ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነኝ

Wednesday, May 4, 2016

+*"#ምጽዋት "*+

#ምጽዋት
• ስለ ምጽዋት ምንነት
ምጽዋት የሚለው ሥርወ ቃል የግእዝ ቋንቋ ሲሆን
ትርጉሙም ስጦታ፣ችሮታ፣ልግስና ማለት ነው፡፡
ምጽዋት፡-
• ምሕረት ነው ( ፍት ነገ አንቀጽ 16 ቁ 125 )
• ለአምላክ የሚሰጥ ብድር ነው ( ለድሀ ቸርነትን የሚያደርግ
ለእግዚአብሔር ያበድራል፤ በጎነቱንም መልሶ ይከፍለዋል፡፡
ምሳ 19፡17 )፣ ( ምጽዋትን የሚመጸውት ሰው
ለእግዚአብሔር በማበደሩ ነው በእጁም የሚበቃ ገንዘብ ያለው
ፈቃዱን ያደርጋል፡፡ ሲራ 29፡1 )
• ብልሆች ሰዎች ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስቀምጡት
አደራ ነው ( ሉቃ 12፡33 )፣ ( ማቴ 6፡19-21 )
• ሰው ለሰው ያለውን በጎ ፈቃድ የሚገልጥበት ክርስቲያናዊ
የሥነ ምግባር ዘርፍ ነው፡፡ ( 2ኛ ቆሮ 8፡2 )
• ጠላትህ ቢራብ እንጀራ አብላው፤ ቢጠማ ውሃ አጠጣው፤
መ.ምሳሌ 25፤21
o የምጽዋት ዓይነቶች
ምጽዋት የሚለው ሲነገር ለሕሊና የሚታይን የገንዘብ የምግብ
የቁሳቁስ ስጦታ ነው፤ ነገር ግን ምጽዋት በገንዘብና በዓይነት
ስጦታ ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡ ምጽዋት ካለው ነገር
የሌለውን ነገር መርዳት አስከሆነ ድረስ በሚቆጠርና በሚሰፈር
ብቻ አይወሰንም፡፡ ደካሞችን በጉልበት ያልተማሩትን
በዕውቀት የሙያ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን በሙያ መርዳት
ምጽዋት ነው፡፡ ( ሐዋ 3፡2-10 ፣ ( ማቴ 25፡14-30 )
• ምጽዋት በቅዱሳት መጻሕፍት
“ ለሰው የሚያዝኑና የሚራሩ ብጹዓን ናቸው ” የተባለው
አንቀጽ የሚያስተላልፈው ሰፊ ትምህርት አለ፡፡ ሊቃውንተ ቤተ
ክርስቲያን ምሕረት የሚለውን ቃል ምሕረት ሥጋዊ፣ ምሕረት
መንፈሳዊና ምሕረት ነፍሳዊ በማለት ተንትነው ለእያንዳንዱ
ቃል ተግባራዊ ትርጉም አስቀምጠውለታል፡፡
1. ምሕረት ሥጋዊ ፡- ለተራበ ቆርሶ ማጉረስ፣ ለታረዘ
ማልበስ፣ የባልንጀራን ችግር መካፈል፣ የተበደሉትን መተው
( ይቅር ማለት ) የበደሉትን ይቅርታ መጠየቅ ነው፡፡
2. ምሕረት መንፈሳዊ፡- የትምህርትና የምክር አገልግሎት
ነው፡፡ መንገዱ የጠፋቸውን ክፉውን እንደ መልካም ሥራ፣
የተሳሳተን እምነት እንደ ትክክለኛ እምነት አድርገው ወደ ጥፋት
መንገድ የሚሔዱትን መክሮ አስተምሮ መመለስ፣ ከክፋት ጎዳና
ማዳን ነው፡፡
3. ምሕረት ነፍሳዊ፡- ከእነዚህ ሁሉ ይጠብቃል፣ ይረቃል፡፡
ምሕረት ነፍሳዊ ራስን ለሌላው ሕይወት አሳልፎ መስጠት
ነው፡፡ እራሳቸውን ለሰው ፍቅር አሳልፈው የሚሰጡ ሰዎች
ክርስቶስን በግብር ይመስሉታል፡፡ ( ማቴ. 5፡7 )፣ ( ዮሐ. 3፡
6 )
ሀ. ምጽዋት በብሉይ ኪዳን
ምጽዋት መስጠት እግዚአብሔር ዘንድ አስፈላጊ እንደሆነ
ምጽዋት ሰጪዎችም በእግዚአብሔር ዘንድ የሚጠብቃቸው
ከፍተኛ ዋጋ እንዳላቸው በብሉይና በሐዲስ ኪዳን በሰፊው
ተገልጦ ይገኛል፡፡
• ‹‹ ድሆች በምድር ላይ አይታጡምና በአገርህ ውስጥ ስለድሃ
ለተቸገረውም ወንድምህ እጅህን ትከፍታለህ ብዬ አዝዤሃለሁ
›› (ዘዳ 15፡11)
• ‹‹ ወንድምህ ቢደኸይ እጁ ቢደክም አጽናው እንደ እንግዳ
እንደ መጻተኛ ከአንተ ጋር ይኑር ›› (ዘሌ 25፡35)
• ‹‹ እኔ የመረጥኩት ጾም… እንጀራህን ለተራበ ትቆርስ ዘንድ
ስደተኞች ድሆችን ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ የተራቆተውን ብታይ
ታለብሰው ዘንድ አይደለምን? ›› (ኢሳ 58፡7)
በብሉይ ኪዳን ስለምጽዋት ትምህርት በቃል ብቻ የተገለጠ
አይደለም በተግባርም ጭምር እንጂ
• ማንኛውም እስራኤላዊ ገበሬ የወይራውን፣ የወይኑን፣
የበለሱን የሌሎችንን ተህሎች ውጤት በሚሰበስብበት ጊዜ
ከማሳው ላይ አጣርቶ አይለቅምም፤ ከመሬት ላይ የወደቀውን
አይሰበስበውም ፡፡ የገብሱንና የስንዴውን የሌላውንም ምድር
ያበቀለችውን የሰብል አይነት ሁሉ አያጭድም ቅርምያውንም
ለድሆች ይተዋል፡፡ ይህም ከእግዚአብሔር የታዘዘ ግዴታ ነው፡፡
( ዘሌ 19፡9-10 )፣ ( ዘዳ 24፡19-21)
• ገበሬው በየሦስት ዓመት ከሚያገባው የምድር ፍሬ ሁሉ
አስራት በኩራቱን ለድሆች ይሰጣል፡፡ ( ዘዳ 14፡28 )
• ማንኛውም እስራኤላዊ ገበሬ ስድስት ዓመት ምድሩን እያረሰ
ይዘራል፡ ምርቱንና ፍሬውን ያገባል፡፡ በሰባተኛው ዓመት ግን
ምድር በጠቅላላው የምታበቅለው ሁሉ ለድሆች ይሆናል፡፡
( ዘዳ 23፡3 )
ለ. ምጽዋት በሐዲስ ኪዳን
ሰው ርኅራኄ እና የቸርነት ተግባር የሚማረው ከፈጣሪው ነው፡፡
ለሚሰጠው ስጦታ ምላሽ ሳይሻ ሳይለምኑት ለፍጥረት
የሚያስፈልገውን አውቆ የሚሰጥ ነው፡፡
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየስስ ክርስቶስ ለተራቡት፣ ለተጠሙትና
ለታረዙት ያዝንላቸውና ይራራላቸው ነበር፡፡ ትምህርቱን
ተአምራቱን ይሰበሰቡ የነበሩትን ሁሉ ‹‹ የሚበሉት ስለሌላቸው
አዘነላቸው፤ በመንገድ እንዳይዝሉ ጦማቸውን ሊሰዳቸው
አልወደደም ›› እያለ የተራቡትን ሁሉ ሕብስት አበርክቶ
ይመግባቸው በቸርነቱም ያጠግባቸው ነበር፡፡ ( ማቴ 15፡3 )
ድሆች በምድር ላይ እስካሉ ድረስ ምጽዋትም የማይቀር ግዴታ
መሆኑን ለማመልከት ‹‹ ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ናቸው ››
ሲል ተናግሮዋል፡፡ ( ማቴ 26፡11 )
አበው ሐዋርያትም ለድሆች ያዝኑ፣ ያስቡላቸውም
ይጠነቀቁላቸውም ነበር፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚገባውን
የምጽዋትና የአስራት ገንዘብ ከልዩ ልዩ አስተዋጽኦ ለነዳያን
መድበው ያካፍሏቸው ነበር፡፡ በየሳምንቱ የሚደረገው ተዝካረ
ሰንበት ከፍተኛው ድርሻ ለድሆች የሚሰጥ ነበር፡፡ ( 1ኛ ቆሮ
10፡17-22 )
• የምጽዋት አቀራረብ
ምጽዋት ብድሩ ከእግዚአብሔር ይገኛል በሚል እምነት
ለተቸገሩ ሰዎች የሚሰጥ ልግስና እንደመሆኑ አቀራረቡ
ከግብዝነትና ከውዳሴ ከንቱ የጠራ መሆን እንዳለበት ጌታችን
አስተምሮናል፡፡በግል የሚፈጸም ምጽዋት ፣ ጾምና ጸሎት
በስውር እንዲሆን አዝዞናል፤ ነገር ግን ለስሙ አብነት
( ትምህርት ምሳሌ ) ለመሆን በገሃድ (በግልጽ) ይፈጸማል፡፡
(ማቴ 5፡16)
• ስለ ተዝካርና ቁርባን
ተዝካር የሚለው ሥርወ ቃል ተዘከረ-አሰበ ከሚለው የግእዝ
ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም መታሰቢያ ማለት ነው፤
መታሰቢያውም የሚደረገው በሞት ለተለዩ ሰዎች በጸሎት፣
በመሥዋዕት፣ በመብራት፣ በማዕጠንትና በምጽዋት ነው፡፡
ለሞተው ሰው መታሰቢያ የሚደረግባቸው ጊዜያትም በዕለተ
ሞት ቀን፣ በሣልስት፣ በሰባት ፣በአስራ ሁለት፣ በሠላሳኛው ቀን፣
በአርባኛው ቀን፣ በሰማንያኛው ቀን፣ በመንፈቅ፣ በሙት ዓመት
ጊዜያት ናቸው፡፡
• የአስራት ክፍያ
የአስራት አስተዋጽዖ ትምህርትና ሥርዓት ከሰዎቸወ ፍላጎትና
ውሳኔ የመጣ አይደለም ከእግዚአብሔር የተሰጠ ትእዛዝ እንጂ፤
ገንዘቡም የሚታወቀው የእግዚአብሔር ገንዘብ በመባል ነው፡፡
(ዘሌ 27፡1)
የአስራት ክፍያ በሙሴ አማካኝነት ከተሰጠው የብሉይ ኪዳን
ሕግ አስቀድሞ የነበረና በሥራ ተጀምሮ የቆየ ነው፡፡ አብርሃም
ከገንዘቡ ሁሉ ለመልከ ጼዴቅ ከአስር አንድ አምጥቶለታል፤
መልከ ጼዴቅም ኅብስት አኮቴት ጽዋዐ በረከት አቅርቦለታል ፤
አብርሃምንም ባርኮታል፡፡ ( ዘፍ 14፡18-2) ፣ ( ዕብ 7፡2 )
አባታችን ያዕቆብም ከገንዘቡ ሁሉ ከአስር አንድ
ለእግዚአብሔር አንደሚሰጥ በራሱ ፍቃድ ብጽዓት አድርጎዋል፤
እግዚአብሔርም ብጽዓቱን ተቀብሎ ያዕቆብን በመንገዱ
ጠብቆታል፡፡ (ዘፍ 28፡22)
• የአስራት ክፍያ የታዘዘበት ምክንያት
1. ሀ. ለፍጥረቱ ሁሉ አስፈላጊ የሆነውን ምግብ ባለማቋረጥ
የሚሰጥ እግዚአብሔርን ለማክበር ( ምሳ 3፡9-10 )
ለ. ለመስጠትም ሆነ ለመንሳት፤ ለማብዛትም ሆነ ለማሳነስ
ሥልጣንና ጌትነት የባሕርዩ የሆነ አምላክ መፍራትን ማክበርን
እንማርበት ዘንድ ስንቀበልም መስጠትንም እናስብ ዘንድ
የተሰጠን ሀብት በጥቂቱ ከፍለን መስጠት ብዙ ትርፍና በረከት
እንድናገኝ ነው፡፡ ( ዘዳ 14፡22 )
2. ለሥርዓተ አምልኮ ማስፈጸሚያ
ለእግዚአብሔር ቤት አምልኮ ማስፈጸሚያ ልግስና አስፈላጊ
ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘይት ለመብራት ( ዘጸ 27፡20 )፣ ዕጣን
ለማዕጠንት ( ዘዳ 30፡36 ) እህል ለቁርባን ( ዘሌ 2፡1-3 )
እንስሳት ለመሥዋዕት አሥራት አስፈላጊ ነበር፡፡ በሐዲስ
ኪዳንም ለዕጣኑ፣ ለዘቢቡ፣ ለልብሰ ተክህኖ ወዘተ… አስራት
አስፈላጊ ነው፡፡
3. ካህናት አገልጋዮችን ለመርዳት ( ዘኁ 18፡21 ) ፣ ( ዘዳ
18፡1-5 ) ፣ ( ሚል 3፡7-9 ) ፣ ( ሚል 3፡10-12 )
4. ለነድያን ( ዘዳ 14፡28-29፣ 26፡12-18፣ 14፡27 )
• ስጦታ ስለሚቀርብበት ቦታ
አስራት በኩራትም ሆነ ሌላውም ለአምላካዊ አገልግሎት
የታዘዘው ስጦታ ሁሉ የሚቀርበው በቤተ እግዚአብሔር ነው፡፡
ነቢዩ ሕዝቅያስም ‹‹ ለእግዚአብሔር ቤት ጎተራ ያዘጋጁ ዘንድ
አዘዘ እናሱም አዘጋጁ ቁርባኑንና አስራቱን የተቀደሱትን ወደዚያ
አስገቡት ›› ( 2ኛ ዜና 31፡12 ) ፣ ( ነህ 13፡5
ለእግዚአብሔር ቤት የሚቀርበውን ማንኛውም ሀብትና
ንብረት ሁሉ እየጠበቁ በተገቢው አገልግሎት እንዲውሉ
የሚያደርጉ የተመረጡ አገልጋዮችና አስተናባሪዎች ነበሩ፡፡
( 2ኛዜና
31፡12 ፣13፡4 )
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment