ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

Wednesday, May 11, 2016

=>+*"ግንቦት 3"*+

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
አሜን
ግንቦት 3
+ ጌታችን ከመረጣቸው ከሰባ ሁለቱ አርድእት ውስጥ አንዱ
የሆነውና ቅዱስ ጳውሎስ በጠርሴስ አገር ላይ ኤጲስቆጶስነት
የሾመው ሐዋርያው ቅዱስ ያሶን ዕረፍቱ ነው፡፡
+ ሰማዕቱ አባ ብሶይ ሰማዕትነቱን በድል ፈጸመ፡፡
+ ‹‹የንጉሥ ወግና ሰገድ እናቱ የሆነች የተባረከች ንግሥት ወለተ
ማርያም›› ዕረፍቷ መሆኑን ስንክሳሩ በስም ይጠቅሳታል፡፡
እርሷም በምግባር፣ በሃይማኖትና በመንፈሳዊ ተጋድሎ
የከበረችና የተመሰገነች ናት፡፡
+ + + + + + + + + + + + + + +
ሰማዕቱ አባ ብሶይ፡- ይኽንንም ቅዱስ ክፉዎችና ጣኦት
አምላኪዎች ይዘውት ሰውነቱን በማጣመምና በመቆልመም
ብዙ አሠቃዩት፡፡ የእግዚአብሔርም መልአክ በእጁ አክሊል ይዞ
‹‹አትፍራ ጽና፣ እነሆ በእጄ ውስጥ አክሊል አለ›› አለው፡፡
ደግሞም ብዙ ካሠቃዩት በኋላ ወደ እሳት ውስጥ ጨመሩት፡፡
ጌታችንንም በማመን እስከመጨረሻው ጸንቶ ተጋድሎውንም
በዚኹ ፈጸመ፡፡ መልአኩም አስቀድሞ አሳይቶ ተስፋ
እንደሰጠው የሰማዕትነት አክሊልን አቀዳጀው፡፡ የሰማዕቱ
የቅዱስ ብሶይ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡
+ + + + + + + + + + + + + + +
ሐዋርያው ቅዱስ ያሶን፡- ይኽም ቅዱስ ሐዋርያ ከከበሩ
ሐዋርያት ጋራ ወንጌልን በሰበከ ጊዜ ብዙ አሠቃቂ መከራዎችን
በጌታችን ስም ተቀበለ፡፡ በ50ኛው ቀን ከሐዋርያት ጋራ አጽናኝ
መንፈስ ቅዱስን ተቀብሏልና ድንቅ ድንቅ የሆኑ ብዙ
ተአምራትን አደረገ፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ያሶን ትውልዱ ከጠርሴስ አገር ነው፡፡
ጠርሴስም ሰዎች አስቀድሞ በወንጌል ያመነው እርሱ ነው፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከተጠራና ካመነ በኋላ ወንጌልን ዞሮ
ሲሰብክ ቅዱስ ያሶን ተከትሎት በብዙ አገሮች በወንጌል
ትምህርት አገልግሎታል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ያሶን
በተሰሎንቄ ከተማ ወንጌልን ሲሰብኩ ክፉዎች ይዘዋቸው
እየጎተቱ ወስደው ከተሰሎንቄ አገር ገዥ ፊት አቅርበዋቸዋል፡፡
ከዚህም በኋላ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ቅዱስ ያሶንን
በጠርሴስ አገር ላይ ኤጲስቆጶስነት ሾመው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ
ያሶንም ቤተ ክርስቲያንን በመልካም አጠባበቅ ጠበቃት፡፡
ምእመናንን በቀናች ሃይማኖት ካጸናቸውና በበጎ ምግባር
ካነጻቸው በኋላ ወደ ምዕራብ አገር ሄዶ በዚያ ወንጌልን ሰበከ፡፡
ስሟ ኮራኮራስ ወደምትባል ደሴትም ገብቶ በውስጧ ወንጌልን
ሰብኮ ነዋሪዎቿን እግዚአብሔርን ወደማመን መለሳቸው፡፡
በደሴቷም ውስጥ በዲያቆናት አለቃ በሰማዕቱ በቅዱስ
እስጢፋኖስ ስም ቤተ ክርስቲያን ሠራላቸው፡፡ የአገሪቱ ገዥም
ይኽንን ባወቀ ጊዜ ቅዱስ ያሶንን ይዞ ከእሥር ቤት ጣለው፡፡
ሐዋርያው ግን በእሥር ቤት ያገኛቸውን ሰባት ኃይለኛ
ወንበዴዎችን አስተምሯቸው ካሳመናቸው በኋላ አጠመቃቸው፡፡
እነርሱም በከሃዲው መኮንን ፊት በጌታችን ታመኑ፡፡ ‹‹በቅዱስ
ያሶን አምላክ እናምናለን›› ብለውም በጮኹ ጊዜ መኮንኑ
ዝፍጥና ድን በተመላ ምጣድ ውስጥ አግብቶ አቃጠላቸው፡፡
የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበሉ፡፡ ረድኤት በረከታቸው
ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን፡፡
ከዚኽም በኋላ መኮንኑ ቅዱስ ያሶንን ከእሥር ቤት አውጥቶ ብዙ
አሠቃየው ነገር ግን ጌታችን መከራውን ያስታግስለት ነበርና
ምንም እንዳልነካው ሆነ፡፡ በተአምራቱም ብዙዎችን
አሳመናቸው፡፡ የንጉሡም ሴት ልጅ ከቤቷ መስኮት ሆና አይታ
በክብር ባለቤት በጌታችን አመነች፡፡ ልብሶቿንና ጌጦቿንም ሁሉ
አውጥታ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች ሰጠችና በሐዋርያው
በቅዱስ ያሶን አምላክ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ
ክርስቶስ ስም ታመነች፡፡ ንጉሡ አባቷም ይኽንን በሰማ ጊዜ
ይዞ አሠራት፡፡ ጌታችንንም በማመን ስለጸናች አባቷ ብዙ
ሥቃጦችን አደረሰባት፡፡ በጢስ አፍኖ አሠቃያት፣ ልብሷን
አውልቆ ካራቆታት በኋላ ሰውነቷን በፍለጻ ነደፋት እርሷም
በዚሁ ሰማዕትነቷን ፈጽማ ነፍሷን ለእግዚአብሔር ሰጠች፡፡
ረድኤት በረከቷ ይደርብን፣ በጸሎቷ ይማረን፡፡
ከዚኽም በኋላ ሐዋርያው ቅዱስ ያሶንን አሠቃይተው ይገድሉት
ዘንድ ከአንድ መኮንንና ከሠራዊቱ ጋራ ወደ ደሴት ሰደደው፡፡
መኮንኑም በመርከብ ወደዚያ በሄደ ጊዜ እግዚአብሔር
መኮንኑን ከነሠራዊቱ አሰጠመው፡፡ ቅዱስ ያሶንም ወንጌልን
ተዘዋውሮ እየሰበከ ብዙ ዘመናት ኖረ፡፡ ሁለተኛም ሌላ መኮንን
በተሾመ ጊዜ ቅዱስ ያሶንን ይዞ በምጣድ ውስጥ ድኝና ዝፍጥ
ሰም መልቶ ነበልባሉ ወደላይ እስኪወጣ ድረስ ከሥሩ አነደደና
ሐዋርያውን በውስጡ ጨመረው፡፡ ነገር ግን የክብር ባለቤት
ጌታችን አገልጋዩን ያለምንም ጉዳት አዳነው፡፡ መኮንኑም
ይኽንን ድንቅ ሥራ ባየጊዜ በክብር ባለቤት በጌታችን በኢየሱስ
ክርስቶስ ስም አመነ፡፡ ቤተሰቦቹና የአገሪቱ ሰዎችም ሁሉ
አብረው አመኑ፡፡ ቅዱስ ያሶንም አጠመቃቸው፡፡ ቤተ
ክርስቲያንም ከሠራላቸው በኋላ የከበረች የወንጌልን ሕግና
ትእዛዝ ሠራላቸው፡፡ እነርሱም በምግባር በሃይማኖት ጸኑ፡፡
ሐዋርያውም ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን አደረገላቸው፡፡
መልካም የሆነውን አገልግለቱንም ፈጽሞ በበጎ ሽምግልና ሆኖ
በዚኽች ዕለት ዐረፈ፡፡ የሐዋርያው የቅዱስ ያሶን ረድኤት በረከቱ
ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡

=>+++ግንቦት 4+++

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
አሜን
ግንቦት 4
በደጃቸው የተቀበረውን ሰው ዐፈር የማያስበሉት ኢትዮጵያዊው
ጻድቅ አቡነ መልከጼዴቅ ዕረፍታቸው ነው፡፡
የብሩክ ፊቅጦር አገልጋዮች የሆኑ ሶሲማ እና ኖዳ በሰማዕትነት
እንዳረፉ ስንክሳሩ በስም ይጠቅሳቸዋል፡፡
ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ መልከጼዴቅ፡- አቡነ መልከጼዴቅ
በ13ኘው መ/ክ/ዘ መጨረሻ በንጉሥ ዐፄ በእደ ማርያም
ዘመነ መንግሥት የነበሩ እደጃቸው የተቀበረውን ሰው አፈር
የማያስበሉ እጅግ ድንቅ ቃል ኪዳን ያላቸው ታላቅ አባት
ናቸው፡፡ የአምላካቸውን የክርስቶስን መከራ ለማሰብ ገዳመ
ቆሮንቶስን የመሰለ ዋሻ ቆፍረውና በዚያ ገብተው ቀንና ሌሊት
ዘግተው በረደኝ ፀሐይ ልሙቅ፣ ጨለመኝ ብርሃን ልይ ሳይሉ
በጸሎት ብቻ ዘግተው በመኖር ራሳቸውን በችንካር እያቆሰሉና
ጭንቅላታቸውን እያተሉ ትሉን ለሰማይ አእዋፍ ይመግቡ
ነበር፡፡ እግዚአብሔር ወልድ የተገረፈውን ግርፋት እያሰቡ
በየቀኑ እስከ 3ሺህ ድረስ ይሰግዱ ሰውነታቸውንም እንዲሁ
ይገርፉ እንደነበር መጽሐፈ ገድላቸው ይናገራል፡፡ የክርስቶስን
መቸንከር እያሰቡ እጅና እግራቸውን፣ ወገብና ደረታቸውን
በብረት ቸንክረው መከራውን ያስቡ ነበር፡፡ ጎኑ በጦር መወጋቱን
አስበው አጥንታቸው እስኪሰበር ድረስ ጎናቸውን ወጉ፡፡ ሐሞትና
ከርቤ መጠጣቱን አስበው እርሳቸውም መራራ ይጠጡና
አንክርዳድን ይመገቡ ነበር፡፡ ሞቱን አስበው ደም እንባን ያነቡ
ነበር፡፡ በእንደዚህ ዓይነቱ ተጋድሎ የክርስቶስን መከራ እያሰቡ
ነቢያን፣ ሐዋርያትን፣ ሰማዕታትን፣ ደናግል መነኮሳትን መስለው
ሁሉን እያከናወኑ እያለ የወዳጆቹን መከራ የማይዘነጋ፣ የሰውን
የድካሙን ዋጋ ፈጽሞ የማያስቀር አምላክ ሠራዊተ መላእክትን
አስከትሎ መጥቶ ‹‹መገረፍህ፣ ስለ እኔ መገረፍ ይሁንልህ፣
የደምህ መፍሰስ ስለ እኔ ደም መፍሰስ ይሁንልህ፣
መቸንከርህም ስለ እኔ መቸንከር ይሁንልህ፣ ሞትህም ስለ እኔ
ሞት ይሁንልህ›› ብሎ የሚከተለውን ቃልኪዳን ሰጥቷቸዋል፡-
‹‹ከዚህ ቦታ መጥቶ የተሳለመውን እምርልሃለሁ፤ ነፍሱ በአንተ
ቃልኪዳን የማይማር በአንተ ቦታ ለመሳለምም፣ ንስሓ
ለመግባትም ሆነ ለመቀበር አላቀርብብህም፤ መጥቶም
የተቀበረውን ሥጋውን አፈር አይበላውም›› የሚል እጅግ ድንቅ
ቃል ኪዳን ነው መድኃኔዓለም የሰጣቸው፡፡ ቃል ኪዳኑንም
የሰጣቸው ቅዱሳን መልእክትን፣ ነቢያትን፣ ሐዋርያትን፣
ጻድቃንን፣ ሰማዕታትን፣ ቀሳውስትን፣ ዲያቆናትን፣ ደናግል
መነኮሳትን ሁሉ ምስክር አቁሞ እንደሆነ ቅዱስ ገድላቸው
ይናገራል፡፡ ይህም ድንቅ ቃልኪዳን ዛሬም በገሀድ እየታየ ነው፡፡
እስከ ዕለተ ምጽዓትም ሲታይ ይኖራል፡፡ በደጃቸው የተቀበረ
ሰው አይበሰብስም፡፡ ይህም የሥጋው አለመበስበስ ለሞተው
ሰው ለሥጋው አንዳች ረብ ጥቅም ኖሮት ሳይሆን የጻዲቁ
ቃልኪዳናቸው እስከ ዕለተ ምፅዓት ድረስ ተፈጻሚ መሆኑንና
ምልክትን ለሚሻ ለዚህ ክፉ ዘመን ትውልድ ምልክት ይሆን
ዘንድ ነው፡፡
ከአ.አ 225 ኪ.ሜ ርቀት ለመራኛ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው
የሚዳ አቡነ መልከጼዴቅ ገዳም ተፈጥሮአዊ አቀማመጡ
እጅግ አስገራሚ በሆነው ዋሻ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሁሉም
ነገር በግልጽ ይታያል፡፡ ይህም እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ሁሉ
በተለይም እኛ ኢትዮጵያውን በኃጢአት ሳንጠፋበት የመዳኛ
መንገድ አድርጎ የሰጠን ድንቅ የቃል ኪዳን አባታችን
መሆናቸውን ተረድቶና አውቆ በቃል ኪዳናቸው መጠቀም
መቻል በራሱ ዕድለኛነት ነው፡፡ አቡነ መልከጼዴቅ ጌታችን
ዕድሜአቸው ረጅም መሆኑን በምሳሌ እያሳየ ሲነግራቸው
‹‹በዚህ ዓለም መኖር ጥቅሙ ምንድር ነው? ወደ እረፍትህ
ውሰደኝ እንጂ›› ብለው ሞታቸውን የለመኑ ቅዱስና ጻዲቅ አባት
ናቸው፡፡ ከመጽሐፈ ገድላቸው ውስጥ አንዳንድ ነጥቦች እንይ፡-
1.ትልቅ የቅድስና ደረጃ ላይ ቢደረስም እንኳ ራስን ለካህን
ማሳየት እንደሚገባ፡- ‹‹አባታችን መልከጼዴቅ ወደ ዋልድባ
ገዳም ሄደ፡፡ ወደ እምፍራንዝ ደብር ሄዶ ቤተክርስቲያንን እጅ
ነሳ፣ ተሳለመ፣ በውስጧም ጸለየ፡፡ ጸሎቱንም በፈጸመ ጊዜ
መድኃኔዓለም ‹አትፍራ፣ በምትሄድበት መንገድ ሁሉ እኔ ከአንተ
ጋር እሆናለሁና› አለው፡፡ ሰላምታንም ሰጥቶት ከእርሱ
ተሰወረ፡፡ ከቤክርስቲያንም ወጥቶ ከቅዱሳን ሁሉ ጋር እጅ
ተነሳሳ፤ ‹አባ አባ ገረምኸን ከየት መጣህ?› አሉት፡፡ ‹እኔ
ኃጢአተኛና በደለኛ ስሆን ከምዕራብ አገር ቅዱሳንን ለመጎብኘት
መጣሁ› አላቸው፡፡ ይህንንም እየተናገረ እያለ እግዚአብሔርን
የምትፈራ አንዲት መነኩሲት ሴት ወደ እርሱ መጣችና እጅ
ነሳችው፡፡ እግሩንም ሳመችው፡፡ ዐይነ ስውር ነበረችና
‹የእግዚአብሔር ሰው ወደ እኛ መምጣትህ መልካም ነው፤
ሰላም ለአንተ ይሁን› አለችው፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ
አስቀድሞ ነገረኝ ‹የእግዚአብሔር ካህን መልከጼዴቅ
ይመጣል፣ እርሱም ይናዘዝሻል አለኝ› አለች፡፡ ይህንን ስትናገር
አባታችን መልከጼዴቅ ይህችን ዐይነ ስውርና ጻዲቅ ሴት ከራስ
ጠጉሯ እስከ እግር ጣቶቿ በወርቅ ልብስ ተሸልማ በመስቀል
ምልክት የተሠራ የብርሃን አክሊል በራስዋ ላይ ደፍታ ቅዱስ
ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል በቀኟና በግራዋ እየጠበቋት አያት፡፡
አባታችን መልከጼዴቅም ይህን ባየ ጊዜ አደነቀ፡፡ ‹እኔን
እንደጻድቅ ሰው አታስመስይኝ፣ ለሴቶች ንስሓ መስጠት
ቢቻላቸውስ ኖሮ እኔን በናዘዝሽኝ ነበር› አላት፡፡
ባስጨነቀችውም ጊዜ ንስሓ ሰጣት፡፡ ጻዲቋ ሴት በእርሱ ዘንድ
የተናዘዘች ኃጢአት ስለሠራች አይምሰላችሁ ‹በቃልህ
የተናዘዘውን ምሬልሃለሁ› ብሎ ለአባታችን ለመልከጼዴቅ
እግዚአብሔር በሰጠው በምህረቱ ቃልኪዳን ትጨመርና
በረከቱን ትቀበል ዘንድ ነው እንጂ፡፡ ወንድሞቸ ሆይ በደላችሁን
ለካህን ማሳየትን አታስታጉሉ፡፡ ጻዲቅ ሰውም እንኳ ቢሆን
ራሱን ለካህን ማሳየትን አያስታጉል፡፡ መጽሐፍ ‹እሳት ወርቅን
ከሚያጠራው በስተቀር ምን ያደርገዋል?› ይላልና፡፡ ይህችም
ጻዲቅ ሴት የዳነች የጠራች ስትሆን እንደ ኃጢአተኛ
ተናዘዘችለት፣ በኋላም በማዘን በቅዱስ መልከጼዴቅ ላይ
የሚመጣውን ሁሉ ትንቢት ነገረችው›› እንዲሁም በብሔረ
ሕያዋን ያለ አንድ የእግዚአብሔር ሰው ወደ ቅዱስ አባታችን
ዘንድ መጥቶ ኑዛዜን እንደተቀበለ አቡነ መልከጼዴቅ
ለተማሪዎቻቸው ነግረዋቸዋል፡፡ ታሪኩ እንዲህ ይነበባል፡-
‹‹አባታችን መልከጼዴቅ አደሴዋ በምትባል ደብር ሳለ እንዲህ
አለ፡- እንደ ነጭ የአውራ በግ ፀጉር ሁለንተናውን የከደነውና
ረጅም የሆነ የአካሉ ፀጉር እንደ ግምጃ የነጣ የራሱም ጫፍ
ከደመና የሚደርስና ቁመቱ ረጅም የሆነ አንድ ሰው ወደ እኔ
መጣ፡፡ ባየሁትም ጊዜ ደነገጥኩና አጋንንትን በማሳድድበት
በሥላሴ ስም በመስቀል ምልክት ፊቴን አማተብሁ፤
ከአጠገቤም ጥቂት ፈቀቅ አላለም፡፡ እኔም አንተ ማነህ?
ከወዴትስ መጣህ?› አልሁት፡፡ እርሱም ‹እኔ ኃጢአተኛ ሰው
ከቀደሙ አባቶች ዘመድ የሆንሁና ከኖኅ ልጆች ወገን ነኝ፣
ስሜም የእግዚአብሔር ሰው ነው፣ በነቢዩ በዳዊት ዘመንም
እግዚአብሔር ከሞት በፊት ሰወረኝ፣ በሕያዋን አገርም
ከሔኖክ፣ ከኤልያስ፣ ከዕዝራና ከጌታ ወዳጅ ከዮሐንስ ጋር
እኖራለሁ፣ ከእርሱም ጋር በሐሰተኛው መሢህ እጅ እሞታለሁ፣
ትናዝዘኝ ዘንድ ወደ አንተ እስከመጣሁበትና እግዚአብሔር ኑር
እስካለኝ ጊዜ ድረስ እኖራለሁ› አለኝ፡፡ ለእግዚአብሔርም
ያለውን አምልኮትና የሃይማኖቱን ደግነት በሰማሁና እንደ ዕንቈ
የሚያበራ የሥጋውን ንጽሕና ባየሁ ጊዜ ምንም እኔ ከጉልበቱ
የማልደርስ ብሆንም ዝቅ ብዬ ከእግሮቹ ስር እጅ ነሳሁ፡፡
እርሱም ከእኔ ፈቀቅ ብሎ ራሱን ወደ እኔ አዘነበለ፡፡ በመስቀል
ምልክት አማተብሁና ባረክሁት፣ ኑዛዜም ሰጠሁት፡፡ እርሱም
እጅ ነሳኝና ከእኔ ተሰወረ፡፡ በዳሞትም፣ በአደሴዋም እንዲሁ
ዘወትር ሲጎበኘኝ ነበረ አላቸው፡፡ አባታችን መልከጼዴቅ
ለተማሪዎቹ ይህን ነገራቸው፡፡ ጸሎቱና በረከቱ የዚህም
የእግዚአብሔር ሰው በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን ዛሬም
ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን፡፡››
2.ኢትዮጵያውያን ሁሉ የቅድስት ድንግል ማርያም የአስራት
ልጆች እንደሆንን ጌታችን የተናገረው፡- ‹‹የእግዚአብሔርም
ቃል በመልከጼዴቅ ላይ መጣና ‹ወንድምህ አቤል በንጉሡ
አዳራሽ ሞተ› አለው፡፡ ያንጊዜም ወደ ገዳም መጥቶ ወደ
እግዚአብሔር ጸለየ፡፡ ‹አቤል ወንድሜን ነፍሱን ያኖርህበትን
አሳየኝ› አለ፡፡ ጌታችንም መጣና ‹ባስቀመጥሁት በሲኦል
ውስጥ ንስሓውን ይፈጽም ዘንድ ተወኝ› አለው፡፡ ጌታችንም
ይህን ብሎ ከእርሱ ተሰወረ፡፡ ንስሓስ ከሞት በኋላ ኖሮ
አይደለም መልከጼዴቅ እንዲፈጽምለት ነገረው እንጂ፡፡ ከዚህ
በኋላ አባታችን መልከጼዴቅ ወደ እግዚአብሔር ይለምንለት
ጀመር፡፡ ደሙም በምድር ላይ እንደ ውሃ እስከሚፈስ ድረስ
ቁጥር በሌለው ብዙ ግርፋት ተገረፈ፡፡ ደም የተቀላቀለው ዕንባ
እያነባ መራራ ልቅሶን አለቀሰ፣ ዐይኑም ታመመ፡፡ ራሱንም
በሰንሰለት ቸንክሮ ሰውነቱን በእጅጉ አደከመ፡፡ ከዚህም በኋላ
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እርሱ መጣና ‹ስለ
ድካምህ ምሬልሃልሁ፡፡ ግርፋትህ በጲላጦስ እጅ እንደተገረፍሁት
ግርፋቴ ይሁን፣ ችንካርህም በዕፀ መስቀል ላይ አይሁድ
እንደቸነከሩኝ ችንካሬ ይሁን፣ መታሰርህም የደምህም መፍሰስ
ስለ ፈሰሰው ደሜ ይሁንልህ፣ ነፍስህን መስጠትህም ስለ ነፍሴ
መውጣት ይሁን፡፡ ዛሬም ና የወንድምህን የአቤል ነፍስ
ያለችበትን ላሳይህ› አለው፡፡ ያን ጊዜም የመንፈስ ቅዱስ ክንፍ
ተሰጠው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እየመራው
ሄደና ከሲኦል በር አደረሰው፡፡ ‹እኔ ወደ ሲኦል ወርጄ የጻድቃንን
ነፍሳት እንዳወጣሁ አንተም ወደ ሲኦል ውረድና ወንድምህ
አቤልን አውጣው› አለው፡፡ አባታችን መልከጼዴቅም ‹እኔ
መሬታዊ ሰው ስሆን ወደ ሲኦል መውረድ እንዴት እችላለሁ?
አንተስ የኃይል ባለቤት ሁሉ የሚቻልህ ስለሆንህ ከውስጧ
ወርደህ የብረት በሮቿን ቀጥቅጠህ ሰባበርህ› አለው፡፡ ጌታችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ‹በእኔ የሚያምን እኔ
የምሠራውን ይሠራልና እምቢ አትበለኝ ሂድ ውረድ› አለው፡፡
አባታችን መልከጼዴቅም ያንጊዜ መርከብ ወደ ጥልቅ ወንዝ
እንደሚወርድ ወደ ሲኦል ወረደ፤ ሲኦልም ደነገጠችና
‹የተሰጡኝን ነፍሳት ይቀማኝ ዘንድ ፈጣሪዬ ዳግመኛ ወረደን?›
አለች፡፡ አባታችንም ወንድሙን አቤልን ያዘውና ከውስጧ
አወጣው፡፡ ከእርሱ ጋርም ብዙዎች የኃጥአን ነፍሳትን አወጣ፡፡
በእርሱ ላይም የነካው የእሳት ሽታ ምንም አልነበረም፡፡
ወንድሙ አቤልን ከእሳት እንዳወጡት የእንጨት ግንድ ከሰል
መስሎ አየው፡፡ ከእርሱ ጋር የወጡት ነፍሳትም እንደ እርሱ
ጠቁረው ነበር፡፡ አባታችን መልከጼዴቅም ጌታችንን
‹ወንድሜን እንዲህ ጠቁሮ አየሁት ታዲያ ምኑን ማርህልኝ?
እነዚህም ነፍሳት እንዲሁ› አለው፡፡ ጌታችንም መላእክቱን
አዘዛቸውና መርተው ወስደው የገነትን ውኃ አሳዩት፡፡ ወንድሙ
አቤልንም በዚህ ውስጥ አጠመቀው፡፡ ከእርሱ ጋር
የወጡትንም ነፍሳት ሁሉ አጠመቃቸው፡፡ ያንጊዜም ፊቱ
ከጸሐይ ሰባት እጅ አበራ፡፡ አምላክን የወለደች እመቤታችን
ማርያምም መጣችና አባታችን መልከጼዴቅን ‹ወንድምህ
አቤልን ስጠኝ ወደ ርስቴ ልውሰደው፣ እርሱ ዕድል ፈንታዬ የእኔ
ድርሻ ነውና› አለችው፡፡ አባታችን መልከጼዴቅም ‹የእኔ ድርሻ
ነው፣ ልጅሽም የደምህ ዋጋ ይሁንህ ብሎኛል› አላት፡፡ እሷም
‹ና ወደ ልጄ እንሂድ› አለችውና ሁለቱም ሄደው ከጌታችን
ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ደረሱ፡፡ እመቤታችንም ‹ይህ
ኢትዮጵያዊ ሰው የሰጠኸኝ የእኔ ድርሻ ነው› አለችው፡፡
አባታችን መልከጼዴቅም ‹ለእኔም የደምህ ዋጋ ይሁንህ
ብለኸኛል› አለ፡፡ ጌታችንም ‹አንተም ኢትዮጵያዊ፣ እርሱም
ኢትዮጵያዊ፣ የኢትዮጵያዊን ሰዎች ሁሉ የእርሷ ድርሻ ይሆኑ
ዘንድ ሰጥቻለሁ› አለው፡፡ ወይቤ እግዚእነ አንተኒ ኢትዮጵያዊ
ወውእቱኒ ኢትዮጵያዊ እስመ ወሃብክዋ ኰሎሙ ሰብአ
ኢትዮጵያ ከመ ይኩኑ መክፈልታ እንዲል መጽሐፍ፡፡ ያንጊዜም
በፊቱ ሰግዳ አቤልን ወሰደችውና የብርሃን ልብስ አልብሳ ወደ
ገነት ደስታ አገባችው፡፡ ከእርሱ ጋር የወጡትን ነፍሳትም
ከጸሐይ ሰባት እጅ አብርተው አባታችን መልከጼዴቅ
ወሰዳቸውና ወደ ዘለዓለም ርስቱ አገባቸው፡፡ ለአባታችን
መልከጼዴቅ ታላቅ ምህረትን ላደረገለት ለእግዚአብሔር
ምስጋና ይሁን! ርስቱንም ይክፈለን! እኛንም ዕድል ፈንታው
ያድርገን! ለዘለዓለሙ አሜን!››
3.መድኃኔዓለም ክርስቶስ ለአቡነ መልከጼዴቅ የተገለጠበት
ልዩ ሁኔታ፡-
3.1.ጌታችን በምድር ላይ ተገልጦ ከአቡነ መልከጼዴቅ ጋር
እየተነጋገረ ሳለ በክብር ዙፋኖ ሆኖ አንድነቱን ሦስትነቱን
እንዳሳያቸው፡- ‹‹የእግዚአብሔር መልአክ አባታችን
መልከጼዴቅን ‹በግራርያ አገር ወደምትገኝ የቅዱስ
ተክለሃይማኖት ደብር ወደሆነች ወደ ደብረ ሊባኖስ ሂድ›
አለው፡፡ አባታችን መልከጼዴቅም በመልአኩ ትእዛዝ ሄዶ
ደብረ ሊባኖስ ደረሰና በዚያ ያሉ ቅዱሳንን እጅ ነሳቸው፡፡ ከንቡረ
ዕድ እንድርያስም ጋር ተቀመጠ፡፡ ትንሽ ዋሻ በዓትን ሰጠውና
‹ትእዛዛቱን በመጠበቅ እግዚአብሔር ያጽናህ፣ የገደልህንም
ፍጻሜ ይስጥህ› አለው፡፡ መልከጼዴቅም ወደዋሻው ገብቶ
ምስጋና፣ ጸሎትና ስግደትን ተግቶ ያዘ፡፡ እንደመጀመሪያውም
ታስሮ እያለ በየለቱ እስከ ሦስት ሺህ ስግደት ይሰግድ ነበር፡፡
ደሙም በምድር ላይ እስከሚፈስ ድረስ መንታ በሆነ የገመድ
ጅራፍ ሰውነቱን ይገርፍ ነበር፡፡ እንባውም እንደክረምት
ነጠብጠብ ይፈስ ነበር፣ የዓይኑ ብሌን እስኪገለበጥ ድረስ ያነባ
ነበር… እንዲህ ሆኖ መከራ ሲቀበልም እግዚአብሔር ዝም
አይልም፣ ሥራውንም ፈጽሞ ያደንቅ ነበር፡፡ ‹ጌታ ሆይ!
የተኛሁትን አንቃኝ፣ የደከምሁትን አበርታኝ፣ የጨለምሁትን
እኔን አብራኝ› ይል ነበር፡፡ ይህንንም የሚለው ለራሱ ብቻ
አይደለም ስለ ዓለሙ ሁሉ ነበር እንጂ፡፡ እርሱስ በኢየሩሳሌም
ከሐዋርያት ጋርና በአርያም ካሉ ከሱራፌል ጋር በክህነት
የሚያገለግል ፍጹም ንጹሕና ጻዲቅ ሰው ነው፡፡ ከዚህም በኋላ
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አባታችን ወደ መልከጼዴቅ
መጣና ‹ወዳጄ ሆይ! ሰላም ለአንተ ይሁን› አለው፡፡
መልከጼዴቅም ‹አንተ ማን ነህ?› አለው፡፡ ጌታችንም ‹እኔ
የድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነኝ› አለው፡፡
ያንጊዜም ከእግሩ በታች ወደቀ፡፡ ጌታም እጁን ይዞ አነሣውና
‹ጽና አትፍራ› አለው፡፡ ያንጊዜም እናቱ ድንግል ማርያም
ከቅዱስ ሚካኤልና ከቅዱስ ገብርኤል ጋር፣ ከሱራፌልና
ከኪሩቤል ጋር፣ ከነቢያትና ከሐዋርያት ጋር፣ ከጻድቃንና
ከሰማዕታት ጋር መጣች፡፡ መድኃኔዓለምም አባታችን
መልከጼዴቅን ‹ከእናትህ ማኅፀን ጀምሮ በምስክር ሁሉ ፊት
መረጥሁህ፣ ካህንም አደረግሁህ፣ ዛሬም የብዙዎች አባት
አድርግሃለሁ፡፡ ኃጢአተኞችንም የምትመልስ ትሆናለህ፡፡ ብሩህ
አክሊልና በሰው እጅ ያልተሠሩ የብርሃን ልብሶችን እሰጥሃለሁ፡፡
ርስትህ ከአጥማቂዬ ከዮሐንስ ጋር ይሁን፤ ሹመትህም ከሃያ
አራቱ ካህናተ ሰማይና ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት ጋር ይሁን›
አለው፡፡ ‹ስምህም የእኔ ምሳሌ በሆነው መልከጼዴቅ ይሁን›
አለው፡፡ የመጀመሪያው በጥምቀት የተሰጠው ስሙ ኅሩየ
ወልድ (በወልድ የተመረጠ) የሚል ነበርና፡፡ ያንጊዜም
ቁመታቸው እስከሰማይ የሚደርስ፣ ብርሃናቸው እንደ ፀሐይ
የሚያበራ ሦስት የወርቅ መስቀሎችን ሰጠው፡፡ ጌታችንም
‹በላያቸው ላይ ውጣ አለኝ፣ እኔም በእያንዳንዳቸው ላይ ሦስት
ጊዜ ወጣሁ፣ እስከ አርያምም አገቡኝ፡፡ በዚያም
የእግዚአብሔርን መንበር አየሁ፡፡ በአንድነት በሦስትነት
የሚኖር የዘመናት ጌታም በላይ ተቀምጧል፡፡› ይህም ነገር
እጅግ ድንቅ ነው ወልድ በምድር ላይ ከእርሱ ጋር እየተነጋገረ
ሳለ በአርያም ደግሞ በሦስትነቱ ተቀምጦ አየው፡፡ ጌታም
‹ሥርዓትህ እንዲሁ እንዳየኸው ይሁን፣ እስከ ዕለተ ዕረፍትህም
ድረስ ስለ ገድልህ ጽናት የሚሆን ሰጥቼሃለሁ› አለው፡፡ በጸሎቱ
የተማጸነውን እንደሚምርለትና ሌላም ብዙ ቃልኪዳን
ሰጠው፡፡ ‹እኔም ከአንተ አልለይም፣ መላእክቶቼም
ይጠብቁሃል› አለው፡፡ መልከጼዴቅም ይህንን በሰማ ጊዜ በፊቱ
ሰገደ፡፡ ‹አቤቱ ለእኔ ለኃጢአተኛው አገልጋይህ ይህን ሁሉ ክብር
የሰጠኸኝ ጌታ ሆይ መንግሥትህ ይባረክ› አለው፡፡ ጌታችንም
ባርኮት በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ዐረገ፡፡››
3.2.ጌታችን ሠራዒ ካህን ሆኖ ከአቡነ መልከጼዴቅ ጋር
እንደቀደሰ፡- ‹‹አባታችን መልከጼዴቅ ወደ እግዚአብሔር ቤተ
መቅደስ ገብቶ በመሠዊያው ፊት ቆመ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠለትና ‹እኔ ሠራዒ ካህን እሆናለሁ፣
አንተም ንፍቅ ሁነኝ› አለው፡፡ አባታችን መልከጼዴቅም ‹ሸክላ
(ጭቃ) ሠሪውን አትሥራኝ ማለት ይችላልን? የአንተ ፈቃድ
ይሁን› አለው፡፡ እነሆ የወርቅ ማዕድና የወርቅ ጽዋ፣
የወርቅም ዕርፈ መስቀል ከሰማይ ወረደና በመሠዊያው ላይ
ተቀመጠ፡፡ ጌታችንም በሰው እጅ ያልተሠራ የቅድስና ልብስ
ለበሰ፡፡ ያንጊዜም የሰማይ ኅብስትና የወይን ጽዋ ወረደ፡፡
ኅብስቱን በማዕድ ላይ፣ ወይኑንም በጽዋው ውስጥ ጨመረና
የራሱን ቅዳሴ ቅዳሴ እግዚእን ይቀድስ ጀመር፡፡ ‹ቅዱስ›
ከሚለው ቃል በደረሰ ጊዜም መላእክት በአንድ ቃል ‹ቅዱስ
ቅዱስ ቅዱስ የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር ፈጽሞ
በሰማይና በምድር ያለ፣ ወደፊትም የሚኖር፣ ሕያው› እያሉ
ጮሁ፡፡ አባታችን መልከጼዴቅም በቅዱሳን ጸሎት እንደ
ሱራፌል በወርቅ ማዕጠንት ዕጣን እያጠነ እንደ እነርሱ
‹ቅዱስ› አለ፡፡ የማዕጠንቱም ፍህም ከሰማይ የወረደ እሳት
ነው፡፡ የጻድቃን ጸሎትም በሚጤስ ጊዜ ቤቱን ይሞላል፡፡
ይህም ከሟች ሰው ልቡና የተሠወረ እፁብ ድንቅ ነገር ነው፡፡
ጌታም ይህን ኅብስት ለመቁረስ በያዘው ጊዜ ሕፃን ሆነ፣
ከዚያም ተመልሶ በግ ሆነ፣ ከዚያም ተመልሶ ኅብስት ሆነ፡፡ ይህ
ኅብስትም ፍህም ሆነ፡፡ አባታችን መልከጼዴቅም ይህን ባየ
ጊዜ ፈጽሞ ደነገጠ፣ ተንቀጠቀጠ፣ ይሸሽም ዘንድ ወደደ፡፡
መድኃኔዓለምም ‹ጽና አይዞህ አትፍራ፣ ከእኔ በኋላ አንተ
በክህነት በምታገለግልበት ጊዜ በእጅህ እንደዚህ
እንደሚደረግልህ አሳይሃለሁና› አለው፡፡ ይህም ነገር ፈጽሞ
የሚያስደንቅ ነው፡፡ እርሱ መሥዋዕት አቅራቢ፣ እርሱም ሕፃን
ይሆናል፡፡ እርሱም አራጅ፣ እርሱም በግ ይሆናል፡፡ እርሱ ፈታች
(ቆራሽ)፣ እርሱም የእሳት ፍህም የተከመረበት ኅብስት
ይሆናል፡፡ ከሰው ወገን በሁለት ወይም በሦስት መንገድ
መገለጥ የሚችል ማነው? እርሱ ግን ሁሉን ቻይ ነውና
ከመንበሩ ሳይነዋወጥ፣ ከሦስትነቱም ሳይለይ በምድር ላይ
በብዙ መንገድ ይገለጣል፡፡
መዓዛ ባለው እንጨት ለኄኖክ የታየበት ጊዜ አለ፤ በቀስተ
ደመና ለኖኅ የታየበት ጊዜ አለ፤ ከሁለት ሰዎች ጋር በሰው
አምሳል ወደ አብርሃም ሄዷል፤ ለይስሃቅ በበግ አምሳል
ታይቷል፣ ለመልከጼዴቅ በኅብስትና በወይን አምሳል ታይቷል፤
ለያዕቆብ በመሰላል ላይ በእሳት ነበልባል ተገልጧል፤ ለኤልያስ
በቀጭን ፉጨት ተገልጧል፤ ለኢሳይያስ በመንግሥቱ ዙፋን
በተቀመጠ ሰው ተገልጧል፤ ለዳንኤል በሽበታም ሰውና
በድንጋይ አምሳል ተገልጧል፤ ለሕዝቅኤል ሕብር ያለው በፍታ
በለበሰ አምሳል ተገልጧል፤ ለኤርምያስ በለውዝ በትር አምሳያ
ታይቷል፤ ለዕዝራ በአንበሳ አምሳል ታይቷል፤ ለአሞፅ
በሽበታም ሰው አምሳል ታይቷል፤ ለእመቤታችን ድንግል
ማርያም በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል አምሳል እንደጠልም
በማኅፀኗ አድሮ ከእርሷ ተወለደና በዚህም ሰው ሆነ፡፡ በአርያም
መላእክት በፈለጉት ጊዜም ከአባቱና ከመንፈስ ቅዱስ፣
ከቅዱሳንም ጋር እንደጥንቱ አገኙት፡፡ ለእንድርያስ በመርከብ
መሪ (ዋናተኛ) አምሳል በባሕር ላይ፣ ለኤዎስጣቴዎስ በበረቱ
ክንዶችና በሕፃን አምሳል በመስቀል ላይ፣ ለእስክንድርያ ሊቀ
ጳጳስ ለተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ ልብሱ በተቀደደ
በሕፃን አምሳል ተገልጧል፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ክብርና
ልዕልናዎቹን ስንቱን እናገራለሁ? እስከዛሬ ድረስ በሁሉም
አምሳል ይመሰላልና፡፡ ወደቀደመው ነገር እንመለስ፡፡ ጌታችን
ይህንን ኅብስት ሲፈትተው መንፈስ ቅዱስ እንደ እሳት እየነደደ
በእርሱ ላይ ወረደ፡፡ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለማክበር
ለመለወጥ መውረዱ እንደማይቋረጥ ተረዳ፣ ታወቀ፡፡
ኅብስቱንም ፈትቶ በጨረሰ ጊዜ ‹ይህ የሕይወት እንጀራ
ከሰማይ የወረደ ሥጋዬ ነው› ብሎ ለአባታችን መልከጼዴቅ
ሰጠው፡፡ ዳግመኛም በሕይወተ ሥጋና ነፍስ ላሉ ሰጣቸው፡፡
ጌታችንም ‹እንደ ነቢዩ ኢሳይያስ ከንፈርህን አስነካሁህ፤
ከኃጢአትህም አነጻሁህ፡፡ ዛሬ እንዳየኸኝ ነገም አንተ እንዲህ
በክህነት አገልግል› አለው፡፡
አባታችን መልከጼዴቅም በአገልግሎት ጊዜ በፈጣሪያችን እጅ
የተሠራ ልብሰ ተክህኖ ለበሰ፡፡ እንደ ትናንቱም ማዕድና ጽዋ፣
የወርቅም ዕርፈ መስቀል፣ የሰማይም ኅብስትና ወይን ወረደ፡፡
በማዕዱ ላይ ኅብስቱን አኖረ፤ በጽዋውም ላይ ወይኑን
ጨመረ፡፡ የጌታችንንም ቅዳሴ ቀደሰ፡፡ ‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ
የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር ዘወትር በሰማይና በምድር
የሚኖር ነው› ባለጊዜ በዚያ የነበሩና በሰማይም ያሉ መላእክት
‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር› ሲሉ ምድር
እስክትነዋወጥ ድረስ የምስጋናቸውን ቃል ሰማ፡፡ የእውነት
መንፈስ ቅዱስ ጰራቅሊጦስን ላከው› ባለጊዜም ሰማይ ተከፍተ፣
የኢየሩሳሌምም የቤቷ ጠፈር ተቀደደ፣ መንፈስ ቅዱስም በዚህ
ኅብስት ላይ ወረደ፡፡ እርሱም ሕፃን ሆነ፣ መድኃኔዓለምም
‹ይህን ሕፃን ሰዋው፣ ለዓለምም ሁሉ መድኃኒት ይሆን ዘንድ›
አለው፡፡ ይህን ሕፃን ሊይዘው በወደደ ጊዜም በግ ሆነ፡፡
እግዚአብሔርም ‹ይህን በግ እረደው› አለው፡፡ ይህንንም በግ
ሊይዘው በወደደ ጊዜ ከእሳት ጋር የተዋሐደ ኅብስት ሆነ፡፡
ይህም እጅግ ድንቅ ነገር ነው፡፡ ጌታ ከአገልጋይ ይናገር ዘንድ፣
ጌታ ንፍቅ ቄስ ሆኖ ከመልከጼዴቅ ጋር እየተነጋገረ ቆሞ ሳለ
በመሠዊያው ላይ ሕፃን ሆነ፤ ሁለተኛም በግ ሆነ፣ ሦስተኛም
ኅብስት ሆነ፡፡ ይህንም ኅብስት በሚፈትተው ጊዜ እንደ እሳት
ይነድ ነበር፡፡ አባታችንም ቅዳሴውን በፈጸመ ጊዜ ከዚህ
ኅብስት ራሱ ተቀበለ፣ በዚያም ለነበሩ ቅዱሳን ሁሉ
አቀበላቸው፡፡ ይህን ታላቅ ክብር ለሰጠው ‹ለአብ ለወልድ
ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁን› በማለት አመሰገነ፡፡›› ከዚሁ
ጋር በተያያዘ ለጻዲቁ ጌታችን የገባላቸውን ልዩ ቃልኪዳንም
አብረን ማየት እንችላለን፡-
‹‹በማግስቱም ቅዱስ ጴጥሮስ ከሰማይ በወረደ ኅብስት ካህን
በሆነ ጊዜ መልከጼዴቅ ንፍቅ ሆነ፤ እንዲሁ ከሁሉም ሐዋርያት
ጋር አሥራ ሁለት ቀን ንፍቅ ሆነ፡፡ ዳግመኛም እርሱ ካህን ሆነ፣
ሐዋርያትም እያንዳንዳቸው አሥራ ሁለት ቀን ንፍቅ ሆኑት፡፡
ለሃያ ስድስት ቀናትም ያህል ሁሉም በኢየሩሳሌም ሆኑ፡፡
ይህንም ተልእኮ በፈጸመ ጊዜ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ‹እኔ ከእናትህ ማኅፀን መረጥሁህ፣ ከአፌ በወጣ
ቃሌም እንደማልዋሽህ ቃልኪዳን ሰጠሁህ› አለው፡፡ ያንጊዜም
እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ከቅዱሳን መላእክቶች ጋር
መጣች፡፡ መላእክትንና ቀደምት አባቶችን፣ ነቢያትንና
ሐዋርያትን፣ ጻደቃን ሰማዕታትን፣ ቀሳውስትና ዲያቆናትን፣
ደናግልና መነኮሳትን፣ ወንዶችንና ሴቶችን ሕፃናትንም
ምስክሮች አድርጎ አቆመ፡፡ ሄሮድስ ያስገደላቸው 144,000
ሕፃናት ከአለቃቸው ከቅዱስ ቂርቆስ ጋር መጡ፡፡ ‹በእኔና
በአንተ መካከል እነዚህ ሁሉ ምስክሮች ይሁኑ፤ ስምህን የጠራ፣
መታሰቢያህን ያደረገ፣ በእጅህ የተጠመቀ፣ በቃልህ የተናዘዘና
በእጅህ የተሳለመ ምሬልሃለሁ፤ የገድልህን መጽሐፍ የጻፈውና
ያጻፈውን ምሬልሃለሁ ከአንተም ጋር ርስት እሰጠዋለሁ፤ የቤትህ
ልጆች መንግሥተ ሰማያትን ከአንተ ጋር ይውረሱ› አለው፡፡
ዳግመኛም ‹ለምህረት ያልጠራኋትን ነፍስ ለመሳለምም ሆነ
ለመባረክ ወይም ለመናዘዝ ወደ አንተ አላቀርብም፤
ከኃጥአንም ወገን አንተ ስለ እነርሱ ከለመንኸኝ እምርልሃለሁ፤
ሥጋቸውንም መሬት አይበላውም› አለው፡፡ ጌታችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ሁሉ ቃልኪዳን
በኢየሩሳሌም ከሰጠው በኋላ አባታችን በመንፈስ ክንፎች
ተመሰጠ፤ ተነጥቆም አዴሴዋ ከምትባል ከትግራይ ምድር
ተመለሰ፡፡ የዚህች አገር ሰዎችም ‹ለምን እስከዛሬ ድረስ
ተደበቅኸን?› አሉት፡፡ ‹እኔስ በቤቴ ውስጥ ታምሜ ነበርሁ›
አላቸው፡፡ ከእርሱ ጋር ከተነጠቁት በቀርም መንፈስ ቅዱስ
ኢየሩሳሌም እንደወሰደው አላወቁም፡፡››
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን! የጻድቁ አባታችን የአቡነ
መልከጼዴቅ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው
ይማረን፡፡
(ምንጭ፡- ገድለ አቡነ መልከጼዴቅ-ሊቀ ጠበብት ዘላለም
መንግሥቱ ከግእዝ ወደ አማርኛ የተረጎሙትና የገዳሙ እድሳት
ኮሚቴ ያሳተመው-2004 ዓ.ም፣ ስንክሳር ዘወርሃ ግንቦት)

=>*++በዓታ_ለማርያም++*

#በዓታ_ለማርያም
ይህ ዕለት የልዑል እግዚአብሔር እውነተኛ መቅደስ የምትሆን
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተ መቅደስ
የገባችበትን ዕለት የምናስብበት ነው፡፡ የአምላክ እናት ከእናት
ከአባቷ ቤት ተለይታ እግዚአብሔር ወደመረጠላት ሥፍራ ወደ
ቤተ መቅደስ ገባች፡፡ ዕድሜዋ ሦስት ዓመት ነበር፡፡
አባታችን ኢዮብ እንደተናገረው “ሁሉን ማድረግ እንደሚቻለው፤
በባሕርይው የሚሣነው እንደሌለ አሳቡንም ይከለከል ዘንድ ከቶ
እንደማይቻል” 《 ኢዮ 42፡2 》አውቀን ለተጠራንበት ዓላማ
መልስ መስጠት ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡
እግዚአብሔር ሲጠራ፣ ልዑል ሲናገር የዕድሜ ጉዳይ የጾታ
ጉዳይ የዜግነት ጉዳይ የአቅም ጉዳይ የጊዜ ጉዳይ የስልጣን
ጉዳይ የእውቀት ጉዳይ ሥፍራ አይገኝላቸውም፡፡ ጥያቄ
ውስጥም የሚገቡ አይደሉም፡፡ እኛ ግን እንኳንስ ራሳችንን
ለሕይወት ዘመን አገልግሎት ልንሰጥ ይቅርና በተወሰነ ሰዓት
ለሚሆነው መውጣት መግባት እየተቸገርን ነው፡፡ አገልግሎት
ለእግዚአብሔር ያለንን ፍጹም ፍቅር የምንገልጽበት
በሕይወታችንም ተጠቃሚ የምንሆንበት ምሥጢር ነው፡፡
ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ
ጥንተ ነገር አባቷ ቅዱስ ኢያቄም እናቷ ቅድስት ሐና እንደ
መጽሐፍ ቃል፥ እንደ አባቶች ሥርዓት፥ እንደኦሪቱ ሕግ
በእግዚአብሔር ትእዛዛትና ሕግጋት ሁሉ እየሄዱ በእግዚአብሔር
ፊት ፍጹም ጻድቅ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ልጅ አልነበራቸውም፡፡
ስዕለት ተሳሉ፤ እግዚአብሔር ልጅ ብቻ ሳይሆን ፈጣሪዋን
የምትወልድ ከመልኳ ደም ግባት ይልቅ የልቡናዋ ደም ግባት
ደስ የሚያሰኝ፤ አሸናፊ የሚሆን የእግዚአብሔር አብን የባሕርይ
ልጅ በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ በድንጋሌ ኅሊና ጸንሳ
የወለደች የብርሃን እናትን ወለዱ፡፡
ሊቃውንቱ “ማኅጸነ ሐና ሕያው ሰማያተ ገብረ”፤ ሕያው የሆነ
የሐና ማኅጸን ሰማይ የተባለች ቅድስት ድንግል ማርያምን
አስገኘ በማለት ዘመሩ፡፡ እግዚአብሔር ስጦታው ድንቅ ነው
የለመኑትን ሳይሆን ሰዎች ፈጽሞ ሊያስቡት ቀርቶ ሊገምቱት
የማይቻለውን ስጦታ ይሰጣል፡፡
የአባታቸውን የነቢዩን ዳዊት ቃል ቃላቸው አድርገው
በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ደጅ ይጠኑ የነበሩ ቅዱስ
ኢያቄምና ቅድስት ሐና “እኔ ግን በምሕረትህ ብዛት ወደ ቤትህ
እገባለሁ አንተን በመፍራት ወደ ቅድስናህ መቅደስ
እሰግዳለሁ” 《 መዝ 5፡7 》 በማለታቸው የጸሎታቸው ውጤት
ብቻ ሳትሆን የእግዚአብሔር ስጦታ የምትሆን፣ ፍጥረት ሁሉ
ተሰብስቦ ቢመዘን የአንዲቱን የጸጉሯን ዘለላ የማያክል ቅድስት
ድንግልን ወለዱ፡፡ ከእግዚአብሔር የተቀበሉአትን ቅድስት
ለእግዚአብሔር ሊሰጡአት ስዕለት ተስለው ነበር፡፡
አስቀድሞ በቤተ እስራኤል ዘንድ ደናግል በቤተ መቅደስ
ውስጥ የሚቀመጡበት ሥርዓት አልነበረም፡፡ በርግጥ በኦሪቱ
ነቢይት በአፍአ እንደነበረች ተገልጧል፤ ነገር ግን የእመቤታችን
ወደቤተ መቅደስ መግባትና የነቢይት ወደ ቤተ መቅደስ
መግባት የተለየ ነው፡፡ በዓይነትም በመጠንም የሚነጻጸር
አይደለም፡፡
ቅድስት ድንግል ማርያም ከሦስት ዓመቷ እስከ አሥራ አምስት
ዓመቷ ለአሥራ ሁለት ዓመታት በቤተ መቅደስ ቆየች፡፡ ሕያው
መቅደስ፥ እመቤትና የአምላክ እናት የምትሆን ቅድስት ድንግል
በእነዚህ ዓመታት መላእክት ምግቧንና መጠጧን እያመጡ
ከዜማው ጣዕም የተነሣ አጥንትን የሚያለመልም
የመላእክትን ዝማሬ እያዳመጠች በቤተ መቅደስ ኖረች፤
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን “ንጽሕተ ንጹሐን ከወይና ከመ ታቦተ
ዶር ዘሲና ውስተ ቤተ መቅደስ ነበረት በድንግልና ሲሳያ ኅብስተ
መና ወስቴሃኒ ስቴ ጽሞና” እያሉ አዲስ ቅኔን ተቀኙላት፡፡
የበዓሉ ትርጉም በዘመኑ ለምንገኝ ክርስቲያኖች
እግዚአብሔር በማንኛውም የዕድሜ ጣራ ሥር የሚገኝ
ክርስቲያንን እንደሚፈልግ የተመለከትንበት ዕለት ነው፡፡
በአቅማችን እንድንነጋገር ስለሚያስፈልግ እንጂ የበዓሉ
ትርጉም ከዚህም በላይ ላይ ነው፡፡ በልዑል እግዚአብሔር ቤተ
መቅደስ ስንኖር ልንከተለው የሚገባ ቅድስና በእግረ ሥጋ
ለምንመላለስ ወገኖች ያለው አስተማሪነት የጎላ ነው፡፡
በሕይወት ዘመን በእግዚአብሔር ቤት ለመኖር እንፈልግ ዘንድ
፣ ሕይወታችንን በፍጹም ቅድስና እንመራ ዘንድ መቅደስ
የተባለ ለእግዚአብሔር ማደሪያነት የተመረጠ ሰውነታችን
ከኃጢአት ሁሉ እንጠብቅ ዘንድ የተማርነበት በዓል ነው፡፡
ይልቁንም በመከራ ጊዜ ከንፈሮቻችን የተናገሩትን ስዕለት
ለእግዚአብሔር መፈጸም እንደሚገባን እግዚአብሔርን
የሚያስደስተው ፍጹም ስጦታ ራሳችንን አሳልፈን ከመስጠት
የበለጠ እንደሌለ ልንረዳ የሚገባን መሆኑን በዓሉ
ያስተምራል፡፡ ልመናዋ ክብሯ የልጇ ቸርነት በሁላችን ላይ
ይደርብን፡፡

ተዋሕዶ ማለት ምን ማለት ነው?

<<<ተዋሕዶ ማለት ምን ማለት ነው? መልስ >>>>>> በስመዓብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ዓሐዱ
አምላክ አመ
****
ብዙ ኦርቶዶክሶች እንዲሁም እራሳቸው ተቃዋሚዎች እኛ
ኦርቶዶክሳውያን ከመናፍቃን ጋር ያለን ልዩነት በቅድስት
ድንግል ማርያም እና በቅዱሳን እንዲሁም በሚስጥራተ
ቤተ ክርስትያን ላይ ብቻ ይመስላቸዋል፡፡
ዋናው እና መሰረታዊ የመናፍቃኑ ልዩነት ከኦርቶዶክሳውያን
ጋር በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለን ልዩነት ነው!
ተቃዋሚዎች ስለ ኢየሱስ:-
አንድ አካል ሁለት ባህሪ ብለው ያምናሉ :: ስጋ እና
መለኮት አልተዋሃዱም ,ያልተዋሀዱ የመለኮትና የትስብዕት
ባህሪ አሉ ብለው ያምናሉ፡፡ ልክ ዘይት ውሃ ላይ ጠልሎ
እንደሚታየው መለኮትና ስጋም ፍጹም አልተዋሃዱም
የሚሉ ናቸው፡፡መናፍቃኑ ባለፈው እንዳየነውና ወደፊት
እንደምንመለከተው እንዲሁ ጥራዝ ነጠቅ ጥቅስ ይዘው
ክርስቶስን አማላጅ ነው ይላሉና መለኮትና ትስብዕት
ፍፁም ስላልተዋሃዱ ትስብዕቱ መለኮቱን ይለምነዋል፤
ሰውነቱ አምላክነቱን ይማልደዋል ብለው በማስተማር
የክርስቶስን ፍጹም ሰው፣ፍጹም አምላክነት ይቃወማሉ!
ተዋሕዶ ስንል ምን ማለታችን ነው?
ተዋሕዶ ማለት የቃል በቃል ትርጉሙ ተዋሀደ አንድ ሆነ
ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን ተዋሕዶ ሲል አንድ
መሆን ማለት ነው።
ምስጢራዊ ፍቹ ግን ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት
ባሕርይ አንድ ባሕርይ የመሆን ምስጢር ነው።
- ሁለት አካላት የተባሉተ አካል መለኮትና አካለ ሥጋ
ናቸው።
- ሁለቱ ባህርይ የተባሉትም ባሕርየ መለኮትና ባሕርየ ሥጋ
ናቸው።
እንደሚታወቀው ሁለቱ አካላትም ሆነ ሁለቱ ባሕርያት
ፈጽመው የማይገናኙ የማይመሳሰሉ ናቸው። ይኸውም
አንደኛው ፈጣሪ ሌላው ፍጡር ከመሆናቸውም ባሻገር
የመለኮት አካል የማይጨበጥ፣ የማይዳደስ፣ ረቂቅ ሲሆን
የሥጋ አካል ደግሞ የሚጨበጥ፣ የሚዳሰስ ግዙፍ ነው።
እንግዲያውስ ከሁለቱ አካል አንድ አካል ሆነ ሲባል ረቂቁ
መለኮት ርቀቱን ሳይለቅ፤ ግዙፉ ሥጋም ግዙፍነቱን
ሳይለቅ: ይህ ማለት ረቂቅ መለኮት ግዙፉን ሥጋ
ሳያረቅቀው፣ ግዙፉ ሥጋም ረቂቁን መለኮት ሳያገዝፈው
በተዓቅቦ አንድ ሆኑ ማለት ነው።
የመለኮት ባሕርይ:
************
የማይሞት፥ የማይታተም፥ የማይደክም፥ የማይለወጥ
ሲሆን
የሥጋ ባሕርይ
*********
ደግሞ መዋቲ ታማሚ፣ የሚደክምና የሚለወጥ ነው።
ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ሆነ ማለት እንግዲህ
መለኮት የራሱ ባሕርይ ያልሆነው የሥጋ ባሕርይ ሕማም
ሞት ድካም ገንዘብ አድርጎ፣ ሥጋም የራሱ ባሕርይ
ያልሆነው የመለኮትን ባሕርይ ገንዘቡ አድርጎ ሁለቱም
ተዋሃዱ አንድ ሆኑ ማለት ነው። ተዋሕዶ መንታነትን
አጥፍቷልና ከእንግዲህ አንድ እንጂ ሁለት ብሎ ነገር
የለም። /ዮሐ 20፥26/
በተዋሕዶ የመለኮት ገንዘብ ለትስብእት፣ የትስእትም
ገንዘብ ለመለኮት ሆኗል።
ይህም ቀደም ሲል እንደተገለጠው መለኮት ትስብእትን /
ሥጋን/ በመዋሀዱ ምሉእ ውሱን፣ ሰጪው ተቀባይ፣
የማያንቀላፋው የሚተኛ፣ ኃያሉ ደካማ፣ ሕያው መዋቲ
ሆኗል።
በግርግም አስተኛችው (ሉቃ 2፥7)
እርሱም ትራስ ተንተርሶ ተኝቶ ነበር (ማር 4፥38)
ይችን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበለሁ (ዮሐ 10፥18)
ውኃ አጠጩኝ (ዮሐ 4፦........)
ሀብታም ሲሆን እናንተ በእርሱ ድህነት ባለወጎች ትሁኑ
ዘንድ ስለእናንተ ድሀ ሆነ:: (2ቆሮ 8፥9)
ኢየሱስም መንገድ ከመሔድ ደክሞ....... (ዮሐ 4፥6-8)
ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ መቼም ነበርሁ
እነሆም ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ ሕያው ነኝ
---- /ራእ 1፥17/
ትስብእትም መለኮትን በመወሃዱ ውሱን ምሉእ፣ ተቀባዩ
ሰጪ፣ ደካማው ኃያል፣ መዋቲው ሕያው ተባለ
ተሰወራቸው ከመቅደስም ወጥቶ በመካከላቸውም አልፎ
ሔደ:: /ዮሐ 8፥59/
ሰላሜን እስጣችኃለሁ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም
እንደሚሰጥ አይደለም:: /ዮሐ 14፥27/
በስሜ የምትለምኑትም ሁሉ አደርገዋለሁ ማናቸውንም
ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አድርገዋለሁ:: /ዮሐ
14፥13፣14/
በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ:: /ጴጥ 3፥18/
ይህ ሁሉ የተመለከትነው በኢየሱስ ክርስቶስ የተነገረና ስለ
እርሱ የተነገረውን ነው:: ታዲያ ከጥቅሶቹ የምንመለከተው
አንድነትን እንጂ ሁለትነትን አይደለም። በመለኮት የሥጋን
ገንዘብ ገንዘቡ አደረገ ሲባል ባሕርዩ ተለውጦ ትስብእቱ /u
ሰው/ የሆነ፤ ትስብእትም የመለኮትን ገንዘብ ገንዘቡ
አደረገ ሲባል ባሕርዩን ለቅቆ መለኮት የሆነ አይደለም።
ተዋሕደው በተዓቅቦ /በመጠባበቅ/ የሆነ ነው እንጂ
በተዋሕዶ ሁለትነትም ሆነ መለወጥ የለም። ምክንያቱም
ውላጤ /መለወጥ/ በእግዚአብሔር አይስማማምና ነው።
እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም:: (ሚል 3፥6)
ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትናና ዛሬ፣ እስከ ዘለዓለምም ያው
ነው:: (ዕብ 13፥18) እንዲል።
ክርስቶስን ከሁለት መክፈል እንደማይቻልና በተሕዶ ውስጥ
ምንታዊ /መንታነት/ እንደሌለ ቅ/ጳውሎስ
''ክርስቶስ ተከፍሏልን?" (1ኛ ቆሮ 1፥13)
''አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው ጌታም አንድ ነው::" (1ኛ
ቆሮ 12፥5) በማለት ያስረዳል። አሁንም ቢሆን
የሚከተሉትን በጽሞና እንመልከታቸው። ነገረ ተዋሕዶንም
ያስተምሩናል።
ያንቀላፋው ከእንቅልፉም ተነስቶ ማዕበሉንና ነፋሱን
የገሠፀው አንዱ ክርስቶስ ነው። /ማቴ 8፥23-27/
ወደ ሠርግ ቤት የተጠራው፣ በዝያ ተገኝቶ ውኃውን
ወደወይን ጠጅ የለወጠው አንዱ ሥግው ቃል ነው:: /
ዮሐ 2፥1-11/
ምራቁን ወደ መሬት የተፋው: ምራቁንም በጭቃ ለውሶ
ለዓይነ ሥውሩ ዓይን የፈጠረለትም እርሱ አንዱ ክርስቶስ
ነው:: /ዮሐ 9፥1-10/
የተጠማውና የማያስጠማ የሕይወትን ውኃ የሚሠጠው
አንዱ ኢየሱስ-ክርስቶስ ነው:: /ዮሐ 4፥6-15፣ ራእ
21፣6-7/
40 ቀንና 40 ሌሊት ከመጸሙ የተነሳ የተራበው ጥቂቱን
ዓሣና እንጀራ ያበረከተውም አንዱ ክርስቶስ ነው። /ማቴ
4፥1-3፣ 14፣ 13-21/
መለኮትና ትስብእት ከጽንሰት ጀምሮ አንድ አካል አንድ
ባሕርይ ሆነዋል። ለትምህርት ሲባል መለኮት፥ ትስብእት
እያልን እንጠራለን እንጂ ከተዋሕዶ በኋላ መለኮት፥
ትስብእት እያሉ መለያየት የለም።
የተዋሕዶ ተቃራኒዎች:
**************
ቢዚህ ዓለም ተቃራኒ የሌለው አንድም ነገር የለም።
ስለሆነም ለተዋሕዶም ተቃራኒ ነገሮች አሉት። እነሱም
የሚከተሉት ናቸው።
1. ውላጤ፦ ውላጤ ማለት መለወጥ ማለት ነው።
አንዳንዶች ቃል ተለውጦ ሥጋ ሆነ ይላሉ። ይህም ማለት
የሎጥ ሚስት ወደጨው ሓውልትነት (ዘፍ 19፦ ......)
የቃና ውኃ ወደ ወይን ጠጅነት እንደተለወጠ /ዮሐ 2፥5/
ማለት ነው ብለው ያምናሉ።
ነገር ግን መለኮት ሥጋን በለበሰ ጊዜ ሥጋ ወደ መሆን
አልተለወጠም በፍፁም ተዋሕዶ ፀና እንጂ። እንደዚያማ
ባይሆን ኖሮ ጌታ ራሱ፦
- እኔና አብ አንድ ነን:: (ዮሐ 10፥30)
- እኔን ያየ አብን አይቷል ባለለም ነበር ዮሐ 14፥19
2. ኅድረት:- ኀድረት ማለት ''ማደር'' ማለት ነው። ይህም
መለኮት በሥጋ ውስጥ አደረ የሚሉ መናፍቃን የሚከተሉት
እምነት ነው። የሚያቀርቡት ማስረጃም፦
- ውኃ በማድረግ - ዳዊት በማኅደር - ሰይፍ በሰገባ
እንደሚያድር መለኮት በሥጋ አድሮ ወጣ ይላሉ።
ለመለኮት ግን እንዲህ አይደለም ተዋሕደው አንደ ነፍስና
ሥጋ ነው እንጂ። ስለዚህም፦
- (ማቴ 3፦27) የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ እንጂ
በእርሱ ያደረው ነው አላለም'' የእግዚአብሔር አብን
ምስክርነት በመከተል ብዙዎችን መስክሯል። ጴጥሮስ
(ማቴ 16፥13-17፣ ዮሐ 6፥ ናትናኤል ዮሐ 1፥50)
እግዚአብሔር ማስተዋሉን ያድለን!
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የቀደመችው እውነተኛይቱ መንገድ፡፡
ወስብሀት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ
ክቡር!!!

+*"የክርስቲያን ሁሉ ዓርማ ማዕተብ"*+

ማዕተብ በቤተክርስቲያን ምን ማለት ነው????
ማዕተብ የክርስቲያን ሁሉ ዓርማ
“ማህተብህን በአንገትህ እሰረው ስትሔድ ይመራሃል ስትተኛ
ይጠብቅሃል ” ምሳ 6÷21
ማተብ (አተበ፤ አመለከተ ፤ባረከ)
ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ነው፡፡ይህም ማለት መታወቂያ ፤
ምልክት ማለት ነው፡፡ይህም ያሙትንና የተጠመቁትን
ካላመኑትና ካልተጠመቁት የሚለዮበት የክርስቲያን መታወቂያ
ነው፡፡
የዚህ ምልክት መሠረቱና ምሳሌውም ጌታችን መድኀኒታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ ከተቀበለው ጸዋትወ መከራ አንዱ በገመድ
ታሥሮ መጎተቱ መሆኑንየሚያመለክት ነው፡፡
ዮሐ19፤12 ቅዱስ ዳዊትም በመዝ59፤4 ላይ ”ወወሀብኮሙ
ትእምርተ ለእለ ይፈርሁከከመያምሥጡእምገጸ ቅስት ፤
ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ ለሚፈሩ ምልከትን ሰጠሃቸው”
ይላል፡፡
አጋንንት የክፋትን ቀስት በዚህ ዓለም በመወርወር የሰውን ልብ
ስለሚወጉ ከዚህ ለመዳን ማዕተብን ማድረግ ታላቅ መንፈሳዊ
እውቀት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
ሲያስረዱ ሥላሴ ማዕተበ ብርሃን ኃይል ሃይማኖቶሙ
ለክርስቲያን፤ሥላሴ ለክርስቲያን ሁሉ የሃይማኖታቸው ጉልበት
መታወቂያ የብርሃን ማዕተብ (ምልክት) ናቸው ብለዋል፡፡
ማዕተብ ያላሠረ ኦርቶዶክሳዊ በውግዘት ከቤተክርስቲያኒቱ እንደ
መናፍቅ ተቆጥሮ ባይለይም ማዕተብ አለማሠሩ ግን የአባቶቹ
ትውፊት እንዳልተቀበለ ያስቆጥረዋል፡፡
በምሳሌያዊ አነጋገርም ሃይማኖት አልባውን ማለትም
ክርስቲያን ያልሆነውን ማዕተብ የለሽ ያልተጠመቀ
አረሚይሉታል ክርስቲያን በማተቡ መነኩሴ በቆቡ እንዲታወቅ
ማዕተብ አልባ መሆን። ደግሞ ክርስቲያን
ይሁን ያልተጠመቀ መሆኑ ለማወቅ ያስቸግራል፡፡
በመለዮዋቸው ሌሎች እንዲታወቁ ክርስቲያን በማዕተቡ
ክርስትናውን ሲያሳውቅኖሯል፡፡ በተለመደው አነጋገር እገሌ
ማዕተብ አለው ባለማዕተብ ነው ሲባል እገሌ ታማኝ ክርስቲያን
ነው።
እውነተኛ :ሐቀኛ ነው የሚል ትርጉምን ይሰጣል
“ባለማዕተቢቱ” ሲባል ከአሚን ባሏ የረጋች ከባሏ
ሌላ የማታውቅ እውነተኛ ታማኝ ክርስቲያን የማል ፍች
አለው፡፡በዚህ ምክንያት በክርስቲያኑ ኅብረተሰብ የማዕተብ
ትርጉም ከፍተኛ ቁም ነገርን አዝሎ ይገኛል፡፡ አንዲት ሀገር ነፃ
መሆኗ የሚታወቀው ወይም ራሷን የቻለች የራሷ መንግሥት
ያላት ከባዕድ ቀንበር ቅኝ ግዛትነፃየወጣችመሆኗየሚታ
ወቀውበባንዲራዋ ምልክትነት እንደሆነ እንደዚሁም አንድ
ክርስቲያን በክርስቶስ አምኖ በጥምቀት ከዲያብሎስ ቁራኝነት
ነፃ መውጣቱ ነፃነት ያለው አማኝ መሆኑ የሚታወቀው
በማዕተቡ ምልክት ነው፡፡
ለደብዳቤ ለጽሑፍ ዓርማ ማኅተም ፊርማ እንደሚያስፈልገው
ያም ለመተማመኛ እንደሚያገለግል ጥቅሙ ታውቆ
ይሠራበታል፡፡
የክርስቲያን ማዕተብም በዚሁ አንፃር ብዙ ኃይማኖታዊ
ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡
መጀመሪያ በልቡ የሚያምነው ሃይማኖት ክርስትናን ሳያፍርበት
በአንገቱ ባለው ማተብ መግለጹ በክርስትናው አለማፈሩን
ክርስትናህን ካድ ማተብህን በጥስ የሚል ዓላዊ ቢመጣና ያንን
ምልክት ዓይቶ
ቢሰዋው የሰማዕትነትን ክብር ያገኝበታል፡፡ ያም ባይሆን
በማተቡ ምልክትነት በመናፍቃንና በኢአማንያን የሚቀበለው
ዘለፋ ስለ ክርስቶስ መስቀል እንደተሸከመ ያስቆጥረዋል፡፡
ሁለተኛው ከክርስቲያን ወገኖች ጋር
ያለጥርጥርማለትምየክርስቲ ያንመሆኑታውቆለት በቀላሉ
ክርስቲያናዊ ተሳትፎውን ማከናወን ይችላል፡፡ ማተብ ከሌለው
ግን ክርስቲያን ይሁን ያልተጠመቀ ስለማይታወቅ በሃይማኖት
ዜጎች ዘንድ በቀላሉ ተቀባይነት ማግኘት አይችልምሦስተኛ
ከማይታወቅበት ሀገር በአደጋም ይሁን በበሽታ እንደወጣ ሞት
ቢደርስበት በማዕተቡ መታወቂያነት የክርስቲያን ሥርዓት
ተፈጽሞለት አስክሬኑ ተፈርቶ በቤተክርስቲን ሊቀበር ይችላል፡፡
ማተብ ከሌለው ምስከር በአካባቢው ለክርስቲያንነቱ
ማረጋገጫ የሰው ያውም በሰበካው ቤተክርስቲያን የሚታመን
ክርስቲያን ከሌለ እንደአልተጠመቀ ተቆጥሮ እንደ አሕዛብ
ሥጋው ዱር ከበረሃ ወድቆ ይቀራል፡፡
ዐራተኛ ማተብና መስቀል ያለው ክርስቲያን በውሃ ዋና ወይም
በበረሃ ጎዳና በውሃ የሚኖሩ ወይም በበረሃ ያሉ አጋንንት
በቀላሉ ሊለክፉት አይችሉም፡፡ ይህምበየጠበሉ ሥፍራ
በተአምራት ተረጋግጧል፡፡ አጋንንት የለከፋቸው ሰዎች ማተብና
መስቀል አይወዱም፡፡ የሠፈረባቸው ርኩስ መንፈስ ማተብ
እንዲበጥሱ መስቀል እንዲጥሉ ያደርጋቸዋል፡፡
ማተብ በሰይጣን ዘንድ ከተጠላ በአጋንንት ላለመለከፍ የማተቡ
መኖር ይጠቅማል ማለት ነው፡፡
አንዳንድ ሰዎች የማዕተብ ሥርዓትን ለመቃወምና ዘመናውያን
መስለው ለመታየት “ሃይማኖት በልብ ነው” ይላሉ
ተሳስተዋል፡፡ ሃይማኖት የልብ ብቻ አይደለም የጠቅላላው
ሕዋሳት ሁሉ ናት እግዚአብሔርን ስንወደውና ስናመልከው
በልባችን ብቻ ሳይሆን በአፋችንም በአንገታችንም በጠቅላላው
ሰብአዊ ተፈጥሮአችን ሁሉ መሆን ይገባዋል፡፡
ምክንያቱም እግዚአብሔር የጠቅላላው ሰውነታችን አምላክና
ፈጣሪ ስለሆነ ነው፡፡ “ስለዚህ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝvሁሉ
እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ በሰው
ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው
በአባቴ ፊት እክደዋለሁ፡፡ “ማቴ ፲፤፴፪-፴፫በዚህ ቃል
መሠረት በኢአማንያን ዘንድ ክርስቲያን መሆናችንን
የምንገልፀው በልባችን ብቻ ሳይሆን በቃላችንና በሥራችንም
ጭምር ነው፡፡
በአንገታችንስ እንዳንመሰክርለት ማን ያግደናል? በአንገታችን
ባለው ማዕተብም ለእግዚአብሔር
እንመሰክራለን የስሙን ምልክት በአንገታችን እናኖራለን
አናፍርበትም ፡፡ የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ በጥምቀታችን
እንደምንመሰክር የጥምቀታችንንም አርማ በማተባችን
እናረጋግጣለን፡፡ (ሮሜ ፲፤፮-፲፫፡፡ ኢዮኤል ፪፤፴፪፡፡ ሮሜ
፮÷፩-፭ ፣ ማቴ ፭÷፲፩-፲፪፡፡ ፩ጴጥ ፫÷፳፩-፳፪ ፩ጴጥ ፬÷፲፪-
፲፮)ተመልከት፡፡
የማዕተብ ጥቅም
1. የክርስትናን ማዕተብ በአንገት ማሰር በልብ ያለውን እምነት
ሳያፍሩ በኃጢአተኛው ትውልድ መካከል ስለ ክርስቶስ
መመስከር እንዲሁም ለሰይፍ ለመከራ መዘጋጀትን ማመልከት
ነው፡፡
2. ክርስቲያን ከሆኑ ምእመናን ጋር ሃይማኖታዊ የሆነውን
ተሳትፎ በቀላሉ ለማከናወንና በክርስቲያን ወገኖች ዘንድ
ተቀባይነት ለማግኘ
3. በጉዞ ላይ ያልታሰበ አደጋ ቢያጋጥምና ሞት ቢደርስ አደጋው
ደርሶበት ያረፈው ክርስቲያን ቤተሰቦቹ ባይገኙ በቅርበት
በማዕተቡ ክርስትናው ተረጋግጦ ጸሎተ ፍትሐት ተደርጎለት
በእምነቱ ተከብሮ አስከሬኑ በክርስቲያኖች መካነ መቃበር
ያርፋል፡፡
ወስበሐት ለእግዚአብሔር!