ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

Tuesday, September 6, 2016

=>+*"+<+>††† ዻጉሜን-1 +" ወርኀ ዻጉሜን "+ †††<+>+"*

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ዻጉሜን-1
+" ወርኀ ዻጉሜን "+
=>#እግዚአብሔር አዝማናትን የፈጠራቸው ለሰው ልጆች
ጥቅም መሆኑ ይታወቃል:: እርሱ ባወቀ: በረቂቅ ሥልጣኑ
ዓለምን ፈጥሮ: ጊዜያትን እንዲከፍሉ ብርሃናትን (ፀሐይ:
ጨረቃ: ከዋክብትን) ፈጥሮልናል::
+ጊዜያትንም በደቂቃ: በሰዓት: በቀን: በሳምንት: በወር:
በዓመታት: በኢዮቤልዩ: በክፍላተ ዘመናት እንድንቆጥር
ያስማረንም እርሱ ነው:: የሰከንድ 540,000 ክፋይ
ከሆነችው 'ሳድሲት' እስከ ትልቁ ቀመር (532 ዓመት) ድረስ
እርሱ ለወደዳቸው እንዲያስተውሉት ገልጧል::
+በየዘመኑም በቅዱስ #ድሜጥሮስ: በቅዱስ #ዮሐንስ
ዘደማስቆ: በቅዱስ #አቡሻኽር እና በሌሎቹም አድሮ
መልካሙን አቆጣጠር አስተምሯል:: ሃገራችን ኢትዮዽያ
ደግሞ የ13 ወራት የፀሐይ ጸጋ (thirteen months sun
shine) ያላት: 4ቱ ወቅቶች የተስማሙላት ናት::
+ሌላው ዓለም ወሮችን 31,30,29 እያደረገ ሲጠቀም እኛ
ግን እንደ ኖኅ (ዘፍ) አቆጣጠር ወሮችን በ30 ቀናት ወስነን:
ዻጉሜንን ለብቻዋ እናስቀምጣለን:: ዻጉሜን 'ኤዻጉሚኖስ'
ከሚል የግሪክ (ጽርዕ) ቃል የተወሰደ ሲሆን ትርጉሙም
'ትርፍ: ጭማሪ' እንደ ማለት ነው::
+የወርኀ ዻጉሜን 5ቱ (6ቱ) ቀናትም ወደ አዲስ ዓመት
መሸጋገሪያ እንደ መሆናቸው ብዙ ምሳሌያት (ምሥጢራት)
አሏቸው:: ዋናው ግን በዚህ ጊዜ ዳግም ምጽዓት ይታሠባል::
ጊዜውንም በጾምና በጸሎት ሊያሳልፉት ይገባል:: ግን በፈቃድ
ነው እንጂ የግዴታ አይደለም::
+" ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ "+
*የቅዱሳኑ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ልጅ
*በማሕጸን ሳለ መንፈስ ቅዱስ የሞላበት
*በበርኀ ያደገና በገዳማዊ ቅድስና ያጌጠ
*እሥራኤልን ለንስሃ ያጠመቀ
*የጌታችንን መንገድ የጠረገ
*ጌታውን ያጠመቀና
*ስለ እውነት አንገቱን የተቆረጠ ታላቅ ሰው ነው::
*ስለዚሕም ቤተ ክርስቲያን ነቢይ: ሐዋርያ: ሰማዕት: ጻድቅ:
ገዳማዊ: መጥምቀ መለኮት: ጸያሔ ፍኖት: ቃለ ዐዋዲ ብላ
ታከብረዋለች::
+ቅዱሱ በዚህች ዕለት ወደ እሥር ቤት ገብቷል:: ይሕስ እንደ
ምን ነው ቢሉ:-
ንጉሡ ሔሮድስ የወንድሙን የፊልዾስን ሚስት ሔሮድያዳን
በማግባቱና በመሰል ክፋቶቹ ቅዱስ ዮሐንስ ይገስጸው ነበር::
ቅዱስ ዮሐንስ "መምሕር ወመገስጽ: ዘኢያደሉ ለገጽ - ፊት
አይቶ የማያዳላ" ነውና ገሰጸው::
+ሔሮድስ ቅዱሱን ይፈራው: ያከብረውም ነበር:: በኋላ ግን
ፈቃደ ሥጋው ስላየለበት: በተለይ ደግሞ ከ7 ቀናት በሁዋላ
ልደቱን ሲያከብር እንዳይረብሸው በመስጋት በዚህች ቀን
በወታደሮቹ አስይዞ እሥር ቤት ውስጥ ጥሎታል:: ለ7 ቀናት
በጨለማ ውስጥ አሥሮ መስከረም 2 ቀን አንገቱን እንዴት
እንዳስቆረጠው ዕለቱን ጠብቀን እንመለከታለንና የዚያ ሰው
ይበለን::
+" ቅዱስ ዑቲኮስ ሐዋርያ "+
=>ቅዱሱ ሐዋርያ ጭራሽ ከነ ስማቸው እንኩዋ እየተዘነጉ
ከሔዱ ሐዋርያት አንዱ ሲሆን ቁጥሩም ከ72ቱ አርድእት
ነው:: በወጣትነት ዘመኑ የጌታችን ደቀ መዝሙር መሆንን
መርጦ ለ3 ዓመታት ከ3 ወራት ምሥጢረ ወንጌልን ጠንቅቆ
ተምሯል::
+መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜም እንደ መጠኑ ተቀብሎ
ለአገልግሎት ወጥቷል:: በመጀመሪያ የወንጌላዊው ዮሐንስ
ተከታይ ሁኖ ብዙ ምሥጢራትን ተካፍሏል:: ቀጥሎም ቅዱስ
ዻውሎስን ተከትሎ ብዙ አሕጉራትን በስብከተ ወንጌል
አዳርሷል::
+በመጨረሻም በእስያ አካባቢ ለብቻው ተጉዞ: ብዙ ነፍሳትን
ማርኮ: ጣዖታትን አጥፍቷል:: ስለዚህ ፈንታም በእሳት:
በስለትና በግርፋት ብዙ መከራዎችን አሳልፏል:: በዚህች
ቀንም በበጐው እርግና (ሽምግልና) ዐርፏል::
+" ቅዱስ ብሶይ ቀሲስ "+
=>በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ካህናት አንዱ የነበረው አባ ብሶይ
ለአገልግሎት ወጥቶ ሲመለስ የቤተሰቦቹ ቤት ሰው
አልነበረበትም:: "የት ሔዱ?" ብሎ ቢጠይቅ "ወንድምህ አባ
ሖርና እናትህ ቅድስት ይድራ ወደ እስክንድርያ ሔደዋል::
በዚያም ስለ ክርስቶስ ፍቅር ተሰውተዋል" አሉት::
+በማግስቱ የኔ ብጤዎችን ጠርቶ ሃብቱን: ንብረቱን: ቤቱን
አካፈላቸው:: ለራሱ ግን አንዲት በትር እና 3 የዳቦ ቁራሾች
ይዞ ጉዞ ተነሳ:: ወደ እስክንድርያ እንደ ደረሰ አፈላልጐ
የቤተሰቦቹን መቃብር አገኘ:: ከፊታቸው ወድቆም የናፍቆት
ለቅሶን አለቀሰ::
+ወዲያውም እንዲህ አላቸው:- "ፈጥኜ ወደ እናንተ
ስለምመጣ ጠብቁኝ:: ደግሞም ጸልዩልኝ::" ከዚያ ተነስቶ
በመኮንኑ ፊት ስለ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት መሰከረ::
በዚህ ምክንያት ብዙ ተሰቃይቶ በዚህች ቀን ሰማዕት ሆኗል::
ከወገኖቹም ጋር ተቀብሯል::
=>አምላከ ቅዱሳን ተረፈ ዘመኑን ባርኮ ለአዲሱ ዘመን በቸር
ያድርሰን:: ከወዳጆቹም ጸጋ በረከትን ይክፈለን::
=>ዻጉሜን 1 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ (የታሠረበት)
2.ቅዱስ ዑቲኮስ ሐዋርያ (ከ72ቱ አርድእት)
3.ቅዱስ ብሶይ ቀሲስ (ሰማዕት)
4.አባ ዻኩሚስ / ባኹም (የ3,000 ቅዱሳን አባት)
5.አባ ሰራብዮን / ሰራፕዮን (የ10,000 ቅዱሳን አባት)
=>+"+ ጌታ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ሊናገር ጀመረ. . .
ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችሁአለሁ ከነቢይም
የሚበልጠውን. . . እውነት እላቹሃለሁ ከሴቶች ከተወለዱት
መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሳም. . .
ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናገሩ::
ልትቀበሉትስ ብትወዱ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይሕ ነው::
የሚሰማ ጀሮ ያለው ይስማ:: +"+ (ማቴ. 11:7-15)
<ወስብሐት ለእግዚአብሔር>

No comments:

Post a Comment