ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

Friday, June 3, 2016

=>+*"+<+>††† ግንቦት 26 †††<+>+"*+

<<< በስመ አብ : ወወልድ : ወመንፈስ ቅዱስ : አሐዱ አምላክ . . . አሜን :: >>>
<+> ግንቦት 26 <+>
+*" አቡነ ሃብተ ማርያም ጻድቅ "*+
=>እኒህ ጻድቅ የሃገራችን ኮከበ ገዳም ናቸው:: "ጽድቅና
ትሩፋት እንደ ሃብተ ማርያም" እንዲሉ አበው:: ባሕር ከሆነ
ጣዕመ ሕይወታቸው ጥቂቱን ለበረከት እንካፈል::
+ጻድቁ መካነ ሙላዳቸው ሽዋ (የራውዕይ) ውስጥ ሲሆን
አባታቸው ፍሬ ቡሩክ : እናታቸው ደግሞ ቅድስት ዮስቴና
ትባላለች:: በተለይ ቅድስት ዮስቴና እጅግ ደመ ግቡ : ምጽዋትን
ወዳጅ : ቡርክት ሴት ነበረች:: እንዲያውም ከጻድቁ መወለድ
በፊት መንና ጭው ካለ በርሃ ገብታ ነበር::
+ግን የበቃ ግኁስ አግኝቷት "ከማሕጸንሽ ደግ የሥላሴ ባርያ
አለና ተመለሽ" ብሏት እንደ ገና ተመልሳለች:: ጻድቁን ወልዳ
አሳድጋም እንደ ገና መንና በተጋድሎ ኑራ 7 አክሊላትን ተቀብላ
ዐርፋለች::
+ወደ ጻድቁ ዜና ሕይወት ስንመለስ አቡነ ሃብተ ማርያም ገና
ሕጻን እያሉ ከእናታቸው ጋር ቆመው ሲያስቀድሱ "እግዚኦ
መሐረነ ክርስቶስ" ሲባል ይሰማሉ:: ይሕችን ጸሎት በሕጻን
አንደበታቸው ይዘው ሌሊት ሌሊት እየተነሱ "ማረን እባክህን?"
እያሉ ይሰግዱ ነበር::
+የ5 ዓመት ሕጻን እንዲህ ሲያደርግ ማየቱ በእውነት
ይደንቃል:: ትንሽ ከፍ ብለው በእረኝነት ሳሉም ፍጹም
ተሐራሚና ጸዋሚ ነበሩ:: ጸጋው ስለ በዛላቸውም ልጅ ሆነው
ብዙ ተአምራትን ሰርተዋል:: የፈጣሪውን ስም ያቃለውን አንድ
እረኛም በዓየር ላይ ሰቅለው አውለውታል::
+ከዚያ ግን ለአካለ መጠን ሲደርሱ ወደ ት/ቤት ገብተው :
መጻሕፍትንም አጥንተው መንነዋል:: በአባ መልከ ጼዴቅ እጅ
ከመነኮሱ በሁዋላ የሠሩትን ትሩፋትና የነበራቸውን ተጋድሎ ግን
የኔ ብጤ ደካማ ሰው ሊዘረዝረው አይችልም::
*ባሕር ውስጥ ሰጥመው 500 ጊዜ ይሰግዳሉ::
*በየቀኑ 4ቱን ወንጌልና 150 መዝሙረ ዳዊትን ይጸልያሉ::
(መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ታላቅ ጸሎት ነው)
*በ40 ቀናት : ቀጥሎም በ80 ቀን አንዴ ብቻ ይመገባሉ::
*ምግባቸው ደግሞ ሣርና ቅጠል ብቻ ነው::
*በየዕለቱ ያለ ማስታጐል ማዕጠንት ያሳርጋሉ:: (ካህን ናቸውና)
*ዘወትር በንጽሕና ቅዱስ ሥጋውን ይበላሉ : ክቡር ደሙን
ይጠጣሉ::
*በፍጹም በልባቸው ውስጥ ቂምን : መከፋትን አላሳደሩም::
+በእነዚህና በሌሎች ትሩፋቶቻቸው ደስ የተሰኘ ጌታም ለጻድቁ
የእሳትና የብርሃን ሠረገላን ሰጥቷቸው በዚያ እየበረሩ
ኢየሩሳሌም ይሔዱ ነበር:: ከብዙ የተጋድሎ ዘመናት በሁዋላም
የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ክርስቶስ አዕላፍ መላእክትን
አስከተትሎ መጥቶ አላቸው::
"1.ስለ እኔ ረሃብና ጥምን ስለ ታገስክ:
2.ስለ ምናኔሕ:
3.ስለ ተባረከ ምንኩስናህ:
4.ስለ ንጹሕ ድንግልናህ:
5.ቂምና በቀልን ስላለመያዝህ:
6.ስለ ንጹሕ ክህነትህና ማዕጠንትህ:
7.ቅዱስ ወንጌልን በፍቅር ስለ ማንበብህ 7 አክሊላትን
እሰጥሃለሁ::"
+"በሰማይም ከመጥምቁ ዮሐንስ ጐን : 500 የእንቁ
ምሰሶዎች ያሉበትን አዳራሽ ሰጥቼሃለሁ:: በስምህ የሚለምኑ :
በቃል ኪዳንህ የሚማጸኑትንም ሁሉ እንድምርልህ 'አማንየ!
በርእስየ!' ብዬሃለሁ" አላቸው::
+ቅዱሳን መላእክትም "ሃብተ ማርያም ወንድማችን" ሲሉ
አቀፏቸው:: ጌታ ግን በዚያች ሰዓት አንድም ሦስትም ሆኖ
ታያቸውና አቅፎ 3 ጊዜ ሳማቸው:: ከፍቅሩ ጽናትም የተነሳ
ነፍሳቸው ከሥጋቸው ተለየች:: በዝማሬም ወሰዷት:: {ይህች ቀን
(ግንቦት 26) ለጻድቁ ዕለተ ልደታቸው ናት::}
=>አምላከ አበው ወሰማዕት ጣዕመ ፍቅራቸውን:
ክብራቸውን: ጸጋ በረከታቸውንም ይክፈለን::
=>+"+ እግዚአብሔር ፍርድን ይወድዳልና::
ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና::
ለዘለዓለምም ይጠብቃቸዋል . . .
ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ::
በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ::
የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል::
አንደበቱም ፍርድን ይናገራል::
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው::
በእርምጃውም አይሰናከልም:: +"+ (መዝ. 36:28-31)
<ወስብሐት ለእግዚአብሔር>

No comments:

Post a Comment