ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

Wednesday, February 22, 2017

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ:=>+*"+<+>††7ቱ ኪዳናት+*"+<+>††

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን
እንኩዋን ለእመቤታችን ቅድስት #ድንግል_ማርያም
ዓመታዊ "የኪዳን በዓል" በሰላም አደረሳችሁ +"+"+
+*" 7ቱ ኪዳናት "*+
=>"ተካየደ" ማለት "ተስማማ : ተማማለ" እንደ ማለት
ሲሆን "ኪዳን" በቁሙ "ውል : ስምምነት" እንደ ማለት
ነው:: ይኸውም እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር: ሰዎችም ከሰዎች
ጋር የሚያደርጉት ሊሆን ይችላል:: ልዩነቱ የእግዚአብሔር
ቃል ኪዳን ቅዱስና የማይለወጥ መሆኑ ነው::
+እግዚአብሔር አምላክ ከሥነ ፍጥረት ጀምሮ በየጊዜው
ከብዙ ወዳጆቹ ጋር ኪዳንን አድርጉዋል:: ቅድስት ቤተ
ክርስቲያንም እነዚህን ኪዳናት ጥቅልል አድርጋ 7 እንደ ሆኑ
ታስተምራለች:: ስለዚህም ዛሬ ፈጣሪ ቢረዳን እነዚሁን 7
ኪዳናት በጥቂቱ እንመለከታለን::
"ኪዳነ ተካየድኩ ምስለ ኅሩያንየ"
"ከመረጥኩዋቸው ጋር ቃል ኪዳንን አደረግሁ" (መዝ. 88:3)
1. +*" ኪዳነ አዳም "*+
=>አዳም ማለት የእግዚአብሔር ድንቅ ፍጥረት: የፍጡራን
አስተዳዳሪ: ነቢይ: ካህንና ንጉሥ ነው:: እግዚአብሔር ከአዳም
ጋር አስቀድሞ በእጸ በለስ አማካኝነት ቃል ኪዳን ነበራቸው::
ነገር ግን አባታችን በዲያብሎስ ሴራ በመረታቱ ኪዳኑ ፈረሰ::
(ዘፍ. 3:1)
+አዳምና ሔዋን ተጸጽተው ቢያለቅሱ ግን አዲስ የኪዳን
ተስፋ: "ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ" የሚል ኪዳንን
ተቀበሉ:: (ቀሌምንጦስ: ገላ. 4:4)
2. +*" ኪዳነ ኖኅ "*+
=>ከአዳም እስከ ኖኅ ድረስ ባሉት 10 ትውልድ ዓለም
በዓመፃ ተሞላች:: ቅዱስ ኖኅ በደግነቱ መርከብ ሠርቶ
ቤተሰቡን ሲያተርፍ ዓለም በማየ ሥራዌ ጠፋች:: ከመርከቡ
ከወጣ በሁዋላ ኖኅና እግዚአብሔር በቀስተ ደመና ምልክትነት
ቃል ኪዳን ተጋቡ:: "ኢያማስና ለምድር ዳግመ በማየ አይኅ"
እንዲል:: (ዘፍ. 9:12)
3. +*" ኪዳነ መልከ ጼዴቅ "*+
=>መልከ ጼዴቅ የእግዚአብሔር ካህኑ: የክርስቶስም
ምሳሌው የሆነ የሳሌም ንጉሥ ነው:: በ15 ዓመቱ መንኖ:
አጽመ አዳምን ይዞ: በቀራንዮ በሕብስትና በወይን ያስታኩት
ነበር::
+እግዚአብሔር ለመልከ ጼዴቅ: በሐዲስ ኪዳን ለምትሠራው
ክህነትና ምሥጢረ ቁርባን ምሳሌ አድርጐ በቃል ኪዳን
አትሞታል:: በዚህም ተሰውሮ ይኖራል እንጂ ሞትን እስካሁን
አልቀመሰም:: ይህም ካህኑ መልከ ጼዴቅ ከአብርሃም ጋር
በተገናኙበት ጊዜ ተገልጧል:: (ዘፍ. 14:17, ዕብ. 7:1)
4. +*" ኪዳነ አብርሃም "*+
=>ቅዱስ አብርሃም የሕዝብና የአሕዛብ አባት: ሥርወ
ሃይማኖት: የጽድቅም አበጋዝ ነው:: ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር
ሲል ከርስቱና ከወገኖቹ ተለይቶ በቅድስና ኑሯልና
እግዚአብሔር "በዘርሕ አሕዛብ ይባረካሉ" አለው:: (ዘፍ.
12:1) የቃል ኪዳን ምልክትም ይሆነው ዘንድ ግዝረትን
ሰጠው:: (ዘፍ. 17:1-14)
5. +*" ኪዳነ ሙሴ "*+
=>ቅዱስ ሙሴ የነቢያት አለቃ: የእሥራኤል እረኛ:
የእግዚአብሔር ሰው እና ፍጹም ትሑት (የዋህ) ሰው ነው::
በፈጣሪው ትዕዛዝ እሥራኤልን ከግብጽ ባርነት አውጥቶ ለ40
ዘመናት በበርሃ ሲመራቸው ከእግዚአብሔር የኪዳንን ጽላትና
አሠርቱን ትዕዛዛት ተቀብሏል:: (ዘጸ. 20:1, 31:18)
6. +*" ኪዳነ ዳዊት "*+
=>ቅዱስ ዳዊት ሥርወ ነገሥት: ጻድቅ: የዋህና ቡሩክ የሆነ
አባት ነው:: እግዚአብሔር ከእረኝነት ጠርቶ ንጉሥ አድርጐ
ሹሞት "ከሆድህ ፍሬ በዙፋንህ ላይ አኖራለሁ" (መዝ.
131:11) ሲል ምሎለታል:: አክሎም ሰፊ ቃል ኪዳን ሰጥቶ
"አልዋሽህም" ብሎ ሲምልለት እንመለከታለን:: (መዝ.
88:35)
7. +*"+ ኪዳነ ምሕረት +"*+
=>በብሉይ ኪዳን የነበሩ 6ቱ ኪዳናት በዘመናቸው ክቡርና
ሕዝቡን ከመቅሰፍት ይታደጉ የነበሩ ቢሆንም ከሲዖል ማዳን
ግን አልቻሉም:: ስለዚህም አንድ ፍጹም ኪዳን ያስፈልግ
ነበር:: ይህን ፍጹም ኪዳን ይፈጽም ዘንድም ከቅድስት ሥላሴ
አንዱ ወልድ ከሰማያት ወርዶ በድንግል ማርያም ማሕጸን
አደረ::
+በፍጹም ተዋሕዶም በሕቱም ድንግልና ተወልዶ: አድጎ:
ተጠምቆ: አስተምሮ: ሙቶ: ተነስቶና ዐርጐ ሥጋ ማርያምን
በዘባነ ኪሩብ አስቀመጠው:: ኪዳነ ምሕረት (የምሕረት
ኪዳን) የምንለው አንዱ ታዲያ ይሔው ነው::
+የጌታችን መጸነሱ: መወለዱ: መሰደዱ: መጠመቁ:
ማስተማሩ: ሥጋውንና ደሙን መስጠቱ: መሰቀሉ: መሞቱና
መነሳቱ: ማረጉና መንፈስ ቅዱስን መላኩ በአንድ ላይ "ኪዳነ
ምሕረት" ይባላል:: ታዲያ ይህ ሁሉ የተደረገው በሥጋ
ማርያም ነውና የኪዳኑ ባለቤት እመቤታችን ቅድስት ድንግል
ማርያም ናት::
+የእርሷ ኪዳን የ6ቱን አበው ኪዳናት ፍጹም በማድረጉ
የኪዳናት ማሕተም ይባላል:: የድንግል ማርያም ኪዳኗ
ከሲዖልና ከገሃነም ሊታደገን አቅሙ አለውና:: መድኃኒታችን
ክርስቶስ ለድንግል እናቱ ቃል ኪዳኑን ያጸናላት ደግሞ ካረገ
ከዓመታት በሁዋላ ጐልጐታ ላይ ነው::
+እመ ብርሃን በዚያ ቁማ ስለ ኃጥአን ስታለቅስ "እናቴ ሆይ!
በስምሽ ያመነውን: በቃል ኪዳንሽ የተማጸነውን
እምርልሻለሁ" ብሎ ደስ አሰኝቷታልና:: ይሔው በእመ ብርሃን
ምልጃና ቃል ኪዳን ምዕመናን ከመቅሰፍትና ከገሃነመ እሳት
ማምለጥ ከጀመሩ 2ሺ ዓመታት ሆኑ:: ዛሬም እኛ ኃጥአን
ልጆቿ ከእሳት እንደምታድነን አምነን በጥላዋ ሥር
እንኖራለን::
+*" ኢትዝክሪ ብነ አበሳነ (ኃጢአተነ : ወጌጋየነ)
ማርያም እሙ ለእግዚእነ:
በኪዳንኪ: ወበስደትኪ ድንግል ተማሕጸነ:: "*+
"ድንግል ሆይ! ኃጢአታችን: አበሳችንና በደላችንን አታስቢብን
ዘንድ በስደትሽና በኪዳንሽ ተማጽነናል::"
=>የአርያም ንግሥት: የሰማያውያንና ምድራውያን ኁሉ
እመቤት: የአምላክ እናት: ቅድስት: ስብሕት: ክብርት:
ልዕልት: ቡርክት: ፍስሕትና ጥዕምት የሆነች ድንግል ማርያም
የድኅነታችን መሠረት: ላመኑባት አንገት የማታስደፋ እውነተኛ
አማላጅ ናት::
+በዚህች ዕለት የካቲት 16 ስለ ወገኖቿ የሰው ልጆች ፍቅር
በእንባ ያቀረበችውን ልመና የባሕርይ አምላክ የሆነ ልጁዋ
ተቀብሎ በማይዋሽ ንጹሕ አንደበቱ ቃል ኪዳን ገብቶላታል::
በስምሽ ያመነ በቃል ኪዳንሽ የተማመነ እሳትን አያይም
ብሏታል::
=>ቸሩ ልጇ ከበረከተ ኪዳኗ አይለየን:: በዓሉንም የሰላም :
የፍቅርና የበረከት ያድርግልን::
=>የካቲት 16 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ኪዳነ ምሕረት (የሰባቱ ኪዳናት ማሕተም)
2.ቅድስት ኤልሳቤጥ (የመጥምቁ ዮሐንስ እናት /
የእመቤታችን አክስት / የሶፍያ ልጅ)
3.ቅዱስ ገብረ ማርያም ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮዽያ (የቅ/ላሊበላ
ወንድም)
=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ አኖሬዎስ ንጉሥ ጻድቅ
2.አባ አቡናፍር ገዳማዊ
3.አባ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ
4.አባ ዳንኤል ጻድቅ
=>+"+"+ . . . ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች
ጊዜ ፅንሱ በማኅፀንዋ ውስጥ ዘለለ:: በኤልሳቤጥም መንፈስ
ቅዱስ ሞላባት:: በታላቅ ድምፅም ጮኻ እንዲህ አለች:-
አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ: የማኅፀንሽም ፍሬ
የተባረከ ነው:: የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት
ይሆንልኛል? እነሆ የሰላምታሽ ድምፅ በጀሮየ በመጣ ጊዜ
ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና:: ከጌታ የተነገረላት ቃል
ይፈፀማልና ያመነች ብፅዕት ናት:: +"+"+ (ሉቃ. 1:39)
<ወስብሐት ለእግዚአብሔር>

No comments:

Post a Comment