ኒቆዲሞስ (የዐቢይ ጾም 7ኛ ሳምንት)
ዮሐ. 3÷1-11 ከፈሪሳውያንም ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ
ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም በሌሊት ወደ
ኢየሱስ መጥቶ። መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር
ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች
ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር
ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን አለው። ኢየሱስም መልሶ።
እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር
የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው።
ኒቆዲሞስም። ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል?
ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን?
አለው። ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል። እውነት እውነት
እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ
እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። ከሥጋ የተወለደ
ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው። ዳግመኛ
ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አታድንቅ። ነፋስ
ወደሚወደው ይነፍሳል፥ ድምፁንም ትሰማለህ፥ ነገር ግን
ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ
የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው። ኒቆዲሞስ መልሶ። ይህ እንዴት
ሊሆን ይችላል? አለው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው።
አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን?
እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን
ያየነውንም እንመሰክራለን፥ ምስክራችንንም አትቀበሉትም።
ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ
ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ? ከሰማይም ከወረደ
በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ
የሚኖረው የሰው ልጅ ነው።
የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)
ሖረ ኀቤሁ ዘስሙ ኒቆዲሞስ ወይቤሎ ለኢየሱስ ረቢ ሊቅ ንሕነ
ነአምን ብከ ከመ እምኀበ አብ መጻእከ ከመ ትኩን መምህረ፤
ዕጓለ አንበሳ ሰከብከ ወኖምከ አንሥአኒ በትንሣኤከ፡፡
ትርጉም: ስሙ ኒቆዲሞስ የተባለው ሰው ወደ ጌታችን ኢየሱስ
ሄደ፤ መምሕር ሆይ ልታስተምር ከእግዚአብሔር አብ ዘንድ
እንደመጣህ እናምንብሃለን አለው። የአንበሳ ደቦል ተኛህ፣
አንቀላፋህም፤ በትንሣኤህ አንሣኝ።
እውነት እውነት እልሃለሁ፡- ሰው ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ
ካልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግሥት አያይም፡፡ ጌታችንና
መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን የተናገረው ለኒቆዲሞስ
ነው፡፡
ኒቆዲሞስ የሃይማኖት ሊቅ ነው፡፡ ብዙ የተማረ ብዙ ያወቀ
ሰው ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ ሊቅ - ምሁር - አለቃ ተብሎ
ተጠርቶአል፡፡ በጊዜው ከነበሩ ሰዎች ከፍ ያለና የላቀ ዕውቀት
የነበረው ሰው ነበር፡፡ በሌሊት ወደ ጌታ እየመጣ ይማር ነበር፡፡
የማታ ተማሪ ነበር፡፡ ቀን - ቀን የምኩራብ አስተማሪ ሆኖ ብዙ
ሰዎችን ያስተምር ስለ ነበረና እርሱ የሚያስተምራቸው አይሁድ
ጌታን ስላልተቀበሉ ቀን ለቀን መጥቶ የሚማርበት አመቺ ጊዜ
አልነበረውም፡፡
በአይሁድ ሕግ ጌታን የሚከተልና የሚቀበል ሰው ከምኲራብ
የሚባረር ስለሆነ እነርሱን ላላማስቀየም ማታ ነበር
የሚማረው፡፡ ኒቆዲሞስ ለጌታ ከሰው ችሎታ በላይ የሆኑ
ተአምራትን ስለምትሠራ እኛን ለማስተማርና ለመምከር
ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልከህ የመጣህ ነህ ብሎ
መስክሮለታል፡፡ ጌታም ለእናንተ ተልኬ የመጣሁ ከሆነና
እናንተን ለማስተማር እንደ መጣሁ ከተረዳህ ሰው ዳግመኛ
ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት
አይገባም አለው፡፡
ኒቆዲሞስ ስላልገባው እኔ አርጅቼአለሁ፤ እንዴት ነው ወደ እናቴ
ማኅጸን ተመልሼ የምገባውና ዳግም የምወለደው? ብሎ
ኢየሱስ ክርስቶስን ጠየቀው፡፡ ጌታም፡- ሰው ከሰው ከተወለደ
ሥጋዊ ነው፤ የሰው ልጅ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆን
በመንፈስ መወለድ አለበት፡፡ ከእግዚአብሔር መወለድ ነፋስ
ከየት ተነሥቶ ወዴት እንደሚነፍስ እንደማይታወቅ ያለ ረቂቅ
ምሥጢር ነው አለው፡፡ አሁንም ያ ሊቅ፤ ያ አዋቂ አልገባኝም
አለ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም፡- አንተ የእስራኤል ሊቅና አዋቂ
ሆነህ እንዴት ይህን አታውቅም አለው፡፡ ከሰማይ ከወረደው
በቀር ወደ ሰማይ የሚወጣ የለም፤ የምናውቀውንም
እንናገራለን ካለው በኋላ ጥያቄውን በዚህ ገታ፡፡
ኒቆዲሞስ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቶ መማሩ
የምያስመሰግነው ተግባር ነው፡፡ አይሁድ ወገኖቹ ጌታን
ሳይከተሉት እርሱ ጌታን መውደዱ የሚያስደንቅ ነው፡፡
ኒቆዲሞስ የሚያመሸው ከጌታ ጋር ነበር፡፡ ባለችው ትርፍ
ጊዜው ሁሉ ወደ ፈጣሪው ይሔድ ነበር፡፡ ይህ ታላቅ ዕድል
ነው፡፡ ቀን ሲያስተምርና ሲደክም ስለሚውል ማታ - ማታ
ማረፍ ይገባው ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ ግን ቤቴ ገብቼ ልረፍ
አላለም፡፡ ባለ ሥልጣንና ባለጸጋ ስለ ነበር ደጅ የሚጠናው
ሕዝብና መሰል ባልንጀሮቹ ይፈልጉት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ
ከእነርሱ ጋር አላመሸም፡፡
ከዚህ አባት ታላቅ ትምህርት ልንማር ያስፈልጋል፡፡ እኛ ዛሬ
የምናመሸው የት ነው? የምናመሸውስ ከማን ጋር ነው? ምን
ስናደርግ ነው የምናመሸው? ኒቆዲሞስ ቤቱ አልነበረም
የሚያመሸው፤ ከእውነተኛው መምህር ጋር እንጂ፡፡ ኒቆዲሞስ
ጽድቁንና በረከቱን እየያዘ ነበር ወደ ቤቱ ይገባ የነበረው፡፡ እኛ
ወደ ቤታችን የምንገባው እየከበርን ነው ወይ? ጸድቀን ነው
የምንገባው ወይስ ጎስቁለን?
የዛሬው ሰው እየሰከረ፣ እየጨፈረ፣ እየደማ፣ እየቆሰለ አብዶ
ነው የሚመለሰው፡፡ በቤት ያሉትም እንቅፋት ያገኘው ይሆን?
ይሞት ይሁን? እያሉ እየተሳቀቁ ነው የሚያመሹት፡፡
የሚሞትም አለ፡፡ ማምሸት እንደ ኒቆዲሞስ ከጌታ ጋር ነው
እንጂ! ኒቆዲሞስ ከጌታ ጋር በማምሸቱ ፈጣሪውን አወቀ፡፡
ጌታን ማወቅ ብቻ ደግሞ አይበቃም፡፡ ማወቅማ አጋንንትም
ያውቁታል፡፡ ከመንፈስ መወለድ መወለድ ያስፈልጋል፡፡
ሰው ዕፀ በለስን በበላ ጊዜ የእግዚአብሔር ልጅነቱን ተነጥቆ
ነበር፡፡ ጌታ መጥቶ ዳግም ሰው እስከሚያደርገን ድረስ
የሰይጣል ልጆች ሆነን ነበር፡፡ ከዚያም በአርባና በሰማኒያ ቀን
ከአብራከ መንፈስ ቅዱስና ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ተወልደናል፡፡
አባታችን የምንለው ለዚህ ነው፡፡ ከእርሱ ከተወለድንና ልጅነትን
ካገኘን እንደገና ልጅነታችንን ካገኘን እንደገና ልጅነታችንን
እንዳናጣ አክብረን እንያዘው፡፡ መጀመሪያም አላወቅንበትም
ነበር፡፡ አዳም ከገነት የሚወጣ አልመሰለውም ነበር፡፡ ሰይጣን
አታሎታል፡፡ እኛም እንደገና እንዳንታለል ልጅነታችን
እንዳይሰረዝ እንጠንቀቅ፡፡
የብዙዎቻችን ልጅነት ዛሬ እየተወሰደ ነው፡፡ ልጅነታችንን
እያስነጠቅነው ነው፡፡ እነ ኤሳው እየነጠቁን ነው፡፡ ብዙዎች
እንደ ያዕቆብ ልጅነታችንን ሊወስዱብን አሰፍስፈዋል፡፡ ሰይጣን
እንደ አዳም ሊነጥቀን አሰፍስፏል፡፡ ዛሬ በጣም አርጅተናል፡፡
ኒቆዲሞስ አርጅቶ ነበር፡፡ በጥምቀትና በንስሓ ግን አዲስ
ሕይወት አግኝቶአል፤ ታድሷል፡፡ ያረጀው ሕይወቱ ለመለመ፡፡
ያረጀው ሰውነታችንን በሥጋውና በደሙ በንስሓ እናድሰው፡፡ ይህ
ከሆነ ነው የእግዚአብሔርን መንግሥት የምንወርሰው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
No comments:
Post a Comment