ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

Monday, May 16, 2016

=>+*"+<+>+ግንቦት 9+<+>+"*+

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
አሜን
#ግንቦት 9
#የታላቁ_ጻድቅ_ንጉሥ_የቆ ስጠንጢኖስ_እናት
#የከበረች_ንግሥት_እሌኒ_ ዐረፈች፡፡ ጌታችን የተሰቀለበት
መስቀል ሙት እያስነሳ ድውይ እየፈወሰ አጋንንት እያወጣ
የተለያዩ ገቢረ ተአምራት ሲሰራ ክፉዎች አይሁዶች አይተው
ሕዝቡ ክርስቲያን እንዳይሆኑ በመፍራት በ34 ዓ.ም
ከኢየሩሳሌም ወጣ ብሎ በሚገኝ ቦታ ቆፍረው ቀበሩት፡፡
ከዚያም የከተማውን ቆሻሻ ሁሉ ከዚያ መስቀሉ በተቀበረበት
ቦታ ላይ እየደፉ ከዘመን ብዛት ቦታው በቆሻሻ ክምር የተነሣ
ተራራ ሆነ፡፡ እስራኤልን ከሮም ቅኝ አገዛዝ ነጻ ለማውጣት
ከ66-70 ዓ.ም ባደረጉት እንቅስቃሴ ጥጦስ የተባለው የሮም
ንጉሠ ነገሥት ዘምቶ ኢየሩሳሌምን በ70 ዓ.ም ደመሰሳት፡፡
ትልቁን የአይሁድ ቤተመቅደስንም አቃጠለው፡፡
እስራኤላውያንም በመላው ዓለም ተበተኑ፡፡ ከዘመነ ሐዋርያት
ጀምሮ በተከታታይ በሮም የነገሡ ነገሥታት /ቄሳሮች/
በክርስቲያኖች ላይ የማያባራ መከራ አድርሰዋል፡፡ ክርስቲያኖች
የተቀበረውን መስቀል አስፈልገው ለማውጣት ቀርቶ
ሃይማኖታቸውን የማመን ነጻነት ስላልነበራቸው ቅዱስ
መስቀል ለ300 ዓመታት ያህል ተቀብሮ የጉድፍ መጣያ ሆኖ
ቆየ፡፡ የመስቀሉ የመገኘት ታሪክ የቤተክርስቲያን የመከራ
ዘመን አልፎ የዕረፍትና የሰላም ዘመን ሲመጣ ለብዙ ዘመን
ተቀብሮ የተረሳውን መስቀል ባለቤቱ መድኃኔዓለም
አልረሳምና እርሱ የፈቀዳት ዕለት ስትደርስ በዕሌኒ ንግሥት
አማካኝነት ከተቀበረበት እንዲወጣ አደረገ፡፡
ዕሌኒና ተርቢኖስ የሚባሉ ሁለት ደጋግ ክርስቲያኖች ተጋብተው
ይኖሩ ነበር፡፡ ተርቢኖስና ዕሌኒ ኑሮአቸው ፍቅርና ሰላም
የሰፈነበት በመሆኑ ለብዙ ሰዎች እንደ ምሳሌ ሆነው ይኖሩ
ነበር፡፡ ተርቢኖስ ነጋዴ ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ራቅ ወዳለ
ሀገር በመርከብ ለንግድ ሄደ፡፡ ዕሌኒም ባለቤቷ ተርቢኖስ
ለንግድ ወጥቶ እስኪመለስ ስለባሏ ከመጸለይና ከማሰብ በቀር
ከግቢዋ አትወጣም ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ተርቢኖስ ለንግድ ሄዶ
ብዙ ዓመታትን ቆይቶ ከጓደኞቹ ጋር ወደሀገሩ ሲመለስ
ከነጋዴዎች አንዱ "በእግዚአብሔር ፈቃድ ከሽፍታና ከማዕበል
ከልዩ ልዩ አደጋ ተርፈን በሰላም ተመልሰን ሚስቶቻችን ሌላ
ሳይወዱ ሳይለምዱ እናገኛቸው ይሆን?" ብሎ ጠየቀ፡፡ ተርቢኖስ
ግን "እንኳን በሰላም አደረሰን እንጂ ሚስቴን በዚህ
አልጠረጥራትም" ብሎ ሲመልስ ሌላው ጓደኛው "ያንተ ሚስት
ከማን ትበልጣለችና ነው አሁን ሄጄ ከሚስትህ ጋር ለምዳኝ
ወዳኝ ወድጃት ብመጣስ ምን ትቀጣለህ?" አለው፡፡
ተርቢኖስም በሚስቱ ዕሌኒ ተማምኖ "ይህንን ብታደርግ ይህን
ያህል ዓመት የለፋሁበት ሀብት ከነትርፉ ውሰድ አንተም
ብታደርግ እንዲሁ ሀብትህ ከነትርፉ ለእኔ ይሁን" ተባብለው
ተወራረዱ፡፡
ከዚያም መርከቡ ወደብ ከመድረሱ በፊት ነጋዴው ወደ ዕሌኒ
ቤት ደረሰና በሩን አንኳኩቶ ሠራተኛይቱን "ዕሌኒን ማነጋገር
እፈልጋለሁና ንገሪልኝ" ብሎ ጠየቃት፡፡ እርሷም እያፈረች
የተላከችውን ለዕሌኒ ነገረቻት፡፡ ዕሌኒም ተቆጥታ "ከመች
ወዲህ ነው እንግዳ የማነጋግረው?" ብላ አሳፈረቻት፡፡
ሠራተኛይቱም ለነጋዴው መልሱን ስትነግረው ነጋዴው
እንደማይሆንለት ከተረዳ በኋላ ሌላ ተንኮል አቀደና
ለሠራተኛይቱ "ባልና ሚስቱ ብቻ የሚያውቁትን አንድ ነገር ብቻ
ብትሰጪኝ ብዙ ገንዘብና ወርቅ እሰጥሻለሁ" ብሎ ወርቅ
ሰጣት፡፡ ሠራተኛይቱም "ሁለቱ ብቻ የሚያውቁት የእመቤቴ
ሀብል አለ ያንን እመጣልሀለሁ መጀመርያ አንተ በከተማው
ውስጥ እየዞርህ ነጋዴዎችን መጡ የብስ ረገጡ እያልክ አስወራ
ከዚያም ተመልሰህ እንድትመጣ" ብላ ሰደደችው፡፡ ነጋዴውም
እንደተመከረው የነጋዴዎቹን መምጣት በከተማይቱ እንዳወራ
የነጋዴዎቹ ቤተሰቦች ነጋዴዎችን ለመቀበል ዝግጅት ማድረግ
ጀመሩ፡፡ የዕሌኒም ሠራተኛ "እመቤቴ ነጋዴዎች መጡ ተብሎ
ይወራልና፡፡ ባለቤትዎ በሰላም ስለመጡ ይዘገጃጁ ገላዎን
ይታጠቡ" ብላ መከረቻት፡፡ ዕሌኒም ገላዋን ስትታጠብ ያንገቷን
ሐብል ቁጭ ካደረገችበት ቦታ ሠራተኛይቱ አንስታ ለነጋዴው
በተቃጠሩበት ዕለት ሰጠችው፡፡ ነጋዴውም ለሠራተኛይቱ
የውለታዋን ብዙ ገንዘብና ወርቅ ሰጥቶአት ደስ እያለው ወደ
ጓደኞቹ ሄደ፡፡ ለተርቢኖስ "ሚስትህን ለምጃት ወድጃት
መጣሁ" አለው፡፡ ተርቢኖስም "ውሸት ነው ለዚህ ምን ምልክት
አለህ?" ብሎ ጠየቀው፡፡ ተንኮለኛውም ነጋዴ ያንን ሐብል
አውጥቶ "ይህ ሀብል የሚስትህ አይደለምን?" ብሎ ሰጠው፡፡
ተርቢኖስም ደነገጠ የሚናገረውን አጣ፡፡ በውርርዱም መሠረት
ሀብቱን ሁሉ አስረከበና ባዶ እጁን ወደቤቱ እያዘነ እየተቆጨ
ሔደ፡፡
ባለቤቷን በናፍቆትና በታማኝነት ስትጠብቅ የከረመችው ዕሌኒ
በተርቢኖስ ያልተለመደ ሀዘንና ብስጭት ግራ ተጋብታ
"ወንድሜ ምን ሆነሀል? ለወትሮው እንኳን ይህን ያህል ዘመን
ተለያይተን ቀርቶ ለጥቂት ቀናት ተለያይተን እንኳ ለጥቂት
ቀናት ተለያይተን ስንገናኝ እንነፋፈቃለን፡፡ አሁን ግን
ከመጣህበት ጊዜ ጀምሮ አዝነህ አይሃለሁ" ብላ ጠየቀችው፡፡
ተርቢኖስም "ብዙ የደከምኩበትና የለፋሁበት ሀብት ንብረቴ
እንዳለ ማዕበል አጠፋብኝ እኔ ያላዘንኩ ማን ይዘን?" አላት፡፡
ዕሌኒም የተማረች ናትና "እግዚአብሔር ሰጠ እግዚአብሔር ነሣ
የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን እንዳለ ኢዮብን
አስበው፡፡ አንተ እንኳን በሰላም መጣህ እንጂ ሀብቱ ውሎ
አድሮ ይመጣል..." እያለች አጽናናችው፡፡ ተርቢኖስም "እንግዲህ
በተከበርኩበት ሀገር ተዋርጄ፣ በሰጠሁበት ሀገር ለምኜ ለመኖር
አልችልምና ወደሌላ ወደማያውቁኝ ሀገር እሔዳለሁ አንቺ ግን
ሁሉ ይወድሻል ያከብርሻል ከወደድሸው ጋር ኑሪ" አላት፡፡
ዕሌኒም "በደስታ ጊዜ አብሬህ እንደሆንኩ በችግርም ጊዜ
ልለይህም የእኔንና ያንተን አንድነት ችግር አይፈታውም ከአንተ
ተለይቼ ወዴት እቀራለሁ ወደምትሄድበት አብሬህ እሄዳለሁ"
ብላ ተነሳች፡፡ ሁለቱም ቤታቸውን ጥለው ሲሄዱ በመንገድ ላይ
ተርቢኖስ በልቡናው ይዞት የነበረውን ምሥጢር አወጣው
"ዕሌኒ ስወድሽ የጠላሽኝ ሳምንሽ የከዳሽኝ ምን አድርጌሽ
ነው?" ብሎ ጠየቃት፡፡ ዕሌኒም "እኔ አንተን አልጠላሁም
አልከዳሁምም ይህንን ሐሳብ እንዴት አሰብህ?" ብትለው ከኪሱ
አውጥቶ ሀብሉን አሳያትና የሆነውን ሁሉ ነገራት፡፡ ዕሌኒም
ያልጠበቀችው ነገር ስለተፈጸመ አዝና የሆነውን እውነተኛ ታሪክ
በሙሉ ነገረችው፡፡ ተርቢኖስ ግን አላመናትም፡፡ ከባህር ዳር
በደረሱ ጊዜ በቁመቷ ልክ ሣጥን አሠርቶ ዕሌኒን በውስጡ
አስገባትና "ብታደርጊውም ባታደርጊውም እንደሥራሽ ሥራሽ
ያውጣሽ" ብሎ ወደ ባሕሩ ወረወራት፡፡
ዕሌኒ ያለችበት ሣጥን በፈቃደ እግዚአብሔር እየተንሳፈፈ
ከወደብ ደረሰ፡፡ በዚያ ወደብ አካባቢ ምዕራብ ሮምን ያስተዳደር
የነበረው ኮስታንዲዮስ (ቁንስጣ) የተባለው ንጉሥ ነበርና
ሣጥኑን አይቶ አውጥቶ እንዲከፍቱት ወታደሮችን አዘዘ፡፡
ሣጥኑን አውጥተውም ሲከፍቱት እጅግ የተዋበች ሴት ሆና
አገኟት፡፡ ንጉሡም ዕሌኒን ወስዶ ሚስቱ አደረጋት፡፡
ኮስታንዲዮስ (ቁንስጣ) የመክስምያኖስ ቄሳር ሆኖ ምዕራብ
ሮምን ያስተዳደር ነበር፡፡ ንግስት ዕሌኒም በ272 ዓ.ም ታላቁ
ቆስጠንጢኖስን ወለደችለት ቆስጠንጢኖስም ገና በወጣትነቱ
የአባቱ እንደራሴ ሆኖ እንደሠራ አባቱ ሞተ፡፡ የአባቱ
ባለሟሎችና ሕዝቡ ተስማምተው የ18 ዓመቱን
ቆስጠንጢኖስን በአባቱ ቦታ ሐምሌ 25 ቀን 316 ዓ.ም
በሮም ምዕራብ ክፍል በገላትያ አነገሡት፡፡ በጦር ሜዳዎች
ብዙ የጀግንነት ሥራዎች ስለሠራ በሠራዊቱ ዘንድ ይወደድ
ነበር፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴን ወላጅ እናቱ በፈርዖን ቤት
ሃይማኖቱን ባሕሉን ታሪኩን በሚገባ እያስተማረች
እንዳሳደገችው ሁሉ ንግሥት ዕሌኒም ልጇን ቆስጠንጢኖስን
ከልጅነቱ ጀምሮ ስለክርስትና ሃይማኖትና ስለክርስቲያኖች
መከራ ታስተምረው ስለነበር በክርስቲያኖች ላይ የነበረው
አመለካከት በሮም ከነገሡት ቄሣሮች ሁሉ የተሻለ ነበር፡፡
በተለይም በ312 ዓ.ም ከጠላቱ ከመክስምያኖስ ጋር ለመዋጋት
"ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት" ብሎ ለዘመቻ እንደተሰለፈ
በራእይ በሰማይ ላይ "በዚህ መስቀል (ምልክት) ጠላትህን ድል
ታደርጋለህ" የሚል የመስቀል ቅርጽና የተጻፈ ጽሑፍ ስላየ
ለሠራዊቱ የመስቀል ምልክት በመሳሪያቸውና በሰንደቅ
ዓላማው ላይ እንዲያደርጉ አዘዘ፡፡ ወደያው ጦርነት ቢገጥም
ጠላቱን ድል ነሥቶ በጠቅላላው የሮም መንግሥት ግዛቶች ሁሉ
ገዥ ሆነ፡፡
ታላቁ ቆስጠንጢኖስ የሮም ንጉሠ ነገሥት ከሆነ በኋላ በ300
ዓመታት ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ ለክርስቲያኖች የነጻነት ዐዋጅ
ዐወጀ፡፡ ክርስትናም ብሔራዊ ሃይማኖት ተባለች፡፡ ንግሥት
እሌኒም በተፈጠረላት አመች ሁኔታ በመጠቀም የጌታችን
መስቀል ከተቀበረበት ለማውጣት በ327 ዓ.ም
ወደኢየሩሳሌም ሔደች፡፡ ዕሌኒ ልጅዋ ቆስጠንጢኖስ
ክርስቲያን ከሆነላት ወደ ኢየሩሳሌም ሔዳ መስቀሉን
ለመፈለግ እንዲሁም በኢየሩሳሌም ያሉ ቅዱሳት መካናትንና
አብያተ ክርስቲያናትን ለማሳነጽ ለእግዚአብሔር ተሳለች፡፡ ከዚህ
በኋላ ቆስጠንጢኖስ አምኖ በ337 ዓ.ም ተጠመቀ፡፡ ቅድስት
ዕሌኒም ወደ ኢየሩሳሌም ሔደች፡፡ ከእርሷም ጋር ብዙ
ሠራዊት ነበር፡፡ እንደደረሰችም ስለ ቅዱስ መስቀል
መረመረች፡፡ ነገር ግን ቦታውን የሚያስረዳት አላገኘችም፡፡
የአይሁድ ወገን እንቢ ቢሉም በኋላ ግን ባደረገችው ጥረት
አረጋዊው ኪራኮስ የጎልጎታን ኮረብታ አመለከታትና አስቆፍሪው
ብሎ ነገራት ኪራኮስም ዘመኑ ከመርዘሙ ጋር ተያይዞ
እውነተኛው ተራራ ይህ ነው ብሎ ማሳየት ባለመቻሉ "ከሦስቱ
ተራሮች አንዱ ነው" ስላላት አይሁድ ተራሮቹን ይቆፍሩ ዘንድ
አዘዘቻቸው፡፡ የጌታችን ቅዱስ መስቀል በሚያደርጋቸው
አስደናቂ ተአምራት የተነሣ ሕዝቡ እያመነ በተቸገሩ ግዜ
ክፉዎች አይሁዶች ማንም እንዳያገኘው የኢየሩሳሌም ነዋሪ
ሁሉ የእቤቱን ቆሻሻ የከበረ መስቀል ባለበት ቦታ እንዲጥል
አዘው ስለነበር ከሁለት መቶ ሃምሳ ዓመት በላይ ጥራጊ
ስለጣሉበት ታላቅ ተራራ ሆነ፡፡
ዕሌኒ ተራሮቹን ለማስቆፈር ከሦስቱ ተራሮች የቱ እንደሆነ
ለመለየት ደመራ አስደምራ ብዙ ዕጣን በመጨመርና
በማቃጠል ከአኢየሩሳሌም ወጣ ብለው ያሉትን ኮረብቶች
አሳያት፡፡ የዕጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ በመውጣት በቀጥታ ተመልሶ
መስቀሉ ባለበት ተራራ ላይ በማረፍና በመስገድ መስቀሉ
ያለበትን ትክክለኛ ሥፍራ አመለከታት፡፡ ቅዱስ ያሬድም "ሰገደ
ጢስ" ጢሱ ሰገደ ብሎታል፡፡ ከዚያም መስከረም 16 ቀን
ቁፋሮው እንዲጀመር አዘዘች፡፡ ሰባት ወር ያህል ከተቆፈረ በኋላ
መጋቢት 10 ቀን ሦስት መስቀሎች በአንድነት ተገኙ፡፡ ንግሥት
ዕሌኒም የክብር ባለቤት ጌታችን የተሰቀለበት የትኛው እንደሆነ
ለማወቅ በወደደች ጊዜ "ከራሱ በላይ ይህ የናዝሬቱ ኢየሱስ
የአይሁድ ንጉሥ ነው" የሚል የተቀረጸበት ጽሑፍ ያለው
እንደሆነ የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ ቅዱስ መቃርስ ነገራት፡፡
ከእርሱም ምልለክት ታይ ዘንድ ወደደች፡፡ የሞተ ሰው አምጥታ
በሁለቱ መስቀሎች ላይ በተራ ቢታስቀምጠው አልተነሣም፡፡
በመጨረሻ ጽሕፈት ባለው በአንዱ መስቀል ላይ
ቢታስቀምጠው ያንጊዜ የሞተው ሰው ተነሣ፡፡ በዚህም
የጌታችንን መስቀል ለየችው፡፡ ዕሌኒም ለጌታችን መስቀል
ሰገደችለት፡፡ ክርስቲያኖች ሁሉ ሰገዱለት፡፡ በየሀገሩ ያሉ
ክርስትያኖች ሁሉ የመስቀሉን መገኘት በሰሙ ግዜ መብራት
አብርተው ደስታቸውን በመግለጥ ለዓለም እንዲታወቅ
አደረጉ፡፡ በዚህም ምክንያት ይህ ታላቅ የድኅነት ምልክት
የሆነው መስቀል የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ደመራ በመደመር
በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ታከብረዋለች፡፡
ንግሥት ዕሌኒ መስከረም 16 ቀን 320 ዓ.ም በዕጣን ጢስ
ምልክት ቁፋሮ አስጀምራ መጋቢት 10 ቀን አግኝታ
በማውጣት ታላቅ ቤተ መቅደስ ጎልጎታ ላይ ሠርታ በክብር
አስቀመጠችው፡፡ ጌታችን ስለ ቅዱስ መስቀሉ ለቅድስት
ንግስት ዕሌኒ ቃልኪዳን ሲገባላት እንዲህ አላት፡- ‹‹በደሜ
የከበረ የመስቀሌን ስም የሚጠራውን እርሱን እምረዋለሁ፡፡
በዕፀ መስቀሌ ቤ/ክ ውስጥ የለመነውን የጸለየውን ሰው
መላእክት እንኳን ተድላ ደስታውን ወደማያውቁት ወደ
መንግሥተ ሰማያት አዳራሽ ያለወቀሳ ይገባል፡፡ ለከበረ
መስቀሌ ከቅርብም ከሩቅም ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ተጉዞ
የመጣውን ወደ መቃብሬ ኢየሩሳሌም እንደጓዘ እኔ
አደርግለታለሁ፡፡ ይህንንም መጽሐፍ የጻፈ ያጻፈ ወይም
ያነበበውን የተረጎመውን ቃሉን በዕዝነ ልቡና የሰማውን
የመጽሐፉንም ገበታዎቹን የሳመውን በተጸለየበት ውኃም
የተጠመቀውን እኔ በሕይወት መጽሐፍ በዓምደ ወርቅ ላይ
በወርቅ ቀለም ስሙን እጽፈዋለሁ፡፡›› (ድርሳነ መስቀል)
የጌታችንን ቅዱስ መስቀል ንግሥት ዕሌኒ መጋቢት 10 ቀን
አግኝታ በማውጣት ታላቅ ቤተ መቅደስ ጎልጎታ ላይ ሠርታ
በክብር ካስቀመጠችው በኋላ ከዚያ ዕለት ጀምሮ እንደ ፀሐይ
እያበራ ድውይ እየፈወሰ አጋንንት እያባረረ ልዩ ልዩ ገቢረ
ተአምራት እየሠራ ሙት እያነሣ ዕውር እያበራ ተአምራቱን
ቀጠለ፡፡ ይህንንም የሰማው ከኃያላን ነገሥታት መካከል የፋርስ
ንጉሥ መስቀሉን ማርኮ ፋርስ ወስዶ አስቀመጠው፡፡ ነገር ግን
ንጉሡ ሕርቃል የጌታችንን ቅዱስ መስቀል አስመልሶታል፡፡
በዚህ ጊዜ የኢየሩሳሌም ምእመናን የድሉን ዜና ሰምተው
ስለነበር የአንድ ቀን መንገድ ያህል ሄደው በመቀበል ካህናቱ
በዝማሬና በእልልታ ችቦ አብርተው ተቀብለዋቸዋል፡፡
የቤተክርስቲያን አባቶች እንደሚሉት ንጉሡ ሕርቃል ይህንን
ታላቅ ድል ለማግኘትና የጌታን ቅዱስ መስቀል ከአሕዛብ
(ከፋርሶች) እጅ ለማስመለስ የቻለው በዚያን ጊዜ አብያተ
ክርስቲያንናት ሁሉ ለአንድ ሳምንት (አንድ ሱባዔ) ባደረጉት ጾም
ጸሎት ነው፡፡ ይህንንም ለማስታወስና ጌታን ለማመስገን
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንና የግብጽ ኮፕቲክ
ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ የዐቢይ ጾም ከመጀመሩ አስቀድሞ
"ጾመ ሕርቃል" ብለው አንድ ሳምንት ይጾማሉ፡፡ የጌታ
መስቀል ለብዙ ጊዜያት ኢየሩሳሌም ከቆየ በኋላ ነገሥታት
‹‹ይህን መስቀል እኔ ልውሰድ፣ እኔ ልውሰድ›› በማለት ጠብ
ፈጠሩ፡፡ በዚህ ጊዜ የአንጾኪያ፣ የኤፌሶን፣ የአርማንያ፣ የግሪክ፣
የእስክንድርያ፣ የመሳሰሉት የሃይማኖት መሪዎች ጠቡን
አበረዱት፡፡ ከዚያም አያይዘው በኢየሩሳሌም የሚገኘውን
የክርስቶስን መስቀል ከአራት ከፍለው በዕጣ አድርገው
በስምምነት ተካፍለው ከሌሎች ታሪካዊ ንዋያተ ቅዱሳት ጋር
በየሀገራቸው ወስደው በክብር አስቀመጡት፡፡ የቀኝ ክንፉ
የደረሰው ለአፍሪቃ ስለነበር ከታሪካዊ ንዋየ ቅዱሳት ጋር
በግብጽ የሚገኘው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ተረክቦ ወስዶ
በክብር አስቀመጠው፡፡ ግማደ መስቀሉ ለብዙ ዘመን
በእስክንድርያ ሲኖር በግብጽ ያሉ እስላሞች እየበዙ ኃይላቸው
እየጠነከረ ሲሔድ በእስክንድርያ የሚኖሩ ክርስትያኖች ላይ
ሥቃይ ያጸኑባቸው ጀመር፡፡ ክርስቲያኖቹም አንድ ሆነው
መክረው ለኢትዮጵያዊው ዓጼ ዳዊት እንዲህ የሚል መልእክት
ላኩ "ንጉሥ ሆይ! በዚህ በግብጽ ያሉ እስላሞች መከራ
አጽንተውብናልና ኃይልህን አንሥተህ አስታግስልን" ብለው
ጠየቁት ዳግማዊ ዐጼ ዳዊትም ለመንፈሳዊ ሃይማኖት
ቀንተው የክርስቶስ ፍቅር አስገድዷቸው 20,000 ሠራዊት
አስከትለው ወደ ግብጽ ዘመቱ በዚህ ጊዜ በግብጽ ያሉ ኃያላን
ፈሩ ተሸበሩ፡፡ ንጉሡ ዳግማዊ ዳዊትም እንዲህ የሚል
መልዕክት ለእስላሞቹ ላከ፡- "በተፈጥሮ ወንድሞቻችሁ ከሆኑት
ክርስቲያኖች ካልታረቃችሁ ሀገራችሁን መጥቼ አጠፋለሁ"
የሚል ማስጠንቀቂያ ላከ፡፡
የንጉሡ መልዕክትም ለእስላሞቹ እንደደረሳቸው ፈርተው እንደ
ጥንቱ በየሃይማታቸው ጸንተው በሰላም እንዲኖሩ ከክርስቲያን
ወንድሞቻቸው ጋር ታረቁ፡፡ መታረቃቸውን ዓጼ ዳዊት ሰሙ
በዚህም ጉዳይ ንጉሡ ደስ አላቸው፡፡ እግዚአብሔርንም
አመሰገኑ በግብጽ የሚኖሩ ክርስቲያኖችም ከ12,000 ወቄት
ወርቅ ጋር ደስታቸውን ለኢትዮጵያዊው ንጉሥ ለዳግማዊ
ዳዊት በደብዳቤ አድርገው ላኩላቸው፡፡ ንጉሡም የደስታውን
ደብዳቤ ተመልክተው ደስ አላቸው ወርቁን ግን መልሰው
በመላክ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጻፉ፡- "በግብጽ የምትኖሩ
የክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ የላካችሁልኝ
12,000 ወቄት ወርቅ መልሼ ልኬላችኋለሁ፡፡ የእኔ ዓላማ
ወርቅ ፍለጋ አይደለም የክርስቶስ ፍቅር አስገድዶኝ በተቻለኝ
ችግራችሁን ሁሉ አስወገድኩላችሁ፤አሁንም የምለምናችሁ
በሀገሬ ኢትዮጵያ ረሀብና ቸነፈር ድርቅ ስለወረደብኝ
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀልና
የቅዱሳን አጽም ከሌሎች ክቡራን ዕቃዎች ጋር እንድትልኩልኝ
ነው" የሚል ነበር፡፡
እስክንድርያ ያሉ ምዕመናንም የዐፄ ዳዊት "በሀገሬ ኢትዮጵያ
ረሀብና ቸነፈር ድርቅ ስለወረደብኝ መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀልና የቅዱሳን አጽም
ከሌሎች ክቡራን ዕቃዎች ጋር እንድትልኩልኝ" የሚለው
መልዕክት እንደደረሳቸው ከሊቃነ ጳጳሳትና ከኤጲስ ቆጶሳቱ ጋር
ውይይት በማድረግ "ይህ ንጉሥ ታላቅ ክርስቲያን ነው፡፡ ስለዚህ
ልቡን ደስ እንዲለው የፈለገውን የጌታችንን ግማደ መስቀል
ከቅዱሳን ዐፅምና ንዋየ ቅዱሳት ጋር አሁን በመለሰው ወቄት
ወርቅ የብርና የነሐስ የመዳብና የወርቅ ሣጥን አዘጋጅተን
እንላክለት" ብለው ተስማምተው በክብር በሥነ ሥርዓት
በሠረገላና በግመል አስጭነው ስናር ድረስ አምጥተው
ለኢትዮጵያውያን ባስረከቧቸው ጊዜ በእጃቸው እያጨበጨቡ
በእግራቸው እያሸበሸቡ በግንባራቸው እየሰገዱ በክብር በደስታ
ተቀበሏቸው፡፡
ግማደ መስቀሉ ወደ መካከለኛው ኢትዮጵያ ሳይደርስ በድንገት
ዐፄ ዳዊት ስናር በሚባል በረሃ ላይ አረፉ፡፡ ግማደ መስቀሉም
የግድ በዚያው በስናር መቆየት አስፈለገው፡፡ ከዚህ በኋላ የሟቹ
የዳግማዊ ዳዊት ልጅ ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ እንደነገሡ ወደ ስናር
ሔደው ግማደ መስቀሉን ከሌሎቹ ንዋያተ ቅዱሳት ጋር
አምጥተው በመናገሻ ከተማቸው በደብረ ብርሃን ላይ
ቤተመቅደስ ሠርተው ለማስቀመጥ ሲደክሙ በሕልማችው
አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል "ወዳጄ ዘርዐ ያዕቆብ ሆይ
መስቀሌን በመስቀለኛ ቦታ ላይ አስቀምጥ" የሚል ራእይ
አዩ፡፡
ከእስክንድርያ ሀገር ከመስቀሉ ጋር በልዩ ልዩ ሣጥን ተቆልፈው
የመጡትም ዝርዝር ስማቸው ጌታችን በዕለተ ዓርብ ለብሶት
የነበረው ቀይ ልብስ፣ ከሮም የመጣው ከለሜዳው፣ ሐሙት
የጠጣበት ሰፍነግ /ጽዋ/፣ ዮሐንስ የሳለው ኩርዓተ ርዕሱ ስዕል
እንዲሁም የተለያዩ የቅዱሳን አጽም፣ ከግብጽ ታላላቅ ገዳማት
የተቆነጠረ አፈር፣ የዮርዳኖስ ውሃ ይገኛል፡፡ ንጉሡም
መስቀለኛ ቦታ እየፈለጉ በኢትዮጵያ አውራጃዎች ሁሉ
በመፈለግ ከብዙ ቦታ አስቀምጠውት ነበር፡፡ ለምሳሌ በሸዋ
በደብር ቅዱስ ደብረ ጽጌ ማርያም ገዳም፣ በማናገሻ ማርያም፣
በወጨጫ መስቀሉን አሳርፈውት ነበር፡፡ ነገር ግን
የመጨረሻውን ቦታ ባለማግኘታቸው በራዕይ እየደጋገመ
አንብር መስቅልየ በዲበ መስቅል መስቀሌን በመስቀለኛ
ሥፍራ አስቀምጥ እያለ ይነግራቸው ነበር፡፡ ዓጼ ዘርዓ
ያዕቆብም ለሰባት ቀን ሱባዔ ገቡ፡፡ በዚያም የተገለጸላቸው
"መስቀለኛውን ቦታ የሚመራህ ዓምደብርሃን ይመጣል"
አላቸው፡፡ እርሳቸውም ከዚያ እንደወጡ መስቀለኛውን ቦታ
የሚመራ የብርሃን ዓምድ ከፊታቸው መጥቶ ቆመ፡፡ በዚያ
መሪነት ወደ ወሎ ክፍለ ሀገር አምባሰል አውራጃ ውስጥ ግሸን
ከምትባል አምባ መርቶ መስከረም 21 ቀን 1440 ዓ.ም
አደረሳቸው፡፡ በእውነትም ይህች ግሸን የተባለችው አምባ
ጥበበኛ ሰው እንደቀረጻት የተዋበች መስቀለኛ ቦታ ሆና
ስላገኟት የልባቸው ስለደረሰ ደስ አላቸው፡፡ እግዚአብሔር ገና
ዓለምን ሲፈጥር የግሸንን ዓምባ ለዚህ ክብር የተዘጋጀች አድርጎ
ፈጥሯታልና፡፡ በዚያም አምባ ታላቅ ቤተ መቅደስ ሠርተው
ቅዱስ መስቀሉንና ሌሎች ንዋየ ቅዱሳቱን በየመዓረጋቸው
የክብር ቦታ መድበው አስቀመጡዋቸው፡፡ ዘመኑም በ14ኛው
ክፍለ ዘመን ነው፡፡ የንግሥት ዕሌኒ ረድኤት በረከቷ ይደርብን
በጸሎቷ ይማረን፡፡ የመስቀሉ ፍቅር ይደረብን!