ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

Thursday, May 19, 2016

=>+*"+<+>ግንቦት 12<+>+"*+

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
አሜን
ግንቦት 12-ዓሥር ታላላቅ ቅዱሳን በዓመታዊ በዓላቸው
ታስበው ይውላሉ፡፡
+ሐዲስ ሐዋርያ ብርሃን ዘኢትዮጵያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
ፍልሠተ ዐፅማቸው ነው፡፡
+ከ57 ዓመት በኋላ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ተገልጠውላቸው
‹‹...ጌታችን የነገረኝ ጊዜ ደርሷልና ሥጋዬን ከዚህ አፍልሰህ
አውጣ›› ብለው ስለ ፍልሠተ ዐፅማቸው የነገሯቸው አቡነ
ሕዝቅያስ ዕረፍታቸው ነው፡፡
+የዓለም ሁሉ መምህር የሆነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ዕረፍቱ
ነው፡፡
+በኢየሩሳሌም አገር በጎልጎታ ላይ ከፀሐይ በልጦ በሚበራ
ብርሃን የከበረ ቅዱስ መስቀል መገለጥ ሆነ፡፡
+እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ እልፍ ነፍሳትን ከሲኦል
ያወጣችበት ዕለት ነው፡፡
+ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ነቢዩ ዳንኤልን የረዳበት
ዕለት ነው፡፡ ዳንኤል በጉድጓድ ተጥሎ ሳለ መልአኩ ነቢዩ
ዕንባቆምን ነጥቆ ወስዶ ዳንኤል ካለበት አድርሶት
እንዲመግበው አደረገው፡፡
+ሃይማኖቱ የቀና የኢትዮጵያው ንጉሥ የበእደ ማርያም ልጅ
ጻድቁ ንጉሥ እስክንድር ዕረፍቱ መሆኑን ስንክሳሩ በስም
ይጠቅሰዋል፡፡
+ሰማዕታት የሆኑ ዲያቆን ሚናስና እስጢፋኖስ መታሰቢያ
በዓላቸው መሆኑን ስንክሳሩ በስም ይጠቅሳቸዋል፡፡
+በአባታችን በተክለ ሃይማኖት መንበር ከተሾሙት የከበሩ
መምህራን 17ኛ የሆነ የደብረ ሊባኖስ መምህር የከበረ አባ
አብርሃም ዕረፍቱ መሆኑን ስንክሳሩ በስም ይጠቅሰዋል፡፡
+የመላልኤል ልጅ የያሬድ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፡፡ ያሬደም
162 ዓመት ኖሮ ኄኖክን ወለደው፡፡ ኄኖክንም ከወለደው በኋላ
800 ዓመት ኖሮ ወንዲችንና ሴቶች ልጆችን ወለደ፡፡ መላ
ዘመኑም 962 ዓመት በሆነው ጊዜ በዕለተ ዐርብ በሦስት ሰዓት
ዐረፈ፡፡
የዓለም ሁሉ መምህር የሆነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፡-
የዓለም ሁሉ መምህር የሆነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሀገሩ
ግሪክ ሲሆን አባቱ አስፋኒዶስ ወታደር ነበር፡፡ እናቱ አትናስያም
እንዲማርላት አቴና አስገባችው፡፡ እርሱም በሚገባ ተምሮ
አድጎ እነ ቅዱስ ባስልዮስ ካሉበት ገዳም ገባ፡፡ በዚያም ሳለ
አባትህ ሞተ ብለው ቢነግሩት ሄዶ የአባቱን ንብረት በሙሉ ሸጦ
ለድኆች ሰጥቶ ወደ ገዳሙ ተመልሶ በታላቅ ተጋድሎ መኖር
ጀመረ፡፡ መልአኩም ተገልጦለት ታየውና ‹‹አይዞህ አትፍራ
በርታ አሁን የአንጾኪያው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፊላታዎስ ወደ አንተ
ይመጣል›› ብሎት ተሰወረ፡፡ መልአኩ ለሊቀ ጳጳሱም ተገልጦ
‹‹ዮሐንስን ዳንኤል ሐዲስ›› ብለህ ስም አውጣለት ብሎታል፡፡
እርሱም አመንኩሶት ስሙን አውጥቶለታል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ምግብ ሲመገብ ገብሱን ከነአሰሩ
ይገብ ነበር እንጂ የላመ የጣፈጠ ቀምሶ አያውቅም፡፡
የቍስጥንጥንያው ሊቀ ጳጳስ ሲያርፍ በምትኩ ቅዱስ ዮሐንስ
አፈወርቅ በ397 ዓ.ም ተሾመ፡፡ በዚህ ጊዜ የነበረው ንጉሥ
አርቃድዮስ ከዮሐንስ አንደበት የሃይማኖትን ነገር ይማር ነበርና
አንድ ቀን ንጉሡ በወንጌል ላይ ስለ እመቤታችን የተጻፈውን
‹‹ጌታችንን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም›› የሚለውን ንባብ
ትርጉሙን አስፍቶና አብራርቶ ሲያስተምረው ንጉሡም አምኖ
ተደሰተ፡፡ በዚህም ጊዜ የእመቤታችን ሥዕል በሰው አንደበት
ሦስት ጊዜ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ዮሐንስ
አፈወርቅ ብላ ስትጠራው እርሱም ሲመልስላት በተራው ሦስት
ጊዜ እሰግድ ለኪ እሰግድ ለኪ እሰግድ ለኪ በማለት አመስግኖ
ሰግዶላታል፡፡ ይህም በተአምረ ማርያም መግቢያ ላይ
ተመዝግቦ ተአምሯ ሲነበብ ምእመናን እንደ ዮሐንስ አፈወርቅ
እሰግድ ለኪ ይሏታል፡፡
አንድ ቀን ዮሐንስ አፈወርቅ አንዲት ሕፃን ልጅን ክርስትና
ሊያነሳ ሲሄድ መልአከ ሞት ደግሞ ሕፃኗን ሊቀስፍ ሲሄድ
በመንገድ ላይ ተገናኙና ዮሐንስ ‹‹ወዴት ትሄዳለህ?›› አለው፡፡
መልአከ ሞቱም ‹‹ሕፃኗን በሞት ቅሰፍ ተብዬ ተልኬ ልቀስፍ
እየሄድኩ ነው›› አለው፡፡ ዮሐንስም ‹‹ሳትጠመቅና ልጅነትን
ሳታገኝ እንዳትቀስፋት እስካጠምቃትም ድረስ
እንዳትንቀሳቀስ›› ብሎ በሥልጣነ ክህነቱ አስሮት ሄደና ሕፃኗን
ካጠመቃት በኋላ እረስቶት በሌላ መንገድ ተመለሰ፡፡ መልአከ
ሞቱም በዮሐንስ ሥልጣነ ክህነት ታስሮ 10 ዓመት እንደቆመ
ቆይቷል፡፡ ከ10 ዓመት በኋላ ዮሐንስ በዚያ መንገድ ሲያልፍ
መልአከ ሞትን ቆሞ ሲያየው ‹‹ለምን ጉዳይ ቆመሃል?››
አለው፡፡ መልአከ ሞትም ‹‹የዛሬ 10 ዓመት አንተ ስትሄድ
እንዳትንቀሳቀስ ስላልከኝ ሥልጣንህ እንደሰንሰለት አስሮ
ይዞኛል›› ቢለው ዮሐንስም ይህን ያህል ጊዜ በመርሳቱ ተጸጽቶ
‹‹ተሳስቻለሁ በል ሂድ ግብርህን ፈጽም›› ብሎት መልአከ
ሞትም ሄደና ልጅቱን ቀስፎ ዐርጓል፡፡ ዮሐንስም እቦታው
ሲደርስ ቤተሰቦቿ ሲያለቅሱ ቢያገኛቸው አስጽናቷቸው
ተመልሷል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ነገረ ሃይማኖትን እጅግ አስፍቶና
አምልቶ ያስተማረ እጅግ ሊቅ የሆነ የቤተ ክርስቲያናችን
መመኪያ ነው፡፡ በስሙ የተጠራውን ቅዳሴ ጨምሮ በጣም
በርካታ ድርሰቶችን ደርሷል፡፡ በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ዘመን
የነበረችው ጨካኟና አረመኔዋ ንግሥት አውዶክሲያ የድሃ
ንብረት እየቀማች ተወስድ ስለነበር ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም
ዘወትር ይመክራትና ይገሥጻት ነበር፡፡ አንድ ቀን አንዱ ድሃ ሄዶ
ለዮሐንስ አፈወርቅ ነግሮት ሄዶ ‹‹የድሃውን ንብረት
መልሺለት›› ቢላት እምቢ ስትለው ከቤተ ክርስቲያን
እንዳትገባና ከክርስቲያኖችም ህብረት እንዳትቀላቀል
አወገዛት፡፡ ‹‹ከግዝትህ ፍታኝ›› ብትለውም ‹‹የድሃውን ገንዘብ
ካልመለሽ አልፈታሽም›› ስላላት ‹‹በከንቱ አወገዘኝ አባት
ያስተምራል እንጂ እንዲህ አያደርግም›› እያለች ታስወራበት
ጀመር፡፡ ለቅዱስ ኤጲፋንዮስም ‹‹ዮሐንስ ያለ አግባብ
አውግዞኛልና መጥተህ አስፈታኝ አለዚያ ሃይማኖቴን
እቀይራለሁ፣ ቤተ ክርስቲያንንም አቃጥላለሁ›› ብላ ላከችት፡፡
ቅዱስ ኤጲፋንዮስም ሄዶ ‹‹ሰይጣን በልቧ አድሮባታል
ያሰበችውንም ያስፈጽማታልና ለአገልግሎታችንም እንቅፋት
እንዳትሆን ፍታት›› ቢለው ቅዱስ ዮሐንስም እምቢ አለው፡፡
እርሷም በየከተማው እየዞረች ‹‹ተመልከቱ ዮሐንስ
ኤጲፋንዮስንም አወገዘው›› እያለች በውሸት ታስወራ ጀመር፡፡
ኤጲፋንዮስም እንዲህ ማለቷን አልሰማም ነበርና ከዮሐንስ ጋር
በኋላ ተሰነባብተው ሊለያዩ ሲሉ ዮሐንስ ‹‹ለምን በነገሬ
ገባህብኝ›› አለው፡፡ ኤጲፋንዮስም ‹‹አልገባሁም›› ቢለው
በንግግር ሳይግባቡ ቀርተው ተጣሉ፡፡ በዚህም ጊዜ ሁለቱም
የሚሞቱበት ጊዜና የሚሞቱበት በምን ዓይነት ሁኔታ እንደሆነ
ተገልጦላቸው አንዳቸው ለአንዳቸው ትንቢት ተነጋግረዋል፡፡
ዮሐንስ ኤጲፋንዮስን ‹‹ሄደህ ከቤትህ አትገባም ከመንገድ ላይ
አንበሳ ሰብሮ ይገድልሃል›› አለው፡፡ ኤጲፋንዮስም ለዮሐንስ
‹‹የእኔን ትላለህ አንተም እንጂ ደግሞ ተግዘህ በከሃዲዮች
ተወግዘህ በአንጾኪያ ደሴት ታስረህ ተሠቃይተህ ትሞታለህ››
አለው፡፡
በተነጋገሩትም ትንቢት መሠረት ኤጲፋንዮስ ወደ በዓቱ ሲሄድ
አንበሳ ገደለውና የአንበሳ ሆድ መቃብሩ ሆነለት፡፡ ዮሐንስም
በግዞት ታስሮ ብዙ ከተሠቃየ በኋላ ግንቦት 12 ቀን ዐረፈ፡፡
ጨካኟና አረመኔዋ ንግሥት አውዶክሲያም ‹‹ዮሐንስ
ኤጲፋንዮስን አውግዞት ወደ ሀገሩ አባሮት በመንገድ ላይ
እንዲሞት አደረገው›› እያለች በሀሰት አስወርታ የቤተ
ክርስቲያን ጠላቶች የሆኑትን ሰዎች ሰብስባ ዮሐንስን
እንዲያወግዙት ካደረገች በኋላ በግዞት ታስሮ እንዲኖርና
ተሠቃይቶ እንዲሞት አድርጋዋለች፡፡ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣
በጸሎቱ ይማረን፡፡
+ + + + + + + + + + + + + + +
ዳግመኛም በዚህች ዕለት እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
እልፍ ነፍሳትን ከሲኦል አውጥታለች፡፡ ሊቀ መላእክት ቅዱስ
ሚካኤል በስሙ የተቀረጸ ጽላት አምጥቶ ለቅድስት ክርስቶስ
ሠምራ ሰጣትና በጓንጉት ደሴት ውስጥ በእርሱ ስም ቤተ
ክርስቲያን እንድታሠራ ነገራት፡፡ ‹‹እንዴት ይሆንልኛል?››
ባለችውም ጊዜ ‹‹እኒያ ያጠመቁሽ ቅዱሳን ከጥቂት ዓመታት
በኋላ እመ ምኔት ትሆኛለሽ ያሉሽን ረሳሽውን? ያ ጊዜ እነሆ ዛሬ
ደረሰ›› ብሎ ነገራትና አባ ይስሐቅ የሚባል መነኩሴ ላከላትና
የእሷ ልጆች ሊሆኑ ከመጡ 600 መነኮሳት ጋር በሦስት ወር
ውስጥ የቅዱስ ሚካኤልን ቤተክርስቲያን ሠርታለች፡፡ ብዙ
ተከታይ መነኮሳትንም አፍርታለች፡፡ በዚህችም ጓንጉት ደሴት
ቆማ ስትጸልይ እንደሁልጊዜው ጌታችን ተገልጦላት ሳለ
‹‹አዳምንና በአርአያህና በአምሳልህ ለምን ፈጠርከው?
በእንጨት መስቀልስ ላይ ለምን ተሰቀልክ? ስለ አዳምና ስለ
ልጆቹ አይደለምን?›› አለቸው፡፡ ጌታችንም ‹‹አዎ ስለ አዳምና
ልጆቹ ስል ነው የተሰቀልሁት›› አላት፡፡ እርሷም ‹‹እንግዲያውስ
መሰቀልህ ስለ እነርሱ ከሆነ ከአቤል ጀምሮ እስከዛሬ የሞቱትን
ከዛሬም በኋላ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የሚሞቱትን
ማራቸው፣ ይቅርም በላቸው›› አለችው፡፡ ጌታችንም ‹‹ወዳጄ
ክርስቶስ ሠምራ ሆይ! እስቲ አንቺ ራስሽ ፈረጂ›› በማለት
በጲላጦስ ዘመን አይሁድ ያደረሱበትን እጅግ አሠቃቂ
መከራዎችና የሞቱን ሁኔታ ሁሉ በዝርዝር ከነገራት በኋላ
‹‹እንግዲህ ይህን ውለታ ዘንግተው ከክፋት የማይመለሱትን፣
ለተንኮል የማያርፉትን ልምራቸው ወይስ ልኮንናቸው ይገባል?
እስቲ ፍረጂ›› አላት፡፡ እንደልብ ጓደኛም ብዙ ከተወያዩ በኋላ
መጨረሻ ላይ ቅድስት እናታችን ‹‹አቤቱ ፈጣሪዬ ፈቃድህስ
ቢሆን የአዳም ልጆች ከሥቃይ ከኩነኔ ይድኑ ዘንድ ዲያብሎስን
ይቅር ትለውና ትምረው ዘንድ እለምንሃለሁ፣ የኃጥእን
መመለሱን እንጂ ጥፋቱን አትወድምና፡፡ የምለምንህ ወድጄው
አይደለም ነገር ግን እርሱ ከተማረ በአዳም ልጆች ላይ ሥቃይና
ኩነኔ ሊኖር አይችልም ብዬ በመገመት ነው እንጂ›› አለችው፡፡
ይህንንም ባለችው ጊዜ ጌታችን በጥያቄዋ ተገርሞ ‹‹ሌሎች
ካንቺ በፊት የነበሩ ካንቺም በኋላ የሚነሡ የማያስቡትን እጅግ
የሚያስደንቅ ልመና ለመንሽኝ›› ብሎ ካደነቃት በኋላ ቅዱስ
ሚካኤልን ጠርቶ ‹‹ሳጥናኤል እሺ ካላት ታወጣው ዘንድ ወደ
ሲኦል ይዘሃት ሂድ›› ብሎ አዞታል፡፡ በእዚያም እንደደረሰች
ለዲያቢሎስ ልታስታርቀው እንደመጣች ነገረችው፣ እርሱ ግን
እንኳን ሊመለስላት ይቅርና እርሷንም እጇን ይዞ ወደ ሲኦል
ወረወራት፡፡ በዚህ ጊዜ ይጠብቃት የነበረው መልአክ በእሳት
ሰይፉ ዲያብሎስን በመቅጣት እርሷን መዞ ሲያወጣት በዚህ ጊዜ
በቅዱስ ሚካኤልና በእርሷም ክንፍ ተጣብቀው ዐሥር ሺህ
ነፍሳት ሊወጡ ችለዋል፡፡ ይኸውም የሆነው በዚህች በዛሬይቱ
ዕለት ግንቦት 12 ቀን ነው፡፡ እርሷም በዚህ እጅግ ተደስታ ወደ
ፈጣሪዋ ሄዳ ‹‹አቤቱ ፍርድህ የቀና ምሕረትህ የበዛ ነው››
እያለች ለጌትነቱ ክብር ሰግዳለች፡፡ የእናታችን የቅድስት
ክርስቶስ ሠምራ ረድኤት በረከቷ ይደርብን፣ በጸሎቷ ይማረን፡፡
+ + + + + + + + + + + + + + +
የኢትዮጵያ ብርሃኗ ሐዲስ ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
ፍልሠተ ዐፅማቸው ስለመከናወኑ፡- አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከብዙ
ሐዋርያዊ አገልግሎታቸው በኋላ ተዘዋውረው ወንጌልን
ለመስበክ የማይችሉት ዕድሜ ላይ ደረሱ፡፡ በዚህም ጊዜ
‹‹ለሌሎች አበራሁ ለራሴ ግን ጨለምኩ፣ ዓለም አጣፈጥሁ እኔ
ግን አልጫ ሆንኩ…›› ብለው በዓት አጽንተው ከቆሙ
ሳይቀመጡ፣ ከዘረጉ ሳያጥፉ ለ7 ዓመት ቆመው ጸለዩ፡፡
ከ1267-1289 ዓ.ም ባለው ጊዜ ደግሞ በደብረ ሊባኖስ
ካለችው ገዳመ አስቦ ዋሻ በመግባት 8 ጦሮችን ተክለው
እጆቻቸውን በትእምርተ መስቀል በመዘርጋት የክርስቶስን
ሕማምና ሞት፣ ነገረ መስቀልን በማሰብ በተመስጦ ሌትና ቀን
ያለማቋረጥ በጾምና በጸሎት በአርምሞ ተወስነው ሲጋደሉ
ከቁመት ብዛት የተነሣ ጥር 4 ቀን 1289 ዓ.ም. አንዲቱ
የእግራቸው አገዳ ተሰብራለች፡፡ ቅዱስ አባታችን በመዓልትና
በሌሊት በትጋትና በቁመት በተጋድሎ ብዛት አንዲት የአገዳ
እግራቸው ስትሰበር ዕድሜያቸው 92 ዓመት ሆኗቸው ነበር፡፡
ከ1289-1296 ዓ.ም ለሰባት ዓመታት በአንድ እግራቸው
በመቆም ያለምግብና ያለውኃ በትኅርምት ሌትና ቀን እንቅልፍ
በማጣት እንደ ምሰሶ ጸንተው፤ በተመስጦ በትጋት ለሰው ዘር
ሁሉ ድኅነትን ሲለምኑ ኖረዋል፡፡ ከሰባቱ ዓመታት ውስጥ ጥቂት
ውኃ የቀመሱት በአራተኛው ዓመት ብቻ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ
ውስጥ ጌታችን ተገልጦላቸው በሰው አእምሮ ሊታሰብና ሊለካ
የማይችል ትልቅና ልዩ የመንግሥት አዳራሽ ከሰጣቸው በኋላ
የመለኮትን ነገር የሚናገር የእሳት አንደበት ያላቸው
የመንግሥት ልብስ አለበሳቸው፡፡ በመስቀል ምልክት የተጌጡት
ሰባት የሕይወት አክሊላትን አቀዳጅቷቸዋል፡፡ ይኸውም ‹‹ስለ
ቀናች ሃይማኖትህ፣ ሃይማኖትን ለማስተማር መላዋን
ኢትዮጵያን ስለመዞርህ፣ ከአረማውያን ሕዝብ ጋር በሃይማኖት
ስትታገል ደምህን ስለማፍሰስህ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ወርደህ ልዩ
ልዩ የቅዱሳን ቦታዎች ስለመሳለምህ፣ በሰባት ዓመታት ቊመት
የአንዱ አገዳ እግርህ ስለመሰበሩ፣ ስለብዙ ጾም ጸሎት
ስግደትህ፣ ስለልብህ ንጽሕናና ቅድስና›› በማለት የሕይወት
አክሊላትን ካቀዳጃቸው በኋላ ዝክራቸውን በማዘከር
መታሰቢያቸውን የሚያደርጉ ሁሉ በዚህ ዓለምም ሆነ
በወዲያኛው ዓለም ፍጹም ዋጋና ፍጹም ክብር እንደሚሰጣቸው
ጌታችን ታላቅ ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡ ሥጋቸውም ወዴት
ይቀበር ዘንድ እንዳላቸው ሲነግራቸው ‹‹እስከ 57 ዓመት
ሥጋህ ከዚህ ይቀበራል፤ ከ57 ዓመት በኋላ ግን ይህች ዋሻ
ትናዳላች፤ በዚህም ገዳም አደባባይ በስምህ ታላቅ ቤተ
ክርስቲያን ልጆችህ ሠርተው ሥጋህን አፍልሰው በውስጡ
ያኖራሉ›› አላቸው፡፡
ቅዱስ አባታችን በሞት ከማረፋቸው በፊት አስቀድሞ ጌታችን
እንደነገራቸው ሥጋቸው ከነፍሳቸው ከተለየች ከ57 ዓመት በኋላ
የካቲት 19 በጸሎት ላይ ለነበሩት ለአቡነ ሕዝቅያስ
ተገልጠውላቸው ‹‹ጌታ የገባልኝ ቃል ይፈጸም ዘንድ ሥጋዬ
የሚፈልስበት ደረሰ፣ ቀኒቱንም በምስጋናና በጸሎት መንፈሳዊ
በዓል አድርጉ፤ እኔ ኃጥኡ በሞትኩበት ቀን እንደነበረው ምስጋና
አቅርቡ፡፡ ሄደህ ለ12 መምህራንና ለልጆቼ ግንቦት 12
እንዲያከብሩ ንገራቸው፡፡ በፍልሰቴ ቀን አባቴ አባቴ የሚለኝ
ሁሉ ይምጣ ያኔ እኔ ወዳጄ ሚካኤልና ልጄ ፊልጶስ አብረን
መጥተን እንባርካለን፡፡ ምልክት ይሆንህም ዘንድ በምመጣበት
ጊዜ የጠፋው የመቅረዙ መብራት ይበራል›› አሉት፡፡ ከዚህም
በኋላ አቡነ ሕዝቅያስ በአባታችን ተባርከው ሄደው በአራቱም
አቅጣጫ ላሉት 12 መምህራንና ለክርስትያኖች ሁሉ አባታችን
የነገሩትን የፍልሰታቸው በዓል ስለማድረግ ወደ ፍልሰቱ በዓል
ያልመጣም በዚያች ቀን (በሰማይ ለምልጃ) አባቴ እንዳይለው
እርሱም ልጄ እንዳይለው ጨምሮ መልእክቱን ላከላቸው፡፡
እነርሱም ከያሉበት ተሰብስበው መጥተው የቅዱስ አባታችንን
ሥጋቸውን አውጥተው ወደ ቤተ ክርስቲያን አፍልሰው 3 ጊዜ
መቅደሱን አዙረው በዓሉንም አባታችን እንዳሉት በዝማሬና
በምስጋና አክብረው ወደ ውስጥ አስገቡት፡፡ በዚህም ጊዜ ብፁዕ
አባታችን ተክለ ሃይማኖት አስቀድመው እንደተናገሩት ጠፍቶ
የነበረው መብራት ቦግ ብሎ በራ፡፡ ከቅዱስ ሚካኤልና
ከልጃቸው ከአቡነ ፊልጶስ ጋር በመሆንም በዓሉን ያከብር
የነበረውን የተክለ ሃይማኖት የጸጋ ልጆቻቸውን ሁሉም ይባርኩ
ነበር፡፡ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ረድኤት በረከታቸው ይደርብን
በጸሎታቸው ይማረን፡፡