሉት
ዘንድ ከአንድ መኮንንና ከሠራዊቱ ጋራ ወደ ደሴት ሰደደው፡፡
መኮንኑም በመርከብ ወደዚያ በሄደ ጊዜ እግዚአብሔር
መኮንኑን ከነሠራዊቱ አሰጠመው፡፡ ቅዱስ ያሶንም ወንጌልን
ተዘዋውሮ እየሰበከ ብዙ ዘመናት ኖረ፡፡ ሁለተኛም ሌላ መኮንን
በተሾመ ጊዜ ቅዱስ ያሶንን ይዞ በምጣድ ውስጥ ድኝና ዝፍጥ
ሰም መልቶ ነበልባሉ ወደላይ እስኪወጣ ድረስ ከሥሩ አነደደና
ሐዋርያውን በውስጡ ጨመረው፡፡ ነገር ግን የክብር ባለቤት
ጌታችን አገልጋዩን ያለምንም ጉዳት አዳነው፡፡ መኮንኑም
ይኽንን ድንቅ ሥራ ባየጊዜ በክብር ባለቤት በጌታችን በኢየሱስ
ክርስቶስ ስም አመነ፡፡ ቤተሰቦቹና የአገሪቱ ሰዎችም ሁሉ
አብረው አመኑ፡፡ ቅዱስ ያሶንም አጠመቃቸው፡፡ ቤተ
ክርስቲያንም ከሠራላቸው በኋላ የከበረች የወንጌልን ሕግና
ትእዛዝ ሠራላቸው፡፡ እነርሱም በምግባር በሃይማኖት ጸኑ፡፡
ሐዋርያውም ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን አደረገላቸው፡፡
መልካም የሆነውን አገልግለቱንም ፈጽሞ በበጎ ሽምግልና ሆኖ
በዚኽች ዕለት ዐረፈ፡፡ የሐዋርያው የቅዱስ ያሶን ረድኤት በረከቱ
ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡

No comments:

Post a Comment