ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

Monday, May 2, 2016

+*" ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ሐዋርያዊ "*+

+*" ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ሐዋርያዊ "*+
=>ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያን
ዐይን ናቸው:: ጻድቁን መንካት የቤተ ክርስቲያንን ዐይኗን
መጠንቆል ነው::
+ተክለ ሃይማኖት እንደ ሊቃውንት ሊቅ: እንደ ሐዋርያት ሰባኬ
ወንጌል: እንደ ሰማዕታት ብዙ ግፍ የተቀበሉ: እንደ ጻድቃን
ትሩፋት የበዛላቸው: እንደ ደናግል ንጽሕናን ያዘወተሩ: እንደ
ባሕታውያን ግኁስ: እንደ መላዕክትም ባለ ክንፍ አባት ነበሩ::
ለዚሕ ነው ተክለ ሃይማኖትን የኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያን ዐይኔ
የምትላቸው::
*ልደት*
=>መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራልና ተክለ ሃይማኖትን
የወለዱት ደጋጉ: ጸጋ ዘአብ ካህኑና እግዚእ ኃረያ ናቸው:: እርሱ
በክህነቱ: እርሷ በደግነቷ: በምጽዋቷ ጸንተው ቢኖሩ
እግዚአብሔር ጣፋጭ ፍሬን ሰጥቷቸዋል::
+በዳሞቱ ገዢ በሞተለሚ አደጋ ቢደርስባቸው ቅዱስ ሚካኤል:
ጸጋ ዘአብን ከሞት: እግዚእ ኃረያን ከትድምርተ አረሚ
(ከአረማዊ ጋብቻ) አድኗቸዋል:: በሁዋላም የቅዱሱን መወለድ
አብስሯቸዋል::
+ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የጸነሱት መጋቢት 24 ቀን
በ1206 ዓ/ም ሲሆን የተወለዱት ደግሞ ታሕሳስ24 ቀን
በ1207 ዓ/ም ነው:: በተወለዱበት ቀንም ብዙ ተአምራት
ተገልጸዋል:: ቤታቸውም በበረከት ሞልቷል::
*ዕድገት*
=>የጻድቁ የመጀመሪያ ስማቸው "ፍሥሃ ጽዮን" ይሰኛል::
ይሕንን ስም ይዘው: አባታቸው ጸጋ ዘአብን ተከትለው
አድገዋል:: በተለይ ቅዱሳት መጻሕፍትን (ብሉያት: ሐዲሳትን)
ተምረዋል:: በሥጋዊው ጐዳናም ብርቱ አዳኝ እንደ ነበሩ
ይነገራል:: ዲቁናም ከወቅቱ ዻዻስ አባ ጌርሎስ ተቀብለዋል::
*" መጠራት "*
=>አንድ ቀን ፍሥሃ ጽዮን ለአደን ወጥቶ ሲያነጣጥር ድንገት
ከሰማይ አስደንጋጭ ድምጽ ተሰማ:: የክብር ባለቤት ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ አእላፍ መላእክት እያመሰገኑ በሚካኤል ክንፍ
ተቀምጦ ወረደ::
+የወጣቱን አዳኝ ፍርሃቱን አርቆ ጌታችን ተናገረ:: "ከዛሬ
ጀምሮ ስምህ ተክለ ሃይማኖት (ተክለ ሥላሴ) ይሁን:: ከዚህ
በሁዋላ አራዊትን ሳይሆን ነፍሳትን ታድናለህ:: ዘወትር ካንተ
ጋር ነኝ" ብሎ በግርማ ዐረገ:: ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዚህ
ጊዜ በሁዋላ ሰዓትን አላጠፉም:: ንብረታቸውን ለነዳያን በትነው
በትር ብቻ ይዘው ቤታቸው እንደ ተከፈተ ወደ ምናኔ ወጡ::
*" አገልግሎት "*
=>ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዻዻሱ ቅስና ተቀብለው የወንጌል
አገልግሎትን ጀመሩ:: በመጀመሪያ ስብከታቸው እዚያው ሽዋ
(ጽላልሽ) አካባቢ ብቻ በ10ሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳምነው
አጠመቁ:: ያን ጊዜ ኢትዮዽያ 2 መልክ ነበራት::
+1ኛ ዮዲት (ጉዲት) በፈጠረችው ጣጣና በእስላሞች ተጽዕኖ
ወደ ደቡብ አካባቢ ያለው ነዋሪ አንድም ሃይማኖቱን ክዷል:
ወይም በባዕድ አምልኮ ተጠምዷል::
+2ኛው ደግሞ በዛግዌ ነገሥታት ጥረት ክርስትናና ምናኔ
ተነቃቅቶ ነበር::
+ግማሹ ሃገር በጨለመበት ወቅት የደረሱት ሐዲስ ሐዋርያ
አባ ተክለ ሃይማኖት በወጣት ጉልበታቸውና በኃይለ መንፈስ
ቅዱስ ብዙ ቦታዎችን አደረሱ:: ሕዝቡን: መሣፍንቱን ወደ
ሃይማኖት መልሰው: ማርያኖችን (ጠንቁዋዮችን)
አጥፍተዋል::
*" ገዳማዊ ሕይወት "*
=>ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት በወንጌል ብርሃን ኢትዮዽያን
ከማብራታቸው ባለፈ ገዳማዊ ሕይወትንም አስፋፍተዋል::
እርሳቸው ከሁሉ የተሻሉ ሳሉም በ3 ገዳማት በረድዕነት
አገልግለዋል::
+እነዚህም በአቡነ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም ለ12 ዓመታት:
በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ ገዳም ለ7 ዓመታት: በደብረ ዳሞ
ከአቡነ ዮሐኒ ጋር ለ7 ዓመታት: በአጠቃላይ ለ26 ዓመታት
አገልግለዋል::
+በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ከመነኮሱ በሁዋላም ወደ ምድረ ሽዋ
(ዞረሬ) ተመልሰው በአንዲት በዓት ውስጥ ለ22 ዓመታት
ቆመው ጸልየዋል:: በተሰበረ እግራቸውም 6 ጦሮችን በግራና
በቀኝ ተክለው ለ7 ዓመታት ጸልየዋል::
*ስድስት ክንፍ*
=>ኢትዮዽያዊው ጻድቅና ሐዋርያ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት
ከኢትዮዽያ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው ከቅዱሳት መካናት
ተባርከዋል:: ጻድቁ ምድረ እሥራኤል የገቡት በየመንገዱ
መንፈሳዊ ዘርን እየዘሩ: እያስተማሩና እያሳመኑ ነበር::
+የወቅቱ ሊቀ ዻዻሳት አባ ሚካኤል ጋርም ተገናኝተው
ቡራኬን ተሰጣጥተዋል:: ዋናው ጉዳይ ግን ከዚህ በሁዋላ ነው::
ጻድቁ እመቤታችንና ጌታችን ከጽንሰታቸው እስከ ዕርገታቸው
የረገጧቸውን ቦታዎች ሲመለከቱ በፍጹም ተደሞ እንባቸው
ይፈስ ነበር::
+ምክንያቱም እግዚአብሔር ስላበቃቸው ተክለ ሃይማኖት
የሚያዩት ቦታውን አልነበረም:: በገሃድ:-
-በቤተ መቅደስ ብስራቱን
-በቤተ ልሔም ልደቱን
-በቤተ ዮሴፍ ግዝረቱን
-በፈለገ ዮርዳኖስ ጥምቀቱን
-በቤተ አልዓዛር ተአምራቱን ይመለከቱ ነበር::
+የጉብኝታቸው የመጨረሻ ክፍል ወደ ሆነው ቀራንዮ ደርሰው
ጌታቸውን እንደ ተሰቀለ ሆኖ ቢመለከቱት ከዓይናቸው ይፈስ
የነበረው ቁጡ እንባ መልኩን ቀየረና ዓይናቸው ጠፋ::
በዚያች ቅጽበት ስም አጠራሯ የከበረ እመቤታችን ድንግል
ማርያም ፈጥና ደርሳ ተክልየን ወደ ሰማይ አሳረገቻቸው::
+በዚያም:-
*የብርሃን ዐይን ተቀብለው
*6 ክንፍ አብቅለው
*የወርቅ ካባ ላንቃ ለብሰው
*ማዕጠንተ ወርቁን ይዘው
*ከ24ቱ ካህናተ ሰማይም ተደምረው
*ሥላሴን በአንድነቱና ሦስትነቱ ተመልክተው
*"ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ ይደሉ" ብለው መንበረ
ጸባኦትን አጥነው ወደ መሬት ተመልሰዋል::
*ተአምራት*
=>የተክልየ ተአምራት እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ነው::
*ሙት አንስተዋል
*ድውያንን ፈውሰዋል
*አጋንንትን አሳደዋል
*እሳትን ጨብጠዋል
*በክንፍ በረዋል
*ደመናን ዙፋን አድርገዋል::
+ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው ደብረ ሊባኖስን
መሥርተዋል:: በዚያም ሴትና ወንድ መነኮሳት እንደ ሕጻናት
አብረው ኑረዋል:: በዘመናቸው ሰይጣን ታሥሯልና::
*ዕረፍት*
=>ጻድቅ: ሰማዕትና ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ብርሃን
ሆነው መከራን በብዙ ተቀብለው: እልፍ አእላፍ ፍሬን
አፍርተው: በተወለዱ በ99 ዓመት: ከ8 ወር: ከ1 ቀናቸው
ነሐሴ 24 ቀን በ1306 ዓ/ም ዐርፈዋል:: ጌታ: ድንግል
ማርያምና ቅዱሳን ከሰማይ ወርደው ተቀብለዋቸዋል:: 10
ትውልድ የሚያስምር ቃል ኪዳንም ተቀብለዋል::
=>አምላከ ቅዱሳን ከጻድቁ አባታችን በረከትን ይክፈለን::
=>+"+ በረከት በጻድቅ ሰው ራስ ላይ ነው:: የኀጥአንን አፍ
ግን ግፍ ይከድነዋል:: የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው::
የኀጥአን ስም ግን ይጠፋል:: +"+ (ምሳሌ 10:6)
<ወስብሐት ለእግዚአብሔር>

+*" ማዕዶት "*+

=>+"+ እንኩዋን ለዕለተ "ማዕዶት" እና ለቅዱስ "ፃና
ሰማዕት" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ +"+
+*" ማዕዶት "*+
=>ማዕዶት ማለት (ዐደወ-ተሻገረ) ከሚል የግእዝ ግስ
የተወረሰ ሲሆን በጥሬው "መሻገር" ማለት ነው:: ይሕም
በደመ ክርስቶስ ተቀድሰን: በትንሳኤውም ድኅነት ተደርጐልን
መከራን: መርገምን: የኃጢአትን ባሕር: አንድም ባሕረ እሳትን
መሻገራችንን ያመለክታል::
+ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከበረ ደሙ
*ከባርነት ወደ ነጻነት
*ከጨለማ ወደ ብርሃን
*ከሞት ወደ ሕይወት
*ከኃጢአት ወደ ጽድቅ
*ከሲዖል ወደ ገነት
*ከገሐነመ እሳት ወደ መንግስተ ሰማያት
አዳምንና እኛን ልጆቹን አሸጋግሮናል::
+አባታችን አዳምና ልጆቹ ከሲዖል የወጡት በዕለተ ዐርብ
በሠርክ ቢሆንም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዚሕ ዕለት
እዲታሰብ ታዛለች::
+ጌታችን ምርኮን ማርኮ: ጥጦስ መንገድ ጠራጊ ሆኖለት ወደ
ገነት ሲያስገባቸው ለድንግል ማርያም አሳይቷታል:: እመ
አምላክም በፍጹም ልቧ ደስ ተሰኝታለች:: አዳምና ልጆቹ
እመቤታችንን ከላይ ሆነው እጅ ነስተዋታል:: እርሷ
የድኅነታቸው ምክንያት ናትና::
=>አማናዊው ብርሃን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ጨለማችንን
በምሕረቱ ያብራልን::
=>+"+ ክርስቶስም እኮ ስለ ሰው ኃጢአት አንድ ጊዜ
ሞቶአል:: ኃጢአት የሌለበት ክርስቶስ ጻድቁ ስለ እኛ ሞተ:: ስለ
ኃጢአታችን እኛን ወደ እግዚአብሔር ያቀርበን ዘንድ::
በሥጋ ሞተ: በመንፈስ ግን ሕያው ነው:: ነፍሳቸው ታስራ ወደ
ነበረችበት ሔደ:: ቀድሞ ክደውት ለነበሩት ነጻነትን
ሰበከላቸው:: +"+ (1ዼጥ. 3:18)
+*" ቅዱስ ፃና "*+
=>በቤተ ክርስቲያናችን በዚህ ስም የሚጠሩ ቅዱሳን አሉ:: ዛሬ
የምናከብረው ሰማዕቱ ቅዱስ ፃና:-
*በዘመነ ሰማዕታት የነበረ:
*ቅዱስ ኤስድሮስ የሚባል ደግ ጉዋደኛ የነበረው:
*ሁለቱንም እናቶቻቸው እንደሚገባ ያሳደጉዋቸው የ3ኛው መቶ
ክ/ዘመን ክርስቲያኖች ነበሩ::
+በወጣትነት ዘመናቸው በድንግልና: ቅዱስ ፃና የሠራዊት
አለቃ: ቅዱስ ኤስድሮስ ደግሞ የልብስ ዝግጅት ባለሙያ ነበሩ::
ከሚያገኙት ገቢ ለዕለት ጉርስ ብቻ እያስቀሩ ለነዳያን
ይመጸውቱ ነበር::
+በመከራ ዘመን (ዘመነ - ሰማዕታት) ቅዱሳኑ ያላቸውን ሁሉ
ለነዳያን አካፍለው በክርስቶስ ስም መሞትን መርጠዋል::
አስቀድሞ ቅዱስ ኤስድሮስ አንገቱን ተሰይፎ የክብርን አክሊል
ተቀዳጅቷል::
+ሰማዕቱ ቅዱስ ፃና ባልንጀራው ኤስድሮስ ከተገደለ በሁዋላ
ለ36 ቀናት በጨለማ እሥር ቤት ውስጥ ከብዙ ስቃይ ጋር
ቆይቷል:: መከራን ቢያፀኑበትም በሃይማኖቱ ጽኑ ነበርና
እርሱንም በዚሕች ቀን ገድለውታል::
+ደግ እናቱ በቦታው ነበረችና መላዕክት በክብር ነፍሱን
ሲያሳርጉ ተመልክታለች::
=>ፈጣሪ ከሰማዕቱ ክብር ያድለን::
=>ሚያዝያ 24 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ፃና ሰማዕት
2.አባ ሱንቱዩ ሊቀ ዻዻሳት
3.አባ ይድራ
4.የደብረ ሲና ቅዳሴ ቤት
=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
2.ቅዱስ አጋቢጦስ (ጻድቅ ኤዺስቆዾስ)
3.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
4.ቅዱስ ሙሴ ፀሊም
5.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
6.ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
7."24ቱ" ካኅናተ ሰማይ (ሱራፌል)
8.አቡነ ዘዮሐንስ ጻድቅ (ኢትዮዽያዊ)
=>+"+ ልጆች ሆይ እናንተ ከእግዚአብሔር ናችሁ:
አሸንፋችሁአቸውማል:: በዓለም ካለው ይልቅ በእናንተ ያለው
ታላቅ ነውና:: እነርሱ ከዓለም ናቸው:: ስለዚህ ከዓለም
የሆነውን ይናገራሉ:: ዓለሙም ይሰማቸዋል:: እኛ
ከእግዚአብሔር ነን:: እግዚአብሔርን የሚያውቅ ይሰማናል::
ከእግዚአብሔር ያልሆነ አይሰማንም:: +"+ (1ዮሐ. 4:4)
<ወስብሐት ለእግዚአብሔር>

#ገድለ_ሊቀ_ሰማዕታት_ቅ ዱስ_ጊዮርጊስ

23 23 23 23 23
#ከገድለ_ሊቀ_ሰማዕታት_ቅ ዱስ_ጊዮርጊስ
23 23 23 23 23
እንኳን ለሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ በዓል አደረሳችሁ!!!
23
በጥር 20 ቀን በ277 ዓ.ም ተወለደ። ሀገሩ ፍልስጤም ሲሆን
ልዩ ስሟ ልዳ ይባላል። ጊዮርጊስ ማለት ኮከብ፣ ብሩህ፣
ሐረገወይን፣ ፀሐይ ማለት ነው። አባቱ ዘሮንቶስ (አንስጣስዮስ)
ይባላል ከልዳ መኳንንት ተሹሞ ይኖር ነበር፤ እናቱ ቴዎብስታ
(አቅሌስያ) ትባላለች። ማርታና እስያ የሚባሉ እህቶች ነበሩት።
10 ዓመት ሲሞላው አባቱ ስለሞተ ሌላ ደግ ክርስቲያናዊ
መስፍን ከቤቱ ወስዶ አሳደገው። በጦር ኃይልም አሠለጠነው።
20 ዓመት ሲሞላው የ15 ዓመት ልጅ ሊያጋቡት ሲሉ
እግዚአብሔር የመስፍኑን ነፍስ ወስደ፤ ቅዱስ ዮርጊስም ወደ
ቤሩት ሄደ።
በቤሩት ደራጎን ን ያመልኩና ሴት ልጃቸውን ይገብሩለት ነበርና
በኃይለ መስቀል ድል ነስቶት ህዝቡን ወደ አምልኮተ
እግዚአብሔር አስገብቷቸዋል።
23
ወደፋርስ ቢመለስ ዱድያኖስ ሰባ ነገሥታት ሰብስቦ ሰባ ጣዖታት
አቁሞ
ሲሰግድ ሲያሰግድ ቢያገኛቸው ለሃይማኖቱ ቀናዒ ነውና
ከቤተመንግስቱ
ገብቶ “እኔ ክርስቲያን ነኝ በኢየሱስ ክርስቶስ አምናለሁ”
አለው። እርሱም
ማንነቱን ከተረዳ በኋላ “አንተማ የኛ ነህ በ10 አህጉር ላይ
እሾምሃለሁ
የኔን አምላክ አጵሎንን አምልክ” አለው። ቅዱስ ጊዮርጊስም
“ሹመት
ሽልማትህ ለአንተ ይሁን እኔ አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስን
አልክድም”
አለ። በዚህ ጊዜ እጅግ ተናዶ መከራን አጸናበት እርሱ ግን “ይህን
ከሀዲ
እስካሳፍረው ድረስ ነፍሴን አትውሰድ” በማለት እግዚአብሔርን
የለመነና
እንደጸሎቱ የተደረገለት። በእምነቱም ጽናት የሰው ልጅ
ሊሸከም
የማይችለውን መከራ የተቀበለ ቅዱስ አባት ነው። ከእነዚህም
መከራዎች
ውስጥ:-
-
1. በእንጨት አስቀቅሎ ሥጋውን በመቃን አስፈተተው
2. ረጃጅም ችንካሮች ያሉበት የብረት ጫማ አጫምቶት ሂድ
አለው።
ቅዱስ ሚካኤልን ልኮለት ፈውሶታል።
3. በሰባ (70) ችንካር አስቸንክሮ በእሳት አስተኩሶ አናቱን
በመዶሻ
አስቀጥቅጦ በሆዱ ላይ የደንጊያ ምሰሶ አሳስሮ
እንዲያንከባልሉት
አደረገ።
4. ሥጋውን በመጋዝ አስተልትሎ ጨው ነስንሶበት ሥጋው
ተቆራርጦ
ወደቀ። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈቀ
ሌሊት
በእጁ ዳስሶ “ገና 6 ዓመት ለስሜ ትጋደላለህ፣ 3 ጊዜ
ትሞታለህ፣ በ4ኛው ታርፋለህ።” አለው።
5. ዱድያኖስ ደንግጦ “የሚያሸንፍልኝ ቢኖር ወርቅ
እሰጠዋለሁ”
ቢል አትናስዮስ የተባለ መሰርይ ከንጉሱ ላምን በጆሮዋ
ሲያንሾካሹክባት ለሁለት ተሰንጥቃ ገድሏት ፈቃድን ተቀበለ።
ሆድ
በጥብጦ አንጀት ቆራርጦ የሚገድል መርዝ ቀምሞ አስማተ
ሰይጣን ደግሞ ሰጠው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን ስመ
እግዚአብሔርን ጠርቶ ቢጠጣው እንደ ጨረቃ ደምቆ እንደ
አበባ
አሸብርቆ ተገኝቷል። ጠንቋዩም ማረኝ ብሎት ከመሬት ውሃን
አፍልቆ ወደ ጌታችን ቢያመለክት ሐዋርያው ቶማስን በመንፈስ
መጥቶ አጥምቆት በሰማዕትነት አርፏል።
6. በመንኮራኩር አስፈጭቶ ከትልቅ ጉድጓድ ጥሎት ደንጊያ
ዘግቶበት አትሞበት ሄዷል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ የተፈጨውን ሥጋ በእጁ ዳስሶ መንፈሱን መልሶ
አንስቶታል፤ ተመልሶም “አምላኬ ከሞት አዳነኝ” ብሏቸዋል።
7. በብረት አልጋ አስቸንክሮ ከበታቹ እሳት አንድዶበታል።
እሳቱም
ደሙ ሲንጠባጠብ ጠፍቷል።
8. ዱድያኖስ “ኢየሱስ አምላክ መሆኑን አሳየኝ” ቢለው
የለመለሙትን ዕፅ አድርቆ፣ የደረቁትን አለምልሞ፣ ከሞቱ
430
ዓመት የሆናቸውን ሙታንን አስነስሰቶ አሳይቶታል። ነገር ግን
ልቡ
ክፉ ነውና በረሀብና በጽም ይሙት ብሎ ምንም ከሌላት መበለት
ቤት አሳስሮታል። እርሷም የሚቀመስ ስትፈልግ ቤቷን በእህል
አትረፍርፎ የታሰረበት ግንድ አፍርቶ ልጇ ጆሮው የማይሰማ
ነበርና
ፈውሶላት መበለቲቷን ከነልጆቿ አጥምቆ ቅዱስ ሚካኤል
ከእስራቱ
ፈትቶት ተመልሷል።
9. ዳግም በመንኩራኩር ፈጭታችሁ ደብረ ይድራስ ወስዳችሁ
ዝሩት
ብሎ አስፈጭቶ ሥጋውን ቢዘሩት ሥጋው ያረፈበት ሳር፣ ቅጠሉ፣
ደንጊያው፣ እንጨቱ ሁሉ “ጊዮርጊስ ቅዱሱ ለእግዚአብሔር፣
ጊዮርጊስ ሰማዕቱ ለእግዚአብሔር፣” እያሉ አመስግነዋል።
ጌታችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለሦስተኛ ጊዜ ከሞት
አስነስቶታል። ሔዶም “አምላኬ ከሞት አዳነኝ” አላቸው።
ጭፍሮቹ ደንግጸው ከእግሩ ስር ወደቁ። ከመሬት ውሃ
አመንጭቶ
ቅዱስ ዮሐንስ አጥምቋቸዋል።
10. “ንጉሡ ልሹምህ ለአጵሎን ስገድ” ብሎ ቢለምነው እሺ
ብሎ
ገብቶ ሲጸልይ የንጉሱ ሚስት እለእስክንድርያ “ምን እያልክ
ነው?”
ብትለው አስተምሯት አሳምኗታል። ሲነጋ ንጉሱ በአዋጅ ህዝብን
አሰብስቦ “ጊዮርጊስ ለጣዖቴ ሊሰግድ ነው’ ብሎ በተሰበሰበ
ህዝብ መካከል አንድን ብላቴና (የመበለቷን ልጅ) “የክርስቶስ
ኢየሱስ አገልጋይ ጊዮርጊስ ይጠራሃል” በል ብሎ ወደጣዖቱ
ቢልከው ጣዖቱ ላይ ያደረው ሰይጣን እየጮኸ ቅዱስ ጊዮርጊስ
ያለበት ቦታ መጣ፤ አምላክ አለመሆኑን አናዞት መሬት ተከፍታ
እንድትውጠው አደረገ። ብዙ ሰዎች ይህንን ተዓምር አይተው
አመኑ። ንጉሱን ሚስቱ እንዲመለስ ብትነግረው በአደባባይ
አሰቅሎ አሰይፏት ሞታለች ደሟን ጥምቀት አድርጎላት ሰማዕት
ሆናለች።
11. በመጨረሻም በሰይፍ እንዲመተር አስደረገ። ቅዱስ
ጊዮርጊስም
ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃልኪዳን
ተገብቶለታል።
። ። ። ። ። ። ።
- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ: ሰባት አክሊላትን አቀዳጅቶታል።
- ጌታችን: አባቴ ስምህን በሠረገላ መንፈስ ቅዱስ ጽፎታልና
አምላከ ጊዮርጊስ እርዳኝ የሚለውን ሁሉ እኔ ፈጥኜ
እሰማዋለሁ አለው።
- ጌታችን ወንድም ሴትም ቢሆኑ በችግር ላይ ሆነው እጅግ
ተስፋ ቢቆርጡ: ይልቁንም የሰዎች ልጆች በሚያዙንበት በጽኑ
መከራ ቢወድቁ በቅዱስ ስምህ ተማጥነው:- ሦስት ጊዜ
አምላከ ጊዮርጊስ ርዳን:
አምላከ ጊዮርጊስ ርዳን:
አምላከ ጊዮርጊስ ርዳን: እያሉ ወደኔ ቢጮሁ ያን ጊዜ
ራራላቸዋለሁ ፈጥኜም ለጸሎታቸው መልስ እሰጣቸዋለሁ:
ከልባቸው የለመኑኝን ሁሉ እፈጽምላቸዋለሁ ከመከራቸውም
አድናቸዋለሁ አለው።
-ጌታችን: ስለ ስሜ የተቀበልከውን መከራ: ያገኘህን ድካም
ገድልህን የሚናገረውን መጽሐፍ የሚጽፈውን ሁሉ ስሙን
በሕይወት መጽሐፍ እጽፈዋለሁ ኃጢአቱንም አስተሰርይለታለሁ
በመንግሥተ ሰማያትም ያንተ ልጅ አደርገዋለሁ: ለዘለዓለም
በአንድነት ከአንተ ጋር አኖረዋለሁ አለው።
- ጌታችን: በሃይማኖት ወንድ ልጁን: ሴት ልጁን በስምህ
የጠራውን እኔ እባርከዋለሁ: ለዘለዓለም ከርሱ ጋር እኖራለሁ
ልቡን ደስ አሰኘዋለሁ አለው።
- ጌታችን: ለቤተክርስቲያን ዕጣን: መብራት: ስንዴ: ወይን
የሚሰጥ በስምህ ለተራበ የሚያበላ: ለተጠማ የሚያጠጣ
የከበረችውን የመታሰቢያህን ቀን የሚያከብረውን እኔ በዚህ
ዓለም እረዳዋለሁ: በሚመጣውም ዓለም ከአንተ ጋር
በመንግሥቴ ደስ እንዲለው አደርጋለሁ። በስምህ ለተራቆተ
የሚያለብሰውን እኔ የክብር ልብስ አለብሰዋለሁ:
ለቤተክርስቲያን በስምህ መብራት የሚያበራውን: ዕጣን
የሰጠውን መላእክት እንዲያበሩለት አደርጋለሁ: ወደ እኔም ደስ
ብሎት ይመጣል። በስምህ እንግዳ የሚቀበለውን እኔ ኃጢአቱን
አስተሰርይለታለሁ: ለዘለዓለም በመንግሥቴ እቀበለዋለሁ።
በስምህ ምጽዋት የመጸወተውን እኔ ከቅዱሳን ጋር
እቆጥረዋለሁ ከዚህ ዓለም ሀብትም ምንም እንዳያጣ
አደርገዋለሁ። እኔ ፈጣሪህ እግዚአብሔር ነኝ ከአንደበቴ
የወጣውን እፈጽማለሁ እንጂ አልለውጥም አለው።
- ሥሉስ ቅዱስ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ፈጥረው በሰባት
አክሊላት ከለሉት በቸርነታቸው የአመነች ነፍስ ሁሉ ከሥጋዋ
በተለየች ጊዜ አስቀድማ ለሥሉስ ቅዱስ ትስገድ ከዚህ በኋላ
ውሰዷትና ለወዳጃችን ለጊዮርጊስ እጅ ትንሣ ብለው ከፍ ከፍ
አደረጉት። ነገር ግን ይህ ሁሉ የተናገርነው ምስጋናው ከክብሩ
ያንሳል ከታላቅ ባሕር አንድ ጭልፋ እንደሚቀዳ ይሆናል የዚህ
ሰማዕት ምስጋናው ክብሩ ብዙ ነውና ጸሎቱና በረከቱ ከ..............
............... ... ለዘለዓለሙ ይኑር አሜን።
። ። ። ። ። ። ።
በ27 ዓመቱ በሚያዝያ 23 ቀን በ9፡00 ሰዓት ሰማዕት ሆኗል።
አንገቱ ሲቆረጥ ውሃ፣ ደም እና ወተት ወጥቷል። ከሊቀ
ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ረድኤት በረከት ይክፈለን!!!
23 23 23
። ። ። ። ። ። ።
#የአድዋ_ድል_ከእግዚአብሔ ር #የተገኘ_ድል_ነው
-
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
አሜን የካቲት 23 ልመናው ጸሎቱ በረከቱ አማላጅነቱ
በዕውነት ይደረግልንና የልዳው ፀሐይ ፍጡነ ረድኤት ቅዱስ
ጊዮርጊስ በጦርነት ላይ ሳለ ሣህለ ማርያምን (ዐፄ ሚኒልክን)
በመርዳት ያደረገው ተአምር ይህ ነው፡
‹‹ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት 1854 ዓመት በኋላ
የኢትዮጵያ ነጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ በነገሠ በ26ኛ
ዓመት የምኒልክ የጦር አለቃ ገበየሁ ድል ካደረጋቸው በኋላ
እንደገና ምኒልክን ወግተው ኢትዮጵያን በቅኝ አገዛዝ ሊገዙ
የሮም ሰዎች መጡ፡፡
ከዚህም በኋላ የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ዐፄ
ምኒልክ
‹አገሬ ኢትዮጵያን እወዳለሁ የሚል ኢትዮጵያዊ ሁሉ በአስቸኳይ
ይነሣ፣
መስቀለ ሞቱንም ተሸክሞ ይከተለኝ፡፡ እግዚአብሔር
የወሰነልንን የባሕር
ወሰን አልፎ አገር የሚያጠፋ፣ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት
መጥቷልና›
ሲል አዋጅ አስነገረ፡፡ ዳግመኛም በፈረሶቻቸው መጣብር ላይ
በጦራቸው
ላይ በጋሻቸው ላይ የመስቀል ምልክት እንዲያደርጉ ወታደሮቹን
አዘዛቸው፡፡ መስቀል ጠላትን ድል አድራጊ እንደሆነ አስቀድሞ
ያውቅ
ነበርና፡፡ ከዚያም ተነሥቶ ወደ ትግራይ ክፍለ ሀገር ዘመተና
ከትግራይ
አውራጃዎች አንዷ የምትሆን አድዋ ከምትባል አገር ደረሰ፡፡
የሣህለ ማርያም (ዐፄ ሚኒልክ) ሚስት ወለተ ሚካኤል (እቴጌ
ጣይቱም) በንጉሡ ትእዛዝ ታቦተ ቅዱስ ጊዮርጊስን አሲዛ ከሊቀ
ጳጳሱ
ከአባ ማቴዎስ እንዲሁም ከቀሳውስቱና ከመነኮሳቱ ጭምር
ከንጉሡ ጋር
ወደ ጦርነቱ ተጓዘች፡፡ በዚያም ጊዜ የአክሱም ጽዮን መነኮሳትና
ካህናት
የእመቤታችንን ሥዕል ይዘው ወደ ንጉሡ ወደ ምኒልክ
መጥተው ከሊቀ
ጳጳሱ ከእነ አቡነ ማቴዎስ ጋር ተቀላቀሉ፡፡ ከዚያም ሌሊቱን
ሙሉ ጸሎተ
ምሕላ ሲያደርሱ አደሩ፡፡ ቅዳሜ ማታ ለእሑድ አጥቢያ
ይኸውም የካቲት
22 ቀን ነው ንጉሡ ሣህለ ማርያም (ዐፄ ሚኒልክ) የጦር
ልብሱን ለብሶ
ከሠራዊቱ ጋር ወደ ጦር ግንባር ሄደ፡፡ ከዚያም ከሮማውያን
የጠላት ጦር
ጋራ ተገናኝቶ ከሌሊቱ በዓሥራ አንድ ሰዓት ጦርነቱን ጀመረ፡፡
የንጉሥ ሣህለ ማርያምን ሚስት ወለተ ሚካኤል (እቴጌ
ጣይቱም) ሌሊት
በታቦተ ቅዱስ ጊዮርጊስና በእመቤታችን ሥዕል ፊት በጸሎትና
በስግደት
እያደረች ሲነጋ ወደ ጦርነቱ ቦታ በመሄድ እጅግ በሚያስደንቅ
የአነጋገሯ
ኃይለ ቃል በጦርነቱ መካከል እየተገኘች ለንጉሡ ወታደሮች
የሞራልና
የብርታት ድጋፍ ትሰጣቸው ነበር፡፡ በዕውነትም ለተመለከታት
ሁሉ
እንደኃይለኛ ተጋዳይ አርበኛ ትመስል ነበረ እንጂ የሴቶች
የተፈጥሮ
ባሕርይ በእርሷ ላይ አይታይባትም ነበር፡፡ የንጉሡም ወታደሮች
የንግሥቲቱን የጀግንነት አነጋገር በሰሙ ጊዜ በእሳት ላይ
እንደተጣደ
የብረት ምጣድ ልባቸው ጋለ፡፡ ይልቁንም ላም እንዳየ አንበሳና
ፍየል
እንዳየ ነብር እየተወረወሩ በጦርነቱ መካከል በመግባት
የጠላትን ጦር
በሰይፍ ይጨፈጭፉት ነበር፡፡ መጽሐፍ ‹ሹመቱን ሽልማቱን ያየ
አርበኛ
ከጦርነት ከሰልፍ ወደኋላ አያፈገፍግም› ብሎ ተናግሯልና፡፡
በዚያንም ጊዜ ንጉሡ ሣህለ ማርያም (ሚኒልክ) በጦርነቱ
መካከል ሳለ
ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ማቴዎስ እንዲሁም የአክሱም መነኮሳት
ሌሎቹ ካህናት
በሙሉ ታቦተ ቅዱስ ጊዮርጊስንና ሥዕለ ማርያምን ይዘው
ከንጉሡ
በስተኋላ በደጀንነት ቆመው ጸሎተ ምሕላ ያደርሱ ነበር፡፡
ንግሥቲቱ
ወለተ ሚካኤል በጸሎት ጊዜ በመዓልትም በሌሊትም ከእነርሱ
አትለይም
ነበር፡፡ የጽዮን አገልጋዮችም በእግዚአብሔር በሕጉ ታቦት ፊት
መለከት
ይነፉ ነበር፡፡ በዚህም ዕለት ይኸውም የካቲት 23 ቀን
በሮማውያንና
በኢትዮጵያውያን መካከል ከፍተኛ ጦርነት ሆነ፡፡ ወዲያውም
በሰማይ
ታላቅ ተአምር ተደረገ፡፡ ይኸውም የቀስተ ደመና ምልክት
ታየ፡፡ ከዚያም
ቀስተ ደመና ውስጥ መልኩ አረንጓዴ የሚመስል ጢስ ይወጣ
ነበር፡፡
ከዚያም ጢስ ውስጥ እንደክረምት ነጎድጓድ ያለ ድምፅ ተሰማ፡፡
ከዚያም
የነጎድጓድ ድምፅ የተነሣ በሮማውያን ወታደሮች ዘንድ ከፍተኛ
ድንጋጤና
ሽብር ሆነ፡፡ ለመዋጋትም አልቻሉም፡፡ ይልቁንም ኃያሉ ገባሬ
ተአምር
ቅዱስ ጊዮርጊስ በአምባ ላይ ፈረስ ተቀምጦ ከነፋስ ሩጫ ይልቅ
እየተፋጠነ በአየር ላይ በተገለጠ ጊዜ በግንባራቸው ፍግም እያሉ
ወደቁ፡፡ ‹የኢትዮጵያ ሕዝብ አምላካቸው ሊረዳቸው መጣ፡፡
እንግዲህ
ማን ያድነናል› አሉ፡፡ ምድር ጠበበቻቸው፡፡ በዚህም ጊዜ
የአትዮጵያ
ሠራዊት የሮምን የጦር ሠራዊት ፈጁዋቸው፡፡ የተረፉትንም
ማረኳቸው፡፡
ፈጽመውም እስኪያጠፏቸው ድረስ በሮማውያን ላይ
በእግዚአብሔር
ሥልጣን የኢትዮጵያውያን እጅ እየበረታች ሄደች፡፡ ከዚህም በኋላ
ንጉሡ
ሣህለ ማርያም በእግዚአብሔር ኃይልና በተአምራት አድራጊው
በቅዱስ
ጊዮርጊስ ተራዳኢነት የሮማውያንን የጦር ሠራዊት በጦርነት
ድል አድርጎ
የድል አክሊል ተቀዳጀ፡፡
23
ስለዚህም ‹በዳዊት የምስጋና ቃል የድል ዘውድ ያቀዳጀኝን
እግዚአብሔርን ባለ ዘመኔ ሁሉ አመሰግነዋለሁ፡፡ ለፈጣሪዬም
እዘምራለሁ› አለ፡፡ ሕዝቡም ሁሉ ‹በክብር ከፍ ከፍ ያለ
እግዚአብሔርን
በፍጹም ምስጋና እናመሰግነዋለን የሮማውያንን ኃይል ቀጥቅጦ
አጥፍቷልና፣ ሠረገሎቻቸውንም ሰባብሯልና፣ ሠራዊቱንም ሁሉ
በምድር
ላይበትኗቸዋልና…› እያሉ አመሰገኑ፡፡ በፈጣሪው በኢየሱስ
ክርስቶስ ኃይል
በጦርነቱ መካከል የረዳቸውን ቅዱስ ጊዮርጊስንም በፍጹም
ማድነቅ
እያደነቁ አመሰገኑት፡፡ የሮማም የጦር ሠራዊት
በኢትዮጵያውያን ፊት
ተዋረዱ፡፡ ዳግመኛም በኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን ከፍ ከፍ
አላደረጉም፡፡
በምኒልክም ዘመነ መንግሥት ኢትዮጵያ ከጦርነት ለ40 ዓመት
ያህል
አረፈች፡፡ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ምኒልክም ከአድዋ ጦርነት
ከተመለሰ
በኋላ አዲስ አበባ በምትባለው ከተማው መካከል በቅዱስ
ጊዮርጊስ
ስም የተዋበች ቤተ ክርስቲያን አሠራ፡፡ ስሟንም ‹ገነተ ጽጌ››
ብሎ
ሰየማት፡፡ ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ በጦርነቱ ሁሉ ይረዳው
ነበርና፡፡
ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን፡፡››
‹‹እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ ጠባቂ በከንቱ ይተጋልና››
ዛሬም
የኢትዮጵያ ገበዝ የአድዋው አርበኛ ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ
ጊዮርጊስ
የዓሥራት አገሩን ቅድስት ኢትዮጵያን ይጠብቅል፡፡ መዝ 127፡
1፡፡ የሰማዕቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተራዳኢነት ከሁላችን ጋር
ይሁን፡፡
23
ምንጭ፡- ገድለ ቅዱስ ጊዮርጊስ
23
የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የድንግል ማርያም አማላጅነት፣
የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣
የቅዱሳን ሐዋርያት፣ የቅዱሳን አበው መነኮሳት፣ የቅዱሳት
አንስት፣ የደናግላንና የቅዱሳን ሁሉ ምልጃና ቃል-ኪዳናቸው
ባለንበት ከሁላችን ጋር ይሁን!!!
†† † ♥ † ††
ለአባ ሕርያቆስ ፤ለቅዱስ ኤፍሬም ፤ለቅዱስ ያሬድ ፤
ለአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የተገለጸች እመቤታችን እኛንም
በበረከት እና በረድኤት ትጎብኘን ፤ ከልጅዋ ከወዳጅዋ
ከመድኃኔዓለም ዘንድ ታማልደን ፤ አሜን!!!
†† † ♥ † ††
ከዋክብት የሚያመሰግኑት በስማቸውም የሚጠራቸው: የፀጋው
ብዛት
የማይታወቅ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ሆይ
ለሐዋሪያት እንዲሁም ለቀደሙ አባቶቻችን ምሥጢሩን
እንደገለጽክላቸው
ለእኛም ግለጽልን። አሜን አሜን አሜን!!!
†† † ♥ † ††
ወ ስ ብ ሐ ት ለ እ ግ ዚ አ ብ ሔ ር
ወ ለ ወ ላ ዲ ቱ ድ ን ግ ል
ወ ለ መ ስ ቀ ሉ ክ ቡ ር

#ትንሣኤ_ዘክርስቶስ - #የክርስቶስ_ትንሳኤ

#ትንሣኤ_ዘክርስቶስ - #የክርስቶስ_ትንሳኤ
✞ ✞ ✞ ✞ ✞
፩ ፥ ፩፦ ሦስት መዓልት እና ሦስት ሌሊት በመቃብር፤
፩ ፥ ፪፦ ሦስት መዓልት እና ሦስት ሌሊት የሞላው እንዴት
ነው?፤
፩ ፥ ፫፦ እንዴት ተነሣ?
፩ ፥ ፬፦ ለምን በአዲስ መቃብር ተቀበረ?
፩ ፥ ፭፦ እንዴት በዝግ መቃበር ተነሣ?
፩ ፥ ፮፦ መቃብሩን ማን ከፈተው?
፩ ፥ ፯፦ በኲረ ትንሣኤ፤
፩ ፥ ፰፦ ከትንሣኤው በኋላ ለምን ተመገበ?
፩ ፥ ፱፦ ለምን አትንኪኝ አላት?
፩ ፥ ፲፦ ተስፋ ትንሣኤ፤
፩ ፥ ፲፩፦ ሙታን እንዴት ይነሣሉ?
፩ ፥ ፲፪፦ የትንሣኤ ጸጋ፤
_እነዚህ ምሥጢራት በሚገባ በስፋት ተዳስሰዋል ይነበብ...
✞ ✞ ✞ ✞ ✞
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
ድኅነተ ዓለምን በመስቀል ላይ ከፈጸመ በኋላ በአካለ ሥጋ ወደ
መቃብር ወረደ÷ ይኸውም በመቃብር ፈርሶ በስብሶ መቅረትን
ሊያስቀርልን ነው፡፡ በአካለ ነፍስ ደግሞ ወደ ሲኦል ወረደ÷
ይኸውም በሲኦል ለነበሩ ነፍሳት ነፃነትን ይሰብክላቸው ዘንድ
ነው፡፡ መለኮት፥ በተዋሕዶ፥ ከሥጋም ከነፍስም ጋር ነበረ፡፡
ለዚህ
ነው፥ መቃብር ሥጋን ሊያስቀረው ያልቻለው፤ ሲኦልም ነፍስን
ማስቀረት አልተቻለውም፡፡ ቅዱስ ዳዊት፡- « ነፍሴን በሲኦል
አትተዋትምና ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተዋትም»
ያለው ይኽንን ታላቅ ምሥጢር በትንቢት ቃል ሲናገር ነው፡፡
መዝ
፲፭÷፲፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም፡- «ክርስቶስ ደግሞ ወደ
እግዚአብሔር (ወደ አብ÷ ወደ ራሱና ወደ መንፈስ ቅዱስ)
እንዲያቀርበን፥ እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ
በኃጢአት ምክንያት (ስለ ሰው ልጆች ኃጢአት ተላልፎ
በመሰጠት) ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ (በፈቃዱ ነፍሱን ከሥጋው
ለየ)÷ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ÷ (ያን ሥጋ ነፍስ
እንድተለየችው መለኰት አልተለየውም)÷ በእርሱም ደግሞ
(መለኰት በተዋሐዳት ነፍስ) ሄዶ በወኅኒ ለነበሩት ነፍሳት
ሰበከላቸው፤» ብሏል።
✞ ✞ ✞
፩ ፥ ፩፦ #ሦስት_መዓልት_እና_ሦስት _ሌሊት_በመቃብር፤

ጌታችን በከርሰ መቃብር የቆየው ሦስት መዓልትና
ሦስት ሌሊት ነው፡፡ «ሥጋዬ ደግሞ በተስፋ ታድራለች፤»
የሚለው ቃለ ትንቢት የሚያረጋግጥልን ይኽንኑ ነው፡፡ መዝ
፲፭፥፱፡፡ ምሥጢራዊ ትርጉሙም «ወደ መቃብር የወረደ
ሥጋዬ
በተስፋ ትንሣኤ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በመቃብር
አደረ፤» ማለት ነው፡፡ ተስፋ ትንሣኤውም በተዋሕዶ ከሥጋ ጋር
ወደ መቃብር የወረደ መለኰት ነው፡፡ ነቢዩ ሆሴዕም፡- «ኑ÷
ወደ
እግዚአብሔር እንመለስ፤ እርሱ ሰብሮናልና÷ (በሞተ ሥጋ ላይ
ሞተ ነፍስን ጨምሮ የፈረደብን እርሱ ነው)÷ እርሱም
ይፈውሰናል፤ (መርገመ ሥጋን መርገመ ነፍስን አስወግዶ ከሞት
ወደ ሕይወት ያሸጋግረናል)፤ እርሱ መትቶናል÷ እርሱም
ይጠግነናል፡፡ ከሁለት ቀን በኋላ ያድነናል፤ በሦስተኛውም ቀን
ያስነሣናል፡፡» በማለት ትንሣኤ ክርስቶስ በሦስተኛው ቀን
መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ሆሴ ፮÷፲፪፡፡ ይልቁንም ጌታችን ራሱ
በመዋዕለ ሥጋዌው፡- ከሽማግሌዎችና ከካህናት አለቆች
ከጻፎችም ብዙ መከራ ይቀበልና ይገደል ዘንድ፥ በሦስተኛውም
ቀን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው ለደቀመዛሙርቱ በግልጥ
ነግሯቸዋል፡፡ ማቴ ፲፮÷፳፩፡፡ በገሊላም ሲመላለሱ፡- «ወልደ
ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስ በሰዎች እጅ አልፎ ይሰጥ ዘንድ
አለው÷ ይገድሉትማል÷ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል፤»
ብሏቸዋል፡፡ ማቴ ፲፯÷፳፡፡ ጻፎችና ፈሪሳውያንም ምልክት
በጠየቁት ጊዜ፡- «ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል÷
ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም፡፡ ዮናስ
በዓሣ አንበሪ ሆድ፥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደነበረ÷
እንዲሁ የሰው ልጅ (ወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስ) በምድር
ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል፡፡» ብሏቸዋል፡፡ ማቴ
፲፪፥፴፰-፵።
✞ ✞ ✞
፩ ፥ ፪፦ #ሦስት_መዓልት_እና_ሦስት
_ሌሊት_የሞላው_እንዴት_ ነው?፤

ጌታ በከርሰ መቃብር የቆየው ሦስት መዓልትና ሦስት
ሌሊት ነው፡፡ ይኽንንም ለመረዳት ዕብራውያን ዕለታትን
እንዴት
እንደሚቆጥሩ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ እኛ በሀገራችን የሌሊቱን
ሰዓት መቁጠር የምንጀምረው ከዋዜማው ከምሽቱ አንድ
ሰዓት
ነው÷ የቀኑን ሰዓት መቁጠር የምንጀምረው ደግሞ ከማለዳው
አንድ ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡ የሌሊቱ ሰዓት የሚያ ልቀው
ከማለዳው አሥራ ሁለት ሰዓት ሲሆን፥ የቀኑ ደግሞ ከምሽቱ
አሥራ ሁለት ሰዓት ሲሆን ነው፡፡ የቀኑም የሌሊቱም ሰ ዓት
ተደምሮ ሃያ አራት ሰዓት ይሆናል፡፡ ሁሉም ሰዓት ዕለቱን
ይወክላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው እሑድ ዕለት ከሃያ አራቱ ሰዓ ት
በአንዱ ቢወለድ እሑድ ተወለደ ይባላል÷ ቢሞትም እሑድ ሞተ
ይባላል፡፡ ዕለቱ በሚጀምርበትም ሰዓት ሆነ፥ በሚያልቅ በት
ሰዓት፥ ድርጊቱ ቢፈጸም ያ ሰዓት እንደ አንድ መዓልትና እንደ
አንድ ሌሊት ይቆጠራል፡፡ አውሮፓውያን አንድ ብለው ሰዓት
መቁጠር የሚጀምሩት በእኛ አቆጣጠር ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት
ነው፡፡ እስከ ሃያ አራት ይቆጥሩና በእኛ አቆጣጠር ከሌሊቱ
ስድስት ሰዓት ሲሆን ይጨርሳሉ፡፡ ሃያ አራት ሰዓት ሲሆን ዜሮ
ይሉና እንደገና አንድ ብለው መቁጠር ይጀምራሉ፡፡ በሌላ
አነጋገር ከሌሊት እስከ ሌሊት ይቆጥራሉ፡፡ አሜሪካውያን
ደግሞ
በእኛ ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ሲሆን አንድ ብለው ይጀምሩና በእኛ
ከቀኑ ስድስት ሰዓት ሲሆን አሥራ ሁለት ብለው ይጨርሳሉ፡፡
ከዚያም በእኛ አቆጣጠር ከቀኑ ሰባት ሰዓት እንደገና አንድ
ብለው ይጀምሩና በእኛ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ሲሆን አሥራ
ሁለት ብለው ይጨርሳሉ፡፡

ዕብራውያን ግን ዕለትን መቁጠር የሚጀምሩት
ከዋዜማው ማለትም በአውሮፓውያን ከአሥራ ሰባት ሰዓት÷
በአሜሪካውያን ከአምስት ሰዓት (P.M.) ÷ በእኛ ደግሞ
ከምሽቱ አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡ ከዚህ ሰዓት ጀምሮ
እስከ ቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ድረስ ሃያ አራት ሰዓት ቆጥረው
አንድ ቀን ይላሉ፡፡ ከላይ እንደተገለጠው እያንዳንዱ ሰዓት
የዕለቱን መዓልትና ሌሊት ይወክላል፡፡ በዚህ መሠረት ጌታችን
ከመስቀል ወርዶ የተቀበረው ዓርብ ቅዳሜ ከመግባቱ በፊት
ነው፡፡ ዓርብ ዕለቱ የሚጀምረው ከዋዜማው ሐሙስ በእኛ
አቆጣጠር ከቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡ ስለዚህ ጌታ
የተቀበረው በዓርብ ሃያ አራት ሰዓት ክልል ውስጥ በመሆኑ
እንደ
አንድ መዓልትና ሌሊት ይቆጠራል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ዓርብ
ከቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ እስከ ቅዳሜ ቀን አሥራ አንድ
ሰዓት ያለው ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ቅዳሜ ከቀኑ አሥራ አንድ
ሰዓት ጀምሮ እስከ እሑድ ቀን አሥራ አንድ ሰዓት ያለው ነው፡፡
ከዚህ በኋላ የሰኞ ምሽት ይገባል፡፡ ጌታ የተነሣው በሦስተኛው
ቀን እሑድ መንፈቀ ሌሊት ነው።
✞ ✞ ✞
፩ ፥ ፫፦ #እንዴት_ተነሣ?

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
ከሙታን ተለይቶ የተነሣው በታላቅ ኃይልና ሥልጣን ነው፡፡ ይህ
ኃይልና ሥልጣን የባሕርይ ገንዘቡ ነው፡፡ ይኽንንም፡- «ነፍሴን
ደግሞ አነሣት ዘንድ (ሰውነቴን ከሞት አነሣት ዘንድ)
አኖራለሁና
(በፈቃዴ እሞታለሁና)፤ ስለዚህ አብ ይወደኛል፡፡ እኔ በፈቃዴ
አኖራታለሁ እንጂ (ነፍሴን በፈቃዴ ከሥጋዬ ለይቼ በገነት÷
ሥጋዬንም በመቃብር አኖራቸዋለሁ እንጂ) ከእኔ ማንም
አይወስዳትም፡፡ (ያለ እኔ ፈቃድ የሚፈጸም ምንም ነገር
የለም)፡፡
ላኖራት (ነፍሴን በገነት÷ ሥጋዬን በመቃብር ላኖራቸው)
ሥልጣን አለኝ፤ ደግሞም ላነሣት (ነፍሴን ከሥጋዬ አዋሕጄ
ላነሣት) ሥልጣን አለኝ፡፡» በማለት አስቀድሞ ተናግሮታል፡፡
ዮሐ
፲÷፲፯-፲፰፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ፡- «ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም
አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት÷ በሸላቶቹም ፊት
ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈ ተም፡፡» በማለት
መናገሩ ኢየሱስ ክርስቶስ በፈቃዱ እንደሚሞት የሚያጠይቅ
ትንቢት ነበር፡፡ ኢሳ ፶፫፥፯፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም
ከዚህ
የሚመሳሰል ቃል ተናግሯል፡፡ ፩ኛጴጥ ፪÷፳፴፡፡ በዚህ ዓይነት
ነቢያትም ሐዋርያትም የተናገሩለት ኢየሱስ ክርስቶስ በኃይሉ
በሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጐ÷ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ
ተነሥቷል፡፡ እርሱ የትንሣኤና የሕይወት ባለቤት ነውና፡፡ ዮሐ
፲፩÷፳፭፡

ይህ እንዲህ ከሆነ÷ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፡-
«የሕይወትን ራስ ገደላችሁት፤» በማለት አይሁድን ከወቀሳቸው
በኋላ፡- «እርሱን ግን እግዚአብሔር ከሙታን አስነሣው፤»
ለምን
አለ? የሚል ጥያቄ ይነሣ ይሆናል፡፡ ይኽንን ኃይለ ቃል በመያዝ
«አብ አስነሣው እንጂ በራሱ አልተነሣም፤» የሚሉ አሉና፡፡
እነዚህም ትርጓሜውን ያልተረዱ ምሥጢሩን ያላስተዋሉ ሰዎች
ናቸው፡፡ ሐዋርያው «እግዚአብሔር አስነሣው፤» ያለው
«እግዚአብሔር» የሚለው ስም የሦስቱም መጠሪያ እንጂ
የአብ
ብቻ አለመሆኑን ስለሚያውቅ ነው፡፡ ምክንያቱም፦ ወልድም
እግዚአብሔር ተብሎ ይጠራል፡፡ ዮሐ ፩÷፩ ፣ የሐዋ ፳÷፳፰፡፡
መንፈስ ቅዱስም እግዚአብሔር ተብሎ ይጠራል፡፡ ዮሐ ፩÷፪፡፡
ስለዚህ፦ ሥላሴ በፈቃድ አንድ በመሆናቸው፥ «አንዲት በሆነች
በአብ በራሱና በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድና ሥልጣን ተነሣ፤
አንድም፦ ወደ መቃብር የወረደ ሥጋ፥ መለኰት የተዋሐደው
ስለሆነ ተነሣ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር በመሆኑ ተነሣ፤»
ተብሎ ይተረጐማል፥ ይታመናል፡፡ ትንቢተ ነቢያትም
የሚያረጋግጥልን ይኽንኑ ነው፡፡ «እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ
እንደሚነቃ ተነሣ÷ የወይን ስካር እንደተወው እንደ ኃያልም
ሰው፤ ጠላቶቹንም በኋላቸው መታ፤» ይላል። መዝ ፸፯፥፷፭።
✞ ✞ ✞
፩ ፥ ፬፦ #ለምን_በአዲስ_መቃብር_ተ ቀበረ?

በእስራኤል ባሕል፥ የአባቶቻቸው አፅም ካረፈበት
መቃብር፥ የመቀበር ልማድ አላቸው፡፡ ዮሴፍ በግብፅ የእስራ
ኤልን ልጆች፡- «እግዚአብሔር ሲያስባችሁ አጥንቴን ከዚህ
አንሥታችሁ ከእናንተ ጋር ውሰዱ፤» ብሎ ያማላቸው፥ የአባቶቹ
የአብርሃም እና የይስሐቅ የያዕቆብም አፅም ካረፈበት
ለመቀበር
ፈልጐ ነው፡፡ ዘፍ. ፶÷፳፭፡፡ በቤቴል የነበረውም ሽማግሌ ነቢ
ይ፡- «በሞትሁ ጊዜ የእግዚአብሔር ሰው በተቀበረበት መቃብር
ቅበሩኝ፤ አጥንቶቼንም በአጥንቶቹ አጠገብ አኑሩ፤» ብሏል ፡፡
፩ኛነገ ፲፫÷፴፩፡፡ ጌታችን የተቀበረው እንደ እስራኤል ባሕል
የቅዱሳን አፅም ካረፈበት ሳይሆን ማንም ካልተቀበረበት
ከአዲስ
መቃብር ነው፡፡ ይኸውም ዮሴፍ ለራሱ ያዘጋጀው ነው፡፡
«ዮሴፍም ሥጋውን ይዞ በንጹሕ በፍታ ከፈነው÷ ከዓለት
በወቀረ
ው በአዲሱ መቃብርም አኖረው÷ በመቃብሩም ደጃፍ ታላቅ
ድንጋይ አንከባሎ ሄደ፤» ይላል ማቴ ፳፯÷፶፱፡፡ ይህም የሆነው
እርሱ ባወቀ በርሱ ጥበብ ነው፡፡ እንዲህም በማድረጉ አይሁድ
ለትንሣኤው ምክንያት እንዳያበጁለት አድርጓቸዋል፡፡ በብሉይ
ኪዳን እንደተጻፈው፥ ከነቢዩ ከኤልሳዕ መቃብር ተቀብሮ
የነበረው
ሰው፥ የነቢዩ አጥንት በነካው ጊዜ፥ በተአምር ተነሥቷል። ፪ኛነገ
፲፫÷፳፡፡ እንግዲህ ጌታችንም፥ ከአንዱ ቅዱስ መቃብር
ተቀብሮ
ቢሆን ኖሮ፥ ሞትን ድል አድርጐ በሚነሣበት ጊዜ «በራሱ
አልተነሣም፥ የቅዱሱ አፅም ነው ያስነሣው፤» ባሉት ነበር፡፡
ይኸንን ምክንያት ለማጥፋት ነው፥ በአዲስ መቃብር
የተቀበረው።
✞ ✞ ✞
፩ ፥ ፭፦ #እንዴት_በዝግ_መቃበር_ተ ነሣ?

ጌታችንን ዮሴፍ ኒቆዲሞስ ገንዘው ከቀበሩት በኋላ፥
የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ወደ ጲላጦስ ተመልሰው፡- « ጌታ
ሆይ÷ ያ ሰው (ክርስቶስ)፥ ገና በሕይወቱ ሳለ፥ ከሦስት ቀን
በኋላ እነሣለሁ፥ እንዳለ ትዝ አለን፡፡ እንግዲህ ደቀመዛሙርቱ
መጥተው በሌሊት እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም ከሙታን ተነሣ
እንዳይሉ÷ የኋለኛይቱ ስሕተት ከፊተኛይቱ ይልቅ የከፋች
ትሆናለችና መቃብሩ እስከ ሦስተኛው ቀን ድረስ እንዲጠበቅ
እዘዝ አሉት፡፡ ጲላጦስም፡- ጠባቆች አሉአችሁ፥ እንዳወቃችሁ
አስጠብቁ፤» አላቸው፡፡ እነርሱም ሄደው ከጠባቆች ጋር
ድንጋዩን
አትመው መቃብሩን አስጠበቁ፡፡» ማቴ ፳፯፥ ፷፫÷፷፮፡፡
በታላቅ
ድንጋይ የተገጠመው መቃብር፥ ድንጋዩ እንደታተመ፥ ክርስቶስ
ሞትን ድል አድርጐ ተነሥቷል፡፡ ይኸውም፦ ምንም
የማያግደው
መለኰት በተዋሕዶ ከሥጋ ጋር በመቃብር ስለነበረ ነው፡፡
ቅዱስ
ቄርሎስ እንደተናገረው፥ በተዋሕዶ፥ የቃል ገንዘብ ለሥጋ፥
የሥጋም ገንዘብ ለቃል በመሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ፦ አይሁድ ብዙ
ጊዜ በድንጋይ ቀጥቅጠው ሊገድሉት ሲፈልጉ፥ እያዩት
ይሰወርባቸው ከእጃቸውም ይወጣ ነበር፡፡ በመካከላቸው አልፎ
ሲወጣ አያዩትም ነበር፡፡ ዮሐ ፰÷፶፱፤ ፲፥፴፱፡፡ ይህም የሆነው፥
እንደ ነፍስና ሥጋ ተዋሕዶ፥ መለኰት ሥጋን በመዋሐዱ ነው፡፡
ከትንሣኤው በኋላም ከአንዴም ሁለት ጊዜ ከተዘጋ ቤት በሩ
ሳይከፈት የገባው ለዚህ ነው፡፡ ዮሐ ፳÷፲፱፤ ፳፮፡፡ በልደቱም
ጊዜ
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በድንግልና
እንደታተመች
የተወለደው ለዚህ ነው፡፡ ኢሳ ፯÷፲፬፡፡ ማቴ ፩÷ ፳-፳፫ ፣ ሉቃ
፪÷፮-፯፡
✞ ✞ ✞
፩ ፥ ፮፦ #መቃብሩን_ማን_ከፈተው?

ጌታችን የተነሣው መግነዝ ፍቱልኝ፥ መቃብሩን ክፈቱልኝ ሳይል
ከሆነ፥ «መቃብሩን ማን ከፈተው? ለምንስ ተከ ፈተ?» የሚል
ጥያቄ ይነሣ ይሆናል፤ በወንጌል እንደተጻፈው፥ የአይሁድ ሰንበት
ቅዳሜ ካለፈ በኋላ፥ እሑድ በማለዳ፥ ፀሐይ ሲወጣ፥
መግደላዊት ማርያም÷ የያዕቆብም እናት ማርያም ሶሎሜም
ሽቱ ሊቀቡት ወደ መቃብሩ መጥተው ነበር፡፡ ትልቁ
ጭንቀታቸው
«ድንጋዩን ከመቃብሩ ደጃፍ ማን ያንከባልልልናል?» የሚል
ነበር÷ ድንጋዩ እጅግ ትልቅ ነበርና፤ አሻቅበውም አይተው
ድንጋዩ ተንከባሎ እንደነበር ተመለከቱ፡፡ ወደ መቃብሩም
ገብተው
ነጭ ልብስ የተጐናጸፈ ጐልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና
ደነገጡ፡፡ በጐልማሳ አምሳል የተገለጠላቸው የጌታ መልአክ
ነው፡፡ እርሱ ግን፡- «አትደንግጡ፤ የተሰቀለውን የናዝሬቱን
ኢየሱስን እንደምትፈልጉ አውቃለሁ፤ ተንሥቷል በዚህ
የለም፡፡»
አላቸው፡፡ ማር ፲፮÷፩-፮፡፡ ጌታችን በዝግ መቃብር ከተነሣ
በኋላ
ባዶ የነበረውን መቃብር የከፈተው ይህ የጌታ መልአክ ነው፡፡
የከፈተበትም ምክንያት በእምነት የመጡ እነዚህ ሴቶች
ያልተነሣ መስሏቸው ዘወትር በመመላለስ እንዳይቸገሩ ነው፡፡
አንድም ትንሣኤውን እንዳይጠራጠሩ ነው፡፡ በቅዱስ ማቴዎስ
ወንጌልም «በሰንበትም መጨረሻ የመጀመሪያው ቀን ሲነጋ፥
መግደላዊት ማርያምና ሁለተኛይቱ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ
መጡ፡፡ እነሆም የጌታ መልአክ ከሰማይ ስለወረደ ታላቅ
የምድር
መናወጥ ሆነ፤ ቀርቦም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ፡፡
መልኩም እንደ መብረቅ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ፡፡
ጠባቆቹም እርሱን ከመፍራት የተነሣ ተናወጡ፡፡ እንደ ሞቱም
ሆኑ፡፡ መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው፥ እናንተስ አትፍሩ፤
የተሰቀለውን ኢየሱስን እንደምትሹ አውቃለሁና፤ እንደ ተናገረ
ተነሥቶአልና በዚህ የለም፤» የሚል ተጽፏል፡፡ ማቴ ፳፰÷፩-፮፡፡
ደቀ መዛሙርቱ በእርግጠኝነት ትንሣኤውን ያመኑት መልአኩ
ወደ
ከፈተው መቃብር ገብተው መግነዙን ካዩ በኋላ ነው። ዮሐ
፳፥፯።
✞ ✞ ✞
፩ ፥ ፯፦ #በኲረ_ትንሣኤ፤

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
ለባሕርይ አባቱ፥ ለአብ ለእናቱ ለድንግል ማርያምም የበኵር
ልጅ ነው፡፡ ዕብ ፩÷፮፣ ሉቃ ፪÷፯፡፡ ለበጎ ነገርም ሁሉ በኵር
በመሆኑ የትንሣኤያችንም በኵር እርሱ ነው፡፡ «አሁን ግን
ክርስቶስ ላንቀላፉት በኵራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቷል፡፡ ሞት
በሰው (በቀዳማዊ አዳም) በኵል ስለመጣ፥ ትንሣኤ ሙታን
በሰው (በተዋሕዶ ሰው በመሆኑ ዳግማዊ አዳም በተባለ
በክርስቶስ) በኩል ሆኗልና፡፡ ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ
ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱ
በራሱ ተራ ይሆናል፤ ክርስቶስ እንደ በኵራት ነው፤» ይላል፡፡
፩ኛቆሮ ፲፭÷፳-፳፫፡፡ በተጨማሪም፡- «በሰማይና በምድር
ያሉት
ሁሉ በእርሱ ተፈጥሯልና፥ ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፡፡
(ከፍጥረታት በፊት የነበረ÷ የፍጥረታት አለቃ÷ የፈጠረውን
ፍጥረት የሚገዛ ነው)፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሯል ፤
እርሱም ከሁሉ በፊት ነው፤ (ለዘመኑ ጥንት የሌለው ከአብና
ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በአንድነት በህልውና የነበረ ነው)፤ ሁሉም
በእርሱ ተጋጥሟል፡፡ እርሱም የአካሉ ማለት የቤተ ክርሰቲያን
ራስ ነው፤ እርሱም በሁሉ ፊተኛ ይሆን ዘንድ መጀመሪያ
ከሙታንም በኵር ነው፡፡» የሚል አለ፡፡ ቈላ ፩÷፲፮-፲፰፡፡
ቅዱስ
ዮሐንስም፡- «ካለውና ከነበረው ከሚመጣውም÷ በዙፋኑም
ፊት
ካሉት ከሰባቱ መናፍስት÷ ከታመነውም ምስክር ከሙታንም
በኵር የምድርም ነገሥታት ገዥ ከሆነ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና
ሰላም ለእናንተ ይሁን፤» ብሏል። ራእ ፩፥፭።

በብሉይ ኪዳን እነ ኤልያስ÷ እነ ኤልሳዕ ሙት
አስነሥተዋል፡፡ ፩ኛነገ ፲፯፥፳፪ ፣ ፪ኛነገ ፬÷፴፪-፴፰፡፡ በአዲስ
ኪዳንም ራሱ ባለቤቱ የመኰንኑን ልጅ ÷ የመበለቲቱን ልጅ÷
አልዓዛርንም ከሞት አንሥቷቸዋል፡፡ ማቴ ፱÷፳፭፣ ሉቃ
፯÷፲፭ ፣
ዮሐ ፲፩÷፵፬፡፡ ነፍሱን በመስቀል ላይ በፈቃዱ አሳልፎ
በሰጠም
ጊዜ አያሌ ሙታን ከእግረ መስቀሉ ተነሥተዋል፡፡ ማቴ
፳፯÷፶፫፡፡
እነዚህ ሁሉ በኵረ ትንሣኤ አልተባሉም፡፡ ምክንያቱም፦
አንደኛ፥
በራሳቸው ኃይል የተነሡ አይደሉም፡፡ ሁለተኛ፥ ለተወሰነ ጊዜ
ከኖሩ በኋላ ተመልሰው ሞተው ትንሣኤ ዘጉባኤን የሚጠብቁ
ሆነዋል፡፡ ሦስተኛ፥ ፍጡራን ናቸው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን
የባሕርይ አምላክ በመሆኑ በራሱ ኃይልና ሥልጣን ተነሥቷል፡፡
ዳግመኛም አይሞትም፡፡ ይኽንንም፡- «ክርስቶስ ከሙታን
ተነሥቶ
ወደፊት እንዳይሞት፥ ሞትም ወደፊት እንዳይገዛው
እናውቃለንና
÷ መሞትን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ለኃጢአት ሞቷልና፡፡» በማለት
ሐዋርያው ገልጦታል፡፡ ሮሜ ፮÷፱፡፡ ጌታችንም፡- «ፊተኛውና
መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፥ ሞቼም ነበርሁ እነሆም
ከዘላለም
እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፤» ብሏል። ራእ ፩፥፲፰።
✞ ✞ ✞
፩ ፥ ፰፦ #ከትንሣኤው_በኋላ_ለምን_ ተመገበ?

ጌታችን በተዘጋ ቤት ገብቶ ለደቀ መዛሙርቱ በተገለጠ
ጊዜ፥ መንፈስ የሚያዩ መስሏቸው ኅሊናቸው ደንግጦ÷
ልባቸውም ፈርቶ ነበር፡፡ እርሱም፡- «ስለ ምን ትደነግጣላችሁ?
ስለምንስ አሳብ በልባችሁ ይነሣል? እኔ ራሴ እንደሆንሁ
እጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት÷ መንፈስ ሥጋና
አጥንት የለውምና፥ እኔን ዳስሳችሁ እዩ፤» ካላቸው በኋላ
እጆቹንና እግሮቹን አሳይቷቸዋል። እነርሱም ከደስታ የተነሣ ገና
ስላላመኑ ሲደነቁ ሳሉ፡- «በዚህ አንዳች የሚበላ አላችሁን?»
አላቸው። እነርሱም ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ቁራጭ ከማር
ወለላም ሰጡት፤ ተቀብሎም በፊታቸው በላ፥ ይላል። ሉቃ
፳፬÷፴፮ -፵፫። ለሦስተኛ ጊዜ በጥብርያዶስ በተገለጠላቸውም
ጊዜ አብሯቸው ተመግቧል፡፡ ዮሐ ፳፩÷፱-፲፬። ይኽንንም
ያደረገው ከትንሣኤ በኋላ መብላት መጠጣት ኖሮ አይደለም፡፡
አለማመናቸውን ለመርዳት ነው፡፡ ደቀመዛሙርቱ በተዋሐደው
ሥጋ ለመነሣቱ እርግጠኞች እንዲሆኑ ነው፡፡ ከወንጌሉ
እንደምንረዳው ደቀመዛሙርቱ ይበልጥ እርግጠኞች የሆኑት
ስላዩት ሳይሆን፥ ያቀረቡለትን በመብላቱና በመጠጣቱ ነውና፡፡
✞ ✞ ✞
፩ ፥ ፱፦ #ለምን_አትንኪኝ_አላት?

መግደላዊት ማርያም ገና ሰማይና ምድሩ ሳይላቀቅ፥
በማለዳ፥ ሽቱ ልትቀባው ከመቃብሩ አጠገብ ተገኝታ ነበር።
እንደደረሰችም ድንጋዩ ከመቃብሩ አፍ ተፈንቅሎ አየች። ይህች
ሴት በሦስተኛው ቀን እንደሚነሣ ከባለቤቱ ብትሰማም፥ «
እንደተናገረ ተነሥቶ ነው፤» ብላ አላመነችም። ላለማመኗም
ምክንያት የሆነው፥ «እኛ ተኝተን ሳለን ደቀመዛሙርቱ በሌሊት
ሰረቁት፤» የሚለው የጭፍሮች ወሬ ነው። ጭፍሮቹ እውነትን
በሐሰት ለውጠው ይኽንን ያወሩት፥ በገንዘብ ተደልለው ነው፡፡
ማቴ ፳፰÷፲፩-፲፭፡፡ ለዚህ ነው ወደ ደቀመዛሙርቱ ሄዳ፡-
«ጌታን
ከመቃብር ወስደውታል፥ ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም፤»
ያለቻቸው፡፡ ዮሐ ፳÷፪፡፡ ከመቃብሩ ራስጌና ግርጌ ሁለት
መላእክት ተገልጠውላት፡- «አንቺ ሴት ስለምን ታለቅሻለሽ?»
ባሏት ጊዜም፥ «ጌታዬን ወስደውታል፥ ወዴትም እንዳኖሩት
አላውቅም፤» ብላቸዋለች፡፡ ዮሐ ፳÷፲፫፡፡ በመጨረሻም ጌታ
ራሱ
ተገልጦላት፡- «አንቺ ሴት ስለምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ
ትፈልጊያለሽ?» ሲላት አላወቀችውም፡፡ ለዚህ ነው፥ አትክልት
ጠባቂ መስሏት፡- «ጌታ ሆይ፥ አንተ ወስደኸው እንደሆንህ፥
ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ፥ እኔም ወስጄ ሽቱ እንድቀባው፤»
ያለችው፡፡ ዮሐ. ፳÷፲፭፡፡ በዚህን ጊዜ፥ «ማርያም»፥ ብሎ
በስሟ
ቢጠራት በድምፁ አወቀችውና «ረቡኒ ( መምሕር ሆይ)»
አለችው፡፡ መልኩን አይታ፥ ድምፁን ሰምታ÷ ትንሣኤውን
አረጋግጣ፥ «አምላኬ» አላላችውም፡፡ ስለዚህ «ገና ወደ አባቴ
አላረግሁምና፤ አትንኪኝ፥ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ (ወደ
ደቀመዛሙርቴ) ሄደሽ እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ÷ ወደ
አምላኬና ወደ አምላካችሁ አርጋለሁ ብሏል፥ ብለሽ
ንገሪያቸው፤» አላት፡፡ እንዲህም ማለቱ የእርሱ የእግዚአብሔር
ልጅ መባልና የእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች መባል ፍጹም
የተለያየ በመሆኑ ነው፡፡ እርሱ፥ «አባቴ» ቢል የባሕርይ ልጅ
በመሆኑ ነው፡፡ እነርሱ ግን የጸጋ ልጆች ናቸው፡፡ እርሱ፥
«አምላኬ» ቢል ስለተዋሐደው ሥጋ ነው፡፡ የተዋሐደው
የፈጠረውን ሥጋ ነውና ፡፡ እነርሱ ግን «አምላካችሁ» ቢባሉ
ፍጡራን ስለሆኑ ነው፡፡ በዚህም እርሱ ፈጣሪ እነርሱ ፍጡራን
መሆናቸውን አስረግጦ ተናግሯል፡፡ ቶማስን ግን፡- «ጣትህን
ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ
አግባው ፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን፤» ብሎታል፡፡ ዮሐ
፳፥፳፯ ፡፡ ምክንያቱም አይቶ፥ ዳስሶ፥ «ጌታዬ አምላኬም»
ብሎ
የሚያምን ነውና፡፡ አንድም ሥጋውንና ደሙን ለመዳሰስ÷
ለመፈተት፥ የተጠራ የተመረጠም ካህን ነውና፡፡
✞ ✞ ✞
፩ ፥ ፲፦ #ተስፋ_ትንሣኤ፤

በብሉይ ኪዳን ዘመን ሁሉም በአዳም ኃጢአት
ምክንያት እየተኰነኑ በሞተ ነፍስ ተይዘው ወደ ሲኦል ይወርዱ
ነበር ። ፩ኛ ቆሮ ፲፭ ÷፳፪፡፡ «ነገር ግን በአዳም መተላለፍ
ምሳሌ
ኃጢአትን ባልሠሩት ላይ እንኳ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ
( እስከ ክርስቶስ) ድረስ ሞት ነገሠ፤» የተባለው ለዚህ ነው፡፡
ሮሜ ፭÷፲፬፡፡ ከዚህ የተነሣ እነ አብርሃም እንኳ ሳይቀሩ
የወረዱት ወደ ሲኦል ነው፡፡ እነ ኢሳይያስ፡- «ጽድቃችንም ሁሉ
እንደመርገም ጨርቅ ነው፤» ያሉት ለዚህ ነው፡፡ ኢሳ ፷፬
÷፮፡፡ እነ
ኤርምያስም፡- «ለሥጋ ለባሽ ሁሉ ሰላም የለም፥ ስንዴን ዘሩ
እሾህንም አጨዱ፡፡» ብለዋል፡፡ ኤር ፲፪÷፲፫። በዚህ
ምክንያት
የብሉይ ኪዳን፥ ዘመን ዘመነ ፍዳ÷ ዘመነ ኵነ ÷ ዘመነ ጽልመት
ተብሏል፡፡ በዚህ ዘመን እነ ቅዱስ ዳዊት፡- «አንሥእ ኃይለከ÷
ወነዓ አድኅነነ፤ ኃይልህን አንሣ÷ እኛንም ለማዳን ና ፤ (በሥጋ
ተገልጸህ÷ ሰው ሁነህ አድነን)፤» እያሉ ወልድን ተማጽነዋል፡፡
መዝ 79÷ 2 ፡፡ «ፈኑ ብርሃነከ ወጽድቀከ፤ ብርሃንህንና
እውነትህን ላክልን፤ (ብርሃን ወልድን÷ እውነት መንፈስ ቅዱስን
ላክልን) ፤ እነርሱ ይምሩን÷ ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ
ማደሪያህ÷ (ወደ ገነት ወደ መንግሥተ ሰማያት) ይውሰዱን »፤
እያሉም አብን ተማጽነዋል፡፡ መዝ ፵÷፫፡፡ ይህም
የሚያመለክተው በዚያ በጨለማ ዘመን ሆነው ተስፋቸው
የክርስቶስ ትንሣኤ እንደነበረ ነው፡፡ በሞት አጠገብ ሕይወት÷
በመቃብር አጠገብ ትንሣኤ እንዳለ ተስፋ እንዲያደርጉ
የሚያደርጋቸው የክርስቶስ ትንሣኤ ነውና፡፡ ያንጊዜ ከሲኦል
እንደሚወጡ፥ የተዘጋች ገነትም እንደምትከፈትላቸው
ያውቃሉና፡፡

የክርስቶስ ትንሣኤ የአዳም ልጆች በጠቅላላ ትንሣኤ
ዘጉባኤን በተስፋ እንዲጠብቁ አድርጓቸዋል፡፡ ይህም ተስፋ
ሃይማኖት እንዲይዙ÷ ምግባር እንዲሠሩ አጽንቷቸዋል፡፡
ምድራዊውን እንዲንቁ፥ ሰማያዊውን እንዲናፍቁ
አድርጓቸዋል፡፡
« ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ
ቃሉ እንጠብቃለን፡፡» ይላል፡፡ ፪ኛ ጴጥ ፫÷፲፫፡፡ ቅዱሳን
በሃይማኖት አይተዋታል፡፡ «አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም
አየሁ÷ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና÷
ባሕርም
ወደፊት የለም፡፡ ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም
ለባልዋ እንደተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ
ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ፡፡» ይላል፡፡ ራእ
፳፩÷፫፡፡
እግዚአብሔርም፡- «እነሆ÷ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር
እፈጥራለሁና፥ የቀደሙትም አይታሰቡም÷ ወደ ልብም
አይገቡም፡፡ ነገር ግን በፈጠርሁት ደስ ይበላችሁ፥ ለዘላለምም
ሐሴት አድርጉ፤ እነሆ÷ ኢየሩሳሌምን ለሐሴት÷ ሕዝቧንም
ለደስታ እፈጥራለሁና፡፡» ብሏል፡፡ ኢሳ ፷፭፥፲፯።
✞ ✞ ✞
፩ ፥ ፲፩፦ #ሙታን_እንዴት_ይነሣሉ?

እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ሲፈጥረው የሚያንቀላፋና
የሚነቃ አድርጐ ፈጥሮታል፡፡ ማንቀላፋቱ የሞት፥ መንቃቱ
ደግሞ
የትንሣኤ ምሳሌ ነው፡፡ አቤል ከሞተ በኋላ በደሙ መናገሩም
የትንሣኤ ምሳሌ ነው፡፡ ዘፍ ፬÷፲፡፡ የሄኖክም ከዓይነ ሞት
ተሰውሮ በእግዚአብሔር መወሰድ የትንሣኤ ምሳሌ ነው፡፡ ዘፍ
፭÷፳፬፡፡ ፍጥረታት በጠቅላላም ትንሣኤን የሚሰብኩ ናቸው፡፡
የፀሐይ መውጣት የመወለድ÷ የፀሐይ መጥለቅ የመሞት÷
ከጠለቀች በኋላም እንደገና መውጣት የትንሣኤ ምሳሌ ነው፡፡

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሙታን
እንደሚነሡ በቃልም በተግባርም አስተምሯል፡፡ በቃል ፡-
«በመቃብር ያሉት ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤
መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ÷ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ
ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ፡፡» ሲል አስተምሯል፡፡ ዮሐ
፭÷፳፱፡፡ በተግባርም የአራት ቀን ሬሳ አልዓዛርን አስነሥቷል፡፡
ዮሐ ፲፩÷፵፫፡፡ ቅዱሳን ነቢያት፡- እነ ኢሳይያስ «ሙታንህ
ሕያዋን
ይሆናሉ፥ ሬሳዎችም ይነሣሉ፡፡» ብለዋል። ኢሳ ፳፮÷፲፱፡፡ እነ
ዳንኤልም፡- «በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉት ብዙዎች
(ሁሉም) ይነቃሉ፤ እኵሌቶችም ወደ ዘላለም ሕይወት÷
እኵሌቶችም ወደ እፍረትና ዘላለም ጉስቊልና፡፡» ብለዋል፡፡
ዳን
፲፪÷፪፡፡ በተለይም ለነቢዩ ለሕዝቅኤል፥ እግዚ አብሔር፦
በአፅም
የተሞላ ታላቅ ሸለቆ ካሳየው በኋላ፥ «እነዚህ የደረቁ አጥንቶች
ተመልሰው በሕይወት የሚኖሩ ይመስ ልሃልን?» ሲል
ጠይቆታል፡፡ ሕዝቅኤልም፡- «እግዚአብሔር ሆይ÷ አንተ
ታውቃለህ፤» የሚል መልስ ሰጥቶቷል፡፡ በመጨ ረሻም እነዚህ
ሁሉ ሕይወት ዘርተው ሲነሡ አይቷል፡፡ ይኸንንም፡-
«እንዳዘዘኝም
ትንቢት ተናገርሁ÷ ትንፋሽም ገባባቸው፥ ሕያዋንም ሆኑ÷
እጅግም ታላቅ ሠራዊት ሆነው በእግራቸው ቆሙ፡፡» በማለት
ገልጦታል፡፡ ሕዝ ፴፯፥፩-፲፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ሙታን ትንሣኤ በሚገባ
ቋንቋ አብራርቶ በምሳሌ ሲያስተምር «ነገር ግን ሰው፥ ሙታን
እንዴት ይነሣሉ? በምንስ ዓይነት አካል ይመጣሉ? የሚል ይኖር
ይሆናል፡፡» ብሎ ከጠየቀ በኋላ፥ «አንተ ሞኝ አንተ
የምትዘራው
ካልሞተ ሕያው አይሆንም፡፡» ብሏል፡፡ ከዚህም አያይዞ
«የሙታን
ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው፡፡ በመበስበስ ይዘራል÷
ባለመበስበስ ይነሣል፤ በውርደት ይዘራል በክብር ይነሣል፤
በድካም ይዘራል÷ በኃይል ይነሣል፤ ፍጥረታዊ አካል ይዘራል÷
መንፈሳዊ አካል ይነሣል ፤ ፍጥረታዊ አካል ካለ መንፈሳዊ
አካል
ደግሞ አለ፡፡ እንዲሁ ደግሞ፡- ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ
ሆነ ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም (ክርስቶስ) ሕይወትን
የሚሰጥ መንፈስ ሆነ፡፡ ነገር ግን አስቀድሞ ፍጥረታዊው
ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው መጀመሪያ
አይደለም። የፊተኛው ሰው ከመሬት መሬታዊ ነው። ሁለተኛው
ሰው ( ክርስቶስ ) ከሰማይ ነው፡፡ መሬታዊው እንደሆነ
መሬታውያን የሆኑት ደግሞ እንዲህ ናቸው÷ ሰማያዊው እንደ
ሆነ ሰማያውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው ፡፡ የዚያንም
የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን የሰማያዊውን መልክ
ደግሞ
እንለብሳለን፡፡» ብሏል። ፩ኛቆሮ ፲፭÷፴፭-፵፱፡፡ በፊልጵስዩስ
መልእክቱም፡- «ክቡር ሥጋውን እንደሚስል የተዋረ ደውን
ሥጋችንን ይለውጣል፡፡» ብሏል፡፡ ፊል ፫÷፳፩። ሐዋርያው
ቅዱስ
ዮሐንስም፡- «እርሱን እንድንመስል እናውቃለን፤» ብሏል፡፡ ፩ኛ
ዮሐ ፫÷፪።
✞ ✞ ✞
፩ ፥ ፲፪፦ #የትንሣኤ_ጸጋ፤

በክርስቶስ ትንሣኤ ያገኘነው ጸጋ ታላቅ ነው። ከጨለማ ወደ
ብርሃን ወጥተናል÷ ከሞት ወደ ሕይወት ተሸጋግረናል ። ሙታን
የነበርን ሕያዋን÷ ምድራውያን የነበርን ሰማያውያን÷
ሥጋውያን
የነበርን መንፈሳውያን ሆነናል፡፡ «ሞት ሆይ÷ መውጊያህ የት
አለ? ሲኦል ሆይ÷ ድል መንሣትህ የት አለ?» የምንል ሆነናል፡፡
ሆሴ ፲፫÷፲፬ ፣ ፩ኛቆሮ ፲÷፶፭፡፡ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ «እኛ
አገራችን በሰማይ ነውና÷ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን
እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠ ባበቃለን፤ እርሱም
ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር ክቡር
ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋች ንን ይለውጣል፡፡»
የምንል ሆነናል፤ ፊል ፫፥ ፳-፳፩፡፡ ናፍቆታችን ሁሉ በትንሣኤ
ያገኘነውን ጸጋ እውን ማድረግ ነው፡፡ «ድንኳን የሚሆነው
ምድራዊው መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ
የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን
እናውቃለንና፡፡ በዚህ ውስጥ በእውነት እንቃትታለንና÷
ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድን ለብስ
እንናፍቃለንና
ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም፡፡» ይላል፡፡ ፪ኛቆሮ ፭፥፩-፪፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም፡- «ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን
በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ÷ እድፈትም ለሌለበት÷
ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት ይባረክ» ብሏል፡፡ ፩ኛጴጥ
፩÷፫፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም፡- «በሚመጡ ዘመ ናትም
በክርስቶስ
ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን
ባለጠግነት ያሳ የን ዘንድ ከእርሱ ጋር አስነ ሣን፤ በክርስቶስ
ኢየሱስም በሰማያዊው ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን።»
ብሏል። ኤፌ፪÷፮-፯።
✞ ✞ ✞
ምንጭ : የተዋሕዶ ቤተሰቦች በመላው ዓለም
ድምጽ...ድህረገጽ

የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የድንግል ማርያም አማላጅነት፣
የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣
የቅዱሳን ሐዋርያት፣ የቅዱሳን አበው መነኮሳት፣ የቅዱሳት
አንስት፣ የደናግላንና የቅዱሳን ሁሉ ምልጃና ቃል-ኪዳናቸው
ባለንበት ከሁላችን ጋር ይሁን!!!
†† † ♥ † ††
ለአባ ሕርያቆስ ፤
ለቅዱስ ኤፍሬም ፤
ለቅዱስ ያሬድ ፤
ለአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
የተገለጸች እመቤታችን እኛንም በበረከት እና በረድኤት
ትጎብኘን ፤ ከልጅዋ ከወዳጅዋ ከመድኃኔዓለም ዘንድ ታማልደን
፤ አሜን!!!
†† † ♥ † ††
ከዋክብት የሚያመሰግኑት
በስማቸውም የሚጠራቸው:
የፀጋው ብዛት የማይታወቅ
ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ
ለሐዋሪያት እንዲሁም ለቀደሙ አባቶቻችን ምሥጢሩን
እንደገለጽክላቸው ለእኛም ግለጽልን። አሜን አሜን አሜን!!!
†† †♥ † ††
ወ ስ ብ ሐ ት ለ እ ግ ዚ አ ብ ሔ ር
ወ ለ ወ ላ ዲ ቱ ድ ን ግ ል
ወ ለ መ ስ ቀ ሉ ክ ቡ ር