ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

Friday, June 3, 2016

=>+*"+<+>††† ግንቦት_27_መድኃኔዓለም †††<+>+"*+

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
አሜን
#ግንቦት_27_መድኃኔዓለም _ክርስቶስ_ለመባዓ
#ጽዮን_ያደረገለት_ተአምር _ይኽ_ነው፡- ‹‹ተክለማርያም
የተባለ መባዓ ጽዮን የመድኃኔዓለምን በዓል ከሌላ ጋር
አይጨምርም ነበር፡፡ ለመድኃኔዓለም መታሰቢያ የሚሆነውን
ሁሉ ለብቻው ያስቀምጠዋል፡፡ በረሃብ እስኪሞት ድረስ
ከመድኃኔዓለም መታሰቢያ እህል ምንም አይቀምስም፡፡
ያዘጋጀውንም ኅብስትና ጽዋ ለሕዝቡ ይሰጣቸዋል፡፡ የታመሙ
ሰዎችም ለመድኃኔዓለም መታሰቢያ ከተዘጋጀው በበሉ ጊዜ
ከሕመማቸው ሁሉ ይድናሉ፡፡ አባታችን የሚያዘጋጀውን
የመድኃኔዓለምን መታሰቢያ ይበሉ ዘንድ እየተጨናነቁ
ከቅርብም ከሩቅም ሰዎች በእምነት ይመጡ ነበር፡፡ በየወሩ
በዓሉም በቀረበ ጊዜ በጾምና በጸሎት ሰባት ቀን ይማለላል፡፡
ሆዱን ሳያጠግብ ራሱን ሳያስተኛ በፍጹም ልቅሶ መከራውን
ያስባል፡፡ ምድርን እስኪያርስ ድረስ ከዓይኖቹ ዕንባውን
ያፈሳል፡፡ ከልቅሶውም ብዛት የተነሣ እስኪጠፋ ድረስ ዓይኖቹ
ታመሙ፡፡ እመቤታችን ማርያምም ብርሌ የሚመስል ጽዋን
በእጇ ይዛ መጣች፡፡ ‹ወዳጄ ተክለማርያም ሆይ! ስለ ልጄ
ፍቅር ለታመሙ ዓይኖችህ መድኃኒትን እሰጥህ ዘንድ እነሆ
መጣሁ› አለችውና ጣቶቿን ከዚያ ጽዋ ነክራ ዓይኖቹን ቀባችው፤
ከሕመሙም ዳነ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሕመም አላገኘውም፡፡
በተቀደሰች በዓርባ ጾምም የመድኃኔዓለምን ግርፋት እያሰበ
ሰውነቱን በእጅጉ ገረፈ፡፡ ደሙ ከመሬት እስኪወርድ ድረስ
ልቡንም አጥቶ ከምድር ላይ ወደቀ፡፡ የመድኃኔዓለምን
መከራውን አስቦ እንደሞተም ሆነ፡፡ መድኃኔዓለምም ወደ
እርሱ መጣና ‹ተነሥ እኔ ቁስልህን እፈውስሃለሁ› ብሎ
የጀርባውን ቁስል ዳሰሰው፡፡ ምንም ሕማም እንዳላገኘውም
ሆነ፡፡ መድኃኔዓለምም አባታችንን ‹በአንተው እጅ ትገደልን?
እኔ እንኳ የተገደልኩት በአመፀኞች በአይሁድ እጅ ነው› አለው፡፡
በዚያችም ሰዓት ጌታ የመባዓ ጽዮንን ከንፈሮቹን ይዞ አፉን
ከፍቶ ሦስት ጊዜ እፍ አለበት፡፡ ‹የከበረ ትንፋሼም ከትንፋስህ
ጋራ ይጨመር፣ ሥጋህም ከነፍስህ ጋራ የከበረ ይሁን› አለው፡፡
‹አንተ በላዩ እፍ ያልህበትም የተቀደሰና የከበረ ይሁን› አለው፡፡
ብፁዕ ተክለማርያምንም አይቶ ለሰው ፈጽሞ የሚያስደንቅ
ነገርን ነገረው፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያምም ስለ ልጇ ስለ
ፍቅሩ ገናንነትም ተደሰተች፡፡ መድኃኔዓለምም አባታችንን ‹ስለ
ሕማሜ ታመሃልና ስለ ክቡር ደሜም ደምህን አፍሰሃልና ስለ
ሞቴም ሞተሃልና እንደወደድኸኝ እኔም እወድሃለሁ፣
ሁልጊዜም ከአንተ አልለይም፡፡ አንተን የወደደ እኔን ወደደ፣
አንተንም የጠላ እኔን ጠላ፣ የላከኝንም ጠላ፣ እኔን እንደጠሉኝ
እንደ አይሁድ ይሁን፡፡ ነፍስህ ከሥጋህ ተለይታ በምትወጣበት
ቀንም ለሌላ አልሰጣትም እኔ እቀበላታለሁ እንጂ› አለው፡፡
‹ወደ አንተ የደረሰ ሁሉ ወደ ቤተክርስቲያንህም የመጣ፣
በአንተም የተማፀነ፣ በእጅህም የተባረከውን ሁሉ
እምርልሃለሁ፡፡ በእኔና በእናቴ ማርያም ስም በማይታበል ቃሌ
ቃልኪዳን ሰጠሁህ፣ መሐላዬንም አላጎድልብህም› አለው፡፡
አባታችንም ይህን ሰምቶ ፈጽሞ ተደሰተ፡፡
‹‹በሌላም ጊዜ ዳግመኛ ጌታችን ደም ግባቱ ያማረ፣ ልብሱም
የመስቀል ምልክት የሆነ ንጹሕ አክሊል በራሱ የተቀዳጀ
ጎልማሳ ሆኖ በፊቱ ቆመ፡፡ ‹ልመናህን እፈጽምልህ ዘንድ እነሆ
ወደ አንተ መጣሁ› አለው፡፡ ‹…እንደ አንተ በዓሌን ያደረገውን
እምረዋለሁ፣ የብርሃን ልብስንም አለብሰዋለሁ…› ብሎ
ቃልኪዳን ከሰጠው በኋላ ሁለመናው በመለኮት ጨውነት
ይጣፍጥ ዘንድ አውራ ጣቱን አጠባው፡፡ ከዚህም በኋላ ከእርሱ
ተሰወረ፡፡ እንዲሁም በሌላ ጊዜ እንዲህ እያለ መለነ፡- ‹ጌታዬ
ፈጣሪዬ ሆይ! በዓልህን አድርግ አንድ አንተ የምትወደውን
ግለጥልኝ› አለ፡፡ ጌታም ‹የሞቴን መታሰቢያ ያደረገ እንደ እኔ
ነፍሳትን ከደይን ያወጣል፣ ‹በእኔ የሚያምን እኔ የምሠራውን
ይሠራል፣ ከዚያም የበለጠ ይሠራል› ብዬ በወንጌሌ
እንደተናገርሁ› አለው፡፡›› ‹‹ክርስቲያኖች ሁሉ የፈጣሪያችንን
የመድኃኔዓለም ክርስቶስን የመታሰቢያ በዓሉን እናድርግ፡፡
የአባቶቻችን የሐዋርያት፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣ የመላእክት
መታሰቢያቸው ባረፉበት በተሾሙበት ቀን ይከበራል፡፡ እነርሱን
የፈጠራቸው እርሱ መድኃኔዓለም ነው፣ ያከበራቸው፣ ከፍ ከፍ
ያደረጋቸው፣ ስማቸውን ለጠራ መታሰቢያቸውን ያደረገ
እንደሚድን ቃልኪዳን የሰጣቸው እርሱ ነው፡፡ የመድኃኔዓለምን
የሞቱን መታሰቢያ ያደረገ ግን የተኮነኑ ነፍሳትን ከደይን
ያወጣል፣ በሞቱም ጊዜ ሥቃይን አያያትመ፡፡›› ‹‹ጌታችንም
ለመባዓ ጽዮን እንዲህ አለው፡- ‹መታሰቢያዬንም እንደ አንተ
በየወሩ የሚያደርግ ሁሉ በዓርብ ቀን ብዙ ነፍሳትን ከሲኦል
አወጣለታለሁ፡፡ አንተ ከምታደርገው ከሞቴ መታሰቢያም
ቁራሽ የበላውን፣ ከሩቅም ወሬህን ሰምቶ በልቡ ደስ ያለውና
የወደደውን ከሞቴ መታሰቢያ መድረስ ባይቻለውም እንኳ
እምረዋለሁ፡፡› መባዓ ጽዮንም ስለተሰጠው የምሕረት
ቃልኪዳን እጅግ ደስ ብሎት እንዲህ አለ፡- ‹ያለቸርነቱ በቀር በጎ
ሥራ ለሌለኝ ለእኔ ለኃጢአተኛው ይኽን ሁሉ ስላደረገልኝ
ለእግዚአብሔር ምን እከፍለዋለሁ?› አለ፡፡ ነገር ግን ስሙ
ለዘለዓለም የተባረከ ይሁን አሜን፡፡››
+ + + + + + + + + + + + + + +
ዳግመኛም በዚኽች ዕለት ከሞተ ከ4 ቀን በኋላ ጌታችን
ያስነሣው ቅዱስ አልዓዛር ዓመታዊ መታሰቢያ በዓሉ ነው፡፡
ይኸውም ቅዱስ አልዓዛር የባለ ሽቱዋ የማርያም እንተ
ዕፍረትና የማርታ ወንድም ሲሆን ጌታችን በጣም ይወደው
ስለነበር አልዓዛር መሞቱን ሲሰማ ከእኅቶቹ ጋር
አልቅሶለታል፡፡ ከሞተም ከ4 ቀን በኋላ ከመቃብር
አስተሥቶታል፡፡ ከጌታችን ዕርገት በኋላም አልዓዛርና እኅቶቹ
ቤታቸውን የወንጌል መማርያና የእንግዶች መቀበያ
አድርገውታል፡፡ እርሱ ከሞት በተነሣ በሳምንቱ ጌታችን
ተሰቅሎ በሥጋ ሞተ፡፡ ከትንሣኤውም በኋላ አልዓዛር
ከሐዋርያት ጋር ሆነ፡፡ በ50ኛውም ቀን ከሐዋርያት ጋር
መንፈስ ቅዱስን ተቀብሏል፡፡
አይሁድም ክርስቶስን ያመኑ ክርስቲያኖችን ሲያሳድዱ
አልዓዛርንና እኅቶቹን በቀዳዳ መርከብ ጭነው ወደ ባሕር
ጥለዋቸዋል፡፡ በተአምራት ከሞት ድነው የፈረንሳይ ግዛት
ወደሆነች አንዲት ከተማ ተሰደው በዚያ እየኖሩ የክርስቶስ
ምስክር ሆነዋል፡፡ ሐዋርያት በቆጵሮስ አገር ላይ በአንብሮተ
እጅ ኤጲስ ቆጶስነት ሾሙት፡፡ መንጋውንም በመልካም
አጠባበቅ እየጠበቀ በሹመቱ 40 ዓመት አገልግሏል፡፡
በከተማዋም የመጀመሪያው ጳጳስ በመሆን ወንጌልን እየሰበከ
ሲያገለግል ኖሮ መጋቢት 17 ቀን በሰማዕትነት ዐርፏል፡፡
ቅዱስ አልዓዛር በሰማዕትነት ካረፈ ከብዙ ዘመን በኋላ
ከክርስቲያን ነገሥታት መካከል አንዱ የቅዱስ አልዓዛር ሥጋው
በቆጵሮስ እንዳለ በሰማ ጊዜ ከቆጵሮስ ደሴት ወደ
ቁስጥንጥንያ አፈለሰው፡፡ ሊያፈልሱትም በወደዱ ጊዜ በከበረ
የድንጋይ ሣጥን ውስጥ ሆኖ በምድር ውስጥ ተቀብሮ አገኙት፡፡
በላዩም እንዲህ የሚል ጽሑፍ ነበረ፡- ‹‹ይህ በመቃብር ውስጥ
አራት ቀን ከኖረ በኋላ ከሙታን ለይቶ ላስነሣው ክብር
ይግባውና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወዳጁ የሆነ የቅዱስ
አልዓዛር ሥጋ ነው፡፡›› ይህንንም ጽሑፍ ባነበቡ ጊዜ ደስ
ተሰኝተው ተሸክመው ወደ ቁስጥንጥንያ አገር ወሰዱት፡፡
ካህናቱም ሁሉ በዝማሬ በክብር ተቀበሉት፡፡ ባማረ ቦታ
አስቀምጠውት ጥቅምት 21 ቀን የፍልሰቱን በዓል
አደረጉለት፡፡ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን፡፡
የመድኃኔዓለም ቸርነቱ የመባዓ ጽዮን አማላጅነቱ አይለየን!

No comments:

Post a Comment