ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

Friday, March 25, 2016

ሊቀ_ዲያቆናት_ቅ ዱስ_እስጢፋኖስ #መታሰቢያ

#እንኳን_ሊቀ_ዲያቆናት_ቅ ዱስ_እስጢፋኖስ #መታሰቢያ
ወርሃዊ በአል አደረሳችሁ አሜን
#እስጢፋኖስ፦የስሙ ትርጉም - በግሪክ ቋንቋ አክሊል ማለት
ነው፡፡ በግብሩ የቀን ሃሩር የሌሊት ቁር የማይለውጠው፣
መብራት ማለት ነው፡፡
አባቱ ስምኦን፣ እናቱ ሃና ይባላሉ፡፡
የተወለደው - ጥር 1 ቀን በእስራኤል ሃገር ውስጥ በብፅዓት /
በስለት/ ነው፡፡ ልዩ ስሟ ሐኖስ በተባለ ቦት ተወለደ
ከመጥምቁ ዮሐንስ እግር ሥር በመሆን ተምሯል፡፡
ጥቅምት 17 ቀን ሐዋርያት ሊቀ-ዲያቆናት አድርገው
ሾሙት፡፡
ወንጌልን በማስተማሩ አይሁድ በጠላልትነት ተነስተውበት
ጥር 1 ቀን በ34 ዓ.ም. በድንጋይ ተወግሮ በስማዕትነት
አረፈ፡፡ በዚህም ቀዳሚ-ሰማዕት ተሰኘ፡፡
ለአህዛብ ተአምራትን ያደርጉላቸው የነበረው ለምንድነው?
አህዛብ ያልተማሩ ስለነበሩ ልቡናቸውን ለመስበርና
የእግዚአብሔርን ኃይልነት ተረድተው እንዲገነዘቡ በማሰብ
ተአምራትን ያደርጉ ነበር፡፡
ቅዱስ እስጢፋኖስ በአህዛብ ፊት ያደረገው ተአምራት
ሊቀዲያቆናት ቅዱስ እስጢፋኖስ በአህዛብ መካከል ቆሞ
ሲያስተምር ከቆየ በኋላ አንድ አንደበቱ ዲዳ የሆነ ሰው
አጠገቡ ቢመጣ በጆሮው የህይወት እስትንፋስ እፍ ቢልበት
መስማት የማይችለው መስማት ቻለ፡፡ በዚህም ጣኦት
አምላኪውን ናኦስ እና ተከታዮቹ ሁሉ ወደ ቅዱስ እስጢፋኖስ
ተመለሱ፡፡
ጣኦት አምላኪው ናኦስ በድርጊቱ በጣም በመናደዱ የተነሣ
በአጠገቡ የቆመውን በሬ ልክ ናኦስ በጆሮው ቢተነፍስበት
በሬው በምትሃት ለሁለት ተሰንጥቆ በመሞቱ ወደ ቅዱስ
እስጢፋኖስ የተመለሱት በናኦስ ምትሃታዊ ድርጊት
በመሣባቸው እንደገና ወደ ናኦስ ተመለሱ፡፡
የአህዛብ ልቡና ወላዋይ እንዳይሆንና እንዳይጠፉም በማሰብ
ናኦስ ለሁለት ሰንጥቆ የገደለውን በሬ በእግዚአብሔር ኃይልና
ድንቅ ሥራ ደግሞ ህይወት ዘርቶ ማስነሳት እንደማይችሉ
በማስተማር ልቦናቸው ወላውሎ ወደ ናኦስ የተመለሱትን
አህዛብ ገንዘቡ እንዲሆኑ በእግዚአብሔር ኃይልነት እንዲያምኑ
አድርጓል፡፡
ናኦስ በአልሸነፍ ባይነትና በአጋንንት ረዳትነት ራሱን ወደ ላይ
እንዲንሣፈፍ አድርጎ በአየር ላይ ቢወጣ ቅዱስ እስጢፋኖስ
የእግዚአብሔርን ተአምር በማሳየት በትዕግስት ጠብቆ
በአጋንንት ረዳትነት ወደ ላይ የተነሳውን ናኦስ በትምዕርተ-
መስቀል ቢያማትብበት ይዘውት የነበሩት አጋንንት ሁሉ
ለቀውት ሲበተኑ ናኦስም ምድር ደርሶ ተንኮታኩቶ በመውደቁ
በጣኦት አምላኪነት የነበሩ ሁሉ ዳግም ወደ ቅዱስ እስጢፋኖስ
ተመልሰዋል፡፡
ቅዱስ እስጢፋኖስ አይሁድን መጀመሪያ ካስተማራቸው በኋላ
የዘለፋቸው ስለምንድነው
መጀመሪያ በዘለፋ ቢጀምር ይወግሩትና ይገድሉት ስለነበር
ምስጢሩን ይገልፅ ዘንድ ነው/ይህን የመሰለ ትምህርት
ባላስቀረልን ነበርና ነው/
አንድም ሰውን ከመዝለፍ በፊት መምከር ማስተማር
ይገባልና ነው
አንድም ከወደዱት ትምህርቱን ይቀበሉታልና ነው፡፡
***የአይሁድ ክስ ምክንያት***
የሙሴን ህግ በመሻር ኦሪት አትጠቅምም አትመግብም
አታድንም ሐዲስ ኪዳን/ወንጌል/ ግን ትመግባለች ታድናለች
በማለቱ፡፡ /የሐ.ሥራ. 6፤13-14/
እግዚአብሔርንም ይዘልፋል /ይሰድባል/ በማለት ነው፡፡
የሐ.ሥራ. 7፤50
አይሁድ እነዚህን ንግግሮች በእግዚአብሔር ላይ እንደተሰነዘሩ
ስድቦች በመቁጠር ነበር የወነጀሉት፡፡
የኦሪት የካህናት አለቃ እስጢፋኖስ ለተከሰሰበት መልስ ይሰጥ
ዘንድ ቢጠይቀው ... ለተከሰሰበት መልስ ከመስጠት ይልቅ
ከአብርሃም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ድረስ ያለውን የመጽሐፍ
ቅዱስ ጽሁፍ በሚገባ ተረከላቸው፡፡ በመጨረሻም
የተገለጠለትን ምሥጢር ‹‹... እነሆ ሰማያት ተከፍተው የሰው
ልጅ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ ተቀምጦ አያለሁ ...›› በማለቱ
ላለመስማት በታላቅ ጩኸት በመቃወም ከከተማ ውጪ
በማውጣት በድንጋይ ወገሩት፡፡
ቅዱስ እስጢፋኖስ በእርሱ ላይ እጃቸውን ላነሱበት ሁሉ ጸሎተ
ምህረት አድርሷል የሚያደርጉትን አያውቁትምና ይህንን
ከኃጢአት አትቁጠርባቸው ሲል ነፍሱንም ለአምላክ አሳልፎ
በመስጠት በተወለደበት ዕለት ጥር 1 ቀን በ34 ዓ.ም.
በሰማዕትነት አልፏል፡፡ ይህም የመጀመሪያው /ቀዳሚ/
ሰማዕት አሰኝቶታል፡፡
ከአብርሃም መጀመሩ ነገረ ልደት/ግዝረት የተከናወነው/
የተጀመረው ከእርሱ ጀምሮ ነው፡፡
***የክርስቶስ አብነት የሆነበት ዓበይት ነጥቦች***
ጌታ ነፍሴን ተቀበላት እንዳለ ሁሉ እስጢፋኖስም አቤቱ ጌታ
ሆይ ነፍሴን ተቀበላት ብሏል፡፡
ጌታ አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው
እንዳለ እስጢፋኖስም ጌታ ሆይ ይህን ኃጥአት አትቁጠርባቸው
ሲል ጸልዮዋል፡፡
በጌታ ጸሎት ፊያታዊ ዘየማን ወደ ንስሐ በመምራት ገነት
መንግስተ ሰማያትን ወርሷል
የክርስቶስ መስቀል ሙት ያስነሣ ድውይ ይፈውስ እንደነበር
ሁሉ የቅዱስ እስጢፋኖስ አፅም ሙት ያስነሣ ድውይ ይፈውስ
ነበር፡፡
ቅዱስ እስጢፋኖስ የተወገረበት ድንጋይ ሰባት አብያተ
ክርስቲያናት ታንፆበታል፡፡ /ሰባት ቤተክርስቲያናትን አንጿል፡፡/
የቅዱሳን ሕይወት አብነታችን እንዲሆነን ታሪካቸውን
ተጋድሎዋቸውን ለእግዚአብሔር ያላቸውን ቅንአት መማር
ማወቅ ይገባናል
ኤዎስጣቲዮስ የሚባል ሊቅ-በቅዱስ እስጢፋኖስ ጸሎት
የጠፋውን ልጅ ሳኦል /ጳውሎስን/ ቤተክርስቲያን አስገኝታለች
ሲል ተናግሯል፡፡
ቅዱስ እስጢፋኖስ የተቀዳጀው ሦስቱ አክሊላት፡-
ስለንፅህናው ስለድንግልናው
ስለሰማዕትነቱ /ስለምስክሩ/ ስለተጋድሎው
ስለስብከቱ /ስለትምህርቱ/ ስለተአምራቱ
የቅዱስ እስጢፋኖስ ሁለቱ ስሞች፡-
ሊቀ ዲያቆናት ቅዱስ እስጢፋኖስ
ሐዋርያት በሰባቱ ዲያቆናት ላይ አለቃ አድርገው በሾሙት ጊዜ
የተሰጠው ስያሜ ነው፡፡
ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ
ከጌታ ቀጥሎ ከምእመናን የመከራውን ገፈት ከተቀበለ /
ሰማዕትነትን ከተቀበለ/ በኋላ የተሰጠው ስያሜ ነው፡፡
የቀዳሚ ሰማዕት የቅዱስ እስጢፋኖስ አፅሙ ሙትን ያስነሣ
ድውይን ይፈውስ ነበርና አይሁድ እንደ ክርስቶስ መከራ
መስቀል የቅዱስ እስጢፋኖስ አፅሙ አርቀው በመቆፈር
ቀብረው በላዩም ቆሻሻ በመጣል ለ300 ዓመት ያህል
ተቀብሮ እንደ ክርስቶስ መስቀል ተቆፍሮ በመውጣት
መስከረም 15 ቀን አፅሙ ወጥቶ በክብር በስሙ የታነፀው
ቤተክርስቲያን አርፏል፡፡
በቀዳሚ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ ሞት ምክንያት ማኀበረ-
እስጢፋኖስ በመበተኑ ለአህዛብም ወንጌል መስበክ ተጀመረ፡፡
ወንድሞች መባላቸው ቀረና ክርስቲያን ተባሉ፡፡
የቤተክርስቲያን አባቶች የቀዳሜ ሰማዕት የቅዱስ እስጢፋኖስ
ሞት ለክርስትና እምነት መስፋፋት ዋነኛ ምክንያት መሆኑ
የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራውን እንድናይበት አድርጎናል ሲሉ
ይገልፁታል እውነት ነውና፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር።
#ረድኤት_በረከቱ_ይድርብን _አሜን!!

No comments:

Post a Comment