ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

Monday, May 2, 2016

+*" ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ሐዋርያዊ "*+

+*" ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ሐዋርያዊ "*+
=>ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያን
ዐይን ናቸው:: ጻድቁን መንካት የቤተ ክርስቲያንን ዐይኗን
መጠንቆል ነው::
+ተክለ ሃይማኖት እንደ ሊቃውንት ሊቅ: እንደ ሐዋርያት ሰባኬ
ወንጌል: እንደ ሰማዕታት ብዙ ግፍ የተቀበሉ: እንደ ጻድቃን
ትሩፋት የበዛላቸው: እንደ ደናግል ንጽሕናን ያዘወተሩ: እንደ
ባሕታውያን ግኁስ: እንደ መላዕክትም ባለ ክንፍ አባት ነበሩ::
ለዚሕ ነው ተክለ ሃይማኖትን የኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያን ዐይኔ
የምትላቸው::
*ልደት*
=>መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራልና ተክለ ሃይማኖትን
የወለዱት ደጋጉ: ጸጋ ዘአብ ካህኑና እግዚእ ኃረያ ናቸው:: እርሱ
በክህነቱ: እርሷ በደግነቷ: በምጽዋቷ ጸንተው ቢኖሩ
እግዚአብሔር ጣፋጭ ፍሬን ሰጥቷቸዋል::
+በዳሞቱ ገዢ በሞተለሚ አደጋ ቢደርስባቸው ቅዱስ ሚካኤል:
ጸጋ ዘአብን ከሞት: እግዚእ ኃረያን ከትድምርተ አረሚ
(ከአረማዊ ጋብቻ) አድኗቸዋል:: በሁዋላም የቅዱሱን መወለድ
አብስሯቸዋል::
+ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የጸነሱት መጋቢት 24 ቀን
በ1206 ዓ/ም ሲሆን የተወለዱት ደግሞ ታሕሳስ24 ቀን
በ1207 ዓ/ም ነው:: በተወለዱበት ቀንም ብዙ ተአምራት
ተገልጸዋል:: ቤታቸውም በበረከት ሞልቷል::
*ዕድገት*
=>የጻድቁ የመጀመሪያ ስማቸው "ፍሥሃ ጽዮን" ይሰኛል::
ይሕንን ስም ይዘው: አባታቸው ጸጋ ዘአብን ተከትለው
አድገዋል:: በተለይ ቅዱሳት መጻሕፍትን (ብሉያት: ሐዲሳትን)
ተምረዋል:: በሥጋዊው ጐዳናም ብርቱ አዳኝ እንደ ነበሩ
ይነገራል:: ዲቁናም ከወቅቱ ዻዻስ አባ ጌርሎስ ተቀብለዋል::
*" መጠራት "*
=>አንድ ቀን ፍሥሃ ጽዮን ለአደን ወጥቶ ሲያነጣጥር ድንገት
ከሰማይ አስደንጋጭ ድምጽ ተሰማ:: የክብር ባለቤት ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ አእላፍ መላእክት እያመሰገኑ በሚካኤል ክንፍ
ተቀምጦ ወረደ::
+የወጣቱን አዳኝ ፍርሃቱን አርቆ ጌታችን ተናገረ:: "ከዛሬ
ጀምሮ ስምህ ተክለ ሃይማኖት (ተክለ ሥላሴ) ይሁን:: ከዚህ
በሁዋላ አራዊትን ሳይሆን ነፍሳትን ታድናለህ:: ዘወትር ካንተ
ጋር ነኝ" ብሎ በግርማ ዐረገ:: ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዚህ
ጊዜ በሁዋላ ሰዓትን አላጠፉም:: ንብረታቸውን ለነዳያን በትነው
በትር ብቻ ይዘው ቤታቸው እንደ ተከፈተ ወደ ምናኔ ወጡ::
*" አገልግሎት "*
=>ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዻዻሱ ቅስና ተቀብለው የወንጌል
አገልግሎትን ጀመሩ:: በመጀመሪያ ስብከታቸው እዚያው ሽዋ
(ጽላልሽ) አካባቢ ብቻ በ10ሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳምነው
አጠመቁ:: ያን ጊዜ ኢትዮዽያ 2 መልክ ነበራት::
+1ኛ ዮዲት (ጉዲት) በፈጠረችው ጣጣና በእስላሞች ተጽዕኖ
ወደ ደቡብ አካባቢ ያለው ነዋሪ አንድም ሃይማኖቱን ክዷል:
ወይም በባዕድ አምልኮ ተጠምዷል::
+2ኛው ደግሞ በዛግዌ ነገሥታት ጥረት ክርስትናና ምናኔ
ተነቃቅቶ ነበር::
+ግማሹ ሃገር በጨለመበት ወቅት የደረሱት ሐዲስ ሐዋርያ
አባ ተክለ ሃይማኖት በወጣት ጉልበታቸውና በኃይለ መንፈስ
ቅዱስ ብዙ ቦታዎችን አደረሱ:: ሕዝቡን: መሣፍንቱን ወደ
ሃይማኖት መልሰው: ማርያኖችን (ጠንቁዋዮችን)
አጥፍተዋል::
*" ገዳማዊ ሕይወት "*
=>ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት በወንጌል ብርሃን ኢትዮዽያን
ከማብራታቸው ባለፈ ገዳማዊ ሕይወትንም አስፋፍተዋል::
እርሳቸው ከሁሉ የተሻሉ ሳሉም በ3 ገዳማት በረድዕነት
አገልግለዋል::
+እነዚህም በአቡነ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም ለ12 ዓመታት:
በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ ገዳም ለ7 ዓመታት: በደብረ ዳሞ
ከአቡነ ዮሐኒ ጋር ለ7 ዓመታት: በአጠቃላይ ለ26 ዓመታት
አገልግለዋል::
+በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ከመነኮሱ በሁዋላም ወደ ምድረ ሽዋ
(ዞረሬ) ተመልሰው በአንዲት በዓት ውስጥ ለ22 ዓመታት
ቆመው ጸልየዋል:: በተሰበረ እግራቸውም 6 ጦሮችን በግራና
በቀኝ ተክለው ለ7 ዓመታት ጸልየዋል::
*ስድስት ክንፍ*
=>ኢትዮዽያዊው ጻድቅና ሐዋርያ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት
ከኢትዮዽያ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው ከቅዱሳት መካናት
ተባርከዋል:: ጻድቁ ምድረ እሥራኤል የገቡት በየመንገዱ
መንፈሳዊ ዘርን እየዘሩ: እያስተማሩና እያሳመኑ ነበር::
+የወቅቱ ሊቀ ዻዻሳት አባ ሚካኤል ጋርም ተገናኝተው
ቡራኬን ተሰጣጥተዋል:: ዋናው ጉዳይ ግን ከዚህ በሁዋላ ነው::
ጻድቁ እመቤታችንና ጌታችን ከጽንሰታቸው እስከ ዕርገታቸው
የረገጧቸውን ቦታዎች ሲመለከቱ በፍጹም ተደሞ እንባቸው
ይፈስ ነበር::
+ምክንያቱም እግዚአብሔር ስላበቃቸው ተክለ ሃይማኖት
የሚያዩት ቦታውን አልነበረም:: በገሃድ:-
-በቤተ መቅደስ ብስራቱን
-በቤተ ልሔም ልደቱን
-በቤተ ዮሴፍ ግዝረቱን
-በፈለገ ዮርዳኖስ ጥምቀቱን
-በቤተ አልዓዛር ተአምራቱን ይመለከቱ ነበር::
+የጉብኝታቸው የመጨረሻ ክፍል ወደ ሆነው ቀራንዮ ደርሰው
ጌታቸውን እንደ ተሰቀለ ሆኖ ቢመለከቱት ከዓይናቸው ይፈስ
የነበረው ቁጡ እንባ መልኩን ቀየረና ዓይናቸው ጠፋ::
በዚያች ቅጽበት ስም አጠራሯ የከበረ እመቤታችን ድንግል
ማርያም ፈጥና ደርሳ ተክልየን ወደ ሰማይ አሳረገቻቸው::
+በዚያም:-
*የብርሃን ዐይን ተቀብለው
*6 ክንፍ አብቅለው
*የወርቅ ካባ ላንቃ ለብሰው
*ማዕጠንተ ወርቁን ይዘው
*ከ24ቱ ካህናተ ሰማይም ተደምረው
*ሥላሴን በአንድነቱና ሦስትነቱ ተመልክተው
*"ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ ይደሉ" ብለው መንበረ
ጸባኦትን አጥነው ወደ መሬት ተመልሰዋል::
*ተአምራት*
=>የተክልየ ተአምራት እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ነው::
*ሙት አንስተዋል
*ድውያንን ፈውሰዋል
*አጋንንትን አሳደዋል
*እሳትን ጨብጠዋል
*በክንፍ በረዋል
*ደመናን ዙፋን አድርገዋል::
+ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው ደብረ ሊባኖስን
መሥርተዋል:: በዚያም ሴትና ወንድ መነኮሳት እንደ ሕጻናት
አብረው ኑረዋል:: በዘመናቸው ሰይጣን ታሥሯልና::
*ዕረፍት*
=>ጻድቅ: ሰማዕትና ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ብርሃን
ሆነው መከራን በብዙ ተቀብለው: እልፍ አእላፍ ፍሬን
አፍርተው: በተወለዱ በ99 ዓመት: ከ8 ወር: ከ1 ቀናቸው
ነሐሴ 24 ቀን በ1306 ዓ/ም ዐርፈዋል:: ጌታ: ድንግል
ማርያምና ቅዱሳን ከሰማይ ወርደው ተቀብለዋቸዋል:: 10
ትውልድ የሚያስምር ቃል ኪዳንም ተቀብለዋል::
=>አምላከ ቅዱሳን ከጻድቁ አባታችን በረከትን ይክፈለን::
=>+"+ በረከት በጻድቅ ሰው ራስ ላይ ነው:: የኀጥአንን አፍ
ግን ግፍ ይከድነዋል:: የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው::
የኀጥአን ስም ግን ይጠፋል:: +"+ (ምሳሌ 10:6)
<ወስብሐት ለእግዚአብሔር>

No comments:

Post a Comment