ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

Saturday, May 28, 2016

=>+*"+<+>ግንቦት 20-የከበረ አፄ ካሌብ ታሪክ<+>+"*+

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
አሜን
ግንቦት 20-የከበረ ጻድቅ የኢትዮጵያ ንጉሥ ዐፄ ካሌብ ዕረፍቱ
ነው፡፡ እርሱም የናግራን ሰማዕታትን ደም የተበቀለና በኋላም
ንግሥናውን ትቶ ዓለምን ንቆ በመመንኮስ ዋሻ የገባ ነው፡፡
የነገሠበትን የወርቅ ዘውዱንም በጌታችን መቃብር ላይ
አስቀምጡልኝ ብሎ ለኢየሩሳሌሙ ሊቀ ጳጳስ ለአባ ዮሐንስ
ልኮለታል፡፡
+ ከአባቶች መምህራን 16ኛ የሆነ በደብረ ሊባኖስ አበ ምኔት
ሆኖ ያገለገለ የከበረ አባ በትረ ወንጌል ዕረፍቱ መሆኑን
ስንክሳሩ በስም ይጠቅሰዋል፡፡
+ ዳግመኛም በዚኽች ዕለት የሀገረ ቶናው የከበረ አባ አሞንዮስ
ዕረፍቱ ነው፡፡
+ የቅዱስ አሞኒ ረድእ የሆነው አባ ዳርማ ዕረፍቱ መሆኑን
ስንክሳሩ በስም ይጠቅሰዋል፡፡
ጻድቁ ንጉሥ ዐፄ ካሌብ፡- ይኽም ጻድቅ ንጉሥ የናግራን
ሰማዕታትን ደም የተበቀለና በኋላም ንግሥናውን ትቶ ዓለምን
ንቆ በመመንኮስ ዋሻ የገባ ነው፡፡ የነገሠበትን የወርቅ
ዘውዱንም በጌታችን መቃብር ላይ አስቀምጡልኝ ብሎ
ለኢየሩሳሌሙ ሊቀ ጳጳስ ለአባ ዮሐንስ የላከ ነው፡፡ ስለ
እርሱም መጽሐፈ ስንክሳሩ ላይ እና አቡነ አረጋዊ ገድል ላይ
የተጻፈውን እያነበብን ዛሬ በሃገራችን ከሚከበረው ብሔራዊ
በዓል ጋር እናነጻጽረው እስቲ! (ምንም እንኳን ብርሃንና
ጨለማ ለንጽጽር ባይበቁም)
ከመጽሐፈ ስንክሳር፡- በቍስጥንጥንያ ዮስጢኖስ በነገሠ
በ5ኛው ዓመት ዐፄ ካሌብ በኢትዮጵያ ነግሦ ነበር፡፡ የአይሁድም
ንጉሥ ፊንሐስ ነበር፡፡ በዚህም ወቅት ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት
የኢየሩሳሌሙ አባ ዮሐንስ፣ የቍስጥንጥንያው አባ ጢሞቴዎስ፣
የእስክንድርያውም አባ ጢሞቴዎስ፣ የአንጾኪያው አባ
አውፍራስዮስ ነበሩ፡፡ ሳባ የምትባለው አገር በኢትዮጵያ
ነገሥታት እጅ ውስጥ ነበረች፡፡
የሮም ነገሥታት አስባስያኖስና ጥጦስ አይሁድን ወረው
ከኢየሩሳሌም አሳደዷቸውና ይህችን ሳባን አይሁድ ወረሷት፡፡
በውስጧም በጌታችን የሚያምኑ ብዙ ሕዝቦች ነበሩባት፡፡ በሳባ
ውስጥም ክርስቲያኖች የሚኖሩባት ታላቅ ከተማ ነበረች፡፡
የአይሁድ ንጉሥ ፊንሐስም ወደ ከተማዋ ገብቶ በሺህ
የሚቆጠሩትን ክርስቲያኖች ገደለ፡፡ ዙሪያ ዳር ድንበሯ
በመስቀል ምልክት የታጠረች ስለነበረች ፊንሐስ መጀመሪያ
መግባት ሳይችል ቢቀር ‹‹ወደ ውስጥ ገብቼ የከተማዋን
አሠራር፣ ገበያዋን፣ አደባባዮቿን መጎብኝት እሻለሁ እንጂ ክፉ
አላስብም፣ የማንንም ደም አላፈስም›› ብሎ ከነሠራዊቱ ከገባ
በኋላ ግን መግደል ጀመረ፡፡ መጀመሪያውንም አቡነ ኂሩተ
አምላክ ‹‹ውሸቱን ነው አታስገቡት፣ ሐሰተኛ ነው ደጁን
ከፍታችሁ አታስገቡት›› ብለው ቢነግሯቸውም የሚሰማቸው
ጠፋ፡፡ ፊንሐስም እንደገባ የሕዝቡን ገንዘብ ዘረፈ፤ ቀጥሎም
ነበልባሉ አየር ላይ ደርሶ እስኪታይ ድረስ እሳት አስነድዶ
‹‹ኤጲስ ቆጶሱን አባ ጳውሎስን አምጡልኝ›› ብሎ አዘዘ፡፡
እንደሞቱም ሲነገረው ዐፅማቸውን ከመቃብር አውጥቶ
አቃጠለው፤ ቀጥሎም ቀሳውስትን፣ ካህናትን፣ ዲያቆናትን፣
መነኮሳትን ሁሉ በእሳቱ ውስጥ እንዲጨምሯቸው አዘዘ፡፡
አራት ሺህ ሃያ ሰባት ክርስቲያኖችም ወደ እሳቱ ተጥለው
በሰማዕትነት ሞቱ፡፡
ፊንሐስም አቡነ ኂሩተ አምላክንና ታላላቅ መኳንንትን ግን
አሳስሮ ብዙ አሠቃያቸው፡፡ ‹‹ክርስቶስን ያልካደ ሁሉ ተሠቃይቶ
ይሞታል›› የሚል አዋጅ በከተማው እንዲነገር አዘዘ፡፡ አቡነ
ኂሩተ አምላክንም አስሮ እያሠቃያቸው በከተማው አዞራቸው፡፡
ሕዝቡም ‹‹ጌታችንን አንክድም›› እያሉ ወጥተው ተገደሉ፡፡
በዚህም ጊዜ የተገደሉት ቁጥራቸው 4252 ሆነ፡፡ የአቡነ አቡነ
ኂሩተ አምላክን ሚስት ቅድስት ድማህን ከ2 ልጆቿ ጋር ይዞ
አሠቃያቸው፡፡ አንደኛዋም የ12 ዓመት ሕፃን ምራቋን
በፊንሐስ ላይ ተፋችበት፣ እርሱም ሰይፉን መዞ አንገቷን
ቆረጠው፡፡ ለእናቷ ለቅድስት ድማህም የልጇን ደም አጠጣት፡፡
ድማህም ‹‹ይህን እንዲሆን የፈቀደ እግዚአብሔር ይክበር
ይመስገን›› ብላ አምላኳን ስታመሰግን ሰምቷት በንዴት
እናቲቱንም አንገቷን ቆረጠው፡፡
ፊንሐስም አቡነ ኂሩተ አምላክን ግን ወደ ውጭ አውጥቶ
‹‹የምታመልኩትን ክርስቶስን ካዱ›› አላቸው፡፡ አቡነ ኂሩተ
አምላክም ‹‹ክብር ይባውና ጌታዬን ኢየሱስ ክርስቶስን
እያለመኩ ስኖር 78 ዓመት ሆነኝ፣ እስከ አራት ትውልድም
ለማየት ደርሻለሁ፡፡ ዛሬም ስለከበረ ስሙ ምስክር ሆኜ ስሞት
እጅግ ደስ ይለኛል፡፡ ወደዚህ ለመግባት ስትምል እኔም
አስቀድሜ መሐላህን እንዳያምኑ ለወገኖቼ ነግሬአቸው ነበር፤
አንተ ሐሰተኛ ነህና ነገር ግን ይህ ሁሉ የእግዚአብሔር ፈቃድ
ነው፤ ለዚህ ተጋድሎ ላበቃኝ ለእርሱ ምስጋና ይሁን›› እያሉ
ፊንሐስን በተናገሩት ጊዜ ወደ ወንዝ ወስዶ አንገታቸውን
አስቆረጠው፡፡ አቡነ ኂሩተ አምላክ በሰማዕትነት ከማረፋቸው
በፊት የኢትዮጵያንና የሮምን መንግሥት ያጸና ዘንድ የአይሁድን
መንግሥት ግን ያጠፋ ዘንድ ጌታችንን ለመኑት፡፡ ዕረፍታቸውም
ኅዳር 26 ቀን ነው፡፡ አቡነ ኂሩተ አምላክም ሕዝቡን
ተሰናብተው በተሰየፉ ጊዜ አንዲት ሴት ደማቸውን ለ5 ዓመቱ
ልጇ ቀባችው፡፡
ይህንንም ሲያዩ ልጇን ነጥቀው ለንጉሡ ሰጥተው እርሷን
ከእሳቱ ውስጥ ጨመሯት፡፡ ንጉሡ ፊንሐስም ሕፃኑን ‹‹እኔን
ትወዳለህ ወይስ ክርስቶስ የሚሉትን?›› ብሎ ጠየቀው፡፡ የ5
ዓመቱ ሕፃንም ‹‹እኔስ የእጁ ሥራ ነኝና ክርስቶስን እወደዋለሁ፣
ይልቅስ ልቀቀኝና ወደ እናቴ ልሂድና ሰማዕትነቴን ልፈጽም››
አለው፡፡ ፊንሐስም ከእጁ እንዳይወጣ በያዘው ጊዜ እግሩን
ነክሶት አምልጦት ሮጦ ሄዶ ከእሳቱ ውስጥ ገባ፡፡ ሁለተኛም
የ10 ወር ሕፃን የተሸከመች አንዲት አማኝ ሴት ወደ ልጇ
እያየች ‹‹ልጄ ሆይ ዛሬስ ላዝንልህ አልቻልኩም›› ብላ ስትናገር
በእቅፏ ያለው የ10 ወሩ ሕፃን ልጇም አንደበቱን ከፍቶ ‹‹እናቴ
ሆይ በፍጥነት ወደ ዘላለም ሕይወት እንሂድ ይህችን እሳት ከዛሬ
በቀር አናያትምና›› አላት፡፡ እርሷም ልጇን ይዛ ዘላ እሳቱ
ውስጥ ተወርውራ ገባች፡፡ የክርስቲያን ወገኖችም ይህን ሁሉ
አይተው እኩሉ ወደ እሳት እኩሉ ወደ ሰይፍ ተሽቀዳደሙ፡፡
ራሳቸው የአይሁድ ሠራዊት ዕፁብ ብለው እስኪያደንቁ ድረስ
ክርስቲያኖቹ ወደ ሰማዕትነት ተፋጠኑ፡፡ በዚህም ጊዜ የሞቱት
ቁጥራቸው ሃያ ሺህ ነበር፡፡ ክርስቲያኖቹም በሞሞቱበት ጊዜ
የረዳቶቻቸውን የቊስጥንጥንያንና የኢትዮጵያን ነገሥታት ስም
በጸሎታቸው ይጠሩ ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ እሳቱ በሰማይ ውስጥ
መልቶ 40 ቀንና 40 ሌሊት ታየ፡፡
ፊንሐስም ወደ ሀገሩ በተመለሰ ጊዜ ወደ ነገሥታቱ ሁሉ በኋይሉ
እየተመካ ላከባቸው፡፡ የሮሜው ንጉሥ ዮስጢኖስም ይህን
ሰምቶ ወደ እስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ ወደ አባ ጢሞቴዎስ
መልአክት ላከ፡፡ ለሀገረ ናግራን ክርስቲያኖች ደማቸውን
ይበቀልላቸው ዘንድ ለኢትዮጵያው ንጉሥ ለዐፄ ካሌብ
መልእክት እንዲልክ ነገረው፡፡ ዐፄ ካሌብም መልእክቱ
ሲደርሰው ፈጥኖ ተነሣና በዋሻ ከሚኖር ከአቡነ ጰንጠሌዎን
በረከትን ተቀብሎ ለአቡነ አረጋዊም በጸሎት እንዲያስቡት
ደብዳቤ ጽፎ ከላከ በኋላ ከሠራዊቱ ጋር በመርከብ ተጭኖ ወደ
ሀገረ ናግራን ሄደ፡፡ ከመሄዱም በፊት ለአቡነ አረጋዊ የላከላቸው
መልእክት እንዲህ የሚል ነው፡- ‹‹ፊንሐስ የተባለ አረማዊ
የናግራን ክርስቲያኖችን ደም በከንቱ ያፈሰሰ፣ ቤተ ክርስቲያንን
የመዘበረና ያጠፋ ፍጹም የእግዚአብሔር ጠላት ወደሚሆን ሄጄ
እዋጋው ዘንድ ተዘጋጅቻለሁ፡፡ ስለዚህ አባቴ ሆይ! አንተም
በበኩልህ ጸሎት አድርግልኝ፣ የጻድቅ ጸሎት ትራዳለች፣
ኃይልንም ታሰጣለች፣ በጠላት ላይ ድልንም ታቀዳጃለችና››
ሲል ላከበት፡፡ አባታችን አቡነ አረጋዊም ለንጉሡ ጭፍሮች
‹ወደ ጦሩ ግንባር ሂድ፣ እግዚአብሔር ጠላቶችህን ከእግርህ
በታች ያስገዛልህ፣ ለአንተም ግርማ ሞገስ ይስጥህ፣ በሰላም
ይመልስህ›› ብለው መርቀው ላኩለት፡፡ ከዚህ በኋላ ዐፄ ካሌብ
ልብሰ መንግሥቱን አውልቆ ጥሎ ማቅ ለብሶ በፍጹም ልመና
ብዙ ጸሎት አደረገ፡፡
ከዚህም በኋላ ዐፄ ካሌብ ሰባ ሺህ ጦሩን አዘጋጅቶ ወደ የመን
ሳባ በመርከብ ተጓዘና ከከሐዲው ፊንሐስ ጋር ጦር ገጠመ፡፡
ከሐዲውን ንጉሥ ፊንሐስን ራሱ ዐፄ ካሌብ ገጠመውና በፈረሱ
ላይ እንደተቀመጠ በጨበጣ በጦር ወግቶ ገደለውና ወደ ባሕር
ገልብጦ ጣለው፡፡ ከዚያም ዐፄ ካሌብ ዛፋር ወደምትባለው
ከተማ ሄዶ እርሷንም ተቆጣጠራት፡፡ በእዚያም ያሉ የፊንሐስን
ሹማምንቶች እያፈላለገ በአደባባይ እንዲገደሉ በማድረግ
የክርስቲያኖቹን ደም በሚገባ ተበቀለ፡፡ የናግራንንም
ሕንፃዎዋን አደሰ፤ የሰማዕታቱንም መታሰቢያ አቆመ፡፡ ወደ
እስክንድርያው አባ ጢሞቴዎስና ወደ ሮሜው ንጉሥ
ዮስጢኖስም የድል መልእክት ላከላቸውና እነርሱም ሰምተው
እጅግ ተደሰቱ፡፡ በአንጾኪያ፣ በእስክንድሪያ፣ በሮም፣
በቊስጥንጥንያና በዓለም ላይ ያሉ ክርስቲያኖች ሁሉ ይህን
ሲሰሙ በእጅጉ ተደሰቱ፡፡ ይህም የሆነው በ525 ዓ.ም ነው፡፡
ጠፍተው የሄዱ ክርስቲያኖችንም ሰበሰባቸውና ወደቀደመ
ቦታቸው መለሳቸው፣ ቤተክርስቲያናቸውን አነጸላቸው፡፡ ከሳባ
ሀገር የማረከውን ንብረት ሁሉ ለቤተክርስቲያን ሰጥቶ ዓሥር
ሺህ ጠባቂ ሠራዊት ሰቷቸው ወደ አክሱም በሰላምና በፍጹም
ደስታ ተመለሰ፡፡
ከአቡነ አረጋዊ ገድል፡- በቍስጥንጥንያ ዮስጢኖስ በነገሠ
በ5ኛው ዓመት ዐፄ ካሌብ በኢትዮጵያ ነግሦ ነበር፡፡ የአይሁድም
ንጉሥ ፊንሐስ ነበር፡፡ በዚህም ወቅት ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት
የኢየሩሳሌሙ አባ ዮሐንስ፣ የቍስጥንጥንያው አባ ጢሞቴዎስ፣
የእስክንድርያውም አባ ጢሞቴዎስ፣ የአንጾኪያው አባ
አውፍራስዮስ ነበሩ፡፡ ‹‹ከክርስቶስ ልደት 524 ዓመት በኋላ
በናግራን ሀገር በክርስቲያኖች በአይሁዶችና በአረማውያን
መካከል ከባድ ፀብ ተነሣ፡፡ ማዝሩቅ ወይም ፊንሐስ የተባለው
የሂማሪያው ንጉሥ የአይሁዶችንና የአረመኔዎቹን ምክር
እየተቀበለ ክርስቲያኖቹን ፈጃቸው፣ አብያተ ክርስቲያናቱንም
ሁሉ አቃጠለ፡፡ አረማዊው ንጉሥ ‹አምላካችሁን ክርስቶስን
ብትክዱት ሕይወታችሁ ይጠበቃል› ቢላቸውም ክርስቲያኖቹ ግን
‹ስለ አምላካችን ስለ ክርስቶስ መሞትን አንፈራም› ስላሉትና
በእምነታቸው ስለጸኑ የክርስቲያኖቹ መሪ የ95 ዓመት ዕድሜ
ያለውን ቅዱስ ኂሩት ከነቤተሰቦቹ በመጀመሪያ በንጉሡ ፊት
ለፍርድ ቀረበ፡፡ ለንጉሡም በድፍረት ‹እንዳንተ ባለው ከሐዲ
ንጉሥ ፊት አምላኬን አልክድም› ብሎ ስለመለሰለት ንጉሡም
በንዴት አንገቱ እንዲቆረጥ ፈረደበትና ቅዱስ ኂሩት ከቤተሰቦቹ
ጋር የሰማዕትነትን ክብር ተቀዳጀ፡፡
ቁጥራቸው ብዙ የሆኑ የቅዱስ ኂሩት ተከታዮችንና
ክርስቲያኖችንም ጥልቅ ጉድጓድ ቆፍሮ በዚያ ውስጥ በእሳት
ተቃጥለው እንዲሞቱ አደረጋቸው፡፡ ክርስቲያኖቹም
በሞሞቱበት ጊዜ የረዳቶቻቸውን የቊስጥንጥንያንና
የኢትዮጵያን ነገሥታት ስም በጸሎታቸው እየጠሩ በሰማዕትነት
ሞቱ፡፡ ቁጥራቸው ሃያ ሺህ ነበር፡፡ ይኽ ጨካኝ አረመኔ ንጉሥ
ቀደም ብለው ያረፉትን የኤጲስ ቆጶሱን የጳውሎስን አፅም
አውጥቶ በእሳት አቃጠለው፡፡ እንዲሁም የቀሩትን ክርስቲያኖች
ካሉበት እያደነ በሰይፍና በእሳት አጠፋቸው፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ
የቊስጥንጥንያው ሊቀ ጳጳስ ጢሞቴዎስ በናግራን አገር
ስለተፈጁት የክርስቲያን ወገኖች በግፍ የተጨፈጨፉበትን
መልእክት የያዘች ደብዳቤ ወደ ኢትዮጵያው ንጉሥ ወደ ዐፄ
ካሌብ ላከ፡፡ ዐፄ ካሌብም መልእክቱን ከተረዳ በኋላ ወደ ብፁዕ
አቡነ አረጋዊ እንዲህ ሲል መልእክት ላከ፣ ‹ፊንሐስ የተባለ
አረማዊ የናግራን ክርስቲያኖችን ደም በከንቱ ያፈሰሰ፣
ቤተክርስቲያንን የመዘበረና ያጠፋ ፍጹም የእግዚአብሔር ጠላት
ወደሚሆን ሄጄ እዋጋው ዘንድ ተዘጋጅቻለሁ፡፡ ስለዚህ አባቴ
ሆይ! አንተም በበኩልህ ጸሎት አድርግልኝ፣ የጻዲቅ ጸሎት
ትራዳለች፣ ኃይልንም ታሰጣለች፣ በጠላት ላይ ድልንም
ታቀዳጃለችና› ሲል ላከበት፡፡ አባታችን አቡነ አረጋዊም ለንጉሡ
ጭፍሮች ‹ወደ ጦሩ ግንባር ሂድ፣ እግዚአብሔር ጠላቶችህን
ከእግርህ በታች ያስገዛልህ፣ ለአንተም ግርማ ሞገስ ይስጥህ፣
በሰላም ይመልስህ› ብለው መርቀው ላኩበት፡፡ ከዚህ በኋላ ዐፄ
ካሌብ ልብሰ መንግሥቱን አውልቆ ጥሎ ማቅ ለብሶ በፍጹም
ልመና ብዙ ጸሎትን አደረገ፡፡
ዐፄ ካሌብ ታላቅ ጻዲቅ ንጉሥ ነበር፣ ከምድር ነገሥታት ወገን
በመንግሥቱ ዙፋን ላይ ተቀምጦ እያለ እንደ እርሱ ድንቅ
ተአምራት ያደረገ የለም፡፡ ከሁሉ በፊት የዑር አገር ሰዎች
ባመፁበት ጊዜ የሀገሪቱ ሰዎች የጦሩን መትመምና ግስጋሴ
አይተው እንዳይሸሹና እንዳያመልጡ እግዚአብሔር በምድር
ውስጥ መንገድን ከፈተለት፡፡ የመንገዱም ርዝመት በፈጣን ሰው
ሩጫ ሦስት ቀን ያስኬዳል፡፡ ንጉሡ እግዚአብሔር በከፈተለት
የምድር ውስጥ መንገድ ገብቶ ገስግሶ ድንገት ደረሰና
ደመሰሳቸው፣ አጠፋቸውም፡፡ ከእነርሱ አንድ ስንኳ አላስቀረም፣
ሀገሪቱንም በእጁ አገባት፣ እስከዛሬም ድረስ አለች፡፡ ከዚያም
ከ524 ዓ.ም በኋላ ሰባ ሺህ ጦሩን አዘጋጅቶ ቀድሞ ወዳሰበበት
ወደ የመን ሳባ በመርከብ ተጓዘና ከከሐዲው ፊንሐስ ጋር ጦር
ገጠመ፡፡ ከሐዲውን ንጉሥ ፊንሐስን ራሱ ዐፄ ካሌብ ገጠመውና
በፈረሱ ላይ እንደተቀመጠ በጨበጣ በጦር ወግቶ ገደለውና ወደ
ባሕር ገልብጦ ጣለው፡፡ ከዚያም ዐፄ ካሌብ ዛፋር
ወደምትባለው ከተማ ሄዶ እርሷንም ተቆጣጠራት፡፡ በእዚያም
ያሉ የፊንሐስን ሹማምንቶች እያፈላለገ በአደባባይ እንዲገደሉ
በማድረግ የክርስቲያኖቹን ደም በሚገባ ተበቀለ፡፡ በአንጾኪያ፣
በእስክንድሪያ፣ በሮም፣ በቊስጥንጥንያና በዓለም ላይ ያሉ
ክርስቲያኖች ሁሉ ይህን ሲሰሙ በእጅጉ ተደሰቱ፡፡ ይህም
የሆነው በ525 ዓ.ም ነው፡፡ ጠፍተው የሄዱ ክርስቲያኖችንም
ሰበሰባቸውና ወደቀደመ ቦታቸው መለሳቸው፣
ቤተክርስቲያናቸውን አነጸላቸው፡፡ ከሳባ ሀገር የማረከውን
ንብረት ሁሉ ለቤተክርስቲያን ሰጥቶ ዓሥር ሺህ ጠባቂ ሠራዊት
ሰቷቸው ወደ አክሱም በሰላምና በፍጹም ደስታ ተመለሰ፡፡ ከዚህ
በኋላ ዐፄ ካሌብ ‹ይህን ያደረገልኝን አምላኬን በምን
ላስደስተው?› ሲል አሰበና ዓለምን ንቆ፣ መንግሥቱንና ክብሩን
ትቶ መንኩሶ በዋሻ ለመቀመጥ ወሰነ፡፡››
ዐፄ ካሌብ ዓለምን ንቆ፣ ልብሰ መንግሥቱን አውልቆ
በመመንኮስ ዋሻ እንደገባ፡- ‹‹ንጉሡ ዐፄ ካሌብ የናግራን
ሰማዕታት ደም ተበቅሎላቸው ሁሉንም ነገር አስተካክሎላቸው
በደስታ ወደ አክሱም ከተመለሰ በኋላ ‹ይህን ያደረገልኝን
አምላኬን በምን ላስደስተው?› ሲል አሰበና ተድላውን፣
ደስታውን ዓለምን ንቆ፣ ልብሰ መንግሥቱን አውልቆ አንዲት
የውኃ መንቀልና አንዲት ምንጣፍ ብቻ ይዞ አባ ጰንጠሌዎን
ገዳም አጠገብ ከሚገኝ ዋሻ ውስጥ ገብቶ በአባ ጰንጠሌዎን እጅ
መንኩሶ ለመቀመጥ ወሰነ፡፡ አባ ጰንጠሌዎንንም
‹አመንኩሰኝ› አለውና የመላእክትን አስኬማ አልብሶ
አመነኮሰው፡፡ ዳግመኛም ከዋሻው ወጥቶ ዓለምን በዓይኑ
እንዳያይ ማለ፡፡ ዋጋው እጅግ የከበረውንና በነገሠ ጊዜ
የጫነውን ዘውዱን ከጌታችን መካነ መቃብር ወይም በር ላይ
ይሰቀልለት ዘንድ ከአደራ ደብዳቤ ጋር ለኢየሩሳሌሙ ሊቀ
ጳጳሳት ለአባ ዮሐንስ ላከለት፡፡
ዳግመኛም ንጉሡ ዐፄ ካሌብ ‹አባቴ ሆይ በአንተ ጸሎት
በእግዚአብሔር ቸርነት ከጦርነቱ በሰላም ተመልሻለሁ፣
አሁንም የክርስቶስን አርዑተ መስቀል ተሸክሜአለሁና
እግዚአብሔር ለፍጻሜው ያብቃህ እያልህ ስለ እኔ ጸልይልኝ›
ብሎ ወደ አባታቸን ወደ አቡነ አረጋዊ ላከበት፡፡ ስለዚህም ነገር
አባታቸን ወደ አቡነ አረጋዊ በጣም ተደሰቶ ‹ልጄ ሆይ!
መልካሙንና የበለጠውን አድርገሃል፣ አሁንም እግዚአብሔር
የፈቀደከውን ነገር ሁሉ ይፈጽምልህ› ብለው መረቁት፡፡
ኢትዮጵያዊው ንጉሥ ዐፄ ካሌብ ይህን ዓለም በመናቅ በበረሃ
በዋሻ 12 ዓመት በጾም በጸሎት በብዙ ተጋድሎ ሲኖር ቆይቶ
በግንቦት 20 ቀን ዐርፎ እስከ ዘለዓለሙ ድረስ የማያልፍ
ሰማያዊ ክብርን ወረሰ፡፡›› ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ
ይማረን፡፡